ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት እንዲታዘዙ እርዳ
ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት እንዲታዘዙ እርዳ
“በመልካም መሬት ላይ የወደቀውም ቃሉን ቅንና በጎ በሆነ ልብ ሰምተው የሚጠብቁ፣ ታግሠውም በመጽናት ፍሬ የሚያፈሩ ናቸው።”—ሉቃስ 8:15
1, 2. (ሀ) ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለው መጽሐፍ የተዘጋጀበት ዓላማ ምንድን ነው? (ለ) ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ይሖዋ፣ ሕዝቡ ሌሎችን ደቀ መዛሙርት ለማድረግ ሲሉ ያደረጉትን ጥረት የባረከው እንዴት ነው?
የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ የሆነች አንዲት የይሖዋ ምሥክር ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? a የተባለውን መጽሐፍ አስመልክታ እንዲህ ብላለች:- “ግሩም መጽሐፍ ነው። እኔም ሆንኩ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቼ በጣም ወደነዋል። ይህ መጽሐፍ ሰዎችን በራቸው ላይ እንደቆሙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር ይረዳል።” በዕድሜ የገፉ አንድ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪ ደግሞ እንዲህ ብለዋል:- “በአገልግሎት ባሳለፍኳቸው 50 ዓመታት፣ ብዙ ሰዎች ይሖዋን እንዲያውቁ የመርዳት መብት አግኝቻለሁ። ይህ የማስጠኛ መጽሐፍ ግን ወደር የሌለው እንደሆነ ለመግለጽ እወዳለሁ። ምሳሌያዊ አገላለጾቹና ሥዕሎቹ እጅግ ማራኪ ናቸው።” አንተስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ስለተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይሰማሃል? ይህ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዳ መጽሐፍ፣ ኢየሱስ “ሂዱና ሕዝቦችን ሁሉ . . . ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ አስተምሯቸው” ሲል የሰጠውን ትእዛዝ እንድትፈጽም ለመርዳት የተዘጋጀ ነው።—ማቴዎስ 28:19, 20
2 በዛሬው ጊዜ፣ 6.6 ሚሊዮን የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉ የሰጣቸውን ትእዛዝ በፈቃደኝነት በመፈጸም ላይ መሆናቸው የይሖዋን ልብ እንደሚያስደስት ምንም ጥርጥር የለውም። (ምሳሌ 27:11) ይሖዋ ጥረታቸውን እየባረከው መሆኑ ግልጽ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ በ2005 የአገልግሎት ዓመት ምሥራቹ በ235 አገሮች የተሰበከ ሲሆን በአማካይ ከ6,061,500 በላይ የሚሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ተመርተዋል። በውጤቱም ብዙ ሰዎች ‘የአምላክን ቃል በሰሙ ጊዜ እንደ ሰው ቃል ሳይሆን እንደ አምላክ ቃል አድርገው ተቀብለውታል።’ (1 ተሰሎንቄ 2:13) ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ከግማሽ ሚሊዮን የሚበልጡ አዳዲስ ደቀ መዛሙርት ሕይወታቸውን ከይሖዋ መሥፈርቶች ጋር በማስማማት ለአምላክ ራሳቸውን ወስነዋል።
3. በዚህ ርዕስ ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለውን መጽሐፍ አጠቃቀም በተመለከተ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?
3 በቅርብ ጊዜ ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስ በማስጠናት የሚገኘውን ደስታ ማጣጣም ችለሃል? አሁንም የአምላክን ቃል ሰምተው ‘የሚጠብቁ፣ ታግሠውም በመጽናት ፍሬ የሚያፈሩ ቅንና በጎ የሆነ ልብ’ ያላቸው ሰዎች በዓለም ዙሪያ ይገኛሉ። (ሉቃስ 8:11-15) የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለውን መጽሐፍ ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ እንዴት ልትጠቀምበት እንደምትችል እስቲ እንመልከት። በዚህ ርዕስ ውስጥ የሚከተሉትን ሦስት ጥያቄዎች እንመረምራለን:- (1) የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመር የምትችለው እንዴት ነው? (2) ይበልጥ ውጤታማ የሆኑት የማስተማሪያ ዘዴዎች የትኞቹ ናቸው? (3) አንድ ሰው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ብቻ ሳይሆን የአምላክ ቃል አስተማሪ እንዲሆን እንዴት ልትረዳው ትችላለህ?
