በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋ አድናቂ አምላክ ነው

ይሖዋ አድናቂ አምላክ ነው

ይሖዋ አድናቂ አምላክ ነው

‘አምላክ ያደረጋችሁትን ሥራ ለስሙም ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመፀኛ አይደለም።’ —ዕብራውያን 6:10 የ1954 ትርጉም

1. ይሖዋ ሞዓባዊቷ ሩት ያከናወነችውን ተግባር እንዳደነቀ ያሳየው እንዴት ነው?

 ይሖዋ ፈቃዱን ለመፈጸም ከልባቸው የሚፈልጉ ሰዎች የሚያደርጉትን ጥረት የሚያደንቅ ከመሆኑም ሌላ አብዝቶ ይባርካቸዋል። (ዕብራውያን 11:6) ታማኙ ቦዔዝ፣ ይህን ግሩም የይሖዋ ባሕርይ ያውቅ ስለነበር መበለት የሆነችውን አማቷን በፍቅር ትንከባከብ ለነበረችው ሞዓባዊቷ ሩት “ስላደረግሽው ሁሉ እግዚአብሔር ዋጋሽን ይክፈልሽ፤ . . . ብድራትሽን አትረፍርፎ ይመልስልሽ” ብሏታል። (ሩት 2:12) ታዲያ አምላክ ሩትን ባርኳታል? እንዴታ! ታሪኳ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መመዝገቡ ለዚህ ማረጋገጫ ነው! ከዚህም በተጨማሪ ቦዔዝን አግብታ የንጉሥ ዳዊትና የኢየሱስ ክርስቶስ ቅድመ አያት ለመሆን በቅታለች። (ሩት 4:13, 17፤ ማቴዎስ 1:5, 6, 16) ይህ ታሪክ ይሖዋ አገልጋዮቹ የሚያደርጉትን ጥረት እንደሚያደንቅ ከሚያሳዩ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ በርካታ ምሳሌዎች አንዱ ነው።

2, 3. (ሀ) ይሖዋ አድናቂ መሆኑ የሚያስገርመው ለምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ የምናከናውነውን አገልግሎት እንዲያደንቅ የሚያደርገው ምንድን ነው? በምሳሌ አስረዳ።

2 ይሖዋ አገልጋዮቹ ላከናወኑት ነገር አድናቆት አለማሳየትን ዓመጸኛ እንደመሆን ይቆጥረዋል። ዕብራውያን 6:10 [የ1954 ትርጉም] እንዲህ ይላል:- “እግዚአብሔር፣ ቅዱሳንን ስላገለገላችሁ እስከ አሁንም ስለምታገለግሉአቸው፣ ያደረጋችሁትን ሥራ ለስሙም ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመፀኛ አይደለም።” ይህን ጥቅስ አስገራሚ የሚያደርገው የሰው ልጆች ኃጢአተኞችና የአምላክ ክብር የጎደላቸው ቢሆኑም እንኳ ይሖዋ ለእርሱ ታማኝ የሆኑ ሰዎችን እንደሚያደንቅ መግለጹ ነው።—ሮሜ 3:23

3 ፍጽምና የሚጎድለን በመሆናችን ለአምላክ ያደርን ለመሆን የምናደርገው ጥረት ከቁጥር እንደማይገባና የእርሱን በረከት ማግኘት እንደማይገባን ሆኖ ሊሰማን ይችላል። ይሁን እንጂ ይሖዋ ውስጣዊ ግፊታችንንና ሁኔታችንን በሚገባ የሚረዳልን ከመሆኑም በላይ በሙሉ ነፍስ የምናከናውነውን አገልግሎት ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል። (ማቴዎስ 22:37) ሁኔታውን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ አንዲት እናት በአነስተኛ ዋጋ የተገዛ የአንገት ሐብል ጠረጴዛዋ ላይ ታገኛለች። ይህች እናት መጀመሪያ ላይ ስጦታውን አቅልላ ትመለከተው ይሆናል። ይሁን እንጂ የአንገት ሐብሉን የሰጠቻት ትንሿ ልጇ እንደሆነች የሚገልጽ ካርድ ከስጦታው ጋር ተያይዞ አገኘች። ይህች ትንሽ ልጅ ሐብሉን የገዛችው ያጠራቀመችውን ገንዘብ በሙሉ አውጥታ ነበር። እናትየዋም ይህን ስታውቅ ለስጦታው ያላት አመለካከት ተለወጠ። ዓይኖቿ በእንባ ተሞልተው ልጇን እቅፍ በማድረግ ልባዊ አድናቆቷን ትገልጽላታለች።

4, 5. ኢየሱስ አድናቆት በማሳየት ረገድ የይሖዋን ምሳሌ የኮረጀው እንዴት ነው?

