በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ልዩ የሆነው ሥርዓተ ፀሐይ የተገኘው እንዴት ነው?

ልዩ የሆነው ሥርዓተ ፀሐይ የተገኘው እንዴት ነው?

ልዩ የሆነው ሥርዓተ ፀሐይ የተገኘው እንዴት ነው?

እኛ ያለንበትን የአጽናፈ ዓለም ክፍል ልዩ የሚያደርጉት ብዙ ነገሮች አሉ። የእኛ ሥርዓተ ፀሐይ የሚገኘው በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ብዙ ከዋክብት በሌሉበት በሁለት የፍኖተ ሐሊብ ጥምዝምዝ ጅራቶች (spiral arms) መካከል ነው። በምሽት የምናያቸው ከዋክብት በሙሉ ለማለት ይቻላል፣ ከእኛ በጣም ርቀው የሚገኙ ስለሆኑ በትልቅ ቴሌስኮፕ ቢታዩ እንኳ ከነጠብጣብ ብዙም አይበልጡም። ያለንበት ሥርዓተ ፀሐይ በእንዲህ ዓይነት ቦታ ላይ መቀመጡ አስፈላጊ ነው?

የእኛ ሥርዓተ ፀሐይ ወደ ፍኖተ ሐሊብ መሃል ተጠግቶ ቢሆን ኖሮ፣ ጥቅጥቅ ባሉ ከዋክብት መካከል መሆን ለሚያስከትለው ጉዳት ይጋለጥ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ የምድር ምሕዋር ሊዛባና የሰው ልጆች ሕልውና አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል። ይሁንና ያለንበት ሥርዓተ ፀሐይ በጋላክሲው ውስጥ በትክክለኛ ቦታ ላይ የተቀመጠ በመሆኑ ይህን ጨምሮ ከሌሎች አደጋዎችም ሊተርፍ ችሏል። ይህም በጋዝ ደመናዎች ውስጥ ማለፍ ከሚያመጣው ከመጠን በላይ የመሞቅ ችግር፣ ለከዋክብት ፍንዳታ እንዲሁም ገዳይ ለሆኑ ሌሎች የጨረር ምንጮች መጋለጥን ከመሳሰሉ አደጋዎች መጠበቅን ይጨምራል።

ፀሐይ ለእኛ ተስማሚ የሆነች ኮከብ ነች። ያለማቋረጥ ተመጣጣኝ የሆነ ሙቀት የምታመነጭ ሲሆን ረጅም ዕድሜም አስቆጥራለች። ከዚህም ባሻገር ከሚገባው በላይ ግዙፍና የምታቃጥል አይደለችም። በእኛ ጋላክሲ ውስጥ ያሉት አብዛኞቹ ከዋክብት ከፀሐይ እጅግ ያነሱ ናቸው። በመሆኑም እንደ ምድር ባለ ፕላኔት ላይ ሕይወት እንዲኖር የሚያስፈልገውን ትክክለኛ ዓይነት ብርሃንም ሆነ ተመጣጣኝ ሙቀት አያመነጩም። በተጨማሪም ብዙዎቹ ከዋክብት ከአንድ ወይም ከብዙ ከዋክብት ጋር በስበት ኃይል አማካኝነት የተሳሰሩ ስለሆኑ አንዳቸው በሌላኛው ዙሪያ ይሽከረከራሉ። ከዚህ በተቃራኒ ፀሐይ ራሷን ችላ የቆመች ናት። ያለንበት ሥርዓተ ፀሐይ በስበት ኃይል የተሳሰሩ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ ፀሐዮች ቢኖሩት ኖሮ ባለበት መርጋት አይችልም ነበር።