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመር የምትችለው እንዴት ነው?
4. አንዳንዶች መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚያቅማሙት ለምንድን ነው? ይህን አመለካከታቸውን እንዲቀይሩስ እንዴት ልትረዳቸው ትችላለህ?
4 አንድ ሰፊ ጅረት በአንድ እርምጃ እንድትሻገር ብትጠየቅ ይህ ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር እንደሆነ ይሰማህ ይሆናል። ይሁንና በየተወሰነ ርቀት ላይ መረማመጃ ድንጋዮች ቢቀመጡልህ ለመሻገር ልትስማማ ትችላለህ። በተመሳሳይም ሥራ የሚበዛበት አንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ያቅማማ ይሆናል። ግለሰቡ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ብዙ ጊዜና ጥረት እንደሚጠይቅ ሊሰማው ይችላል። ይህን አመለካከቱን እንዲቀይር እንዴት ልትረዳው ትችላለህ? የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለውን መጽሐፍ ተጠቅመህ፣ ትምህርት ሰጪ የሆኑና አጠር ያሉ ቀጣይ ውይይቶችን በማድረግ ግለሰቡን መደበኛ ወደሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ልታሸጋግረው ትችላለህ። በሚገባ ተዘጋጅተህ የምትሄድ ከሆነ ለግለሰቡ የምታደርግለት እያንዳንዱ ተመላልሶ መጠየቅ ከይሖዋ ጋር ለሚመሠርተው ዝምድና እንደ መረማመጃ ድንጋይ ይሆንለታል።
5. የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለውን መጽሐፍ ማንበብህ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
5 ይሁን እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ከተባለው መጽሐፍ እንዲጠቀሙ ሌሎችን ለመርዳት ከመነሳትህ በፊት አንተ ራስህ መጽሐፉን በደንብ ልታውቀው ይገባል። መጽሐፉን ከዳር እስከ ዳር አንብበኸዋል? አንድ ባልና ሚስት ለእረፍት በሄዱ ጊዜ መጽሐፉን ይዘው ስለነበር በባሕር ዳርቻ ላይ እየተዝናኑ ያነብቡት ጀመር። ለጎብኚዎች ዕቃ የምትሸጥ በአካባቢው የምትኖር አንዲት ሴት ወደ እነርሱ ስትቀርብ ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የሚለውን ርዕስ ተመለከተች። ከዚያም ይህቺ ሴት፣ በዚያው ዕለት ትንሽ ቀደም ብላ ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምን እንደሆነ ለማወቅ እንዲረዳት ወደ አምላክ ጸሎት አቅርባ እንደነበር ነገረቻቸው። ባልና ሚስቱም መጽሐፉን በደስታ ሰጧት። አንተስ የቀጠሮህ ሰዓት እስኪደርስ ወይም ደግሞ በትምህርት ቤት አሊያም በመሥሪያ ቤት የእረፍት ጊዜህ ላይ ይህንን ጽሑፍ ምናልባትም ለሁለተኛ ጊዜ ለማንበብ ‘ጊዜ እየዋጀህ’ ነው? (ኤፌሶን 5:15, 16) እንዲህ ማድረግህ፣ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ከሚረዳው ከዚህ ጽሑፍ ጋር ይበልጥ ለመተዋወቅ የሚያስችልህ ሲሆን የያዛቸውን ቁም ነገሮች ለሌሎች ለማካፈልም አጋጣሚ ይከፍትልሃል።
6, 7. የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተሰኘውን መጽሐፍ፣ ጥናት ለማስጀመር እንዴት ልትጠቀምበት ትችላለህ?
