‘ልጆች ሆይ፣ ለወላጆቻችሁ ታዘዙ’
‘ልጆች ሆይ፣ ለወላጆቻችሁ ታዘዙ’
“ልጆች ሆይ፤ ለወላጆቻችሁ በጌታ ታዘዙ፤ ይህ ተገቢ ነውና።”—ኤፌሶን 6:1
1. ታዛዥነት የሚጠብቅህ እንዴት ነው?
እስከ ዛሬ በሕይወት ልንቆይ የቻልነው በመታዘዛችን ሊሆን ይችላል፤ ሌሎች ደግሞ ባለመታዘዛቸው ሕይወታቸውን አጥተው ይሆናል። እኛ የታዘዝነው ሌሎች ያልታዘዙት ምንድን ነው? ‘ግሩምና ድንቅ ሆኖ የተፈጠረው’ አካላችን የሚሰጠንን ማስጠንቀቂያ የመሰሉ የተለያዩ ማስጠንቀቂያዎችን ሊሆን ይችላል። (መዝሙር 139:14) ለምሳሌ ያህል፣ ጥቁር ደመና እናይ፣ የነጎድጓድ ድምፅ እንሰማ እንዲሁም መብረቅ በሚፈጥረው ኤሌክትሪክ ፀጉራችን ይቆም ይሆናል። እነዚህ ምልክቶች አደጋ እንዳለ የሚጠቁሙ መሆናቸውን ለተማሩ ሰዎች፣ ሊመጣ ካለው ለሕይወት አደገኛ የሆነ መብረቅና በረዶ የቀላቀለ ኃይለኛ ዝናብ መጠለያ እንዲሹ ማስጠንቀቂያ ይሆኗቸዋል።
2. ልጆች ማስጠንቀቂያ ማግኘት የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው? ወላጆቻቸውን መታዘዝ የሚገባቸውስ ለምንድን ነው?
2 እናንት ልጆች አደጋ ስለሚያስከትሉ ነገሮች ማስጠንቀቂያ ማግኘት ያስፈልጋችኋል። ይህን የማድረጉ ኃላፊነት የተጣለው በወላጆቻችሁ ላይ ነው። “ምድጃውን አትንካ፤ ያቃጥልሃል”፣ “ወደ ወንዙ እንዳትሄድ፤ አደገኛ ነው”፣ “የመኪና መንገድ ከመሻገርህ በፊት ግራና ቀኝ ተመልከት” እየተባለ ይነገራችሁ እንደነበር ታስታውሱ ይሆናል። የሚያሳዝነው ግን፣ ብዙ ልጆች ባለመታዘዛቸው ምክንያት ለጉዳት ወይም ለሞት ተዳርገዋል። ለወላጆቻችሁ መታዘዛችሁ “ተገቢ ነው።” በተጨማሪም ጥበብ ነው። (ምሳሌ 8:33) ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ደግሞ ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን “ደስ የሚያሰኝ” መሆኑን ይናገራል። በእርግጥም አምላክ ወላጆቻችሁን እንድትታዘዙ ይጠብቅባችኋል።—ቈላስይስ 3:20፤ 1 ቆሮንቶስ 8:6
ታዛዥነት የሚያስገኘው ዘላለማዊ በረከት
3. አብዛኞቻችን የምናገኘው ‘እውነተኛ ሕይወት’ ምንድን ነው? ልጆችስ ይህን ሕይወት ሊያገኙ የሚችሉት እንዴት ነው?
3 ለወላጆችህ መታዘዝህ ‘የአሁኑን ሕይወትህን’ ይጠብቅልሃል፤ ከዚያም አልፎ ‘እውነተኛ ሕይወት’ ተብሎ የተጠራውን ‘የሚመጣውን ሕይወት’ ያስገኝልሃል። (1 ጢሞቴዎስ 4:8፤ 6:19) ለአብዛኞቻችን ይህ እውነተኛ ሕይወት፣ አምላክ ትእዛዛቱን በታማኝነት ለሚጠብቁ ሰዎች ቃል በገባው አዲስ ዓለም ውስጥ በምድር ላይ ለዘላለም መኖር ነው። በጣም አስፈላጊ ከሆኑት ከእነዚህ ትእዛዛት መካከል አንዱ “‘አባትህንና እናትህን አክብር’ በሚለው ቀዳሚ ትእዛዝ ውስጥ ያለው ተስፋ፣ ‘መልካም እንዲሆንልህ፣ ዕድሜህም በምድር ላይ እንዲረዝም’” የሚል ነው። ስለዚህ ወላጆችህን የምትታዘዝ ከሆነ ደስተኛ ትሆናለህ። የወደፊት ሕይወትህም አስተማማኝ ይሆንልሃል፤ እንዲሁም ገነት በሆነች ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት ከሚያገኙት መካከል ልትሆን ትችላለህ!—ኤፌሶን 6:2, 3
4. ልጆች አምላክን ማክበር የሚችሉት እንዴት ነው? ይህስ እንዴት ይጠቅማቸዋል?
