በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሚስቶች ሆይ፣ ባሎቻችሁን በጥልቅ አክብሩ

ሚስቶች ሆይ፣ ባሎቻችሁን በጥልቅ አክብሩ

ሚስቶች ሆይ፣ ባሎቻችሁን በጥልቅ አክብሩ

‘ሚስቶች ሆይ፤ ለባሎቻችሁ ተገዙ።’—ኤፌሶን 5:22

1. በአብዛኛው ሚስቶች ባሎቻቸውን ማክበር አስቸጋሪ የሚሆንባቸው ለምንድን ነው?

 በብዙ አገሮች ውስጥ አንድ ወንድና ሴት ሲጋቡ ሙሽራዋ ባሏን በጥልቅ እንደምታከብረው በመግለጽ ቃለ መሐላ ትፈጽማለች። ይሁን እንጂ በርካታ ባሎች የትዳር ጓደኞቻቸውን የሚይዙበት መንገድ ሚስቶች ከዚህ ቃለ መሐላ ጋር ተስማምቶ መኖር እንዲከብዳቸው ወይም ቀላል እንዲሆንላቸው ሊያደርግ ይችላል። ጋብቻ አጀማመሩ ግሩም ነበር። አምላክ ከመጀመሪያው ሰው ከአዳም አንድ የጎድን አጥንት ወስዶ ሴትን ሠራት። አዳምም “ይህች ዐጥንት ከዐጥንቴ፣ ሥጋም ከሥጋዬ ናት” በማለት በደስታ ተናግሮ ነበር።—ዘፍጥረት 2:19-23

2. ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሴቶች በትዳር ውስጥ ባላቸው ቦታና ለጋብቻ ባላቸው አመለካከት ረገድ ምን ለውጦች ታይተዋል?

2 ጋብቻ እንደዚህ ያለ ግሩም አጀማመር የነበረው ቢሆንም፣ በ1960ዎቹ መባቻ ላይ ሴቶችን ከወንዶች የበላይነት ለማላቀቅ የሚሞክር የሴቶች ነጻ አውጪ የሚባል ንቅናቄ በዩናይትድ ስቴትስ ተጀመረ። በዚያን ወቅት በአብዛኛው ቤተሰባቸውን ጥለው የሚሄዱት ወንዶች የነበሩ ሲሆን በ1960ዎቹ መገባደጃ ላይ ግን እንዲህ የሚያደርጉት ሴቶች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጨመረ። በአሁኑ ጊዜ የሚሳደቡ፣ የሚጠጡ፣ የሚያጨሱና የሥነ ምግባር ብልግና የሚፈጽሙ ሴቶች ቁጥር ከወንዶች እኩል የሆነ ይመስላል። ታዲያ ሴቶች እንዲህ በማድረጋቸው ይበልጥ ደስተኞች ሆነዋል? በፍጹም። በአንዳንድ አገሮች ትዳር ከሚመሠርቱት ሰዎች መካከል ግማሽ የሚያህሉት ጋብቻቸው በፍቺ ያበቃል። አንዳንድ ሴቶች ትዳራቸውን ለማሻሻል ያደረጉት ጥረት ሁኔታዎቹ እንዲስተካከሉ አድርጓል ወይስ ችግሩን አባብሶታል?—2 ጢሞቴዎስ 3:1-5

3. በጋብቻ ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ ያለው መሠረታዊ ችግር ምንድን ነው?

