በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አድናቆታችሁ እየጨመረ ይሂድ

አድናቆታችሁ እየጨመረ ይሂድ

አድናቆታችሁ እየጨመረ ይሂድ

‘አምላክ ሆይ፤ ሐሳብህ እንዴት ክቡር ነው! ቍጥሩስ ምንኛ ብዙ ነው!’—መዝሙር 139:17

1, 2. የአምላክን ቃል ማድነቅ ያለብን ለምንድን ነው? መዝሙራዊው አድናቆቱን የገለጸውስ እንዴት ነው?

 አስደናቂ ግኝት ነበር። በኢየሩሳሌም የነበረው የይሖዋ ቤተ መቅደስ በሚታደስበት ጊዜ ሊቀ ካህኑ ኬልቅያስ “በሙሴ አማካይነት የተሰጠውን የእግዚአብሔርን ሕግ መጽሐፍ አገኘ።” ይህ መጽሐፍ ከ800 ዓመታት በፊት የተጻፈው የመጀመሪያው ቅጂ ሳይሆን አይቀርም! ፈሪሃ አምላክ የነበረው ንጉሥ ኢዮስያስ መጽሐፉን ሲመለከት ምን ተሰምቶት እንደሚሆን መገመት ትችላለህ? ንጉሡ፣ ጸሐፊው ሳፋን ወዲያውኑ ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲያነብለት ማድረጉ በእርግጥም ለመጽሐፉ ትልቅ ቦታ እንደሰጠው ያሳያል።—2 ዜና መዋዕል 34:14-18

2 በዛሬው ጊዜ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሙሉውንም ሆነ ከፊሉን የአምላክ ቃል ሊያገኙ ይችላሉ። ይህ መሆኑ ታዲያ የቅዱሳን መጻሕፍትን ዋጋማነት ወይም ጠቀሜታ ይቀንሰዋል? በጭራሽ! እነዚህ መጻሕፍት ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ለጥቅማችን ሲል ያስጻፈውን ሐሳብ የያዙ በመሆናቸው ከፍተኛ ዋጋ አላቸው። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) መዝሙራዊው ለአምላክ ቃል ያለውን ስሜት ሲገልጽ “አምላክ ሆይ፤ ለእኔ ያለህ ሐሳብ እንዴት ክቡር ነው! ቍጥሩስ ምንኛ ብዙ ነው!” ብሏል።—መዝሙር 139:17

3. ዳዊት ጥልቅ መንፈሳዊ ማስተዋል እንደነበረው የሚያሳየው ምንድን ነው?

3 ዳዊት፣ ለይሖዋና ለቃሉ እንዲሁም እውነተኛውን አምልኮ ለማከናወን ለተደረጉት ዝግጅቶች የነበረው አድናቆት ፈጽሞ አልቀነሰም። ዳዊት ያቀናበራቸው በርካታ ግሩም መዝሙራት ስሜቱን የሚገልጹ ናቸው። ለምሳሌ ያህል፣ በመዝሙር 27:4 ላይ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “እግዚአብሔርን አንዲት ነገር እለምነዋለሁ፤ እርሷንም እሻለሁ፤ ይኸውም በሕይወቴ ዘመን ሁሉ፣ በእግዚአብሔር ቤት እኖር ዘንድ፣ የእግዚአብሔርን ክብር ውበት አይ ዘንድ፣ በመቅደሱም ሆኜ አሰላስል ዘንድ ነው።” ይህ መዝሙር መጀመሪያ በተጻፈበት በዕብራይስጥ ቋንቋ “አሰላስል ዘንድ” የሚለው ሐረግ፣ ጊዜ ወስዶ ማውጠንጠንና በጥንቃቄ መመርመር እንዲሁም በደስታ፣ በሐሴትና በአድናቆት መመልከት የሚል ትርጉም አለው። ከዚህ በግልጽ እንደምንመለከተው ዳዊት ጥልቅ መንፈሳዊ ማስተዋል ነበረው፤ ይህ መዝሙራዊ የይሖዋን መንፈሳዊ ዝግጅቶች ከልቡ ከማድነቁም በላይ አምላክ የገለጸውን መንፈሳዊ እውነት በሙሉ በደስታ ያጣጥም ነበር። ዳዊት የነበረው የአድናቂነት መንፈስ ልንኮርጀው የሚገባ ነው።—መዝሙር 19:7-11

የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የማወቅ አጋጣሚ ማግኘትህን አድንቅ

4. ኢየሱስ “በመንፈስ ቅዱስ ሐሤት” ያደረገው ለምን ነበር?

4 የአምላክን ቃል ማወቃችን ባለን የማስተዋል ችሎታ ወይም በዓለማዊ ትምህርት ላይ የተመካ አይደለም፤ እንዲያውም እነዚህ ነገሮች ለኩራት መንስኤ ይሆናሉ። ከዚህ በተቃራኒ የአምላክን ቃል ማወቅ የቻልነው ይሖዋ ለመንፈሳዊ ፍላጎታቸው ንቁ ለሆኑ ትሑትና ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች በሚያሳየው ይገባናል በማንለው ደግነቱ የተነሳ ነው። (ማቴዎስ 5:3፤ 1 ዮሐንስ 5:20) ኢየሱስ ፍጹማን ያልሆኑ አንዳንድ ሰዎች ስማቸው በሰማይ መጻፉን ሲያስብ “በመንፈስ ቅዱስ ሐሤት አድርጎ እንዲህ አለ፤ ‘የሰማይና የምድር ጌታ፤ አባት ሆይ፤ ይህን ሁሉ ከጥበበኞችና ከዐዋቂዎች ሰውረህ ለሕፃናት ስለ ገለጥህላቸው አመሰግንሃለሁ።’”—ሉቃስ 10:17-21

5. የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ስለ አምላክ መንግሥት የተገለጡላቸውን እውነቶች አቅልለው መመልከት ያልነበረባቸው ለምንድን ነው?

5 ኢየሱስ ከላይ ያለውን ከልብ የመነጨ ጸሎት ካቀረበ በኋላ ወደ ደቀ መዛሙርቱ ዘወር ብሎ እንዲህ አላቸው:- “እናንተ የምታዩትን የሚያዩ ዐይኖች ብፁዓን ናቸው፤ እላችኋለሁና፤ ብዙ ነቢያትና ነገሥታት እናንተ የምታዩትን ለማየት ፈልገው አላዩም፤ የምትሰሙትንም ለመስማት ፈልገው አልሰሙም።” አዎን፣ ኢየሱስ ታማኝ ተከታዮቹ ስለ አምላክ መንግሥት የተገለጡላቸውን ውድ እውነቶች አቅልለው እንዳይመለከቱ አበረታቷቸዋል። እነዚህ እውነቶች ቀደም ባሉት ዘመናት ለኖሩት የአምላክ አገልጋዮችም ሆነ በኢየሱስ ጊዜ ለነበሩት ‘ጥበበኞችና ዐዋቂዎች’ አልተገለጡላቸውም።—ሉቃስ 10:23, 24

6, 7. (ሀ) መለኮታዊውን እውነት እንድናደንቅ የሚያደርጉን ምን ምክንያቶች አሉን? (ለ) በዛሬው ጊዜ በእውነተኛውና በሐሰተኛው ሃይማኖት መካከል ምን ልዩነት ይታያል?