4 ወላጆችህን በመታዘዝ ስታከብራቸው፣ እነርሱን እንድትታዘዝ የነገረህ አምላክ ስለሆነ ለእርሱም ክብር መስጠትህ ነው። ይህን ማድረግ አንተንም ይጠቅምሃል። መጽሐፍ ቅዱስ “እኔ እግዚአብሔር አምላክህ፣ የሚበጅህ ምን እንደ ሆነ የማስተምርህ . . . ነኝ” ይላል። (ኢሳይያስ 48:17፤ 1 ዮሐንስ 5:3) ታዛዥ መሆንህ የሚጠቅምህ እንዴት ነው? እንዲህ ማድረግህ እናትህንና አባትህን ያስደስታል። እነርሱም በአጸፋው ሕይወትህን ይበልጥ አስደሳች ለማድረግ በመጣር ደስታቸውን እንደሚገልጹ ጥርጥር የለውም። (ምሳሌ 23:22-25) ከሁሉም በላይ ግን ታዛዥነትህ በሰማይ የሚኖረውን አባትህን ስለሚያስደስተው አስደናቂ በሆኑ መንገዶች ይባርክሃል! ‘ምንጊዜም የሚያስደስተውን አደርጋለሁ’ በማለት የተናገረውን ኢየሱስን ይሖዋ እንዴት እንደባረከውና እንደጠበቀው እስቲ እንመልከት።—ዮሐንስ 8:29
ኢየሱስ ታታሪ ሠራተኛ ነበር
5. ኢየሱስ ታታሪ ሠራተኛ ነበር ለማለት የሚያስችሉ ምን ማስረጃዎች አሉ?
5 ኢየሱስ ለእናቱ ለማርያም የበኩር ልጅ ሲሆን አሳዳጊ አባቱ ዮሴፍ አናጢ ነበር። ኢየሱስም ሙያውን ከዮሴፍ በመማር አናጢ ሆኗል። (ማቴዎስ 13:55፤ ማርቆስ 6:3፤ ሉቃስ 1:26-31) ኢየሱስ እንዴት ያለ አናጢ የነበረ ይመስልሃል? ኢየሱስ ተአምራዊ በሆነ መንገድ በድንግል ማርያም ከመጸነሱ በፊት ገና በሰማይ እያለ “[በአምላክ] ዘንድ ዋና ሠራተኛ ነበርሁ፤ ዕለት ዕለት ደስ አሰኘው ነበርሁ” በማለት በጥበብ ተመስሎ ተናግሯል። ኢየሱስ በሰማይ ሳለ ታታሪ ሠራተኛ ስለነበር አምላክ ተደስቶበታል። በምድር ላይ ባሳለፈው በልጅነት ዕድሜውስ ታታሪና በሙያው የተካነ አናጢ ለመሆን ይጥር የነበረ አይመስልህም?—ምሳሌ 8:30 የ1954 ትርጉም፤ ቈላስይስ 1:15, 16
6. (ሀ) ኢየሱስ ልጅ ሳለ ቤት ውስጥ ይሠራ ነበር ብለህ እንድታምን ያደረገህ ምንድን ነው? (ለ) ልጆች ኢየሱስን በምን መንገዶች ሊኮርጁት ይችላሉ?