3 መሠረታዊው ችግር ምንድን ነው? በተወሰነ ደረጃ ችግሩ የጀመረው፣ ዓመጸኛው መልአክ ይኸውም ‘ዲያብሎስ ወይም ሰይጣን ተብሎ የሚጠራው የጥንቱ እባብ’ ሔዋንን ባሳታት ጊዜ ነው። (ራእይ 12:9፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:13, 14) ሰይጣን የአምላክን ትምህርት አቃልሎታል። ለምሳሌ ያህል፣ አምላክ ስለ ጋብቻ የሚሰጠው መመሪያ ጥብቅና ከባድ እንዲመስል አድርጓል። ሰይጣን፣ ገዥ በሆነበት በዚህ ዓለም የመገናኛ ብዙኃን አማካኝነት የሚያስፋፋው ፕሮፖጋንዳ የአምላክ መመሪያዎች ለአንድ ወገን የሚያደሉና ጊዜ ያለፈባቸው እንደሆኑ ለማስመሰል ታቅዶ የሚዘጋጅ ነው። (2 ቆሮንቶስ 4:3, 4) ይሁንና ሴቶች በጋብቻ ውስጥ ስላላቸው ድርሻ አምላክ የሚሰጠውን መመሪያ በቀና አስተሳሰብ ብንመረምር፣ የአምላክ ቃል ጥበብ ያዘለና ጠቃሚ እንደሆነ እንመለከታለን።

ትዳር ለሚመሠርቱ የተሰጠ ማሳሰቢያ

4, 5. (ሀ) ትዳር ለመመሥረት የሚያስቡ ሰዎች ጥንቃቄ ማድረግ ያለባቸው ለምንድን ነው? (ለ) አንዲት ሴት ለማግባት ከመስማማቷ በፊት ምን ማድረግ አለባት?

4 መጽሐፍ ቅዱስ ትዳርን በተመለከተ የሚሰጠው ምክር ማሳሰቢያም የያዘ ነው። ዲያብሎስ በሚመራው በዚህ ዓለም ውስጥ የተሳካ ትዳር ያላቸው ሰዎችም እንኳ “ችግር” እንደሚያጋጥማቸው የአምላክ ቃል ይናገራል። ጋብቻ የአምላክ ዝግጅት ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስ ትዳር ለሚመሠርቱ ሰዎች የሚሰጠው ማሳሰቢያ አለ። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ፣ ባሏ በመሞቱ ምክንያት እንደገና ለማግባት ነጻነት ስላላት ሴት ሲናገር “ሳታገባ እንዲሁ ብትኖር ይበልጥ ደስተኛ ትሆናለች” በማለት በአምላክ መንፈስ ተነሳስቶ ጽፏል። ኢየሱስም ነጠላ ሆነው መኖርን ‘መቀበል የሚችሉ’ ሰዎች ሳያገቡ ቢኖሩ የተሻለ እንደሆነ ተናግሯል። ሆኖም አንድ ሰው ለማግባት ከመረጠ የሚያገባው ግለሰብ “በጌታ” መሆን አለበት፤ ይህም ግለሰቡ ራሱን ለአምላክ ወስኖ የተጠመቀ ሊሆን ይገባል ማለት ነው።—1 ቆሮንቶስ 7:28, 36-40 የ1954 ትርጉም፤ ማቴዎስ 19:10-12

5 “ያገባች ሴት ከባሏ ጋር በሕግ የታሰረች” እንደሆነች የሚገልጸው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኘው ማሳሰቢያ አንዲት ሴት የምታገባውን ሰው በጥንቃቄ መምረጥ ያለባት ለምን እንደሆነ ያሳያል። ያገባች ሴት ከባሏ “ሕግ ነጻ” የምትሆነው ባሏ ከሞተ ወይም ምንዝር በመፈጸሙ ምክንያት ከተፋቱ ብቻ ነው። (ሮሜ 7:2, 3) መጀመሪያ እንደተያዩ መዋደድ አስደሳች ስሜት የሚፈጥር ቢመስልም በትዳር ደስተኛ ለመሆን ግን ይህ በቂ መሠረት አይሆንም። በመሆኑም አንዲት ነጠላ ሴት ‘በዚህ ሰው ሕግ ሥር እንድሆን በሚያደርገኝ ዝግጅት ውስጥ ለመግባት ፈቃደኛ ነኝ?’ ብላ ራሷን መጠየቅ ይኖርባታል። በዚህ ጥያቄ ላይ ማሰብ ያለባት ከጋብቻ በፊት እንጂ ትዳር ውስጥ ከገባች በኋላ አይደለም።

6. በዛሬው ጊዜ የሚገኙ አብዛኞቹ ሴቶች ምን ውሳኔ ማድረግ ይችላሉ? ይህስ ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ የሆነው ለምንድን ነው?

