በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋን በመፍራት በሕይወትህ ደስተኛ ሁን

ይሖዋን በመፍራት በሕይወትህ ደስተኛ ሁን

ይሖዋን በመፍራት በሕይወትህ ደስተኛ ሁን

‘እናንተ ቅዱሳኑ፤ ይሖዋን ፍሩት፤ እርሱን የሚፈሩት አንዳች አያጡምና።’—መዝሙር 34:9

1, 2. (ሀ) በሕዝበ ክርስትና ውስጥ አምላክን በመፍራት ረገድ ምን የተለያየ አመለካከት ይታያል? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

 የሕዝበ ክርስትና ሰባኪዎች ሰዎች አምላክን መፍራት እንዳለባቸው ሲያስተምሩ፣ አምላክ ኃጢአተኞችን በዘላለማዊ የሲኦል እሳት እንደሚያቃጥል በመግለጽ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድጋፍ የሌለው ትምህርት ይሰጣሉ። እንዲህ ያለው መሠረተ ትምህርት ይሖዋ የፍቅርና የፍትሕ አምላክ እንደሆነ ከሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ጋር ይጋጫል። (ዘፍጥረት 3:19፤ ዘዳግም 32:4፤ ሮሜ 6:23፤ 1 ዮሐንስ 4:8) ከዚህ በተቃራኒ ሌሎች የሕዝበ ክርስትና ሰባኪዎች ደግሞ አምላክን ስለ መፍራት ጨርሶ አይናገሩም። ከዚህ ይልቅ አምላክ ማንኛውንም አካሄድ እንደሚፈቅድና አንድ ሰው የፈለገውን አኗኗር ቢከተልም አምላክ እንደሚቀበለው ያስተምራሉ። ይህም ቢሆን ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ጋር አይስማማም።—ገላትያ 5:19-21

2 እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ አምላክን እንድንፈራ ያበረታታናል። (ራእይ 14:7) ሆኖም ይህ ሐቅ አንዳንድ ጥያቄዎችን ያስነሳል። አፍቃሪ የሆነ አምላክ እንድንፈራው የሚፈልገው ለምንድን ነው? አምላክ የሚፈልገው እንዴት ዓይነት ፍርሃት እንዲኖረን ነው? አምላክን መፍራታችንስ የሚጠቅመን እንዴት ነው? የቀሩትን የመዝሙር 34 ክፍሎች በመመርመር ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ እናገኛለን።

አምላክን መፍራት ያለብን ለምንድን ነው?

3. (ሀ) አምላክን እንድንፈራ የተሰጠንን ትእዛዝ እንዴት ትመለከተዋለህ? (ለ) ይሖዋን የሚፈሩ ሰዎች ደስተኞች የሆኑት ለምንድን ነው?

3 ይሖዋ፣ ፈጣሪና የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዢ እንደመሆኑ መጠን ሊፈራ ይገባዋል። (1 ጴጥሮስ 2:17) ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው ፍርሃት አምላክ ጨካኝ እንደሆነ በማሰብ እንድንርድ የሚያደርግ አይደለም። አምላክን መፍራት ሲባል የይሖዋን ማንነት በማሰብ ጥልቅ አክብሮታዊ ፍርሃት ማዳበር ማለት ነው። ይህ ዓይነቱ ፍርሃት እርሱን ላለማሳዘን መፍራትንም ይጨምራል። አምላካዊ ፍርሃት የላቀ ደረጃ ያለውና በእኛ ላይ በጎ ተጽዕኖ የሚያሳድር እንጂ የሚያስጨንቅ ወይም የሚያሸብር ነገር አይደለም። “ደስተኛ አምላክ” የሆነው ይሖዋ ሰብዓዊ ፍጥረታቱ በሕይወታቸው እንዲደሰቱ ይፈልጋል። (1 ጢሞቴዎስ 1:11 NW) ደስተኛ ለመሆን ግን ከአምላክ መሥፈርቶች ጋር ተስማምተን መኖር አለብን። ብዙዎች ይህን ለማድረግ አኗኗራቸውን መለወጥ አስፈልጓቸዋል። አስፈላጊውን ለውጥ ያደረጉ ሁሉ መዝሙራዊው ዳዊት እንደሚከተለው በማለት የተናገረው ሐሳብ እውነት መሆኑን በሕይወታቸው ውስጥ ይመለከታሉ:- “እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ቸር መሆኑን ቀምሳችሁ እዩ፤ እርሱን መጠጊያ የሚያደርግ ምንኛ ቡሩክ ነው! እናንተ ቅዱሳኑ፤ እግዚአብሔርን [“ይሖዋን፣” NW] ፍሩት፤ እርሱን የሚፈሩት አንዳች አያጡምና።” (መዝሙር 34:8, 9) ይሖዋን የሚፈሩ ሁሉ ከአምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና ስላላቸው ዘላቂ ጥቅም ያለው አንድም ነገር አያጡም።

