በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ደስታህ ፍጹም ይሆናል’

‘ደስታህ ፍጹም ይሆናል’

‘ደስታህ ፍጹም ይሆናል’

“ለአምላክህ ለእግዚአብሔር በዓሉን ሰባት ቀን አክብር፤ . . . ደስታህም ፍጹም ይሆናል።”—ዘዳግም 16:15

1. (ሀ) ሰይጣን ምን ጥያቄዎችን አስነስቷል? (ለ) ይሖዋ፣ አዳምና ሔዋን ካመጹ በኋላ ምን ትንቢት ተናግሯል?

 ይጣን አዳምና ሔዋን በፈጣሪያቸው ላይ እንዲያምጹ ባደረጋቸው ጊዜ ሁለት ወሳኝ ጥያቄዎችን አስነስቷል። በመጀመሪያ ደረጃ፣ የይሖዋን እውነተኝነትና የአገዛዙን ትክክለኛነት ተገዳድሯል። በሁለተኛ ደረጃ፣ ሰዎች ለአምላክ የሚገዙት በራስ ወዳድነት ተነሳስተው ነው ሲል በተዘዋዋሪ መንገድ ተናግሯል። ሰይጣን ይህን ሐሳብ በኢዮብ ዘመን በቀጥታ ጠቅሶታል። (ዘፍጥረት 3:1-6፤ ኢዮብ 1:9, 10፤ 2:4, 5) ይሁንና ይሖዋ ሁኔታውን ለማስተካከል ፈጣን እርምጃ ወስዷል። እንዲያውም ይሖዋ፣ አዳምና ሔዋን ገና በኤደን ውስጥ እያሉ ለዚህ ጉዳይ እልባት የሚሰጠው እንዴት እንደሆነ አስቀድሞ ተናግሯል። አንድ ‘ዘር’ እንደሚመጣና ተረከዙ እንደሚቀጠቀጥ ከዚያም ይህ ዘር የሰይጣንን ራስ ቀጥቅጦ ከሕልውና ውጭ እንደሚያደርገው ትንቢት ተናግሯል።—ዘፍጥረት 3:15

2. ይሖዋ በዘፍጥረት 3:15 ላይ የተመዘገበው ትንቢት እንዴት ፍጻሜውን እንደሚያገኝ የሚጠቁሙ መረጃዎችን ቀስ በቀስ የሰጠው እንዴት ነው?

2 ጊዜ እያለፈ ሲሄድ፣ ይሖዋ ይህን ትንቢት ይበልጥ ግልጽ የሚያደርጉ መረጃዎችን ሰጥቷል፤ ይህም ትንቢቱ መፈጸሙ የማይቀር መሆኑን ያመለክታል። ለምሳሌ ያህል፣ አምላክ ለአብርሃም ‘ዘሩ’ በእርሱ የትውልድ ሃረግ በኩል እንደሚመጣ ነግሮታል። (ዘፍጥረት 22:15-18) ከዚያም የአብርሃም የልጅ ልጅ የሆነው ያዕቆብ የ12ቱ የእስራኤል ነገዶች አባት ለመሆን በቃ። በ1513 ከክርስቶስ ልደት በፊት እነዚህ ነገዶች ራሱን የቻለ አንድ ብሔር በሆኑበት ወቅት ይሖዋ የሚተዳደሩበትን ሕግ ሰጣቸው። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ የተለያዩ ዓመታዊ በዓላትን የሚመለከቱ ነበሩ። ሐዋርያው ጳውሎስ እነዚህ በዓላት “ሊመጡ ላሉ ነገሮች ጥላ” መሆናቸውን ገልጿል። (ቈላስይስ 2:16, 17፤ ዕብራውያን 10:1) ይሖዋ ዘሩን አስመልክቶ ያለው ዓላማ እንዴት እንደሚፈጸም ፍንጭ ይሰጣሉ። እስራኤላውያን በዓላቱን ማክበራቸው ታላቅ ደስታ አምጥቶላቸዋል። እነዚህን በዓላት በአጭሩ መመርመራችን ይሖዋ የሰጠን ተስፋዎች መፈጸማቸው እንደማይቀር ያለንን እምነት ያጠናክርልናል።

ዘሩ ተገለጠ

3. ተስፋ የተደረገበት ዘር ማን ነው? ተረከዙ የተቀጠቀጠውስ እንዴት ነው?

