በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከልጆች ምን ልትማር ትችላለህ?

ከልጆች ምን ልትማር ትችላለህ?

ከልጆች ምን ልትማር ትችላለህ?

“ለምን እንደ ልጅ ትሆናለህ?” አዋቂዎች እንደዚህ ብንባል ቅር መሰኘታችን አይቀርም። ትናንሽ ልጆች ደስ የሚሉን ቢሆንም ከዕድሜ ጋር የሚመጣው ብስለት፣ ተሞክሮና ጥበብ እንደሚጎድላቸው የታወቀ ነው።—ኢዮብ 12:12

ይሁንና ኢየሱስ በአንድ ወቅት ለደቀ መዛሙርቱ “እውነት እላችኋለሁ፣ ካልተለወጣችሁ እንደ ሕፃናት ካልሆናችሁ ፈጽሞ ወደ መንግሥተ ሰማይ አትገቡም” ብሏቸው ነበር። (ማቴዎስ 18:3) ኢየሱስ ምን ማለቱ ነበር? ሕፃናት፣ አዋቂዎች ሊኮርጇቸው የሚገቡ ምን ባሕርያት አሏቸው?

እንደ ሕፃናት ያለ ትሕትና ማዳበር

ኢየሱስ ከላይ ያለውን እንዲናገር ያደረገውን ሁኔታ እንመልከት። ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ረጅም ጉዞ ካደረጉ በኋላ ቅፍርናሆም ሲደርሱ ክርስቶስ “በመንገድ ላይ የምትከራከሩት ስለ ምን ነበር?” ብሎ ጠየቃቸው። ደቀ መዛሙርቱም ከመካከላቸው ማን እንደሚበልጥ እየተከራከሩ ስለነበር አፍረው ዝም አሉ። በኋላ ግን ደፈር ብለው “በመንግሥተ ሰማይ ከሁሉ የሚበልጥ ማን ነው?” በማለት ኢየሱስን ጠየቁት።—ማርቆስ 9:33, 34፤ ማቴዎስ 18:1

ደቀ መዛሙርቱ ከኢየሱስ ጋር ወደ ሦስት ዓመት ገደማ ካሳለፉ በኋላ ስለ ሥልጣን ወይም ቦታ መከራከራቸው አስገራሚ ይመስል ይሆናል። ሆኖም ደቀ መዛሙርቱ ያደጉት ለእነዚህ ነገሮች ትልቅ ቦታ ይሰጥ በነበረው በአይሁድ ሃይማኖት ውስጥ ነው። ይህ ዓይነቱ አስተዳደግ ከሰብዓዊ አለፍጽምና ጋር ተዳምሮ በደቀ መዛሙርቱ አስተሳሰብ ላይ ተጽዕኖ አሳድሮ መሆን አለበት።

ኢየሱስ አረፍ ካለ በኋላ ደቀ መዛሙርቱን ወደ እርሱ ጠርቶ “መጀመሪያ ለመሆን የሚፈልግ፣ ከሁሉ መጨረሻና የሁሉም አገልጋይ ይሁን” አላቸው። (ማርቆስ 9:35) ደቀ መዛሙርቱ በዚህ ንግግር በጣም ሳይገረሙ አልቀሩም። የኢየሱስ ንግግር አይሁዳውያን ስለ ታላቅነት ከነበራቸው አመለካከት ጋር በቀጥታ የሚጋጭ ነበር! ከዚያም ኢየሱስ አንድ ሕፃን ልጅ ጠርቶ አጠገቡ ካቆመው በኋላ ሕፃኑን እቅፍ አድርጎ እንዲህ በማለት ነጥቡን የሚያጠናክር ሐሳብ ተናገረ:- “እውነት እላችኋለሁ፣ ካልተለወጣችሁ እንደ ሕፃናት ካልሆናችሁ ፈጽሞ ወደ መንግሥተ ሰማይ አትገቡም። ስለዚህ በመንግሥተ ሰማይ ከሁሉ የሚበልጥ እንደዚህ ሕፃን ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ነው።”—ማቴዎስ 18:3, 4

