‘የመጀመሪያው ትንሣኤ’ በመከናወን ላይ ነው!
‘የመጀመሪያው ትንሣኤ’ በመከናወን ላይ ነው!
“በክርስቶስ የሞቱትም አስቀድመው ይነሣሉ።”—1 ተሰሎንቄ 4:16
1, 2. (ሀ) የሞቱ ሰዎች ምን ተስፋ አላቸው? (ለ) በትንሣኤ ለማመን የሚያስችል ምን በቂ ምክንያት አለህ? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)
አዳም ኃጢአት ከሠራበት ጊዜ አንስቶ “ሕያዋን እንደሚሞቱ ያውቃሉ” የሚለው አባባል እውነት መሆኑ በግልጽ ታይቷል። በታሪክ ዘመናት ሁሉ ሰዎች ውሎ አድሮ መሞታቸው እንደማይቀር ያውቁ ነበር፤ ስለሆነም ብዙዎቹ ‘ስንሞት ምን እንሆናለን? ሙታን በምን ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ?’ እንደሚሉት ያሉትን ጥያቄዎች ያነሳሉ። መጽሐፍ ቅዱስ “ሙታን ግን ምንም አያውቁም” በማለት ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል።—መክብብ 9:5
2 ታዲያ የሞቱ ሰዎች ተስፋ አላቸው? አዎን፣ አምላክ ለሰው ልጆች ያለው የመጀመሪያ ዓላማ ፍጻሜ እንዲያገኝ ከተፈለገ ተስፋ ሊኖራቸው ይገባል። ባለፉት መቶ ዘመናት የኖሩ የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች ሁሉ ይሖዋ፣ ሰይጣንን ስለሚያጠፋውና እርሱ ያስከተለውን ጉዳት ስለሚያስወግደው ዘር በሰጠው ተስፋ ላይ እምነት ነበራቸው። (ዘፍጥረት 3:15) ይሁንና በአሁኑ ሰዓት ብዙዎቹ በሕይወት የሉም። እነዚህ ሰዎች ይህን ተስፋ ጨምሮ ይሖዋ የሰጣቸው ሌሎች ተስፋዎች ፍጻሜያቸውን ሲያገኙ መመልከት ካለባቸው ከሞት መነሳት ይኖርባቸዋል። (ዕብራውያን 11:13) ይህ በእርግጥ ሊሆን ይችላል? አዎን፣ ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ “ጻድቃንና ኀጥአን ከሙታን እንደሚነሡ” ገልጿል። (የሐዋርያት ሥራ 24:15) በአንድ ወቅት ጳውሎስ፣ ከሦስተኛ ፎቅ ከመስኮት ላይ ወድቆ ‘የሞተውን’ አውጤኪስ የተባለ አንድ ወጣት ከሞት አስነስቷል። ይህ ወጣት መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሱት ከሞት የተነሱ ዘጠኝ ሰዎች መካከል የመጨረሻው ነው።—የሐዋርያት ሥራ 20:7-12 a
3. በዮሐንስ 5:28, 29 ላይ ከተጠቀሱት የኢየሱስ ቃላት አንተ በግልህ ምን ማጽናኛ አግኝተሃል? ለምንስ?
3 እነዚህ ዘጠኝ ትንሣኤዎች በጳውሎስ ቃላት እንድናምን የሚያደርጉን በቂ ማስረጃዎች ናቸው። ከዚህም ባሻገር ኢየሱስ “በዚህ አትደነቁ፤ መቃብር ውስጥ ያሉ ሁሉ ድምፁን [የኢየሱስን] የሚሰሙበት ጊዜ ይመጣል” ሲል በሰጠን ማረጋገጫ ላይ ያለንን እምነት ያጠናክሩልናል። (ዮሐንስ 5:28, 29) ምንኛ የሚያስደስቱ ቃላት ናቸው! እነዚህ ቃላት የሚወዷቸውን ሰዎች በሞት ያጡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን እጅግ ያጽናናሉ!
4, 5. መጽሐፍ ቅዱስ ስለ የትኞቹ ትንሣኤዎች ይናገራል? በዚህ ርዕስ ላይ የምንመረምረው ስለ የትኛው ትንሣኤ ነው?
