ዓላማ ያለው ሕይወት የሚመሩ የዕድሜ ባለጠጋ
ዓላማ ያለው ሕይወት የሚመሩ የዕድሜ ባለጠጋ
ኤሊን በቅርቡ ስዊድን ውስጥ 105 ዓመትና ከዚያ በላይ እንደሆናቸው ከተመዘገቡ 60 ሰዎች መካከል አንዷ ሲሆኑ እርሳቸውም 105 ዓመት ሞልቷቸዋል። እኚህ ሴት በአረጋውያን መንከባከቢያ ቤት ውስጥ የሚኖሩ ቢሆንም ጤንነታቸው ቀናተኛ የይሖዋ ምሥክር ሆነው እንዳያገለግሉ አላገዳቸውም። ኤሊን ይህን የሕይወት ጎዳና ለመከተል የመረጡት ከዛሬ 60 ዓመት በፊት ነበር።
ኤሊን ለሌሎች በመስበክ ረገድ ሐዋርያው ጳውሎስ የቁም እስረኛ ሆኖ ከቤት እንዳይወጣ በተደረገበት ጊዜ የተወውን ምሳሌ ኮርጀዋል። ጳውሎስ ሊጠይቁት ለመጡ ሁሉ ይሰብክ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 28:16, 30, 31) በተመሳሳይም ኤሊን ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ለጽዳት ሠራተኞች፣ ለጥርስ ሐኪሞች፣ ለዶክተሮች፣ ለፀጉር አስተካካዮች፣ ለነርሶችና እዚያ ለሚያገኟቸው ሌሎች ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ምሥራች ይናገራሉ። እንዲያውም አንዳንዴ በኤሊን ጉባኤ ውስጥ የሚገኙ ወንድሞችና እህቶች ከእርሳቸው እውቀትና ተሞክሮ እንዲጠቀሙ በማሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻቸውን ወደ አረጋውያን መንከባከቢያው ይዘዋቸው ይሄዳሉ።
በኤሊን ጉባኤ የሚገኙ ወንድሞችና እህቶች እኚህ ሴት ያላቸውን የደስተኝነት መንፈስና የማወቅ ጉጉት ያደንቃሉ። አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል:- “ኤሊን በጉባኤ ውስጥ የሚከናወኑ ነገሮችን የመከታተል ችሎታቸው ያስደንቃል። የሁሉንም ልጆች ስም ሌላው ቀርቶ በቅርቡ ወደ ጉባኤያችን የተዛወሩ ሰዎችን ስም እንኳ ያስታውሳሉ።” ከዚህም በተጨማሪ እኚህ እህት በእንግዳ ተቀባይነታቸው፣ በተጫዋችነታቸውና ለሕይወት ባላቸው አዎንታዊ አመለካከት ይታወቃሉ።
ኤሊን ደስተኛ ሆነው እንዲኖሩና ዓላማቸውን ሳይዘነጉ እንዲመላለሱ የረዳቸው ምንድን ነው? ኤሊን በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር የተባለውን ቡክሌት በየቀኑ ያነብባሉ። በተጨማሪም አጉሊ መነጽር በመጠቀም በየዕለቱ የተወሰኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን ያነብባሉ። ኤሊን የይሖዋ ምሥክሮች በየሳምንቱ ለሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ይዘጋጃሉ፤ በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ በአካል ለመገኘት አቅም ባይኖራቸውም እንኳ ትምህርቱ የተቀዳበትን ካሴት ያዳምጣሉ። በየትኛውም የዕድሜ ክልል ውስጥ እንገኝ መጽሐፍ ቅዱስንና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን በየዕለቱ ማንበባችን እንዲሁም በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አዘውትረን መገኘታችን የሚያረካና ዓላማ ያለው ሕይወት እንድንመራ ያስችለናል።—መዝሙር 1:2፤ ዕብራውያን 10:24, 25