6 መጽሐፉን በአገልግሎት ላይ በምታበረክትበት ጊዜ በገጽ 4, 5 እና 6 ላይ ያሉትን ሥዕሎች፣ ጥቅሶችና ጥያቄዎች ውጤታማ በሆነ መንገድ ተጠቀምባቸው። ለምሳሌ የሚከተለውን ጥያቄ በመጠየቅ ውይይት መጀመር ትችላለህ:- “በዛሬው ጊዜ የሰው ዘር ካሉበት በርካታ ችግሮች አንጻር አስተማማኝ መመሪያ ማግኘት የሚቻለው ከየት ነው?” ግለሰቡ የሚሰጥህን መልስ በጥሞና ካዳመጥክ በኋላ 2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17ን አንብብለት፤ እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ልጆች ላሉባቸው ችግሮች ትክክለኛ መፍትሔ እንደሚሰጥ አብራራለት። ከዚያም የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በተባለው መጽሐፍ ገጽ 4 እና 5 ላይ የሚገኙትን ሥዕሎች በማሳየት “በሥዕሉ ላይ ከምታያቸው ነገሮች መካከል በጣም የሚያስጨንቅህ የትኛው ነው?” ብለህ ጠይቀው። ከሥዕሎቹ ውስጥ አንዱን ሲጠቁምህ መጽሐፉን እንዲይዝልህ አድርግና ችግሩን አስመልክቶ የተጠቀሰውን ጥቅስ ከመጽሐፍ ቅዱስህ ላይ አንብብለት። ቀጥሎም ገጽ 6ን አንብብለትና “በዚህ ገጽ መጨረሻ ላይ ከሚገኙት ስድስት ጥያቄዎች መካከል የትኛው እንዲመለስልህ ትፈልጋለህ?” የሚል ጥያቄ አቅርብለት። አንዱን ሲመርጥ፣ የጥያቄውን መልስ የሚያብራራውን ምዕራፍ አሳየውና መጽሐፉን አበርክትለት፤ ከዚያም በሌላ ቀን ተገናኝታችሁ በጥያቄው ላይ እንድትወያዩ ቁርጥ ያለ ቀጠሮ ያዝ።
7 ከላይ ያለውን ሐሳብ በመጠቀም አምስት ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ውይይት ማድረግ ይቻላል። ይሁንና በእነዚህ ጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ የቤቱ ባለቤት ምን እንደሚያሳስበው ማወቅ፣ ሁለት ጥቅሶች አንብበህ ማብራራት እንዲሁም ለተመላልሶ መጠየቅ መሠረት መጣል ችለሃል። ከዚህ ሰው ጋር ያደረግኸው አጭር ውይይት ከምንም በላይ አጽናንቶትና አበረታቶት ሊሆን ይችላል። በመሆኑም ሥራ የሚበዛበት ሰው እንኳ ካንተ ጋር ጥቂት ደቂቃዎች ለማሳለፍ ፈቃደኛ መሆኑ አይቀርም። በዚህ መንገድ ‘ወደ ሕይወት የሚያደርሰውን መንገድ’ ለማግኘት የሚያስችለውን ቀጣይ እርምጃ እንዲወስድ ትረዳዋለህ። (ማቴዎስ 7:14) የቤቱ ባለቤት ፍላጎት እያደገ ሲሄድ በጥናቱ ላይ የምታሳልፉት ጊዜ መርዘም ይኖርበታል። ይህን ለማድረግ ደግሞ ቤት ውስጥ ቁጭ ብላችሁ ረዘም ላለ ጊዜ እንድታጠኑ ሐሳብ ልታቀርብለት ትችላለህ።
ይበልጥ ውጤታማ የሆኑት የማስተማሪያ ዘዴዎች
8, 9. (ሀ) የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪህ የሚያጋጥሙትን መሰናክሎች እና ፈተናዎች ለመቋቋም ዝግጁ እንዲሆን እንዴት ልትረዳው ትችላለህ? (ለ) ጠንካራ እምነት ለመገንባት የሚያስፈልጉትን እሳት መቋቋም የሚችሉ ማዕድናት ከየት ማግኘት ይቻላል?