4 ይሖዋ ውስጣዊ ግፊታችንንና ያሉብንን የአቅም ገደቦች በሚገባ ስለሚያውቅ ምርጣችንን እስከሰጠነው ድረስ የምናከናውነው አገልግሎት ይነስም ይብዛ በአድናቆት ይመለከተዋል። በዚህ ረገድ ኢየሱስ የአባቱ ፍጹም ነጸብራቅ ነው። ስለ መበለቲቷ አነስተኛ ስጦታ የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ማስታወስ ይቻላል። “ኢየሱስ ቀና ብሎ ሲመለከት ሀብታሞች በቤተ መቅደሱ መባ መሰብሰቢያ ውስጥ መባቸውን ሲጨምሩ አየ። ደግሞም አንዲት ድኻ መበለት ሁለት ትናንሽ የናስ ሳንቲሞች በዚያ ስትጨምር ተመለከተ፤ እንዲህም አለ፤ ‘እውነት እላችኋለሁ፤ ከሁሉም ይልቅ ይህች ድኻ መበለት የበለጠ ሰጥታለች፤ እነዚህ ሰዎች የሰጡት ከትርፋቸው ላይ ሲሆን፣ እርሷ ግን የሰጠችው በድኻ ዐቅሟ ያላትን መተዳደሪያ በሙሉ ነው።’”—ሉቃስ 21:1-4

5 አዎን ኢየሱስ፣ ሴትየዋ መበለትና ድሃ መሆኗን ስላስተዋለ ስጦታዋ ትልቅ ዋጋ እንዳለው የተገነዘበ ሲሆን አድናቆቱንም ገልጿል። ይሖዋም ቢሆን የኢየሱስ ዓይነት አመለካከት አለው። (ዮሐንስ 14:9) ያለህበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን አድናቂ በሆነው አምላካችንና በልጁ ዘንድ ሞገስ ማግኘት እንደምትችል ማወቅህ የሚያበረታታ አይደለም?

ይሖዋ ፈሪሃ አምላክ የነበረውን ኢትዮጵያዊ ባርኮታል

6, 7. ይሖዋ አቤሜሌክን እንዲያደንቅ ያደረገው ምንድን ነው? አድናቆቱንስ ያሳየው እንዴት ነው?

6 ይሖዋ ፈቃዱን የሚያደርጉ ሰዎችን እንደሚያደንቅ በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ በተደጋጋሚ ጊዜያት ተገልጿል። በኤርምያስ ዘመን ለኖረው አቤሜሌክ የተባለ ፈሪሃ አምላክ ያለው ኢትዮጵያዊ ምን እንዳደረገለት እንመልከት። አቤሜሌክ ታማኝ ባልሆነው በይሁዳ ንጉሥ በሴዴቅያስ ቤተ መንግሥት ውስጥ ያገለግል ነበር። ፈሪሃ አምላክ ያለው ይህ ሰው፣ የይሁዳ መኳንንት ነቢዩ ኤርምያስን በመንግሥት ላይ ዓመጽ እንደሚያነሳሳ በመግለጽ በሐሰት እንደወነጀሉትና በረሃብ እንዲሞት በውኃ ጉድጓድ ውስጥ እንደጣሉት አወቀ። (ኤርምያስ 38:1-7) አቤሜሌክ፣ ኤርምያስ በሚሰብከው መልእክት የተነሳ ከፍተኛ ጥላቻ እንዳተረፈ በመገንዘቡ የራሱን ሕይወት አደጋ ላይ ጥሎ ጉዳዩን ወደ ንጉሡ አቀረበው። ኢትዮጵያዊው እንዲህ በማለት በድፍረት ተናገረ:- “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፤ እነዚህ ሰዎች በነቢዩ በኤርምያስ ላይ ባደረጉት ነገር ሁሉ ክፋትን አድርገዋል፤ . . . በራብ እንዲሞት ጕድጓድ ውስጥ ጥለውታል።” ከዚያም አቤሜሌክ ከንጉሡ ፈቃድ ካገኘ በኋላ 30 ሰዎች ወስዶ የአምላክን ነቢይ አዳነው።—ኤርምያስ 38:8-13