4. ዳዊትም ሆነ ኢየሱስ ምን ማረጋገጫ ሰጥተዋል?

4 ዳዊት፣ ‘ቅዱስ’ የሚለው ቃል በዚያን ጊዜ በነበረው ትርጉም መሠረት አብረውት የነበሩትን ሰዎች “ቅዱሳን” ብሎ በመጥራት እንዳከበራቸው ልብ በል። እነዚህ ሰዎች የአምላክ ቅዱስ ብሔር አባላት ነበሩ። ከዚህም በላይ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው ዳዊትን ተከትለውታል። ከንጉሥ ሳኦል ይሸሹ የነበሩ ቢሆንም ይሖዋ መሠረታዊ ፍላጎቶቻቸውን ማሟላቱን እንደሚቀጥል ዳዊት እርግጠኛ ነበር። ዳዊት “አንበሶች ሊያጡ፣ ሊራቡም ይችላሉ፤ እግዚአብሔርን [“ይሖዋን፣” NW] የሚሹ ግን መልካም ነገር አይጐድልባቸውም” ብሏል። (መዝሙር 34:10) ኢየሱስም ለተከታዮቹ ተመሳሳይ ማረጋገጫ ሰጥቷቸዋል።—ማቴዎስ 6:33

5. (ሀ) በርካታ የኢየሱስ ተከታዮች ምን ዓይነት የኑሮ ደረጃ ነበራቸው? (ለ) ኢየሱስ ፍርሃትን በተመለከተ ምን ምክር ሰጥቷል?

5 ኢየሱስን ያዳምጡት ከነበሩት ሰዎች መካከል አብዛኞቹ በአይሁድ ኅብረተሰብ ውስጥ ዝቅተኛ ኑሮ ካለውና ችግረኛ ከሆነው ክፍል የመጡ ነበሩ። በመሆኑም ኢየሱስ “እረኛ እንደሌለው በግ ተጨንቀውና ተመልካች የለሽ ሆነው ባየ ጊዜ አዘነላቸው።” (ማቴዎስ 9:36) እንደነዚህ ያሉት ዝቅተኛ ኑሮ ያላቸው ሰዎች ኢየሱስን ለመከተል ድፍረት ይኖራቸው ይሆን? ይህን ለማድረግ ሰዎችን ሳይሆን ይሖዋን መፍራት ይኖርባቸዋል። ኢየሱስ እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “ሥጋን የሚገድሉትን፣ ከዚያ ወዲያ ግን ምንም ማድረግ የማይችሉትን አትፍሩ። ነገር ግን መፍራት የሚገባችሁን አሳያችኋለሁ፤ ከገደለ በኋላ ወደ ገሃነም ለመጣል ሥልጣን ያለውን እርሱን ፍሩት፤ አዎን፤ እርሱን ፍሩት እላችኋለሁ። አምስት ድንቢጦች በዐሥር ሳንቲም ይሸጡ የለምን? ይሁን እንጂ ከእነርሱ አንዷ እንኳ በእግዚአብሔር ዘንድ አትዘነጋም። የእናንተ የራሳችሁ ጠጉር ሁሉ እንኳ የተቈጠረ ነው፤ እንግዲህ አትፍሩ፤ ከብዙ ድንቢጦች የበለጠ ዋጋ አላችሁ።”—ሉቃስ 12:4-7