4 ትንሣኤ ከሚያገኙት መካከል አብዛኞቹ የሚነሱት በአምላክ መንግሥት አማካኝነት ሰላም በሚሰፍንባት ምድር ላይ ለመኖር ነው። (መዝሙር 37:10, 11, 29፤ ኢሳይያስ 11:6-9፤ 35:5, 6፤ 65:21-23) ይህ ከመሆኑ በፊት ግን ሌሎች ትንሣኤዎች ይከናወናሉ። በመጀመሪያ ደረጃ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የመሥዋዕቱን ዋጋ ስለ እኛ ሲል ለአምላክ ለማቅረብ ከሞት መነሳት ይኖርበታል። ኢየሱስ የሞተውና ትንሣኤ ያገኘው በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ነው።
5 ቀጥሎም፣ በመንፈስ የተቀቡት ‘የአምላክ እስራኤል’ አባላት ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ለመተባበር ትንሣኤ አግኝተው ሰማያዊ ክብር መጎናጸፍ ይኖርባቸዋል፤ በዚያም ‘ለዘላለም ከጌታ ጋር ይሆናሉ።’ (ገላትያ 6:16፤ 1 ተሰሎንቄ 4:17) ይህ ክንውን ‘የመጀመሪያው ትንሣኤ’ በመባል ይታወቃል። (ራእይ 20:6) ይህ ትንሣኤ ሲጠናቀቅ ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያላቸው በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከሞት መነሳት የሚጀምሩበት ጊዜ ይከተላል። በዚህም የተነሳ፣ ተስፋችን ሰማያዊም ሆነ ምድራዊ ‘የመጀመሪያውን ትንሣኤ’ ትኩረት ሰጥተን መመርመራችን ተገቢ ነው። የመጀመሪያው ትንሣኤ ምን ዓይነት ነው? የሚፈጸመውስ መቼ ነው?
“በምን ዐይነት አካል?”
6, 7. (ሀ) ቅቡዓን ክርስቲያኖች ወደ ሰማይ ከመሄዳቸው በፊት ምን መሆን አለባቸው? (ለ) ምን ዓይነት አካል ይዘው ይነሳሉ?
6 ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጻፈው የመጀመሪያ ደብዳቤ ላይ የመጀመሪያውን ትንሣኤ አስመልክቶ “ሙታን እንዴት ይነሣሉ? የሚወጡትስ በምን ዐይነት አካል ነው?” የሚሉትን ጥያቄዎች አንስቷል። ከዚያም ለጥያቄዎቹ እንደሚከተለው በማለት መልስ ሰጠ:- “የምትዘራው ካልሞተ ሕይወት አያገኝም። . . . እግዚአብሔር ግን እንደ ፈቀደ አካልን ይሰጠዋል፤ . . . የሰማያዊ አካላት ክብር አንድ ነው፤ የምድራዊም አካላት ክብር ሌላ ነው።”—1 ቆሮንቶስ 15:35-40
7 የጳውሎስ ቃላት በመንፈስ ቅዱስ የተቀቡ ክርስቲያኖች ሰማያዊ ሽልማታቸውን ከመውረሳቸው በፊት መሞት እንዳለባቸው ያሳያሉ። በሚሞቱበት ጊዜም ሥጋዊ አካላቸው ወደ አፈር ይመለሳል። (ዘፍጥረት 3:19) አምላክ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ ለሰማያዊ ሕይወት ተስማሚ የሆነ ሌላ ዓይነት አካል ለብሰው ይነሳሉ። (1 ዮሐንስ 3:2) ከዚህም በላይ አምላክ ያለመሞትን ባሕርይ ይሰጣቸዋል። ይህ ባሕርይ ሰዎች የማትሞት ነፍስ አለቻቸው ተብሎ እንደሚነገረው ሲወለዱ ጀምሮ የሚኖራቸው አይደለም። ጳውሎስ “የሚሞተው የማይሞተውን ሊለብስ ይገባዋል” ብሏል። ያለመሞት ባሕርይ ከአምላክ የሚገኝ ስጦታ ሲሆን ‘የሚለብሱት’ ደግሞ በመጀመሪያው ትንሣኤ የሚካፈሉት ናቸው።—1 ቆሮንቶስ 15:50, 53፤ ዘፍጥረት 2:7፤ 2 ቆሮንቶስ 5:1, 2, 8
8. አምላክ 144,000ዎቹን የሚመርጠው ከተለያዩ ሃይማኖቶች አለመሆኑን እንዴት እናውቃለን?