7 አቤሜሌክ እምነት ስለነበረው ፍርሃት እንዲሰማው ሊያደርጉ የሚችሉ ሁኔታዎችን ያሸነፈ ሲሆን ይሖዋም ይህን ተመልክቷል። በመሆኑም ይሖዋ፣ በኤርምያስ በኩል ለአቤሜሌክ እንደሚከተለው የሚል መልእክት በመላክ አድናቆቱን አሳይቷል:- “እድገት ሳይሆን ጥፋት በማምጣት በዚህች ከተማ ላይ ቃሌን እፈጽማለሁ፤ . . . አንተን ግን በዚያ ቀን አድንሃለሁ፤ . . . ለምትፈራቸው ሰዎች ዐልፈህ አትሰጥም። እታደግሃለሁ፤ በእኔ ታምነሃልና በሕይወት ታመልጣለህ።” (ኤርምያስ 39:16-18) አዎን፣ ይሖዋ አቤሜሌክንና ኤርምያስን ከክፉዎቹ የይሁዳ መኳንንትም ሆነ ኢየሩሳሌምን ሙሉ በሙሉ ካጠፏት ባቢሎናውያን ታድጓቸዋል። መዝሙር 97:10 እንደሚለው ‘ይሖዋ የታማኞቹን ነፍስ ይጠብቃል፤ ከዐመፀኞችም እጅ ይታደጋቸዋል።’

“በስውር የተደረገውን የሚያይ አባትህም ዋጋህን ይከፍልሃል”

8, 9. ከኢየሱስ መማር እንደምንችለው ይሖዋ የሚያደንቀው ምን ዓይነት ጸሎቶችን ነው?

8 መጽሐፍ ቅዱስ ጸሎትን አስመልክቶ የሚሰጠው ሐሳብ ይሖዋ ለእርሱ ያደርን ሆነን ለመኖር የምናደርገውን ጥረት እንደሚያደንቀውና ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተው የሚያሳይ ሌላው ማስረጃ ነው። ጠቢቡ ሰው “የቅኖች ጸሎት ግን [አምላክን] ደስ ያሰኘዋል” በማለት ተናግሯል። (ምሳሌ 15:8) በኢየሱስ ዘመን በርካታ የሃይማኖት መሪዎች በሕዝብ ፊት ይጸልዩ የነበረ ሲሆን ይህንንም የሚያደርጉት ሰዎችን ለማስደመም እንጂ ከልባቸው ለአምላክ ያደሩ ሆነው አልነበረም። ኢየሱስ እነዚህ ሰዎች “ሙሉ ዋጋቸውን ተቀብለዋል” ካለ በኋላ ለተከታዮቹ “አንተ ግን ስትጸልይ ወደ ክፍልህ ግባ፤ በሩንም ዘግተህ በስውር ወዳለው አባትህ ጸልይ፤ በስውር የተደረገውን የሚያይ አባትህም ዋጋህን ይከፍልሃል” የሚል ምክር ሰጥቷቸዋል።—ማቴዎስ 6:5, 6

9 ኢየሱስ ራሱ በሕዝብ ፊት የጸለየባቸው ወቅቶች ስለነበሩ ከላይ ያለውን ሲናገር እንዲህ ዓይነቱን ጸሎት ማውገዙ እንዳልነበረ ግልጽ ነው። (ሉቃስ 9:16) ይሖዋ ሌሎችን ለማስደመም ብለን ሳይሆን በቅን ልቦና የምናቀርበውን ጸሎት በጣም ያደንቀዋል። በግል የምናቀርባቸው ጸሎቶች ለአምላክ ያለን ፍቅር ምን ያህል ጥልቅ እንደሆነና በእርሱ ላይ የቱን ያህል እንደምንታመን ያሳያሉ። በመሆኑም ኢየሱስ ብዙ ጊዜ ብቻውን ሆኖ የሚጸልይበት ቦታ ይፈልግ የነበረ መሆኑ የሚያስገርም አይደለም። በአንድ ወቅት “ማለዳም ገና ጎሕ ሳይቀድ” ለመጸለይ ወጥቶ እንደነበረ እናነባለን። በሌላ ጊዜ ደግሞ “ለመጸለይ ብቻውን ወደ ተራራ [ወጥቷል]።” አሥራ ሁለቱን ሐዋርያት ከመምረጡ በፊትም ሌሊቱን ሙሉ ብቻውን ሲጸልይ አድሯል።—ማርቆስ 1:35፤ ማቴዎስ 14:23፤ ሉቃስ 6:12, 13

10. አምላክን ለማስደሰት ባለን ልባዊ ፍላጎት ተነሳስተን የምንጸልይ ከሆነ ስለ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን?