የእኛን ሥርዓተ ፀሐይ ልዩ የሚያደርገው ሌላው ነገር ደግሞ ከፀሐይ ርቀው የሚገኙት ግዙፍ ፕላኔቶች ምህዋራቸው ከሞላ ጎደል ክብ በመሆኑ፣ የስበት ኃይላቸው እንደ ምድር ያሉትን ፕላኔቶች የሚያሰጋ አለመሆኑ ነው። a እንዲያውም እነዚህ ትላልቅ ፕላኔቶች አደጋ ሊያስከትሉ የሚችሉ ግኡዝ አካላትን ስበው በማስቀረት ወይም አቅጣጫቸውን በማስቀየር አነስተኛ ለሆኑት ፕላኔቶች ከለላ ሆነውላቸዋል። ፒተር ዎርድ እና ዳነልድ ብራውንሊ የተባሉት ሳይንቲስቶች ሬር ኧርዝ—ኋይ ኮምፕሌክስ ላይፍ ኢዝ አንኮመን ኢን ዚ ዩኒቨርስ በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ “ከእኛ በኋላ እንዳለችው ጁፒተር ያሉ በአብዛኛው በጋዝ የተሞሉ ትላልቅ ፕላኔቶች በመኖራቸው አስተሮይዶችና ኮሜቶች የከፋ ጉዳት አያደርሱብንም” በማለት ገልጸዋል። ግዙፍ ፕላኔቶች ያሏቸው ሌሎች ሥርዓተ ፀሐዮች እንዳሉ ለማወቅ ተችሏል። ይሁንና ከእነዚህ ግዙፍ ፕላኔቶች ውስጥ አብዛኞቹ ያላቸው ምሕዋር እንደ ምድር ያሉ አነስተኛ ፕላኔቶችን ሕልውና አደጋ ላይ የሚጥል ነው።

ጨረቃ ያላት ሚና

ከጥንት ዘመን ጀምሮ ጨረቃ የሰው ልጆችን ቀልብ ስትማርክ ቆይታለች። ብዙ ገጣሚዎችና ሙዚቀኞች ስለ ጨረቃ ጽፈዋል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ዕብራዊ ገጣሚ ጨረቃን ‘በሰማይ ታማኝ ምስክር ሆና ለዘላለም እንደተመሠረተች’ አድርጎ ገልጿታል።—መዝሙር 89:37

ጨረቃ በምድር ላይ ላለ ሕይወት ጠቃሚ አስተዋጽኦ የምታበረክትበት አንዱ መንገድ በስበት ኃይሏ አማካኝነት ማዕበል እንዲነሳ ማድረግ ነው። ማዕበል ለባሕር ሞገድ መፈጠር እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ይታመናል፤ የባሕር ሞገድ ደግሞ የአየር ሁኔታ መዛባትን ይከላከላል።

ጨረቃችን የምትጫወተው ሌላው ቁልፍ ሚና፣ የስበት ኃይሏ ምድር ያጋደለችበት ማለትም የምትሽከረከርበት ዛቢያ ያዘመመበት ዲግሪ ቋሚ እንዲሆን ማድረጉ ነው። ኔቸር የተባለው የሳይንስ መጽሔት እንደገለጸው ጨረቃ ባትኖር ኖሮ የምድር ዛቢያ ጋደል ያለበት መጠን በረጅም ጊዜ ውስጥ “ከ0 እስከ 85 ዲግሪ” ሊለዋወጥ ይችል ነበር። ምድር ጋደል ያለች ባትሆን ኖሮ ምን ሊከሰት እንደሚችል አስብ! አስደሳች የሆነው የወቅቶች መፈራረቅ አይኖርም፤ እንዲሁም በዝናብ እጥረት እንሠቃይ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ ምድር ጋደል ማለቷ የምድራችን የሙቀት መጠን ሕልውናችንን ስጋት ላይ እስኪጥል ድረስ በጣም ከፍተኛ ወይም ዝቅተኛ እንዳይሆን ያግዳል። የሥነ ፈለክ ተመራማሪ የሆኑት ዣክ ላስካር “የማይለዋወጥ የአየር ጠባይ ሊኖር የቻለው ጨረቃ በመኖሯ ነው” ሲሉ ተናግረዋል። ጨረቃ ይህንን ተግባሯን እንድትወጣ ያስቻላት ትልቅ መሆኗ ነው። ግዙፎቹ ፕላኔቶች ካሏቸው ጨረቃዎች አንጻር ስትታይ የእኛ ጨረቃ ለምድራችን ትልቅ ነች።

