መጽሐፍ ቅዱስን በአፍሪካውያን ቋንቋ በማዘጋጀቱ ሥራ አዲስ ምዕራፍ የከፈቱ ክስተቶች
መጽሐፍ ቅዱስን በአፍሪካውያን ቋንቋ በማዘጋጀቱ ሥራ አዲስ ምዕራፍ የከፈቱ ክስተቶች
በአውሮፓና በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ ቅን አስተሳሰብ ያላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ አንባቢዎች፣ አፍሪካውያን የአምላክን ቃል በራሳቸው ቋንቋ ማንበብ መቻላቸው ያለውን አስፈላጊነት ከተገነዘቡ ቆይተዋል። ይህን ክቡር ዓላማ ከግብ ለማድረስ ሲሉ ብዙ ሰዎች የአፍሪካውያንን ቋንቋ ለመማር ወደ አፍሪካ አመሩ። ከእነዚህ ሰዎች መካከል የተወሰኑት፣ ለአንዳንድ የአፍሪካ ቋንቋዎች በጽሑፍ ለማስፈር የሚያስችሉ ፊደላትን ፈጥረውላቸዋል፤ እንዲሁም መዝገበ ቃላቶችን አዘጋጅተዋል። ከዚያ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን ወደተለያዩ የአፍሪካ ቋንቋዎች መተርጎም ጀመሩ። ይህ ደግሞ ቀላል ሥራ አልነበረም። ዘ ካምብሪጅ ሂስትሪ ኦቭ ዘ ባይብል የተባለው መጽሐፍ “አንድ ተርጓሚ በጣም ቀላልና መሠረታዊ የሚባለውን የክርስትና ትምህርት የሚወክል ተስማሚ ቃል ለማግኘት ለዓመታት መልፋት ሊያስፈልገው ይችላል” ብሏል።
ፊደል የሌለው ቋንቋ ከነበራቸው የአፍሪካ ሕዝቦች መካከል የጽዋና ሕዝቦች በ1857 የተሟላ መጽሐፍ ቅዱስ በማግኘት ቀዳሚዎች ሆነዋል። a ይህ መጽሐፍ በተለያዩ ጥራዞች ተከፋፍሎ የታተመ እንጂ በአንድ ጥራዝ የተዘጋጀ አልነበረም። ውሎ አድሮ መጽሐፍ ቅዱስ በአፍሪካ በሚነገሩ ሌሎች ቋንቋዎችም ይተረጎም ጀመር። በአፍሪካ ቋንቋ ከተዘጋጁት ከእነዚህ የቀድሞ ትርጉሞች መካከል አብዛኞቹ በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትም (“ብሉይ ኪዳን”) ይሁን በግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት (“አዲስ ኪዳን”) ውስጥ ይሖዋ የሚለውን የአምላክን ስም ይጠቀሙ ነበር። ይሁንና፣ ከዚያ በኋላ ተሻሽለው የወጡትንም ሆነ በአዲስ መልክ የተተረጎሙትን መጽሐፍ ቅዱሶች ያዘጋጁት ሰዎች የመጽሐፉ ባለቤት ለሆነው ለይሖዋ ቅዱስ ስም አክብሮት አልነበራቸውም። እነዚህ ሰዎች የአይሁዳውያንን አጉል እምነት በመከተል መለኮታዊውን ስም አምላክ ወይም ጌታ እንደሚሉት ባሉ የማዕረግ ስሞች ተክተውታል። በመሆኑም አምላክን ለሚወዱ አፍሪካውያን መለኮታዊውን ስም የያዘ አዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ማዘጋጀት አስፈላጊ ሆነ።
ከ1980ዎቹ ዓመታት አንስቶ የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል የአዲስ ዓለም የቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉም በአፍሪካ በሚነገሩ ዋና ዋና ቋንቋዎች እንዲተረጎም ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ ቋይቷል። በዚህም ምክንያት በዛሬው ጊዜ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ለመጽሐፍ ቅዱስ ከፍተኛ ግምት የሚሰጡ አፍሪካውያን አዲስ ዓለም ትርጉምን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ማንበብ ችለዋል። በአሁኑ ወቅት አዲስ ዓለም ትርጉም በሙሉም ሆነ በከፊል በ17 የአፍሪካውያን ቋንቋዎች ይገኛል።
