በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ከዚህ ዓለም ያልሆነውን’ መንግሥት መጠበቅ

‘ከዚህ ዓለም ያልሆነውን’ መንግሥት መጠበቅ

የሕይወት ታሪክ

‘ከዚህ ዓለም ያልሆነውን’ መንግሥት መጠበቅ

ኒኮላይ ጉሱልያክእንደተናገረው

የነበርኩበት ወኅኒ ቤት ለ41 ቀናት በቆየ ዓመጽ እየታመሰ ነበር። አንድ ሌሊት፣ የመድፍ ተኩስ ከእንቅልፌ አባነነኝ። ታንኮችና ወታደሮች ወደ ወኅኒ ቤቱ ግቢ በመግባት በእስረኞቹ ላይ ተኩስ ከፈቱ። ሕይወቴ አደጋ ላይ ወድቆ ነበር።

እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ሊያጋጥመኝ የቻለው እንዴት እንደሆነ ላውጋችሁ። ጊዜው 1954 ሲሆን በወቅቱ 30 ዓመቴ ነበር። በሶቭየት አገዛዝ ሥር ይኖሩ እንደነበሩት በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች ሁሉ እኔም ከፖለቲካዊ ጉዳዮች ገለልተኛ በመሆኔና ለሰዎች ስለ አምላክ መንግሥት በመስበኬ ወኅኒ ቤት ተጣልኩ። በእስር ቤት ውስጥ 46 ወንድሞችና 34 እህቶች ይገኙ ነበር። የታሰርነው በመካከለኛው ካዛክስታን በሚገኘው ከንጊር በሚባለው መንደር አቅራቢያ ባለ የጉልበት ሥራ የሚሠራበት ካምፕ ውስጥ ሲሆን በዚያም በሺዎች ከሚቆጠሩ ሌሎች እስረኞች ጋር እንኖር ነበር።

የሶቪየት ሕብረት መሪ የነበሩት ጆሴፍ ስታሊን ከአንድ ዓመት በፊት በመሞታቸው፣ በርካታ እስረኞች በሞስኮ የሚገኘው አዲሱ መንግሥት በወኅኒ ቤቱ ውስጥ ስላለው አስከፊ ሁኔታ ያሰሙትን ቅሬታ እንደሚሰማ ተስፋ አድርገው ነበር። የእስረኞቹ ቅሬታ እያደር ወደ ዓመጽ ተቀየረ። በዚህ የተነሳ በተፈጠረው ግጭት መሃል እኛ የይሖዋ ምሥክሮች በቁጣ ገንፍለው ለተነሱት ዓማጺ እስረኞችም ሆነ ለወታደሮቹ አቋማችንን ግልጽ ማድረግ አስፈልጎን ነበር። እንዲህ ያለ የገለልተኝነት አቋም ለመያዝ በአምላክ ላይ እምነት ማሳደር ጠይቆብናል።

ዓመጽ ተቀሰቀሰ!

ግንቦት 16 ቀን በእስር ቤቱ ውስጥ ዓመጽ ተቀሰቀሰ። ከሁለት ቀናት በኋላ ከ3,200 በላይ የሚሆኑ እስረኞች የወኅኒ ቤቱ ሁኔታ ካልተሻሻለና የፖለቲካ እስረኞች አንዳንድ መብቶቻቸው ካልተከበሩላቸው ሥራ እንደማይሠሩ ገለጹ። ከዚያ በኋላ ነገሮች በፍጥነት ተለዋወጡ። መጀመሪያ ዓማጺያኑ የወኅኒ ቤቱን ጠባቂዎች ከግቢው አስወጧቸው። ከዚያም አጥሩን በመቅደድ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ክፍተት አበጁ። ቀጥሎ ደግሞ የወንዶችንና የሴቶችን ክፍል የሚለየውን ግድግዳ በማፍረስ ሁሉም እስረኞች እንዲቀላቀሉ አደረጉ። በቀጣዮቹ ቀናት አንዳንድ እስረኞች እዚያው ታስረው በነበሩ ቄሶች አማካኝነት የጋብቻ ሥነ ሥርዓታቸውን ፈጸሙ። ዓመጹ በተቀሰቀሰባቸው በሦስቱ ሕንፃዎች ውስጥ ከሚገኙት 14,000 እስረኞች አብዛኞቹ በዓመጹ ተካፍለዋል።

