በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የኢሳይያስ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች—ክፍል 2

የኢሳይያስ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች—ክፍል 2

የይሖዋ ቃል ሕያው ነው

የኢሳይያስ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች—ክፍል 2

ኢሳይያስ በነቢይነት የተሰጠውን ተልዕኮ በታማኝነት እየተወጣ ነው። አሥሩን ነገዶች ባቀፈው የእስራኤል መንግሥት ላይ ያስተላለፈው የፍርድ መልእክት ፍጻሜውን አግኝቷል። አሁን ደግሞ ስለ ኢየሩሳሌም የወደፊት ዕጣ የሚናገረው ሌላ መልእክት አለው።

ኢየሩሳሌም የምትጠፋ ሲሆን ነዋሪዎቿም በግዞት ይወሰዳሉ። ይሁንና ከተማዋ ባድማ ሆና አትቀርም። ከጊዜ በኋላ እውነተኛው አምልኮ እንደገና ይቋቋማል። ከኢሳይያስ 36:1 እስከ 66:24 ድረስ ያሉት ምዕራፎች የያዙት ዋና መልእክት ይህ ነው። a በእነዚህ ምዕራፎች ውስጥ የሚገኙት አብዛኞቹ ትንቢቶች ዋነኛ ፍጻሜያቸውን የሚያገኙት በዘመናችን ወይም በቅርቡ ስለሆነ ሐሳቦቹን መመርመራችን ይጠቅመናል። ይህ የኢሳይያስ መጽሐፍ ክፍል ስለ መሲሑ የሚናገሩ አስደሳች ትንቢቶችንም ይዟል።

‘እነሆ፤ ቀን ይመጣል’

(ኢሳይያስ 36:1 እስከ 39:8)

ንጉሥ ሕዝቅያስ በነገሠ በ14ኛው ዓመት (በ732 ከክርስቶስ ልደት በፊት) አሦራውያን ይሁዳን ወረሩ። ይሖዋ ኢየሩሳሌምን እንደሚጠብቃት ቃል ገባ። አንድ የይሖዋ መልአክ ብቻውን 185,000 የአሦራውያን ወታደሮችን በገደለ ጊዜ ይሁዳ ከወረራው ስጋት ነጻ ሆነች።

ሕዝቅያስ በጠና ታመመ። በዚህ ጊዜ ይሖዋ ጸሎቱን ሰምቶ ከበሽታው ፈወሰው እንዲሁም በዕድሜው ላይ 15 ዓመት ጨመረለት። የባቢሎን ንጉሥ ‘እንኳን ደስ አለህ’ ለማለት መልእክተኞች በላከ ጊዜ ሕዝቅያስ ለመጡት ሰዎች ያለውን ሀብት ሁሉ በማሳየት ጥበብ የጎደለው ድርጊት ፈጸመ። በመሆኑም ኢሳይያስ ከይሖዋ የመጣውን መልእክት ለሕዝቅያስ እንዲህ በማለት ነገረው:- “እነሆ፤ በቤተ መንግሥትህ ያለው ሁሉ፣ አባቶችህ እስከዚህች ቀን ድረስ ያከማቹትም ሁሉ ወደ ባቢሎን ተማርኮ የሚወሰድበት ቀን ይመጣል።” (ኢሳይያስ 39:5, 6) ይህ ትንቢት ከ100 ዓመት በኋላ ተፈጽሟል።

ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-

38:8—ጥላው ወደኋላ እንዲመለስ የተደረገበት “ደረጃ” ምንድን ነው? ግብጻውያንና ባቢሎናውያን ከ8ኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት ጀምሮ የፀሓይ ጥላ ያረፈበትን አቅጣጫ በመመልከት ጊዜውን የሚያውቁበት እንደ ሰዓት መቁጠሪያ የሚያገለግል መሣሪያ ይጠቀሙ ነበር። በመሆኑም ይህ “ደረጃ” የሕዝቅያስ አባት አካዝ ይጠቀምበት የነበረውን ሰዓት መቁጠሪያ የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። አሊያም ደግሞ በቤተ መንግሥቱ ውስጥ ያሉትን ደረጃዎች ሊያመለክት ይችላል። በደረጃዎቹ ዳር የቆሙት ምሰሶዎች ፀሐይ ሲያርፍባቸው ጥላቸውን በደረጃዎቹ ላይ ስለሚያጠሉ፣ ጥላዎቹ ጊዜን ለመቁጠር አገልግለው ሊሆን ይችላል።

ምን ትምህርት እናገኛለን?

