በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሳሙኤል እውነተኛውን አምልኮ አስፋፍቷል

ሳሙኤል እውነተኛውን አምልኮ አስፋፍቷል

ሳሙኤል እውነተኛውን አምልኮ አስፋፍቷል

ነቢዩ ሳሙኤል ሰብዓዊ ንጉሥ እንዲያነግሥላቸው የጠየቁትን ባልንጀሮቹን የገሠጻቸው ሲሆን አምላክን እንዲታዘዙም አሳሰባቸው። ሳሙኤል ከአምላክ ሥልጣን እንደተሰጠው ለሕዝቡ ለማረጋገጥ ሲል ነጎድጓድና ዝናብ በመላክ ምልክት እንዲያሳይ ይሖዋን ለመነ። በእስራኤል የስንዴ መከር ወቅት ኃይለኛ ዝናብ መዝነቡ እምብዛም የተለመደ አልነበረም። ያም ሆኖ አምላክ ነጎድጓድና ዝናብ ላከ። በዚህም ምክንያት ሕዝቡ ይሖዋንም ሆነ ወኪሉን ሳሙኤልን እጅግ ፈሩ።—1 ሳሙኤል 12:11-19

ነቢዩ ሳሙኤል ጸሐፊም ነበር። ሳሙኤል በጽሑፍ ያሰፈረው አስደናቂ ዘገባ የ330 ዓመታት ገደማ ታሪክ የሚሸፍን ሲሆን የእስራኤል መሳፍንት ያከናወኗቸውን ታላላቅ ሥራዎችም ይዟል። ለምሳሌ ያህል፣ በምድር ከኖሩት ሰዎች ሁሉ በጥንካሬው ተወዳዳሪ ስላልተገኘለት ስለ ሳምሶን የሚተርከው እውነተኛ የሕይወት ታሪክ ለብዙ ግጥሞች፣ ሙዚቃዊ ተውኔቶች፣ እንዲሁም ለመድረክና ለፊልም ሥራዎች መነሻ ሐሳብ በመሆን አገልግሏል። (መሳፍንት ምዕራፍ 13-16) ከዚህም በተጨማሪ ሳሙኤል ችግረኛ ስለነበሩት መበለቶች ማለትም ስለ ሩትና ስለ አማቷ ኑኃሚን ጽፏል። አስደሳች መደምደሚያ ያለው ይህ እውነተኛ ታሪክም ቢሆን ልብ የሚማርክ ነው።—ሩት ምዕራፍ 1-4

ከሳሙኤል የሕይወት ታሪክና ከጻፋቸው ነገሮች ምን እንማራለን? እውነተኛውን አምልኮ ያስፋፋውስ እንዴት ነው?

የልጅነት ጊዜው

የሳሙኤል አባት ሕልቃና ይሖዋን የሚያመልክ አፍቃሪ ባል ነበር። የሕልቃና ሚስት ሐናም ብትሆን በመንፈሳዊ ጠንካራ ሴት ነበረች። በአንድ ወቅት፣ መካን የነበረችው ሐና ሴሎ በሚገኘው የይሖዋ ቤት ሳለች ከልብ የመነጨ ጸሎት በማቅረብ እንዲህ ስትል ተሳለች:- “የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ የአገልጋይህን መዋረድ ተመልክተህ ብታስበኝና አገልጋይህን ሳትረሳት ወንድ ልጅ ብትሰጣት፣ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ለእግዚአብሔር እሰጠዋለሁ፤ ምላጭም በራሱ ላይ አይደርስም።” (1 ሳሙኤል 1:1-11) ይህም ማለት የሚወለደው ልጅ ለይሖዋ አገልግሎት የተወሰነ ይሆናል።