8 አንድ ሰው የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርቶች መታዘዝ ሲጀምር እድገቱን ሊገቱ የሚችሉ እንቅፋቶች ሊያጋጥሙት ይችላሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ “በክርስቶስ ኢየሱስ በእውነተኛ መንፈሳዊ ሕይወት መኖር የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ” በማለት ተናግሯል። (2 ጢሞቴዎስ 3:12) ጳውሎስ ይህን ፈተና ጥራት በሌላቸው ቁሳቁሶች የተገነባ ሕንፃን ከሚያጠፋ፣ ሆኖም እንደ ወርቅ፣ ብርና የከበረ ድንጋይ በመሰሉ ቁሳቁሶች የታነጸውን ግን መጉዳት ከማይችል እሳት ጋር አወዳድሮታል። (1 ቆሮንቶስ 3:10-13፤ 1 ጴጥሮስ 1:6, 7) የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪህ የሚያጋጥሙትን ፈተናዎች ለመወጣት የሚያስችሉትን ባሕርያት እንዲያዳብር ለመርዳት፣ እሳትን መቋቋም በሚችሉ ቁሳቁሶች መገንባት ይኖርብሃል።
9 መዝሙራዊው የይሖዋን ቃል ‘ሰባት ጊዜ ከተጣራና፣ በምድር ላይ በከውር ከተፈተነ ብር’ ጋር አመሳስሎታል። (መዝሙር 12:6) በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ ጠንካራ እምነት ለመገንባት የሚያስችሉ ውድ ማዕድናት ይዟል። (መዝሙር 19:7-11፤ ምሳሌ 2:1-6) የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለው መጽሐፍ፣ ጥቅሶችን ውጤታማ በሆነ መንገድ መጠቀም የምትችለው እንዴት እንደሆነ ይጠቁማል።
10. ተማሪህ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንዲያተኩር ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?
10 በጥናቱ ወቅት ተማሪው በምዕራፉ ውስጥ ባሉት ጥቅሶች ላይ እንዲያተኩር እርዳው። ቁልፍ የሆኑ ጥቅሶችን እንዲረዳና በሕይወቱ ውስጥ እንዴት ሊሠራባቸው እንደሚችል እንዲያስተውል ለማድረግ ጥያቄዎችን ተጠቀም። ምን ማድረግ እንደሚገባው ከመንገር ተቆጠብ። ከዚህ ይልቅ የኢየሱስን ምሳሌ ኮርጅ። በአንድ ወቅት ኢየሱስ አንድ ሕግ አዋቂ ላቀረበለት ጥያቄ መልስ ሲሰጥ “በሕግ የተጻፈው ምንድን ነው? እንዴትስ ታነበዋለህ?” ሲል ጠይቆት ነበር። ሕግ አዋቂው ከቅዱሳን መጻሕፍት በመጥቀስ መልሱን ሰጠ። ከዚያም ኢየሱስ፣ ሰውየው መሠረታዊ ሥርዓቱን በሕይወቱ ውስጥ ተግባራዊ ማድረግ የሚችለው እንዴት እንደሆነ እንዲያስተውል ረዳው። በተጨማሪም ምሳሌ በመንገር ትምህርቱ እንዴት እንደሚነካው እንዲገነዘብ አደረገ። (ሉቃስ 10:25-37) የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለው መጽሐፍ ተማሪህ ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያዎች በሕይወቱ ውስጥ እንዴት እንደሚሠሩ እንዲያስተውል ለመርዳት የሚያስችሉህ ቀላል የሆኑ በርካታ ምሳሌዎችን ይዟል።
11. በእያንዳንዱ የጥናት ክፍለ ጊዜ ምን ያህል አንቀጽ መሸፈን ይኖርባችኋል?
