በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጊልያድ ተመራቂዎች ልብ የሚነካ ትምህርት ተሰጣቸው

የጊልያድ ተመራቂዎች ልብ የሚነካ ትምህርት ተሰጣቸው

የጊልያድ ተመራቂዎች ልብ የሚነካ ትምህርት ተሰጣቸው

የ121ኛው ክፍል የጊልያድ ተማሪዎች የምረቃ ሥነ ሥርዓት መስከረም 9, 2006 ፓተርሰን፣ ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የትምህርት ማዕከል ተካሂዶ ነበር። ይህ ፕሮግራም እጅግ የሚያበረታታ ነበር።

የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ጄፍሪ ጃክሰን 56ቱን ተመራቂዎች እና ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የመጡትን 6,366 የሚያክሉ ሌሎች ተሰብሳቢዎች እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት የፕሮግራሙን መክፈቻ ንግግር አቀረበ። በዚህ ንግግሩ ላይ መዝሙር 86:11ን ያብራራ ሲሆን ጥቅሱ “እግዚአብሔር ሆይ፤ መንገድህን አስተምረኝ፤ በእውነትህም እሄዳለሁ፤ ስምህን እፈራ ዘንድ፣ ያልተከፋፈለ ልብ ስጠኝ” ይላል። ወንድም ጃክስን በዚህ ጥቅስ ላይ ጎላ ብለው ስለተገለጹት ሦስት ነጥቦች እንዲህ በማለት ተናገረ:- “በመጀመሪያው ዓረፍተ ነገር ላይ ትምህርት ስለመቅሰም፣ በሁለተኛው ዓረፍተ ነገር ላይ ደግሞ ስለ ተግባር፤ እንዲሁም በሦስተኛው ላይ ስለ ውስጣዊ ግፊት ተጠቅሷል። እነዚህ ሦስት ነገሮች በተለይ ለእናንተ ለሚስዮናውያን ወደ ምድብ ቦታችሁ በምትሄዱበት ወቅት በጣም ይረዷችኋል።” ቀጥሎም እነዚህን ሦስት ነጥቦች የሚያብራሩትን ተከታታይ ንግግሮችና ቃለ ምልልሶች አስተዋወቀ።

አስደሳች ትምህርቶች

የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት አባል የሆነው ወንድም ዊልያም ማሌንፎንት “ከሁሉ የተሻለ ሕይወት” በሚል ጭብጥ ንግግር ያቀረበ ሲሆን በዚህ ንግግሩ ላይ የማርታ እህት ማርያም የተወችውን ምሳሌ አንስቷል። በአንድ ወቅት ኢየሱስ ሊጠይቃቸው ቤታቸው ሄዶ ሳለ ማርያም ከእርሱ መማርን ከሁሉ ነገር አስበልጣ ስለተመለከተችው እግሩ ሥር ቁጭ ብላ ታዳምጠው ጀመር። ኢየሱስም ለማርታ “ማርያም እኮ የሚሻለውን ድርሻ መርጣለች፤ ይህም ከእርሷ አይወሰድም” በማለት ነግሯታል። (ሉቃስ 10:38-42) ተናጋሪው ወንድም በመቀጠል እንዲህ አለ:- “እስቲ ስለዚህ ጉዳይ ቆም ብላችሁ አስቡ፤ ማርያም በኢየሱስ እግር ሥር ተቀምጣ አስደሳች መንፈሳዊ እውነቶችን ከእርሱ በቀጥታ መስማቷን ለዘላለም አትረሳውም። ይህ ሁሉ የሆነው የተሻለ ምርጫ በማድረጓ ነው። ተናጋሪው ተመራቂዎቹ ላደረጉት ጥሩ መንፈሳዊ ምርጫ ካመሰገናቸው በኋላ “ያደረጋችሁት ምርጫ ከሁሉ ወደተሻለ ሕይወት መርቷችኋል” በማለት ተናገረ።