ዘገባው ሐና በልቧ ትጸልይ ስለነበር “ከንፈሯ ይንቀሳቀስ እንጂ” ድምጿ አይሰማም ነበር በማለት ይገልጻል። በመሆኑም ሊቀ ካህኑ ዔሊ የሰከረች ስለመሰለው ገሠጻት። ሐና ግን ያለችበትን ሁኔታ በአክብሮት ገለጸችለት። በዚህ ጊዜ ዔሊ “በሰላም ሂጂ፤ የእስራኤል አምላክ የለመንሺውን ይስጥሽ” አላት። ዘገባው በመቀጠል ይሖዋ የሐናን ልመና እንደሰማ ሲገልጽ እንዲህ ይላል:- “ሐና ፀነሰች፤ የእርግዝናዋ ወራት በተፈጸመ ጊዜም ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙንም፤ ‘ከእግዚአብሔር ለምኜዋለሁ’ ስትል ሳሙኤል አለችው።”—1 ሳሙኤል 1:12-20

ሳሙኤል ያደገው “በጌታ ምክርና ተግሣጽ” ተኮትኩቶ ነው። (ኤፌሶን 6:4) ጡት በጣለ ጊዜ ሐና ሴሎ ወደሚገኘው የይሖዋ ቤት አምጥታ በሊቀ ካህኑ በዔሊ ፊት አቀረበችው። ብላቴናው በዔሊ ሥር ሆኖ ‘የይሖዋ አገልጋይ’ ሆነ። ሐና የተሰማትን ከፍተኛ ደስታ ልብ በሚነኩ የምስጋና ቃላት የገለጸች ሲሆን በኋላ ላይ ሳሙኤል እነዚህን ቃላት በጽሑፍ አስፍሯቸዋል።—1 ሳሙኤል 2:1-11

ወላጅ ከሆንክ ልጆችህ ይሖዋን ማገልገልን የሙሉ ጊዜ ሥራቸው እንዲያደርጉት ታበረታታቸዋለህ? አንድ ሰው እውነተኛውን አምልኮ ከማስፋፋት በተሻለ ኃይሉን ሊጠቀምበት የሚችል መስክ የለም።

ሳሙኤል በቤተ መቅደስ ካለው ሕይወት ጋር ራሱን አላምዷል። በመሆኑም ‘በይሖዋ ፊት እያደገና በአምላክም ሆነ በሰው ፊት ሞገስ እያገኘ ሄደ።’ በዚህ ጊዜም በሌሎች ዘንድ ተወዳጅ እንዲሆን ያደረጉትን አምላካዊ ባሕርያት ለማፍራት ችሏል።—1 ሳሙኤል 2:21, 26

ምናምንቴዎች የተባሉት የዔሊ ልጆች አፍኒን እና ፊንሐስ ግን ሁኔታቸው ከዚህ ፈጽሞ የተለየ ነው። የዔሊ ልጆች ‘ይሖዋን አይፈሩም ነበር።’ እንዲያውም የጾታ ብልግና ይፈጽሙና ሕዝቡ ወደ ቤተ መቅደስ ከሚያመጣው መሥዋዕት ላይ ምርጥ የሆነውን ለራሳቸው ይወስዱ ነበር። አምላክ፣ ዔሊ የሚደርስበትን ቅጣት እንዲነግረው ነቢይ ልኮበት ነበር። ይህ መልእክት የሁለት ልጆቹን ሞት ይጨምራል። (1 ሳሙኤል 2:12, 15-17, 22-25, 27, 30-34) ይሖዋ ሌላ የፍርድ መልእክት እንዲያስተላልፍ ሳሙኤልን ይጠቀማል።

ሳሙኤል ነቢይ ሆኖ አገለገለ

አምላክ ለሳሙኤል እንዲህ ብሎታል:- “ዔሊ በሚያውቀው ኀጢአት ምክንያት በቤተ ሰቡ ላይ ለዘላለም እንደምፈርድ ነግሬው ነበር፤ ልጆቹ አስጸያፊ ነገር አድርገዋል፤ እርሱ ግን አልከለከላቸውም።” ይህን መልእክት ማስተላለፍ ቀላል አልነበረም። ዔሊ ደግሞ አንዳች ሳይደብቅ እንዲነግረው ሳሙኤልን ወተወተው። ስለዚህ ሳሙኤል ይሖዋ ያለውን ሁሉ አንድ በአንድ ነገረው። እንዲህ ማድረግ ድፍረት ይጠይቅ ነበር!—1 ሳሙኤል 3:10-18