ዓማጺያኑ ከወታደሮቹ ጋር የሚደራደር ኮሚቴ አቋቋሙ። ብዙም ሳይቆይ ግን በኮሚቴው አባላት መካከል አለመግባባት በመፈጠሩ አክራሪ የሆኑት ወገኖች ወኅኒ ቤቱን ተቆጣጠሩት። ሁኔታው ይበልጥ እየተጋጋለ መጣ። የዓመጹ መሪዎች “ሥርዓት” ለማስከበር በሚል የደኅንነት፣ የጦር ኃይልና የፕሮፓጋንዳ ክፍል አቋቋሙ። እነዚህ መሪዎች፣ በግቢው ዙሪያ በተተከሉ ምሰሶዎች ላይ በተሰቀሉ የድምፅ ማጉያዎች አማካኝነት ኃይለኛ መልእክቶችን በማስተላለፍ ዓመጹን ለማጋጋል ይጥሩ ነበር። ዓማጺያኑ ሌሎች እስረኞች እንዳያመልጡ ይከለክሉ፣ የሚቃወሟቸውን ይቀጡ እንዲሁም በእነርሱ ዘንድ ተቀባይነት የሌለውን ሰው እንደሚገድሉ ይዝቱ ነበር። እንዲያውም አንዳንድ እስረኞች እንደተገደሉ ይወራ ነበር።

ዓማጺያኑ ወታደራዊ ጥቃት እንደሚሰነዘርባቸው ይጠብቁ ስለነበር ራሳቸውን ለመከላከል አስፈላጊውን ዝግጅት አደረጉ። የዓመጹ መሪዎች፣ በተቻለ መጠን በርካታ ቁጥር ያላቸው እስረኞች ወኅኒ ቤቱን ከጥቃት ለመከላከል የሚያስፈልጋቸው ትጥቅ እንዲኖራቸው ስለፈለጉ ሁሉም እስረኞች መሣሪያ እንዲይዙ ትእዛዝ አስተላለፉ። ለዚህም ሲባል እስረኞቹ የመስኮቶቹን ብረቶች በማውለቅ ጩቤና ሌሎች መሣሪያዎችን ሠሩ። ሌላው ቀርቶ ጠመንጃና ፈንጂም ጭምር ማግኘት ችለው ነበር።

በዓመጹ እንድንካፈል ጫና ተደረገብን

በዚህ ወቅት ሁለት ዓማጺያን ወደ እኔ መጡ። አንደኛው የተሳለ ጩቤ አወጣና “ይህንን ያዝ! ራስህን ለመከላከል ያስፈልግሃል” አለኝ። ይሖዋ እንድረጋጋ እንዲረዳኝ በልቤ ከጸለይኩ በኋላ እንዲህ ብዬ መለስኩለት:- “እኔ ክርስቲያን የይሖዋ ምሥክር ነኝ። እኔና ሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች እዚህ የታሰርነው ውጊያችን ከሰዎች ጋር ሳይሆን ከማይታዩ መንፈሳዊ ኃይላት ጋር በመሆኑ ነው። ከእነዚህ ኃይላት ጋር የምንዋጋባቸው መሣሪያዎች ደግሞ በአምላክ መንግሥት ላይ ያለን እምነትና ተስፋ ናቸው።”—ኤፌሶን 6:12

ሰውየው የተናገርኩት ነገር እንደገባው ለመግለጽ ጭንቅላቱን ሲነቀንቅ በጣም ተገረምኩ። ይሁን እንጂ አብሮት የነበረው ሰው በኃይል መታኝ። ከዚያም ጥለውኝ ሄዱ። ዓማጺያኑ ወደ ተለያዩ የወኅኒ ቤቱ ክፍሎች በመሄድ የይሖዋ ምሥክሮችም በዓመጹ እንዲካፈሉ ለማስገደድ ሞክረው ነበር። ሆኖም ክርስቲያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በሙሉ ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ አልሆኑም።