ቀጥሎ የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል አባል የሆነው አንቶኒ ሞሪስ በሮሜ 13:14 ላይ የተመሠረተውንና “ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ልበሱት” የሚል ጭብጥ ያለውን ንግግር አቀረበ። ክርስቶስን መልበስ የምንችለው እንዴት ነው? ወንድም ሞሪስ “‘ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን መልበስ’ የጌታን ባሕርይ መኮረጅን ያጠቃልላል” በማለት ተናገረ። ይህም ሲባል የኢየሱስን ምሳሌ እንዲሁም ዝንባሌ መኮረጅ ማለት ነው። ተናጋሪው በመቀጠል “ኢየሱስ ሰዎች ከእርሱ ጋር መሆን እንዳይከብዳቸው ያደርግ ነበር፤ ይህን የሚያደርገው ከልብ ያስብላቸው ስለነበረ ነው። እነርሱም ከልብ እንደሚያስብላቸው ይሰማቸው ነበር” ብሏል። አክሎም ተማሪዎቹ ኤፌሶን 3:18 እንደሚናገረው የእውነትን ‘ስፋት፣ ርዝመት፣ ከፍታና ጥልቀት ለመገንዘብ’ በጊልያድ ቆይታቸው ወቅት ምን እንዳደረጉ ተናገረ። ይሁን እንጂ በቁጥር 19 መሠረት ‘ከመታወቅ በላይ የሆነውን የክርስቶስን ፍቅር ለማወቅ’ የበለጠ ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው አስታወሳቸው። በመጨረሻም ወንድም ሞሪስ ተማሪዎቹን እንዲህ በማለት አበረታቷቸዋል:- “የግል ጥናት በምታደርጉበት ጊዜ ሁሉ ክርስቶስ ያሳየውን ከፍቅር የመነጨ ርኅራኄ መኮረጅና ‘ጌታ ክርስቶስ ኢየሱስን መልበስ’ የምትችሉት እንዴት እንደሆነ አሰላስሉ።”

የጊልያድ አስተማሪዎች የመሰነባበቻ ምክር

ቀጥሎም የጊልያድ አስተማሪ የሆነው ወንድም ዋላስ ሊቨራንስ በምሳሌ 4:7 ላይ የተመሠረተ ንግግር አቀረበ። ወንድም አምላካዊ ጥበብ በጣም አስፈላጊ መሆኗን ገልጾ ‘ማስተዋልን ገንዘብ ለማድረግ’ መጣጣርም እንደሚገባን ተናገረ። ይህ ደግሞ የአንድን ጉዳይ ሁለንተናዊ ገጽታ መገንዘብ እንድንችል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች ላይ የተገለጹ እውነቶችን በማዋሃድ አንዱ ከሌላው ጋር ያለውን ዝምድና ለመረዳት ጥረት ማድረግን ይጨምራል። እንዲሁም ተናጋሪው ማስተዋልን ገንዘብ ማድረግ ደስታ እንደሚያስገኝ ገልጿል። ለምሳሌ በነህምያ ዘመን ሌዋውያን ለሕዝቡ ‘ሕጉን ይተረጕሙላቸው’ እንዲሁም ማስተዋል እንዲችሉ “ይተነትኑላቸው” ነበር። ስለዚህም “ሕዝቡ ሁሉ የተነገራቸውን ቃል ተረድተው ስለ ነበረ . . . ሐሴት” ለማድረግ ሄዱ። (ነህምያ 8:7, 8, 12) ወንድም ሊቨራንስ “ደስታ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈውን የአምላክ ቃል ከመረዳት ወይም ከማስተዋል የሚገኝ ውጤት ነው” በማለት ንግግሩን ደመደመ።

ሌላኛው የጊልያድ ትምህርት ቤት አስተማሪ ማርክ ኑሜር ያቀረበው ንግግር ደግሞ “በእርግጥ ጠላታችሁ ማን ነው?” የሚል ጭብጥ ነበረው። በጦርነት ወቅት ብዙ ወታደሮች ከወገን ጦር በተተኮሰ ጥይት ይሞታሉ። “እኛ በምናካሂደው መንፈሳዊ ውጊያስ ተመሳሳይ ሁኔታ ይፈጠር ይሆን?” በማለት ጥያቄ አቀረበ። አክሎም “ካልተጠነቀቅን እኛም እውነተኛ ጠላታችን ማን እንደሆነ ግራ ስለምንጋባ በራሳችን ወታደሮች ላይ ተኩሰን ማቁሰላችን የማይቀር ነው።” ቅናት አንዳንዶች እውነተኛ ጠላታቸው ማን እንደሆነ መለየት እንዳይችሉ ሊያደርጋቸው ይችላል። ለምሳሌ ይህ ባሕርይ ንጉሥ ሳኦል እውነተኛ ጠላቶቹ ፍልስጥኤማውያን ሆነው ሳሉ እንደ እርሱ የይሖዋ አምላኪ የሆነውን ዳዊትን ለመግደል እንዲሞክር አድርጎታል። (1 ሳሙኤል 18:7-9፤ 23:27, 28) ከዚያም ተናጋሪው በመቀጠል እንዲህ አለ:- “አብሯችሁ የሚያገለግለው ሚስዮናዊ ከእናንተ በብዙ መንገዶች የሚበልጥ ቢሆን ምን ታደርጋላችሁ? ከጎናችሁ ተሰልፎ የሚዋጋውን ይህን ወታደር ኃይለኛ ትችት በመሰንዘር ታቆስሉታላችሁ? ወይስ ሌሎች ከእናንተ በተለያየ መንገድ ሊበልጡ እንደሚችሉ አምናችሁ በመቀበል ሰላም ትፈጥራላችሁ? በሌሎች አለፍጽምና ላይ ማተኮር እውነተኛው ጠላታችን ማን እንደሆነ ግራ እንድንጋባ ከማድረግ ውጪ ምንም ፋይዳ የለውም። እውነተኛውን ጠላት ማለትም ሰይጣንን ተዋጉ።”