8 የመጀመሪያውን ትንሣኤ የሚያገኙት 144,000ዎቹ ብቻ ናቸው። ይሖዋ እነዚህን ሰዎች መምረጥ የጀመረው ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ማለትም በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በጰንጠቆስጤ ዕለት ነው። ሁሉም ‘የእርሱ [የኢየሱስ] ስምና የአባቱ ስም በግምባራቸው ላይ ተጽፎባቸዋል።’ (ራእይ 14:1, 3) በመሆኑም ከተለያዩ ሃይማኖቶች የተመረጡ አይደሉም። ሁሉም የክርስቶስ ተከታዮች ሲሆኑ የአባቱን የይሖዋን ስም በመሸከማቸው ኩራት ይሰማቸዋል። ትንሣኤ ካገኙ በኋላ በሰማይ የሚያከናውኑት ሥራ ይሰጣቸዋል። ወደፊት አምላክን በቅርብ ሆነው እንደሚያገለግሉት ማወቃቸው እጅግ እንደሚያስደስታቸው ምንም ጥርጥር የለውም።
ትንሣኤው እየተከናወነ ነው?
9. ራእይ 12:7 እና 17:14 የመጀመሪያው ትንሣኤ የሚጀምርበትን ጊዜ ለመገመት የሚረዱን እንዴት ነው?
9 የመጀመሪያው ትንሣኤ የሚከናወነው መቼ ነው? የመጀመሪያው ትንሣኤ እየተከናወነ መሆኑን የሚያሳዩ ጠንካራ ማስረጃዎች አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙ ሁለት ምዕራፎችን እናወዳድር። በመጀመሪያ፣ ራእይ ምዕራፍ 12ን እንመልከት። በዚህ ምዕራፍ ላይ አዲስ የተሾመው ንጉሥ ማለትም ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅዱሳን መላእክቱ ጋር ሆኖ በሰይጣንና በአጋንንቱ ላይ ጦርነት ማወጁን እናነባለን። (ራእይ 12:7-9) ይህ መጽሔት ብዙ ጊዜ እንደሚገልጸው ጦርነቱ የተካሄደው በ1914 ነው። b ይሁንና በሰማይ በተካሄደው ጦርነት ላይ ከክርስቶስ ቅቡዓን ተከታዮች መካከል ማናቸውም ቢሆኑ ከኢየሱስ ጋር አብረው እንደነበሩ አለመጠቀሱን ልብ በል። አሁን ደግሞ ራእይ ምዕራፍ 17ን ተመልከት። በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ‘ከታላቂቱ ባቢሎን’ ጥፋት በኋላ በጉ ነገሥታትን ድል እንደሚነሳቸው ተገልጿል። በተጨማሪም “ከእርሱ ጋር ያሉ የተጠሩት፣ የተመረጡትና የታመኑትም አብረው ድል ይነሣሉ” ይላል። (ራእይ 17:5, 14) የሰይጣን ዓለም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሲጠፋ “የተጠሩት፣ የተመረጡትና የታመኑት” ከኢየሱስ ጋር መሆን ካለባቸው፣ በዚያ ወቅት ትንሣኤ አግኝተዋል ማለት ነው። ስለሆነም ከአርማጌዶን በፊት የሞቱ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ከ1914 እስከ አርማጌዶን ባለው ጊዜ ውስጥ ትንሣኤ ያገኛሉ ብሎ ማሰቡ ምክንያታዊ ነው።
10, 11. (ሀ) ሃያ አራቱ ሽማግሌዎች እነማን ናቸው? ከእነዚህ ሽማግሌዎች መካከል አንዱ ለዮሐንስ ምን ገለጠለት? (ለ) ከዚህ በመነሳት ምን መደምደሚያ ላይ መድረስ እንችላለን?
