ቬሰል ካንስፎርት “ከተሃድሶ በፊት የነበረ የለውጥ አራማጅ”
ቬሰል ካንስፎርት “ከተሃድሶ በፊት የነበረ የለውጥ አራማጅ”
በ1517 ስለተጀመረው የፕሮቴስታንት ተሃድሶ የሚያጠኑ ሰዎች ሁሉ ሉተር፣ ቲንደል እና ካልቪን የሚሉትን ስሞች በሚገባ ያውቋቸዋል። ቬሰል ካንስፎርት የተባለውን ሰው የሚያውቁት ግን ጥቂቶች ናቸው። ይህ ሰው “ከተሃድሶ በፊት የነበረ የለውጥ አራማጅ” ተብሎ ተጠርቷል። ስለዚህ ሰው ይበልጥ ማወቅ ትፈልጋለህ?
ቬሰል የተወለደው በ1419 በግሮኒንገን፣ ኔዘርላንድ ነው። በ15ኛው መቶ ዘመን ብዙዎች ትምህርት ቤት የመግባት አጋጣሚ ያልነበራቸው ቢሆንም ቬሰል ይህን አጋጣሚ አግኝቶ ነበር። ቬሰል በትምህርቱ ጎበዝ ነበር፤ ሆኖም ወላጆቹ ያጡ የነጡ ድሆች ስለነበሩ በዘጠኝ ዓመቱ ትምህርቱን ለማቋረጥ ተገደደ። ደግነቱ ባሏ የሞተባት አንዲት ሀብታም ሴት ጎበዝ ተማሪ ስለነበረው ስለ ትንሹ ቬሰል ስትሰማ የትምህርት ቤት ክፍያውን ልትሸፍንለት ፈቃደኛ ሆነች። በዚህም ምክንያት ትምህርቱን መቀጠል ቻለ። ቬሰል ከጊዜ በኋላ የማስትሬት ዲግሪውን ያገኘ ሲሆን ቆየት ብሎም የሃይማኖት ትምህርት ዶክተር የሚል ማዕረግ የተሰጠው ይመስላል።
ቬሰል ከፍተኛ የእውቀት ጥማት ነበረው። ይሁን እንጂ በጊዜው የነበሩት ቤተ መጻሕፍት ጥቂት ነበሩ። በእርሱ ዘመን እያንዳንዱ ፊደል በተቀረጸባቸው የተለያዩ ብረቶች አማካኝነት ሕትመት ይካሄድ የነበረ ቢሆንም አብዛኞቹ መጻሕፍት በእጅ የተጻፉና ውድ ነበሩ። ቬሰል፣ ወደተለያዩ ቤተ መጻሕፍትና ገዳማት በመሄድ እምብዛም የማይገኙ ጥንታዊ ጽሑፎችን እንዲሁም የጠፉ መጻሕፍትን ከሚያፈላልጉ ምሑራን አንዱ ነበር። እነዚህ ምሑራን ካገኟቸው ጽሑፎች የቀሰሙትን እውቀት አንዳቸው ለሌላው ያካፍላሉ። ቬሰል ከፍተኛ እውቀት ያካበተ ሲሆን የግል ማስታወሻ ደብተሩ ጥንታዊ ከሆኑ የግሪክኛና የላቲን ጽሑፎች በተወሰዱ ጥቅሶች እንዲሁም ሐሳቦች የተሞላ ነው። ሌሎች የሃይማኖት ምሑራን፣ ቬሰል እነርሱ ሰምተው የማያውቋቸውን በርካታ ነገሮች በማወቁ በጥርጣሬ ይመለከቱት ነበር። ቬሰል ማጂስተር ኮንትራዲክቲዮኒስ ወይም ቀንደኛው ተጻራሪ ተብሎ ተጠርቷል።
“ወደ ክርስቶስ ለምን አትመራኝም?”
