በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከአፍሪካ የተገኙ ተሞክሮዎች

ከአፍሪካ የተገኙ ተሞክሮዎች

የ2007 የዓመት መጽሐፍ

ከአፍሪካ የተገኙ ተሞክሮዎች

አገሮች 57

የሕዝብ ብዛት 802,232,357

አስፋፊዎች 1,043,396

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች 1,903,665

ሩዋንዳ ከጥቂት ጊዜያት በፊት የፕሮቴስታንት ቤተ ክርስቲያን አባላት የሆኑ ሰዎች በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ የተባለውን መጽሐፍ መንገድ ላይ ወድቆ አገኙ። እነዚህ ሰዎች መጽሐፉን የቤተ ክርስቲያናቸው ሽማግሌ ለሆነው ግለሰብ ሰጡት። ይህ ሰው መጽሐፉን በጉጉት ካነበበው በኋላ የይሖዋ ምሥክሮችን ፈልጎ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረ። ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እውነት ያለው እውቀት እየጨመረ ሲሄድ ከቤተ ክርስቲያኑ ተሰናበተና ራሱን ለይሖዋ ወስኖ ተጠመቀ። በዚህ መሃል በፊት የነበረበት ቤተ ክርስቲያን አባላት ለሆኑ ሰዎች ስለ እውነት በቅንዓት ይሰብክ ነበር፤ በዚህም ምክንያት 25 ሰዎች የይሖዋ ምሥክር ለመሆን ሲሉ ከቤተ ክርስቲያኑ ተሰናበቱ። መጀመሪያ እውነትን የሰማውን የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌ የተካው ሰውም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የጀመረ ሲሆን እርሱም ከቤተ ክርስቲያኑ ለቀቀ። ይህ ሰው በአሁኑ ጊዜ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ የሚገኝ ሲሆን አስፋፊ ለመሆን እንደሚፈልግም ተናግሯል። ባለቤቱ በቅርቡ በተደረገ ልዩ ስብሰባ ላይ ራሷን ወስና ተጠምቃለች። ይህ ሁሉ ውጤት የተገኘው በመንገድ ላይ ወድቆ በተገኘ አንድ መጽሐፍ አማካኝነት መሆኑ በጣም አስገራሚ ነው!

ኮት ዲቩዋር በዋና ከተማው በአቢጃን፣ በረንዜ የተባለ አንድ ወጣት የይሖዋ ምሥክር ወደ መስክ አገልግሎት እየሄደ ሳለ ዳቦ የምትሸጥ አንዲት ሴት በአጠገቡ አለፈች። ሴትየዋ ሳይታወቃት የ5,000 ፍራንክ ኖት (10 የአሜሪካ ዶላር) ጣለች። በረንዜ ገንዘቡን ሊሰጣት አስቦ ልክ ሲያነሳው ከሌላ አቅጣጫ የምትመጣ አንዲት ሴት “አምጣ! የእኔ ገንዘብ ነው!” በማለት ጮኸችበት። ሆኖም በረንዜ ገንዘቡ ምን ያህል እንደሆነ ሲጠይቃት ተናድዳ ጥላው ሄደች። ከዚያም በረንዜ ገንዘቡን የጣለችው ሴት ላይ ለመድረስ እየሮጠ ተከተላት። የሚገርመው ግን ሴትየዋ ገንዘብ እንዳልጠፋት የተናገረች ከመሆኑም በላይ “እኔን ለመዝረፍ የፈጠርከው ዘዴ ነው” አለችው። ሆኖም በረንዜ ደጋግሞ ስለጠየቃትና እውነቱን እንደሆነ ስላሰበች ገንዘብ ጠፍቶባት እንደሆነ ተመለከተች፤ እውነትም 5,000 ፍራንክ (የ50 ዳቦ ዋጋ) ጥላ ነበር።