3 ይሖዋ የመጀመሪያውን ትንቢት ከተናገረ ከ4,000 ዓመታት በኋላ ተስፋ የተደረገበት ዘር ተገለጠ። ይህ ዘር ኢየሱስ ነበር። (ገላትያ 3:16) ፍጹም ሰው የነበረው ኢየሱስ እስከ ሞት ድረስ በአቋሙ በመጽናት የሰይጣን ውንጀላ መሠረተ ቢስ መሆኑን አሳይቷል። ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ ኃጢአት የሌለበት በመሆኑ መሥዋዕታዊ ሞቱ ከፍተኛ ዋጋ ነበረው። በዚህ መሥዋዕት አማካኝነት ኢየሱስ ታማኝ የሆኑትን የአዳምና የሔዋንን ዘሮች ከኃጢአትና ከሞት ነጻ አውጥቷቸዋል። ኢየሱስ በመከራ እንጨት ላይ ተሰቅሎ መሞቱ ተስፋ የተሰጠበት ዘር ‘ተረከዝ መቀጥቀጡን’ ያመለክታል።—ዕብራውያን 9:11-14

4. ለኢየሱስ መሥዋዕት ጥላ የሆነው ምን ነበር?

4 ኢየሱስ ኒሳን 14, 33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ሞተ። a በእስራኤል፣ ኒሳን 14 የማለፍ በዓል የሚከበርበት አስደሳች ዕለት ነበር። በየዓመቱ፣ በዚህ ቀን ቤተሰቦች አንድ ላይ ሆነው ንጹሕ የሆነን አንድ ጠቦት ጨምሮ የተለያዩ ምግቦችን ይመገቡ ነበር። ይህም ኒሳን 14, 1513 ከክርስቶስ ልደት በፊት አንድ መልአክ የግብጻውያንን በኩር በገደለበትና የእስራኤላውያን በኩሮች ደግሞ በዳኑበት ጊዜ የጠቦቱ ደም የነበረውን ሚና ለማስታወስ ያስችላቸዋል። (ዘፀአት 12:1-14) ሐዋርያው ጳውሎስ “የፋሲካ በጋችን የሆነው ክርስቶስ ተሠውቶአል” በማለት የማለፍ በግ ለኢየሱስ ጥላ ሆኖ ማገልገሉን ገልጿል። (1 ቆሮንቶስ 5:7) የፈሰሰው የኢየሱስ ደም እንደ ማለፍ በግ ደም ለብዙ ሰዎች መዳን አስገኝቷል።—ዮሐንስ 3:16, 36

‘ከሙታን በኩር’

5, 6. (ሀ) ኢየሱስ ከሞት የተነሳው መቼ ነበር? በሕጉ ውስጥ ለዚህ ነገር ጥላ ሆኖ ያገለገለው ምንድን ነው? (ለ) የኢየሱስ ከሞት መነሳት ዘፍጥረት 3:15 ፍጻሜውን እንዲያገኝ ያስቻለው እንዴት ነው?

5 ኢየሱስ የመሥዋዕቱን ዋጋ ለአባቱ ለማቅረብ በሦስተኛው ቀን ከሞት ተነሳ። (ዕብራውያን 9:24) ለዚህ የኢየሱስ ትንሣኤ ጥላ ሆኖ ያገለገለ አንድ ሌላ በዓል አለ። በኒሳን 14 ማግሥት የቂጣ በዓል መከበር ይጀምራል። በቀጣዩ ቀን ማለትም ኒሳን 16 እስራኤላውያን በመከር ወቅት የሰበሰቡትን የመጀመሪያውን ወይም በኩሩን የገብስ ነዶ በይሖዋ ፊት እንዲወዘወዝ ወደ ካህኑ ያመጡታል። (ዘሌዋውያን 23:6-14) ይሖዋ፣ ሰይጣን “ታማኝና እውነተኛ ምሥክር” የሆነውን ልጁን እስከ መጨረሻው ዝም ለማሰኘት ያቀናበረውን መሰሪ ዘዴ ኒሳን 16, 33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ እንዲከሽፍ ማድረጉ በእርግጥም ተገቢ ነው! በዚህ ዕለት ይሖዋ፣ ለኢየሱስ የማይሞት መንፈሳዊ ሕይወት በመስጠት ከሞት አስነስቶታል።—ራእይ 3:14፤ 1 ጴጥሮስ 3:18

