በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

በራእይ 7:3 ላይ የተጠቀሰው መታተም ምን ያመለክታል?

ራእይ 7:1-3 እንዲህ ይላል:- “ከዚህ በኋላ አራት መላእክት በአራቱ የምድር ማእዘኖች ቆመው አየሁ፤ እነርሱም ነፋስ በምድር ወይም በባሕር፣ ወይም በማንኛውም ዛፍ ላይ እንዳይነፍስ አራቱን የምድር ነፋሶች ያዙ። ከዚያም የሕያው አምላክ ማኀተም ያለው ሌላ መልአክ ከምሥራቅ ሲመጣ አየሁ፤ እርሱም ምድርንና ባሕርን ለመጉዳት ሥልጣን የተሰጣቸውን አራቱን መላእክት በታላቅ ድምፅ እንዲህ አላቸው፤ ‘በአምላካችን አገልጋዮች ግንባር ላይ ማኀተም እስከምናደርግባቸው ድረስ ምድርን ወይም ባሕርን፣ ወይም ዛፎችን አትጒዱ።’”

‘አራቱ የምድር ነፋሶች’ ሲለቀቁ “ታላቁ መከራ” ማለትም የሐሰት ሃይማኖት እንዲሁም የተቀረው ክፉ ዓለም ጥፋት ይጀምራል። (ራእይ 7:14) ‘የአምላካችን አገልጋዮች’ የተባሉት በምድር ላይ ያሉት የክርስቶስ ቅቡዓን ወንድሞች ናቸው። (1 ጴጥሮስ 2:9, 16) በመሆኑም ይህ ትንቢት ታላቁ መከራ ከመጀመሩ በፊት የክርስቶስን ወንድሞች የማተሙ ሂደት ሙሉ በሙሉ እንደሚጠናቀቅ ይጠቁማል። ይሁን እንጂ ከዚህ በፊት መከናወን የሚኖርበት ሌላ የማተም ሥራ እንዳለ የሚጠቀሙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አሉ። አንዳንድ ጊዜ ስለ መጀመሪያው መታተም እና ስለ መጨረሻው መታተም የምንናገረው ለዚህ ነው። በእነዚህ በሁለቱ መታተሞች መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው?

እስቲ በመጀመሪያ “ማኅተም” የሚለውን ቃል ትርጉም እንመልከት። በጥንት ዘመን ማኅተም በአንድ ሰነድ ላይ ምልክት ለማድረግ የሚያገለግል መሣሪያ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ ቃሉ ምልክቱን ራሱን ለማመልከትም ይሠራበታል። በዚያ ወቅት የአንድን ሰነድ ወይም የአንዳንድ ነገሮችን ትክክለኝነትና የባለቤትነት መብት ለማረጋገጥ ሲባል ከሰነዱ ወይም ከእነዚህ ነገሮች ጋር ማኅተም ማያያዝ የተለመደ ነበር።—1 ነገሥት 21:8፤ ኢዮብ 14:17 የ1954 ትርጉም

ጳውሎስ መንፈስ ቅዱስን ከማኅተም ጋር በማመሳሰል እንዲህ ብሏል:- “እንድንቆም የሚያደርገን እግዚአብሔር ነው፤ የቀባንም እርሱ ነው፤ የእርሱ ለመሆናችን ማኅተሙን ያተመብን ደግሞም ወደ ፊት ለምናገኘው ነገር የመንፈሱን ዋስትና በልባችን ያኖረ እርሱ ነው።” (2 ቆሮንቶስ 1:21, 22) በመሆኑም ይሖዋ እነዚህ ክርስቲያኖች የእርሱ ንብረት መሆናቸውን ለማሳየት በመንፈሱ አማካኝነት ቀብቷቸዋል።

ይሁን እንጂ የእነዚህ ቅቡዓን ክርስቲያኖች መታተም ሁለት ደረጃዎች አሉት። የመጀመሪያው መታተም ከመጨረሻው መታተም (1ኛ) በዓላማ (2ኛ) ደግሞ በጊዜ ይለያል። አንድ ክርስቲያን ለመጀመሪያ ጊዜ የሚታተመው በቅቡዓን ክርስቲያኖች ቡድን ላይ አንድ አዲስ አባል ለመጨመር ነው። ለመጨረሻ ጊዜ መታተሙ ደግሞ የተመረጠውና የታተመው ይህ ግለሰብ ታማኝ መሆኑን ሙሉ በሙሉ በተግባር እንዳሳየ የሚያመለክት ነው። በአንድ ቅቡዕ ክርስቲያን ‘ግንባር ላይ’ ቋሚ ማኅተም የሚደረገው በዚህ ጊዜ ይኸውም በመጨረሻው መታተም ወቅት ነው። ይህ ማኅተም ግለሰቡ የተፈተነና ታማኝነቱን ያስመሠከረ ‘የአምላክ አገልጋይ’ መሆኑን ለይቶ የሚያሳውቅ ይሆናል። በራእይ 7 ላይ የተጠቀሰው ማኅተም የሚያመለክተው ይህንን የመጨረሻ መታተም ነው።—ራእይ 7:3