6 በዛሬው ጊዜ በብዙ ቦታዎች አንዲት ሴት የጋብቻ ጥያቄ ሲቀርብላት ለመቀበል ወይም ላለመቀበል መምረጥ ትችላለች። ያም ቢሆን አንዲት ሴት በትዳር ውስጥ የሚኖረውን ፍቅር ለማግኘትና ቅርበት ያለው ግንኙነት ለመመሥረት ከፍተኛ ፍላጎት ሊኖራት ስለሚችል ጥበብ የተሞላበት ምርጫ ማድረግ በሕይወቷ ውስጥ ከምታደርጋቸው ውሳኔዎች ሁሉ ከባድ ሊሆንባት ይችላል። አንድ ጸሐፊ እንዲህ ብለዋል:- “አንድን ነገር ለማድረግ (ማግባት ወይም ተራራ መውጣት ሊሆን ይችላል) ይበልጥ በፈለግን መጠን ሁኔታዎቹ ጥሩ እንደሆኑ ወደማሰብ ከማዘንበላችንም ሌላ መስማት የምንፈልገውን መረጃ ብቻ በትኩረት እንከታተላለን።” ተራራ የሚወጣ ሰው ሳያመዛዝን ውሳኔ ማድረጉ ሕይወቱን ሊያሳጣው ይችላል፤ ጥበብ የጎደለው የትዳር ጓደኛ ምርጫም አስከፊ መዘዝ ሊያስከትል ይችላል።

7. የትዳር ጓደኛ መምረጥን በተመለከተ ምን ጥበብ የተሞላበት ምክር ተሰጥቷል?

7 አንዲት ሴት የጋብቻ ጥያቄ ባቀረበላት ሰው ሕግ ሥር መሆን ምን ነገሮችን እንደሚጨምር በቁም ነገር ማሰብ አለባት። ከዓመታት በፊት አንዲት ሕንዳዊት ወጣት እንዲህ በማለት በትሕትና ተናግራ ነበር:- “ወላጆቻችን በዕድሜ የሚበልጡን ከመሆኑም በላይ የበለጠ ጥበበኞች ስለሆኑ እንደ እኛ በቀላሉ አይታለሉም፤ . . . እኔ ግን በቀላሉ ልሳሳት እችላለሁ።” በእርግጥም፣ ወላጆችና ሌሎች ሰዎች የሚሰጡት እርዳታ አስፈላጊ ነው። አንድ ጥበበኛ መካሪ፣ ወጣቶች ሊያገቡ ያሰቡትን ሰው ወላጆች ለማወቅ ጥረት እንዲያደርጉና ግለሰቡ ከወላጆቹም ሆነ ከሌሎች የቤተሰቡ አባላት ጋር ያለውን ግንኙነት በጥንቃቄ እንዲመለከቱ ያበረታታ ነበር።

ኢየሱስ ለራስነት ሥልጣን እንደሚገዛ ያሳየው እንዴት ነው?

8, 9. (ሀ) ኢየሱስ ለአምላክ ስለ መገዛት ምን አመለካከት ነበረው? (ለ) ለራስነት ሥልጣን መገዛት ምን ጥቅም ሊያስገኝ ይችላል?

8 ለራስነት ሥልጣን መገዛት ከባድ ሊሆን ቢችልም ሴቶች ይህን ማድረጋቸውን እንደ ክብር ሊቆጥሩት ይችላሉ፤ በዚህ ረገድ ኢየሱስ ምሳሌ ትቷል። ኢየሱስ ለአምላክ በመገዛቱ መሠቃየትና በመከራ እንጨት ላይ ተሰቅሎ መሞት የነበረበት ቢሆንም ይህን ማድረጉ ደስታ አስገኝቶለታል። (ሉቃስ 22:41-44፤ ዕብራውያን 5:7, 8፤ 12:3) መጽሐፍ ቅዱስ “የሴትም ራስ ወንድ ነው፤ የክርስቶስም ራስ እግዚአብሔር ነው” ስለሚል ሴቶች ኢየሱስን እንደ ምሳሌያቸው አድርገው ሊመለከቱት ይችላሉ። (1 ቆሮንቶስ 11:3) ሆኖም ሴቶች ለወንዶች የራስነት ሥልጣን መገዛት ያለባቸው ሲያገቡ ብቻ አለመሆኑ ልብ ሊባል ይገባል።

