ወንድና ሴት—እያንዳንዳቸው ያላቸው የተከበረ ቦታ
ወንድና ሴት—እያንዳንዳቸው ያላቸው የተከበረ ቦታ
ይሖዋ አምላክ መጀመሪያ አዳምን ከዚያም ሔዋንን ፈጠረ። አዳም ሔዋን ከመፈጠሯ በፊት የተወሰነ የሕይወት ተሞክሮ አግኝቷል። በዚህ ጊዜ ውስጥ አዳም ከይሖዋ አንዳንድ መመሪያዎችን ተቀብሏል። (ዘፍጥረት 2:15-20) አዳም የአምላክ ቃል አቀባይ በመሆን መመሪያዎቹን ለሚስቱ ማስተላለፍ ነበረበት። ከሁኔታው ለመረዳት እንደሚቻለው አዳም አምልኮን በሚመለከቱ ጉዳዮች ሁሉ ቀዳሚ መሆን ይገባው ነበር።
በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ዝግጅት ስለሚገኝ ይህን መመርመራችን ይጠቅመናል። ሐዋርያው ጳውሎስ “ሴት ዝም እንድትል እንጂ . . . በወንድ ላይ ሥልጣን እንዲኖራት አልፈቅድም። ምክንያቱም አዳም ቀድሞ ተፈጥሮአል፤ ከዚያም ሔዋን ተፈጠረች” በማለት ጽፏል። (1 ጢሞቴዎስ 2:12, 13) ዝም ትበል ሲባል ግን አንዲት ሴት በጉባኤ ስብስባዎች ላይ ምንም ነገር መናገር የለባትም ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ከወንዶች ጋር ሙግት ከመግጠም፣ ሹመታቸውን አቃልላ ከመመልከት ወይም ጉባኤውን ለማስተማር ከመሞከር መቆጠብ ይኖርባታል ማለት ነው። ጉባኤውን በበላይነት የመምራትና የማስተማር ኃላፊነት የተሰጠው ለወንዶች ነው። ያም ሆኖ ሴቶች በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ በተለያየ መንገድ ተሳትፎ በማድረግ ጠቃሚ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ።
ሐዋርያው ጳውሎስ ወንዶችና ሴቶች በአምላክ ዝግጅት ውስጥ ያላቸውን ቦታ አስመልክቶ እንደሚከተለው ሲል ያሰፈረው ሐሳብ ግንዛቤያችንን ይበልጥ ያሰፋልናል:- “ሴት ከወንድ ተገኘች እንጂ ወንድ ከሴት አልተገኘም። . . . በጌታ ዘንድ ግን ሴት ያለ ወንድ፣ ወንድም ያለ ሴት [አንዱ ያለ ሌላው] አይሆንም። ሴት ከወንድ እንደ ተገኘች ሁሉ፣ ወንድም ከሴት ይወለዳልና፤ ነገር ግን የሁሉም መገኛ እግዚአብሔር ነው።”—1 ቆሮንቶስ 11:8-12
ሴቶች ግሩም መብቶች አሏቸው
አምላክ ለእስራኤላውያን የሰጣቸው ሕግ ለሴቶች ብዙ መብቶችን ይሰጥ የነበረ ሲሆን አንዳንድ ነገሮችን በራሳቸው ተነሳሽነት እንዲያከናውኑም ይፈቅድላቸው ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ምሳሌ 31:10-31 ምርጥ ጨርቅ በመግዛት ለቤተሰቧ ጥራት ያለው ልብስ ስለምትሠራ ‘ጠባየ መልካም [“ልባም፣” የ1954 ትርጉም] ሚስት’ ይናገራል። እንዲያውም “የበፍታ መጐናጸፊያዎችን ሠርታ ትሸጣለች”! (ቁጥር 13, 21-24) ይህች ልባም ሴት ልክ “እንደ ንግድ መርከብ” ሩቅ ቦታ መሄድ ቢጠይቅባትም እንኳ ጥሩ ምግብ ሸምታ ታመጣለች። (ቁጥር 14) “ራሷ አስባ የዕርሻ መሬት ትገዛለች”፤ እንዲሁም “ወይን ትተክላለች።” (ቁጥር 16) ‘ንግድዋ መልካም ስለሆነ’ ሥራዋ አትራፊ ነው። (ቁጥር 18 የ1954 ትርጉም) ይህች ይሖዋን የምትፈራ ታታሪ ሴት ‘የቤተ ሰዎቿን ጕዳይ በትጋት ከመከታተሏም’ በተጨማሪ ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ ስሜት ሌሎችን ትረዳለች። (ቁጥር 20, 27) ታዲያ ሌሎች ቢያመሰግኗት ምን ያስደንቃል!—ቁጥር 31