አስደሳች ተሞክሮዎችና ትምህርት አዘል ቃለ ምልልሶች

ቀጣዩ ክፍል የጊልያድ አስተማሪ በሆነው በሎውረንስ ቦወን የቀረበ ሲሆን “የወንጌል ሰባኪን ተግባር አከናውን” የሚል ጭብጥ ነበረው፤ ንግግሩ ቃለ ምልልሶችንና ተሞክሮዎችን ያካተተ ነበር። ተናጋሪው ወንድም በዚህ ንግግር ላይ እንዲህ አለ:- “ከጊልያድ የተመረቁ ሚስዮናውያን ዋነኛ ሥራቸው ምሥራቹን በተለያዩ ቦታዎች ማሠራጨት ነው፣ የዚህ ክፍል ተማሪዎች ሰዎችን ባገኙባቸው ቦታዎች ሁሉ ይህንን ሲያደርጉ ቆይተዋል።” ከዚያም አንዳንድ አስደሳች ተሞክሮች በሠርቶ ማሣያ መልክ ቀረቡ።

ቀጥሎ የቤቴል ቤተሰብ አባላት የሆኑት ማይክል በርኔት እና ስኮት ሾፍነር ሁለት ንግግሮችን በተከታታይ አቀረቡ። እነዚህ ወንድሞች ከአውስትራሊያ፣ ከባርባዶስ፣ ከኮሪያና ከኡጋንዳ ለመጡ የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባሎች ቃለ ምልልስ አድርገዋል። የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባላቱ ጥሩ ቤትንና የጤና አገልግሎትን ጨምሮ ሚስዮናውያን የሚያስፈልጓቸውን ነገሮችን ለማሟላት ከፍተኛ ጥረት እንደሚደረግ ገልጸዋል። እንዲሁም ውጤታማ ሚስዮናውያን ራሳቸውን ከአካባቢው ሁኔታ ጋር ለማስማማት ፈቃደኞች እንደሆኑ አበክረው ተናግረዋል።

ስሜት ቀስቃሽ መደምደሚያ

የበላይ አካል አባል ሆኖ ለረጅም ዓመታት ያገለገለው ወንድም ጆን ባር ‘አምላክን ፍሩ፤ ክብርም ስጡት’ በሚል ጭብጥ የፕሮግራሙን ዋነኛ ንግግር አቀረበ። በራእይ 14:6, 7 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ ያብራራ ሲሆን ጥቅሱም እንዲህ ይላል:- “ከዚያም ሌላ መልአክ በሰማይ መካከል ሲበር አየሁ፤ እርሱም በምድር ላይ ለሚኖሩ ለሕዝብ፣ ለነገድ፣ ለቋንቋና ለወገን ሁሉ የሚሰብከውን የዘላለም ወንጌል ይዞ ነበር፤ በታላቅ ድምፅም፣ ‘እግዚአብሔርን ፍሩ፤ ክብርም ስጡት፤ ምክንያቱም የፍርዱ ሰዓት ደርሶአል . . .’ አለ።”

