እውነቱን መናገር አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
እውነቱን መናገር አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
ማንፍሬድ በ18 ዓመቱ በአንድ መሥሪያ ቤት ውስጥ ይሠለጥን ነበር። a የሚሠራበት ኩባንያ እርሱና ሌሎች በርካታ ሠልጣኞች በሳምንት ሁለት ቀን በሙያ ኮሌጅ ውስጥ እንዲማሩ ዝግጅት አደረገላቸው። አንድ ቀን ሠልጣኞቹ ከተለመደው ሰዓት ቀደም ብለው ተለቀቁ። በኩባንያው ደንብ መሠረት ሠልጣኞቹ ወደ ሥራ ገበታቸው መመለስ የነበረባቸው ቢሆንም ከማንፍሬድ በስተቀር ሁሉም ለመዝናናት ሄዱ። በአጋጣሚ ደግሞ የሠልጣኞቹን ጉዳይ የሚከታተለው የመሥሪያ ቤቱ ኃላፊ ወደሚሠሩበት ቢሮ መጣ። ኃላፊው ማንፍሬድን ሲመለከት “ዛሬ ትምህርት የለም እንዴ? ሌሎቹ ሠልጣኞችስ ወዴት ሄዱ?” በማለት ጠየቀው። ማንፍሬድ ምን መልስ መስጠት ይኖርበታል?
የዚህ ዓይነት አጣብቂኝ ሁኔታ ብዙ ጊዜ ያጋጥማል። ማንፍሬድ እውነቱን መናገር አለበት? ወይስ የሌሎቹን ሠልጣኞች ጥፋት ለመሸፈን ሲል እውነቱን መደበቅ ይኖርበታል? እውነቱን ቢናገር ሌሎቹ ችግር ውስጥ ከመግባታቸውም በላይ ማንፍሬድ ሊጠላ ይችላል። በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ሥር ውሸት መናገር ስህተት ነው? አንተ ብትሆን ኖሮ ምን ታደርግ ነበር? ማንፍሬድ ምን እንዳደረገ በኋላ እንመለስበታለን። መጀመሪያ ግን፣ እውነቱን መናገር አለብን ወይስ የለብንም የሚለውን ጉዳይ መወሰን በሚኖርብን ጊዜ ልናስብባቸው የሚገቡ ነጥቦችን እስቲ እንመልከት።
እውነትና ሐሰት—መሠረታዊ ግጭት
በሰው ዘር ታሪክ መጀመሪያ ላይ ውሸት የሚባል ነገር አልነበረም። ሐቁን የሚያዛባ፣ እውነቱን አጣምሞ የሚያቀርብ ወይም የተሳሳተ መረጃ የሚሰጥ አካል አልነበረም። ፈጣሪያችን የሆነው ይሖዋ “የእውነት አምላክ” ነው። ቃሉ እውነት ከመሆኑም ሌላ እርሱም አይዋሽም፤ ይሖዋ ውሸትንና ውሸታሞችንም ይጠላል።—መዝሙር 31:5፤ ዮሐንስ 17:17፤ ቲቶ 1:2
ይህ ከሆነ ታዲያ ውሸት ከየት መጣ? ኢየሱስ፣ እርሱን ለመግደል ይፈልጉ ለነበሩት ሃይማኖታዊ ተቃዋሚዎቹ እንደሚከተለው ብሎ በተናገረ ጊዜ ትክክለኛውን መልስ ሰጥቶናል:- “እናንተ የአባታችሁ የዲያብሎስ ናችሁ፤ የአባታችሁንም ፍላጎት ለመፈጸም ትሻላችሁ። እርሱ ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ ነበር፤ በእርሱ ዘንድ እውነት ስለሌለ በእውነት አልጸናም፤ እርሱ ሐሰተኛ፣ የሐሰትም አባት በመሆኑ ሐሰትን ሲናገር፣ የሚናገረው ከራሱ አፍልቆ ነው።” (ዮሐንስ 8:44) ኢየሱስ እንዲህ ሲል በኤድን የአትክልት ቦታ ስለተከናወነው ነገር መናገሩ እንደሆነ ግልጽ ነው። ሰይጣን የመጀመሪያዎቹን ሰብዓዊ ባልና ሚስት በማታለል በአምላክ ላይ እንዲያምጹና በኃጢአት እንዲወድቁ ያደረጋቸው ሲሆን ይህ ደግሞ ሞት አስከትሎባቸዋል።—ዘፍጥረት 3:1-5፤ ሮሜ 5:12