ሃይማኖታዊ ተሃድሶ ከመካሄዱ ከ50 ዓመታት ገደማ በፊት ቬሰል ከቶማስ ኣ ኬምፒስ (1379-1471 ገደማ) ጋር ተገናኝቶ ነበር፤ ይህ ሰው ታዋቂ የሆነው ደ ኢሚቴቲዮኒ ክሪስቲ (ክርስቶስን መምሰል) የተባለው መጽሐፍ ደራሲ እንደሆነ በሰፊው ይታመናል። ቶማስ ኣ ኬምፒስ፣ ብሬትረን ኦቭ ዘ ኮመን ላይፍ በመባል የሚታወቀው ለአምላክ ያደሩ ሆኖ የመኖርን አስፈላጊነት የሚያጎላ እንቅስቃሴ አባል ነበር። ቶማስ ኣ ኬምፒስ፣ እርዳታ ለማግኘት ወደ ማርያም እንዲጸልይ ቬሰልን በተለያዩ አጋጣሚዎች ያበረታታው እንደነበር የቬሰልን የሕይወት ታሪክ የጻፉት ሰው ገልጸዋል። ቬሰል “ሸክማቸው የከበዳቸው ሁሉ ወደ እርሱ እንዲመጡ በደግነት ወደሚጋብዘው ወደ ክርስቶስ ለምን አትመራኝም?” የሚል መልስ ሰጥቶታል።
ቬሰል ቄስ ሆኖ መሾምን ይቃወም እንደነበር ይነገራል። የቀሳውስት ክፍል እንደሆነ ለማሳየት ፀጉሩን ለመላጨት ፈቃደኛ ያልሆነው ለምን እንደሆነ ሲጠየቅ የማሰብ ችሎታው እስካልተነካ ድረስ ተሰቅሎ መሞትን እንደማይፈራ ተናግሮ ነበር። ቬሰል ይህን ያለው ቀሳውስት ሕግ ፊት ስለማይቀርቡ ሳይሆን አይቀርም፤ በርካታ ቀሳውስት ወንጀል ቢፈጽሙም ቄስ በመሆናቸው ከሞት ማምለጥ ይችሉ የነበረ ይመስላል። ቬሰል አንዳንድ የተለመዱ ሃይማኖታዊ ልማዶችንም ይቃወም ነበር። ለአብነት ያህል፣ በዘመኑ በነበረው ዳያሎገስ ሚራኩሎረም በተባለው ታዋቂ መጽሐፍ ላይ የሚገኙትን ተአምራዊ ክንውኖች ለማመን ፈቃደኛ ባለመሆኑ ትችት ይሰነዘርበት ነበር። ቬሰል ለዚህ ምላሽ ሲሰጥ “ቅዱሳን መጻሕፍትን ማንበቡ የተሻለ ነው” ብሏል።
“የምናውቀው የምንጠይቀውን ያህል ብቻ ነው”
ቬሰል የዕብራይስጥና የግሪክኛ ቋንቋን ያጠና ሲሆን ስለ ቀድሞዎቹ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ጽሑፎች ሰፊ እውቀት ነበረው። ቬሰል የኖረው ከኢራስመስና ከሮችሊን በፊት በመሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ ለተጻፈባቸው ቋንቋዎች ልዩ ፍቅር ማዳበሩ የሚገርም ነው። a ሃይማኖታዊ ተሃድሶ ከመካሄዱ በፊት የግሪክኛን ቋንቋ የሚያውቁ ሰዎች በጣም ውስን ነበሩ። በጀርመን የነበሩት ግሪክኛ የሚያውቁ ምሑራን በጣት የሚቆጠሩ ሲሆኑ ቋንቋውን ለመማር የሚያገለግሉ መሣሪያዎችም አልነበሩም። በ1453 የኮንስታንቲኖፕል ከተማ ከወደቀች በኋላ፣ ቬሰል ወደ ምዕራቡ ዓለም ከሸሹ ግሪካውያን መነኮሳት ጋር ተገናኝቶ የግሪክኛን ቋንቋ መሠረታዊ ነገሮች ሳይማር አልቀረም። በዚያ ወቅት ዕብራይስጥ አይሁዳውያን ብቻ የሚናገሩት ቋንቋ ሲሆን ቬሰልም የቋንቋውን መሠረታዊ ነገሮች የተማረው ወደ አይሁድ እምነት ከተለወጡ ሰዎች ይመስላል።
