በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ የምደሰትበት ምክንያት

ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ የምደሰትበት ምክንያት

የሕይወት ታሪክ

ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ የምደሰትበት ምክንያት

ፓምላ ሞዝሊ እንደተናገረችው

በ1941 እናቴ በሌስተር ከተማ ወደተደረገው የይሖዋ ምሥክሮች የአውራጃ ስብሰባ ስትወስደኝ እንግሊዝ በጦርነት እየታመሰች ነበር። በዚህ ስብሰባ ላይ ወንድም ጆሴፍ ራዘርፎርድ ልጆችን አስመልክቶ ልዩ ንግግር አቀረበ። እኔና እናቴ በዚህ ስብሰባ ላይ ስንጠመቅ መንፈሳዊ እድገት እንድናደርግ የረዱን ክርስቲያኖች በጣም እንደተደሰቱ አስተዋልኩ። ሰዎችን የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ መርዳት ምን ያህል እንደሚያስደስት በዚያን ወቅት አልተገነዘብኩም ነበር።

ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ለመሆን በመንፈሳዊ እድገት ማድረግ የጀመርነው በ1940 ነበር። በመስከረም ወር 1939 ሁለተኛው የዓለም ጦርነት የፈነዳበትን አሰቃቂ ቀን እስካሁን አስታውሰዋለሁ። እናቴ ፊቷ በእንባ እየታጠበ “ዓለም ሰላም ማግኘት ያልቻለው ለምንድን ነው?” በማለት ደጋግማ ትጠይቅ ነበር። ወላጆቼ በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በጦር ሠራዊት ውስጥ ስላገለገሉ ጦርነት የሚያስከትለውን ሰቆቃ ቀምሰዋል። እናቴ በብሪስቶል ለሚገኝ የአንግሊካን ቤተ ክርስቲያን ቄስ ይህንኑ ጥያቄ አቀረበችለት። ቄሱ ግን “ምንጊዜም ቢሆን ጦርነት ነበር፤ ወደፊትም ይኖራል” ከማለት ሌላ ምንም ሊመልስላት አልቻለም።

ከጥቂት ጊዜ በኋላ በዕድሜ ጠና ያሉ አንዲት ሴት ወደ ቤታችን መጡ። ሴትየዋ የይሖዋ ምሥክር ነበሩ። እናቴም “ዓለም ሰላም ማግኘት ያልቻለው ለምንድን ነው?” በማለት ያንኑ ጥያቄ አቀረበችላቸው። እኚህ እህት በዚህ ክፉ ሥርዓት መጨረሻ ዘመን ላይ እንደምንኖር ከሚጠቁሙት ምልክቶች አንዱ ጦርነት እንደሆነ አብራሩላት። (ማቴዎስ 24:3-14) ብዙም ሳይቆይ ሴት ልጃቸው መጽሐፍ ቅዱስን ታስጠናን ጀመር። በተጠመቅንበት ዕለት በደስታ ይመለከቱን ከነበሩት ሰዎች መካከል እኚህ እህትና ልጃቸው ይገኙበታል። ሰዎችን ደቀ መዛሙርት ማድረግ ይህን ያህል አስደሳች የሆነው ለምንድን ነው? ከጊዜ በኋላ ለዚህ ጥያቄ መልስ አግኝቻለሁ። ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ባሳለፍኳቸው ከ65 የሚበልጡ ዓመታት ውስጥ ምን እንደተማርኩ እስቲ ላጫውታችሁ።

በማስተማሩ ሥራ የሚገኘውን ደስታ መቅመስ

በመንግሥቱ ስብከት ሥራ መካፈል የጀመርኩት በብሪስቶል ሲሆን በወቅቱ 11 ዓመቴ ነበር። አንድ ወንድም ንግግር የተቀረጸበት ሸክላ ማጫወቻና የመመሥከሪያ ካርድ ከሰጠኝ በኋላ “ከመንገዱ ባሻገር ያሉትን ቤቶች አንኳኪ” አለኝ። በወቅቱ በጣም ብፈራም ብቻዬን ማገልገል ቀጠልኩ። ለማገኛቸው ሰዎች፣ በሸክላ የተቀረጸ ቅዱስ ጽሑፋዊ ንግግር ካሰማኋቸው በኋላ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን እንዲወስዱ የሚጋብዝ የመመሥከሪያ ካርድ አሳያቸው ነበር።