6 ኢየሱስ ‘ከሙታን በኩር’ ሆኗል። (1 ቆሮንቶስ 15:20) ኢየሱስ ከእርሱ በፊት ከሞት ተነስተው እንደነበሩት ሰዎች ተመልሶ አልሞተም። ከዚህ ይልቅ በይሖዋ ቀኝ ለመቀመጥ ወደ ሰማይ አርጓል፤ በዚያም የይሖዋ ሰማያዊ መንግሥት ንጉሥ የሚሆንበትን ጊዜ ሲጠባበቅ ቆይቷል። (መዝሙር 110:1፤ የሐዋርያት ሥራ 2:32, 33፤ ዕብራውያን 10:12, 13) ኢየሱስ የንግሥና ሥልጣን የተሰጠው በመሆኑ የቀንደኛ ጠላቱን ራስ በመቀጥቀጥ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማጥፋት ብሎም ዘሮቹን ለመደምሰስ በሚያስችለው ሁኔታ ላይ ይገኛል።—ራእይ 11:15, 18፤ 20:1-3, 10

የአብርሃም ዘር ተጨማሪ አባላት

7. የሱባኤ በዓል ምንድን ነው?

7 ኢየሱስ፣ ይመጣል ተብሎ በኤደን ውስጥ ተስፋ የተሰጠበትና ይሖዋ ‘የዲያብሎስን ሥራ ለማፍረስ’ መሣሪያ አድርጎ የሚጠቀምበት ዘር ነው። (1 ዮሐንስ 3:8) ይሁን እንጂ ይሖዋ አብርሃምን ባነጋገረው ጊዜ የአብርሃም ‘ዘር’ አንድ ግለሰብ ብቻ እንደማይሆን አመልክቷል። ከዚህ ይልቅ ዘሩ “እንደ ሰማይ ከዋክብት፣ እንደ ባሕር ዳር አሸዋም” እንደሚሆን ተናግሯል። (ዘፍጥረት 22:17) ከዚህ ጋር በተያያዘ አንድ አስደሳች በዓል ለሌሎቹ ‘የዘሩ’ ክፍሎች መገለጥ ጥላ ሆኖ አገልግሏል። ኒሳን 16 ከዋለ ከሃምሳ ቀን በኋላ እስራኤላውያን የሱባኤን በዓል ያከብራሉ። ሕጉ ይህን በዓል አስመልክቶ እንዲህ ይላል:- “እስከ ሰባተኛው ሰንበት ማግስት ድረስ አምሳ ቀን ቍጠሩ፤ ከዚያም የአዲስ እህል ቍርባን ለእግዚአብሔር አቅርቡ። በሁለት ዐሥረኛ የኢፍ መስፈሪያ የላመ ዱቄት፣ በእርሾ የተጋገረ ሁለት እንጀራ [“ኅብስት፣” የ1980 ትርጉም] ለሚወዘወዝ መሥዋዕት፣ የበኵራት ስጦታ እንዲሆን ከየቤታችሁ ለእግዚአብሔር አምጡ።” bዘሌዋውያን 23:16, 17, 20

8. በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በጰንጠቆስጤ ዕለት ምን አስደናቂ ሁኔታ ተከሰተ?