በረንዜ እንዲህ ብሏል:- “ገንዘቡን ከሰጠኋት በኋላ እንዲህ ያደረግሁት አምላኬ ይሖዋ፣ አገልጋዮቹ ታማኝ እንዲሆኑ ስለሚያስተምራቸው እንደሆነ ነገርኳት። እርሷም ካመሰገነችኝ በኋላ እንዲህ አለች:- ‘ሁሉም ሰው እንደ ይሖዋ ምሥክሮች ቢሆን ኖሮ ሰዎች ሁሉ ወዳጆች በሆኑ ነበር። አንድ ወጣት እንዲህ ሲያደርግ ስመለከት ይህ በሕይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።’ ትራክት የሰጠኋት ሲሆን እርሷም ከዚህ በኋላ የይሖዋ ምሥክሮችን እንደምትሰማቸው ቃል ገብታለች። የዚያን ዕለት ኪሴ ውስጥ የነበረኝ 50 ፍራንክ ብቻ ነበር። ያም ሆኖ ትክክል የሆነውን በማድረጌ ደስተኛ ነበርኩ።”

ኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፑብሊክ ዩጂን የተባለ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ፣ አልማዝ ወደ ውጭ በሚልክ ድርጅት ውስጥ የጽዳትና የጥበቃ ሠራተኛ ነበር። ዩጂን እንዲህ በማለት ያስታውሳል:- “አንድ ቀን ምሽት ላይ አንድ ሰው 22,000 የአሜሪካ ዶላር የሚያወጣ አልማዝ ለመሸጥ ወደ ሱቁ መጣ። ሆኖም አልማዙን የያዘበት ቦርሳ ከኪሱ ወድቆ ነበር። በድንጋጤ ዙሪያውን ቢፈልግም ሊያገኘው አልቻለም። በነጋታው የዚህ ሰው አለቃና አብሮት የሚሠራው ሰው ቦርሳውን መንገድ ላይ ቢፈልጉትም አላገኙትም። ከዚያም የሱቁን ደጃፍ ስጠርግ አልማዝ የያዘውን ቦርሳ አገኘሁት! ቦርሳውን አንስቼ ቤልጅየማዊ ወደሆነው አለቃዬ እየሮጥሁ ሄድኩ። አለቃዬ ቦርሳውን ወስጄ በመስጠቴ በጣም ተገረመ። የይሖዋ ምሥክር እንደሆንኩና ለአምላኬ አክብሮታዊ ፍርሃት እንዳለኝ ነገርኩት። የአልማዙ ባለቤት በሐቀኝነቴ በጣም በመገረሙ ‘ይህ ፈጽሞ የማይታመን ነው!’ ሲል ተናገረ።”

“አብረውኝ ከሚሠሩት ሰዎች አንዱ ‘ዩጂን፣ የሱቃችን መልካም ስም እንዳይጎድፍ አድርገሃል!’ አለኝ።”

“እኔም ‘አመሰግናለሁ! መመስገን ያለበት ግን ታማኝ እንድሆን ያስተማረኝ ይሖዋ ነው’ በማለት መለስኩለት።”