6 መጽሐፍ ቅዱስ በጥንት ዘመን የነበሩ ልጆች አንዳንድ ጨዋታዎችን ይጫወቱ እንደነበር ስለሚገልጽ ኢየሱስም በልጅነቱ አልፎ አልፎ ይጫወት እንደነበረ አያጠራጥርም። (ዘካርያስ 8:5፤ ማቴዎስ 11:16, 17) ይሁንና አነስተኛ ገቢ ባለው ትልቅ ቤተሰብ ውስጥ ያለ የመጀመሪያ ልጅ እንደመሆኑ መጠን ከዮሴፍ ከሚማረው የአናጢነት ሙያ በተጨማሪ ቤት ውስጥ የተለያዩ ሥራዎችን ይሠራ እንደነበር መገመት አያዳግትህም። ከጊዜ በኋላ ኢየሱስ ሰባኪ ከመሆኑም በላይ የግል ምቾቱን መሥዋዕት በማድረግ አገልግሎቱን በሙሉ ልብ አከናውኗል። (ሉቃስ 9:58፤ ዮሐንስ 5:17) ኢየሱስን መምሰል የምትችልበት መንገድ ይኖር ይሆን? ወላጆችህ መኝታ ቤትህን እንድታጸዳ ወይም ሌላ የቤት ውስጥ ሥራ እንድትሠራ ይጠይቁሃል? በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ በመገኘትና እምነትህን ለሌሎች በመንገር በይሖዋ አምልኮ እንድትካፈል ያበረታቱሃል? ኢየሱስ በልጅነቱ ተመሳሳይ ጥያቄ ቢቀርብለት ምን ምላሽ የሚሰጥ ይመስልሃል?
ትጉህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪና አስተማሪ
7. (ሀ) ኢየሱስ የማለፍ በዓልን ለማክበር የተጓዘው ከእነማን ጋር ሊሆን ይችላል? (ለ) ሌሎቹ ወደ ቤታቸው ለመመለስ ጉዞ ሲጀምሩ ኢየሱስ የት ነበር? በዚያ የቀረውስ ለምንድን ነው?
7 ሁሉም እስራኤላውያን ወንዶች በሦስቱ የአይሁዳውያን ዓመታዊ በዓላት ወቅት ይሖዋን ለማምለክ ወደ ቤተ መቅደሱ እንዲሄዱ ታዝዘው ነበር። (ዘዳግም 16:16) ኢየሱስ የ12 ዓመት ልጅ ሳለ የማለፍ በዓልን ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም የተጓዘው ከመላው ቤተሰቡ ጋር ሳይሆን አይቀርም። ይህ ደግሞ ሌሎቹን የማርያምና የዮሴፍ ወንድና ሴት ልጆች ሊጨምር ይችላል። በተጨማሪም ከቤተሰቡ ጋር ከተጓዙት መካከል ሰሎሜ (የማርያም እህት ሳትሆን አትቀርም)፣ ባለቤቷ ዘብዴዎስ እና በኋላ ላይ ሐዋርያት የሆኑት ልጆቻቸው ያዕቆብና ዮሐንስ ይገኙበት ይሆናል። a (ማቴዎስ 4:20, 21፤ 13:54-56፤ 27:56፤ ማርቆስ 15:40፤ ዮሐንስ 19:25) ከበዓሉ ሲመለሱ ዮሴፍና ማርያም፣ ኢየሱስ ከዘመዶቻቸው ጋር እንደሆነ አድርገው ስላሰቡ መጀመሪያ ላይ አብሯቸው አለመኖሩን አላስተዋሉም ነበር። ከሦስት ቀን በኋላ ግን በቤተ መቅደስ ውስጥ “በመምህራን መካከል ተቀምጦ ሲያዳምጣቸውና ጥያቄ ሲያቀርብላቸው” አገኙት።—ሉቃስ 2:44-46
8. ኢየሱስ በቤተ መቅደስ ውስጥ ምን ሲያደርግ ነበር? በዚያ የተገኙት ሰዎች የተደነቁትስ ለምንድን ነው?