10 ይሖዋ፣ ልጁ ያቀረበውን ልባዊ ጸሎት ምን ያህል በትኩረት ያዳምጠው እንደነበር መገመት ትችላለህ! በእርግጥም ኢየሱስ በአንዳንድ ወቅቶች “ከታላቅ ጩኸትና ከእንባ ጋር” የጸለየ ሲሆን “ፍጹም ትሑት ሆኖ በመታዘዙም ጸሎቱ ተሰማለት።” (ዕብራውያን 5:7፤ ሉቃስ 22:41-44) እኛም እንደ ኢየሱስ አምላክን ለማስደሰት ባለን ልባዊ ፍላጎት ተነሳስተን ከጸለይን በሰማይ የሚኖረው አባታችን በትኩረትና በአድናቆት እንደሚሰማን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። አዎን፣ “እግዚአብሔር . . . በእውነት ለሚጠሩት ሁሉ ቅርብ ነው።”—መዝሙር 145:18

11. ይሖዋ በስውር ስለምናደርጋቸው ነገሮች ምን ይሰማዋል?

11 ይሖዋ በስውር የምናቀርበውን ጸሎት ከፍ አድርጎ የሚመለከተው ከሆነ በስውር ስንታዘዘውማ እንዴት አብልጦ ያደንቀው! ይሖዋ በስውር የምናደርገውን ነገር እንደሚያውቅ ግልጽ ነው። (1 ጴጥሮስ 3:12) ብቻችንን በምንሆንበት ጊዜም እንኳ ታማኝና ታዛዥ መሆናችን ይሖዋን “በፍጹም ልብ” እንደምናገለግለው ማለትም ልባችን ትክክል የሆነውን ለማድረግ እንደማያወላውልና ውስጣዊ ግፊታችን ንጹሕ እንደሆነ ያሳያል። (1 ዜና መዋዕል 28:9) እንዲህ ማድረጋችን የይሖዋን ልብ ምንኛ ያስደስተው!—ምሳሌ 27:11፤ 1 ዮሐንስ 3:22

12, 13. አእምሯችንንም ሆነ ልባችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው? ታማኝ ደቀ መዝሙር የነበረውን ናትናኤልን እንዴት መምሰል እንችላለን?

12 በመሆኑም ታማኝ ክርስቲያኖች አእምሮንና ልብን የሚበክሉ የብልግና ፊልሞችንና ሥዕሎችን እንዲሁም ዓመጽን እንደመመልከት ካሉ ስውር ኃጢአቶች ይርቃሉ። አንዳንድ ኃጢአቶችን ከሰዎች መደበቅ ቢቻልም “ስለ ራሳችን መልስ መስጠት በሚገባን በእርሱ ፊት ሁሉም ነገር የተራቈተና የተገለጠ” እንደሆነ እንገነዘባለን። (ዕብራውያን 4:13፤ ሉቃስ 8:17) ይሖዋን ከሚያሳዝኑ ነገሮች ለመራቅ የምንጥር ከሆነ ንጹሕ ሕሊና ይኖረናል፤ እንዲሁም የአምላክን ሞገስ እንዳገኘን ስለምናውቅ እንደሰታለን። “አካሄዱ ንጹሕ የሆነ፣ ጽድቅን የሚያደርግ፤ ከልቡ እውነትን የሚናገር” ሰው የይሖዋን አድናቆት እንደሚያተርፍ ምንም ጥርጥር የለውም።—መዝሙር 15:1, 2