ከ1950ዎቹ ጀምሮ ግን ከቤት ወደ ቤት በምናደርገው አገልግሎት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅሶችን ማንበብ አስፈላጊ እንደሆነ ጎላ ተደርጎ ተገለጸ። ዓይናፋር በመሆኔ ከማላውቃቸው ሰዎች ጋር መነጋገርና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ማብራራት መጀመሪያ ላይ አስቸጋሪ ሆኖብኝ ነበር። እያደር ግን ፍርሃቴ እየለቀቀኝ መጣ። ይህም አገልግሎት አስደሳች እንዲሆንልኝ ረዳኝ። ከዚያ ቀደም አንዳንድ ሰዎች መጽሐፍ አዟሪዎች እንመስላቸው ነበር፤ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ አውጥተን ስናነብላቸውና ስናብራራላቸው ግን የአምላክ ቃል አስተማሪዎች እንደሆንን ተገነዘቡ። አገልግሎቱን በጣም ስለወደድኩት በዚህ ሥራ ይበልጥ ለመካፈል ፈለግሁ። ስለዚህ በመስከረም ወር 1955 አቅኚ ሆኜ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መካፈል ጀመርኩ።

ጽናት በረከት ያስገኛል

በአገልግሎቴ ካገኘኋቸው ትምህርቶች አንዱ ለሰዎች ደግነት በማሳየት መጽናት በረከት ሊያስገኝ የሚችል መሆኑን ነው። በአንድ ወቅት ቫዮሌት ሞሪስ ለተባለች ሴት መጠበቂያ ግንብ አበረከትኩላት። ተመልሼ ስሄድ ቫዮሌት በሯን ወለል አድርጋ ከፈተችና መጽሐፍ ቅዱስን ሳብራራላት እጆቿን አጣጥፋ ዘና ባለ መንፈስ ተመስጣ አዳመጠችኝ። ከዚያ በኋላ ቤቷ በምሄድባቸው ጊዜያት ሁሉ ልባዊ ፍላጎት ያላት ብትመስልም መጽሐፍ ቅዱስን በቋሚነት እንድታጠና ስጋብዛት ግን “ይቅርብኝ፤ ባይሆን ልጆቹ ሲያድጉ አጠናለሁ” ትለኛለች። ይህም በጣም ያሳዝነኝ ነበር! መጽሐፍ ቅዱስ “ለመፈለግ ጊዜ አለው፤ ለመተው ጊዜ አለው” ይላል። (መክብብ 3:6) እኔ ግን ላለመተው ወሰንኩ።

ከአንድ ወር በኋላ ወደ ቫዮሌት ተመልሼ በመሄድ ሌሎች ጥቅሶችን አነበብኩላት። ብዙም ሳይቆይ በሯ ላይ ቆመን በየሳምንቱ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመርን። በመጨረሻም አንድ ቀን “ወደ ቤት ብትገቢ ይሻላል፤ አይመስልሽም?” አለችኝ። ቫዮሌት ግሩም የእምነት ባልንጀራዬና የቅርብ ጓደኛዬ ሆነች! አዎን፣ ቫዮሌት ተጠምቃ የይሖዋ ምሥክር ሆናለች።

አንድ ቀን ቫዮሌት፣ ባለቤቷ እርሷ ሳትሰማ ቤታቸውን እንደሸጠውና ጥሏት እንደሄደ አወቀች፤ በወቅቱ በሁኔታው በጣም ደንግጣ ነበር። ደስ የሚለው ግን የዚያኑ ዕለት ከሰዓት በኋላ አንድ ወንድም ሌላ ቤት እንድታገኝ ረዳት። ቫዮሌትም ለይሖዋ ምስጋናዋን ለመግለጽ ስትል ቀሪ ሕይወቷን አቅኚ ሆና ለማገልገል ወሰነች። የይሖዋ መንፈስ ለእውነተኛው አምልኮ ቅንዓት እንዲያድርባት እንደረዳት ስመለከት ደቀ መዛሙርት ማድረግ ይህን ያህል የሚያስደስተው ለምን እንደሆነ ገባኝ። አዎን፣ ይህ በሕይወቴ ሙሉ ላከናውነው የሚገባ ሥራ ነው!