10 የመጀመሪያው ትንሣኤ የሚጀምርበትን ጊዜ በትክክል ማወቅ ይቻላል? ይህን አስመልክቶ ራእይ 7:9-15 ጥሩ ፍንጭ ይሰጠናል። በዚህ ጥቅስ ላይ ሐዋርያው ዮሐንስ ‘ማንም ሊቈጥራቸው የማይችል እጅግ ብዙ ሕዝቦችን’ በራእይ እንደተመለከተ ተገልጿል። ዮሐንስ በራእይ ያያቸውን እጅግ ብዙ ሕዝቦች ማንነት የገለጸለት ከ24ቱ ሽማግሌዎች መካከል አንዱ ሲሆን እነዚህ ሽማግሌዎች ከክርስቶስ ጋር የሚወርሱትንና ሰማያዊ ክብር የተጎናጸፉትን 144,000ዎቹን ይወክላሉ። c (ሉቃስ 22:28-30፤ ራእይ 4:4) ዮሐንስ ራሱ በሰማይ የመኖር ተስፋ ካላቸው መካከል ነው። ይሁንና ሽማግሌው እርሱን ባነጋገረው ወቅት ገና በምድር ላይ ስለነበረ በዚህ ራእይ ውስጥ ዮሐንስ የሚወክለው ሰማያዊ ሽልማታቸውን ያላገኙትን በምድር ላይ ያሉ ቅቡዓን ክርስቲያኖችን መሆን አለበት።
11 ከ24ቱ ሽማግሌዎች መካከል አንዱ ለዮሐንስ የእጅግ ብዙ ሰዎችን ማንነት እንደገለጠለት መጠቀሱ ምን ድምዳሜ ላይ እንድንደርስ ይረዳናል? ትንሣኤ ያገኙት የ24ቱ ሽማግሌዎች አባላት በዛሬው ጊዜ መለኮታዊውን እውነት በማስተላለፍ ተግባር ላይ እየተካፈሉ መሆናቸውን ሊጠቁም ይችላል። ይህ ጉዳይ አሳሳቢ የሆነው ለምንድን ነው? ምክንያቱም በምድር ላይ ያሉት የአምላክ ቅቡዓን አገልጋዮች የእጅግ ብዙ ሕዝቦችን እውነተኛ ማንነት ያወቁት በ1935 ነበር። ይህን ውድ እውነት የገለጠላቸው ከሃያ አራቱ ሽማግሌዎች መካከል አንዱ ከሆነ ትንሣኤ አግኝቶ ወደ ሰማይ የሄደው ቢያንስ ቢያንስ በ1935 መሆን ይኖርበታል። ይህ ደግሞ የመጀመሪያው ትንሣኤ የጀመረው ከ1914 እስከ 1935 ባሉት ዓመታት መሆኑን ይጠቁማል። ይሁንና ጊዜውን ከዚህም በበለጠ በትክክል ማወቅ ይቻላል?
12. የመጀመሪያው ትንሣኤ የጀመረው በ1918 የጸደይ ወቅት ነው ብሎ ማሰቡ ምክንያታዊ የሆነው ለምን እንደሆነ ግለጽ።
12 ለዚህ ሁኔታ ተምሳሌት ሊሆን የሚችልን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰ አንድ ክንውን መመርመራችን ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። በ29 ከክርስቶስ ልደት በኋላ መገባደጃ አካባቢ ኢየሱስ ክርስቶስ የአምላክ መንግሥት የወደፊት ንጉሥ በመሆን ተቀባ። ከሦስት ዓመት ተኩል በኋላ ማለትም በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በጸደይ ወራት ኃያል መንፈሳዊ ፍጡር ሆኖ ከሞት ተነሳ። ታዲያ ኢየሱስ የነገሠው በ1914 መገባደጃ አካባቢ ከሆነ ታማኝ የሆኑት ተከታዮቹ ከሞት መነሳት የጀመሩት ከሦስት ዓመት ተኩል በኋላ ማለትም በ1918 የጸደይ ወቅት ሊሆን አይችልም? ይህ ሊሆን የሚችል ነገር ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ይህ ስለመሆኑ ግልጽ ማስረጃ ባይሰጠንም ሐሳቡ የመጀመሪያው ትንሣኤ የሚጀምረው ኢየሱስ በንጉሣዊ ሥልጣኑ ላይ ከተገኘ ከጥቂት ጊዜ በኋላ መሆኑን ከሚጠቁሙ ሌሎች ጥቅሶች ጋር ይስማማል።
13. አንደኛ ተሰሎንቄ 4:15-17 የመጀመሪያው ትንሣኤ የሚጀምረው በክርስቶስ መገኘት መጀመሪያ አካባቢ መሆኑን የሚጠቁመው እንዴት ነው?
