በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ልጅ በሚያምጽበት ጊዜ ወላጆች በጽናት መቆም የሚችሉት እንዴት ነው?

ልጅ በሚያምጽበት ጊዜ ወላጆች በጽናት መቆም የሚችሉት እንዴት ነው?

ልጅ በሚያምጽበት ጊዜ ወላጆች በጽናት መቆም የሚችሉት እንዴት ነው?

ጆይ የምትባል አንዲት ክርስቲያን (እውነተኛ ስሟ አይደለም) ልጇን ለይሖዋ አምላክ ፍቅር እንዲኖረው አድርጋ ለማሳደግ የተቻላትን ያህል ጥራለች። ይሁንና በአሥራዎቹ ዕድሜው መጨረሻ ላይ ሲደርስ ዓምጾ ከቤት ወጣ። ጆይ የተሰማትን ስትገልጽ እንዲህ ብላለች:- “በሕይወቴ ይህን ያህል ያሳዘነኝ ነገር ገጥሞኝ አያውቅም። እንደተከዳሁ ሆኖ ተሰማኝ፣ ቅስሜ ተሰበረ እንዲሁም ተስፋ ቆረጥኩ፤ አእምሮዬ በአፍራሽ አስተሳሰብ ተሞላ።”

ምናልባት እናንተም ልጆቻችሁን አምላክን እንዲወዱትና እንዲያገለግሉት አድርጋችሁ ለማሳደግ ጥራችሁ ሊሆን ይችላል። ከጊዜ በኋላ ግን ከልጆቻችሁ መካከል አንዱ ወይም የተወሰኑት ለአምላክ ጀርባቸውን ሰጥተው ይሆናል። እንደዚህ ዓይነቱን ከባድ ሐዘን መቋቋም የምትችሉት እንዴት ነው? ይሖዋን በማገልገል እንድትጸኑ ምን ሊረዳችሁ ይችላል?

የይሖዋ ልጆች ባመጹ ጊዜ

በመጀመሪያ ደረጃ ይሖዋ ምን እንደሚሰማችሁ በሚገባ የሚያውቅ መሆኑን መገንዘብ ይኖርባችኋል። በኢሳይያስ 49:15 ላይ እንዲህ የሚል እናነባለን:- “እናት የምታጠባውን ልጇን ልትረሳ ትችላለችን? ለወለደችውስ ልጅ አትራራለትምን? ምናልባት እርሷ ትረሳ ይሆናል፣ እኔ ግን አልረሳሽም።” አዎን፣ ይሖዋ አባቶችና እናቶች የሚሰማቸው ዓይነት ስሜት አለው። በመሆኑም ልጆቹ የሆኑት መላእክት በሙሉ ሲያወድሱትና ሲያገለግሉት በነበረበት ጊዜ ምን ያህል ተደስቶ እንደሚሆን አስቡ። ይሖዋ የእምነት አባት ለሆነው ለኢዮብ “በዐውሎ ነፋስ ውስጥ ሆኖ” በመለሰለት ጊዜ አንድነት ካለው መንፈሳዊ ቤተሰቡ ጋር ያሳለፉትን የደስታ ጊዜ በማስታወስ እንዲህ ብሎታል:- “ምድርን በመሠረትሁ ጊዜ አንተ የት ነበርህ? . . . ይህም የሆነው የንጋት ከዋክብት በዘመሩበት ጊዜ፣ መላእክትም እልል ባሉበት ጊዜ ነበር።”—ኢዮብ 38:1, 4, 7

ከጊዜ በኋላ፣ እውነተኛው አምላክ ፍጹም ከሆኑት መንፈሳዊ ልጆቹ መካከል አንዱ በእርሱ ላይ ዓምጾ ሰይጣን ወይም “ተቃዋሚ” ሲሆን አይቷል። ከዚህም በላይ ይሖዋ የመጀመሪያዎቹ ሰብዓዊ ልጆቹ ማለትም አዳምና ፍጹም የሆነችው ሚስቱ ሔዋን በዚህ ዓመጽ ሲተባበሩ ተመልክቷል። (ዘፍጥረት 3:1-6፤ ራእይ 12:9) ቆየት ብሎም መላእክት የሆኑት ሌሎች ልጆቹ ‘መኖሪያቸውን በመተው’ በአምላክ ላይ ዓምጸዋል።—ይሁዳ 6