የዘፍጥረት መጽሐፍ ጸሐፊ እንደገለጸው የምድራችን የተፈጥሮ ሳተላይት ማለትም ጨረቃ የምታከናውነው ሌላ ተግባር በሌሊት የብርሃን ምንጭ መሆኗ ነው።—ዘፍጥረት 1:16

በአጋጣሚ የተገኘ ነው ወይስ በዓላማ የተሠራ?

አንድ ሰው ሕይወት በምድር ላይ እንዲኖር ብቻ ሳይሆን አስደሳችም እንዲሆን ያስቻሉትን በርካታ ምክንያቶች ሲመለከት ምን ማብራሪያ ይሰጣል? ያሉት አማራጮች ሁለት ብቻ ናቸው። የመጀመሪያው፣ እነዚህ ሁሉ ነገሮች እንዲሁ ያላንዳች ዓላማ በድንገት ተገኝተዋል የሚለው ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ከእነዚህ ነገሮች በስተጀርባ ጥልቅ ማስተዋል የተንጸባረቀበት ዓላማ አለ የሚለው ነው።

ከብዙ ሺህ ዓመታት በፊት ቅዱሳን መጻሕፍት አጽናፈ ዓለም የተነደፈውም ሆነ የተሠራው በፈጣሪ ማለትም ሁሉን ቻይ በሆነው አምላክ መሆኑን ተናግረዋል። ይህ እውነት ከሆነ በእኛ ሥርዓተ ፀሐይ ውስጥ ያሉት ነገሮች በሙሉ በአጋጣሚ የተገኙ ሳይሆኑ በዓላማ የተነደፉ ናቸው ማለት ነው። ፈጣሪ፣ በምድር ላይ ሕይወት እንዲኖር ለማድረግ ደረጃ በደረጃ የወሰዳቸው እርምጃዎች በጽሑፍ እንዲሰፍሩ አድርጎልናል። ይህ ዘገባ ከተጻፈ 3,500 ዓመታት ገደማ ቢያልፉም በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ስለተከናወኑት ነገሮች የተዘገበው ታሪክ፣ ሳይንቲስቶች አጽናፈ ዓለም ተገኝቶበታል ብለው ከሚያምኑት ሐሳብ ጋር የሚስማማ መሆኑ ሳያስገርምህ አይቀርም። በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘው ይህ ዘገባ ምን እንደሚል ተመልከት።

በዘፍጥረት መጽሐፍ ላይ የሰፈረው የፍጥረት ዘገባ

“በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ።” (ዘፍጥረት 1:1) የመጽሐፍ ቅዱስ የመክፈቻ ቃላት የሚናገሩት፣ ፕላኔታችንን ጨምሮ ያለንበትን ሥርዓተ ፀሐይ እንዲሁም በቢሊዮን በሚቆጠሩ ጋላክሲዎች ውስጥ የሚገኙትን ከዋክብት ያቀፈው አጽናፈ ዓለም ስለመፈጠሩ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ መሠረት በአንድ ወቅት ምድር “ቅርጽ የለሽና ባዶ” ነበረች። የብስም ሆነ ፍሬያማ መሬት አልነበረም። ይሁንና ቀጥሎ ያለው ሐሳብ ሳይንቲስቶች በአንድ ፕላኔት ላይ ሕይወት እንዲኖር የግድ ያስፈልጋል ስለሚሉት ነገር ይኸውም ስለ ብዙ ውኃ ይናገራል። መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ መንፈስ “በውሆች ላይ ይረብብ ነበር” ይላል።—ዘፍጥረት 1:2