ሳሙኤል እያደገ ሲሄድ መላው እስራኤል እርሱ የአምላክ ነቢይ መሆኑን አወቀ። (1 ሳሙኤል 3:19, 20) ሳሙኤል የተናገረው የፍርድ መልእክት መፈጸም የጀመረው እስራኤላውያን በፍልስጥኤማውያን አሳፋሪ ሽንፈት በገጠማቸው ጊዜ ነበር። አፍኒን እና ፊንሐስ በውጊያው ላይ የሞቱ ሲሆን የይሖዋ የቃል ኪዳን ታቦትም በፍልስጥኤማውያን ተማረከ። ዔሊ ልጆቹ እንደሞቱና ታቦቱ እንደተማረከ ሲሰማ ከተቀመጠበት ወንበር ላይ በጀርባው ወደቀ፤ በዚህም ሳቢያ አንገቱ ተሰብሮ ሞተ።—1 ሳሙኤል 4:1-18

ሃያ ዓመታት ካለፉ በኋላ ሳሙኤል እስራኤላውያን የሐሰት አምልኮን እንዲያስወግዱ አሳሰባቸው። እነርሱም ጣዖቶቻቸውን በማስወገድ፣ በመጾምና ኃጢአታቸውን በመናዘዝ ለማሳሰቢያው ምላሽ ሰጡ። ሳሙኤልም እነርሱን ወክሎ ጸሎትና የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረበ። ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? ፍልስጥኤማውያን ሊወጓቸው በመጡ ጊዜ አምላክ አሸበራቸው፤ እስራኤላውያንም ጠላቶቻቸውን መልሰው በማጥቃት ድል ማድረግ ቻሉ። በይሖዋ እርዳታ የእስራኤል ሁኔታ ከፍተኛ መሻሻል ያሳየ ከመሆኑም በላይ ፍልስጥኤማውያን የወሰዷቸውን ከተሞችም አስመለሱ።—1 ሳሙኤል 7:3-14

በእርግጥም ሳሙኤል እውነተኛውን አምልኮ አስፋፍቷል። ለምሳሌ ያህል፣ ከጦርነት ከተገኘው ምርኮ የተወሰነው ለመገናኛ ድንኳኑ እድሳት እንዲውል አድርጓል። የማለፍ በዓልንና የሌዋውያን በር ጠባቂዎችን ሥራ በማደራጀት አስተዋጽኦ አበርክቷል። (1 ዜና መዋዕል 9:22፤ 26:27, 28፤ 2 ዜና መዋዕል 35:18) ሳሙኤል አርማቴም ከሚገኘው ቤቱ ተነስቶ በየዓመቱ ወደተለያዩ ከተሞች በመሄድ በእስራኤል ላይ ይፈርድ የነበረ ሲሆን ሐቀኛና የማያዳላ መሆኑም ተመሥክሮለታል። ሰዎች ያከብሩት ስለነበረ መንፈሳዊ እርዳታ ሊያደረግላቸው ችሏል። (1 ሳሙኤል 7:15-17፤ 9:6-14፤ 12:2-5) ሐቀኛና መንፈሳዊ ሰው መሆኑ ብዙዎች የእርሱን ምሳሌ እንዲኮርጁ እንዳነሳሳቸው አያጠራጥርም። የሳሙኤል የሕይወት ታሪክ ተመሳሳይ እርምጃ እንድትወስድ አነሳስቶሃል?