11 ኢየሱስ ውስብስብ ሐሳቦችን ለማስረዳት ቀለል ባሉ አገላለጾች ይጠቀም እንደነበረ ሁሉ ይህ መጽሐፍም የአምላክን ቃል ቀላልና ግልጽ በሆነ መንገድ ያብራራል። (ማቴዎስ 7:28, 29) ስለዚህ ትምህርቱን ቀላልና ግልጽ በሆነ መንገድ እንዲሁም በትክክል በማስተላለፍ የኢየሱስን ምሳሌ ተከተል። ምዕራፉን ለመጨረስ አትጣደፍ። በእያንዳንዱ የጥናት ክፍለ ጊዜ ምን ያህል አንቀጽ መሸፈን እንዳለባችሁ የሚወስኑት በወቅቱ ያሉት ሁኔታዎችና የተማሪው ችሎታ ናቸው። ኢየሱስ የደቀ መዛሙርቱን የአቅም ውስንነት ያውቅ ስለነበር በጊዜው ከሚያስፈልጋቸው በላይ ብዙ ሐሳብ በመንገር አላስፈላጊ ሸክም አልጫነባቸውም።—ዮሐንስ 16:12
12. ተጨማሪ ክፍሉን እንዴት ልትጠቀምበት ይገባል?
12 የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለው መጽሐፍ 14 ርዕሰ ጉዳዮችን የሚዳስስ ተጨማሪ ክፍል አለው። አስተማሪው እንደመሆንህ መጠን የተማሪህን ፍላጎት ግምት ውስጥ በማስገባት ይህ ክፍል በምን መንገድ ቢሸፈን የተሻለ እንደሚሆን መወሰን ይኖርብሃል። ለምሳሌ ያህል፣ ተማሪው አንድን ርዕሰ ጉዳይ መረዳት ቢከብደው ወይም በፊት ያምንበት ከነበረው ትምህርት የተነሳ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ጥያቄ ቢኖረው መልሱን ከተጨማሪ ክፍሉ ላይ ራሱ እንዲመለከት መጠቆም ብቻ በቂ ሊሆን ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ የተማሪው ሁኔታ ክፍሉን አብረኸው እንድትሸፍን ሊያነሳሳህ ይችላል። ተጨማሪ ክፍሉ፣ “‘ነፍስ’ እና ‘መንፈስ’—የእነዚህ ቃላት ትርጉም ምንድን ነው?” እንዲሁም “‘ታላቂቱ ባቢሎንን’ ለይቶ ማወቅ” እንደሚሉት ያሉ አስፈላጊ ቅዱስ ጽሑፋዊ ርዕሰ ጉዳዮችን ይዟል። እነዚህን ነጥቦች ከተማሪህ ጋር ልትወያይባቸው ትፈልግ ይሆናል። በተጨማሪ ክፍሉ ውስጥ ለሚገኙት ርዕሰ ጉዳዮች የመወያያ ጥያቄዎች ስላልተዘጋጁላቸው ትርጉም ያዘሉ ጥያቄዎችን አንስተህ ለማወያየት እንድትችል ትምህርቱን በደንብ ማወቅ ይኖርብሃል።
13. ጸሎት እምነትን በማጠንከር ረገድ ምን ሚና ይጫወታል?
13 መዝሙር 127:1 “እግዚአብሔር ቤትን ካልሠራ፣ ሠራተኞች በከንቱ ይደክማሉ” ይላል። ስለሆነም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመምራት ስትዘጋጅ የይሖዋን እርዳታ ለማግኘት ጸልይ። በጥናቱ መጀመሪያና መጨረሻ ላይ የምታቀርበው ጸሎት ከይሖዋ ጋር ያለህን የቅርብ ዝምድና የሚያንጸባርቅ ይሁን። ተማሪው የአምላክን ቃል ለመረዳት የሚያስችለውን ጥበብ፣ እንዲሁም ምክሩን በተግባር ለማዋል የሚረዳውን ጥንካሬ ማግኘት ይችል ዘንድ ወደ ይሖዋ እንዲጸልይ አበረታታው። (ያዕቆብ 1:5) እንዲህ ማድረጉ ፈተናዎችን ለመቋቋም የሚያስችል ጥንካሬ ያስገኝለታል፤ እንዲሁም እምነቱ እየጠነከረ ይሄዳል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የአምላክ ቃል አስተማሪዎች እንዲሆኑ እርዳ
14. የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ምን ዓይነት እድገት ማድረግ ይኖርባቸዋል?