ውኃ ፈሳሽ ሆኖ እንዲቆይ አንድ ፕላኔት ከፀሐይ ትክክለኛ ርቀት ላይ መገኘት አለበት። ፕላኔቶችን የሚያጠኑ አንድሪው ኢንገርሶል የተባሉ ሳይንቲስት “ማርስ በጣም ቀዝቃዛ ስትሆን ቬኑስ ደግሞ እጅግ ሞቃታማ ናት፤ ምድር ግን ፍጹም ተስማሚ የአየር ጠባይ አላት” ሲሉ ገልጸዋል። በተመሳሳይም ዕፅዋት እንዲያድጉ ከተፈለገ በቂ ብርሃን መኖር አለበት። መጽሐፍ ቅዱስ በመጀመሪያዎቹ የፍጥረት “ቀናት” ስለተከናወኑት ነገሮች ያሰፈረው ዘገባ ትልቅ ትርጉም ይዟል። በዚያን ጊዜ አምላክ የፀሐይ ብርሃን፣ ባሕሩን እንደ ሕፃን ልጅ “መጠቅለያ” ሸፍኖት የነበረውን ጥቁር ደመና ሰንጥቆ እንዲያልፍ አደረገ።—ኢዮብ 38:4, 9፤ ዘፍጥረት 1:3-5

የዘፍጥረት መጽሐፍ ቀጣይ ቁጥሮች፣ ፈጣሪ መጽሐፍ ቅዱስ “ጠፈር” ብሎ የሚጠራውን ነገር እንደሠራ ይናገራሉ። (ዘፍጥረት 1:6-8) የዚህ ጠፈር በጋዝ መሞላት የምድርን ከባቢ አየር አስገኝቷል።

ከዚያም መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ቅርጽ የለሽ የነበረውን ምድር በማስተካከል የብስ እንዲገኝ እንዳደረገ ይናገራል። (ዘፍጥረት 1:9, 10) አምላክ የላይኛው የምድር ንጣፍ እንዲንቀሳቀስ እንዳደረገ ምንም ጥርጥር የለውም። በዚህም ምክንያት ጥልቅ ሸለቆዎች እንዲፈጠሩና ይህም አህጉራት ከባሕር በላይ ወጥተው እንዲታዩ አድርጎ ሊሆን ይችላል።—መዝሙር 104:6-8

ምድር ከተፈጠረች በውል ከማይታወቅ ጊዜ በኋላ፣ አምላክ በባሕር ውስጥ በዓይን የማይታዩ ጥቃቅን አልጌዎችን ፈጠረ። እነዚህ ያለ ተጓዳኝ መራባት የሚችሉ ባለ አንድ ሕዋስ ፍጥረታት፣ የፀሐይ ሙቀት በመጠቀም ካርቦን ዳይኦክሳይድን ወደ ምግብነት ቀይረው ኦክሲጅንን ወደ ከባቢ አየር ማስወጣት ጀመሩ። በሦስተኛው የፍጥረት “ቀን” ላይ ቀስ በቀስ ምድርን የሸፈኑት ዕፅዋት በመፈጠራቸው ይህ አስደናቂ ሂደት ተፋጠነ። ይህም በከባቢ አየር ውስጥ ያለው የኦክሲጅን መጠን እንዲጨምር በማድረጉ ሰዎች እና እንስሳት በሕይወት ለመቆየት የሚያስፈልጋቸው አየር እንዲገኝ አስችሏል።—ዘፍጥረት 1:11, 12