ቅዱሳን መጻሕፍት ይሖዋ ፍጹም ከሆኑት ልጆቹ መካከል የተወሰኑት ባመጹ ጊዜ ምን ተሰምቶት እንደነበር አይገልጹም። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ሲል በግልጽ ይናገራል:- “እግዚአብሔር አምላክ የሰው ዐመፅ በምድር ላይ የበዛና የልቡም ሐሳብ ዘወትር ወደ ክፋት ብቻ ያዘነበለ መሆኑን ተመለከተ። እግዚአብሔር ሰውን በምድር ላይ በመፍጠሩ ተጸጸተ፤ ልቡም እጅግ አዘነ።” (ዘፍጥረት 6:5, 6) ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ ምርጥ ሕዝቦቹ የነበሩት እስራኤላውያን ባመጹ ጊዜ ‘አዝኗል።’—መዝሙር 78:40, 41

በመሆኑም ይሖዋ ልጆቻቸው በማመጻቸው ምክንያት ያዘኑ ወላጆችን ስሜት እንደሚረዳ ምንም ጥርጥር የለውም። እንደነዚህ ያሉት ወላጆች የደረሰባቸውን ሁኔታ ለመቋቋም የሚያስችላቸውን ጠቃሚ ምክርና ማበረታቻ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ሰጥቷል። አምላክ የሚያስጨንቃቸውን በእርሱ ላይ እንዲጥሉ፣ ራሳቸውን በትሕትና ዝቅ እንዲያደርጉና ሰይጣን ዲያብሎስን ጸንተው እንዲቃወሙት አሳስቧቸዋል። ይህ ማሳሰቢያ ልጃችሁ በሚያምጽበት ጊዜ በአቋማችሁ እንድትጸኑ የሚረዳችሁ እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

የሚያስጨንቃችሁን በይሖዋ ላይ ጣሉት

ይሖዋ፣ ወላጆች ልጆቻቸው ራሳቸውን ሊጎዱ ወይም በሌሎች ሊጠቁ እንደሆነ ሲሰማቸው በጣም እንደሚጨነቁ ያውቃል። ሐዋርያው ጴጥሮስ ይህን መሰሉንም ሆነ ሌሎች አስጨናቂ ሁኔታዎችን መቋቋም የምንችልበትን መንገድ ሲጠቁም “እርሱ ስለ እናንተ ስለሚያስብ የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ [በይሖዋ] ላይ ጣሉት” ብሏል። (1 ጴጥሮስ 5:7) ይህ የሚያጽናና ግብዣ በተለይ ልጃቸው ላመጸባቸው ወላጆች ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

ልጃችሁ ትንሽ ሳለ እርሱን ከአደጋ ለመጠበቅ ንቁ ነበራችሁ፤ እርሱም ቢሆን የምትሰጡትን ፍቅራዊ መመሪያ ይቀበል እንደነበር አያጠራጥርም። ይሁንና እያደገ ሲሄድ በእርሱ ላይ የምታደርጉት ቁጥጥር እየቀነሰ ሊመጣ ይችላል። እርሱን ከጉዳት ለመጠበቅ ያላችሁ ፍላጎት ግን አይቀንስም፤ እንዲያውም ይጨምር ይሆናል።

በዚህ ምክንያት፣ ልጃችሁ ዓምጾ መንፈሳዊ፣ ስሜታዊና አካላዊ ጉዳት ሲደርስበት ስታዩ ለዚህ ሁኔታ ተጠያቂው ራሳችሁ እንደሆናችሁ ይሰማችሁ ይሆናል። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ጆይ እንዲህ ተሰምቷት ነበር። እንዲህ ትላለች:- “በየቀኑ በጥፋተኝነት ስሜት እሠቃይና ምን አጥፍቼ ይሆን እያልኩ ስላለፈው ጊዜ አወጣና አወርድ ነበር።” በተለይ በዚህ ወቅት ይሖዋ ‘የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ እንድትጥሉ’ ይፈልጋል። እንደዚህ ካደረጋችሁ ይረዳችኋል። መዝሙራዊው “የከበደህን ነገር በእግዚአብሔር ላይ ጣል፤ እርሱ ደግፎ ይይዝሃል፤ የጻድቁንም መናወጥ ከቶ አይፈቅድም” ብሏል። (መዝሙር 55:22) ጆይ እንዲህ ማድረጓ ምን ያህል እንዳጽናናት ስትገልጽ “የልቤን ሁሉ አንድም ሳላስቀር ለይሖዋ ነገርኩት። ስሜቴን ግልጥልጥ አድርጌ መንገሬም ትልቅ እፎይታ አስገኝቶልኛል” ብላለች።