8 የሱባኤ በዓል ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ወቅት ጰንጠቆስጤ (“ሃምሳኛ” የሚል ትርጉም ካለው ግሪክኛ ቃል የመጣ ነው) በመባል ይታወቅ ነበር። በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በጰንጠቆስጤ ዕለት ከሞት የተነሳው ታላቁ ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ኢየሩሳሌም ውስጥ ተሰብስበው በነበሩ 120 ደቀ መዛሙርት ላይ መንፈስ ቅዱስ አወረደባቸው። በዚህ መንገድ እነዚህ ደቀ መዛሙርት የተቀቡ የአምላክ ልጆችና የኢየሱስ ክርስቶስ ወንድሞች ሆኑ። (ሮሜ 8:15-17) እነዚህ ሰዎች አዲስ ብሔር ማለትም ‘የአምላክ እስራኤል’ ለመሆንም ቻሉ። (ገላትያ 6:16) ይህ ብሔር ከአነስተኛ ቁጥር ተነስቶ በመጨረሻ ላይ 144,000 አባላትን ያቀፈ ይሆናል።—ራእይ 7:1-4

9, 10. በጰንጠቆስጤ ዕለት የሚደረጉት ነገሮች ለቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤ ጥላ የሆኑት እንዴት ነው?

9 በጰንጠቆስጤ ዕለት በይሖዋ ፊት እንዲወዘወዙ የሚደረጉት ከቦካ ሊጥ የሚጋገሩ ሁለት ኅብስቶች ለቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤ ጥላ ሆነው አገልግለዋል። ኅብስቶቹ ከቦካ ሊጥ የተጋገሩ መሆናቸው ቅቡዓን ክርስቲያኖች ከወረሱት የኃጢአት እርሾ እንዳልነጹ ያሳያል። ይሁን እንጂ በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ወደ ይሖዋ መቅረብ ይችላሉ። (ሮሜ 5:1, 2) ኅብስቶቹ ለምን ሁለት ሆኑ? ይህ የሆነው የተቀቡት የአምላክ ልጆች ከሁለት ቡድን ማለትም በመጀመሪያ ከሥጋዊ እስራኤላውያን በኋላም ከአሕዛብ የተውጣጡ መሆናቸውን ለማመልከት ሊሆን ይችላል።—ገላትያ 3:26-29፤ ኤፌሶን 2:13-18

10 በጰንጠቆስጤ ዕለት የሚቀርቡት ሁለት ኅብስቶች የሚዘጋጁት በስንዴ መከር ወቅት ከሚሰበሰበው ከመጀመሪያው ወይም ከበኩሩ ነዶ ነው። ከዚህ ጋር በሚመሳሰል መልኩ በመንፈስ የተወለዱት ክርስቲያኖች “የፍጥረቱ በኵራት” ተብለው ተጠርተዋል። (ያዕቆብ 1:18) በፈሰሰው የኢየሱስ ክርስቶስ ደም አማካኝነት ኃጢአታቸው ከሚሰረይላቸው ሰዎች መካከል እነርሱ የመጀመሪያዎቹ ናቸው፤ ይህም ከክርስቶስ ጋር በመንግሥቱ ለመግዛት የማይጠፋ ሰማያዊ ሕይወት ለመውረስ ያስችላቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 15:53፤ ፊልጵስዩስ 3:20, 21፤ ራእይ 20:6) እንዲህ ያለው ቦታ በቅርቡ ብሔራትን ‘በብረት በትር የመግዛት’ እንዲሁም ‘ሰይጣን ከእግራቸው በታች ሲቀጠቀጥ’ የማየት አጋጣሚ ይከፍትላቸዋል። (ራእይ 2:26, 27፤ ሮሜ 16:20) ሐዋርያው ዮሐንስ “በጉ ወደ ሚሄድበት ሁሉ ይከተሉታል፤ ለእግዚአብሔርና ለበጉ በኵራት እንዲሆኑ ከሰዎች መካከል የተዋጁ ናቸው” ብሏል።—ራእይ 14:4

የኃጢአት ስርየት የሚገኝበት ዕለት

11, 12. (ሀ) በስርየት ቀን ምን ይከናወን ነበር? (ለ) እስራኤላውያን ከወይፈኑና ከፍየሎቹ መሥዋዕት ምን ጥቅሞች ያገኛሉ?