ምድር ፍሬያማ እንድትሆን ለማድረግ ፈጣሪ በዓይን የማይታዩ የተለያዩ ዓይነት ረቂቅ ተሕዋስያን በአፈር ውስጥ እንዲኖሩ አድርጓል። (ኤርምያስ 51:15 NW) እነዚህ ረቂቅ ተሕዋስያን የሞቱ ነገሮችን ወደ ብስባሽ በመቀየር ለዕፅዋት እድገት አስፈላጊ የሆኑት ንጥረ ነገሮች በድጋሚ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ያደርጋሉ። በአፈር ውስጥ የሚገኙ ልዩ የሆኑ ባክቴሪያዎች ናይትሮጂንን ከአየር በመውሰድ ይህንን ለእድገታቸው አስፈላጊ የሆነ ንጥረ ነገር ለዕፅዋቱ ያቀርቡላቸዋል። በጣም የሚገርመው አንድ እፍኝ ለም አፈር በአማካይ ስድስት ቢሊዮን በዓይን የማይታዩ ረቂቅ ተሕዋስያን ሊይዝ ይችላል!

ዘፍጥረት 1:14-19 በአራተኛው የፍጥረት “ቀን” ፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብት እንደተፈጠሩ ይናገራል። ላይ ላዩን ሲታይ ይህ ሐሳብ ቀደም ብለን ከተመለከትነው ቅዱስ ጽሑፋዊ ማብራሪያ ጋር የሚጋጭ ይመስላል። ይሁን እንጂ ዘፍጥረትን የጻፈው ሙሴ የፍጥረትን ዘገባ ያሰፈረው፣ ከምድር ሆኖ የሚመለከት ሰው ቢኖር ኖሮ ሊያየው ከሚችለው አንጻር መሆኑን ማስታወስ ይኖርብሃል። ምድር ላይ ሆኖ ፀሐይን፣ ጨረቃንና ከዋክብትን ማየት የተቻለው ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ይመስላል።

የዘፍጥረት ዘገባ በአምስተኛው የፍጥረት “ቀን” የባሕር ፍጥረታት፣ በስድስተኛው ደግሞ የየብስ እንስሳትና የሰው ልጅ መፈጠራቸውን ይናገራል።—ዘፍጥረት 1:20-31

ምድር የተሠራችው የሰው ልጆች ተደስተው እንዲኖሩባት ነው

በዘፍጥረት መጽሐፍ ዘገባ ላይ እንደተገለጸው ሕይወት የተገኘበት መንገድ የሰው ልጆች በምድር ላይ ተደስተው እንዲኖሩ ታስቦ እንደነበር አያሳይህም? ፀሐይ ፍንትው ብላ በወጣችበት ቀን ከመኝታህ ተነስተህ ንጹሕ አየር ስትተነፍስ ‘መኖር እንዴት ደስ ይላል’ ያልክበት ጊዜ የለም? ምናልባትም በአንድ መናፈሻ ውስጥ እየተንሸራሸርክ የአበቦቹን ውበትና መዓዛ አድንቀህ ይሆናል። ወይም በዛፎች መሃል ስታልፍ ጣፋጭ ፍሬዎች ለቅመህ ይሆናል። እነዚህ አስደሳች ነገሮች ሊኖሩ የቻሉት በሚከተሉት ምክንያቶች ነው:- (1) ምድር ውኃ በብዛት ያላት መሆኑ፤ (2) ፀሐይ ትክክለኛ መጠን ያለው ሙቀትና ብርሃን መስጠቷ፤ (3) ከባቢ አየር ውስጥ ያሉት ጋዞች በሚያስፈልገው መጠን መገኘታቸው፤ እንዲሁም (4) ለም መሬት መኖሩ።