6. (ሀ) ኢየሱስ ክርስቲያኖችን የሚያጠናክር ምን ሐሳብ ሰጥቷል? (ለ) ኢየሱስ፣ አምላካዊ ፍርሃትን በማሳየት ረገድ ወደር የማይገኝለት ምሳሌ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

6 ይሖዋን የሚፈሩ ሰዎች አምላክን ማገልገላቸውን እንዲያቆሙ በጠላቶቻቸው ተጽዕኖ ሲደረግባቸው ኢየሱስ እንደሚከተለው በማለት የሰጠውን ምክር ሊያስታውሱ ይችላሉ:- “በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ የሰው ልጅ ደግሞ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ይመሰክርለታል። በሰው ፊት የሚክደኝም በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ይካዳል።” (ሉቃስ 12:8, 9) ይህ አባባል ክርስቲያኖችን በተለይ ደግሞ እውነተኛው አምልኮ በታገደባቸው አገሮች ውስጥ የሚኖሩትን የይሖዋ አምላኪዎች አጠናክሯቸዋል። እነዚህ የይሖዋ አገልጋዮች በክርስቲያናዊ ስብሰባዎችና ለሕዝብ በሚሰጡት ምሥክርነት ይሖዋን በጥበብ ያወድሱታል። (የሐዋርያት ሥራ 5:29) ኢየሱስ ‘አምላክን በመፍራት’ ረገድ የላቀ ምሳሌ ትቶልናል። (ዕብራውያን 5:7 የ1954 ትርጉም) ስለ እርሱ የተነገረው ትንቢት “የእግዚአብሔር መንፈስ፣ . . . እግዚአብሔርን የመፍራት መንፈስ ያርፍበታል። እግዚአብሔርን በመፍራት ደስ ይለዋል” ይላል። (ኢሳይያስ 11:2, 3) ከዚህ ለመመልከት እንደምንችለው አምላካዊ ፍርሃት ስለሚያስገኛቸው ጥቅሞች እኛን ለማስተማር ከኢየሱስ የበለጠ ብቃት ያለው ግለሰብ የለም።

7. (ሀ) ክርስቲያኖች ዳዊት ካቀረበው ግብዣ ጋር ለሚመሳሰለው ጥሪ ምላሽ የሚሰጡት እንዴት ነው? (ለ) ወላጆች የዳዊትን ግሩም ምሳሌ መከተል የሚችሉት እንዴት ነው?

7 የኢየሱስን ምሳሌ የሚከተሉና ትምህርቶቹን የሚታዘዙ ሁሉ ዳዊት ካቀረበው ግብዣ ጋር የሚመሳሰለውን ጥሪ እየተቀበሉ ነው ማለት ይቻላል። ዳዊት “ልጆቼ ሆይ፣ ኑ፤ ስሙኝ፤ እግዚአብሔርን [“ይሖዋን፣” NW] መፍራት አስተምራችኋለሁ” ብሎ ነበር። (መዝሙር 34:11) ከዳዊት ጋር የነበሩት ሰዎች እንደ መሪያቸው ይመለከቱት ስለነበር እነርሱን “ልጆቼ” ብሎ መጥራቱ ተገቢ ነው። ዳዊት፣ ተከታዮቹ ይሖዋን እንዲፈሩ የረዳቸው ሲሆን ይህም አንድነት እንዲኖራቸውና የአምላክን ሞገስ እንዲያገኙ አስችሏቸዋል። ይህ ለክርስቲያን ወላጆች እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው! ይሖዋ፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን ‘በጌታ ምክርና ተግሣጽ እንዲያሳድጓቸው’ ለወላጆች ሥልጣን ሰጥቷቸዋል። (ኤፌሶን 6:4) ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር በየዕለቱ መንፈሳዊ ውይይት በማድረግና መጽሐፍ ቅዱስን በቋሚነት አብረዋቸው በማጥናት ልጆቻቸው ይሖዋን በመፍራት ደስተኛ ሕይወት መምራት እንዲችሉ ይረዷቸዋል።—ዘዳግም 6:6, 7

