በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ፍቅራችሁን ማስፋት ትችላላችሁ?

ፍቅራችሁን ማስፋት ትችላላችሁ?

ፍቅራችሁን ማስፋት ትችላላችሁ?

አንዲት የቆመች መርከብ በነፋስ ኃይል ተገፍታ እንዳትሄድ ከተፈለገ የታሰረችበት የመልሕቅ ሰንሰለት የሚያጋጥመውን ከፍተኛ ግፊት መቋቋም የሚችል መሆን ይኖርበታል። ይህ የሚሆነው ግን የሰንሰለቱ ቀለበቶች እርስ በርስ የተያያዙበት መንገድ አስተማማኝና ጥብቅ ከሆነ ብቻ ነው። ካልሆነ ግን ሰንሰለቱ ሊበጠስ ይችላል።

የክርስቲያን ጉባኤ ሁኔታም ከዚህ ጋር ተመሳሳይነት አለው ለማለት ይቻላል። አንድ ጉባኤ ጠንካራ እንዲሁም ጤናማ እንዲሆን ካስፈለገ ሁሉም የጉባኤው አባላት እርስ በርስ ተሳስረው አንድ መሆን ይገባቸዋል። እርስ በርስ እንዲተሳሰሩ የሚያደርጋቸው ምንድን ነው? አንድነት ለማምጣት ከፍተኛ ኃይል ያለው ፍቅር ነው። ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ “አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ፤ ይኸውም እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ ነው፤ እንግዲህ እኔ እንደ ወደድኋችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ። እርስ በርሳችሁ ብትዋደዱ፣ ሰዎች ሁሉ የእኔ ደቀ መዛሙርት እንደ ሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ” ሲል መናገሩ የሚያስደንቅ አይደለም። በእርግጥም እውነተኛ ክርስቲያኖች ከተራ ጓደኝነት እንዲሁም እርስ በርስ ከመከባበር ያለፈ እንዲህ ያለ ፍቅር አላቸው። የራስን ጥቅም መሥዋዕት ለማድረግ የሚያስችል ፍቅር አዳብረዋል።—ዮሐንስ 13:34, 35

የእምነት ባልንጀሮቻችንን ማድነቅ

በበርካታ ጉባኤዎች ውስጥ የተለያየ ዕድሜ፣ ዘር፣ ብሔር፣ ቋንቋ እንዲሁም አስተዳደግ ያላቸው ሰዎች ይገኛሉ። እያንዳንዱ የጉባኤ አባል በግሉ የሚጠላውና የሚወደው፣ የሚመኘውም ሆነ የሚፈራው ነገር ያለው ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ የራሱ ሸክም ምናልባትም የጤንነት ወይም የገንዘብ ችግር ይኖርበታል። ይህ ልዩነት ክርስቲያናዊ አንድነት ተፈታታኝ እንዲሆን ሊያደርግ ይችላል። ታዲያ ፍቅራችንን እንድናሰፋ እንዲሁም ተፈታታኝ ችግሮች እያሉም እንኳ አንድነታችንን መጠበቅ እንድንችል የሚረዳን ምንድን ነው? በጉባኤው ውስጥ ላሉት ሁሉ ልባዊ አድናቆት ማዳበራችን እርስ በርስ ያለን ፍቅር ጥልቀት እንዲኖረው ይረዳናል።

እንግዲያው አንድን ሰው ማድነቅ ሲባል ምን ማለት ነው? ዘ ኒው ሾርተር ኦክስፎርድ ኢንግሊሽ ዲክሽነሪ “ማድነቅ” የሚለውን ቃል “ለሰዎች ስሜት መጠንቀቅ፣ ከፍ አድርጎ መመልከት፣ ጠቃሚ ወይም ዋጋማ እንደሆኑ መቀበል፣ ማመስገን” በማለት ፈቶታል። የእምነት ባልንጀሮቻችንን የምናደንቅ ከሆነ ለሚያስፈልጋቸው ነገር ንቁ እንሆናለን፣ ከፍ አድርገን እንመለከታቸዋለን፣ ጠቃሚ እንደሆኑ አምነን እንቀበላለን እንዲሁም አንድ ላይ ሆነን እውነተኛውን አምላክ በማምለካችን እንደሰታለን። ይህ ደግሞ ለእነርሱ ያለን ፍቅር እያደገ እንዲሄድ ያደርጋል። ሐዋርያው ጳውሎስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን በቆሮንቶስ ለነበሩ ክርስቲያኖች የጻፈላቸውን መልእክት በአጭሩ መመርመራችን ክርስቲያናዊ ፍቅርን ሙሉ በሙሉ እንዴት ማሳየት እንዳለብን ማስተዋል እንድንችል ይረዳናል።

የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ‘ፍቅራቸውን ነፍገው’ ነበር

ጳውሎስ በ55 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ለቆሮንቶስ ጉባኤ የመጀመሪያውን ደብዳቤ የጻፈ ሲሆን ሁለተኛውን ደግሞ አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ጽፎላቸዋል። በደብዳቤው ላይ የሰፈሩት ሐሳቦች እንደሚያመለክቱት በቆሮንቶስ ጉባኤ የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች ለእምነት ባልንጀሮቻቸው አድናቆት አጥተው ነበር። ጳውሎስ ሁኔታውን እንዲህ በማለት ገልጾታል:- “የቆሮንቶስ ሰዎች ሆይ፤ ሁሉን በግልጽ ነግረናችኋል፤ ልባችንንም ወለል አድርገን ከፍተንላችኋል። ፍቅራችሁን የነፈጋችሁን እናንተ ናችሁ እንጂ እኛስ ፍቅራችንን አልነፈግናችሁም።” (2 ቆሮንቶስ 6:11, 12) ጳውሎስ “ነፈጋችሁን” ሲል ምን ማለቱ ነበር?

ጳውሎስ እንዲህ ሲል ከልብ ፍቅር አላሳያችሁንም ማለቱ ነበር። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑር የቆሮንቶስ ወንድሞች ጳውሎስን በተመለከተ “አድሮባቸው የነበረው መሠረተ ቢስ ጥርጣሬና ቅሬታ እንቅፋት ስለሆነባቸው ፍቅራቸው ተገድቦ” እንደነበር ተናግረዋል።

ጳውሎስ ምን ዓይነት ምክር እንደሰጠ ልብ በል:- “ልጆቼ እንደ መሆናችሁ መጠን ይህን አሳስባችኋለሁ፤ እናንተም በዚያው ልክ ልባችሁን ወለል አድርጋችሁ ክፈቱልን።” (2 ቆሮንቶስ 6:13) ጳውሎስ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ለእምነት ባልንጀሮቻቸው ያላቸውን ፍቅር እንዲያሰፉ እያበረታታቸው ነበር። ይህም በጥርጣሬና በቅሬታ ከመሸነፍ ይልቅ አዎንታዊ አመለካከት መያዝና ልባዊ ፍቅር ማሳየት ይኖርባቸዋል ማለት ነው።

በዛሬው ጊዜም ፍቅርን ማስፋት ያስፈልጋል

ዛሬ ያሉ የአምላክ እውነተኛ አምላኪዎች እርስ በርስ ያላቸውን ፍቅር ለማስፋት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ መመልከት የሚያስደስት ነው። ፍቅርን ማስፋት ጥረት እንደሚጠይቅ የተረጋገጠ ነው፤ አንድ ሰው እንዲህ ማድረግ እንዳለበት ስላወቀ ብቻ ፍቅሩን አስፍቷል ማለት አይደለም። ፍቅርን ማስፋት በመጽሐፍ ቅዱስ የአቋም ደረጃዎች ከማይመሩ ሰዎች የተለየ ባሕርይ ማንጸባረቅን ይጠይቃል። አብዛኛውን ጊዜ እነዚህ ሰዎች ሌሎችን በአድናቆት አይመለከቱም። ደንታ ቢሶች፣ ለሰዎች ተገቢ አክብሮት የሌላቸው እንዲሁም ነቃፊዎች ሊሆኑ ይችላሉ። ስለዚህ ይህ ዓይነቱ ዝንባሌ ተጽዕኖ እንዲያሳድርብን መፍቀድ አይኖርብንም። በቆሮንቶስ እንደነበሩት ሰዎች ተጠራጣሪዎች ሆነን ፍቅራችን ቢቀዘቅዝ ምንኛ የሚያሳዝን ነው። ዛሬም እኛ ቶሎ የሚታየን የወንድሞቻችን ጠንካራ ጎን ሳይሆን ደካማ ጎናቸው ከሆነ ይህ ሁኔታ ሊከሰት ይችላል። እንዲሁም አንድ ሰው ባሕሉ ከእኛ የተለየ ስለሆነ ብቻ ፍቅራችንን የምንነፍገው ከሆነም ተመሳሳይ ስህተት ልንሠራ እንችላለን።