ይሖዋ በሙሴ በኩል የሰጠው ሕግ ሴቶች በመንፈሳዊ እንዲያድጉ ብዙ አጋጣሚዎችን ይከፍትላቸው ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ በኢያሱ 8:35 ላይ እንዲህ የሚል እናነባለን:- “ኢያሱ በመላው የእስራኤል ጉባኤ ፊት ሴቶች፣ ሕፃናትና በመካከላቸው የኖሩ መጻተኞች ባሉበት ያነበበው፣ አንድም ሳይቀር ሙሴ ያዘዘውን ቃል ሙሉ በሙሉ ነበር።” ካህኑን ዕዝራን በተመለከተም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚከተለው ይላል:- “ዕዝራ በሰባተኛው ወር የመጀመሪያ ቀን ወንዶች፣ ሴቶችና ማስተዋል የሚችሉ ሁሉ በተገኙበት ጉባኤ ፊት የሕጉን መጽሐፍ አመጣ። እርሱም በ‘ውሃው በር’ ትይዩ ወደሚገኘው አደባባይ ፊቱን አቅንቶ፣ በወንዶች፣ በሴቶችና በሚያስተውሉ ሰዎች ሁሉ ፊት በመቆም፣ ከማለዳ ጀምሮ እስከ ቀትር ድረስ ድምፁን ከፍ አድርጎ አነበበ፤ ሕዝቡም ሁሉ የሕጉን መጽሐፍ በጥሞና አደመጡ።” (ነህምያ 8:2, 3) ሴቶች ከሚነበበው ሕግ ተጠቃሚዎች ሆነዋል። ከዚህም በተጨማሪ ሃይማኖታዊ በዓላትን ያከብሩ ነበር። (ዘዳግም 12:12, 18፤ 16:11, 14) ከሁሉም በላይ ደግሞ በጥንቷ እስራኤል የነበሩ ሴቶች ከይሖዋ አምላክ ጋር የግል ዝምድና መመሥረትና ወደ እርሱ መጸለይ ይችሉ ነበር።—1 ሳሙኤል 1:10
በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ሴቶች ኢየሱስን የማገልገል መብት አግኝተው ነበር። (ሉቃስ 8:1-3) ኢየሱስ ቢታንያ በተባለች ከተማ በማዕድ ላይ ተቀምጦ ሳለ አንዲት ሴት እግሩንና ራሱን በሽቶ አብሳዋለች። (ማቴዎስ 26:6-13፤ ዮሐንስ 12:1-7) ኢየሱስ ከትንሣኤው በኋላ ከተገለጠላቸው ሰዎች መሃል ሴቶችም ይገኙበታል። (ማቴዎስ 28:1-10፤ ዮሐንስ 20:1-18) ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ አንድ ላይ ይሰበሰቡ ከነበሩት 120 ሰዎች መካከል አንዳንድ ‘ሴቶችና የኢየሱስ እናት ማርያም’ ይገኙበታል። (የሐዋርያት ሥራ 1:3-15) ከእነዚህ ሴቶች ውስጥ ብዙዎቹ ምናልባትም ሁሉም በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት፣ በኢየሩሳሌም በሚገኝ አንድ ቤት ሰገነት ላይ ከተሰበሰቡት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት መሃል እንደነበሩ ምንም አያጠራጥርም። በዚህ ዕለት ደቀ መዛሙርቱ መንፈስ ቅዱስ ተቀብለው በልዩ ልዩ ቋንቋዎች በተአምር ተናግረዋል።—የሐዋርያት ሥራ 2:1-12