በ1957 እኔና ሜሪ ሮቢንሰን በግላስጎው፣ ስኮትላንድ በሚገኘው ራዘርግላን የተባለ ፋብሪካዎች የሚበዙበት አካባቢ እንድናገለግል ተመደብን። አየሩ ጭጋጋማ ቢሆንም፣ ኃይለኛ ነፋስና ዝናብ ቢኖርም እንዲሁም በረዶ ቢጥልም እንሰብክ ነበረ፤ ልፋታችንም ከንቱ ሆኖ አልቀረም። አንድ ቀን ጄሲ የተባለች ሴት አነጋገርኩ። ከጄሲ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ያስደስተኝ ነበር። ኮሚኒስት የነበረው ባለቤቷ ዌሊ ግን መጀመሪያ ላይ ሊቀርበኝ አይፈልግም ነበር። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ሲጀምርና ለሰው ልጆች ከሁሉ የተሻለ ሕይወት የሚያመጣው የአምላክ መንግሥት ብቻ መሆኑን ሲገነዘብ በጣም ተደሰተ። ከጊዜ በኋላ ሁለቱም ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ መካፈል ጀመሩ።

መጀመሪያ ላይ የምናገኘው ምላሽ ሊያሳስት ይችላል

ቆየት ብሎም በፔዝሊ፣ ስኮትላንድ እንድናገለግል አዲስ ምድብ ተሰጠን። አንድ ቀን እያገለገልኩ ሳለ አንዲት ሴት በሯን ፊቴ ላይ ዘጋችብኝ። ወዲያው ግን ያችው ሴት ተከትላኝ መጥታ ይቅርታ ጠየቀችኝ። በሳምንቱ ተመልሼ ስሄድ “በአምላክ ላይ በሩን እንደዘጋሁ ሆኖ ተሰማኝ፤ እንደገና የፈለግሁሽ ለዚህ ነው” አለችኝ። ይህቺ ሴት ፐርል ትባላለች። በወዳጆቿና በዘመዶቿ በጣም ስላዘነች እውነተኛ ጓደኛ ለማግኘት ወደ አምላክ እንደጸለየች ነገረችኝ። “ከዚያም አንቺ ወደ ቤቴ መጣሽ። ለጸሎቴ ምላሽ የምትሆኚው እውነተኛ ጓደኛ አንቺ መሆን አለብሽ ብዬ ደመደምኩ” አለችኝ።

የፐርል ጓደኛ መሆን ቀላል አልነበረም። ቤቷ ለመድረስ ቀጥ ያለውን አቀበት በእግሬ መውጣት ነበረብኝ። ለመጀመሪያ ጊዜ ስብሰባ ልወስዳት ወደ ቤቷ ስሄድ ንፋስ የቀላቀለ ኃይለኛ ዝናብ ይጥል ስለነበር ልወድቅ ምንም አልቀረኝም። ዣንጥላዬም ስለተገነጣጠለ ጣልኩት። ፐርል በሯን ፊቴ ላይ ከዘጋችብኝ ከስድስት ወራት በኋላ ራሷን ለአምላክ መወሰኗን በውኃ ጥምቀት አሳየች።

ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ባለቤቷም መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ወሰነ፤ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው አገልግሎት ከእኔ ጋር መካፈል ጀመረ። እንደወትሮው ሁሉ የዚያን ዕለትም ይዘንብ ስለነበር የፐርል ባለቤት “ስለ እኔ አታስቢ፤ በእንደዚህ ዓይነት አየር እግር ኳስ ለመመልከት ለበርካታ ሰዓታት ስለምቆም ለይሖዋም ይህንን ማድረግ አያቅተኝም” አለኝ። የስኮትላንድ ሰዎች መንፈሰ ጠንካራነት ሁልጊዜ ያስደንቀኛል።

ብዙ ዓመታት ካለፉ በኋላ ወደዚህ ቦታ ስመለስ መጽሐፍ ቅዱስን ካስጠናኋቸው ሰዎች አብዛኞቹ በእምነታቸው ጸንተው እንደቆሙ መመልከት ምንኛ የሚክስ ነው! ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ እንዲህ ያለ ደስታ ያስገኛል። (1 ተሰሎንቄ 2:17-20) በስኮትላንድ ከስምንት ዓመት በላይ በአቅኚነት ካገለገልኩ በኋላ በ1966 በጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት በሚስዮናዊነት እንድሠለጥን ተጋበዝኩ።