11 ኤታኒም (ከጊዜ በኋላ ቲሽሪ ተብሏል) c በተሰኘው ወር አሥረኛ ቀን ላይ እስራኤላውያን የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ጥቅም ላይ የሚውልባቸውን መንገዶች በተመለከተ ጥላ ሆኖ የሚያገለግል በዓል ያከብራሉ። በዚህ ዕለት የኃጢአት ይቅርታ የሚያስገኘውን መሥዋዕት በማቅረብ የስርየትን ቀን ለማክበር ሕዝቡ ሁሉ አንድ ላይ ይሰበሰባል።—ዘሌዋውያን 16:29, 30

12 በስርየት ቀን ሊቀ ካህናቱ አንድ ወይፈን ካረደ በኋላ ጥቂት ደም ወስዶ ቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ ባለው የታቦቱ መክደኛ ላይ ሰባት ጊዜ ይረጨዋል፤ ይህን በማከናወኑም ደሙን በይሖዋ ፊት መሥዋዕት አድርጎ እንዳቀረበው ይቆጠር ነበር። ይህ መሥዋዕት ለሊቀ ካህናቱና “ለቤተሰቡ፣” ይኸውም ለበታች ካህናት እንዲሁም ለሌዋውያን ኃጢአት ማስተሰረያነት ያገለግላል። ቀጥሎም ሊቀ ካህናቱ ሁለት ፍየሎችን ይወስዳል። አንደኛው ፍየል “ለሕዝቡ” ኃጢአት መሥዋዕት ሆኖ ይቀርባል። ከዚህ ፍየል ጥቂት ደም ተወስዶ ቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ በሚገኘው በታቦቱ መክደኛ ላይ ይረጫል። ከዚያ በኋላ ሊቀ ካህናቱ እጆቹን በሁለተኛው ፍየል ራስ ላይ በመጫን የእስራኤላውያንን ኃጢአት በሙሉ ይናዘዝበታል። በምሳሌያዊ ሁኔታ የእስራኤላውያንን ኃጢአት የተሸከመው ይህ ፍየል ወደ ምድረ በዳ ተወስዶ ይለቀቃል።—ዘሌዋውያን 16:3-16, 21, 22

13. በስርየት ቀን ይከናወኑ የነበሩ አንዳንድ ድርጊቶች ኢየሱስ ለሚጫወተው ሚና ጥላ ሆነው ያገለገሉት እንዴት ነው?

13 በጥላነት የሚያገለግሉት እነዚህ ክንውኖች እንደሚያመለክቱት ታላቁ ሊቀ ካህናት ኢየሱስ የኃጢአት ስርየት ለማስገኘት የደሙን ዋጋ አቅርቧል። በመጀመሪያ ደረጃ ከደሙ ተጠቃሚ የሚሆኑት ‘በመንፈሳዊ ቤት’ የተወከሉት 144,000 ቅቡዓን ክርስቲያኖች ሲሆኑ ይህም ጻድቃን ሆነው እንዲቆጠሩና በይሖዋ ፊት ንጹሕ አቋም እንዲያገኙ ያስችላቸዋል። (1 ጴጥሮስ 2:5፤ 1 ቆሮንቶስ 6:11) ወይፈኑ መሥዋዕት ሆኖ መቅረቡ ለዚህ ጥላ ሆኖ አገልግሏል። ስለሆነም ሰማያዊ ውርሻቸውን ለመቀበል የሚያስችል አጋጣሚ ተከፍቶላቸዋል። በሁለተኛ ደረጃ፣ ፍየሉ መሥዋዕት መሆኑ እንደሚያሳየው የኢየሱስ ደም በእርሱ የሚያምኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ኃጢአት ለማስተሰረይ ይውላል። እነዚህ ሰዎች አዳምና ሔዋን ያጡትን ውርሻ የማግኘት ይኸውም በዚህች ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር መብት ያገኛሉ። (መዝሙር 37:10, 11) ሁለተኛው ፍየል የእስራኤላውያንን ኃጢአት ተሸክሞ ወደ ምድረ በዳ እንደሄደው ሁሉ ኢየሱስም በፈሰሰው ደሙ አማካኝነት የሰው ልጆችን ኃጢአት ያስወግዳል።—ኢሳይያስ 53:4, 5

በይሖዋ ፊት መደሰት

14, 15. በዳስ በዓል ጊዜ ምን ይከናወን ነበር? ይህስ እስራኤላውያንን ምን ነገር ያስታውሳቸዋል?

