የአንባቢያን ጥያቄዎች
የአንባቢያን ጥያቄዎች
ሰባኪው “ከሺህ ወንዶች መካከል አንድ ቅን ሰው” ብቻ እንዳገኘ “[ከሴቶች] መካከል ግን አንዲት ቅን ሴት” እንዳላገኘ የተናገረው ከምን አንጻር ነው?—መክብብ 7:28
የእነዚህን በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉ ቃላት ትርጉም በትክክል ለመገንዘብ በቅድሚያ አምላክ ለሴቶች ያለውን አመለካከት መረዳት ይኖርብናል። መጽሐፍ ቅዱስ የኑኃሚን ምራት የሆነችው መበለቷ ሩት “ምግባረ መልካም ሴት” እንደነበረች ይናገራል። (ሩት 3:11) በምሳሌ 31:10 ላይ እንደተገለጸው ጥሩ ሚስት “ከቀይ ዕንቍ እጅግ ትበልጣለች።” ታዲያ የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ሰሎሞን “ከሺህ ወንዶች መካከል አንድ ቅን ሰው አገኘሁ፣ . . . [ከሴቶች] መካከል ግን አንዲት ቅን ሴት አላገኘሁም” ሲል ምን ማለቱ ነበር?
በጥቅሱ ዙሪያ ያለው ሐሳብ በሰሎሞን ዘመን ይኖሩ በነበሩት ሴቶች ዘንድ የሥነ ምግባር ብልሹነት ተስፋፍቶ እንደነበር ይጠቁማል። (መክብብ 7:26) ይህ ሁኔታ የበኣል አምላኪዎች የሆኑ የባዕድ አገር ሴቶች ያሳደሩት ተጽዕኖ ውጤት ሊሆን ይችላል። ራሱ ንጉሥ ሰሎሞን እንኳ ከባዕድ አገር ያገባቸው በርካታ ሚስቶቹ ላሳደሩበት ተጽዕኖ ተንበርክኳል። መጽሐፍ ቅዱስ ሰሎሞን “ከነገሥታት የተወለዱ ሰባት መቶ ሚስቶችና ሦስት መቶ ቁባቶች” እንደነበሩት፣ “ሚስቶቹም ልቡ ወደ ሌላ እንዲያዘነብል” ማለትም የሐሰት አማልክት እንዲያመልክ እንዳደረጉት ይናገራል። (1 ነገሥት 11:1-4) የወንዶቹ የሥነ ምግባር አቋምም ቢሆን ጥሩ አልነበረም። ከሺህ ወንዶች አንድ ጻድቅ ሰው ብቻ መገኘቱ ጻድቅ አለ የሚያስብል አይደለም። ስለሆነም ሰሎሞን “ይህን አንድ ነገር ብቻ አገኘሁ፤ እግዚአብሔር ሰውን ቅን አድርጎ መሥራቱን፣ ሰዎች ግን ውስብስብ ዘዴ ቀየሱ” የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሷል። (መክብብ 7:29) ሰሎሞን የደረሰበት ይህ መደምደሚያ የተነገረው ስለ መላው የሰው ዘር እንጂ ወንድን ከሴት ጋር በማወዳደር አልነበረም። በመሆኑም በመክብብ 7:28 ላይ የሚገኘው የሰሎሞን ሐሳብ በዘመኑ ስለነበሩት ሰዎች አጠቃላይ የሥነ ምግባር ሁኔታ ለመግለጽ እንደተነገረ ተደርጎ መታየት ይኖርበታል።
ነገር ግን፣ ይህ ጥቅስ ሌላም ትርጉም ሊኖረው ይችላል። ለይሖዋ ፍጹም ታዛዥ የሆነች ሴት እንደሌለች የሚጠቁም ትንቢታዊ ይዘት ያለው አባባል ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ፍጹም ታዛዥ የሆነ አንድ ወንድ አለ። እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።—ሮሜ 5:15-17
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“ከሺህ ወንዶች መካከል አንድ ቅን ሰው”