6 ይሖዋ ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ በኩል ሕዝቦቹ ቃሉን በጥልቅ እንዲረዱ ስላስቻላቸው በዘመናችንም መለኮታዊውን እውነት የምናደንቅበት ተጨማሪ ምክንያት አለን። (ማቴዎስ 24:45 የ1954 ትርጉም፤ ዳንኤል 12:10) ነቢዩ ዳንኤል የፍጻሜውን ዘመን አስመልክቶ “ብዙዎች ወዲያ ወዲህ ይራወጣሉ፤ ዕውቀትም ይበዛል” በማለት ጽፏል። (ዳንኤል 12:4) በዛሬው ጊዜ የአምላክ እውቀት ‘በዝቷል’ ቢባል አትስማማም? ለይሖዋ አገልጋዮችስ የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ እየቀረበላቸው አይደለም?

7 ስለ አምላክ እንዲሁም ስለ ዓላማው ጥልቅ እውቀት ባላቸው የይሖዋ ሕዝቦችና በሃይማኖታቸው ግራ በተጋቡት የታላቂቱ ባቢሎን አባላት መካከል ያለው ልዩነት እንዴት ሰፊ ነው! በመሆኑም ብዙዎች በሐሰት ሃይማኖት ውስጥ በሚደረገው ነገር ስለሚያዝኑ ወይም ሁኔታው ስለሚያስጠላቸው ወደ እውነተኛው አምልኮ ዘወር እያሉ ነው። እነዚህም ‘በታላቂቱ ባቢሎን ኃጢአት ለመተባበር ወይም ከመቅሰፍቷ ለመካፈል’ የማይፈልጉ በግ መሰል ሰዎች ናቸው። ይሖዋና አገልጋዮቹ እንደነዚህ ያሉትን ግለሰቦች በሙሉ ወደ እውነተኛው ክርስቲያን ጉባኤ እንዲመጡ ይጋብዟቸዋል።—ራእይ 18:2-4፤ 22:17

አድናቂ የሆኑ ሰዎች ወደ አምላክ ይጎርፋሉ

8, 9. በዛሬው ጊዜ ሐጌ 2:7 ፍጻሜውን እያገኘ ያለው እንዴት ነው?

8 ይሖዋ፣ መንፈሳዊ የአምልኮ ቤቱን በተመለከተ እንዲህ በማለት አስቀድሞ ተናግሯል:- “ሕዝቦችን ሁሉ አናውጣለሁ፤ የሕዝቦችም ሀብት ሁሉ ወደዚህ ይመጣል፤ ይህንም ቤት በክብር እሞላዋለሁ።” (ሐጌ 2:7) በሐጌ ዘመን ከምርኮ ተርፈው ወደ አገራቸው የተመለሱት የአምላክ ሕዝቦች በኢየሩሳሌም የሚገኘውን ቤተ መቅደስ እንደገና በገነቡበት ወቅት ይህ አስገራሚ ትንቢት ፍጻሜውን አግኝቷል። በዛሬው ጊዜም የሐጌ ትንቢት ከይሖዋ ታላቅ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ጋር በተያያዘ ተጨማሪ ፍጻሜውን እያገኘ ነው።

9 በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በምሳሌያዊው ቤተ መቅደስ ውስጥ አምላክን “በመንፈስና በእውነት” እያመለኩት ሲሆን በየዓመቱ ደግሞ “የሕዝቦችም ሀብት ሁሉ” ከተባሉት መካከል ከ200,000 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ወደዚህ ቤት እየጎረፉ ነው። (ዮሐንስ 4:23, 24) ለምሳሌ ያህል፣ ከ2006 የአገልግሎት ዓመት ዓለም አቀፍ ሪፖርት መመልከት እንደሚቻለው 248,327 የሚያህሉ ሰዎች ራሳቸውን ለይሖዋ መወሰናቸውን ለማሳየት ተጠምቀዋል። ይህም በአማካይ 680 የሚያህሉ ሰዎች በየቀኑ ተጠምቀዋል ማለት ነው! እነዚህ ሰዎች ለእውነት ያላቸው ፍቅርና የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሆነው ይሖዋን ለማገልገል ያላቸው ፍላጎት አምላክ ወደራሱ እንደሳባቸው የሚያሳይ ማስረጃ ነው።—ዮሐንስ 6:44, 65