ኢየሱስ ትሕትናን በተመለከተ በምሳሌ የተደገፈ ግሩም ትምህርት ሰጥቷቸዋል! እስቲ ሁኔታውን በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር። የተወሰኑ አዋቂዎች በአንድ ሕፃን ዙሪያ ተሰብስበዋል። ሰዎቹ ሕፃኑን ትኩር ብለው እየተመለከቱት ነው። ሕፃኑ ምን ያህል ሊፈራ እንደሚችል አስብ! ያም ሆኖ በቀላሉ ሌሎችን ያምናል። ይህ ትንሽ ልጅ የፉክክር ዝንባሌም ሆነ ክፋት የለውም! ታዛዥ ከመሆኑም በላይ የኩራት መንፈስ አይታይበትም! አዎን፣ ይህ ሕፃን አምላካዊ ባሕርይ የሆነውን ትሕትናን ግሩም አድርጎ ያንጸባርቃል።

ኢየሱስ ማስተላለፍ የፈለገው ነጥብ ግልጽ ነው። ሁላችንም የአምላክን መንግሥት ለመውረስ ከፈለግን እንደ ሕፃናት ትሑቶች መሆን አለብን። እንደ ቤተሰብ በሆኑት እውነተኛ ክርስቲያኖች መካከል የፉክክር መንፈስ ወይም ኩራት ቦታ የላቸውም። (ገላትያ 5:26) ሰይጣን ዲያብሎስ መጀመሪያውኑም ቢሆን በአምላክ ላይ እንዲያምጽ ያነሳሱት እነዚህ ባሕርያት ነበሩ። ይሖዋ እነዚህን ባሕርያት መጥላቱ ምንም አያስገርምም!—ምሳሌ 8:13

እውነተኛ ክርስቲያኖች ሰዎችን ለማገልገል እንጂ በሌሎች ላይ ለመሠልጠን አይፈልጉም። አንድ ሥራ ምንም ያህል የማያስደስት ቢሆን ወይም የምናገለግለው ሰው የቱንም ያህል ዝቅ ያለ ቢመስል እውነተኛ ትሕትና ሌሎችን እንድናገለግል ያነሳሳናል። ይህ ዓይነቱ ትሕትና የተሞላበት አገልግሎት የተትረፈረፈ በረከት ያስገኛል። ኢየሱስ “ከእነዚህ ሕፃናት አንዱን በስሜ የሚቀበል ሁሉ እኔን ይቀበላል፤ እኔንም የሚቀበለኝ ሁሉ የሚቀበለው እኔን ሳይሆን የላከኝን ነው” ብሏል። (ማርቆስ 9:37) ልግስና የሚንጸባረቅበት የትሕትና መንፈስ በማዳበር ሕፃናትን መኮረጃችን በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ታላቅ ከሆነው አካልና ከልጁ ጋር አንድነት እንዲኖረን ያደርጋል። (ዮሐንስ 17:20, 21፤ 1 ጴጥሮስ 5:5) ከዚህም በላይ በመስጠት የሚገኘውን ደስታ እናጭዳለን። (የሐዋርያት ሥራ 20:35) እንዲሁም በአምላክ ሕዝቦች መካከል በግልጽ ለሚታየው ሰላምና አንድነት የበኩላችንን አስተዋጽኦ በማድረጋችን እርካታ እናገኛለን።—ኤፌሶን 4:1-3

ለመማር ፈቃደኞችና በሰዎች ላይ እምነት የሚጥሉ

ኢየሱስ በመቀጠል አዋቂዎች ከሕፃናት ሊያገኙ የሚችሉትን ተጨማሪ ትምህርት ሲያጎላ “የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደ ሕፃን የማይቀበል ሁሉ ከቶ አይገባባትም” ብሏል። (ማርቆስ 10:15) ሕፃናት ትሑቶች ብቻ ሳይሆኑ ለመማርም ፈቃደኞች ናቸው። አንዲት እናት “[ሕፃናት] የሚሰጣቸውን ትምህርት እንደ ስፖንጅ ምጥጥ አድርገው ይወስዳሉ” በማለት ተናግራለች።