ቬሰል ለመጽሐፍ ቅዱስ ይህ ነው የማይባል ፍቅር ነበረው። መጽሐፍ ቅዱስን በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት እንደተጻፈ መጽሐፍ አድርጎ ይመለከተው የነበረ ከመሆኑም በላይ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት በሙሉ እርስ በርስ እንደሚስማሙ ያምን ነበር። ቬሰል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አተረጓጎም በዙሪያቸው ካለው ሐሳብ ጋር የሚስማማ መሆን እንዳለበትና ሐሳቡን ማጣመም እንደማይገባ ይገልጽ ነበር። ማንኛውም የተጣመመ ማብራሪያ መናፍቃዊ ትምህርት እንደሆነ ሊጠረጠር እንደሚገባ ይሰማው ነበር። ቬሰል ከሚወዳቸው ጥቅሶች መካከል “ፈልጉ፣ ታገኛላችሁ” የሚለው በማቴዎስ 7:7 ላይ የሚገኘው ሐሳብ አንዱ ነው። በዚህ ጥቅስ መሠረት ቬሰል ጥያቄዎችን መጠየቅ ጠቃሚ እንደሆነ አጥብቆ ያምን የነበረ ሲሆን “የምናውቀው የምንጠይቀውን ያህል ብቻ ነው” በማለት ይናገር ነበር።
አስገራሚ ጥያቄ
በ1473 ቬሰል ሮምን ሲጎበኝ ከሊቀ ጳጳስ ሲክስተስ አራተኛ ጋር የመነጋገር አጋጣሚ አገኘ። የእኚህ ሊቀ ጳጳስና ከእርሳቸው በኋላ የነበሩት አምስት ተተኪዎቻቸው ዓይን ያወጣ ምግባረ ብልሹነት ከጊዜ በኋላ የፕሮቴስታንት የተሃድሶ እንቅስቃሴ እንዲጀመር ምክንያት ሆኗል። ባርባራ ተክማን የተባሉት የታሪክ ምሑር እንደገለጹት ሲክስተስ አራተኛ “ያለ ምንም እፍረት፣ በገሃድ እንዲሁም ማቆሚያ በሌለው መልኩ የግል ጥቅምን ማሳደድና በኃይል ላይ የተመሠረተ ፖለቲካዊ አካሄድን መከተል” እንዲለመድ አድርገዋል። ሊቀ ጳጳሱ ቤተሰባቸውንና ወዳጆቻቸውን ለመጥቀም ሲሉ ሥልጣናቸውን በገሃድ አላግባብ መጠቀማቸው ለምዕመናኑም ሆነ ለሌላው ሕዝብ አስደንጋጭ ነበር። አንድ ታሪክ ጸሐፊ፣ ሲክስተስ የሊቀ ጳጳሱን ቢሮ በቤተሰቦቻቸው ለመሙላት ሳያስቡ እንዳልቀሩ ገልጸዋል። እንዲህ ያለውን ምግባረ ብልሹነት ለማውገዝ የደፈሩት ጥቂቶች ብቻ ነበሩ።
ቬሰል ካንስፎርት ግን የተለየ አመለካከት ነበረው። አንድ ቀን ሲክስተስ፣ ቬሰልን “ልጄ፣ የምትፈልገውን ማንኛውንም ነገር ጠይቅ፤ እንሰጥሃለን” አሉት። ቬሰልም ቀበል አድርጎ እንዲህ የሚል ምላሽ ሰጠ:- “ቅዱስ አባት ሆይ፣ . . . እርስዎ በምድር ላይ የታላቁን ካህንና እረኛ ቦታ ስለያዙ፣ . . . ይህን ላቅ ያለ ኃላፊነትዎን . . . ታላቁ የበጎች እረኛ ሲመጣ ‘ደግ አድርገሃል፤ አንተ መልካም ታማኝ አገልጋይ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ’ እንዲልዎት በሚያደርግ መንገድ እንዲወጡ እጠይቅዎታለሁ።” ሲክስተስ ይህን የማድረግ ኃላፊነት እንዳለባቸው ከገለጹ በኋላ ቬሰል ለራሱ አንድ ነገር እንዲጠይቅ አበረታቱት። ቬሰልም “እንግዲያው ከቫቲካን ቤተ መጻሕፍት ውስጥ የግሪክኛና የዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱሶችን እንዲሰጡኝ እጠይቅዎታለሁ” በማለት መለሰ። ሊቀ ጳጳሱ የጠየቀውን ከሰጡት በኋላ፣ ቬሰል ሞኝ እንደሆነና የጵጵስና ማዕረግ እንዲሰጠው ሊጠይቅ ይገባ እንደነበረ ተናገሩ።