በማርስ፣ በቬኑስና በእኛ ሥርዓተ ፀሐይ ውስጥ ባሉ ሌሎች ፕላኔቶች ላይ የማይገኙት እነዚህ ነገሮች፣ በአጋጣሚ የተገኙ አይደሉም። ከዚህ ይልቅ ሕይወት በምድር ላይ አስደሳች እንዲሆን ለማድረግ ተስተካክለው የተሠሩ ናቸው። በተጨማሪም የሚቀጥለው ርዕስ እንደሚያሳየው መጽሐፍ ቅዱስ ፈጣሪ ውብ የሆነችውን ፕላኔታችንን የሠራት ለዘላለም እንድትኖር መሆኑን ይገልጻል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a በእኛ ሥርዓተ ፀሐይ ውስጥ የሚገኙት አራቱ ለፀሐይ ቅርብ የሆኑት ፕላኔቶች ማለትም ሜርኩሪ፣ ቬኑስ፣ ምድር እና ማርስ ድንጋያማ ገጽታ ስላላቸው ተሬስትሪያል (terrestrial planets) የሚል ስያሜ ተሰጥቷቸዋል። ከፀሐይ ርቀው የሚገኙት ግዙፍ ፕላኔቶች (outer planets) ማለትም ጁፒተር፣ ሳተርን፣ ዩራነስ እና ኔፕቲዩን በዋነኝነት በጋዝ የተሞሉ ናቸው።

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

“ጂኦሎጂስት እንደመሆኔ መጠን የዘፍጥረት መጽሐፍ የተጻፈለትን ለሚመስል ተራ አርብቶ አደር ማኅበረሰብ፣ ምድርና በላይዋ ያለው ሕይወት ስለተገኙበት መንገድ አሁን ያለንን ዘመናዊ ጽንሰ ሐሳብ በአጭሩ ግለጽ ብባል፣ በዘፍጥረት መጽሐፍ የመጀመሪያ ምዕራፍ ላይ የሰፈረውን አገላለጽ ከመኮረጅ የተሻለ ሌላ አማራጭ ማግኘት የምችል አይመስለኝም።”—ጂኦሎጂስት ዋለስ ፕራት

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ምድራችን ለሥነ ፈለክ ምርምር ተስማሚ ቦታ ላይ ትገኛለች

ፀሐይ በጋላክሲያችን ውስጥ አሁን ያለችበት ቦታ ላይ ባትሆን ኖሮ ከዋክብትን እንዲህ በግልጽ ማየት አንችልም ነበር። ዘ ፕሪቭሌጅድ ፕላኔት የተሰኘው መጽሐፍ እንደሚከተለው በማለት ገልጿል:- “የእኛ ሥርዓተ ፀሐይ ከፍተኛ ብርሃን ከሚገኝበት በብናኝ የተሞላ አካባቢ የራቀ መሆኑ በቅርብ ያሉትን ከዋክብትም ሆነ ርቆ ያለውን የአጽናፈ ዓለም ክፍል በደንብ ለማየት ያስችላል።”

ከዚህም በላይ የጨረቃ መጠንና ከምድር ያላት ርቀት በፀሐይ ግርዶሽ ወቅት ጨረቃ ፀሐይን ሙሉ በሙሉ እንድትሸፍን ያስችሏታል። እነዚህ ከስንት አንዴ የሚከሰቱ አስደናቂ ክስተቶች የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች ፀሐይን እንዲያጠኑ ሁኔታዎችን አመቻችተውላቸዋል። እነዚህ ጥናቶች ከዋክብት ብርሃናቸውን ስለሚፈነጥቁበት መንገድ ምስጢር ሆነው የኖሩ በርካታ ነገሮችን ለመግለጥ አስችለዋል።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የምድር ዛቢያ ያዘመመበት ዲግሪ ባለበት እንዲቆይ ያስቻለው የጨረቃ መጠን ትልቅ መሆን ነው

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሕይወት በምድር ላይ እንዲኖር ያስቻለው ምንድን ነው? ብዙ ውኃ፣ ትክክለኛ መጠን ያለው ብርሃንና ሙቀት፣ ከባቢ አየር እንዲሁም ለም መሬት መኖሩ ነው

[ምንጭ]

ሉል:- Based on NASA Photo; ስንዴ:- Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.