እኛም የአምላክን መንግሥት ለመውረስ የመንግሥቱን መልእክት መቀበልና መታዘዝ አለብን። (1 ተሰሎንቄ 2:13) አዲስ እንደተወለዱ ሕፃናት ‘በድነታችን እንድናድግ ንጹሑን መንፈሳዊ ወተት መመኘት’ ይኖርብናል። (1 ጴጥሮስ 2:2) ሆኖም አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ለመረዳት ቢከብደንስ? ልጆችን የምትንከባከብ አንዲት ሴት እንዲህ ብላለች:- “ሕፃናት ለጥያቄዎቻቸው አጥጋቢ መልስ እስኪያገኙ ድረስ ‘ለምን?’ እያሉ መጠየቃቸውን አይተዉም።” እኛም ምሳሌያቸውን ብንኮርጅ እንጠቀማለን። ስለዚህ ማጥናታችሁን አታቋርጡ። የጎለመሱ ክርስቲያኖችን አማክሩ። እንዲሁም ይሖዋ ጥበብ እንዲሰጣችሁ ጠይቁት። (ያዕቆብ 1:5) በጸሎት ከጸናችሁ ይዋል ይደር እንጂ በረከት እንደምታገኙ ምንም ጥርጥር የለውም።—ማቴዎስ 7:7-11

ይሁን እንጂ አንዳንዶች ‘ለመማር ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎች በቀላሉ ሊታለሉ አይችሉም?’ ብለው ይጠይቁ ይሆናል። እምነት የሚጣልበት መመሪያ የሚያገኙ ከሆነ አይሳሳቱም። ለምሳሌ ያህል፣ ልጆች መመሪያ ለማግኘት የሚሞክሩት ከወላጆቻቸው ነው። አንድ አባት እንዲህ ብሏል:- “ወላጆች በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ልጆቻቸውን ከአደጋ በመጠበቅና የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች በማሟላት እምነት ሊጣልባቸው እንደሚችል ያሳያሉ።” እኛም በሰማይ በሚኖረው አባታችን በይሖዋ እንድንታመን የሚያደርጉን ተመሳሳይ ምክንያቶች አሉን። (ያዕቆብ 1:17፤ 1 ዮሐንስ 4:9, 10) ይሖዋ በቃሉ በኩል አስተማማኝ መመሪያ ይሰጠናል። ቅዱስ መንፈሱና ድርጅቱ ያጽናኑናል እንዲሁም ይደግፉናል። (ማቴዎስ 24:45-47፤ ዮሐንስ 14:26) በእነዚህ ዝግጅቶች መጠቀማችን ደግሞ ከመንፈሳዊ ጉዳት ይጠብቀናል።—መዝሙር 91:1-16

ሕፃናት በአዋቂዎች ላይ እምነት እንደሚጥሉ ሁሉ እኛም በይሖዋ መታመናችን የአእምሮ ሰላም ይሰጠናል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑር እንዲህ ብለዋል:- “ሕፃናት ሳለን ለጉዞ የምንከፍለው ገንዘብ ሳይኖረንና ወደምንሄድበት ቦታ የምንደርሰው እንዴት እንደሆነ ሳናውቅ [ወላጆቻችንን ተከትለን] ጉዞ እንጀምራለን፤ እንደዚህም ሆኖ ወላጆቻችን ወደምንሄድበት ቦታ በደህና እንደሚያደርሱን ፈጽሞ አንጠራጠርም።” እኛስ በሕይወት ጎዳና ስንጓዝ በይሖዋ ላይ ተመሳሳይ እምነት አለን?—ኢሳይያስ 41:10

በአምላክ ሙሉ በሙሉ የምንተማመን ከሆነ መንፈሳዊነታችንን አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ አመለካከቶችንና ድርጊቶችን እናስወግዳለን። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ እንደተናገረው በሰማይ የሚኖረው አባታችን የምናደርገውን ነገር እንደሚያውቅና የአምላክን መንግሥትና ጽድቁን እስካስቀደምን ድረስ እንደሚንከባከበን ሙሉ እምነት አለን። ይህም መንፈሳዊ ኃላፊነቶቻችንን ችላ ብለን ቁሳዊ ነገሮች ላይ ለማተኮር እንዳንፈተን ይረዳናል።—ማቴዎስ 6:19-34

“ለክፉ ነገር ሕፃናት”

ሕፃናት ሲወለዱም ጀምሮ ፍጹም ባይሆኑም ልባቸውና አእምሯቸው ንጹሕ ነው። በዚህም ምክንያት መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖችን “ለክፉ ነገር ሕፃናት ሁኑ” በማለት ይመክራቸዋል።—1 ቆሮንቶስ 14:20

