በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እውነት መናገር—ከሌሎች ብቻ የምንጠብቀው ባሕርይ ነው?

እውነት መናገር—ከሌሎች ብቻ የምንጠብቀው ባሕርይ ነው?

እውነት መናገር—ከሌሎች ብቻ የምንጠብቀው ባሕርይ ነው?

“ውሸትን እጠላለሁ፤ ሰዎች ሲዋሹኝ አልወድም!” ይህን የተናገረችው አንዲት የ16 ዓመት ወጣት ናት። አብዛኞቻችን እንደዚህች ወጣት ይሰማናል። በቃል የሚነገረንም ሆነ የምናነበው ነገር እውነት እንዲሆን እንፈልጋለን። ይሁን እንጂ እኛ ለሌሎች እውነቱን እንናገራለን?

በጀርመን በተካሄደ አንድ ጥናት ላይ ከተካፈሉት ሰዎች አብዛኞቹ፣ “ራስንም ሆነ ሌሎችን ከጉዳት ለመጠበቅ ሲባል ቀላል በሆኑ ጉዳዮች ላይ መዋሸት ስህተት እንዳልሆነ ያስባሉ፤ እንዲያውም ከሰዎች ጋር ተስማምቶ ለመኖር ይህን ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ” ይሰማቸዋል። አንዲት ጋዜጠኛ “ሁልጊዜ እውነቱን ብቻ መናገር ድንቅ ሐሳብ ቢሆንም አሰልቺ ነው” ስትል ጽፋለች።

ሌሎች እውነቱን እንዲነግሩን የምንፈልግ ቢሆንም እኛ ግን አንዳንድ ጊዜ ለመዋሸት በቂ ምክንያት እንዳለን ይሰማናል? እውነቱን መናገር አለመናገራችን ለውጥ ያመጣል? ውሸት መናገር ምን መዘዝ ያስከትላል?

ውሸት የሚያስከትለው ጉዳት

ውሸት የሚያስከትላቸውን ጉዳቶች እንመልከት። መዋሸት በትዳር ጓደኛሞችና በቤተሰብ አባላት መካከል መተማመን እንዳይኖር ያደርጋል። ያልተረጋገጠ ወሬ የአንድን ሰው ስም ያጎድፋል። ሠራተኞች ማጭበርበራቸው የድርጅቱን ወጪ ስለሚጨምረው የሸቀጦች ዋጋ ይንራል። ግብር ከፋዮች ገቢያቸውን በትክክል አለማስመዝገባቸው መንግሥት ኅብረተሰቡን የሚጠቅም የልማት ሥራ ለማከናወን የሚያስፈልገውን ገቢ እንዲያጣ ያደርገዋል። ተመራማሪዎች ሐቀኝነት የጎደላቸው መረጃዎች ማቅረባቸው በሙያቸው ስኬታማ መሆን የሚችሉበትን አጋጣሚ ያሳጣቸዋል፤ የሚሠሩበትን ተቋም መልካም ስምም ያጎድፋል። አንዳንድ ጠንቃቃ ያልሆኑ ሰዎች በአጭር ጊዜ ለመክበር እንደሚያስችሉ በሚነገርላቸው ሐቀኝነት የጎደላቸው ዘዴዎች በመታለላቸው ዕድሜያቸውን ሙሉ ያጠራቀሙትን ጥሪት ከማጣታቸውም በላይ ለከፋ ጉዳት ተዳርገዋል። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ አምላክ ከሚጸየፋቸው ነገሮች መካከል “ሐሰተኛ ምላስ” እና “በውሸት ላይ ውሸት የሚጨምር ሐሰተኛ ምስክር” እንደሚገኙበት መጥቀሱ ምንም አያስገርምም!—ምሳሌ 6:16-19

ብዙዎች የሚዋሹ መሆኑ በግለሰቦችም ሆነ በማኅበረሰቡ ላይ ጉዳት ያስከትላል። ይህን እውነታ ማንም ሰው አይክደውም። ታዲያ ሰዎች ሆን ብለው የሚዋሹት ለምንድን ነው? እውነት ያልሆነ ንግግር ሁሉ ውሸት ነው? በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ለእነዚህና ለሌሎች ጥያቄዎች መልስ እናገኛለን።

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መዋሸት በትዳር ጓደኛሞች መካከል መተማመን እንዳይኖር ያደርጋል