8 ኢየሱስ ለመምህራኑ “ጥያቄ ሲያቀርብላቸው” የነበረው በምን መንገድ ነው? ጥያቄዎቹ የማወቅ ፍላጎቱን ለማርካት ወይም መረጃ ለማግኘት ብቻ የቀረቡ ላይሆኑ ይችላሉ። እዚህ ላይ የተሠራበት ግሪክኛ ቃል በፍርድ ምርመራ ጊዜ የሚቀርቡ ጥያቄዎችን ሊያመለክት ስለሚችል መስቀለኛ ጥያቄዎችንም ሊጨምር ይችላል። አዎን፣ ኢየሱስ በዚያ በለጋ ዕድሜው እንኳ የሃይማኖት ምሁራንን ያስደመመ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ለመሆን በቅቷል! መጽሐፍ ቅዱስ “የሰሙትም ሁሉ በማስተዋሉና በመልሱ ይደነቁ ነበር” ይላል።—ሉቃስ 2:47
9. መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ረገድ የኢየሱስን ምሳሌ መከተል የምትችለው እንዴት ነው?
9 ኢየሱስ ገና በልጅነቱ ተሞክሮ ያላቸውን መምህራን እንኳ በመጽሐፍ ቅዱስ እውቀቱ ለማስደነቅ የቻለው ለምን ይመስልሃል? ከሕፃንነቱ ጀምሮ መለኮታዊ መመሪያዎችን የሚያስተምሩት ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ወላጆች የነበሩት መሆኑ ጠቅሞታል። (ዘፀአት 12:24-27፤ ዘዳግም 6:6-9፤ ማቴዎስ 1:18-20) ዮሴፍ፣ ቅዱሳን መጻሕፍት ሲነበቡና ሲብራሩ እንዲሰማ ኢየሱስን ከልጅነቱ ጀምሮ ወደ ምኩራብ ይዞት ይሄድ እንደነበር አያጠራጥርም። አንተስ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያስተምሩህና ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች የሚወስዱህ ወላጆች አሉህ? ኢየሱስ እንዳደረገው ሁሉ የወላጆችህን ጥረት ታደንቃለህ? ልክ እንደ እርሱ የተማርከውን ለሌሎች ታካፍላለህ?
ኢየሱስ ታዛዥ ነበር
10. (ሀ) የኢየሱስ ወላጆች ልጃቸው የት እንዳለ ማወቅ የነበረባቸው ለምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ ለልጆች ምን ግሩም ምሳሌ ትቷል?
10 ማርያምና ዮሴፍ ከሦስት ቀን በኋላ ኢየሱስን በቤተ መቅደስ ሲያገኙት ምን የተሰማቸው ይመስልሃል? ትልቅ እፎይታ እንደተሰማቸው አያጠራጥርም! ሆኖም ኢየሱስ ወላጆቹ ያለበትን ቦታ አለማወቃቸው አስገርሞት ነበር። ወላጆቹ ኢየሱስ በተዓምራዊ መንገድ መወለዱን ያውቃሉ። ከዚህም በተጨማሪ ሁሉንም ዝርዝር ጉዳይ ባያውቁም እንኳ አዳኝና የአምላክ መንግሥት ገዥ በመሆን ወደፊት ስለሚጫወተው ሚና የተወሰነ እውቀት ነበራቸው። (ማቴዎስ 1:21፤ ሉቃስ 1:32-35፤ 2:11) በመሆኑም ኢየሱስ “ለምን ፈለጋችሁኝ? በአባቴ ቤት መገኘት እንደሚገባኝ አላወቃችሁምን?” ሲል ጠየቃቸው። እንደዚያም ሆኖ በታዛዥነት ከወላጆቹ ጋር ወደ መኖሪያቸው ወደ ናዝሬት ተመለሰ። መጽሐፍ ቅዱስ “ይታዘዝላቸውም ነበር” በማለት ይገልጻል። ከዚህም በላይ ‘እናቱ ይህን ሁሉ ነገር በልቧ ትጠብቀው ነበር።’—ሉቃስ 2:48-51
11. ስለ ታዛዥነት ከኢየሱስ ምን ልትማር ትችላለህ?