9 መጽሐፍ ቅዱስ፣ ያገቡም ሆኑ ነጠላ ሴቶች በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ በበላይ ተመልካችነት ለሚያገለግሉት መንፈሳዊ ብቃት ያላቸው ወንዶች ሊገዙ እንደሚገባ ይገልጻል። (1 ጢሞቴዎስ 2:12, 13፤ ዕብራውያን 13:17) ሴቶች አምላክ የሰጣቸውን ይህን መመሪያ ሲከተሉ በይሖዋ ድርጅታዊ ዝግጅት ውስጥ ላሉት መላእክት ምሳሌ ይሆናሉ። (1 ቆሮንቶስ 11:8-10) ከዚህም በተጨማሪ በዕድሜ የገፉ ያገቡ ሴቶች ጥሩ ምሳሌ በመሆንና ጠቃሚ ምክሮችን በመስጠት ወጣት ሴቶች “ለባሎቻቸው የሚገዙ እንዲሆኑ” ያስተምሯቸዋል።—ቲቶ 2:3-5

10. ኢየሱስ በመገዛት ረገድ ምሳሌ የተወው እንዴት ነው?

10 ኢየሱስ፣ አምላክ ባዘዘው መሠረት የመገዛትን አስፈላጊነት ተገንዝቦ ነበር። በአንድ ወቅት ኢየሱስ፣ ከእርሱም ሆነ ከጴጥሮስ የሚጠበቀውን ግብር ለሰብዓዊ ባለ ሥልጣናት እንዲከፍል ለሐዋርያው የነገረው ከመሆኑም በላይ ይህን ለማድረግ የሚያስፈልገውን ገንዘብም አዘጋጅቶለት ነበር። ከጊዜ በኋላ ጴጥሮስ “ስለ ጌታ ብላችሁ ለምድራዊ ባለ ሥልጣን ሁሉ ተገዙ” በማለት ጽፏል። (1 ጴጥሮስ 2:13፤ ማቴዎስ 17:24-27) ኢየሱስ ለራስነት ሥልጣን በመገዛት ረገድ የተወውን የላቀ ምሳሌ በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “የባሪያን መልክ ይዞ፣ በሰውም አምሳል ተገኝቶ፣ ራሱን ባዶ አደረገ፤ ሰው ሆኖ ተገልጦም፣ ራሱን ዝቅ አደረገ፤ እስከ ሞት፣ . . . ድረስ ታዛዥ ሆነ።”—ፊልጵስዩስ 2:5-8

11. ጴጥሮስ፣ የማያምን የትዳር ጓደኛ ያላቸው ሚስቶችም እንኳ ለባሎቻቸው እንዲገዙ ያበረታታው ለምንድን ነው?

11 ጴጥሮስ አስቸጋሪ ለሆኑና ፍትሕን ለሚያጓድሉ የዚህ ዓለም ባለ ሥልጣናትም ጭምር እንዲገዙ ክርስቲያኖችን ሲያበረታታ እንዲህ ብሏል:- “የተጠራችሁትም ለዚሁ ነው፤ ምክንያቱም ክርስቶስ ስለ እናንተ መከራን የተቀበለው የእርሱን ፈለግ እንድትከተሉ ምሳሌን ሊተውላችሁ ነው።” (1 ጴጥሮስ 2:21) ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ ምን ያህል እንደተሠቃየና ለአምላክ በመገዛት እንዴት እንደጸና ከገለጸ በኋላ የማያምኑ ባሎች ያሏቸውን ሚስቶች እንዲህ በማለት አበረታቷቸዋል:- “ሚስቶች ሆይ፤ እናንተም እንደዚሁ ለባሎቻችሁ ተገዙ፤ አንዳንድ ለቃሉ የማይታዘዙ ቢኖሩ፣ ያለ ቃል በሚስቶቻቸው አኗኗር ተማርከው ይመለሳሉ፤ ይህም የሚሆነው ንጹሕና ፍጹም አክብሮት የተሞላውን ኑሮአችሁን ሲመለከቱ ነው።”—1 ጴጥሮስ 3:1, 2

12. ኢየሱስ መገዛቱ ምን ጥቅሞች አስገኝቷል?