10, 11. ሰዎች ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት እንዴት አድናቆት እንዳደረባቸው የሚያሳይ ተሞክሮ ተናገር።

10 ቅን ልብ ካላቸው ከእነዚህ ሰዎች አብዛኞቹ ወደ እውነት የተሳቡት “በጻድቁና በኀጢአተኛው መካከል፣ እግዚአብሔርን በሚያገለግለውና በማያገለግለው መካከል ያለውን ልዩነት” ስላስተዋሉ ነው። (ሚልክያስ 3:18) የፕሮቴስታንት ቤተ ክርስቲያን አባላት ቢሆኑም መልስ ያላገኙላቸው በርካታ ጥያቄዎች የነበሯቸውን ዌን እና ቨርጂንያ የተባሉ ባልና ሚስት ተሞክሮ እንመልከት። እነዚህ ባልና ሚስት ጦርነትን የሚጠሉ ከመሆኑም በላይ ቀሳውስት ወታደሮችንና የጦር መሣሪያዎችን ሲባርኩ መመልከታቸው ግራ ያጋባቸው እንዲሁም ይረብሻቸው ነበር። ቨርጂንያ ለብዙ ዓመታት የሰንበት ትምህርት ቤት አስተማሪ የነበሩ ቢሆንም፣ እነዚህ ባልና ሚስት በዕድሜ እየገፉ ሲሄዱ የቤተ ክርስቲያኗ አባላት ችላ እንዳሏቸው ተሰማቸው። “ቤታችን መጥቶ የሚጠይቀን ወይም ስለ መንፈሳዊነታችን የሚያስብ አንድም ሰው አልነበረም። ቤተ ክርስቲያኗ ከእኛ የምትፈልገው ገንዘባችንን ብቻ ነበር። ይህ ሁኔታ በጣም ግራ አጋብቶን ነበር” በማለት ተናግረዋል። በዚህ ላይ ደግሞ ቤተ ክርስቲያኗ ግብረ ሰዶምን መቀበሏ ይበልጥ አሳዘናቸው።

11 በዚህ መሃል የዌንና የቨርጂንያ የልጅ ልጅ፣ ቆየት ብሎ ደግሞ እናቷ የይሖዋ ምሥክሮች ሆኑ። ዌንና ቨርጂንያ ልጃቸውና ሴት ልጇ እንዲህ በማድረጋቸው መጀመሪያ ላይ ቢበሳጩም በኋላ ግን አመለካከታቸውን ለውጠው መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመሩ። ዌን እንዲህ ብለዋል:- “ባለፉት 70 ዓመታት ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ካወቅነው ይበልጥ በእነዚህ ሦስት ወራት ውስጥ ብዙ መማር ችለናል! የአምላክ ስም ይሖዋ እንደሆነ ሰምተን አናውቅም ነበር፤ ስለ መንግሥቱም ሆነ ምድር ገነት ስለመሆኗም ምንም የምናውቀው ነገር አልነበረም።” ብዙም ሳይቆይ ቅን ልብ ያላቸው እነዚህ ባልና ሚስት በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘትና በአገልግሎት መካፈል ጀመሩ። ቨርጂንያ “ስለ እውነት ለሰው ሁሉ መናገር እንፈልጋለን” ብለዋል። በ2005 ሁለቱም በ80ዎቹ ዕድሜ ውስጥ እያሉ ተጠመቁ። እነዚህ ባልና ሚስት “እውነተኛ የክርስቲያን ቤተሰብ አግኝተናል” በማለት ተናግረዋል።

“ለመልካም ሥራ ሁሉ ብቁ” እንድትሆን የሚደረግልህን እርዳታ አድንቅ

12. ይሖዋ ምንጊዜም ለአገልጋዮቹ ምን ይሰጣቸዋል? ከሚሰጠው መመሪያስ ለመጠቀም ምን ማድረግ አለብን?

