እውነተኛውን አምልኮ መለየት የምንችለው እንዴት ነው?
እውነተኛውን አምልኮ መለየት የምንችለው እንዴት ነው?
አብዛኞቹ ሃይማኖቶች ትምህርታቸው ከአምላክ የመነጨ እንደሆነ ይናገራሉ። በመሆኑም የኢየሱስ ሐዋርያ የሆነው ዮሐንስ የሰጠውን የሚከተለውን ማሳሰቢያ ልብ ማለት ያስፈልጋል:- “ወዳጆች ሆይ፤ መንፈስን ሁሉ አትመኑ፤ ነገር ግን መናፍስት ከእግዚአብሔር መሆናቸውን መርምሩ፤ ምክንያቱም ብዙ ሐሰተኞች ነቢያት ወደ ዓለም ወጥተዋልና።” (1 ዮሐንስ 4:1) ታዲያ አንድ ትምህርት ከአምላክ የመነጨ መሆኑን መመርመር የምንችለው እንዴት ነው?
ከአምላክ የመነጨ ትምህርት ሁሉ የእርሱን ባሕርያት በተለይም ዋነኛ ባሕርይው የሆነውን ፍቅሩን ያንጸባርቃል። ለአብነት ያህል፣ የአምላክ ፍቅር መግለጫ የሆነው የማሽተት ችሎታችን በዕፅዋትና በአበቦች መዓዛ እንዲሁም በትኩስ ዳቦ ሽታ ለመደሰት ያስችለናል። አምላክ እንደሚወደን የሚያሳየው የማየት ችሎታችንም የሕፃናትን ፈገግታና ቢራቢሮዎችን እንዲሁም ጀንበር ስትጠልቅ ለመመልከት ያስችለናል። አስደሳች ጣዕመ ዜማዎችን፣ የአእዋፍን ዝማሬ ወይም የምንወደውን ሰው ድምፅ የመስማት ችሎታችንም ሌላው የአምላክ ፍቅር መግለጫ ነው። አሁን ፍጹም ባንሆንም እንኳ አፈጣጠራችን ራሱ የአምላክን ፍቅር ያንጸባርቃል። ኢየሱስ “ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ [“ደስተኛ፣” NW] ነው” በማለት የተናገራቸውን ቃላት እውነተኝነት ብዙውን ጊዜ በሕይወታችን ውስጥ የምንመለከተው ለዚህ ነው። (የሐዋርያት ሥራ 20:35) የተፈጠርነው “በእግዚአብሔር መልክ” በመሆኑ ለሌሎች ፍቅር ማሳየት ያስደስተናል። (ዘፍጥረት 1:27) ይሖዋ በርካታ ባሕርያት ቢኖሩትም ዋነኛ ባሕርይው ፍቅር ነው።
በመሆኑም አምላክ ያስጻፋቸው ጽሑፎች የእርሱን ፍቅር የሚያንጸባርቁ መሆን አለባቸው። በዓለም ላይ የሚገኙት ሃይማኖቶች በርካታ ጥንታዊ ጽሑፎች አሏቸው። እነዚህ ጽሑፎች የአምላክን ፍቅር በማንጸባረቅ ረገድ ምን ያህል ተሳክቶላቸዋል?