የዓማጺያኑ ኮሚቴ ባደረገው ስብሰባ ላይ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች የገለልተኝነት አቋም ውይይት ተደረገ። “የሁሉም ሃይማኖቶች አባላት ማለትም ጴንጤዎች፣ አድቬንቲስቶች፣ ባብቲስቶች እንዲሁም ሌሎቹ እስረኞች በሙሉ በዓመጹ ተባባሪ ሆነዋል። ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ ያልሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ ናቸው” በማለት ተናገሩ። “ምን ብናደርጋቸው ይሻላል?” ሲሉ ከመካከላቸው አንዱ ተነስቶ፣ እነርሱን ለማስፈራራት መፍትሔው አንዱን የይሖዋ ምሥክር የእስር ቤቱ ምድጃ ውስጥ መክተት እንደሆነ ሐሳብ አቀረበ። ሆኖም ሌሎቹ እስረኞች የሚያከብሩት የቀድሞ ወታደራዊ ባለ ሥልጣን ተነሳና እንዲህ አለ:- “እንዲህ ማድረጉ ትክክል አይደለም። ሁሉንም ሰብስበን የወኅኒ ቤቱ በር አጠገብ ባለው ክፍል ውስጥ እናስገባቸው። ወታደሮቹ በታንክ ጥቃት ቢሰነዝሩብን መጀመሪያ የሚገደሉት የይሖዋ ምሥክሮች ይሆናሉ። እኛም እነርሱ በመሞታቸው ተጠያቂዎች አንሆንም።” ሌሎቹም በሐሳቡ ተስማሙ።

አደገኛ ቦታ ላይ አስቀመጡን

ብዙም ሳይቆይ እስረኞቹ በግቢው ውስጥ እየዞሩ “የይሖዋ ምሥክሮች ውጡ!” እያሉ ይጮኹ ጀመር። ከዚያም ሰማንያዎቻችንንም በግቢው ዳር ወደሚገኝ ክፍል ወሰዱን። ክፍሉ ሰፋ እንዲል ተደራራቢ አልጋዎቹን እየጎተቱ ካወጡ በኋላ እንድንገባ አዘዙን። ይህ ክፍል በእስር ቤት ውስጥ ያለ ሌላ እስር ቤት ሆነብን።

አብረውን የታሰሩት ክርስቲያን እህቶች አንሶላዎችን አገጣጥመው ከሰፉ በኋላ የነበርንበትን ክፍል ለሁለት ከፈልነውና አንደኛውን ለወንዶች ሌላውን ለሴቶች አደረግነው። (ከጊዜ በኋላ፣ በሩሲያ የሚኖር አንድ ወንድም ይህን ክፍል የሚያሳየውን ከታች ያለውን ሥዕል ስሏል።) በዚህ በተጨናነቀ ክፍል ውስጥ ስንኖር ይሖዋ ጥበብና “እጅግ ታላቅ ኀይል” እንዲሰጠን በመማጸን ብዙ ጊዜ በአንድነት እንጸልይ ነበር።—2 ቆሮንቶስ 4:7

በዚህ ሁሉ ጊዜ በዓማጺያኑና በሶቪየት ሠራዊት መካከል ባለ አደገኛ ቦታ ላይ ነበርን። ማናችንም ብንሆን ከሁለት አንዳቸው ቀጥሎ ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ የምናውቅበት መንገድ አልነበረም። አንድ ታማኝ አረጋዊ ወንድም “ምን ሊሆን እንደሚችል ለመገመት አትሞክሩ። ይሖዋ አይተወንም” በማለት ይመክሩን ነበር።