14 እስራኤላውያን ከስርየት ቀን በኋላ በዓመቱ ውስጥ ከሚያከብሯቸው በዓላት ሁሉ እጅግ አስደሳች የሆነውን የዳስ በዓል ያከብራሉ። (ዘሌዋውያን 23:34-43) በዓሉ የሚከበረው ከኤታኒም 15 እስከ 21 ሲሆን ወሩ በገባ በ22ኛው ቀን በሚካሄደው አንድ ትልቅ ስብሰባ ይደመደማል። በዓሉ መከሩን የመሰብሰቡ ሥራ ማብቃቱን የሚጠቁማቸው ከመሆኑም ሌላ ከአምላክ ላገኟቸው የተትረፈረፉ በረከቶች አመስጋኝነታቸውን መግለጽ የሚችሉበት አጋጣሚ ይሰጣቸዋል። ከዚህም የተነሳ ይሖዋ በዓሉን የሚያከብሩትን ሰዎች “አምላክህ እግዚአብሔር በእህል ምርትህና በጅህ ሥራ ሁሉ ይባርክሃል፤ ደስታህም ፍጹም ይሆናል” ብሏቸዋል። (ዘዳግም 16:15) ይህ እንዴት የሚያስደስት ጊዜ ነበር!

15 እስራኤላውያን በዓሉን በሚያከብሩበት ወቅት ለሰባት ቀናት በዳስ ውስጥ ይኖሩ ነበር። ይህም በምድረ በዳ በነበሩበት ወቅት በዳስ ውስጥ ይኖሩ እንደነበረ ያስታውሳቸዋል። በዓሉ ይሖዋ ያደረገላቸውን አባታዊ እንክብካቤ ለማሰላስል የሚያስችል ሰፊ አጋጣሚ ይከፍትላቸው ነበር። (ዘዳግም 8:15, 16) ከዚህም በተጨማሪ ሃብታሞችም ሆኑ ድሆች ተመሳሳይ በሆኑ ዳሶች ውስጥ ይኖሩ ስለነበር ሁሉም እስራኤላውያን ከዚህ በዓል ጋር በተያያዘ እኩል እንደሆኑ ያስታውሳቸዋል።—ነህምያ 8:14-16

16. የዳስ በዓል ጥላ ሆኖ ያገለገለው ለምን ነገር ነው?

16 የዳስ በዓል፣ መከር የሚሰበሰብበት ወቅት የሚከበርበት አስደሳች በዓል ሲሆን በኢየሱስ ክርስቶስ የሚያምኑ ሰዎችን ለመሰብሰቡ አስደሳች ሥራ በጥላነት አገልግሏል። ይህ የመሰብሰብ ሥራ የጀመረው የኢየሱስ 120 ደቀ መዛሙርት “ቅዱሳን ካህናት” እንዲሆኑ በተቀቡበት በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በተከበረው የጰንጠቆስጤ ዕለት ነው። እስራኤላውያን ለጥቂት ቀናት በዳስ ውስጥ ይኖሩ እንደነበረ ሁሉ ቅቡዓን ክርስቲያኖችም ከአምላክ በራቀው በዚህ ዓለም ውስጥ “እንግዶችና መጻተኞች” መሆናቸውን ያውቃሉ። ተስፋቸው ሰማያዊ ነው። (1 ጴጥሮስ 2:5, 11) ቅቡዓን ክርስቲያኖችን የመሰብሰቡ ሥራ የሚጠናቀቀው የ144,000ዎቹ የመጨረሻ አባላት በሚሰበሰቡበት በዚህ ‘የመጨረሻ ዘመን’ ላይ ነው።—2 ጢሞቴዎስ 3:1

17, 18. (ሀ) ቅቡዓን ክርስቲያኖች ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች ሰዎችም ከክርስቶስ መሥዋዕት ተጠቃሚዎች እንደሚሆኑ የሚጠቁመው ምንድን ነው? (ለ) በዛሬው ጊዜ፣ የዳስ በዓል ጥላ ከሆነለት ክንውን እየተጠቀሙ ያሉት እነማን ናቸው? ይህ አስደሳች በዓል የመጨረሻ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚደርሰው መቼ ነው?