ከዚህ በተቃራኒ ግን ፍቅሩን ለማስፋት የሚጥር አንድ የአምላክ አገልጋይ ለእምነት ባልንጀሮቹ እውነተኛ አድናቆት ይኖረዋል። በተጨማሪም ከፍ አድርጎ ይመለከታቸዋል፣ ክብራቸውን ይጠብቅላቸዋል እንዲሁም ለሚያስፈልጋቸው ነገር ንቁ ነው። ቅር እንዲሰኝ የሚያደርገው በቂ ምክንያት ቢኖረውም እንኳ ይቅር ለማለት ዝግጁ ነው፤ እንዲሁም ቂም ከመያዝ ይቆጠባል። እንዲያውም የእምነት ባልንጀራው ያደረገበትን ነገር በበጎ ይተረጉመዋል። ይህም ኢየሱስ “እርስ በርሳችሁ ብትዋደዱ፣ ሰዎች ሁሉ የእኔ ደቀ መዛሙርት እንደ ሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ” ብሎ በተናገረ ጊዜ በአእምሮው ይዞት የነበረውን ዓይነት ፍቅር እንዲያዳብር ይረዳዋል።—ዮሐንስ 13:35

ፍቅራችሁን በማስፋት ከሌሎችም ጋር ተቀራረቡ

ከልብ የመነጨ ፍቅር ማዳበራችን በፊት ካሉን ጓደኞቻችን ጋር ብቻ ሳይሆን በጉባኤያችን ውስጥ ብዙም ከማንቀርባቸው ሰዎች ጋር እንድንግባባ ያደርገናል። እነዚህ ሰዎች እነማን ሊሆኑ ይችላሉ? አንዳንድ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ዓይናፋር በመሆናቸው ወይም በሌሎች ምክንያቶች የተነሳ ብዙ ጓደኞች የሏቸውም። ከእነዚህ ወንድሞቻችን ጋር በአምልኮ አንድ ከመሆን ውጪ ብዙም የሚያመሳስለን ነገር እንደሌለ ይሰማን ይሆናል። ይሁን እንጂ ላይ ላዩን ሲታዩ ምንም የሚያመሳስላቸው ነገር የሌላቸው የሚመስሉ ነገር ግን ጥብቅ ወዳጅነት የመሠረቱ አንዳንድ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠቅሰው ይገኛሉ።

ለምሳሌ ሩትና ኑኃሚን ከፍተኛ የዕድሜ ልዩነት ነበራቸው፤ ዜግነታቸውም ሆነ ባሕላቸው እንዲሁም የአፍ መፍቻ ቋንቋቸውም የተለያየ ነው። ሆኖም እነዚህ ልዩነቶች ወዳጅነት ለመመሥረት እንቅፋት አልሆኑባቸውም። ዮናታን የንጉሥ ልጅ ሲሆን ዳዊት ደግሞ በልጅነቱ እረኛ ነበር። በመካከላቸው ያለው የዕድሜ ልዩነትም በጣም ሰፊ ነው። ነገር ግን በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ጥብቅ ወዳጅነት እንደመሠረቱ ከተነገረላቸው ሰዎች መካከል እነርሱም ይገኙበታል። እነዚህ ሰዎች የመሠረቱት ወዳጅነት በችግር ጊዜ የደስታ ምንጭ የሆናቸው ከመሆኑም ሌላ መንፈሳዊ ድጋፍ እንዲያገኙ ረድቷቸዋል።—ሩት 1:16፤ 4:15፤ 1 ሳሙኤል 18:3፤ 2 ሳሙኤል 1:26