በኢዩኤል 2:28, 29 ላይ የሰፈረው ትንቢት በጰንጠቆስጤ ዕለት ተሰብስበው በነበሩት ወንዶችና ሴቶች ላይ ፍጻሜውን አግኝቷል። ሐዋርያው ጴጥሮስ ይህን ትንቢት ጠቅሶ እንዲህ ብሏል:- “[እኔ ይሖዋ] መንፈሴን በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ አፈሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁ ትንቢት ይናገራሉ፤ . . . በዚያ ጊዜ በወንዶችና በሴቶች አገልጋዮቼ ላይ፣ መንፈሴን አፈሳለሁ፤ እነርሱም ትንቢት ይናገራሉ።” (የሐዋርያት ሥራ 2:13-18) ክርስቲያን ሴቶች ከ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ለተወሰነ ጊዜ ያህል የቀጠለ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ነበራቸው። በልሳን ከመናገራቸውም በተጨማሪ ትንቢት ተንብየዋል፤ ይህም ስለወደፊቱ ጊዜ አዲስ ነገር ተናግረዋል ማለት ላይሆን ይችላል፤ ከዚህ ይልቅ የቅዱሳን መጻሕፍትን እውነት ማወጃቸውን ያመለክታል።
ሮሜ 16:1, 2, 12) እነዚህ ሴቶች በጥንቱ የክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የበላይ ተመልካቾች ወይም አገልጋዮች ሆነው ባይሾሙም እንኳ አምላክ እነርሱንም ሆነ ሌሎች ሴቶችን ከልጁ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በሰማያዊው መንግሥት እንዲገዙ ስለመረጣቸው ተባርከዋል።—ሮሜ 8:16, 17፤ ገላትያ 3:28, 29
ሐዋርያው ጳውሎስ ለሮም ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ‘ፌቤን የተባለችውን እህት’ በበጎ አንስቷታል። በተጨማሪም ፕሮፊሞናንና ጢሮፊሞሳን ‘በጌታ ሆነው በትጋት የሚሠሩ ሴቶች’ በማለት ጠርቷቸዋል። (በዛሬው ጊዜም ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ሴቶች እጅግ ታላቅ መብት አግኝተዋል! መዝሙር 68:11 (የ1980 ትርጉም) “እግዚአብሔር ትእዛዝ ሰጠ፤ ብዙ ሴቶችም ዜናውን አሰራጩ” ይላል። እነዚህ ሴቶች ምስጋና ሊቸራቸው ይገባል። ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስን በማስተማር ችሎታቸው ብዙ ሰዎች አምላክ የሚደሰትበትን እውነተኛ ትምህርት እንዲቀበሉ ረድተዋል። ከዚህም በተጨማሪ ልጆቻቸው አማኞች እንዲሆኑ የሚረዱና በጉባኤ ውስጥ ብዙ ኃላፊነት የተሸከሙትን ባሎቻቸውን የሚደግፉ ክርስቲያን ሴቶች ሊመሰገኑ ይገባል። (ምሳሌ 31:10-12, 28) ያላገቡ ሴቶችም በአምላክ ዝግጅት ውስጥ የተከበረ ቦታ አላቸው። ክርስቲያን ወንዶች “አሮጊቶችን እንደ እናቶች፣ ወጣት ሴቶችን ደግሞ እንደ እኅቶች በፍጹም ንጽሕና” እንዲይዟቸው ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል።—1 ጢሞቴዎስ 5:1, 2
ወንዶች ያሏቸው የተለያዩ ኃላፊነቶች
ክርስቲያን ወንዶች ከአምላክ ኃላፊነት የተሰጣቸው ሲሆን ይህን ኃላፊነታቸውንም በአግባቡ እንዲወጡ ይጠበቅባቸዋል። ጳውሎስ “ነገር ግን ይህን እንድታውቁ እወዳለሁ፤ የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ ነው፤ የሴትም ራስ ወንድ ነው፤ የክርስቶስም ራስ እግዚአብሔር ነው” ብሏል። (1 ቆሮንቶስ 11:3) በመሆኑም ወንድ ራስ አለው፤ እርሱም ክርስቶስ ነው። በእርግጥም ወንድ በክርስቶስ ብሎም በአምላክ ዘንድ ተጠያቂ ነው። አምላክ፣ ወንድ ያለውን የራስነት ሥልጣን በፍቅር እንዲጠቀምበት