17 ጥንት የዳስ በዓል በሚከበርበት ወቅት 70 ወይፈኖች ይታረዱ የነበረ መሆኑ ትኩረት የሚስብ ጉዳይ ነው። (ዘኍልቍ 29:12-34) ሰባ ቁጥር 7 ሲባዛ በ10 ማለት ነው፤ እነዚህ ቁጥሮች ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰማያዊና ምድራዊ ፍጽምናን ያመለክታሉ። ከዚህም የተነሳ የኖኅ ዝርያ ከሆኑት 70 ቤተሰቦች የመጡት ታማኝ አገልጋዮች በሙሉ ከኢየሱስ መሥዋዕት ተጠቃሚዎች ይሆናሉ። (ዘፍጥረት 10:1-29) ከዚህ ጋር በሚስማማ መልኩ በዛሬው ጊዜ የመሰብሰቡ ሥራ በኢየሱስ ላይ እምነት ያላቸውንና ገነት በሆነች ምድር ውስጥ ለመኖር ተስፋ የሚያደርጉትን ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ሰዎችን የሚያጠቃልል ሆኗል።

18 ሐዋርያው ዮሐንስ በዘመናችን የሚደረገውን ይህን የመሰብሰብ ሥራ በራእይ ተመልክቶ ነበር። በመጀመሪያ ላይ የ144,000ዎቹ የመጨረሻ አባላት መታተማቸውን የሚገልጽ ድምጽ ሰማ። ከዚያ በኋላም “የዘንባባ ዝንጣፊ በእጃቸው ይዘው” በዙፋኑና በበጉ ፊት የቆሙ “ማንም ሊቈጥራቸው የማይችል . . . እጅግ ብዙ ሕዝብ” ተመለከተ። እነዚህ ሰዎች ‘ከታላቁ መከራ’ ተርፈው ወደ አዲሱ ዓለም ‘የመጡ’ ናቸው። እነዚህም ቢሆኑ ለዚህ ሊጠፋ ለተቃረበ አሮጌ ሥርዓት እንግዶች ናቸው። ከዚህም ባሻገር ‘በጉ እረኛቸው የሚሆንበትንና ወደ ሕይወት ውሃ ምንጭ የሚመራቸውን’ ጊዜ በጉጉት ይጠባበቃሉ። በዚያን ጊዜ አምላክ “እንባን ሁሉ ከዐይናቸው ያብሳል።” (ራእይ 7:1-10, 14-17) የዳስ በዓል ጥላ የሆነለት ክንውን የመጨረሻው ከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚደርሰው የክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ከተደመደመ በኋላ ይኸውም በትንሣኤ የሚነሱትን ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ጨምሮ እጅግ ብዙ ሕዝቦች የዘላለም ሕይወት በሚያገኙበት ጊዜ ነው።—ራእይ 20:5 የ1954 ትርጉም

19. እስራኤላውያን ያከብሯቸው በነበሩት በዓላት ላይ ማሰላሰላችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?

19 አይሁዳውያን ያከብሯቸው በነበሩት ጥንታዊ በዓሎች ላይ ስናሰላስል የእኛም ‘ደስታ ፍጹም ይሆናል።’ ይሖዋ ቀደም ሲል በኤደን ውስጥ የተናገረው ትንቢት ፍጻሜውን የሚያገኘው እንዴት እንደሆነ የሚገልጹ አንዳንድ ፍንጮችን መመርመራችንና ትንቢቱ ደረጃ በደረጃ ፍጻሜውን ሲያገኝ መመልከታችን እጅግ አስደሳች ነው። በዛሬው ጊዜ፣ ዘሩ መምጣቱንና ተረከዙ መቀጥቀጡን እናውቃለን። በአሁኑ ጊዜ እርሱ በሰማይ ላይ ንጉሥ ነው። ከዚህም በተጨማሪ አብዛኞቹ የ144,000 አባላት እስከ ሞት ድረስ ታማኝ መሆናቸውን አስመስክረዋል። ከትንቢቱ ውስጥ ሳይፈጸም የቀረው ምንድን ነው? ትንቢቱ ሙሉ በሙሉ ፍጻሜውን የሚያገኘውስ መቼ ነው? እነዚህ ጥያቄዎች በቀጣዩ ርዕስ ላይ ይብራራሉ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ኒሳን ወር በጊዜያችን የቀን አቆጣጠር መጋቢት/ሚያዝያን ያመለክታል።