12 ይሖዋ ምንጊዜም ቢሆን አገልጋዮቹ ፈቃዱን እንዲያደርጉ ይረዳቸዋል። ለምሳሌ ኖኅ መርከቡን እንዴት መገንባት እንዳለበት ዝርዝር የሆኑ ግልጽ መመሪያዎች ተሰጥተውት ነበር። ኖኅ መርከቡን በድጋሚ ለመገንባት አጋጣሚ ስለማያገኝ ከመጀመሪያውም ቢሆን በትክክል ሊሠራው ይገባ ነበር። መርከቡም በትክክል ተሠርቷል። ይህ ሊሆን የቻለው ኖኅ ‘ሁሉን እግዚአብሔር እንዳዘዘው ስላደረገ’ ነው። (ዘፍጥረት 6:14-22) ዛሬም በተመሳሳይ ይሖዋ፣ አገልጋዮቹ ፈቃዱን ለማድረግ ብቁ እንዲሆኑ በሚገባ ያስታጥቃቸዋል። ዋነኛ ሥራችን በሰማይ ስለተቋቋመው የአምላክ መንግሥት የሚገልጸውን ምሥራች መስበክና የሚገባቸው ሰዎች የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ መርዳት ነው። ስለዚህ ልክ እንደ ኖኅ ስኬታማ ለመሆን መታዘዝ አለብን። ታዛዦች በመሆን ይሖዋ በቃሉና በድርጅቱ በኩል የሚሰጠንን መመሪያ መከተል ይኖርብናል።—ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20

13. ይሖዋ ሥልጠና የሚሰጠን በምን መንገድ ነው?

13 ይህን ሥራ ለማከናወን ዋነኛ መሣሪያችን የሆነውን የአምላክን ቃል እንዴት ‘በትክክል ማስረዳት’ እንደምንችል መማር አለብን። የአምላክ ቃል “ለማስተማር፣ ለመገሠጽ፣ ለማቅናት በጽድቅም መንገድ ለመምከር [ይጠቅማል]፤ ይኸውም የእግዚአብሔር ሰው ለመልካም ሥራ ሁሉ ብቁ ሆኖ እንዲገኝ ነው።” (2 ጢሞቴዎስ 2:15፤ 3:16, 17) በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበረው ሁሉ ዛሬም ይሖዋ በክርስቲያን ጉባኤ አማካኝነት ጠቃሚ ሥልጠና ይሰጠናል። በአሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ በሚገኙ 99,770 የሚያህሉ ጉባኤዎች ውስጥ የቲኦክራሲያዊ አገልግሎት ትምህርት ቤትና የአገልግሎት ስብሰባ በየሳምንቱ የሚከናወኑ ሲሆን እነዚህ ስብሰባዎችም ለስብከቱ ሥራ ይረዱናል። በእነዚህ አስፈላጊ ስብሰባዎች ላይ አዘውትረህ በመገኘትና የተማርከውን ተግባራዊ በማድረግ አድናቆትህን ታሳያለህ?—ዕብራውያን 10:24, 25

14. የይሖዋ አገልጋዮች እርሱን የማገልገል መብታቸውን እንደሚያደንቁ የሚያሳዩት እንዴት ነው? (ከገጽ 27 እስከ 30 ላይ የሚገኘውን ሪፖርት በመልስህ ውስጥ ማካተት ትችላለህ።)