12 ለሚያፌዝብንና ለሚሰድበን ሰው መገዛት ደካማ እንደመሆን ተደርጎ ሊቆጠር ይችላል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ነገሩን በዚህ መልክ አልተመለከተውም። ጴጥሮስ ስለ ኢየሱስ ሲጽፍ “ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም፤ መከራ ሲደርስበት አልዛተም” ብሏል። (1 ጴጥሮስ 2:23) የኢየሱስን ሥቃይ የተመለከቱ አንዳንድ ሰዎች በተወሰነ ደረጃም ቢሆን በእርሱ አምነዋል፤ ከእነዚህም መካከል አጠገቡ የተሰቀለው ወንጀለኛና ሲሞት ቆሞ ይመለከት የነበረው የመቶ አለቃ ይገኙበታል። (ማቴዎስ 27:38-44, 54፤ ማርቆስ 15:39፤ ሉቃስ 23:39-43) በተመሳሳይም በሚስቶቻቸው ላይ በተለያየ መንገድ ጉዳት የሚያደርሱትን ጨምሮ አንዳንድ የማያምኑ ባሎች፣ ሚስቶቻቸው እንደሚገዙላቸው ሲመለከቱ ክርስቲያኖች ሊሆኑ እንደሚችሉ ጴጥሮስ ጠቁሟል። በዛሬው ጊዜ ይህ እየተፈጸመ እንዳለ የሚያሳዩ ተሞክሮዎች እየተመለከትን ነው።

ሚስቶች ባሎቻቸውን መማረክ የሚችሉት እንዴት ነው?

13, 14. ሚስቶች ለማያምኑ ባሎቻቸው መገዛታቸው ጠቃሚ የሆነው እንዴት ነው?

13 አማኝ የሆኑ ሚስቶች የክርስቶስ ዓይነት አኗኗር በመከተል ባሎቻቸውን መማረክ ችለዋል። በቅርቡ በተደረገ የይሖዋ ምሥክሮች የአውራጃ ስብሰባ ላይ አንድ ባል ክርስቲያን ስለሆነችው ሚስቱ ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “ሚስቴን አስቸግራት የነበረ ቢሆንም እርሷ ግን በጣም ታከብረኝ ነበር። እኔን የሚያቃልል ነገር ፈጽሞ አድርጋ አታውቅም። እምነቷን በግድ እንድቀበል ለማድረግ አልሞከረችም። በፍቅር ትንከባከበኝ ነበር። ወደ ትልልቅ ስብሰባዎች ስትሄድ ምግቤን ቀደም ብላ ለማዘጋጀትና የቤቱን ሥራዎች ለማጠናቀቅ ከፍተኛ ጥረት ታደርግ ነበር። ባሕርይዋ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የማወቅ ፍላጎት እንዲያድርብኝ አደረገ። ይኸው አሁን የይሖዋ ምሥክር ለመሆን በቅቻለሁ!” አዎን፣ ይህ ባል በሚስቱ አኗኗር ‘ተማርኮ ያለ ቃል ሊመለስ’ ችሏል።