11 ሁልጊዜ ወላጆችህን በመታዘዝ ረገድ የኢየሱስን ምሳሌ መከተል ቀላል ሆኖ አግኝተኸዋል? ወይስ እነርሱ ዘመናዊ እንዳልሆኑና አንተ የተሻለ እንደምታውቅ ይሰማሃል? እውነት ነው፣ ስለ አንዳንድ ነገሮች፣ ለምሳሌ ስለ ሞባይል ስልኮች፣ ስለ ኮምፒውተሮችና ዘመናዊ ስለሆኑ ሌሎች መሣሪያዎች ከእነርሱ የበለጠ ታውቅ ይሆናል። ይሁንና ተሞክሮ ያላቸውን መምህራን “በማስተዋሉና በመልሱ” ያስደነቀውን ኢየሱስን አስብ። ከእርሱ ጋር ስትወዳደር አንተ ያለህ እውቀት እጅግ አነስተኛ እንደሆነ ሳይሰማህ አይቀርም። ሆኖም ኢየሱስ ያለአንዳች ማንገራገር ለወላጆቹ ይታዘዝ ነበር። እንዲህ ሲባል ግን ሁልጊዜ በውሳኔያቸው ይስማማ ነበር ማለት ላይሆን ይችላል። ያም ሆኖ በወጣትነት ዕድሜውም ሳይቀር “ይታዘዝላቸው” ነበር። ከኢየሱስ ምሳሌ ምን ትምህርት ማግኘት ትችላለህ?—ዘዳግም 5:16, 29
ታዛዥ መሆን ቀላል አይደለም
12. ታዛዥነት ሕይወትህን ሊያድንልህ የሚችለው እንዴት ነው?
12 ታዛዥ መሆን ሁልጊዜ ቀላል አይደለም። ከተወሰኑ ዓመታት በፊት የተከሰተ አንድ ሁኔታ እንመልከት:- ሁለት ሴት ልጆች በእግረኞች መሻገሪያ ድልድይ ከመጠቀም ይልቅ መኪኖች በፍጥነት የሚያልፉበትን ባለ ስድስት ረድፍ የመኪና መንገድ ሮጠው ለማቋረጥ አሰቡ። አብሯቸው የነበረው ጓደኛቸው ወደ እግረኛ መሻገሪያው ሲያመራ “ጆን፣ ና እንጂ። ከእኛ ጋር ትሻገራለህ አይደል?” አሉት። ሲያመነታ አንደኛዋ “ፈሪ!” ስትል አፌዘችበት። ጆን ፈርቶ ባይሆንም “እናቴን መስማት አለብኝ” ሲል መለሰላቸው። ጆን ድልድዩን በማቋረጥ ላይ እያለ ሲጢጥ የሚል የጎማ ድምፅ ሰማ። ወደ ታች ሲመለከት ሁለቱ ልጆች በመኪና ሲገጩ አየ! በዚህ አደጋ አንደኛዋ ሕይወቷን ያጣች ሲሆን፣ ሌላኛዋ ደግሞ ከባድ ጉዳት ስለደረሰባት አንድ እግሯ ተቆረጠ። በእግረኞች ማቋረጫ እንዲሻገሩ ትነግራቸው የነበረችው እናታቸው፣ በኋላ ላይ ለጆን እናት “ምናለ ልጆቼ እንደ አንቺ ልጅ ታዛዥ ቢሆኑልኝ ኖሮ” አለቻት።—ኤፌሶን 6:1
13. (ሀ) ወላጆችህን መታዘዝ ያለብህ ለምንድን ነው? (ለ) አንድ ልጅ ወላጁን ለመታዘዝ ፈቃደኛ የማይሆነው መቼ ነው?
13 አምላክ ‘ልጆች ሆይ፤ ለወላጆቻችሁ ታዘዙ’ ያለው ለምንድን ነው? ወላጆቻችሁን መታዘዛችሁ ለአምላክ ታዛዥ መሆናችሁን ስለሚያሳይ ነው። ከዚህም በላይ ወላጆቻችሁ ከእናንተ የበለጠ ተሞክሮ አላቸው። ለምሳሌ ከላይ የተጠቀሰው አደጋ ከመድረሱ ከአምስት ዓመት በፊት የጆን እናት ጓደኛ ልጅ ያንኑ አውራ ጎዳና ሲያቋርጥ በመኪና ተገጭቶ ሞቷል። እውነት ነው፣ ሁልጊዜ ወላጆችህን መታዘዝ ቀላል ላይሆን ይችላል። ቢሆንም አምላክ እንድትታዘዝ ይጠብቅብሃል። በሌላ በኩል ደግሞ ወላጆችህ ወይም ሌሎች ሰዎች እንድትዋሽ፣ እንድትሰርቅ ወይም በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት የሌለውን ማንኛውንም ነገር እንድታደርግ ቢነግሩህ ‘ከሰው ይልቅ ለአምላክ ልትታዘዝ’ ይገባል። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ለወላጆቻችሁ ታዘዙ’ ብቻ ሳይሆን “ለወላጆቻችሁ በጌታ ታዘዙ” ብሎ የሚናገረው ለዚህ ነው። ይህ ከአምላክ ሕግ ጋር የሚስማማ እስከሆነ ድረስ በማንኛውም ነገር ወላጆችህን መታዘዝን ይጨምራል።—የሐዋርያት ሥራ 5:29
14. ፍጹም የሆነ ሰው ታዛዥ መሆን የማይከብደው ለምንድን ነው? ያም ሆኖ ታዛዥነትን መማር የሚያስፈልገው ለምንድን ነው?