እስራኤላውያን ንጉሥ እንዲነግሥላቸው ጠየቁ

ሳሙኤል በሸመገለ ጊዜ ኢዮኤልና አብያ የተባሉትን ልጆቹን ፈራጅ አድርጎ ሾማቸው። እነርሱ ግን “የአባታቸውን ፈለግ አልተከተሉም፤ ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት ሲሉ ከመንገዱ ወጡ፤ ጒቦ ተቀበሉ፤ ፍርድም አጣመሙ።” ይህ ድርጊታቸው የእስራኤል ሽማግሌዎች ንጉሥ እንዲነግሥላቸው እንዲጠይቁ አነሳሳቸው። (1 ሳሙኤል 8:1-5) ይሁንና ሳሙኤል በዚህ ጥያቄያቸው አልተደሰተም። ስለ ጉዳዩ በጸለየ ጊዜ ግን ይሖዋ “ንጉሣቸው እንዳልሆን የናቁት እኔን እንጂ አንተን አይደለም” አለው። (1 ሳሙኤል 8:6, 7) አምላክ ሳሙኤልን ምኞታቸውን እንዲያሟላላቸውና በንጉሣዊ አገዛዝ ሥር መሆናቸው በተወሰነ መጠን ነፃነት እንደሚያሳጣቸው በመንገር እንዲያስጠነቅቃቸው አዘዘው። ሕዝቡ እምቢ ባለ ጊዜ፣ ሳሙኤል ሳኦልን ለንጉሥነት እንዲቀባው ይሖዋ ዝግጅት አደረገ።—1 ሳሙኤል 8:6-22፤ 9:15-17፤ 10:1

ሳሙኤል ቅር የተሰኘ ቢሆንም እንኳ ዝግጅቱን ደግፏል። እስራኤላውያን በአሞናውያን ላይ ድል ከተቀዳጁ በኋላ ሳኦል ንጉሥ ሆኖ መቀባቱን ለማስታወቅ ሕዝቡን በጌልገላ ሰበሰበ። (1 ሳሙኤል 10:17-24፤ 11:11-15) ከዚያም ሳሙኤል የእስራኤልን ታሪክ በአጭሩ ከተረከላቸው በኋላ ንጉሡም ሆነ ሕዝቡ ይሖዋን መታዘዝ እንዳለባቸው አሳሰበ። በመግቢያችን ላይ እንደተጠቀሰው አምላክ ወቅቱ ባይሆንም እንኳ ነጎድጓድና ዝናብ በመላክ ለሳሙኤል ጸሎት ምላሽ ሰጠ። የጣለው ኃይለኛ ዝናብ ሕዝቡ ይሖዋን አለመፈለጋቸው ስህተት መሆኑን እንዲያምኑ አድርጓቸዋል። ሕዝቡ ሳሙኤልን እንዲጸልይላቸው በጠየቁት ጊዜ “እኔ ለእናንተ ከመጸለይ ወደ ኋላ በማለት እግዚአብሔርን መበደል ከእኔ ይራቅ፤ እኔ መልካምና ቅን የሆነውን መንገድ አስተምራችኋለሁ” ሲል መለሰላቸው። ለይሖዋም ሆነ ለሕዝቡ ጽኑ ፍቅር በማሳየት ረገድ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው! (1 ሳሙኤል 12:6-24) አንተስ ቲኦክራሲያዊ ዝግጅቶችን በመደገፍና የእምነት ባልንጀሮችህን ወክለህ በመጸለይ ረገድ ይህን የመሰለ የፈቃደኝነት መንፈስ ታሳያለህ?

የመጀመሪያዎቹ ሁለት የእስራኤል ነገሥታት

ሳኦል የይሖዋን ሞገስ ያገኘ ትሑት ሰው ነበር። (1 ሳሙኤል 9:21፤ 11:6) ይሁንና ከጊዜ በኋላ መለኮታዊ መመሪያዎችን ችላ ማለት ጀመረ። ለምሳሌ ያህል፣ ሳኦል እንደታዘዘው በትዕግሥት በመጠበቅ ፈንታ ተቻኩሎ መሥዋዕት ስላቀረበ ሳሙኤል ገሥጾታል። (1 ሳሙኤል 13:10-14) አማሌቃዊውን ንጉሥ አጋግን በታዘዘው መሠረት ሳይገድለው በቀረ ጊዜ ሳሙኤል እንዲህ ብሎታል:- “እግዚአብሔር የእስራኤልን መንግሥት ዛሬ ከአንተ ቀዶታል፤ ከአንተም ለሚሻል ለጎረቤትህ አሳልፎ ሰጥቶታል።” ሳሙኤል ራሱ አጋግን የገደለው ሲሆን ለሳኦልም አለቀሰለት።—1 ሳሙኤል 15:1-35