14 ጴጥሮስ ጎላ አድርጎ እንደገለጸው ጥሩ ውጤት የሚያስገኘው የአንዲት ሚስት ንግግር ሳይሆን ተግባሯ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች ከተማረች በኋላ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ቆርጣ የተነሳች የአንዲት ሚስት ተሞክሮ ይህን ያሳየናል። ይህቺ ሴት ስብሰባ ልትሄድ ስትል ባሏ “አግነስ በዚያ በር ከወጣሽ፣ ተመልሰሽ እንዳትመጪ!” ሲል በንዴት ጮኸባት። አግነስ፣ “በዚያ በር” ባትወጣም በሌላ በር ወጥታ ወደ ስብሰባ ሄደች። በሚቀጥለው የስብሰባ ምሽት ደግሞ “ስትመለሺ እዚህ አታገኚኝም” በማለት አስፈራራት። እንዳለውም ስትመለስ ባለቤቷ ቤት አልነበረም፤ ከዚያ በኋላም ለሦስት ቀናት ያህል ወደ ቤት አልተመለሰም። በመጨረሻም ወደ ቤት ሲመጣ አግነስ “የሚበላ ነገር ላቅርብልህ?” በማለት በደግነት ጠየቀችው። አግነስ ለይሖዋ የምታቀርበውን አምልኮ በምንም መንገድ አላጓደለችም። ውሎ አድሮ ባለቤቷ መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት የተስማማ ሲሆን ከጊዜ በኋላ ራሱን ለአምላክ ወሰነ። ቆየት ብሎም በርካታ ኃላፊነቶችን ተቀብሎ በበላይ ተመልካችነት ያገለግል ጀመር።

15. ክርስቲያን ሚስቶች ምን ዓይነት ‘ውበት’ ሊኖራቸው ይገባል?

15 ከላይ የተጠቀሱት ሚስቶች፣ ሐዋርያው ጴጥሮስ አድንቆ የገለጸው ዓይነት ‘ውበት’ እንዳላቸው አሳይተዋል፤ ይህ ውበት ‘ሹሩባ ለመሠራት ወይም ለልብስ’ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት የሚገኝ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ጴጥሮስ “ውበታችሁ በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ፣ ገርና ጭምት መንፈስ ያለበት፣ ምንጊዜም የማይጠፋ የውስጥ ሰውነት ውበት ይሁን” ብሏል። ይህ ዓይነቱ መንፈስ የሚንጸባረቀው ተገቢ በሆነ የድምጽ ቃና እንዲሁም ምግባር እንጂ የፉክክር ዝንባሌ በማሳየት ወይም የፈለግነውን ለማግኘት በመነዝነዝ አይደለም። በዚህ መንገድ አንዲት ክርስቲያን ሚስት ለባሏ ጥልቅ አክብሮት እንዳላት ታሳያለች።—1 ጴጥሮስ 3:3, 4

ልንኮርጃቸው የሚገቡ ምሳሌዎች

16. ሣራ ለክርስቲያን ሚስቶች ግሩም ምሳሌ የምትሆነው በየትኞቹ መንገዶች ነው?

16 ጴጥሮስ “ተስፋቸውን በእግዚአብሔር ላይ የጣሉ የቀድሞ ቅዱሳት ሴቶች ራሳቸውን ያስዋቡት . . . ለባሎቻቸው በመገዛት ነበር” በማለት ጽፏል። (1 ጴጥሮስ 3:5) እነዚህ ሴቶች የይሖዋን መመሪያ በመከተል እርሱን ማስደሰት፣ የቤተሰብ ደስታ እንዲሁም የዘላለም ሕይወት ሽልማት እንደሚያስገኝ ተገንዝበው ነበር። ጴጥሮስ፣ ውብ የነበረችውን የአብርሃምን ሚስት ሣራን በመጥቀስ “አብርሃምን ‘ጌታዬ’ እያለች ትታዘዘው” እንደነበር ገልጿል። ሣራ ፈሪሃ አምላክ ያለውን ባሏን ትደግፈው ነበር፤ አምላክ አብርሃምን ወደ ሩቅ አገር ሄዶ እንዲያገለግል ሲልከው ሣራ የተደላደለ ኑሮዋን የተወች ከመሆኑም በላይ ሕይወቷን እንኳ አደጋ ላይ ጥላ ነበር። (ዘፍጥረት 12:1, 10-13) ጴጥሮስ “እናንተም ምንም ሳትፈሩ መልካም ብታደርጉ የእርሷ ልጆች ናችሁ” በማለት ሣራ የተወችውን ድፍረት የተሞላበት ምሳሌ አድንቋል።—1 ጴጥሮስ 3:6

17. ጴጥሮስ፣ አቢግያን ለክርስቲያን ሚስቶች ምሳሌ እንደምትሆን አስቧት ሊሆን ይችላል የምንለው ለምንድን ነው?