13 ለምሳሌ ጳውሎስ እንደሚከተለው በማለት ጽፏል:- “በጌታ ቃል የምንላችሁ ይህን ነው፤ እኛ በሕይወት ያለንና ጌታ እስኪመጣ [“እስኪገኝ፣” NW] ድረስ [የመገኘቱ ማብቂያ ላይ ማለት አይደለም] የምንቀር ያንቀላፉትን አንቀድምም፤ ጌታ ራሱ በታላቅ ትእዛዝ፣ በመላእክት አለቃ ድምፅና በእግዚአብሔር የመለከት ድምፅ ከሰማይ ይወርዳልና። በክርስቶስ የሞቱትም አስቀድመው ይነሣሉ። ከዚያም በኋላ እኛ የቀረነው፣ በሕይወትም የምንኖረው ጌታን በአየር ላይ ለመቀበል ከእነርሱ ጋር በደመና እንነጠቃለን፤ በዚህም መሠረት ለዘላለም ከጌታ ጋር እንሆናለን።” (1 ተሰሎንቄ 4:15-17) በመሆኑም ከክርስቶስ መገኘት በፊት የሞቱት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ክርስቶስ በሚገኝበት ጊዜ ከሞት በመነሳት ገና በሕይወት ካሉት ቀድመው ሰማያዊውን ሕይወት ያገኛሉ። ይህም ሲባል የመጀመሪያው ትንሣኤ ክርስቶስ በሥልጣን ላይ ከተገኘበት ከመጀመሪያዎቹ ዓመታት አንስቶ በሥልጣን ‘በሚገኝበት ጊዜ’ ሁሉ ይቀጥላል ማለት ነው። (1 ቆሮንቶስ 15:23 NW) የመጀመሪያውን ትንሣኤ የሚያገኙ ሰዎች ከሞት የሚነሱት በአንድ ላይ ሳይሆን ረዘም ባለ ጊዜ ውስጥ ቀስ በቀስ ነው።
“ለእያንዳንዳቸው ነጭ ልብስ ተሰጣቸው”
14. (ሀ) በራእይ ምዕራፍ 6 ላይ ያሉት ራእዮች ፍጻሜያቸውን ያገኙት መቼ ነው? (ለ) በራእይ 6:9 ላይ የተገለጸው ስለ ምን ነገር ነው?
14 ከዚህም በተጨማሪ፣ በራእይ ምዕራፍ 6 ላይ የሚገኘውን ሌላ ማስረጃ ተመልከት። በዚህ ምዕራፍ ላይ ኢየሱስ ድል ለመንሳት እንደሚጋልብ ንጉሥ ተደርጎ ተገልጿል። (ራእይ 6:2) መንግሥታት በአስከፊ ጦርነት ውስጥ ይዘፈቃሉ። (ራእይ 6:4) ረሃብ ይስፋፋል። (ራእይ 6:5, 6) ገዳይ ወረርሽኞች የሰውን ልጅ ሕይወት እንደ ቅጠል ያረግፋሉ። (ራእይ 6:8) እነዚህ ሁሉ ክስተቶች ከ1914 ወዲህ ያሉትን ዓመታት በትክክል የሚገልጹ ናቸው። ይሁንና ሌላም የሚፈጸም ነገር አለ። መሥዋዕት በሚቀርብበት መሠዊያ ላይ ትኩረታችንን የሚስብ ነገር አለ። ከመሠዊያው በታች ‘ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ጠበቁትም ምስክርነት የታረዱ ሰዎች ነፍሶች’ ይታያሉ። (ራእይ 6:9) “የፍጡር ሕይወት [ወይም ነፍስ] በደሙ ውስጥ” በመሆኑ ከመሠዊያው በታች ባሉት ነፍሳት የተመሰለው በድፍረትና በቅንዓት በመስበካቸው ምክንያት መሥዋዕት የሆኑት የኢየሱስ ታማኝ አገልጋዮች ደም ነው።—ዘሌዋውያን 17:11
15, 16. ራእይ 6:10, 11 የመጀመሪያውን ትንሣኤ የሚያመለክተው እንዴት እንደሆነ አብራራ።