በሌላ አገር ማገልገል

በጊልያድ ከሠለጠንኩ በኋላ በቦሊቪያ በምትገኘው ሳንታ ክሩዝ የተባለች ሞቃታማ ከተማ እንዳገለግል ተመደብኩ፤ በዚህች ከተማ 50 የሚያህሉ አባላት ያሉት ጉባኤ ነበር። ከተማዋ በሆሊዉድ ፊልሞች ላይ የሚታየውን የዩናይትድ ስቴትስ ምዕራባዊ ክፍል (ዋይልድ ዌስት) እንዳስታውስ አደረገችኝ። ወደኋላ መለስ ብዬ ሳስብ በሚስዮናዊነት ሕይወቴ ብዙም ችግሮች አላጋጠሙኝም ማለት እችላለሁ። አዞዎች አልተተናኮሉኝም፣ የሕዝብ ረብሻ አላጋጠመኝም፣ በረሃ ውስጥ አልጠፋሁም ወይም ደግሞ የመርከብ አደጋ አልደረሰብኝም። ያም ቢሆን ግን ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ በጣም አስደሳች ሆኖልኛል።

በሳንታ ክሩዝ መጽሐፍ ቅዱስን ካስጠናኋቸው ሴቶች አንዷ አንቶኒያ ናት። በስፓንኛ ቋንቋ ማስጠናት ለእኔ ትግል ነበር። አንድ ጊዜ የአንቶኒያ ትንሽ ልጅ “እማዬ፣ የምትሳሳተው ሆነ ብላ እኛን ለማሳቅ ነው?” በማለት ጠይቋት ነበር። ከጊዜ በኋላ አንቶንያና ሴት ልጇ ዮላንዳ ደቀ መዛሙርት ሆኑ። ዮላንዳ፣ ዲቶ በሚል ቅጽል ስም የሚጠራና በዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሕግ ተማሪ የሆነ ጓደኛ ነበራት፤ እርሱም መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትና በስብሰባዎቻችን ላይ መገኘት ጀመረ። ዲቶን ለመርዳት ባደረግኩት ጥረት ያገኘሁት ሌላው ትምህርት አንዳንድ ሰዎች እርምጃ እንዲወስዱ ደግነት የተሞላበት ግፊት የሚያስፈልጋቸው መሆኑን ነው።

ይህ ወጣት ጥናቱ ላይ መቅረት ሲጀምር “ዲቶ፣ ይሖዋ መንግሥቱን እንድትደግፍ አያስገድድህም። ይህን የምታደርገው በምርጫህ መሆን አለበት” አልኩት። ዲቶም አምላክን ለማገልገል እንደሚፈልግ ሲነግረኝ እንዲህ ብዬ ጠየቅኩት:- “የአንድ አብዮታዊ መሪ ምሥሎችን ክፍልህ ለጥፈሃል። ታዲያ አንተ ጋር የሚመጣ ሰው እነዚህን ምሥሎች ሲመለከት የአምላክን መንግሥት ለመደገፍ እንደመረጥህ ማወቅ ይችላል?” ዲቶ ያስፈለገው እንዲህ ያለ ግፊት ነበር።

ከሁለት ሳምንት በኋላ ዓመጽ በመቀስቀሱ በዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችና በፖሊሶች መካከል ተኩስ ተከፈተ። ዲቶ ጓደኛውን “ከዚህ ቦታ ቶሎ እንውጣ!” አለው። ጓደኛው ግን “በፍጹም አላደርገውም! ይህ እኮ ስንጠብቀው የነበረው ታላቅ ቀን ነው” በማለት ከመለሰለት በኋላ ጠመንጃ ይዞ የዩኒቨርሲቲው ሕንፃ ጣሪያ ላይ ወጣ። በዚያን ቀን ከተገደሉት ስምንት የዲቶ ጓደኞች አንዱ ይህ ወጣት ነበር። እውነተኛ ክርስቲያን ለመሆን ባይወስን ኖሮ ሊገደል ይችል የነበረውን ዲቶን መመልከት ምን ያህል እንደሚያስደስተኝ መገመት ትችላላችሁ?