ሐቁ እንደሚያሳየው አብዛኞቹ ጥንታዊ የሃይማኖት ጽሑፎች አምላክ ምን ያህል እንደሚወደንም ሆነ እኛ አምላክን እንዴት ልንወደው እንደምንችል እምብዛም አይገልጹም። በመሆኑም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች “አምላክ እንደሚወደን ከፍጥረት ሥራዎቹ መመልከት የምንችል ቢሆንም ሥቃይና ክፋት ያልተወገደው ለምንድን ነው?” ብለው ሲጠይቁ መልስ አያገኙም። የአምላክን ፍቅር በሚገባ የሚገልጸው ጥንታዊ ጽሑፍ መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ለሌሎች ፍቅር ማሳየት የምንችለው እንዴት እንደሆነም ያስተምራል።
ስለ ፍቅር የሚገልጽ መጽሐፍ
የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ ‘የፍቅር አምላክ’ እንደሆነ ይገልጻል። (2 ቆሮንቶስ 13:11) ይሖዋ፣ ለመጀመሪያዎቹ ሰብዓዊ ፍጥረታት ከበሽታና ከሞት ነጻ የሆነ ሕይወት የሰጣቸው በፍቅሩ ተገፋፍቶ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ይሁን እንጂ የሰው ልጆች በአምላክ ሥልጣን ላይ በማመጻቸው ለሥቃይ ተዳረጉ። (ዘዳግም 32:4, 5፤ ሮሜ 5:12) ይሖዋ የሰው ልጆች ያጡትን ነገር መልሰው እንዲያገኙ ሲል የወሰደውን እርምጃ በተመለከተ የአምላክ ቃል እንዲህ ይላል:- “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስከ መስጠት ድረስ ዓለምን እንዲሁ ወዶአል።” (ዮሐንስ 3:16) አምላክ፣ ታዛዥ ለሆኑ የሰው ልጆች እንደገና ሰላምን ለማስፈን በኢየሱስ የሚመራ ፍጹም መንግሥት እንዳዘጋጀ የሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብም የአምላክን ፍቅር ይበልጥ ግልጽ ያደርግልናል።—ዳንኤል 7:13, 14፤ 2 ጴጥሮስ 3:13
መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ልጅ ያለበትን ግዴታ ጠቅለል አድርጎ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “‘ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ሐሳብህ ውደድ፤’ ይህ የመጀመሪያውና ከሁሉ የሚበልጠው ትእዛዝ ነው፤ ሁለተኛውም ያንኑ ይመስላል፤ ይህም፣ ‘ጎረቤትህን እንደ ራስህ ውደድ’ የሚለው ነው፤ ሕግና ነቢያት በሙሉ በእነዚህ ሁለት ትእዛዛት ላይ የተንጠለጠሉ ናቸው።” (ማቴዎስ 22:37-40) መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት እንደተጻፈ የሚገልጽ ሐሳብ ይዟል። ይህ መጽሐፍ፣ የይሖዋን ባሕርያት በግልጽ ስለሚያንጸባርቅ ‘ከፍቅር አምላክ’ የመነጨ እንደሆነ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—2 ጢሞቴዎስ 3:16
በዚህ መሥፈርት አማካኝነት በትክክል ከአምላክ የመነጩት ጥንታዊ ጽሑፎች የትኞቹ እንደሆኑ ማወቅ እንችላለን። እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮች ፍቅር በማሳየት ረገድ አምላክን ስለሚመስሉ፣ ፍቅር እውነተኛ አምላኪዎችን ለመለየትም ያስችለናል።
አምላክን የሚወዱ ሰዎች ተለይተው የሚታወቁት እንዴት ነው?