ይፈልጋል። (ኤፌሶን 5:25) የሰው ልጆች ከተፈጠሩበት ጊዜ አንስቶ የአምላክ ዓላማ ይኸው ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ፣ ለወንድ ከራስነት ሥልጣኑ ጋር የሚስማማ ኃላፊነት እንደሰጠው ይገልጻል። ለምሳሌ ይሖዋ፣ ኖኅ በውኃ ጥፋት ጊዜ ሕይወት ለማዳን የሚያገለግል መርከብ እንዲሠራ አድርጓል። (ዘፍጥረት 6:9 እስከ 7:24) አብርሃም ሁሉም የምድር ቤተሰቦችና ሕዝቦች በእርሱ ዘር አማካኝነት ራሳቸውን እንደሚባርኩ ቃል ተገብቶለታል። ዋነኛው የዘሩ ክፍል ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። (ዘፍጥረት 12:3፤ 22:18፤ ገላትያ 3:8-16) አምላክ፣ እስራኤላውያንን ከግብጽ እየመራ እንዲያወጣ ሙሴን ሾሞታል። (ዘፀአት 3:9, 10, 12, 18) ይሖዋ የሕጉን ቃል ኪዳን ወይም የሙሴን ሕግ የሰጠው በሙሴ በኩል ነበር። (ዘፀአት 24:1-18) ሁሉም የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ወንዶች ናቸው።
ኢየሱስ የክርስቲያን ጉባኤ ራስ እንደመሆኑ መጠን “ስጦታ የሆኑ ወንዶችን” ሾሟል። (ኤፌሶን 1:22፤ 4:7-13 NW) ጳውሎስ የበላይ ተመልካች ለመሆን የሚያስፈልጉትን ብቃቶች የዘረዘረው ለወንዶች ነው። (1 ጢሞቴዎስ 3:1-7፤ ቲቶ 1:5-9) በመሆኑም በይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ውስጥ የበላይ ተመልካቾች ማለትም ሽማግሌዎች እንዲሁም የጉባኤ አገልጋዮች በመሆን የሚያገለግሉት ወንዶች ናቸው። (ፊልጵስዩስ 1:1, 2፤ 1 ጢሞቴዎስ 3:8-10, 12) በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ እረኞች ሆነው ማገልገል ያለባቸው ወንዶች ብቻ ናቸው። (1 ጴጥሮስ 5:1-4) ሆኖም ቀደም ብለን እንደተመለከትነው ሴቶች ከአምላክ ያገኟቸው ግሩም መብቶች አሏቸው።
ባላቸው ቦታ ደስተኞች ናቸው
ወንዶችም ሆኑ ሴቶች አምላክ የሰጣቸውን ኃላፊነት በሚገባ መወጣታቸው ደስታ ያስገኝላቸዋል። ባሎችና ሚስቶች የክርስቶስንና የጉባኤውን ምሳሌ መኮረጃቸው ትዳራቸው ደስታ የሰፈነበት እንዲሆን ያደርጋል። ጳውሎስ “ባሎች ሆይ፤ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳትና ራሱንም ስለ እርሷ አሳልፎ እንደ ሰጠ፣ እናንተም ሚስቶቻችሁን ውደዱ፤ . . . እያንዳንዱ ሚስቱን እንደ ራሱ አድርጎ ይውደድ” ሲል ጽፏል። (ኤፌሶን 5:25-33) በመሆኑም ባሎች የራስነት ሥልጣናቸውን በራስ ወዳድነት ሳይሆን በፍቅር ሊጠቀሙበት ይገባል። የክርስቶስ ጉባኤ የተገነባው ፍጹም በሆኑ ሰዎች አይደለም። ያም ሆኖ ኢየሱስ ጉባኤውን ይወደዋል እንዲሁም ይንከባከበዋል። በተመሳሳይም፣ አንድ ክርስቲያን ባል ሚስቱን ሊወዳትና ሊንከባከባት ይገባል።