የይሖዋ መንፈስ የሚያከናውነውን ሥራ መመልከት

አንድ ቀን እንዳንኳኳነው ባሰብኩት አንድ ቤት በኩል ሳልፍ የቤቱ ባለቤት ጠራችኝ። ሴትየዋ ኢግናሲያ ትባላለች። ስለ ይሖዋ ምሥክሮች የምታውቅ ቢሆንም ግዙፍ ሰውነት ያለውና ፖሊስ የሆነው አዳልቤርቶ የተባለው ባለቤቷ አጥብቆ ስለሚቃወማት በመንፈሳዊ እድገት ማድረግ አልቻለችም። ኢግናሲያ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ትምህርቶች ግራ ያጋቧት ስለነበር ከእኔ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረች። አዳልቤርቶ መጽሐፍ ቅዱስን እንዳታጠና ለማድረግ ቆርጦ የነበረ ቢሆንም ከእርሱ ጋር ስለ ሌሎች ጉዳዮች ለረጅም ሰዓታት እንወያይ ነበር። ይህም ጓደኝነት እንድንመሠርት የረዳን የመጀመሪያው እርምጃ ነበር።

ኢግናሲያ፣ አፍቃሪ የጉባኤው አባል ስትሆንና መጽናናት ለሚያስፈልጋቸው በርካታ ሰዎች መንፈሳዊም ሆነ ሥጋዊ እርዳታ ስታደርግ መመልከት ምን ያህል እንደሚያስደስተኝ መገመት ትችላላችሁ። ከጊዜ በኋላ ባለቤቷና ሦስት ልጆቿ የይሖዋ ምሥክሮች ሆኑ። እንዲያውም አዳልቤርቶ የእውነት ትርጉም ሲገባው ወደ ፖሊስ ጣቢያው ሄዶ በግለት በመስበኩ 200 የሚያህሉ ፖሊሶችን የመጠበቂያ ግንብና የንቁ! መጽሔት ኮንትራት ማስገባት ችሏል።

ይሖዋ ያሳድገዋል

በሳንታ ክሩዝ ለስድስት ዓመታት ካገለገልኩ በኋላ የቦሊቪያ ዋና ከተማ በሆነችው ላ ፓዝ ተመደብኩ፤ በዚያም 25 ዓመታት አሳልፌያለሁ። በ1970ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ በላ ፓዝ የነበረው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ 12 አባላት ብቻ ነበሩት። የስብከቱ ሥራ እየተስፋፋ ሲሄድ ግን ትላልቅ ሕንፃዎች በማስፈለጋቸው በፍጥነት በማደግ ላይ ባለችው በሳንታ ክሩዝ ከተማ አዲስ ቅርንጫፍ ቢሮ ተሠራ። በ1998 ቅርንጫፍ ቢሮው ወደዚያ የተዛወረ ሲሆን እኔም ከ50 በላይ አባላት ካሉት የቤቴል ቤተሰብ ጋር እንዳገለግል ተጋበዝኩ።

በ1966 በሳንታ ክሩዝ የነበረው አንድ ጉባኤ አድጎ አሁን በዚህች ከተማ ውስጥ ከ50 በላይ ጉባኤዎች ይገኛሉ። በዚያን ጊዜ በመላው ቦሊቪያ የነበሩት 640 የይሖዋ ምሥክሮችም ዛሬ ወደ 18,000 ተጠግተዋል!

በቦሊቪያ ያከናወንኩት ሥራ ፍሬያማ በመሆኑ ደስተኛ ነኝ። በዓለም ዙሪያ የሚገኙት ታማኝ ክርስቲያን ባልንጀሮቼ የሚያከናውኑት ሥራም ያበረታታኛል። ይሖዋ የመንግሥቱን ስብከት ሥራ ሲባርከው ማየት ሁላችንንም ያስደስተናል። ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ መካፈል በእርግጥም አስደሳች ነው።—ማቴዎስ 28:19, 20

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በስኮትላንድ በአቅኚነት ሳገለግል

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በቦሊቪያ ቅርንጫፍ ቢሮ ሳገለግል፤

(ከላይ የተደረበው ፎቶ) በ42ኛው ክፍል የጊልያድ ትምህርት ቤት የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