13 ይሁን እንጂ በክፋት በተሞላ ዓለም ውስጥ እየኖርን አእምሯችንንና ልባችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው? (ምሳሌ 4:23፤ ኤፌሶን 2:2) ይሖዋ ከሚያቀርብልን መንፈሳዊ ዝግጅቶች ሙሉ በሙሉ ከመጠቀም በተጨማሪ ክፋትን ለመጥላትና መልካም የሆነውን ለማድረግ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ አለብን። ተገቢ ያልሆኑ ምኞቶች በውስጣችን እንዳይፈጠሩና ኃጢአትን እንዳይወልዱ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል። (ያዕቆብ 1:14, 15) ኢየሱስ፣ ናትናኤልን “እነሆ፤ ተንኮል የሌለበት እውነተኛ [ሰው]” ብሎት ነበር፤ ስለ አንተም እንዲህ ብሎ ቢናገር ምን ያህል እንደምትደሰት አስበው። (ዮሐንስ 1:47) በርተሎሜዎስም ተብሎ የሚጠራው ናትናኤል በኋላ ላይ ከኢየሱስ 12 ሐዋርያት አንዱ የመሆን መብት አግኝቷል።—ማርቆስ 3:16-19

“መሓሪና ታማኝ ሊቀ ካህናት”

14. ኢየሱስ ማርያም ላከናወነችው ነገር ከሌሎች በተለየ መልኩ ምን ምላሽ ሰጠ?

14 “የማይታየው አምላክ [የይሖዋ] አምሳል” የሆነው ኢየሱስ በንጹሕ ልባቸው አምላክን ለሚያገለግሉ ሰዎች አድናቆት በማሳየት ረገድ አባቱን ሙሉ በሙሉ ይመስለዋል። (ቈላስይስ 1:15) ለምሳሌ ያህል፣ ክርስቶስ ሕይወቱን አሳልፎ ከመስጠቱ ከአምስት ቀናት በፊት ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ በቢታንያ በሚኖረው በስምዖን ቤት ተጋብዘው ነበር። በዚያን ምሽት የአልዓዛርና የማርታ እህት የሆነችው ማርያም “ዋጋው ውድ የሆነ፣ ግማሽ ሊትር ንጹሕ የናርዶስ ሽቱ አምጥታ” በኢየሱስ ራስና እግር ላይ አፈሰሰችው፤ ሽቶው የአንድ ዓመት ደሞዝ ያህል ዋጋ ነበረው። (ዮሐንስ 12:3) አንዳንዶች “ይህ ሁሉ ብክነት ለምንድነው?” ብለው ተናገሩ። ኢየሱስ ግን ሁኔታውን የተመለከተው ለየት ባለ መንገድ ነበር። ብዙም ሳይቆይ እንደሚሞትና እንደሚቀበር ስለሚያውቅ፣ የማርያምን ድርጊት ታላቅ ደግነት የተንጸባረቀበት አስፈላጊ ተግባር እንደሆነ አድርጎ ተመለከተው። በመሆኑም ኢየሱስ፣ ማርያምን ከመውቀስ ይልቅ ያከበራት ሲሆን ስለ እርሷም እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “ይህ ወንጌል በሚሰበክበት በዓለም ዙሪያ ሁሉ፣ በየትኛውም ስፍራ እርሷ ያደረገችው በመታሰቢያነት ይነገርላታል።”—ማቴዎስ 26:6-13

15, 16. ኢየሱስ ሰው ሆኖ በምድር ላይ በመኖር አምላክን ማገልገሉ የሚጠቅመን እንዴት ነው?

15 ኢየሱስን የመሰለ የሚያደንቅ መሪ በማግኘታችን ምንኛ ታድለናል! ክርስቶስ፣ መጀመሪያ ለቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤ ከዚያም ለመላው ዓለም ሊቀ ካህናትና ንጉሥ ሆኖ የማገልገል ኃላፊነት የተሰጠው ሲሆን ሰው ሆኖ በምድር ላይ ያሳለፈው ሕይወት ደግሞ ይሖዋ ለሰጠው ለዚህ ሥራ አዘጋጅቶታል።—ቈላስይስ 1:13፤ ዕብራውያን 7:26፤ ራእይ 11:15