ወጣቶችም ሆኑ በዕድሜ የገፉ ውድ ክርስቲያን እህቶቻችን ግሩም የሆነ ጽናት አሳይተዋል። ሰማንያ ዓመት ገደማ የሚሆናቸው አንዲት አረጋዊት እህት ተጨማሪ እርዳታ ያስፈልጋቸው ነበር። ከመካከላችን የታመሙና የሕክምና እርዳታ የሚያሻቸውም ነበሩ። በዚህ ክፍል ውስጥ በቆየንበት ጊዜ ሁሉ ዓማጺያኑ እኛን ለመቆጣጠር እንዲችሉ በሮቹ ክፍት እንዲሆኑ አድርገው ነበር። ምሽት ላይ መሣሪያ የታጠቁ እስረኞች ወደነበርንበት ክፍል ይመጣሉ። አንዳንድ ጊዜ፣ “የአምላክ መንግሥት ተኝቷል” ሲሉ እንሰማቸዋለን። ቀን ላይ ወደ ወኅኒ ቤቱ የምግብ አዳራሽ እንድንሄድ ሲፈቅዱልን ምንጊዜም አብረን በመሆን ይሖዋ ከዓመጸኞች እንዲጠብቀን እንጸልይ ነበር።

በነበርንበት ክፍል ውስጥ በመንፈሳዊ እርስ በርስ ለመደጋገፍ እንጥር ነበር። ለምሳሌ፣ ብዙውን ጊዜ አንድ ወንድም ሁላችንም እንድንሰማው ድምፁን ከፍ አድርጎ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ይነግረናል። ከዚያም ታሪኩን ካለንበት ሁኔታ ጋር ያዛምደዋል። በተለይ አንድ በዕድሜ የገፉ ወንድም ስለ ጌድዮን ሠራዊት መናገር ይወዱ ነበር። “የሙዚቃ መሣሪያ የያዙ 300 ሰዎች ከ135,000 የታጠቁ ወታደሮች ጋር በይሖዋ ስም ተዋግተው 300ቹም ምንም ጉዳት ሳይደርስባቸው ተመልሰዋል” በማለት ያስታውሱን ነበር። (መሳፍንት 7:16, 22፤ 8:10) ይህና ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች መንፈሳዊ ጥንካሬ ሰጥተውናል። የይሖዋ ምሥክር የሆንኩት ከመታሰሬ ትንሽ ቀደም ብሎ ቢሆንም ይበልጥ ተሞክሮ ያላቸውን ወንድሞችና እህቶች ጠንካራ እምነት መመልከቴ በጣም አበረታቶኛል። ይህ ሁኔታ ይሖዋ በእርግጥም ከእኛ ጋር እንደሆነ እንዲሰማኝ አድርጎኛል።

ውጊያው ተጀመረ

በዚህ ሁኔታ ሳምንታት እያለፉ ሲሄዱ በወኅኒ ቤቱ ውስጥ ውጥረት መፈጠር ጀመረ። በዓማጺያኑና በባለ ሥልጣናቱ መካከል የሚደረገው ድርድር እየተካረረ መጣ። የዓማጺያኑ መሪዎች፣ በሞስኮ የነበረው ማዕከላዊ መንግሥት ከእነርሱ ጋር የሚወያይ ተወካይ እንዲልክ ይወተውቱ ነበር። ባለ ሥልጣናቱ ደግሞ ዓማጺያኑ እጃቸውን እንዲሰጡ፣ መሣሪያቸውን እንዲያስረክቡና ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ ትእዛዝ አስተላለፉ። ሁለቱም ወገኖች አቋማቸውን ለማላላት አሻፈረኝ አሉ። በዚህ ወቅት ወኅኒ ቤቱ ጥቃት ለመሰንዘር ዝግጁ ሆነው በሚጠባበቁ ወታደሮች ተከብቦ ነበር። ዓማጺያኑም ወታደሮቹ እንዳይገቡ መከላከያ ሠርተውና መሣሪያ አከማችተው ለውጊያ ተዘጋጁ። ሁሉም ሰው በሠራዊቱና በእስረኞቹ መካከል ለረጅም ጊዜ ሲካሄድ የቆየው ውዝግብ በማንኛውም ሰዓት በውጊያ ሊደመደም እንደሚችል ይጠብቅ ነበር።