36:2, 3, 22 ሳምናስ ከመጋቢነት አገልግሎቱ እንዲወርድ ቢደረግም በእርሱ እግር ለተተካው ግለሰብ ጸሐፊ ሆኖ በመሥራት ንጉሡን ማገልገሉን ቀጥሏል። (ኢሳይያስ 22:15, 19) እኛስ በይሖዋ ድርጅት ውስጥ የነበረንን ኃላፊነት በሆነ ምክንያት ብናጣ አምላክ በፈቀደው በየትኛውም መስክ እርሱን ማገልገላችንን መቀጠል አይገባንም?

37:1, 14, 15፤ 38:1, 2 በምንጨነቅበት ጊዜ በጸሎት ወደ ይሖዋ መቅረባችንና ሙሉ በሙሉ በእርሱ መታመናችን ጥበብ የተሞላበት አካሄድ ነው።

37:15-20፤ 38:2, 3 አሦራውያን በኢየሩሳሌም ላይ ስጋት በፈጠሩበት ጊዜ፣ ሕዝቅያስን በዋነኝነት ያሳሰበው የከተማዋ መሸነፍ በይሖዋ ስም ላይ ሊያመጣ የሚችለው ነቀፋ ነበር። ሕዝቅያስ ከበሽታው እንደማይድን ካወቀ በኋላም ቢሆን ይበልጥ ያሳሰበው የራሱ ሁኔታ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ልጅ ሳይወልድ መሞቱ በዳዊት የነገሥታት የዘር ሐረግ ላይ ተጽዕኖ እንደሚኖረው ተገንዝቦ ነበር። ከአሦራውያን ጋር የሚደረገውን ውጊያ ማን ሊመራው እንደሚችልም አሳስቦት ነበር። እኛም እንደ ሕዝቅያስ ከራሳችን መዳን የበለጠ የሚያሳስበን የይሖዋ ስም መቀደስና የዓላማው መፈጸም መሆን ይኖርበታል።

38:9-20 ይህ የሕዝቅያስ መዝሙር፣ በአንድ ሰው ሕይወት ውስጥ ይሖዋን ከማወደስ የበለጠ አስፈላጊ የሆነ ነገር እንደሌለ ያስተምረናል።

‘እንደገና ትሠራለች’

(ኢሳይያስ 40:1 እስከ 59:21)

ኢሳይያስ ኢየሩሳሌም እንደምትጠፋና ነዋሪዎቿም ተማርከው ወደ ባቢሎን እንደሚወሰዱ ከተናገረ በኋላ ስለ መልሶ መቋቋም ተንብዮአል። (ኢሳይያስ 40:1, 2) ኢሳይያስ 44:28 ‘[ኢየሩሳሌም] እንደገና ትሠራለች’ ይላል። የባቢሎናውያን ጣዖታት እንደ “ተራ ዕቃ” ተጭነው ይወሰዳሉ። (ኢሳይያስ 46:1 NW) ባቢሎንም ትጠፋለች። እነዚህ ትንቢቶች ከሁለት መቶ ዓመታት በኋላ ተፈጻሚነታቸውን አግኝተዋል።

ይሖዋ አገልጋዩን ‘ለአሕዛብ ብርሃን ያደርገዋል።’ (ኢሳይያስ 49:6) የባቢሎናውያን ‘ሰማይ’ ማለትም ገዢው መደብ ‘እንደ ጢስ በኖ ይጠፋል’፤ ነዋሪዎቿም “እንደ አሸን ፈጥነው ይረግፋሉ።” ‘ምርኮኛዪቱ የጽዮን ልጅ ግን የዐንገቷን የእስራት ሰንሰለት አውልቃ ትጥላለች።’ (ኢሳይያስ 51:6፤ 52:2) ይሖዋ ወደ እርሱ ለሚቀርቡትና ለሚያዳምጡት እንዲህ ብሏቸዋል:- “ለዳዊት በገባሁት በጽኑ ፍቅሬ፣ ከእናንተም ጋር የዘላለም ኪዳን አደርጋለሁ።” (ኢሳይያስ 55:3) ከአምላክ የጽድቅ መሥፈርቶች ጋር ተስማምቶ የሚኖር ሰው ‘በይሖዋ ደስ ይለዋል።’ (ኢሳይያስ 58:14) በሌላ በኩል ግን የሕዝቡ በደል ‘ከአምላካቸው ለይቷቸዋል።’—ኢሳይያስ 59:2

ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-

40:27, 28—እስራኤል “መንገዴ ከእግዚአብሔር ተሰውራለች፤ ፍርዴም በአምላኬ ቸል ተብላለች” ያለው ለምንድን ነው? በባቢሎን የነበሩ አንዳንድ አይሁዳውያን ይደርስባቸው የነበረው የፍትሕ መጓደል ከይሖዋ እንደተሰወረ ወይም እርሱ እንደማያየው ሆኖ ተሰምቷቸው ሊሆን ይችላል። ይሁንና ባቢሎን ከማይደክመው ወይም ከማይታክተው የምድር ፈጣሪ አቅም በላይ እንዳልሆነች እንዲያስታውሱ ተነግሯቸዋል።

43:18-21—ከምርኮ የሚመለሱት እስራኤላውያን ‘ያለፈውን እንዳያስቡ’ የተነገራቸው ለምንድን ነው? እንዲህ ሲባሉ ይሖዋ ባለፉት ዘመናት ሕዝቡን ለማዳን ያደረገውን ነገር መርሳት አለባቸው ማለት አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ ለእነርሱ በሚያደርግላቸው “አዲስ ነገር” ተነሳስተው እንዲያመሰግኑት ይፈልጋል። ከእነዚህ ‘አዲስ ነገሮች’ መካከል ምድረ በዳ አቋርጠው ወደ ኢየሩሳሌም በሰላም እንዲደርሱ ማድረጉ ይገኝበታል። “ከታላቁ መከራ” የሚተርፉት ‘እጅግ ብዙ ሕዝቦች’ ይሖዋን ለማወደስ የሚያነሳሳቸው አዲስና የየግላቸው የሆነ በቂ ምክንያት ይኖራቸዋል።—ራእይ 7:9, 14

49:6—የመሲሑ ምድራዊ አገልግሎት ለእስራኤላውያን ብቻ የተወሰነ ሆኖ ሳለ “ለአሕዛብ ብርሃን” የሆነው እንዴት ነው? ይህ የሆነው ከኢየሱስ ሞት በኋላ በተከናወኑት ነገሮች ምክንያት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ኢሳይያስ 49:6ን የኢየሱስን ደቀ መዛሙርት ለማመልከት ተጠቅሞበታል። (የሐዋርያት ሥራ 13:46, 47) በዛሬው ጊዜ፣ በእጅግ ብዙ ሕዝቦች የሚታገዙት ቅቡዓን ክርስቲያኖች “እስከ ምድር ዳርቻ” የሚገኙ ሰዎችን በማስተማር “ለአሕዛብ ብርሃን” ሆነው በማገልገል ላይ ናቸው።—ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20

53:11—መሲሑ ‘ብዙዎችን የሚያጸድቅበት’ እውቀት ምንድን ነው? ይህ፣ ኢየሱስ ሰው ሆኖ በምድር ላይ በመወለድና ፍትሕ በጎደለው መንገድ ተሠቃይቶ በመሞት ያገኘው እውቀት ነው። (ዕብራውያን 4:15) በዚህ መንገድ በመሞት ኢየሱስ ቅቡዓን ክርስቲያኖችና እጅግ ብዙ ሰዎች በአምላክ ፊት ጻድቅ ሆነው እንዲቆጠሩ የሚያስችላቸውን ቤዛዊ መሥዋዕት አቅርቧል።—ሮሜ 5:19፤ ያዕቆብ 2:23, 25

56:6—“መጻተኞች” የተባሉት እነማን ናቸው? ‘[የይሖዋን] ቃል ኪዳን የሚጠብቁትስ’ በየትኞቹ መንገዶች ነው? “መጻተኞች” የተባሉት የኢየሱስ “ሌሎች በጎች” ናቸው። (ዮሐንስ 10:16) እነዚህ ሰዎች ከቃል ኪዳኑ ጋር የተያያዙ ሕጎችን በመታዘዝ፣ በቃል ኪዳኑ በኩል የተደረጉ ዝግጅቶችን በሙሉ ልብ በመደገፍ፣ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ከሚመገቡት መንፈሳዊ ማዕድ በመመገብ እንዲሁም በመንግሥቱ ስብከትና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ቅቡዓኑን በመደገፍ አዲሱን ቃል ኪዳን ይጠብቃሉ።

ምን ትምህርት እናገኛለን?