አለፍጽምና ያለባችሁ ወላጆች እንደመሆናችሁ መጠን ልጃችሁን በምታሳድጉበት ጊዜ አንዳንድ ስህተቶችን ሠርታችሁ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ለምን በስህተታችሁ ላይ ብቻ ታተኩራላችሁ? ይሖዋ በስህተታችሁ ላይ አያተኩርም። መዝሙራዊው በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት “እግዚአብሔር ሆይ፤ ኀጢአትን ብትቈጣጠር፣ ጌታ ሆይ፤ ማን ሊቆም ይችላል?” ሲል የዘመረው ለዚህ ነው። (መዝሙር 130:3) ፍጹም ወላጅ ብትሆኑ እንኳ ልጃችሁ ሊያምጽ ይችላል። ስለዚህ ስሜታችሁን ለይሖዋ በጸሎት ንገሩት፤ እርሱም ችግራችሁን እንድትቋቋሙ ይረዳችኋል። ይሁንና እናንተ ራሳችሁ ይሖዋን በማገልገል ጸንታችሁ እንድትቀጥሉና የሰይጣን ጥቃት ሰለባ እንዳትሆኑ ከዚህ የበለጠ ማድረግ ይኖርባችኋል።

ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ

ጴጥሮስ “እርሱ በወሰነው ጊዜ ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከእግዚአብሔር ብርቱ እጅ በታች ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ” በማለት ጽፏል። (1 ጴጥሮስ 5:6) አንድ ወላጅ ልጁ በሚያምጽበት ጊዜ ትሑት መሆን የሚያስፈልገው ለምንድን ነው? ልጃችሁ ማመጹ የጥፋተኝነት ስሜትና ሐዘን እንዲሰማችሁ ከማድረጉም በተጨማሪ ለኀፍረት ሊዳርጋችሁ ይችላል። በተለይ ልጁ ከክርስቲያን ጉባኤ ከተወገደ ድርጊቱ የቤተሰባችሁን ስም እንዳጎደፈ ሆኖ ይሰማችሁ ይሆናል። በመሆኑም ራስን መኮነን ከኀፍረት ስሜት ጋር ተዳምሮ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ከመገኘት ወደኋላ እንድትሉ ሊያደርጋችሁ ይችላል።

እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥማችሁ ጥበበኛ መሆን ያስፈልጋችኋል። ምሳሌ 18:1 (የ1954 ትርጉም) “መለየት የሚወድድ ምኞቱን ይከተላል፣ መልካሙንም ጥበብ ሁሉ ይቃወማል” በማለት ያስጠነቅቃል። ሐዘን ቢኖርባችሁም አዘውትራችሁ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘታችሁ ጠቃሚ መመሪያና ማበረታቻ እንድታገኙ ያስችላችኋል። ጆይ “መጀመሪያ ላይ የሰው ዓይን ማየት አሳፍሮኝ ነበር” ስትል የተሰማትን ሳትሸሽግ ተናግራለች። አክላም እንዲህ ብላለች:- “ነገር ግን መንፈሳዊ ልማዴን አለማቋረጤ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ አሰብኩ፤ ቤት ብቀመጥም ችግሬን ከማብሰልሰል በቀር ሌላ ምንም አላደርግም። ስብሰባዎች ገንቢ በሆኑ መንፈሳዊ ነገሮች ላይ እንዳተኩር ረድተውኛል። ራሴን ባለማግለሌና ወንድሞቼና እህቶቼ ከሚሰጡኝ ፍቅራዊ ድጋፍ መጠቀም በመቻሌ እጅግ አመስጋኝ ነኝ።”—ዕብራውያን 10:24, 25