ከኢየሱስ ንግግር በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው ውሸትን ያመነጨው ‘የሐሰት አባት’ የሆነው ሰይጣን ነው። ዛሬም ቢሆን ውሸትን በዋነኝነት የሚያስፋፋው እርሱ ሲሆን ‘ዓለምን ሁሉ እያሳተ’ ነው። ባለንበት ዘመን ውሸት በመስፋፋቱ ምክንያት በሰው ዘሮች ላይ እየደረሰ ላለው ጉዳት ዋነኛው ተጠያቂ ሰይጣን ነው።—ራእይ 12:9
ሰይጣን ዲያብሎስ ያስጀመረው በእውነትና በሐሰት መካከል ያለው መሠረታዊ ግጭት እስከ ዘመናችን ድረስ ዘልቋል። ይህ ሁኔታ የማይነካው የኅብረተሰብ ክፍል ወይም ግለሰብ የለም። የአንድ ሰው አኗኗር በዚህ ግጭት ውስጥ በየትኛው ወገን እንደተሰለፈ ያሳያል። በአምላክ ጎን የተሰለፉ ሰዎች ሕይወታቸውን የሚመሩት የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ እውነት መሠረት ነው። አንድ ሰው የእውነትን መንገድ የማይከተል ከሆነ ግን ‘መላው ዓለም በክፉው ሥር’ በመሆኑ አውቆም ሆኖ ሳያውቅ በሰይጣን እጅ ይወድቃል።—1 ዮሐንስ 5:19፤ ማቴዎስ 7:13, 14
ሰዎች የሚዋሹት ለምንድን ነው?
“መላው ዓለም” በሰይጣን ቁጥጥር ሥር መሆኑን ማወቃችን በርካታ ሰዎች ለምን እንደሚዋሹ ለመገንዘብ ይረዳናል። ይሁን እንጂ ‘“የሐሰትም አባት” የሆነው ሰይጣን እንዲህ ያደረገው ለምንድን ነው?’ ብለን እንጠይቅ ይሆናል። ይሖዋ የመጀመሪያዎቹን ባልና ሚስት ጨምሮ የፍጥረታቱ በሙሉ ሉዓላዊ ገዢ የመሆን መብት እንዳለው ሰይጣን ያውቃል። ያም ሆኖ ግን ሰይጣን ለእርሱ የማይገባውን ይህን የላቀና ልዩ የሆነ ቦታ ተመኘ። በስግብግብነትና በራስ ወዳድነት ተነሳስቶ የይሖዋን ቦታ አላግባብ ለመያዝ አሴረ። ሰይጣን ይህን ዓላማውን ለማሳካት ሲል በውሸትና በማታለል ተጠቀመ።—1 ጢሞቴዎስ 3:6
በዛሬው ጊዜስ? በርካታ ሰዎች እንዲዋሹ የሚገፋፋቸው ስግብግብነትና ራስ ወዳድነት ነው ቢባል አትስማማም? ስግብግብ በሆነው የንግዱ ዓለም፣ በሙስና በተሞላው የፖለቲካ ሥርዓትና በሐሰት ሃይማኖት ውስጥ ማታለል፣ ውሸት፣ ሌሎችን መጠቀሚያ ማድረግና ማጭበርበር ተስፋፍቷል። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? ሰዎች ከሌሎች ልቀው ለመታየት አሊያም የማይገባቸውን ሀብት፣ ሥልጣን ወይም ቦታ ለማግኘት ስለሚመኙ አይደለም? የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ጠቢቡ ሰሎሞን “ሀብት ለማግኘት የሚጣደፍ ግን ንጹሕ ሆኖ አይቀጥልም” በማለት አስጠንቅቋል። (ምሳሌ 28:20 NW) ሐዋርያው ጳውሎስም “የገንዘብ ፍቅር የክፋት ሁሉ ሥር ነው” ሲል ጽፏል። (1 ጢሞቴዎስ 6:10) ሥልጣንም ሆነ ከፍተኛ ቦታ ለማግኘት ከመጠን በላይ መመኘትን በተመለከተም ይኸው አባባል ይሠራል።
ሰዎች እንዲዋሹ የሚያደርጋቸው ሌላው ምክንያት ደግሞ ፍርሃት ነው። እውነቱን ቢናገሩ የሚመጣውን መዘዝ በመፍራት ወይም ሌሎች ምን ይሉኛል በማለት ይዋሻሉ። በሰዎች ዘንድ ተወዳጅ ለመሆን ወይም ተቀባይነት ለማግኘት መፈለግ ያለ ነገር ነው። ይሁን እንጂ ይህ ፍላጎት ብዙዎች ጉድለቶቻቸውን እንዲሸፋፍኑ፣ እምብዛም የማይማርኩ እውነታዎችን እንዲደብቁ ወይም ሌሎች ስለ እነርሱ ጥሩ ግምት እንዲኖራቸው ለማድረግ ሲሉ በጥቂቱም ቢሆን እውነቱን አዛብተው እንዲያቀርቡ ሊያነሳሳቸው ይችላል። በእርግጥም ሰሎሞን “ሰውን መፍራት ወጥመድ ነው፤ በእግዚአብሔር የሚታመን ግን በሰላም ይኖራል” ብሎ መጻፉ ተገቢ ነው።—ምሳሌ 29:25
ለእውነት አምላክ ታማኝ መሆን
በመግቢያችን ላይ የጠቀስነው ማንፍሬድ ለመሥሪያ ቤቱ ኃላፊ ምን መልስ ሰጠው? ማንፍሬድ እንዲህ በማለት እውነቱን ተናገረ:- “መምህሩ ቀደም ብሎ ስለለቀቀን ወደ ሥራዬ ተመለስኩ፤ ስለ ሌሎቹ ግን መናገር አልችልም። ምናልባት አንተ ልትጠይቃቸው ትችላለህ።”
ማንፍሬድ በሌሎቹ ሠልጣኞች ዘንድ ተወዳጅነት የሚያተርፍለት የብልጠት መልስ በመስጠት እውነቱን መደበቅ ይችል ነበር። ሆኖም እንዲህ ያላደረገበት ምክንያት
ነበረው። ማንፍሬድ የይሖዋ ምሥክር መሆኑ ሐቁን እንዲናገር ያደረገው ሲሆን ይህ ደግሞ ንጹሕ ሕሊና እንዲኖረው ረድቶታል። ከዚህም በተጨማሪ በአሠሪው ዘንድ አመኔታ ማትረፍ ችሏል። በተለምዶ ሠልጣኞች ጌጣጌጥ በሚገኝበት ቦታ እንዲሠሩ የማይፈቀድላቸው ቢሆንም እርሱ ግን ሠልጣኝ እያለ በዚህ ክፍል እንዲሠራ ተመደበ። ይህ ከሆነ ከ15 ዓመታት ገደማ በኋላ ማንፍሬድ በድርጅቱ ውስጥ በኃላፊነት ቦታ ሲሾም ይኸው ኃላፊ ‘እንኳን ደስ አለህ’ ለማለት የደወለለት ሲሆን ከዓመታት በፊት እውነቱን የተናገረበትን ጊዜም አስታወሰው።ይሖዋ የእውነት አምላክ በመሆኑ ከእርሱ ጋር የቀረበ ዝምድና ለመመሥረት የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ‘ውሸትን አስወግዶ እውነትን መናገር’ አለበት። የአምላክ አገልጋይ የሆነ ሰው እውነትን መውደድ አለበት። ጠቢቡ ሰው “ታማኝ ምስክር አይዋሽም” በማለት ጽፏል። ይሁን እንጂ ውሸት ምንድን ነው?—ኤፌሶን 4:25፤ ምሳሌ 14:5
ውሸት ምንድን ነው?