በዛሬውም ጊዜ ቢሆን ሰፊ የዕድሜ ልዩነት ያላቸው ወይም ፈጽሞ የተለያየ የሕይወት ተሞክሮ ያላቸው እውነተኛ ክርስቲያኖች ጥብቅ ወዳጅነት መመሥረት ይችላሉ። ለምሳሌ ሬጂና በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሁለት ልጆቿን ብቻዋን የምታሳድግ እናት ናት። a በሥራ በጣም የተወጠረች ስለሆነች ከሌሎች ጋር ማኅበራዊ ግንኙነት ለመመሥረት የሚያስችል ብዙ ጊዜ የላትም። ሃራልት እና ዩተ ደግሞ ልጅ የሌላቸው ጡረታ የወጡ ባልና ሚስት ናቸው። ላይ ላዩን ሲታይ እነዚህን ሁለት ቤተሰቦች የሚያመሳስላቸው ነገር ያለ አይመስልም። ነገር ግን ሃራልት እና ዩተ መጽሐፍ ቅዱስ ፍቅርን ስለ ማስፋት የሚናገረውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ ፈለጉ። ስለዚህም ሬጂናም ሆነች ልጆቿ አገልግሎትንና መዝናኛን በመሳሰሉት በርካታ እንቅስቃሴዎች ከእነርሱ ጋር እንዲካፈሉ ማድረግ ጀመሩ።

ፍቅራችንን በማስፋት የቅርብ ጓደኞቻችንን ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም ለመቅረብ እንጥራለን? የሌላ አገር ዜግነትና የተለየ ባሕል ካላቸው ወይም በዕድሜ እኩዮቻችሁ ካልሆኑ የእምነት ባልንጀሮቻችሁ ጋር ለምን የጠበቀ ወዳጅነት ለመመስረት አትሞክሩም?

ለሌሎች ፍላጎት ትኩረት መስጠት

የልግስና መንፈስ ያለን መሆኑ ሌሎች ለሚያስፈልጓቸው ነገሮች ንቁ እንድንሆን ይገፋፋናል። ሌሎች የሚያስፈልጋቸው ነገር ምን ይሆን? ይህን ለማወቅ የክርስቲያን ጉባኤን መቃኘቱ ጠቃሚ ነው። ወጣቶች መመሪያ፣ አረጋውያን ማበረታቻ፣ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የተሰማሩት ደግሞ ምስጋናና ድጋፍ እንዲሁም ያዘኑ የእምነት ባልንጀሮቻችን የሚያዳምጣቸው ሰው ይፈልጋሉ። እያንዳንዱ ሰው የሚፈልገው የራሱ የሆነ ነገር አለው። ለዚህ ፍላጎታቸው ደግሞ የአቅማችንን ያህል ምላሽ መስጠት እንፈልጋለን።

ፍቅርን ማስፋት ሲባል ለየት ያለ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ያሉበትን ሁኔታ መረዳትንም ይጨምራል። አንድ በጠና የታመመ ሰው ወይም በሕይወቱ ውስጥ የተለየ መከራ የደረሰበት ሰው ታውቃለህ? ፍቅርን ማስፋት እንዲሁም የለጋስነት መንፈስ ማዳበር የተቸገሩ ሰዎች ያሉበትን ሁኔታ እንድትረዳ ብሎም እንድትደግፋቸው ይረዳሃል።

የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች በቅርቡ ፍጻሜያቸውን በሚያገኙበት ጊዜ ከሀብት፣ ከችሎታና ከስኬት የበለጠ ጠቀሜታ የሚኖረው በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የምንመሠርተው ጠንካራ አንድነት ነው። (1 ጴጥሮስ 4:7, 8) እያንዳንዳችን ለእምነት ባልንጀሮቻችን ያለንን ፍቅር በማስፋት በጉባኤያችን ውስጥ ያለውን አንድነት ይበልጥ ለማጠናከር የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማድረግ እንችላለን። ኢየሱስ ክርስቶስ “ትእዛዜ ይህች ናት፤ እኔ እንደ ወደድኋችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ” በማለት የሰጠንን ትእዛዝ ተግባራዊ ስናደርግ ይሖዋ አብዝቶ እንደሚባርከን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ዮሐንስ 15:12

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ማድነቅ ሲባል ሁሉንም ከፍ አድርገን መመልከት፣ ክብራቸውን መጠበቅ እንዲሁም ለሚያስፈልጓቸው ነገሮች ንቁ መሆን ማለት ነው