ሰኔ 26 ሌሊት ላይ ጆሮ የሚያደነቁር የመድፍ ተኩስ ከእንቅልፋችን ቀሰቀሰን። ታንኮች አጥሩን ደርምሰው ወደ ግቢው ሲገቡ ከኋላቸው የተከተሉት ወታደሮች የጥይት እሩምታ ያርከፈክፉ ነበር። ወንድ ሴት ሳይል እስረኞቹ “ሆ” እያሉ ወደ ታንኮቹ በመሮጥ ድንጋይ፣ ቤት ውስጥ የተሠሩ ቦምቦችና ያገኙትን ማንኛውም ነገር መወርወር ጀመሩ። ከዚያ በኋላ ኃይለኛ ውጊያ የተካሄደ ሲሆን እኛም በዚያ መሃል አጣብቂኝ ውስጥ ገባን። ይሖዋ እንዲረዳን ላቀረብነው ጸሎት ምላሽ የሚሰጠን እንዴት ይሆን?

በድንገት ወታደሮች እኛ ወዳለንበት ክፍል ገቡና “እናንተ ቅዱሳን፣ ኑ ውጡ!” በማለት ጮኹ። “ቶሎ ብላችሁ ከአጥሩ ውጪ ወዳለው ቦታ ሽሹ!” አሉን። ኃላፊው መኮንን፣ ወታደሮቹ አጠገባችን ሆነው እንዲከላከሉልን እንጂ እንዳይገድሉን አዘዛቸው። ጦርነቱ በተፋፋመበት ወቅት ከግቢው ውጪ ባለው ሣር ላይ ተቀምጠን ነበር። ለአራት ሰዓታት ያህል በግቢው ውስጥ ፍንዳታና ተኩስ እንዲሁም ሰዎች ሲጮኹና በሥቃይ ሲያቃስቱ ይሰማን ነበር። ከዚያም ሁሉ ነገር ጸጥ እረጭ አለ። ጎህ ሲቀድ ወታደሮቹ የሞቱትን ሰዎች ከግቢው ውስጥ ሲያወጡ ተመለከትን። በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንደቆሰሉና እንደሞቱ አወቅን።

ረፋዱ ላይ አንድ የማውቀው ባለ ሥልጣን ወደ እኛ መጣና “እሺ ኒኮላይ፣ ያዳናችሁ ማን ነው? እኛ ነን ወይስ ይሖዋ?” በማለት በኩራት ጠየቀኝ። ሕይወታችንን ስላተረፈልን ከልባችን ካመሰገንነው በኋላ “ሁሉን ቻይ የሆነው አምላካችን ይሖዋ፣ መጽሐፍ ቅዱስ በተጻፈበት ዘመን የነበሩ አገልጋዮቹን ለማዳን ሌሎች ሰዎችን ያነሳሳ እንደነበረ ሁሉ እኛንም ለማዳን በእናንተ ተጠቅሟል” አልነው።—ዕዝራ 1:1, 2

ወታደሮቹ የእኛን ማንነትና የት እንዳለን እንዴት እንዳወቁ ይኸው ባለ ሥልጣን ነገረን። ወታደሮቹና ዓማጺያኑ በሚደራደሩበት ወቅት፣ ወታደሮቹ ‘እናንተን የማይደግፉ እስረኞችን ገድላችኋል’ በማለት ዓማጺያኑን ወንጅለዋቸው ነበር። ዓመጺያኑ ግን የይሖዋ ምሥክሮች በዓመጹ ባይካፈሉም እንዳልተገደሉና ከዚህ ይልቅ ቅጣት እንዲሆናቸው ሲሉ ሁሉንም የይሖዋ ምሥክሮች በአንድ ክፍል ውስጥ እንዳጐሯቸው ተናገሩ። ባለ ሥልጣናቱም ይህን ንግግር አልረሱትም።