በመጨረሻም ይሖዋ ለሳሙኤል “በእስራኤል ላይ እንዳይነግሥ ለናቅሁት ለሳኦል የምታለቅስለት እስከ መቼ ነው?” ሲል ተናገረው። ከዚያም የእሴይን ልጅ ለንግሥና እንዲቀባ ወደ ቤተልሔም ላከው። ይሖዋ ለንግሥና የመረጠው የእሴይን የመጨረሻ ልጅ ዳዊትን መሆኑን እስኪያሳውቀው ድረስ ሳሙኤል ሌሎቹን ልጆች አንድ በአንድ ተመለከታቸው። ሳሙኤል በዚያን ዕለት አንድ ጠቃሚ ትምህርት አግኝቷል:- “እግዚአብሔር የሚያየው፣ ሰው እንደሚያየው አይደለም። ሰው የውጭውን ገጽታ ያያል፤ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል።”—1 ሳሙኤል 16:1-13

ሳሙኤል ሳኦል ታዛዥ ባለመሆኑ በጣም ካዘነ፣ በጥላቻ ተነሳስቶ ዳዊትን ለመግደል ማሴሩን ሲመለከት ደግሞ ምንኛ አዝኖ ይሆን? ሳሙኤል እነዚህን የመሳሰሉ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙትም በሽምግልና ዕድሜው በይሖዋ አገልግሎት የተቻለውን ያህል በንቃት ተካፍሏል።—1 ሳሙኤል 19:18-20

ሳሙኤል የተወልን ውርስ

ሳሙኤል በሞተ ጊዜ፣ እስራኤላውያን በብዙዎች ሕይወት ላይ በጎ ተጽዕኖ ላሳደረው ለዚህ ትሑትና ደፋር ነቢይ አልቅሰውለታል። (1 ሳሙኤል 25:1) ሳሙኤል ፍጹም ሰው አልነበረም፤ እንዲያውም የተሳሳተባቸው ጊዜያትም ነበሩ። ድክመቶች የነበሩበት ቢሆንም ይሖዋን ብቻ አምልኳል፤ እንዲሁም ሌሎችም እንዲህ እንዲያደርጉ ለመርዳት ያለመታከት ጥሯል።

ከሳሙኤል ዘመን ወዲህ ብዙ ነገሮች የተለዋወጡ ቢሆንም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሰፈረው የሕይወት ታሪኩ ግን ጠቃሚ ትምህርት ይዞልናል። ከሁሉም በላይ ሳሙኤል እውነተኛውን የይሖዋን አምልኮ ተከትሏል እንዲሁም አስፋፍቷል። አንተስ እንዲህ እያደረግህ ነው?

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

በሳሙኤል የሕይወት ታሪክ ላይ አሰላስል

• የሳሙኤል ወላጆች የአምላክን ቃል እንዳስተማሩት ሁሉ አንተም ልጆችህን “በጌታ ምክርና ተግሣጽ” አሳድጋቸው።—ኤፌሶን 6:4

• ልጆችህ ይሖዋን ማገልገልን የሙሉ ጊዜ ሥራቸው በማድረግ የሳሙኤልን ምሳሌ እንዲከተሉ አበረታታቸው።

• ሳሙኤል ያፈራቸው አምላካዊ ባሕርያት በሌሎች ዘንድ ተወዳጅ እንዲሆን አድርገውታል፤ ይህም ልንከተለው የሚገባ ጥሩ ምሳሌ ነው።

• ሳሙኤል እውነተኛውን አምልኮ ለማስፋፋት የተቻለውን ሁሉ አድርጓል፤ እኛም እንዲሁ ልናደርግ ይገባል።

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሳሙኤል እውነተኛውን አምልኮ ያስፋፋ ሲሆን ሌሎችን በመንፈሳዊ ለመርዳትም ፈቃደኛ ነበር