15 ጻድቅ እንደነበረው እንደ አቤል ደም ሁሉ የእነዚህ ክርስቲያን ሰማዕታት ደምም ፍትሕን ለማግኘት ይጮኻል። (ዘፍጥረት 4:10) “እነርሱም በታላቅ ድምፅ፣ ‘ሁሉን የምትገዛ ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ፤ እስከ መቼ አትፈርድም? እስከ መቼስ ደማችንን በምድር በሚኖሩት ላይ አትበቀልም?’ አሉ።” ከዚያስ ምን ሆነ? “ለእያንዳንዳቸው ነጭ ልብስ ተሰጣቸው፤ ወደ ፊት እንደ እነርሱ የሚገደሉ የአገልጋይ ባልንጀሮቻቸውና ወንድሞቻቸው ቊጥር እስኪሞላ ድረስ ጥቂት ጊዜ እንዲታገሡ [“እንዲያርፉ፣” የ1954 ትርጉም] ተነገራቸው።”—ራእይ 6:10, 11
16 ነጩ ልብስ የተሰጠው ከመሠዊያው በታች ለተጠራቀመው ደም ነው? በፍጹም! ልብሱ የተሰጠው በምሳሌያዊ መንገድ ደማቸው በመሠዊያው ላይ እንደፈሰሰ ተደርጎ ለተገለጹት ግለሰቦች ነው። እነዚህ ሰዎች ሕይወታቸውን ለኢየሱስ ስም ሲሉ ሠውተዋል እንዲሁም በአሁኑ ጊዜ መንፈሳዊ አካል ለብሰው ከሞት ተነስተዋል። ይህን እንዴት እናውቃለን? ቀደም ባለው የራእይ መጽሐፍ ክፍል ላይ “ድል የሚነሣም እንደ እነርሱ ነጭ ልብስ ይለብሳል፤ . . . ስሙንም ከሕይወት መጽሐፍ አልደመስስም” የሚል ሐሳብ እናነባለን። ከዚህም በተጨማሪ 24ቱ ሽማግሌዎች “ነጭ ልብስ የለበሱና በራሳቸውም ላይ የወርቅ አክሊል የደፉ” መሆናቸውን አስታውስ። (ራእይ 3:5፤ 4:4) በመሆኑም ጦርነት፣ ረሃብና ቸነፈር ምድርን ማናወጥ ከጀመሩ በኋላ ከመሠዊያው በታች ባለው ደም የተመሰሉት ሞተው የነበሩት የ144,000 ክፍል አባላት በሰማይ ለመኖር ትንሣኤ አግኝተው ምሳሌያዊውን ነጭ ልብስ ይለብሳሉ።
17. ነጩን ልብስ የለበሱት ሰዎች ‘የሚያርፉት’ በምን መንገድ ነው?
17 ከሞት የተነሱት ቅቡዓን ‘ማረፍ’ ይኖርባቸዋል። የአምላክን የበቀል ቀን መምጣት በትዕግሥት መጠባበቅ ይገባቸዋል። “አገልጋይ ባልንጀሮቻቸው” ይኸውም ገና በምድር ላይ ያሉት ቅቡዓን ክርስቲያኖች በመከራ መጽናታቸውን ማሳየት ይጠበቅባቸዋል። መለኮታዊው ፍርድ ሲመጣ ‘የሚታገሡበት’ ጊዜ ያበቃል። (ራእይ 7:3) በዚህ ጊዜ ትንሣኤ ያገኙት ሰዎች ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በመተባበር የንጹሐን ክርስቲያኖችን ደም ያፈሰሱትን ጨምሮ ክፉዎችን ያጠፋሉ።—2 ተሰሎንቄ 1:7-10
ለእኛ ምን ትርጉም አለው?
18, 19. (ሀ) የመጀመሪያው ትንሣኤ በመካሄድ ላይ ነው ብለህ እንድታምን የሚያደርጉህ ምክንያቶች ምንድን ናቸው? (ለ) ስለ መጀመሪያው ትንሣኤ ያገኘኸው እውቀት ምን ስሜት አሳድሮብሃል?