በተጨማሪም እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ክርስቲያናዊ ኃላፊነትን በተመለከተ “የራሱን ሸክም ሊሸከም” እንደሚገባው አትዘንጉ። (ገላትያ 6:5) ይሖዋ፣ ወላጆች ልጆቻቸውን እንዲወዷቸውና አስፈላጊውን ተግሣጽ እንዲሰጧቸው ይፈልጋል። ልጆችም ወላጆቻቸውን እንዲታዘዙና እንዲያከብሩ ይጠብቅባቸዋል። ወላጆች ልጆቻቸውን “በጌታ ምክርና ተግሣጽ” ኮትኩተው ለማሳደግ የተቻላቸውን ሁሉ ካደረጉ በአምላክ ዘንድ መልካም ስም ያተርፋሉ። (ኤፌሶን 6:1-4) አንድ ልጅ የወላጆቹን ፍቅራዊ ተግሣጽ ለመቀበል አሻፈረኝ ካለ መጥፎ ስም የሚያተርፈው እርሱ ራሱ ነው። ምሳሌ 20:11 “ሕፃን እንኳ ጠባዩ ንጹሕና ቅን መሆኑ፣ ከአድራጎቱ ይታወቃል” ይላል። የሰይጣን ማመጽ ሐቁን በሚያውቁ ዘንድ የይሖዋ ስም እንዲጎድፍ አላደረገም።

ዲያብሎስን ጸንታችሁ ተቃወሙት

ጴጥሮስ “ራሳችሁን የምትገዙ ሁኑ፤ ንቁም፤ ጠላታችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን በመፈለግ እንደሚያገሣ አንበሳ ወዲያ ወዲህ ይዞራል” በማለት አስጠንቅቋል። (1 ጴጥሮስ 5:8) ዲያብሎስ ልክ እንደ አንበሳ አብዛኛውን ጊዜ ለማጥቃት የሚመርጠው ወጣቶችንና ተሞክሮ የሌላቸውን ነው። በጥንት እስራኤል አንበሶች የቤት እንስሳት ወደሚሰማሩባቸው መስኮች ይወጡ ስለነበር ከመንጋው የተነጠለ አንድ ግልገል በቀላሉ የጥቃት ሰለባ ሊሆን ይችላል። እናቲቱ ግልገሏን ለማዳን ስትል በደመ ነፍስ ሕይወቷን አደጋ ላይ ትጥል ይሆናል። ሆኖም አንድ ትልቅ በግ እንኳ አንበሳን መቋቋም አይችልም። በመሆኑም መንጋውን የሚጠብቁ ደፋር እረኞች ያስፈልጉ ነበር።—1 ሳሙኤል 17:34, 35

ይሖዋ ምሳሌያዊ በጎቹን ‘ከሚያገሳው አንበሳ’ ለመጠበቅ ሲል “የእረኞች አለቃ” በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ሥር ሆነው መንጋውን የሚንከባከቡ መንፈሳዊ እረኞች አዘጋጅቷል። (1 ጴጥሮስ 5:4) ጴጥሮስ ለእነዚህ የተሾሙ ወንዶች የሚከተለውን ማሳሰቢያ ሰጥቷቸዋል:- “በእናንተ ኀላፊነት ሥር ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ፤ የምትጠብቁትም ከእግዚአብሔር እንደሚጠበቅባችሁ በግድ ሳይሆን በፈቃደኝነት፣ ለጥቅም በመስገብገብ ሳይሆን ለማገልገል ባላችሁ ጽኑ ፍላጎት ይሁን።” (1 ጴጥሮስ 5:1, 2) የእናንተ የወላጆች ትብብር ታክሎበት እነዚህ እረኞች ልጃችሁ መንፈሳዊ አቋሙን እንዲያስተካክል ሊረዱት ይችሉ ይሆናል።

ክርስቲያን እረኞች ያመጸውን ልጃችሁን ለመገሠጽ ሲሞክሩ ልትከላከሉለት ትፈልጉ ይሆናል። ይሁንና እንዲህ ያለውን አካሄድ መከተል ከባድ ስህተት ነው። ጴጥሮስ “[ዲያብሎስን] ጸንታችሁ ተቃወሙት” አለ እንጂ መንፈሳዊ እረኞችን ተቃወሙ አላለም።—1 ጴጥሮስ 5:9

ከባድ ተግሣጽ በሚሰጥበት ጊዜ

ልጃችሁ የተጠመቀ ክርስቲያን ከሆነና፣ ኃጢአት ሠርቶ ንስሐ ካልገባ ጥብቅ ተግሣጽ ሊሰጠው ማለትም ከጉባኤ ሊወገድ ይችላል። ከዚህ በኋላ ከእርሱ ጋር የሚኖራችሁ ግንኙነት በዕድሜውና በሌሎች ሁኔታዎች ላይ የተመካ ይሆናል።