17 ተስፋቸውን በአምላክ ላይ ከጣሉት ሴቶች ሌላዋ፣ ደፋር የነበረችው አቢግያ ናት፤ ጴጥሮስ ከላይ ያለውን ሲጽፍ እርሷንም አስቦ ሊሆን ይችላል። አቢግያ “አስተዋይ” ስትሆን ባሏ ናባል ግን “ባለጌና ምግባረ ብልሹ ሰው ነበረ።” ናባል፣ ዳዊትንና አብረውት የነበሩትን ሰዎች ሊረዳቸው ፈቃደኛ ባለመሆኑ እነዚህ ሰዎች እርሱንና ቤተሰቡን ሊያጠፉ ተነስተው ነበር። ይሁን እንጂ አቢግያ ቤተሰቧን ለማዳን እርምጃ ወሰደች። ለዳዊትና ለሰዎቹ የሚሆን ምግብ በአህያዎች ላይ ጭና ስትሄድ መሣሪያ የታጠቁትን እነዚህን ሰዎች መንገድ ላይ አገኘቻቸው። አቢግያ፣ ዳዊትን እንዳየችው ከአህያዋ ወርዳ እግሩ ላይ በመውደቅ የችኮላ እርምጃ እንዳይወስድ ተማጸነችው። ዳዊትም በሁኔታው ልቡ ስለተነካ አቢግያን እንዲህ አላት:- “ዛሬ እንድታገኚኝ ወደ እኔ የላከሽ፣ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን። . . . ስለ በጎ ሐሳብሽ አንቺም የተባረክሽ ሁኚ።”—1 ሳሙኤል 25:2-33

18. ሚስቶች የትዳር ጓደኛቸው ያልሆነ ሰው እንደሚወዳቸው ቢገልጽላቸው የማንን ምሳሌ ሊያስታውሱ ይገባል? ለምንስ?

18 ለሚስቶች ግሩም ምሳሌ የምትሆነው ሌላዋ ወጣት ደግሞ ለጋብቻ ለታጨችለት ተራ እረኛ ታማኝ የነበረችው ሱላማጢሷ ልጃገረድ ናት። አንድ ባለጸጋ ንጉሥ ይህችን ወጣት እንደወደዳት ቢገልጽላትም እርሷ ግን ለእረኛው ያላት ፍቅር ጠንካራ ነበር። ወጣቱን እረኛ ምን ያህል እንደምትወደው ስትገልጽ እንዲህ ብላለች:- “በልብህ እንዳለ፣ በክንድህም እንደምትይዘው ማኅተም አስቀምጠኝ፤ ፍቅር እንደ ሞት የበረታች . . . ናትና፤ . . . የውሃ ብዛት ፍቅርን ሊያጠፋ አይችልም፣ ፈሳሾችም አያሰጥሟትም።” (ማሕልየ መሓልይ 8:6, 7) ለጋብቻ የቀረበላቸውን ጥያቄ የሚቀበሉ ሴቶች ሁሉ እንደዚህች ወጣት ለባሎቻቸው ታማኝ ለመሆንና እነርሱን በጥልቅ ለማክበር ቁርጥ ውሳኔ ሊያደርጉ ይገባል።

ተጨማሪ መለኮታዊ ምክር

19, 20. (ሀ) ሚስቶች ለባሎቻቸው መገዛት ያለባቸው ለምንድን ነው? (ለ) ሚስቶች የማንን ግሩም ምሳሌ መኮረጅ ይችላሉ?