ሐዋርያው ጳውሎስ የመጀመሪያው ማኅተም የሚደረግበትን ጊዜ በተመለከተ ለቅቡዓን ክርስቲያኖች እንዲህ በማለት ጽፏል:- “እናንተም ደግሞ የእውነትን ቃል ይህም የድነታችሁን ወንጌል በሰማችሁ ጊዜ ወደ ክርስቶስ ተጨምራችኋል፤ አምናችሁም፣ በእርሱ በመሆን ተስፋ ሆኖ በተሰጠው በመንፈስ ቅዱስ ማኅተም ታትማችኋል።” (ኤፌሶን 1:13, 14) ብዙውን ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ምሥራቹን ሰምተው በክርስቶስ ሲያምኑ ወዲያውኑ በመንፈስ ቅዱስ ይታተሙ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 8:15-17፤ 10:44) ይህ መታተም አምላክ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደተቀበላቸው የሚያሳይ እንጂ የመጨረሻውን ማረጋገጫ እንዳገኙ የሚያሳይ ምልክት አይደለም። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?

ሐዋርያው ጳውሎስ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ‘ነጻ ለሚወጡበት ቀን እንደታተሙ’ ገልጿል። (ኤፌሶን 4:30 NW) ይህም ከመጀመሪያ መታተም በኋላ ብዙ ጊዜ ምናልባትም ዓመታት ሊያልፉ እንደሚችሉ ያሳያል። ስለዚህ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በመንፈስ ቅዱስ ከታተሙበት ዕለት አንስቶ ከሥጋዊ አካላቸው ‘ነጻ እስከሚወጡበት’ ይኸውም እስከሚሞቱበት ቀን ድረስ ታማኝ ሆነው መቆየት ይኖርባቸዋል። (ሮሜ 8:23፤ ፊልጵስዩስ 1:23፤ 2 ጴጥሮስ 1:10) በመሆኑም ጳውሎስ “ሩጫውን ጨርሻለሁ፤ ሃይማኖትንም ጠብቄአለሁ። ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል” በማለት ሊናገር የሚችለው በሕይወቱ መጨረሻ ላይ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 4:6-8) ከዚህም በላይ ኢየሱስ ለአንድ የቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤ “እስከ ሞት ድረስ ታማኝ ሁን፤ እኔም የሕይወትን አክሊል እሰጥሃለሁ” በማለት ተናግሯል።—ራእይ 2:10፤ 17:14

“አክሊል” የሚለው ቃል ራሱ በመጀመሪያ መታተም እና በመጨረሻው መታተም መካከል የተወሰነ ጊዜ እንደሚኖር ተጨማሪ ማስረጃ ይሆናል። እንዴት? በጥንት ዘመን በሩጫ ላሸነፈ ሰው አክሊል የመስጠት ልማድ ነበር። ይህን አክሊል ለመቀበል አንድ ሰው በሩጫው መሳተፍ ብቻ ሳይሆን እስከ መጨረሻው ድረስ መሮጥ ይጠበቅበታል። በተመሳሳይም ቅቡዓን ክርስቲያኖች በሰማይ የዘላለም ሕይወት አክሊል የሚያገኙት እስከ ሕይወታቸው ፍጻሜ ማለትም የመጀመሪያ ማኅተም ከተደረገላቸው ጊዜ ጀምሮ የመጨረሻው ማኅተም እስከሚደረግባቸው ድረስ ከጸኑ ብቻ ነው።—ማቴዎስ 10:22፤ ያዕቆብ 1:12

የመጀመሪያውን ማኅተም ያገኙ ቅቡዓን ቀሪዎች የመጨረሻው ማኅተም የሚደረግባቸው መቼ ነው? እስካሁን ድረስ በምድር ላይ ያሉ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ታላቁ መከራ ከመፈንዳቱ በፊት ‘ግንባራቸው ላይ’ ማኅተሙ ይደረግባቸዋል። አራቱ የመከራ ነፋሳት በሚለቀቁበት ወቅት ገና ምድራዊ ሕይወታቸውን ያላጠናቀቁ ጥቂት ቅቡዓን ክርስቲያኖች የሚኖሩ ቢሆንም እንኳ በሁሉም መንፈሳዊ እስራኤላውያን ላይ የመጨረሻውን ማኅተም የማድረጉ ሂደት ከዚያ በፊት ይጠናቀቃል።