ውሸት፣ እውነት ያልሆነን ነገር ሁሉ ያመለክታል፤ እውነት ያልሆነ ነገር ሁሉ ግን ውሸት አይደለም። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? አንድ መዝገበ ቃላት፣ ውሸት የሚባለው “ሌሎችን ለማታለል ሲሉ እውነት እንዳልሆነ የሚያውቁትን ወይም የሚያምኑበትን ነገር መናገር” እንደሆነ ገልጿል። አዎን፣ ውሸት አንድን ሰው ለማታለል በማሰብ የምንናገረውን ነገር ሁሉ ይጨምራል። በመሆኑም ባለማወቅ እውነት ያልሆነ ነገር መናገር መዋሸት አይደለም፤ ለምሳሌ አንድ ሰው ተሳስቶ ትክክል ያልሆነ ሐሳብ ወይም አኃዛዊ መረጃ ቢያስተላልፍ ዋሽቷል ሊባል አይችልም።
ከዚህም በተጨማሪ መረጃ የሚጠይቀን ግለሰብ ሁሉንም ነገር የማወቅ መብት ያለው መሆን አለመሆኑን ማሰብ ይኖርብናል። ለምሳሌ፣ ለማንፍሬድ ጥያቄውን ያቀረበለት የሌላ ድርጅት ኃላፊ ቢሆን ኖሮ ማንፍሬድ ሁሉንም ነገር የመንገር ግዴታ ይኖርበት ነበር? ይህ ኃላፊ እንዲህ ያለውን መረጃ የማግኘት መብት ስለሌለው ማንፍሬድም መልስ የመስጠት ግዴታ አይኖርበትም። እርግጥ በዚህ ጊዜም ቢሆን ማንፍሬድ ውሸት ቢናገር ስህተት ነበር።
ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ረገድ ምን ምሳሌ ትቶልናል? በአንድ ወቅት፣ ደቀ መዛሙርቱ ያልሆኑ ሰዎች “ከዚህ ወደ ይሁዳ ሂድ” በማለት ስለ ጉዞው ሐሳብ ሰጥተውት ነበር። ኢየሱስ ምን ምላሽ ሰጠ? “እናንተ ወደ በዓሉ ሂዱ፤ ለእኔ ትክክለኛው ጊዜ ስላልደረሰ ወደ በዓሉ አልሄድም” በማለት ወደ ኢየሩሳሌም እንደማይሄድ ገለጸላቸው። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን ኢየሱስ ለበዓሉ ወደ ኢየሩሳሌም ተጓዘ። ታዲያ እንደዚያ ብሎ የመለሰላቸው ለምን ነበር? እነዚህ ሰዎች ኢየሱስ የት እንደሚሄድ የማወቅ መብት አልነበራቸውም። ስለዚህ ኢየሱስ ውሸት ባይናገርም ሰዎቹ በእርሱም ሆነ በተከታዮቹ ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ ሲል የተሟላ መልስ ከመስጠት ተቆጥቧል። ይህን በማለቱ አልዋሸም፤ ምክንያቱም ሐዋርያው ጴጥሮስ ስለ እርሱ ሲጽፍ “እርሱ ኀጢአት አላደረገም፤ በአፉም ተንኰል አልተገኘበትም” ብሏል።—ዮሐንስ 7:1-13፤ 1 ጴጥሮስ 2:22
ስለ ጴጥሮስስ ምን ለማለት ይቻላል? ኢየሱስ በተያዘበት ሌሊት ጴጥሮስ ኢየሱስን እንደማያውቀው በመናገር ማቴዎስ 26:69-75፤ የሐዋርያት ሥራ 4:18-20፤ 5:27-32፤ ያዕቆብ 3:2