14 ልክ እንደ ኢየሱስ ‘ንጹሕና ከኀጢአተኞች የተለየህ’ ፍጹም ሰው ብትሆን ኖሮ ሁልጊዜም ለወላጆችህ መታዘዝ ቀላል እንደሚሆንልህ ይሰማሃል? (ዕብራውያን 7:26) ፍጹም ብትሆን ኖሮ እንደ አሁኑ ክፉ ነገር የመፈጸም ዝንባሌ አይኖርህም ነበር። (ዘፍጥረት 8:21፤ መዝሙር 51:5) ይሁንና ኢየሱስ እንኳ መታዘዝን መማር አስፈልጎታል። መጽሐፍ ቅዱስ “ልጅ ቢሆንም እንኳ፣ ከተቀበለው መከራ መታዘዝን ተማረ” ይላል። (ዕብራውያን 5:8) ኢየሱስ በሰማይ ሳለ መማር ያላስፈለገውን ትምህርት ማለትም መታዘዝን ከመከራ የተማረው እንዴት ነው?
15, 16. ኢየሱስ መታዘዝን የተማረው እንዴት ነው?
15 ኢየሱስ ልጅ ሳለ ዮሴፍና ማርያም የይሖዋን መመሪያ በመከተል ከጉዳት ጠብቀውታል። (ማቴዎስ 2:7-23) ከጊዜ በኋላ ግን አምላክ ለኢየሱስ መለኮታዊ ጥበቃ ማድረጉን አቁሟል። ኢየሱስ የደረሰበት አእምሯዊና አካላዊ ሥቃይ ከባድ ስለነበር፣ መጽሐፍ ቅዱስ “ጸሎትንና ልመናን ከታላቅ ጩኸትና ከእንባ ጋር አቀረበ” በማለት ይገልጻል። (ዕብራውያን 5:7) ይህ የሆነው መቼ ነው?
16 በተለይ ይህ የሆነው ሰይጣን የኢየሱስን ጽኑ አቋም ለማበላሸት የተቻለውን ሁሉ ጥረት ባደረገበትና የኢየሱስ ምድራዊ ሕይወት ሊያበቃ ጥቂት ሰዓታት በቀሩበት ወቅት ላይ ነበር። ኢየሱስ እንደ ወንጀለኛ ተቆጥሮ መሞቱ በአባቱ ስም ላይ የሚያስከትለው ነቀፋ እጅግ ስላስጨነቀው “[በጌቴሴማኒ የአትክልት ስፍራ] በብርቱ ይጸልይ ነበር፤ ላቡም እንደ ደም ነጠብጣብ ወደ ምድር ይፈስ ነበር።” ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ኢየሱስ በመከራ እንጨት ላይ ተሰቅሎ ሊሞት ሲል ከፍተኛ ሥቃይ ስለነበረው ‘ከእንባ ጋር ታላቅ ጩኸት’ አሰምቷል። (ሉቃስ 22:42-44፤ ማርቆስ 15:34) በዚህ መንገድ ‘ከተቀበለው መከራ መታዘዝን ተማረ፤’ በዚህም የአባቱን ልብ ደስ አሰኝቷል። በአሁኑ ወቅት በሰማይ የሚገኘው ኢየሱስ ታዛዥ ለመሆን የምናደርገው ትግል የሚያስከትልብንን ሥቃይ ይረዳልናል።—ምሳሌ 27:11፤ ዕብራውያን 2:18፤ 4:15
ታዛዥነትን መማር
17. ለተግሣጽ ምን አመለካከት ሊኖረን ይገባል?