“ውሸትና ስሕተት”
ሲክስተስ፣ በአሁኑ ጊዜ ታዋቂ የሆነውን ሰስቲን የተባለ የጸሎት ቤት ለመገንባት ገንዘብ ስላስፈለጋቸው ለሞቱ ሰዎች የኃጢአት ሥርየት የመሸጥን ልማድ መከተል ጀመሩ። ይህ ልማድም ሰፊ ተቀባይነት አገኘ። ቪካርስ ኦቭ ክራይስት—ዘ ዳርክ ሳይድ ኦቭ ዘ ፓፓሲ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ብሏል:- “የትዳር ጓደኛቸውን በሞት ያጡ ወንዶችና ሴቶች እንዲሁም ልጆቻቸውን በሞት የተነጠቁ ወላጆች ቤተሰቦቻቸውን ከመንጽሔ ለማውጣት ሲሉ
ጥሪታቸውን ያሟጥጡ ነበር።” ተራው ሕዝብ፣ ሊቀ ጳጳሱ የሞቱ ዘመዶቻቸውን ወደ ሰማይ እንዲሄዱ ማድረግ እንደሚችሉ ሙሉ እምነት ስለነበረው ይህን ልማድ በደስታ ተቀበለው።ቬሰል ግን ሊቀ ጳጳሱን ጨምሮ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ኃጢአትን ይቅር ማለት እንደማትችል አጥብቆ ያምን ነበር። ቬሰል የኃጢአት ሥርየትን የመሸጥ ልማድን “ውሸትና ስሕተት” በማለት በግልጽ አውግዞታል። የኃጢአት ይቅርታ ለማግኘት ለቀሳውስት የመናዘዝን አስፈላጊነትም አያምንበትም ነበር።
ከዚህም በተጨማሪ ቬሰል፣ ሊቀ ጳጳሱ አይሳሳቱም የሚለውን አመለካከት አልተቀበለውም፤ ሊቀ ጳጳሳቱም ስሕተት ስለሚሠሩ ሰዎች ሁልጊዜ እነርሱን እንዲያምኑ የሚጠበቅባቸው ከሆነ የእምነቱ መሠረት ጠንካራ እንደማይሆን ይናገር ነበር። ቬሰል፣ “ሊቀ ጳጳሳቱ የአምላክን ትእዛዝ ጥሰው የራሳቸውን ሰው ሠራሽ ትእዛዛት የሚያወጡ ከሆነ . . . የሚያደርጉትም ሆነ የሚናገሩት ነገር ከንቱ ነው” በማለት ጽፏል።
ቬሰል ለሃይማኖታዊው ተሃድሶ መንገድ ጠርጓል
ቬሰል በ1489 ሞተ። ይህ ምሑር በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ የሚፈጸሙትን አንዳንድ የተሳሳቱ ድርጊቶችን ቢያወግዝም እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ ካቶሊክ ነበር። የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንም መናፍቅ ብላ አላወገዘችውም። ቬሰል ከሞተ በኋላ ግን አክራሪ የካቶሊክ መነኮሳት፣ የእርሱ ጽሑፎች ከቤተ ክርስቲያኗ ትምህርቶች ጋር ሙሉ በሙሉ ስለማይስማሙ ሊያጠፏቸው ጥረት አድርገው ነበር። በሉተር ዘመን ቬሰል የሚለው ስም ጨርሶ ተረስቶ ነበር ማለት ይቻላል፤ ከሥነ ጽሑፍ ሥራዎቹ መካከልም ለሕትመት የበቃ አልነበረም። በእጅ ከተገለበጡት ጽሑፎቹ መካከል የተረፉት በጣም ጥቂት ነበሩ። በመጨረሻም በ1520 እና በ1522 መካከል በነበሩት ዓመታት ውስጥ የቬሰል ሥራዎች የመጀመሪያ እትም ወጣ። ይህ እትም ሉተር የቬሰልን ጽሑፎች በማድነቅ የጻፈውን ደብዳቤም ይዞ ነበር።