የአምስት ዓመቷን ሞኒክን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ሞኒክ “አዲሷ ጓደኛዬ ሣራ ፀጉሯ ልክ እንደ እኔ ጥቅልል የሚል ነው!” በማለት ለእናቷ ነገረቻት። ሞኒክ፣ የሣራ የቆዳ ቀለምና ዘር ከእርሷ የተለየ መሆኑን አልጠቀሰችም። አንዲት ወላጅ “ሕፃናት የቀለም ልዩነት አይታያቸውም። የዘር ልዩነት ምን እንደሆነ አይገባቸውም፤ እንዲሁም ጭፍን ጥላቻ የላቸውም” ብላለች። በዚህ ረገድ ሕፃናት የማያዳላውንና ሁሉንም ሕዝቦች የሚወደውን የአምላካችንን ባሕርይ ግሩም አድርገው ያንጸባርቃሉ።—የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35

ሕፃናት ይቅር በማለት ረገድም የሚደነቅ ችሎታ አላቸው። አንድ ወላጅ እንደሚከተለው ብሏል:- “ትንንሾቹ ጃክ እና ሊቫይ ሲጣሉ ይቅርታ እንዲጠይቁ እንነግራቸዋለን፤ ብዙም ሳይቆይ እንደገና በደስታ መጫወት ይጀምራሉ። አያኮርፉም፣ ያለፈውን አያነሱም ወይም ይቅርታ ከማድረጋቸው በፊት አንድ ነገር እንዲደረግላቸው አይጠይቁም። እንደ ቀድሟቸው ጓደኛ ሆነው ጨዋታቸውን ይቀጥላሉ።” አዋቂዎች ሊኮርጁት የሚገባ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው!—ቈላስይስ 3:13

ከዚህም በተጨማሪ ትናንሽ ልጆች አምላክ መኖሩን ለማመን አይቸገሩም። (ዕብራውያን 11:6) በተፈጥሯቸው ግልጽ መሆናቸው ብዙውን ጊዜ ለሌሎች በድፍረት ለመመሥከር ያነሳሳቸዋል። (2 ነገሥት 5:2, 3) ያልተወሳሰበና ከልብ የመነጨ ጸሎታቸው ደንዳና የሆነውን ልብ እንኳ ሊነካ ይችላል። ፈተና ሲያጋጥማቸው አስደናቂ የሆነ ጽናት ሊያሳዩ ይችላሉ። ሕፃናት እንዴት ያሉ ውድ ስጦታዎች ናቸው!—መዝሙር 127:3, 4

ግሩም የሆኑትን ባሕርያት እንደገና መላበስ

‘አዋቂዎች፣ ሕፃናት ያሏቸውን ግሩም ባሕርያት እንደገና ማዳበር ይችሉ ይሆን?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። መልሱ ‘አዎን ይችላሉ’ ነው፤ ይህን ማወቃችንም ያበረታታናል! ኢየሱስ “እንደ ሕፃናት” እንድንሆን ማሳሰቡ ይህን ማድረግ እንደሚቻል ያረጋግጥልናል።—ማቴዎስ 18:3

በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ የሥነ ጥበብ ሥራዎችን የሚያድሱ ባለሞያዎች በዋጋ ሊገመት የማይችል ውድ ቅርስ እያደሱ ነው እንበል። ሥራቸውን ሲያከናውኑ በቅርሱ ላይ የተጋገሩትን ቆሻሻዎች ያስወግዳሉ፤ እንዲሁም ቀደም ሲል ለማደስ በተደረገው ሙከራ የተበላሹ ነገሮችን ያስተካክላሉ። እነዚህ ባለሞያዎች ትዕግሥት የተሞላበት ከፍተኛ ጥረት ካደረጉ በኋላ ቅርሱ መጀመሪያ የነበረው የሚያምር ቀለምና ውበት መታየት ይጀምራል። በተመሳሳይም ያለማቋረጥ ጥረት በማድረግ፣ በይሖዋ ቅዱስ መንፈስ እርዳታና በክርስቲያን ጉባኤ ፍቅራዊ ድጋፍ አማካኝነት ሕፃናት እያለን የነበሩንን ግሩም ባሕርያት እንደገና መላበስ እንችላለን።—ኤፌሶን 5:1

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሕፃናት በተፈጥሯቸው ትሑት ናቸው

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ትናንሽ ልጆች ጭፍን ጥላቻ የላቸውም፤ እንዲሁም በቀላሉ ይቅር ማለትና መርሳት ይችላሉ