አምላክን ከልባቸው የሚወዱ ሰዎች በተለይ መጽሐፍ ቅዱስ ‘የመጨረሻው ዘመን’ ብሎ በሚጠራው በዛሬው ጊዜ ከሌሎች ተለይተው ይታወቃሉ። ከመቼውም ጊዜ የበለጠ በአሁኑ ወቅት ሰዎች “ራሳቸውን የሚወዱ . . . ገንዘብን የሚወዱ . . . ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ” ሆነዋል።—2 ጢሞቴዎስ 3:1-4
ታዲያ አምላክን የሚወዱ ሰዎችን እንዴት ለይተህ ማወቅ ትችላለህ? መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔርን መውደድ ትእዛዛቱን መፈጸም ነው” ይላል። (1 ዮሐንስ 5:3) ሰዎች ለአምላክ ያላቸው ፍቅር የመጽሐፍ ቅዱስን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ለማክበር ያነሳሳቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ የጾታ ግንኙነትንና ጋብቻን በተመለከተ በአምላክ ቃል ውስጥ የሠፈረ ሕግ አለ። የጾታ ግንኙነት መፈጸም ያለባቸው የተጋቡ ሰዎች ብቻ ሲሆኑ ጋብቻም ዘላቂ ጥምረት ሊሆን ይገባዋል። (ማቴዎስ 19:9፤ ዕብራውያን 13:4) በስፔን የምትኖርና የሃይማኖት ትምህርት የምትከታተል አንዲት ሴት፣ የይሖዋ ምሥክሮች የመጽሐፍ ቅዱስን የሥነ ምግባር ሕግጋት በሚማሩበት ስብሰባ ላይ ከተገኘች በኋላ እንዲህ በማለት ተናግራለች:- “ከስብሰባው ስመለስ፣ በቀረቡት ትምህርት ሰጪ የሆኑ ቅዱስ ጽሑፋዊ ንግግሮች እንዲሁም በእነዚህ ሰዎች መካከል በሚታየው አንድነት፣ በመልካም ባሕርያቸውና ላቅ ብሎ በሚታየው የሥነ ምግባር አቋማቸው ተበረታትቼ ነበር።”
እውነተኛ ክርስቲያኖች አምላክን ከመውደዳቸውም በተጨማሪ ለሰዎች በሚያሳዩት ፍቅር በቀላሉ ተለይተው ይታወቃሉ። እነዚህ ክርስቲያኖች የሰው ዘር ብቸኛ ተስፋ ስለሆነው የአምላክ መንግሥት ለሌሎች የመስበኩን ሥራ ከማንኛውም ነገር በላይ ከፍ አድርገው ይመለከቱታል። (ማቴዎስ 24:14) ሰዎች ስለ አምላክ እውቀት እንዲያገኙ ከመርዳት የበለጠ ዘላቂ ጥቅም የሚያመጣ ነገር የለም። (ዮሐንስ 17:3) እውነተኛ ክርስቲያኖች ፍቅራቸውን በሌሎች መንገዶችም ያሳያሉ። በሥቃይ ላይ ለሚገኙ ሰዎች ጠቃሚ እርዳታ ያበረክታሉ። ለአብነት ያህል፣ በጣሊያን የመሬት መናወጥ ከፍተኛ ጉዳት ባደረሰበት ወቅት በአካባቢው የሚታተም አንድ ጋዜጣ የይሖዋ ምሥክሮች ስላደረጉት ነገር እንዲህ በማለት ዘግቧል:- “መከራ የደረሰባቸው ሰዎች የየትኛውም ሃይማኖት አባላት ቢሆኑ የእርዳታ እጃቸውን በመዘርጋት ጠቃሚ ተግባር አከናውነዋል።”
እውነተኛ ክርስቲያኖች ለአምላክና ለሌሎች ሰዎች ፍቅር ከማሳየታቸውም በተጨማሪ እርስ በርሳቸው ይዋደዳሉ። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- “አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ፤ ይኸውም እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ ነው፤ እንግዲህ እኔ እንደ ወደድኋችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ። እርስ በርሳችሁ ብትዋደዱ፣ ሰዎች ሁሉ የእኔ ደቀ መዛሙርት እንደ ሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ።”—ዮሐንስ 13:34, 35