ሦስት ጊዜ አልዋሸም? አዎን፣ ጴጥሮስ ሰውን በመፍራት ዋሽቷል። ሆኖም ወዲያውኑ ‘ምርር ብሎ በማልቀስ’ ንስሐ በመግባቱ ኃጢአቱ ይቅር ተብሎለታል። ከዚህም በላይ ጴጥሮስ ከስህተቱ ተምሯል። ከጥቂት ቀናት በኋላ በሕዝብ ፊት ስለ ኢየሱስ የተናገረ ሲሆን በኢየሩሳሌም የሚገኙ የአይሁድ ባለ ሥልጣናት መስበኩን እንዲያቆም ቢያስፈራሩትም ስለ ኢየሱስ ከመናገር ወደኋላ አላለም። ጴጥሮስ ለጊዜው ቢሰናከልም ወዲያው አቋሙን መልሶ ማስተካከሉ ለሁላችንም ማበረታቻ ይሆነናል። ምክንያቱም ማናችንም ብንሆን በቀላሉ ባሉብን ድክመቶች ልንሸነፍና በንግግራችንም ሆነ በድርጊታችን ልንሰናከል እንችላለን።—እውነት ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል
ምሳሌ 12:19 “እውነት የሚናገሩ ከንፈሮች ለዘላለም ጸንተው ይኖራሉ፤ ሐሰተኛ አንደበት ግን ለቅጽበት ያህል ብቻ ነው” ይላል። በእርግጥም እውነተኛ ንግግር ዘላቂ ነው። ሰዎች እርስ በርስ ያላቸው ግንኙነት አስደሳችና ዘላቂ የሚሆነው እውነትን ሲናገሩ እንዲሁም ከንግግራቸው ጋር ተስማምተው ሲኖሩ ነው። እውነት መናገር በአሁኑ ጊዜም በረከት ያስገኛል። እነዚህ በረከቶች፣ ንጹሕ ሕሊና ማግኘትንና መልካም ስም ማትረፍን እንዲሁም በትዳር ውስጥ፣ በቤተሰብና በጓደኛሞች መካከል ሌላው ቀርቶ በሥራ ቦታ እንኳ ጥሩ ግንኙነት መመሥረትን ያካትታሉ።
በሌላ በኩል ግን ውሸት ውሎ አድሮ መጋለጡ አይቀርም። ሐሰተኛ ምላስ ለተወሰነ ጊዜ ማታለል ቢችልም አይዘልቅም። በተጨማሪም የእውነት አምላክ የሆነው ይሖዋ ውሸትንም ሆነ ውሸታሞችን የሚታገስበት ጊዜ ያበቃል። ይሖዋ፣ ዓለምን ሁሉ እያሳተ ያለውና የሐሰት አባት የሆነው ሰይጣን ዲያብሎስ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ እንደሚያስወግደው መጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ሰጥቷል። በቅርቡ ይሖዋ ውሸትንም ሆነ ውሸታሞችን ያጠፋል።—ራእይ 21:8
“እውነትን የሚናገሩ ከንፈሮች” ለዘላለም ጸንተው ሲኖሩ እንዴት ያለ እፎይታ ይሆናል!
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a እውነተኛ ስሙ አይደለም።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በርካታ ሰዎች እንዲዋሹ የሚገፋፋቸው ስግብግብነትና ራስ ወዳድነት ነው
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ውሸት፣ እውነት ያልሆነን ነገር ሁሉ ያመለክታል፤ እውነት ያልሆነ ነገር ሁሉ ግን ውሸት አይደለም
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጴጥሮስ ኢየሱስን መካዱ ምን ያስተምረናል?
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እውነትን መናገር አስደሳችና ዘላቂ ግንኙነት ለመመሥረት ያስችላል