አንጎላ ዥዋው የተባለ የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኖ የሚያገለግል ሚስዮናዊ ወንድም አንድን ገጠራማ አካባቢ ሲጎበኝ በአካባቢው ለሚገኙት ወንድሞችና ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ኖኅ አካሄዱን ከአምላክ ጋር አደረገዳዊት በአምላክ ታመነ የተባለውን በዲቪዲ የተዘጋጀ ፊልም ለማሳየት ፈለገ። ወንድም በእጅ የሚያዝ ኮምፒውተር፣ አነስተኛ ጀነሬተር፣ ሁለት የድምጽ ማጉያዎችና የተወሰነ ቤንዚን ይዞ ነበር። መጀመሪያ በጎበኘው መንደር በአንድ አነስተኛ የጭቃ ቤት ውስጥ ያረፈ ሲሆን ፊልሙን በዚያው ምሽት ለማሳየት ዝግጅት አደረገ። ወንድም ዥዋው እንዲህ ብሏል:- “ሠላሳ ስምንት የሚያህሉ ሰዎች ወንበሮችን፣ አግዳሚዎችን፣ ድንጋዮችን፣ የወተት ቆርቆሮዎችን እንዲሁም ለመቀመጫነት የሚያገለግሉ ሌሎች ነገሮችን ይዘው ሲመጡ በጣም ተገረምኩ። ቤቱ ከመጡት ሰዎች ለግማሾቹ እንኳ ስለማይበቃ ፊልሙን ውጪ መመልከት ነበረብን። ሰማዩ ጥርት ያለ ነበር፤ ኮምፒውተሩን ከጭቃ በተሠራ ጡብ ላይ አስቀመጥኩት። አብዛኞቹ ሰዎች በቀለማት ያሸበረቁ የአፍሪካ ልብሶችን መሬት ላይ አንጥፈው ተቀምጠው ነበር።” ወሬው በፍጥነት በመሰራጨቱ ብዙ ሰዎች ዥዋው ወደነበረበት መንደር መጡ። ወንድም ዥዋው “ፊልሙ ካለቀ በኋላም እንኳ ማንም መሄድ አልፈለገም” በማለት ያስታውሳል። “አብዛኞቹ በሕይወታቸው ውስጥ በጣም የተደሰቱበት ምሽት እንደነበር የተናገሩ ሲሆን ይሖዋ ላደረገላቸው መንፈሳዊ ዝግጅት ያላቸውን ጥልቅ አድናቆት ገልጸዋል።” ወንድም ዥዋው በገጠራማ አካባቢዎች የሚገኙ ቡድኖችን በጎበኘባቸው ሦስት ሳምንታት ውስጥ 1,568 ሰዎች ፊልሙን ተመልክተዋል!

ጋና በአክራ የምትኖር ከምግብ ጋር የተያያዙ ነገሮችን የምትሸጥ ቪዳ የተባለች ሴት በጋና ለሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ አትክልቶችን ለማቅረብ አመንትታ ነበር። ለምን? የቤተ ክርስቲያኗ ቄስ፣ የይሖዋ ምሥክሮች የእነርሱ እምነት ተከታይ ያልሆኑ ሰዎችን እንደሚጠሉ ነግሯት ነበር። በመሆኑም ቪዳ ለመጀመሪያ ጊዜ ለቅርንጫፍ ቢሮው የምትሸጣቸውን ምግቦች ስትወስድ ወጥ ቤት ውስጥ የሚሠሩት ወንድሞች ወዳጃዊ በሆነ ስሜት በፈገግታ ሲቀበሏትና በትሕትና አድናቆታቸውን ሲገልጹላት በጣም ተገረመች። ከዚያ በኋላ ባሉት ሳምንታት በቅርንጫፍ ቢሮው ውስጥ ከሚያገለግሉት ፈቃደኛ ሠራተኞች ጋር የተግባባች ሲሆን ሁሉም በደግነት እንደተቀበሏት አስተዋለች። ይህም የቤተ ክርስቲያኗ ቄስ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች የነገራት ነገር እውነት እንዳልሆነ እንድትገነዘብ አደረጋት።

ቪዳ የበለጠ ለማወቅ ስለፈለገች፣ ማንበብ ባትችልም እንኳ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲጀመርላት ጠየቀች። በስድስት ወራት ውስጥ የራሷን መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ የቻለች ሲሆን በቅርቡ በተደረገ የአውራጃ ስብሰባ ላይ ተጠምቃለች። ቪዳ፣ ቤተሰቦቿና የቀድሞ ጓደኞቿ ቢቃወሟትም የአጎቷን ልጅ ያልተጠመቀች አስፋፊ እንድትሆን ረድታታለች።