ቬሰል እንደ ሉተር የለውጥ አራማጅ ባይሆንም እንኳ ሃይማኖታዊ ተሃድሶ እንዲካሄድ ያደረጉትን አንዳንድ ስህተቶች በግልጽ አውግዟል። እንዲያውም የማክሊንቶክና ስትሮንግ ሳይክሎፔዲያ፣ ቬሰል “የጀርመን ዝርያ ካላቸው ሰዎች ሁሉ ለተሃድሶው መንገድ የጠረገ በጣም ጠቃሚ ሰው” እንደሆነ ይገልጻል።
ሉተር፣ ቬሰል የእርሱን አመለካከት እንደሚደግፍ አድርጎ ይመለከተው ነበር። ኮርኔሊየስ ኦውከስቲን የተባሉት ደራሲ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “ሉተር እርሱ የነበረበትን ዘመንና ያጋጠመውን ሁኔታ ከኤልያስ ጋር አመሳስሎታል። ነቢዩ ኤልያስ የአምላክን ውጊያ ብቻውን እንደሚፋለም እንደተሰማው ሁሉ ሉተርም ከቤተ ክርስቲያኗ ጋር በሚያደርገው ትግል ብቻውን እንደሆነ ተሰምቶት ነበር። የቬሰልን ሥራዎች ካነበበ በኋላ ግን ጌታ ‘በእስራኤል ውስጥ ቅሬታ’ እንዳዳነ ተገነዘበ።” “እንዲያውም ሉተር፣ ‘የቬሰልን ጽሑፎች ከዚህ ቀደም አንብቤ ቢሆን ኖሮ ጠላቶቼ ሉተር ሐሳቡን ሁሉ የወሰደው ከቬሰል ነው ብለው ያስቡ ነበር፤ አመለካከቱ ከእኔ ጋር በጣም ይስማማል’ በማለት ተናግሯል።” b
“ታገኛላችሁ”
የፕሮቴስታንት ሃይማኖታዊ ተሃድሶ በድንገት የተከሰተ ነገር አልነበረም። በተለያዩ ወቅቶች የመነጩት ሐሳቦች ይህ ተሃድሶ እንዲካሄድ መንስኤ ሆነዋል። ቬሰል የሊቀ ጳጳሳቱ የሥነ ምግባር ዝቅጠት ውሎ አድሮ ለውጥ እንዲካሄድ ማድረጉ እንደማይቀር ተገንዝቦ ነበር። በአንድ ወቅት ለአንድ ተማሪ:- “ታታሪው ተማሪ በአንተ የሕይወት ዘመን፣ እውነተኛ ክርስቲያኖች የሆኑ ምሑራን ሁሉ . . . ተከራካሪ የሆኑ የሃይማኖት ሊቃውንትን ትምህርቶች የማይቀበሉበት ጊዜ ይመጣል” ብሎት ነበር።
ቬሰል በጊዜው የነበሩትን አንዳንድ ስህተቶችና የሚታየውን ምግባረ ብልሹነት ቢያስተውልም የተሟላውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ብርሃን መግለጥ አልቻለም። ያም ሆኖ ግን ቬሰል፣ መጽሐፍ ቅዱስ ሊነበብና ሊጠና የሚገባው መጽሐፍ እንደሆነ ይሰማው ነበር። ኤ ሂስትሪ ኦቭ ክርስቺያኒቲ የተባለው መጽሐፍ እንደሚገልጸው ቬሰል “መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ ቅዱስ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ በመሆኑ ከእምነት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ረገድ የመጨረሻው ባለ ሥልጣን እንደሆነ ያምን ነበር።” በዘመናችንም እውነተኛ ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ የአምላክ ቃል እንደሆነ ያምናሉ። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) በአሁኑ ጊዜ ግን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች የተሰወሩ ወይም ለመረዳት አስቸጋሪ አይደሉም። ቀደም ካሉት ዓመታት ይበልጥ በዛሬው ጊዜ “ፈልጉ፣ ታገኛላችሁ” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት እውነት መሆኑ እየታየ ነው።—ማቴዎስ 7:7፤ ምሳሌ 2:1-6
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a እነዚህ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ በተጻፈባቸው ቋንቋዎች ላይ ለሚካሄደው ጥናት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል። በ1506 ሮችሊን የዕብራይስጥን ቋንቋ ሰዋስው የያዘ መጽሐፍ ያሳተመ ሲሆን ይህ መጽሐፍ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን በጥልቅ ለማጥናት አስችሏል። ኢራስመስ ደግሞ ለክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም መሠረት የሚሆን የግሪክኛ ጽሑፍ በ1516 አዘጋጅቷል።
b ቬሰል ካንስፎርት (1419-1489) ኤንድ ኖርዘርን ሂውማኒዝም፣ ገጽ 9, 15
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ቬሰል እና የአምላክ ስም
ቬሰል በጽሑፎቹ ውስጥ የአምላክን ስም በብዙ ቦታዎች ላይ “ዮሓቫ” በማለት አስቀምጦታል። ሆኖም ቬሰል “ዪሖቫ” የሚለውን ስም ቢያንስ በሁለት አጋጣሚዎች ተጠቅሞበታል። ሃይኮ ኦበርማን የተባሉት ደራሲ ቬሰል እንደሚከተለው ያለ ስሜት እንደነበረው ተናግረዋል:- ቶማስ አኩዋይነስ እና ሌሎች ሰዎች የዕብራይስጥን ቋንቋ ቢያውቁ ኖሮ “ለሙሴ የተገለጠለት አምላክ ስም ‘ያለና የሚኖር’ ሳይሆን ‘የምሆነውን እሆናለሁ’ የሚል ትርጉም እንዳለው ይገነዘቡ ነበር።” c አዲስ ዓለም ትርጉም “መሆን የሚያስፈልገኝን ሁሉ እሆናለሁ” በማለት የአምላክን ስም ትክክለኛ ትርጉም አስቀምጦታል።—ዘፀአት 3:13, 14
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
c ቬሰል ካንስፎርት (1419-1489) ኤንድ ኖርዘርን ሂውማኒዝም፣ ገጽ 105
[ምንጭ]
Manuscript: Universiteitsbibliotheek, Utrecht
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቬሰል፣ ሊቀ ጳጳስ ሲክስተስ አራተኛ የተቀበሉትን የኃጢአት ሥርየትን የመሸጥ ልማድ አውግዞታል