አምላካዊ ፍርሃትን በሕይወታችን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

8, 9. (ሀ) በአኗኗራችን አምላካዊ ፍርሃት ማሳየት አስደሳች ሕይወት እንድንመራ የሚረዳን ለምንድን ነው? (ለ) አንደበታችንን መከልከል ምን ማድረግን ይጨምራል?

8 ቀደም ብሎ እንደተገለጸው ይሖዋን መፍራት ደስታ አያሳጣንም። ዳዊት “ሕይወትን የሚወድ፣ በጎውንም ያይ ዘንድ ዕድሜን የሚመኝ ማን ነው?” በማለት ጠይቋል። (መዝሙር 34:12) በግልጽ ለመመልከት እንደሚቻለው በደስታ የተሞላ ረጅም ዘመን ለመኖርና በጎውን ለማየት ቁልፉ ይሖዋን መፍራት ነው። “አምላክን እፈራለሁ” ብሎ መናገር ቀላል ነው። ይህንን በአኗኗራችን ማሳየት ግን የመናገሩን ያህል አይቀልም። በመሆኑም ዳዊት አምላካዊ ፍርሃትን እንዴት ማሳየት እንደምንችል ሲገልጽ ቀጥሎ እንዲህ ብሏል።

9 “አንደበትህን ከክፉ ነገር ከልክል፤ ከንፈርህንም ከሽንገላ ጠብቅ።” (መዝሙር 34:13) ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ ክርስቲያኖችን በመካከላቸው የወንድማማች መዋደድ እንዲኖር ከመከራቸው በኋላ በአምላክ መንፈስ ተነሳስቶ ከላይ የተጠቀሰውን የመዝሙር 34 ክፍል ጽፏል። (1 ጴጥሮስ 3:8-12) አንደበታችንን ከክፉ ነገር መከልከል ሲባል ሐሜትን ከማሰራጨት መቆጠብ ማለት ነው። ከዚህ በተቃራኒ ከሌሎች ጋር ስናወራ ምንጊዜም የሚያንጽ ነገር ለመናገር እንጥራለን። ከዚህም በላይ ደፋሮች በመሆን እውነቱን ለመናገር ጥረት እናደርጋለን።—ኤፌሶን 4:25, 29, 31፤ ያዕቆብ 5:16

10. (ሀ) ከክፉ መሸሽ ምን ማለት እንደሆነ አብራራ። (ለ) መልካም ማድረግ ምን ነገሮችን ይጨምራል?

10 “ከክፉ ሽሽ፤ መልካሙንም አድርግ፤ ሰላምን ፈልጋት፤ ተከተላትም።” (መዝሙር 34:14) አምላክ ከሚያወግዛቸው እንደ ጾታ ብልግና፣ ስርቆት፣ መናፍስታዊነት፣ ዓመፅ፣ ስካር እንዲሁም አደገኛ ዕፆችን አላግባብ መጠቀም ካሉ ድርጊቶች እንርቃለን። ከዚህም በላይ እንደ ወሲባዊ ሥዕሎች ወይም ፊልሞች ያሉ አስጸያፊ ነገሮችን የሚያቀርብ መዝናኛም አንመለከትም። (ኤፌሶን 5:10-12) ከዚህ ይልቅ ጊዜያችንን መልካም ለማድረግ እንጠቀምበታለን። ከሁሉ የላቀው መልካም ተግባር ስለ አምላክ መንግሥት በመስበኩና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ አዘውትረን በመካፈል ሰዎች መዳን እንዲያገኙ መርዳት ነው። (ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20) መልካም ማድረግ ለክርስቲያናዊ ስብሰባዎች መዘጋጀትንና በስብሰባዎች ላይ መገኘትን፣ ለዓለም አቀፉ ሥራ የገንዘብ መዋጮ ማድረግን፣ የመንግሥት አዳራሻችንን በአግባቡ መያዝን እንዲሁም ችግረኛ የሆኑ ክርስቲያኖችን መርዳትን ይጨምራል።