40:10-14, 26, 28 ይሖዋ ኃያልና ርኅሩኅ፣ ሁሉን ቻይና ጥበበኛ እንዲሁም ማስተዋሉ የማይመረመር አምላክ ነው።

40:17, 23፤ 41:29፤ 44:9፤ 59:4 ፖለቲካዊ ጥምረቶችም ሆኑ ጣዖታት “መና” ናቸው። በእነርሱ መታመን ከንቱ ነው።

42:18, 19፤ 43:8 በጽሑፍ የሰፈረውን የአምላክን ቃል ችላ የምንልና ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ በኩል ከሚሰጠን መመሪያ ጆሯችንን የምንመልስ ከሆነ በመንፈሳዊ ሁኔታ ዕውሮችና ደንቆሮዎች የሆንን ያህል ነው።—ማቴዎስ 24:45 የ1954 ትርጉም

43:25 ይሖዋ ስለ ራሱ ሲል መተላለፍን ይደመስሳል። የይሖዋ ስም መቀደስ፣ ከኃጢአትና ከሞት ባርነት ነጻ ከመውጣታችንም ሆነ ሕይወት ከማግኘታችን ይበልጥ አሳሳቢ ጉዳይ ነው።

44:8 እንደ ዐለት ጽኑ የሆነው ይሖዋ ይደግፈናል። ስለዚህ ስለ አምላክነቱ ለመመሥከር ፈጽሞ መፍራት የለብንም!—2 ሳሙኤል 22:31, 32

44:18-20 ጣዖትን ማምለክ የልብን ንጹሕ አለመሆን ያመለክታል። በልባችን ውስጥ ይሖዋ ሊኖረው የሚገባውን ቦታ ለምንም ነገር ልንሰጠው አይገባም።

46:10, 11 ይሖዋ ‘ዓላማው እንዲጸና’ ወይም እንዲፈጸም ማድረግ መቻሉ አምላክነቱን በማያሻማ መንገድ ያረጋግጣል።

48:17, 18፤ 57:19-21 የይሖዋን ማዳን ተስፋ ካደረግን፣ ወደ እርሱ ከቀረብንና ሕግጋቱን ከታዘዝን ሰላማችን እንደ ወንዝ ውኃ ይትረፈረፋል፤ የጽድቅ ሥራችንም እንደ ባሕር ሞገድ ይበዛል። የአምላክን ቃል ሰምተው የማይታዘዙ ሰዎች ግን “እንደሚናወጥ ባሕር ናቸው።” ሰላምም የላቸውም።

52:5, 6 ባቢሎናውያን እውነተኛው አምላክ ደካማ ነው የሚል የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ ደርሰው ነበር። እስራኤላውያን በግዞት የተወሰዱት ይሖዋ ስላዘነባቸው መሆኑን ሳያስተውሉ ቀርተዋል። እኛም ሌሎች መከራ ሲደርስባቸው መንስዔው ይህ ወይም ያ ነው ብለን ለመደምደም መቸኮላችን ጥበብ አይሆንም።

52:7-9፤ 55:12, 13 የመንግሥቱን ምሥራች በመስበኩና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ላይ በደስታ እንድንካፈል የሚያነሳሱን ቢያንስ ሦስት ምክንያቶች አሉ። በመንፈሳዊ በተራቡ ትሑታን ዓይን እግሮቻችን ያማሩ ናቸው። ይሖዋን ‘በዓይናችን አይተነዋል’ ማለትም ከእርሱ ጋር የቅርብ ዝምድና መመሥረት ችለናል። ከዚህም ባሻገር መንፈሳዊ ብልጽግና አግኝተናል።

52:11, 12፦ ‘የይሖዋን ዕቃ’ ለመሸከም ማለትም ከቅዱስ አገልግሎቱ ጋር በተያያዘ አምላክ ባደረገው ዝግጅት ላይ ለመካፈል ከፈለግን መንፈሳዊና ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናችንን መጠበቅ ይገባናል።

58:1-14 ለስሙ ያህል ለአምላክ ያደሩና ጻድቅ መስሎ መታየት ከንቱ ነው። እውነተኛ አምላኪዎች ከልባቸው ለአምላክ ያደሩ እንደሆኑና የወንድማማች ፍቅር እንዳላቸው በተግባራቸው በግልጽ ማሳየት ይኖርባቸዋል።—ዮሐንስ 13:35፤ 2 ጴጥሮስ 3:11

59:15ለ-19 ይሖዋ ሰዎች የሚያደርጉትን ነገር ይመለከታል፤ በራሱ ጊዜም ነገሮችን ለማስተካከል ጣልቃ ይገባል።

“የክብር አክሊል” ትሆናለች

(ኢሳይያስ 60:1 እስከ 66:24)