ታዲያ በእውነተኛ ክርስቲያኖች መካከል ያለው ፍቅር ያን ያህል ለየት ብሎ የሚታይ ነው? ኤማ የተባለች አንዲት የቤት ሠራተኛ እንደዚህ ተሰምቷታል። ኤማ የምትሠራው በላ ፓዝ፣ ቦሊቪያ ሲሆን በዚያ ባለው የዘር መከፋፈል ሳቢያ በሰዎች የኑሮ ደረጃ ላይ ልዩነት ይታያል። ኤማ እንዲህ ብላለች:- “ለመጀመሪያ ጊዜ በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ በተገኘሁበት ወቅት ጥሩ አለባበስ ያለው አንድ ሰው አንዲት ሕንዳዊት ሴት አጠገብ ተቀምጦ ሲያነጋግራት ተመለከትሁ። ከዚያ ቀደም እንደዚህ ያለ ሁኔታ አይቼ አላውቅም ነበር። በዚያች ቅጽበት እነዚህ ሰዎች የአምላክ ሕዝቦች እንደሆኑ ተሰማኝ።” በተመሳሳይም ሚሪያም የተባለች አንዲት ብራዚላዊት ወጣት እንዲህ ብላለች:- “በቤተሰቤ መካከል ሆኜም እንኳ እንዴት ደስተኛ መሆን እንደምችል አላውቅም ነበር። ለመጀመሪያ ጊዜ ፍቅር በተግባር ሲገለጽ የተመለከትኩት በይሖዋ ምሥክሮች መካከል
ነው።” በዩናይትድ ስቴትስ የአንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ የዜና ክፍል ኃላፊም እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “ብዙ ሰዎች የእናንተ ሃይማኖት እንደሚያስተምረው ቢኖሩ ኖሮ ይህች አገር አሁን ባለችበት ሁኔታ ባልተገኘች ነበር። የዜና ዘጋቢ ስሆን ድርጅታችሁ በፈጣሪ ላይ ባላችሁ ጠንካራ እምነትና በፍቅር ላይ የተመሠረተ እንደሆነ አውቃለሁ።”እውነተኛውን አምልኮ ፈልግ
ፍቅር የእውነተኛው አምልኮ መለያ ምልክት ነው። ኢየሱስ እውነተኛውን አምልኮ ማግኘትን፣ ትክክለኛውን ጎዳና ከማግኘትና በዚያ ለመጓዝ ከመምረጥ ጋር አመሳስሎታል። ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራው ብቸኛው መንገድ ይህ ነው። ኢየሱስ ይህን መንገድ በተመለከተ እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “በጠባቡ በር ግቡ፤ ወደ ጥፋት የሚወስደው መንገድ ትልቅ፣ በሩም ሰፊ ነውና፤ ብዙዎችም በዚያ ይገባሉ። ወደ ሕይወት የሚያደርሰው ግን መንገዱ ቀጭን፣ በሩም ጠባብ ነው፤ የሚገቡበትም ጥቂቶች ብቻ ናቸው።” (ማቴዎስ 7:13, 14) በእውነተኛው አምልኮ ጎዳና ላይ ከአምላክ ጋር በአንድነት የሚጓዘው የእውነተኛ ክርስቲያኖች ቡድን አንድ ብቻ ነው። በመሆኑም የምትመርጠው ሃይማኖት ለውጥ ያመጣል። ይህንን መንገድ ካገኘኸውና በእርሱ ላይ ለመጓዝ ከመረጥህ ከሁሉ የተሻለውን የሕይወት ጎዳና አግኝተሃል፤ ምክንያቱም ይህ መንገድ የፍቅር ጎዳና ነው።—ኤፌሶን 4:1-4
በእውነተኛው አምልኮ ጎዳና ላይ ስትጓዝ ምን ያህል ደስተኛ ልትሆን እንደምትችል አስበው! በዚህ ጎዳና ላይ መጓዝ ከአምላክ ጋር እንደመሄድ ነው። አምላክ ከሌሎች ጋር ጥሩ ግንኙነት ለመመሥረት የሚያስችልህን ጥበብና ፍቅር ያስተምርሃል። ከዚህም በላይ ስለ ሕይወት ዓላማ ከአምላክ መማርና እርሱ የገባውን ቃል መረዳት ትችላለህ፤ እንዲሁም ለወደፊቱ ጊዜ ተስፋ ይኖርሃል። እውነተኛውን አምልኮ ለማግኘት ጥረት በማድረግህ መቼም ቢሆን አትቆጭም።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጥንታዊ ከሆኑት ሃይማኖታዊ ጽሑፎች መካከል ስለ አምላክ ፍቅር የሚገልጸው መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እውነተኛ ክርስቲያኖች በፍቅራቸው ተለይተው ይታወቃሉ