በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

በአርማጌዶን የሚከናወነው ‘ሁሉን የሚችል አምላክ ጦርነት’ ምንድን ነው? ውጤቱስ ምን ይሆናል?—ራእይ 16:14, 16

በአጭር አገላለጽ አርማጌዶን፣ ይሖዋ ንጉሥ አድርጎ የሾመው ኢየሱስ ክርስቶስ ወደፊት የአምላክን ጠላቶች የሚያጠፋበት ዓለም አቀፍ ጦርነት ነው። እነዚህ ጠላቶች ማለትም ‘የዓለም ሁሉ ነገሥታት በአጋንንት መናፍስት’ እየተነዱ “ሁሉን በሚችል አምላክ ታላቅ ቀን ለሚሆነው ጦርነት . . . በዕብራይስጥ አርማጌዶን በሚባል ስፍራ” እንደሚሰበሰቡ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል።—ራእይ 16:14, 16

እነዚህ ነገሥታት ከአምላክ ጋር ለመዋጋት የሚሰበሰቡበት ቦታ ቃል በቃል አንድን ስፍራ አያመለክትም። አርማጌዶን የሚለው ቃል “የመጊዶ ተራራ” የሚል ትርጉም አለው። (ራእይ 16:16አዲሱ መደበኛ ትርጉም ከማጥኛ ጽሑፍ ጋር የግርጌ ማስታወሻ) ይሁን እንጂ በዚህ ስም የሚጠራ ተራራ ኖሮ አያውቅም። ከዚህም በተጨማሪ “የምድር ነገሥታትና ሰራዊታቸው” ቃል በቃል በአንድ ስፍራ ሊሰበሰቡ አይችሉም። (ራእይ 19:19) ከዚህ ይልቅ “ስፍራ” የሚለው ቃል የምድር ፖለቲካዊ መሪዎችና ደጋፊዎቻቸው ይሖዋን እንዲሁም “የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ” በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ወታደራዊ አመራር ሥር ያለውን ‘የሰማይ ሰራዊት’ በመቃወም የሚሰባሰቡበትን ሁኔታ ያመለክታል።—ራእይ 19:14, 16

አርማጌዶን የሚለው ቃል ከጥንቷ የእስራኤል ከተማ ከመጊዶ ጋር የተዛመደ መሆኑ ትልቅ ትርጉም አለው። መጊዶ፣ በዚያን ጊዜ ታላላቅ የንግድ መሥመሮችንና ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን ለመቆጣጠር የምትመች ከቀርሜሎስ ተራራ በስተ ምሥራቅ ባለው ቁልፍ ቦታ ላይ የምትገኝ ከተማ ነበረች። እንዲሁም በስፍራው የማያዳግሙ ጦርነቶች ይካሄዱ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ የእስራኤል መስፍን የነበረው ባራቅ በጄኔራል ሲሣራ የሚመራውን ኃያል የከነዓናውያን ሠራዊት ድል ያደረገው “በመጊዶ ውሆች አጠገብ” ነበር። (መሳፍንት 4:12-24፤ 5:19, 20) መስፍኑ ጌዴዎንም ምድያማውያንን በዚሁ አካባቢ አሸንፏቸዋል። (መሳፍንት 7:1-22) መጽሐፍ ቅዱስ መጪውን ጦርነት ከመጊዶ ጋር አያይዞ መግለጹ፣ አምላክ በልጁ በኩል ጠላቶቹን ሙሉ በሙሉ እንደሚደመስሳቸው ያረጋግጥልናል።

ታዲያ ውጤቱ ምን ይሆናል? የአርማጌዶን ጦርነት ማንኛውንም ዓይነት የሥነ ምግባር ውድቀትና ክፋት ከምድር ገጽ ያስወግዳል። በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ልዩ የሆነ አዲስ ምዕራፍ እንዲከፈት መንገድ ይጠርጋል። (ራእይ 21:1-4) በአምላክ መንግሥት ፍቅራዊ አመራር ሥር ምድር ወደ ገነትነት የምትለወጥ ሲሆን በዚያም ጻድቃን ለዘላለም ይኖራሉ።—መዝሙር 37:29