ልጁ ለአካለ መጠን ካልደረሰና አብሯችሁ የሚኖር ከሆነ የሚያስፈልጉትን ቁሳዊ ነገሮች ማሟላታችሁን እንደምትቀጥሉ ግልጽ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ሥነ ምግባራዊ ሥልጠናና ተግሣጽ ያስፈልገዋል፤ ይህንን የመስጠቱ ኃላፊነትም የእናንተው ነው። (ምሳሌ 1:8-18፤ 6:20-22፤ 29:17) የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ልትመሩለት ትፈልጉም ይሆናል፤ እንዲህ ለማድረግ ከወሰናችሁ በጥናቱ ላይ እንዲሳተፍ ማድረግ ይኖርባችኋል። የተለያዩ ጥቅሶችን ልብ እንዲልና “ታማኝና ልባም ባሪያ” ካዘጋጃቸው ጽሑፎች ተጠቃሚ እንዲሆን እርዱት። (ማቴዎስ 24:45 የ1954 ትርጉም) ልጃችሁን ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ልትወስዱትና አብሯችሁ እንዲቀመጥ ልታደርጉ ትችላላችሁ። ይህ ሁሉ የሚደረገው የተሰጠውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ልብ እንዲል ለመርዳት ታስቦ ነው።

የተወገደው ልጅ ለአካለ መጠን የደረሰና ራሱን ችሎ የሚኖር ከሆነ ግን ሁኔታው ከዚህ የተለየ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ በጥንት ቆሮንቶስ ይኖሩ የነበሩትን ክርስቲያኖች እንዲህ ሲል አሳስቧቸዋል:- “‘ወንድም ነኝ’ እያለ ከሚሴስን ወይም ከሚስገበገብ ወይም ጣዖትን ከሚያመልክ ወይም ከሚሳደብ ወይም ከሚሰክር ወይም ከሚቀማ ጋር እንዳትተባበሩ ነው፤ ከእንደዚህ ዐይነቱ ሰው ጋር ምግብ እንኳ አትብሉ።” (1 ቆሮንቶስ 5:11) አንዳንድ አስፈላጊ የሆኑ የቤተሰብ ጉዳዮች ከተወገደው ሰው ጋር እንድትገናኙ ሊያደርጓችሁ ቢችሉም፣ አንድ ክርስቲያን ወላጅ አላስፈላጊ ቅርርብ ላለመፍጠር መጣር ይኖርበታል።

ክርስቲያን እረኞች ኃጢአት የሠራን ልጅ በሚገሥጹበት ጊዜ ያስተላለፏቸውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ውሳኔዎች ለመቃወም ወይም ለማቃለል መሞከር ጥበብ አይሆንም። ላመጸው ልጃችሁ መወገናችሁ ከዲያብሎስ ጥቃት እውነተኛ ከለላ አያስገኝለትም። እንዲያውም የራሳችሁን መንፈሳዊ ጤንነት ለአደጋ ታጋልጣላችሁ። በሌላ በኩል ደግሞ የእረኞቹን ጥረት ብትደግፉ “በእምነት ጸንታችሁ” መቆምና ልጃችሁን ከሁሉ በተሻለ መንገድ መርዳት ትችላላችሁ።—1 ጴጥሮስ 5:9

ይሖዋ ይደግፋችኋል

ልጃችሁ ዓምጾባችሁ ከሆነ ይህ በእናንተ ላይ ብቻ የደረሰ አለመሆኑን አስታውሱ። ሌሎች ክርስቲያን ወላጆችም ተመሳሳይ ሁኔታ አጋጥሟቸዋል። ምንም ዓይነት ፈተና ይድረስብን ይሖዋ ይደግፈናል።—መዝሙር 68:19

ወደ ይሖዋ በመጸለይ በእርሱ እንደምትታመኑ አሳዩ። በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አዘውትራችሁ ተገኙ። የተሾሙ እረኞች የሚሰጡትን ተግሣጽ ደግፉ። ይህን ማድረጋችሁ ጸንታችሁ እንድትቆሙ ይረዳችኋል። እንዲሁም የእናንተ መልካም ምሳሌነት ልጃችሁ፣ ይሖዋ ወደ እርሱ እንዲመለስ ያቀረበለትን ፍቅራዊ ግብዣ እንዲቀበል ይረዳው ይሆናል።—ሚልክያስ 3:6, 7

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጸሎትና የክርስቲያን ጉባኤ ከሚያስገኙት ብርታት ተጠቀም