ኤፌሶን 5:33) እርሷም በዚህ ረገድ የጉባኤውን ምሳሌነት መኮረጅ ትችላለች። ኤፌሶን 5:21-24 እንዲህ ይላል:- “ለክርስቶስ ካላችሁ አክብሮታዊ ፍርሀት የተነሣ አንዳችሁ ለአንዳችሁ ተገዙ። ሚስቶች ሆይ፤ ለጌታ እንደምትገዙ ለባሎቻችሁም ተገዙ ክርስቶስ፣ አካሉ ለሆነችውና አዳኟ ለሆናት ቤተ ክርስቲያን ራስ እንደ ሆነ ሁሉ፣ ባልም የሚስቱ ራስ ነውና። እንግዲህ ቤተ ክርስቲያን ለክርስቶስ እንደምትገዛ፣ ሚስቶችም ለባሎቻቸው በማንኛውም ነገር እንደዚሁ መገዛት ይገባቸዋል።” አንዲት ሚስት ለባሏ መገዛት አስቸጋሪ በሚሆንባት ጊዜም እንኳ ይህን ማድረጓ “በጌታ ዘንድ ተገቢ” ነው። (ቈላስይስ 3:18) ለባሏ መገዛቷ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን እንደሚያስደስተው ካስታወሰች ይህን ማድረግ ቀላል ይሆንላታል።
አንዲት ክርስቲያን ሚስት በጥልቅ ‘ባሏን ማክበር’ አለባት። (አንዲት ክርስቲያን ሚስት ባሏ አማኝ ባይሆንም እንኳ ለራስነት ሥልጣኑ ትገዛለች። ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ ብሏል:- “ሚስቶች ሆይ፤ . . . ለባሎቻችሁ ተገዙ፤ አንዳንድ ለቃሉ የማይታዘዙ ቢኖሩ፣ ያለ ቃል በሚስቶቻቸው አኗኗር ተማርከው ይመለሳሉ፤ ይህም የሚሆነው ንጹሕና ፍጹም አክብሮት የተሞላውን ኑሮአችሁን ሲመለከቱ ነው።” (1 ጴጥሮስ 3:1, 2) ባሏን አብርሃምን ታከብር የነበረችው ሣራ ይስሐቅን የመውለድና የኢየሱስ ክርስቶስ ቅድመ አያት የመሆን መብት አግኝታለች። (ዕብራውያን 11:11, 12፤ 1 ጴጥሮስ 3:5, 6) የሣራን ምሳሌ የሚከተሉ ሚስቶች አምላክ ወሮታውን እንደሚከፍላቸው እርግጠኞች መሆን ይችላሉ።
ወንዶችና ሴቶች አምላክ በሰጣቸው ቦታ ኃላፊነታቸውን በተገቢው መንገድ ሲወጡ ሰላምና ስምምነት ይሰፍናል። ይህ ደግሞ እርካታና ደስታ ያስገኝላቸዋል። ከዚህም በላይ እያንዳንዳቸው ከመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ጋር ተስማምተው መኖራቸው በአምላክ ዓላማ ውስጥ ያላቸው ከፍ ያለ ቦታ የሚያስገኘውን ክብር ያላብሳቸዋል።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አምላክ ስለሰጣቸው ቦታ ምን ይሰማቸዋል?
ሱዛን እንዲህ ትላለች:- “ባለቤቴ የራስነት ሥልጣኑን በፍቅርና በደግነት ይጠቀምበታል። ውሳኔ የሚጠይቅ ነገር ሲኖር ብዙውን ጊዜ እንወያያለን፤ ምን መደረግ እንዳለበትና እንደሌለበት ሲወስንም ለቤተሰባችን ጥቅም መሆኑ ይገባኛል። ይሖዋ ለክርስቲያን ሚስቶች የሰጠው ቦታ የሚያስደስተኝ ከመሆኑም ባሻገር ትዳራችንን አጠናክሮልናል። ከባለቤቴ ጋር በጣም እንቀራረባለን፤ መንፈሳዊ ግቦቻችን ላይ ለመድረስም አብረን እንሠራለን።”
ሚንዲ የተባለች ሴት ደግሞ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥታለች:- “ይሖዋ ለሴት አገልጋዮቹ የሰጠው ቦታ እንደሚወደን የሚያረጋግጥ ነው። ባለቤቴን ማክበርና የጉባኤ ኃላፊነቶቹን እንዲወጣ ድጋፍ መስጠት ለይሖዋ ዝግጅት ያለኝን አድናቆት የምገልጽበት መንገድ እንደሆነ ይሰማኛል።”
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ለወንድ ከተሰጠው የራስነት ሥልጣን ጋር በሚስማማ መልኩ አምላክ ለኖኅ፣ ለአብርሃምና ለሙሴ የተለያዩ ኃላፊነቶችን ሰጥቷቸዋል
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“ብዙ ሴቶችም ዜናውን አሰራጩ”