ወንድም ባር፣ ተማሪዎቹ ይህን መልአክ በተመለከተ ሦስት ነገሮችን ልብ እንዲሉ አሳሰባቸው። በመጀመሪያ ደረጃ ይህ መልአክ ኢየሱስ ሙሉ ንጉሣዊ ሥልጣኑን ይዞ እየገዛ መሆኑን የሚናገረውን የዘላለም ወንጌል መስበክ ነበረበት። ወንድም ባር እንዲህ በማለት ተናገረ:- “ኢየሱስ ንግሥናውን የተቀበለው በ1914 እንደሆነ ሙሉ በሙሉ እናምናለን። ስለዚህም ይህ አስደሳች ዜና በመላው ምድር መሰበክ አለበት።” በሁለተኛ ደረጃ መልአኩ ‘አምላክን ፍሩ’ ብሎ ተናግሯል። ተናጋሪው ተመራቂዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻቸው አምላክን የሚያሳዝን ምንም ነገር እንዳያደርጉ ለመርዳት ለእርሱ ጥልቅ አክብሮት እንዲያዳብሩ ማበረታታት እንዳለባቸው ገልጿል። በሦስተኛ ደረጃ መልአኩ ‘ለአምላክ ክብር ስጡት’ በማለት አዟል። ተናጋሪው ተማሪዎቹን “የምናገለግለው ለራሳችን ሳይሆን ለአምላክ ክብር ለማምጣት መሆኑን ፈጽሞ መዘንጋት የለባችሁም” በማለት አሳስቧል። ከዚያም “የፍርዱ ሰዓት” የሚለውን ሐሳብ ሲያብራራ “የመጨረሻው ፍርድ ሊሰጥ የቀረው ጊዜ በጣም ጥቂት ነው። ስለዚህ በአገልግሎት ክልላችን የሚኖሩ ብዙ ሰዎች ጊዜው ከማብቃቱ በፊት ምሥራቹን መስማት ያስፈልጋቸዋል” ብሏል።

ሃምሳ ስድስቱ ተመራቂዎች እነዚህ ቃላት በጆሯቸው ላይ እያቃጨሉ ዲፕሎማቸውን ተቀብለው እስከ ምድር ዳር ድረስ ተላኩ። ተመራቂዎቹም ሆኑ በዚያ የተገኙት ሌሎች ተሰብሳቢዎች በዚያ አስደሳች ዕለት በቀረቡት ስሜት ቀስቃሽ ንግግሮች ልባቸው በጥልቅ ተነክቷል።

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ተማሪዎቹን የሚመለከት አኃዛዊ መረጃ

ተማሪዎቹ የተውጣጡባቸው አገሮች ብዛት:- 6

የተመደቡባቸው አገሮች ብዛት:- 25

የተማሪዎቹ ብዛት:- 56

አማካይ ዕድሜ:- 35.1

በእውነት ውስጥ የቆዩባቸው ዓመታት በአማካይ:- 18.3

በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የቆዩባቸው ዓመታት በአማካይ:- 13.9

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት 121ኛ ክፍል ተመራቂዎች

(1) ፎክስ ዩኮ፣ ከኒኪ ዶውን፣ ዊልኪንሰን ሳራህ፣ ካዋሞቶ ሳቺዮ፣ ኮንሶላንዲ ጂና፣ ማየን ክሪስቲ፤ (2) ሳንቲያጎ ናተሊ፣ ክላንሲ ሬቸል፣ ፊሸር ሚካኤላ፣ ደ ኧብረው ሌስሊ፣ ዴቪስ ኤሪካ፤ (3) ህዋንግ ጄን፣ ሆፍማን ዳርሊን፣ ሪጅዌ ሊኦኒ፣ ኢብራሂም ጆ፣ ዳበልሽታይን አንያ፣ ባካበክ ሚሪየም፤ (4) ፔተርስ ማርሊስ፣ ጆንስ ክሪስተል፣ ፎርድ ሻነን፣ ፓረ ሳሊ፣ ሮትሮክ ዳያነ፣ ታትሎ ሙርዬል፣ ፔሬዝ ኤሊዛቤት፤ (5) ደ ኧብረው ፈርናንዶ፣ ካዋሞቶ ሺንሱኬ፣ አይቭስ ሱዛን፣ በርዶ ጄኒፈር፣ ህዋንግ ጄምስ፣ ዊልኪንሰን ዲ፤ (6) ፎክስ አንዲ፣ ባካበክ ጄት፣ ሲካዉስኪ ፒይላኒ፣ ፎርዬ ክሪስተል፣ ማየን ስቴፈን፣ ኮንሶላንዲ ኤንዞ፣ ሪጅዌ ዌን፤ (7) ፓረ ቤን፣ ፔሬዝ ቤን፣ ታትሎ ፊሊፕ፣ ሳንቲያጎ ማርከስ፣ ኢብራሂም ዩገል፣ ከኒኪ ክሪስ፤ (8) በርዶ ካለን፣ ሲካዉስኪ ብራየን፣ አይቭስ ኬን፣ ፎርድ አለን፣ ሮትሮክ ጂም፣ ሆፍማን ደስተን፣ ዴቪስ ማርከስ፤ (9) ፔተርስ ክሪስትያን፣ ዳበልሽታይን ክሪስ፣ ጆንስ ኬት፣ ክላንሲ ሰቴፈን፣ ፊሸር ዮከን፣ ፎርዬ ሲልቨን።