14 በዓለም ዙሪያ የሚገኙ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የአምላክ ሕዝቦች በአገልግሎታቸው ጠንክረው በመሥራት ለሚያገኙት ሥልጠና አድናቆታቸውን ያሳያሉ። ለምሳሌ ያህል በ2006 የአገልግሎት ዓመት 6,741,444 የሚያህሉ የመንግሥቱ አስፋፊዎች በሁሉም የአገልግሎት ዘርፎች በመካፈል 1,333,966,199 ሰዓታት ያሳለፉ ሲሆን 6,286,618 የሚሆኑ ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ አስጠንተዋል። እነዚህ በዓለም አቀፉ ሪፖርት ላይ ከሰፈሩት የሚያበረታቱ አኃዞች ጥቂቶቹ ናቸው። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ወንድሞቻችን በጊዜያቸው ስለነበረው የስብከት ሥራ መስፋፋት መስማታቸው በጣም ያበረታታቸው እንደነበረ ሁሉ አንተም ጊዜ ወስደህ ይህንን ሪፖርት በመመልከት ማበረታቻ ማግኘት ትችላለህ።—የሐዋርያት ሥራ 1:15፤ 2:5-11, 41, 47፤ 4:4፤ 6:7

15. ማንኛውም ሰው ይሖዋን በሙሉ ነፍሱ እስካገለገለ ድረስ ተስፋ መቁረጥ የሌለበት ለምንድን ነው?

15 በርካታ የይሖዋ አገልጋዮች በየዓመቱ ለአምላክ የሚያቀርቡት ውዳሴ እርሱን የማወቅና ምሥክሮቹ የመሆን መብት በማግኘታቸው የሚሰማቸውን ጥልቅ አድናቆት የሚያንጸባርቅ ነው። (ኢሳይያስ 43:10) እውነት ነው፣ አንዳንድ በዕድሜ የገፉ ወይም የታመሙ አሊያም አቅመ ደካማ የሆኑ ወንድሞችና እህቶች የሚያቀርቡት የምሥጋና መሥዋዕት ከመበለቲቱ አነስተኛ ስጦታ ጋር ሊወዳደር ይችላል። ሆኖም ይሖዋና ልጁ በሙሉ ነፍሳቸው አምላክን የሚያገለግሉትን ማለትም የአቅማቸውን ሁሉ የሚያደርጉትን በጥልቅ እንደሚያደንቋቸው መርሳት የለብንም።—ሉቃስ 21:1-4፤ ገላትያ 6:4

16. አምላክ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የትኞቹን የማስተማሪያ መሣሪያዎች ሰጥቶናል?

16 ይሖዋ ለአገልግሎታችን ከሚሰጠን ሥልጠና በተጨማሪ በድርጅቱ በኩል ግሩም የሆኑ የማስተማሪያ መሣሪያዎች በማቅረብ ብቁ እንድንሆን ያስታጥቀናል። ከእነዚህም መካከል ከቅርብ አሥርተ ዓመታት ወዲህ የወጡት ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራው እውነት፣ በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ፣ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት እና ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የሚሉት መጻሕፍት ይገኙበታል። እነዚህን ዝግጅቶች ከልባቸው የሚያደንቁ ክርስቲያኖች በአገልግሎታቸው ጥሩ አድርገው ይጠቀሙባቸዋል።

የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለውን መጽሐፍ በሚገባ ተጠቀሙበት

17, 18. (ሀ) በአገልግሎት ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በተባለው መጽሐፍ ስትጠቀም የትኞቹን ክፍሎች ማጉላት ያስደስትሃል? (ለ) አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የሚለውን መጽሐፍ አስመልክቶ ምን ብሏል?

17 አሥራ ዘጠኝ ምዕራፎችና ጥልቀት ያለው ማብራሪያ የያዘ ተጨማሪ ክፍል ያካተተው ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለው መጽሐፍ ግልጽና ቀላል በሆነ መንገድ የተዘጋጀ በመሆኑ በአገልግሎት ከፍተኛ ጠቀሜታ እያበረከተ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ምዕራፍ 12 “አምላክን በሚያስደስት መንገድ መኖር” የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ያብራራል። ይህ ምዕራፍ ተማሪው እንዴት የአምላክ ወዳጅ መሆን እንደሚችል ይገልጻል፤ ብዙዎች ይህንን ጉዳይ ፈጽሞ አስበውበት አያውቁም ወይም እንዲህ ማድረግ የሚቻል አይመስላቸውም። (ያዕቆብ 2:23) ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስን ለማስጠናት የሚረዳው ይህ መጽሐፍ ምን ምላሽ እያገኘ ነው?