b በእርሾ የተጋገሩ ሁለት ኅብስቶች ለሚወዘወዝ መሥዋዕት በሚቀርቡበት ወቅት አብዛኛውን ጊዜ ካህኑ ሁለቱን ኅብስቶች በእጁ ይዞ ወደ ላይ ከፍ ካደረጋቸው በኋላ ወደ ቀኝና ወደ ግራ ያወዛውዛቸዋል። ይህ እንቅስቃሴ መሥዋዕቱ ለይሖዋ የቀረበ መሆኑን ያመለክታል።—በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ጥራዝ 2፣ ገጽ 528ን ተመልከት።

c ኤታኒም ወይም ቲሽሪ በዘመናችን የቀን አቆጣጠር መስከረም/ጥቅምትን ያመለክታል።

ልታብራራ ትችላለህ?

• የማለፍ በዓል በግ የሚወክለው ማንን ነው?

• የጰንጠቆስጤ በዓል ለየትኛው የመሰብሰብ ሥራ ጥላ ሆኖ አገልግሏል?

• የኢየሱስ መሥዋዕት ጥቅም ላይ የሚውልበትን መንገድ የሚጠቁሙት በስርየት ቀን ይካሄዱ የነበሩት የትኞቹ ክንውኖች ናቸው?

• የዳስ በዓል ክርስቲያኖችን ለመሰብሰቡ ሥራ ጥላ የሆነው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 22, 23 ላይ የሚገኝ ግራፍ/ሰንጠረዥ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

የማለፍ በዓል

ኒሳን 14

ክንውኑ፦

የማለፍ በግ መሠዋት

ጥላ የሆነለት ነገር፦

የኢየሱስ መሥዋዕት መሆን

የቂጣ በዓል (ኒሳን 15-21)

ኒሳን 15

ክንውኑ፦

ሰንበት

ኒሳን 16

ክንውኑ፦

የገብስ መሥዋዕት መቅረብ

ጥላ የሆነለት ነገር፦

የኢየሱስ ትንሣኤ

50 ቀናት

የሱባኤ በዓል (ጰንጠቆስጤ)

ሲቫን 6

ክንውኑ፦

የሁለት ኅብስቶች መሥዋዕት መቅረብ

ጥላ የሆነለት ነገር፦

ኢየሱስ ቅቡዓን ወንድሞቹን በይሖዋ ፊት ማቅረቡ

የስርየት ቀን

ቲሽሪ 10

ክንውኑ፦

የወይፈንና የሁለት ፍየሎች መሥዋዕት መቅረብ

ጥላ የሆነለት ነገር፦

ኢየሱስ ለሁሉም የሰው ዘር ጥቅም ሲል የደሙን ዋጋ ማቅረቡ

የዳስ በዓል (የመከር መሰብሰብ፣ ድንኳኖች)

ቲሽሪ 15-21

ክንውኑ፦

እስራኤላውያን በዳስ ውስጥ በደስታ ይቀመጡ ነበር፣ በመከሩ ሥራ ይደሰታሉ፣ 70 ወይፈኖች መሥዋዕት ሆነው ይቀርባሉ

ጥላ የሆነለት ነገር፦

የቅቡዓን ክርስቲያኖችና ‘የእጅግ ብዙ ሕዝብ’ መሰብሰብ

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለማለፍ በዓል እንደሚታረደው በግ ደም ሁሉ የፈሰሰው የኢየሱስ ደምም ለብዙዎች መዳንን አስገኝቷል

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኒሳን 16 የሚቀርበው የመጀመሪያው የገብስ ነዶ መሥዋዕት ለኢየሱስ ትንሣኤ ጥላ ሆኖ አገልግሏል

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በጰንጠቆስጤ ዕለት የሚቀርቡት ሁለት ኅብስቶች ለቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤ ጥላ ሆነዋል

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የዳስ በዓል አስደሳች ለሆነው ለቅቡዓን ክርስቲያኖችና ‘ለእጅግ ብዙ ሕዝብ’ መሰብሰብ ጥላ በመሆን አገልግሏል