19 በመጨረሻም ይህ የጥናት ርዕስ በተመሠረተበት “ሚስቶች ሆይ፤ . . . ለባሎቻችሁም ተገዙ” በሚለው ጥቅስ ዙሪያ የሚገኙትን ሐሳቦች እንመልከት። (ኤፌሶን 5:22) ይህ ዓይነቱ ተገዢነት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ጥቅሱ በመቀጠል “ክርስቶስ፣ . . . [የቤተ ክርስቲያን] ራስ እንደ ሆነ ሁሉ፣ ባልም የሚስቱ ራስ ነውና” ይላል። በመሆኑም “ቤተ ክርስቲያን ለክርስቶስ እንደምትገዛ፣ ሚስቶችም ለባሎቻቸው በማንኛውም ነገር እንደዚሁ መገዛት ይገባቸዋል” የሚል ማሳሰቢያ ለሚስቶች ተሰጥቷል።—ኤፌሶን 5:23, 24, 33

20 ሚስቶች ይህንን መመሪያ ለመታዘዝ፣ በቅቡዓን ክርስቲያኖች የተገነባውን የክርስቶስ ጉባኤ ምሳሌ ማጥናት እንዲሁም መኮረጅ ያስፈልጋቸዋል። ሁለተኛ ቆሮንቶስ 11:23-28ን በማንበብ የዚህ ጉባኤ አባል የሆነው ሐዋርያው ጳውሎስ ራሱ ለሆነው ለኢየሱስ ክርስቶስ ታማኝ ለመሆን ሲል የደረሰበትን ተቋቁሞ እንዴት እንደጸና በመመልከት ትምህርት እንድትወስዱ እናበረታታችኋለን። ልክ እንደ ጳውሎስ፣ ሚስቶችም ሆኑ ሌሎች የጉባኤው አባላት ለኢየሱስ በታማኝነት መገዛት አለባቸው። ሚስቶች ደግሞ ለባሎቻቸው በመገዛት ታማኝነታቸውን ያሳያሉ።

21. ሚስቶች ለባሎቻቸው እንዲገዙ ምን ሊያበረታታቸው ይችላል?

21 በዛሬው ጊዜ የሚገኙ በርካታ ሚስቶች መገዛት የሚለው ሐሳብ ሊያበሳጫቸው ቢችልም ጥበበኛ ሴት ግን እንዲህ ማድረግ የሚያስገኛቸውን ጥቅሞች ታስባለች። ለምሳሌ አንዲት ሚስት፣ አማኝ ያልሆነው ባሏ የአምላክን ሕግጋት ወይም መሠረታዊ ሥርዓቶች እንድትጥስ እስካልጠየቃት ድረስ ለራስነት ሥልጣኑ በሁሉም ነገር መገዛቷ ‘ባሏን በማዳን’ በረከት እንድታገኝ ያስችላት ይሆናል። (1 ቆሮንቶስ 7:13, 16) ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ አምላክ የምትከተለውን መንገድ እንደሚደግፈውና የውድ ልጁን ምሳሌ በመኮረጇ አብዝቶ እንደሚባርካት ማወቋ እርካታ ሊያስገኝላት ይችላል።

ታስታውሳለህ?

• አንዲት ሚስት ባሏን ማክበር ከባድ እንዲሆንባት የሚያደርገው ምን ሊሆን ይችላል?

• አንዲት ሴት ለጋብቻ የቀረበላትን ጥያቄ መቀበል በቁም ነገር ልታስብበት የሚገባ ጉዳይ የሆነው ለምንድን ነው?

• ኢየሱስ ለሚስቶች ምሳሌ የሚሆነው እንዴት ነው? የእርሱን ምሳሌ መከተልስ ምን ጥቅሞች ያስገኛል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንዲት ሴት የጋብቻ ጥያቄ ሲቀርብላት፣ ለመቀበልም ሆነ ላለመቀበል የምታደርገውን ውሳኔ በቁም ነገር ልታስብበት የሚገባው ለምንድን ነው?

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሚስቶች እንደ አቢግያ ካሉት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ሰዎች ምሳሌ ምን ትምህርት ሊያገኙ ይችላሉ?