16 ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊትም ቢሆን የሰው ልጆችን ይወዳቸውና በጥልቅ ያስብላቸው ነበር። (ምሳሌ 8:31) ሰው ሆኖ በምድር ላይ መኖሩ ደግሞ አምላክን ስናገለግል የሚያጋጥመንን መከራ ይበልጥ እንዲገነዘብ አድርጎታል። ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ኢየሱስ ሲናገር “በሁሉም ነገር ወንድሞቹን መምሰል ተገባው” ብሏል። “ይህንም ያደረገው መሓሪና ታማኝ ሊቀ ካህናት ሆኖ” ለማገልገል ሲሆን “እርሱ ራሱ በተፈተነ ጊዜ መከራን ስለ ተቀበለ፣ የሚፈተኑትን ሊረዳቸው ይችላል።” ኢየሱስ ‘ምንም ኀጢአት ባይሠራም እንደ እኛ በማንኛውም ነገር የተፈተነ በመሆኑ በድካማችን ይራራልናል።’—ዕብራውያን 2:17, 18፤ 4:15, 16

17, 18. (ሀ) ኢየሱስ በትንሿ እስያ ለሚገኙት ሰባት ጉባኤዎች የላካቸው ደብዳቤዎች ለእነዚህ ክርስቲያኖች ጥልቅ አድናቆት እንደነበረው የሚያሳዩት እንዴት ነው? (ለ) ቅቡዓን ክርስቲያኖች የትኛውን ኃላፊነታቸውን ለመወጣት እየተዘጋጁ ነበር?

17 ኢየሱስ በተከታዮቹ ላይ የሚደርሰውን መከራ ይበልጥ እንደተገነዘበ ከትንሣኤው በኋላ ግልጽ ሆነ። ኢየሱስ በትንሿ እስያ ለሚገኙት ሰባት ጉባኤዎች የላካቸውንና ሐዋርያው ዮሐንስ በጽሑፍ ያሰፈራቸውን ደብዳቤዎች እንመልከት። በሰምርኔስ የሚገኘውን ጉባኤ “መከራህንና ድኽነትህን ዐውቃለሁ” ብሎት ነበር። እዚህ ላይ ኢየሱስ ‘ችግራችሁ ይገባኛል፤ በምን ሁኔታ ላይ እንዳላችሁም በሚገባ አውቃለሁ’ ብሎ የተናገረ ያህል ነው። እርሱ ራሱ እስከ ሞት ድረስ ስለተሠቃየ ለእነዚህ ክርስቲያኖች “እስከ ሞት ድረስ ታማኝ ሁን፤ እኔም የሕይወትን አክሊል እሰጥሃለሁ” በማለት ርኅራኄ የተሞላበት ጠንካራ ማረጋገጫ ሰጥቷቸዋል።—ራእይ 2:8-10

18 ኢየሱስ ለሰባቱ ጉባኤዎች የላካቸው ደብዳቤዎች፣ ደቀ መዛሙርቱ የሚያጋጥሟቸውን መከራዎች በሚገባ እንደተገነዘበና ታማኝነታቸውን በጥልቅ እንደሚያደንቅ የሚገልጹ በርካታ ሐሳቦች ይዘዋል። (ራእይ 2:1 እስከ 3:22) መልእክቶቹ ከኢየሱስ ጋር በሰማይ የመግዛት ተስፋ ላላቸው ቅቡዓን ክርስቲያኖች የተላኩ መሆናቸውን ልብ በል። እነዚህ ክርስቲያኖች፣ በሥቃይ ላይ ያለው የሰው ዘር የክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ከሚያስገኛቸው በረከቶች እንዲጠቀም ርኅራኄ በተሞላበት መንገድ የመርዳት የላቀ ድርሻ የተሰጣቸው ሲሆን እነርሱም የጌታቸውን ፈለግ በመከተል ይህን ኃላፊነታቸውን ለመወጣት እየተዘጋጁ ነበር።—ራእይ 5:9, 10፤ 22:1-5

19, 20. ‘የእጅግ ብዙ ሕዝብ’ አባላት ለይሖዋና ለልጁ ያላቸውን አድናቆት የሚያሳዩት እንዴት ነው?