14 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችን ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ያዘዘውን “ሁሉ” እንዲጠብቁ ከተፈለገ የአምላክ ቃል ተማሪዎች ከመሆን አልፈው አስተማሪዎች ሊሆኑ ይገባል። (ማቴዎስ 28:19, 20፤ የሐዋርያት ሥራ 1:6-8) አንድ ተማሪ ይህን መሰሉን መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርግ እንዴት ልትረዳው ትችላለህ?
15. የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪህ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ እንዲገኝ ልታበረታታው የሚገባው ለምንድን ነው?
15 ማጥናት ከጀመራችሁበት ጊዜ አንስቶ ተማሪው በስብሰባዎች ላይ እንዲገኝ ጋብዘው። የአምላክ ቃል አስተማሪ እንድትሆን ሥልጠና ያገኘኸው በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ እንደሆነ ንገረው። ለተወሰኑ ሳምንታት ከእያንዳንዱ የጥናት ክፍለ ጊዜ በኋላ ጥቂት ደቂቃዎች ወስደህ በጉባኤና በትልልቅ ስብሰባዎች ላይ ያገኘኸውን መንፈሳዊ ትምህርት አካፍለው። እነዚህ ስብሰባዎች ያስገኙልህን ጥቅሞች ሞቅ ባለ መንፈስ ተናገር። (ዕብራውያን 10:24, 25) ተማሪው በስብሰባዎች ላይ አዘውትሮ መገኘት ከጀመረ የአምላክ ቃል አስተማሪ መሆኑ አይቀርም።
16, 17. አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ሊደርስባቸው የሚችላቸው እንዴት ያሉ ግቦች ማውጣት ይችላል?
16 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪው ሊደርስባቸው የሚችላቸው ግቦች እንዲያወጣ እርዳው። ለምሳሌ፣ እየተማረ ስላለው ነገር ለጓደኛው ወይም ለዘመዱ እንዲናገር ልታበረታታው ትችላለህ። ከዚህም በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስን አንብቦ የመጨረስ ግብ እንዲያወጣ ሐሳብ አቅርብለት። አዘውትሮ መጽሐፍ ቅዱስን የማንበብ ልማድ እንዲያዳብር ከረዳኸው፣ ይህ ልማዱ ከተጠመቀ ከረጅም ጊዜ በኋላ እንኳ ይጠቅመዋል። ከዚህም ባሻገር ተማሪው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ከተሰኘው መጽሐፍ ውስጥ ከእያንዳንዱ ምዕራፍ ላይ ቁልፍ ለሆነ ጥያቄ መልስ የሚሰጥ ቢያንስ አንድ ጥቅስ በቃሉ የመያዝ ግብ እንዲኖረው ለምን አታበረታታውም? ይህም ‘የማያፍርና የእውነትን ቃል በትክክል የሚያስረዳ የተመሠከረለት ሠራተኛ’ እንዲሆን ያደርገዋል።—2 ጢሞቴዎስ 2:15
17 አንድ ተማሪ የተዘጋጀበትን ጥቅስ አስታውሶ እንዲናገር ወይም የጥቅሱን ሐሳብ በአጭሩ እንዲገልጽ ብቻ ከማድረግ ይልቅ ስለ እምነቱ ለሚጠይቁት መልስ መስጠት ቢያስፈልገው ጥቅሱ እየተወያያችሁበት ካለው ርዕሰ ጉዳይ ጋር ያለውን ዝምድና እንዲያብራራ አበረታታው። አንተ እንደ አንድ ዘመዱ ወይም የሥራ ባልደረባው ሆነህ ስለ እምነቱ እንዲያብራራልህ በመጠየቅ የምትለማመዱበት ፕሮግራም ቢኖር ጥሩ ነው። ተማሪው “በትሕትናና በአክብሮት” መልስ መስጠት የሚችለው እንዴት እንደሆነ አሳየው።—1 ጴጥሮስ 3:15
18. አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ያልተጠመቀ አስፋፊ ለመሆን ብቃቱን ሲያሟላ ምን ተጨማሪ እርዳታ ልታደርግለት ትችላለህ?