ሱዳን አንዲት እህት ከቤት ወደ ቤት ስታገለግል ሁለት ልጃገረዶች አገኘችና ወደ ቤት እንድትገባ ጋበዟት። የሚገርመው ነገር ልጆቹ ከመጽሐፍ ቅዱሳቸው ጥቅሶችን ለማውጣት ሲሞክሩ እህት እንድትረዳቸው አልፈለጉም። በአካባቢያቸው የሚገኘው ቄስ፣ የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱሳቸውን ከነኩት መጽሐፍ ቅዱሱ ወዲያው ተቀይሮ ከእነርሱ ትምህርት ጋር የሚስማማ እንደሚሆን አስጠንቅቋቸው ነበር። ልጆቹ እህትን ለመጨበጥ እንኳ አልፈለጉም። ያም ሆኖ ግን ጥቅሶቹን ራሳቸው እያወጡ ሲያነቡ ሐሳቡ እህት ከተናገረችው ነገር ጋር እንደሚስማማ ተመለከቱ። ቄሱ እንደዋሻቸው ስለተገነዘቡ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ወሰኑ። ሁኔታው ያሳሰበው ይህ ቄስ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናታቸውን ካቆሙ ለምግብ መግዣ የሚሆን ገንዘብ እንደሚሰጣቸው ቃል ገባላቸው። ታዲያ ልጆቹ ምን ምላሽ ሰጡ? “እኛ የምንፈልገው ሆዳችንን በምግብ መሙላት ሳይሆን በአምላክ ቃል መሞላት ነው” አሉት። እነዚህ ልጆች በአሁኑ ጊዜ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ይገኛሉ።

ኢትዮጵያ አወቀ የተባለ አንድ ሰው ባለቤቱ ለአሥር ዓመት ያህል በእውነት ውስጥ የቆየች ቢሆንም እርሱ ግን ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ብዙም ፍላጎት አልነበረውም። ሆኖም ለሁለት ወራት የሚሠጥ ሥልጠና ለመውሰድ ወደ ሌላ የአገሪቱ ክፍል ሲሄድ የይሖዋ ምሥክሮችን ለማግኘት ወሰነ። በቦታው ሲደርስ ሰዎች አንዲት እህት የምትሠራበትን መሥሪያ ቤት ጠቆሙት። ይህች እህት በዚያ ያለውን ጉባኤ የሚረዳ ወንድም እንዲመጣ ስትጸልይ ነበር። የይሖዋ ምሥክሮችን የሚፈልግ ሰው እንዳለ ስትሰማ ጸሎቷ ትዝ አላት። ጥሩ አለባበስ ያለውን አወቀን ስታየው ደግሞ እንዲመጣ ስትጸልይ የነበረው ወንድም እርሱ እንደሆነ አሰበች። በጣም ስለተደሰተች በፍጥነት ወደ አወቀ ሄዳ ሞቅ ያለ አቀባበል አደረገችለት። አወቀ በጣም እንደተደሰተች ስለተመለከተና ቅር እንዲላት ስላልፈለገ ከሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች ጋር ስታስተዋውቀውም እንደተሳሳተች ሊነግራት አልደፈረም። አወቀ በዚያ በቆየበት ጊዜ በሁሉም የጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ይገኝ ነበር። ሥልጠናውን ጨርሶ ወደመጣበት የሚመለስበት ጊዜ ሲደርስ የተወሰኑ እህቶች ምሳ ጋበዙትና እንዲጸልይ ጠየቁት። ቤቱ እያለ ሚስቱ ምግብ ሲቀርብ ራሷን ሸፍና በኢየሱስ ስም እንዴት ትጸልይ እንደነበረ በማስታወስ ጥሩ አድርጎ ጸለየ። ግብዣውም በጥሩ ሁኔታ ተከናወነ። አወቀ በዚያ አካባቢ በቆየበት ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ባሳዩት ደግነት ልቡ ስለተነካ እውነተኛ ወንድም ለመሆን ወሰነ። ወደ ቤቱ ሲመለስ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የጀመረ ሲሆን በቅርቡ በተደረገ ትልቅ ስብሰባ ላይ ተጠመቀ። ባለቤቱ በዚህ በጣም ተደስታለች፤ አወቀም ለሥልጠና በሄደበት አካባቢ ለነበረው ጉባኤ ተሞክሮውን ለመናገር ይጓጓል።