19 ኢየሱስ ቅቡዓን ተከታዮቹን ብቻ ሳይሆን ታማኝ የሆኑትን ‘ሌሎች በጎችም’ ይወዳቸዋል። በዛሬው ጊዜ የሌሎች በጎች ክፍል የሆኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የሚገኙ ሲሆን በቅርቡ ከሚመጣው “ከታላቁ መከራ” በሕይወት እንደሚተርፍ የተነገረለት ‘ከሕዝብ ሁሉ የተውጣጣ እጅግ ብዙ ሕዝብም’ በእነዚህ ሰዎች የተዋቀረ ነው። (ዮሐንስ 10:16፤ ራእይ 7:9, 14) ይህ እጅግ ብዙ ሕዝብ ለኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕትና ከፊቱ ለተዘረጋለት የዘላለም ሕይወት ተስፋ አድናቆት ስላለው ከኢየሱስ ጎን ለመሰለፍ እየጎረፈ ነው። ይህ ሕዝብ አድናቆቱን የሚገልጸው እንዴት ነው? ‘ቀንና ሌሊት አምላክን በማገልገል’ ነው።—ራእይ 7:15-17

20 ከገጽ 27 እስከ 30 ላይ የሚገኘው የ2006 የአገልግሎት ዓመት ዓለም አቀፍ ሪፖርት እንደሚያሳየው በእርግጥም እነዚህ ታማኝ አገልጋዮች ይሖዋን ‘ቀንና ሌሊት እያገለገሉት’ ነው። እንዲያውም ባለፈው ዓመት ይህ እጅግ ብዙ ሕዝብና በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው በምድር ላይ የቀሩ የተቀቡ ክርስቲያኖች በአጠቃላይ 1,333,966,199 ሰዓት ለሕዝብ በመስበክ አሳልፈዋል፤ ይህን አኃዝ ወደ ዓመት ብንቀይረው ከ150,000 በላይ ይሆናል!

አድናቆት ማሳየታችሁን ቀጥሉ!

21, 22. (ሀ) አድናቆት በማሳየት ረገድ በተለይ በዛሬው ጊዜ ክርስቲያኖች አመለካከታቸው እንዳይዛባ መጠንቀቅ ያለባቸው ለምንድን ነው? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ የምንመረምረው የትኛውን ጉዳይ ነው?

21 ይሖዋና ልጁ ፍጹም ላልሆኑ የሰው ዘሮች ያሳዩት ጥልቅ አድናቆት በእርግጥም አስገራሚ ነው። የሚያሳዝነው ግን አብዛኞቹ የሰው ልጆች የራሳቸውን ፍላጎት ሲያሳድዱ ለአምላክ እምብዛም ትኩረት አይሰጡትም። ጳውሎስ “በመጨረሻው ዘመን” የሚኖሩ ሰዎች “ራሳቸውን በጣም የሚወዱ፣ . . . ገንዘብን የሚወዱ፣ . . . ፈጽሞ የማያመሰግኑ” እንደሚሆኑ ጽፏል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5ፊሊፕስ) እንደነዚህ ያሉ ሰዎች፣ ልባዊ ጸሎት በማቅረብና በፈቃደኝነት በመታዘዝ እንዲሁም በሙሉ ነፍስ በማገልገል አምላክ ላደረገላቸው ነገሮች ሁሉ አድናቆታቸውን ከሚያሳዩት እውነተኛ ክርስቲያኖች ምንኛ የተለዩ ናቸው!—መዝሙር 62:8፤ ማርቆስ 12:30፤ 1 ዮሐንስ 5:3

22 በሚቀጥለው የጥናት ርዕስ ላይ ይሖዋ በፍቅር ተነሳስቶ ካደረገልን በርካታ መንፈሳዊ ዝግጅቶች ውስጥ አንዳንዶቹን እንመረምራለን። በእነዚህ ‘በጎ ስጦታዎች’ ላይ ስናሰላስል አድናቆታችን ይበልጥ እያደገ እንዲሄድ ምኞታችን ነው።—ያዕቆብ 1:17

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ይሖዋ አድናቂ አምላክ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?

• ብቻችንን በምንሆንበት ጊዜ የይሖዋን ልብ ማስደሰት የምንችለው እንዴት ነው?

• ኢየሱስ አድናቆት እንዳለው ያሳየው በየትኞቹ መንገዶች ነው?

• ኢየሱስ ሰው ሆኖ በምድር ላይ መኖሩ ርኅሩኅና አድናቂ መሪ እንዲሆን የረዳው እንዴት ነው?

[[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንዲት ወላጅ ልጇ የሰጠቻትን አነስተኛ ስጦታ እንደምትወደው ሁሉ ይሖዋም ምርጣችንን ስንሰጠው ያደንቃል