ኢሳይያስ 61:1, 2) በሉቃስ ወንጌል ላይ የሰፈረው ኢየሱስ ያነበበው ይህ የኢሳይያስ ክፍል በአዲስ ዓለም ትርጉም ላይ እንዲህ ይላል:- “የይሖዋ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ለድኾች ወንጌልን እንድሰብክ ቀብቶኛልና፤ ለታሰሩት መፈታትን፣ ለታወሩትም ማየትን እንዳውጅ፣ የተጨቈኑትን ነጻ እንዳወጣ፣ የተወደደችውንም የይሖዋን ዓመት እንዳውጅ ልኮኛል።”—ሉቃስ 4:18, 19
በአፍሪካውያን ቋንቋ የተዘጋጁትን እነዚህን መጽሐፍ ቅዱሶች የሚያነብቡ ሰዎች ይሖዋ ለሚለው የአምላክ ክቡር ስም ትልቅ ቦታ የሚሰጥ መጽሐፍ ቅዱስ በማግኘታቸው ተደስተዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ ናዝሬት በሚገኘው ምኩራብ ሳለ የመጣበትን ተልዕኮ ያስታወቀው ከኢሳይያስ ጥቅልል ላይ የተወሰነ ክፍል በማንበብ ነበር፤ በዚህ ክፍል ላይ የአባቱ ስም ይገኛል። (መጽሐፍ ቅዱስን በአፍሪካውያን ቋንቋ በማዘጋጀቱ ሥራ፣ ሌላ ምዕራፍ የተከፈተው ደግሞ በነሐሴ 2005 ነው። በዚህ ወር፣ በደቡብ አፍሪካ የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ከ76,000 የሚበልጡ በአፍሪካውያን ቋንቋ የተዘጋጁ የአዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱሶችን ለማተም ችሏል። ከእነዚህ ውስጥ በሾና ቋንቋ የተዘጋጁ 30,000 መጽሐፍ ቅዱሶች ይገኙበታል። ይህ መጽሐፍ ቅዱስ በዚምባብዌ በተደረገውና “አምላካዊ ታዛዥነት” የሚል ርዕስ በነበረው የይሖዋ ምሥክሮች የአውራጃ ስብሰባ ላይ ወጥቷል።
በዚያ የማይረሳ ወር የደቡብ አፍሪካን ቅርንጫፍ ቢሮ የጎበኙ ወንድሞች በሌሎች የአፍሪካ ቋንቋዎች የተዘጋጁ መጽሐፍ ቅዱሶች ሲታተሙ በማየታቸው በጣም ተደስተዋል። የቤቴል ቤተሰብ አባል የሆነውና በጥረዛ ክፍል ውስጥ የሚሠራው ንግህላንግህላ እንዲህ ብሏል:- “በሾናም ሆነ በሌሎች የአፍሪካ ቋንቋዎች የአዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ ሲታተም የመርዳት መብት በማግኘቴ እጅግ ተደስቻለሁ።” የዚህ ወንድም አስተያየት የደቡብ አፍሪካ ቤቴል ቤተሰብ አባላት በሙሉ ያላቸውን ስሜት የሚያንጸባርቅ ነው።
አሁን አፍሪካውያን መጽሐፍ ቅዱሶችን ከባሕር ማዶ እየታተሙ ይመጡ ከነበረበት ጊዜ በተሻለ ፍጥነትና በአነስተኛ ዋጋ ማግኘት ይችላሉ። ከሁሉም በላይ፣ በአሁኑ ጊዜ አፍሪካውያን የታላቁን የመጽሐፍ ቅዱስ ባለቤት የይሖዋ አምላክን ስም የያዘ ትክክለኛ ትርጉም አግኝተዋል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a መጽሐፍ ቅዱስ፣ በ1835 የማዳጋስካር ቋንቋ በሆነው በማለጋሲ፣ በ1840 ደግሞ በአማርኛ ተተርጉሞ ነበር። በእነዚህ ቋንቋዎች መጽሐፍ ቅዱስ ከመተርጎሙ ከረጅም ጊዜ በፊት አንስቶ ቋንቋዎቹ በጽሑፍ እንዲሰፍሩ የሚያስችሏቸው ፊደላት ነበሯቸው።
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መለኮታዊው ስም፣ በ1840 በታተመው የጽዋና መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ
[የሥዕል ምንጭ]
Harold Strange Library of African Studies
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከስዋዚላንድ የመጡ ጎብኚዎች በደቡብ አፍሪካ ቅርንጫፍ ቢሮ በመታተም ላይ ያሉትን መጽሐፍ ቅዱሶች ሲመለከቱ