ኢሳይያስ 60:1 በጥንት ዘመንም ሆነ በዘመናችን እውነተኛው አምልኮ ተመልሶ እንደሚቋቋም ሲገልጽ “ብርሃንሽ መጥቶአልና ተነሺ አብሪ፤ የእግዚአብሔርም ክብር ወጥቶልሻል” ይላል። ጽዮን “በእግዚአብሔር እጅ የክብር አክሊል” ትሆናለች።—ኢሳይያስ 62:3

ኢሳይያስ በባቢሎን በግዞት ሆነው ንስሐ የሚገቡትን ወገኖቹን በመወከል ወደ ይሖዋ ጸልዮአል። (ኢሳይያስ 63:15 እስከ 64:12) ነቢዩ፣ እውነተኛ አገልጋዮችን ከሐሰተኞች ጋር ካነጻጸረ በኋላ ይሖዋ እርሱን የሚያገለግሉትን እንዴት እንደሚባርካቸው ተናግሯል።—ኢሳይያስ 65:1 እስከ 66:24

ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-

61:8, 9—“የዘላለም ኪዳን” የተባለው ምንድን ነው? ‘ዘሮቻቸውስ’ እነማን ናቸው? ይህ ኪዳን ይሖዋ ከቅቡዓን ክርስቲያኖች ጋር የገባው አዲስ ቃል ኪዳን ነው። “ዘሮቻቸው” የተባሉት ደግሞ መልእክታቸውን የተቀበሉት በሚሊዮን የሚቆጠሩ “ሌሎች በጎች” ናቸው።—ዮሐንስ 10:16

63:5 የ1954 ትርጉም—አምላክን ቁጣው ያገዘው እንዴት ነው? የአምላክ ቁጣ ከቁጥጥር ውጪ የሆነ ስሜት ሳይሆን የጽድቅ ቁጣ ነው። ቁጣው የጽድቅ ፍርድ እንዲያስተላልፍ ያነሳሳዋል እንዲሁም ያግዘዋል።

ምን ትምህርት እናገኛለን?

64:6 ፍጽምና የጎደላቸው የሰው ልጆች ራሳቸውን ማዳን አይችሉም። የጽድቅ ሥራዎቻቸውም ኃጢአትን ከማስተሰረይ አኳያ ሲታዩ ካደፈ ጨርቅ የሚሻሉ አይደሉም።—ሮሜ 3:23, 24

65:13, 14 ይሖዋ በመንፈሳዊ የሚያስፈልጋቸውን አትረፍርፎ በመስጠት ታማኝ አገልጋዮቹን ይባርካል።

66:3-5 ይሖዋ ግብዝነትን ይጠላል።

“ደስ ይበላችሁ”

ስለ መልሶ መቋቋም የተነገረው ትንቢት በባቢሎን ግዞት የነበሩትን ታማኝ አይሁዳውያን እጅግ አጽናንቷቸው መሆን አለበት! ይሖዋ “በምፈጥረው፣ ደስ ይበላችሁ፤ ለዘላለም ሐሤት አድርጉ። ኢየሩሳሌምን ለደስታ፣ ሕዝቧን ለሐሤት እፈጥራለሁና” ብሏቸዋል።—ኢሳይያስ 65:18

እኛም የምንኖረው ምድር በጨለማ ሕዝቦቿም በድቅድቅ ጨለማ በተዋጡበት ዘመን ላይ ነው። (ኢሳይያስ 60:2) ያለንበት ጊዜ በጣም ‘አስጨናቂ’ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) በመሆኑም በኢሳይያስ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘው የይሖዋ የማዳን መልእክት በእጅጉ ያበረታታናል።—ዕብራውያን 4:12

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a ከኢሳይያስ 1:1 እስከ 35:10 ድረስ ስላሉት ምዕራፎች ማብራሪያ ለማግኘት በታኅሣሥ 1, 2006 መጠበቂያ ግንብ ላይ የሚገኘውን “የይሖዋ ቃል ሕያው ነው—የኢሳይያስ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች—ክፍል 1” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሕዝቅያስ ከአሦራውያን እንዲድን የጸለየበት ዋነኛ ምክንያት ምን እንደሆነ ታውቃለህ?

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

‘በተራሮች ላይ የቆሙ፣ የምሥራች ይዘው የሚመጡ እግሮች እንዴት ያማሩ ናቸው!’