17 አባትና እናትህ ተግሣጽ ሲሰጡህ ለአንተ የተሻለውን ነገር እንደሚመኙልህና እንደሚወዱህ እያሳዩ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “አባቱ የማይቀጣው ልጅ ማን ነው?” የሚል ጥያቄ ያቀርባል። ወላጆችህ ጊዜ ወስደው አንተን ለማረም ጥረት እንዲያደርጉ የሚያነሳሳቸው ፍቅር ቢጎድላቸው እንዴት ያሳዝናል! በተመሳሳይም ይሖዋ ስለሚወድህ ያርምሃል። እውነት ነው፣ “ቅጣት ሁሉ በወቅቱ የሚያሳዝን እንጂ ደስ የሚያሰኝ አይመስልም፤ በኋላ ግን ለለመዱት ሰዎች የጽድቅና የሰላም ፍሬ ያስገኝላቸዋል።”—ዕብራውያን 12:7-11
18. (ሀ) በፍቅር የሚሰጥ ተግሣጽ የምን ማረጋገጫ ነው? (ለ) እንዲህ ያለው ተግሣጽ በጎ ውጤት እንደሚያስገኝ የሚያሳይ ተሞክሮ ታውቃለህ?
18 ኢየሱስ ታላቅ ጥበብ እንዳለው የተናገረለት የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ፣ ወላጆች በፍቅር ተነሳስተው የሚሰጡት እርማት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ተናግሯል። ሰሎሞን “በአርጩሜ ከመቅጣት የሚሳሳለት ልጁን ይጠላል፤ የሚወደው ግን በጥንቃቄ ይቀጣዋል” ሲል ጽፏል። ከዚህም በላይ ሰሎሞን ፍቅራዊ እርማት የሚቀበል ሰው ነፍሱን ከሞት እንደሚያድን ተናግሯል። (ምሳሌ 13:24፤ 23:13, 14፤ ማቴዎስ 12:42) አንዲት ክርስቲያን፣ ልጅ ሳለች በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ስትረብሽ አባቷ ቤት ሲመለሱ እንደሚቀጣት ይነግራት እንደነበር ታስታውሳለች። አባቷ ሕይወቷን በጥሩ መንገድ የሚቀርጽላት ፍቅራዊ ተግሣጽ ስለሰጣት እስከ አሁን ድረስ እጅግ እንደምትወደው ትናገራለች።
19. ወላጆችህን የምትታዘዝበት ዋነኛ ምክንያት ምንድን ነው?
19 ወላጆችህ ጊዜ ወስደው ለአንተ ፍቅራዊ ተግሣጽ ለመስጠት ጥረት በማድረግ እንደሚወዱህ የሚያሳዩ ከሆነ አመስጋኝ መሆን ይገባሃል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወላጆቹን ዮሴፍንና ማርያምን እንደታዘዘው ሁሉ አንተም ወላጆችህን ታዘዝ። ከሁሉ በላይ ደግሞ የሰማዩ አባትህ ይሖዋ አምላክ እንድትታዘዝላቸው ስለሚጠብቅብህ ይህን ማድረግ ይገባሃል። እንዲህ ማድረግህ ይጠቅምሃል፤ ‘መልካም ይሆንልሃል፤ ዕድሜህም በምድር ላይ ይረዝማል።’—ኤፌሶን 6:2, 3
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል የተባለውን መጽሐፍ (እንግሊዝኛ) ጥራዝ 2፣ ገጽ 841ን ተመልከት።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• ልጆች ወላጆቻቸውን በመታዘዛቸው ምን ጥቅሞች ሊያገኙ ይችላሉ?
• ኢየሱስ ልጅ በነበረበት ጊዜ ወላጆቹን በመታዘዝ ረገድ ምን ምሳሌ ትቷል?
• ኢየሱስ መታዘዝን የተማረው እንዴት ነው?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ በአሥራ ሁለት ዓመቱ ቅዱሳን መጻሕፍትን ጠንቅቆ ያውቅ ነበር
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ ከደረሰበት መከራ መታዘዝን የተማረው እንዴት ነው?