18 በአውስትራሊያ የሚገኝ አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ስለተባለው መጽሐፍ ሲናገር “የቤቱ ባለቤት ወዲያው በውይይቱ መካፈል እንዲጀምር የሚገፋፋ ማራኪ አቀራረብ አለው” ብሏል። በዚህ መጽሐፍ መጠቀም በጣም ቀላል በመሆኑ “ብዙ የመንግሥቱ አስፋፊዎች ይበልጥ በልበ ሙሉነት ማገልገልና በስብከቱ ሥራ መደሰት ችለዋል። አንዳንዶች ይህን ጽሑፍ ‘ወርቅ የሆነ መጽሐፍ’ ብለው መጥራታቸው የሚያስገርም አይደለም!” በማለት አክሎ ተናግሯል።

19-21. የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለው መጽሐፍ ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ የሚያሳዩ ተሞክሮዎች ተናገር።

19 በጉያና፣ አንድ አቅኚ ከቤት ወደ ቤት ሲያገለግል ያገኛት ሴት “አንተን የላከህ አምላክ መሆን አለበት” አለችው። ይህች ሴት ከአንድ ሰው ጋር ትኖር የነበረ ቢሆንም ግለሰቡ እርሷንም ሆነ ሁለት ትንንሽ ልጆቿን ትቷቸው ከሄደ ብዙም አልቆየም። አቅኚውም የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ከተባለው መጽሐፍ ላይ ምዕራፍ አንድን አወጣና “አምላክ ስለሚደርስብን ግፍ ምን ይሰማዋል?” በሚለው ንዑስ ርዕስ ሥር የሚገኘውን አንቀጽ 11ን አነበበላት። ይህ ወንድም “የቀረበው ነጥብ ልቧን ስለነካት ወደ ሱቋ ጀርባ ሄዳ ስቅስቅ ብላ አለቀሰች” በማለት ተናግሯል። ይህች ሴት በአካባቢዋ ከምትገኝ እህት ጋር መጽሐፍ ቅዱስን በቋሚነት እንድታጠና የቀረበላትን ግብዣ የተቀበለች ሲሆን ጥሩ እድገትም እያደረገች ነው።

20 በስፔን የሚኖረው ሆሴ ባለቤቱን በመኪና አደጋ አጥቷል። አደገኛ ዕፅ በመውሰድ ሐዘኑን ለመርሳት ይሞክር የነበረ ከመሆኑም በላይ የሥነ ልቦና ሐኪሞች እርዳታ ያደርጉለት ነበር። ይሁን እንጂ እነዚህ ሐኪሞች ሆሴን በጣም ያስጨንቀው የነበረውን “አምላክ ባለቤቴ እንድትሞት የፈቀደው ለምንድን ነው?” የሚለውን ጥያቄ ሊመልሱለት አልቻሉም። አንድ ቀን ሆሴ አብሮት ከሚሠራ ፍራንቼስክ ከተባለ ሰው ጋር ውይይት አደረገ። ፍራንቼስክም የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በተባለው መጽሐፍ ምዕራፍ 11 ላይ እንዲወያዩ ሐሳብ አቀረበለት፤ ምዕራፉ “አምላክ በሰው ልጆች ላይ መከራ እንዲደርስ የፈቀደው ለምንድን ነው?” የሚል ርዕስ አለው። በዚህ ርዕስ ሥር የሚገኘው ቅዱስ ጽሑፋዊ ማብራሪያ እንዲሁም ስለ አንድ አስተማሪና ተማሪ የቀረበው ምሳሌ ሆሴን በጥልቅ ነካው። ሆሴ በቁም ነገር ማጥናት የጀመረ ሲሆን በወረዳ ስብሰባ ላይም ተገኝቷል፤ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ በአካባቢው በሚገኝ የመንግሥት አዳራሽ በሚደረጉት ስብሰባዎች ላይ ይገኛል።