18 የአምላክ ቃል የመጀመሪያው ትንሣኤ የሚከናወንበትን ቁርጥ ያለ ቀን አይነግረንም፤ ይሁንና ክርስቶስ በሥልጣኑ ላይ በሚገኝበት ጊዜ ውስጥ የሚከናወን መሆኑን ግልጽ ያደርግልናል። ከክርስቶስ መገኘት በፊት የሞቱ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ከሞት ለመነሳት ቀዳሚዎች ይሆናሉ። በክርስቶስ መገኘት ወቅት ምድራዊ ሕይወታቸውን በታማኝነት የሚያጠናቅቁት ቅቡዓን ክርስቲያኖች “በቅጽበተ ዐይን” ተለውጠው ኃያል መንፈሳዊ ፍጥረታት ይሆናሉ። (1 ቆሮንቶስ 15:52) ታዲያ ሁሉም ቅቡዓን ክርስቲያኖች ከአርማጌዶን ጦርነት በፊት ሰማያዊ ሽልማታቸውን ይቀበላሉ? ስለዚህ ጉዳይ በእርግጠኝነት የምናውቀው ነገር የለም። ሆኖም አምላክ የወሰነው ትክክለኛ ጊዜ ሲደርስ 144,000ዎቹ በሙሉ በሰማያዊው የጽዮን ተራራ መቆማቸው እንደማይቀር እናውቃለን።
19 ከዚህም በተጨማሪ አብዛኞቹ የ144,000 አባላት በአሁኑ ጊዜ ከክርስቶስ ጋር መሆናቸውን አውቀናል። በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ በምድር ላይ የቀሩት እጅግ ጥቂት ናቸው። በእርግጥም ይህ፣ የአምላክ የፍርድ ቀን በፍጥነት እየቀረበ መሆኑን የሚያሳይ ጉልህ ማስረጃ ነው! መላው የሰይጣን ሥርዓት በቅርቡ ይጠፋል። ሰይጣንም ራሱ ወደ ጥልቁ ይጣላል። ከዚያም አጠቃላዩ ትንሣኤ ይጀምራል እንዲሁም ታማኝ የሰው ልጆች በክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት አዳም ያጣውን የፍጽምና ደረጃ በድጋሚ ያገኛሉ። በዘፍጥረት 3:15 ላይ የሰፈረው ይሖዋ የተናገረው ትንቢት በሚያስደንቅ ሁኔታ ፍጻሜውን በማግኘት ላይ ነው። በዚህ ጊዜ መኖራችን ምንኛ ታላቅ መብት ነው!
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ከሞት የተነሱትን የሌሎቹን ስምንት ሰዎች ታሪክ በ1 ነገሥት 17:21-23፤ በ2 ነገሥት 4:32-37፤ 13:21፤ በማርቆስ 5:35, 41-43፤ በሉቃስ 7:11-17፤ 24:34፤ በዮሐንስ 11:43-45፤ በሐዋርያት ሥራ 9:36-42 ላይ ማንበብ ትችላለህ።
b ክርስቶስ በመንግሥታዊ ሥልጣኑ ላይ መገኘት የጀመረው በ1914 መሆኑን የሚያሳዩ ማስረጃዎችን ለማግኘት፣ በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ከገጽ 215-218ን ተመልከት።
c ሃያ አራቱ ሽማግሌዎች ሰማያዊ ቦታቸውን የያዙትን ቅቡዓን ክርስቲያኖች የሚወክሉት እንዴት እንደሆነ ለማወቅ በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ራእይ—ታላቁ መደምደሚያው ደርሷል! የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 77ን ተመልከት።
ልታብራራ ትችላለህ?
የሚከተሉት ጥቅሶች ‘የመጀመሪያው ትንሣኤ’ የሚከናወንበትን ጊዜ ለይተን እንድናውቅ የሚረዱን እንዴት ነው?
• 1 ቆሮንቶስ 15:23፤ 1 ተሰሎንቄ 4:15-17
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አጠቃላዩ ትንሣኤ ከመጀመሩ በፊት የትኞቹ ትንሣኤዎች ይከናወናሉ?
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በሞት ላንቀላፉት ሰዎች ነጭ ልብስ የተሰጣቸው በምን መንገድ ነው?