የአምላክን መንግሥት በጽናት ደግፈናል

ታዋቂው ሩሲያዊ ደራሲ አሌክሳንደር ሶልዠኒትሰን ዘ ጉላግ አርኪፔላጎ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እኛ ወኅኒ ቤት በነበርንበት ወቅት ስለተቀሰቀሰው ዓመጽ ጠቅሰዋል። በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ አስመልክተው ሲጽፉ፣ ዓመጹ የተቀሰቀሰው “ነጻነት ማግኘት ስለፈለግን ነበር . . . ይሁን እንጂ [ነጻነት] ማን ሊሰጠን ይችላል?” ብለዋል። በዚያው እስር ቤት ውስጥ የነበርን የይሖዋ ምሥክሮችም ነጻነት ለማግኘት እንጓጓ ነበር። እኛ የምንፈልገው ግን ከእስር ቤት ለመውጣት ብቻ ሳይሆን ከአምላክ መንግሥት በቀር ማንም ሊያመጣው የማይችለውን ነጻነት ለማግኘት ነው። ወኅኒ ቤት እያለን ከአምላክ መንግሥት ጎን ጸንተን ለመቆም ይሖዋ የሚሰጠን ኃይል እንደሚያስፈልገን ተገንዝበን ነበር። እርሱም የሚያስፈልገንን ሁሉ ሰጥቶናል። ጩቤም ሆነ ቦምብ መጠቀም ሳያስፈልገን ድል ማድረግ እንድንችል ረድቶናል።—2 ቆሮንቶስ 10:3

ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ለጲላጦስ “የእኔ መንግሥት ከዚህ ዓለም አይደለም፤ ቢሆንማ ኖሮ . . . ሎሌዎቼ በተከላከሉልኝ ነበር” ብሎታል። (ዮሐንስ 18:36) የክርስቶስ ተከታዮች እንደመሆናችን መጠን እኛም በፖለቲካዊ ትግል ውስጥ አልተካፈልንም። በወኅኒ ቤቱ ውስጥ ዓመጽ በተቀሰቀሰበት ወቅትም ሆነ ከዚያ በኋላ ለአምላክ መንግሥት ታማኞች መሆናችን ለሌሎች በግልጽ መታየቱ አስደስቶናል። ሶልዠኒትሰን በጊዜው ስለነበረን አቋም ሲጽፉ እንዲህ ብለዋል:- “የይሖዋ ምሥክሮች ማንንም ሳይፈሩ የእምነታቸውን መመሪያዎች የተከተሉ ሲሆን መከላከያ ለመሥራት ወይም ጥበቃ ለመቆም ፈቃደኛ አልነበሩም።”

ይህ አስጨናቂ ሁኔታ ከደረሰብን ከ50 የሚበልጡ ዓመታት አልፈዋል። ይሁን እንጂ ይሖዋን በትዕግሥት መጠበቅንና በእርሱ ኃያል ክንድ ሙሉ በሙሉ መታመንን የመሰሉ ዘላቂ ትምህርቶች ስላገኘሁበት ብዙ ጊዜ ያንን ወቅት መለስ ብዬ ሳስበው በአመስጋኝነት ስሜት እሞላለሁ። አዎን፣ በቀድሞዋ ሶቪየት ሕብረት እንደነበሩት ሌሎች በርካታ ውድ የይሖዋ ምሥክሮች ሁሉ እኔም ‘ከዚህ ዓለም ያልሆነውን’ መንግሥት ለሚጠባበቁ ሰዎች ይሖዋ ነጻነት እንደሚሰጣቸው፣ ጥበቃ እንደሚያደርግላቸውና እንደሚያድናቸው በሕይወቴ ለመመልከት ችያለሁ።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እኛ የነበርንበት በካዛክስታን የሚገኘው የጉልበት ሥራ የሚሠራበት ወኅኒ ቤት

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የይሖዋ ምሥክሮች በነበሩበት እስር ቤት ውስጥ የሴቶቹን ክፍል የሚያሳይ ሥዕል

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከወኅኒ ቤት እንደተለቀቅን ከክርስቲያን ወንድሞች ጋር