21 በፖላንድ የሚኖረውና በንግድ ሥራ ላይ የተሰማራው ሮማን የተባለ የ40 ዓመት ሰው ለአምላክ ቃል አክብሮት ነበረው። ይሁን እንጂ በሥራ በጣም የተጠመደ ስለነበር በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱ ብዙ መግፋት አልቻለም። ያም ቢሆን በአውራጃ ስብሰባ ላይ የተገኘ ሲሆን በስብሰባው ላይም የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለውን መጽሐፍ ወሰደ። ከዚያ በኋላ ሮማን ትልቅ ለውጥ አደረገ። “በዚህ መጽሐፍ አማካኝነት መሠረታዊ ስለሆኑት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ሁሉ የተሟላ ግንዛቤ አግኝቻለሁ” ብሏል። ሮማን በአሁኑ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን በቋሚነት እያጠና ሲሆን ጥሩ እድገትም እያደረገ ነው።

አድናቆታችሁ እየጨመረ ይሂድ

22, 23. ከፊታችን ያለውን ተስፋ እንደምናደንቅ ማሳየታችንን መቀጠል የምንችለው እንዴት ነው?

22 “መዳናችን ቀርቧል!” በተባለው አስደሳች የአውራጃ ስብሰባ ላይ እንደተገለጸው እውነተኛ ክርስቲያኖች አምላክ ቃል የገባውንና በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት የሚፈጸመውን “የዘላለም መዳን” [NW] ለማግኘት ይናፍቃሉ። “ሕያው እግዚአብሔርን እንድናመልክ ኅሊናችንን ከምውት ሥራ” ከማንጻት የተሻለ ለዚህ ውድ ተስፋ ያለንን ልባዊ አድናቆት ለመግለጽ የሚያስችለን መንገድ የለም።—ዕብራውያን 9:12, 14

23 ሰዎች የራሳቸውን ፍላጎት እንዲያስቀድሙ ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ከፍተኛ ተጽዕኖ እየተደረገባቸው ባለበት በዚህ ወቅት ከስድስት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች በታማኝነት አምላክን የሚያገለግሉ መሆኑ በእርግጥም ተአምር ነው። ከዚህም በላይ የይሖዋ አገልጋዮች አምላክን የማገልገል ክብር ማግኘታቸውን በጥልቅ እንደሚያደንቁት የሚያሳይ ነው፤ ‘ለጌታ የሚደክሙት በከንቱ እንዳልሆነ’ ያውቃሉ። ይህ የአድናቆት መንፈስ እየጨመረ እንዲሄድ ምኞታችን ነው!—1 ቆሮንቶስ 15:58፤ መዝሙር 110:3

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• አምላክንና መንፈሳዊ ዝግጅቶቹን ማድነቅን በተመለከተ ከመዝሙራዊው ምን ትምህርት እናገኛለን?

• በዛሬው ጊዜ ሐጌ 2:7 ፍጻሜውን እያገኘ ያለው እንዴት ነው?

• ይሖዋ፣ አገልጋዮቹ ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዲያገለግሉት እያስታጠቃቸው ያለው እንዴት ነው?

• ለይሖዋ ጥሩነት ያለህን አድናቆት ለማሳየት ምን ማድረግ ትችላለህ?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[ከገጽ 27-30 የሚገኝ ሰንጠረዥ]

የ2006 የአገልግሎት ዓመት የይሖዋ ምሥክሮች ዓለም አቀፍ ሪፖርት

(መጽሔቱን ተመልከት)

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ ፈቃዱን ለማድረግ ብቁ እንድንሆን በሚገባ ያስታጥቀናል