18 ከጊዜ በኋላ ተማሪው በመስክ አገልግሎት ለመሳተፍ ብቁ ሊሆን ይችላል። በዚህ ሥራ መካፈል ትልቅ መብት መሆኑን በአጽንኦት ንገረው። (2 ቆሮንቶስ 4:1, 7) ሽማግሌዎች ያልተጠመቀ አስፋፊ ለመሆን ብቃቱን እንደሚያሟላ ከወሰኑ ቀለል ያለ መግቢያ እንዲዘጋጅ እርዳው። ከዚያም አብረኸው አገልግል። አዘውትረህ በተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች አብረኸው ሥራ፤ እንዲሁም ውጤታማ ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግ እንዴት መዘጋጀት እንደሚችል አሳየው። በዚህ ረገድ የአንተ ጥሩ ምሳሌነት በጎ ተጽዕኖ ይኖረዋል።—ሉቃስ 6:40
‘ራስህንና የሚሰሙህን ታድናለህ’
19, 20. ምን ግብ ሊኖረን ይገባል? ለምንስ?
19 አንድ ሰው “እውነትን ወደ ማወቅ” እንዲደርስ መርዳት ከፍተኛ ጥረት እንደሚጠይቅ ግልጽ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 2:4) ይሁንና ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት እንዲታዘዙ መርዳት ይህ ነው የማይባል ደስታ ያስገኛል። (1 ተሰሎንቄ 2:19, 20) ዓለም አቀፍ በሆነው በዚህ የማስተማር ሥራ ‘ከአምላክ ጋር አብረን የምንሠራ’ መሆናችን እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው!—1 ቆሮንቶስ 3:9
20 በቅርቡ ይሖዋ በኢየሱስ ክርስቶስና በኃያላን መላእክቱ አማካኝነት ‘አምላክን በማያውቁትና ለጌታችንም ለኢየሱስ ወንጌል በማይታዘዙት’ ላይ ፍርዱን ያስፈጽማል። (2 ተሰሎንቄ 1:6-8) የሰዎች ሕይወት በአደጋ ላይ ነው። ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ የምታስጠናው ቢያንስ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማግኘት ለምን ግብ አታወጣም? በዚህ ሥራ ላይ መካፈልህ ‘ራስህንና የሚሰሙህን ለማዳን’ የሚያስችል አጋጣሚ ያስገኝልሃል። (1 ጢሞቴዎስ 4:16) በዛሬው ጊዜ፣ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውን እንዲታዘዙ ሰዎችን መርዳት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ እጅግ አጣዳፊ ነው።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።
ምን ትምህርት አግኝተሃል?
• የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለው መጽሐፍ የተዘጋጀበት ዓላማ ምንድን ነው?
• የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለውን መጽሐፍ ተጠቅመህ ጥናት ማስጀመር የምትችለው እንዴት ነው?
• ይበልጥ ውጤታማ የሆኑት የማስተማሪያ ዘዴዎች የትኞቹ ናቸው?
• አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ የአምላክ ቃል አስተማሪ እንዲሆን እንዴት ልትረዳው ትችላለህ?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይህን መጽሐፍ በጥሩ ሁኔታ እየተጠቀምክበት ነው?
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አጠር ያለ ውይይት አንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱስን የማወቅ ፍላጎት እንዲያድርበት ሊያደርግ ይችላል
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ተማሪው ትኩረቱን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንዲያደርግ እንዴት ልትረዳው ትችላለህ?
[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪው እድገት እንዲያደርግ እርዳው