11. (ሀ) ዳዊት ስለ ሰላም የተናገረውን በተግባር ያዋለው እንዴት ነው? (ለ) በጉባኤ ውስጥ ‘ሰላምን ለመከተል’ ምን ማድረግ ትችላለህ?

11 ዳዊት ሰላምን በመከተል ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል። ሳኦልን ለመግደል ሁለት አጋጣሚዎች የነበሩት ቢሆንም በሁለቱም ጊዜያት ከዓመጽ በመራቅ ይህን ከማድረግ ተቆጥቧል። እንዲሁም ሰላም ለማውረድ ሲል ንጉሡን በአክብሮት አነጋግሮታል። (1 ሳሙኤል 24:8-11፤ 26:17-20) በዛሬው ጊዜ የጉባኤውን ሰላም የሚያደፈርስ ሁኔታ ቢፈጠር ምን ማድረግ ይቻላል? ‘ሰላምን መፈለግና መከተል’ ይኖርብናል። በመሆኑም በእኛና በእምነት ባልንጀራችን መካከል ያለው ግንኙነት እንደሻከረ ካስተዋልን “በመጀመሪያ ሄደህ ከወንድምህ ጋር ተስማማ” የሚለውን የኢየሱስ ምክር እንታዘዛለን። ከዚያ በኋላ በሌሎች የእውነተኛ አምልኮ ዘርፎች መካፈል እንችላለን።—ማቴዎስ 5:23, 24፤ ኤፌሶን 4:26

አምላክን መፍራት የተትረፈረፈ በረከት ያስገኛል

12, 13. (ሀ) አምላክን የሚፈሩ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ ምን ጥቅሞች ያገኛሉ? (ለ) ታማኝ የይሖዋ አምላኪዎች በቅርቡ ምን ታላቅ ሽልማት ያገኛሉ?

12 “የእግዚአብሔር [“የይሖዋ፣” NW] ዐይኖች ወደ ጻድቃን ናቸው፤ ጆሮዎቹም ለጩኸታቸው ክፍት ናቸው።” (መዝሙር 34:15) አምላክ ለዳዊት ስላደረገለት ነገሮች የሚገልጸው ዘገባ የዚህን ጥቅስ እውነተኝነት ያረጋግጥልናል። በዛሬው ጊዜም ይሖዋ እንደሚመለከተን ማወቃችን ከፍተኛ ደስታና ውስጣዊ ሰላም ያስገኝልናል። በጣም በሚያስጨንቅ ሁኔታ ውስጥም እንኳ ብንሆን ይሖዋ የሚያስፈልጉንን ነገሮች እንደሚያሟላልን እርግጠኞች ነን። በትንቢት በተነገረው መሠረት በቅርቡ የአምላክ እውነተኛ አገልጋዮች በሙሉ በማጎጉ ጎግ ጥቃት እንደሚሰነዘርባቸውና ‘የሚያስፈራው የይሖዋ ቀን’ እንደሚመጣ እናውቃለን። (ኢዩኤል 2:11, 31፤ ሕዝቅኤል 38:14-18, 21-23) በዚያ ወቅት ምንም ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥመን “ጻድቃን ሲጮኹ፣ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ይሰማቸዋል፤ ከመከራቸውም ሁሉ ያድናቸዋል” የሚሉት የዳዊት ቃላት በእኛም ላይ እንደሚፈጸሙ እርግጠኞች ነን።—መዝሙር 34:17

13 በዚያ ወቅት ይሖዋ ታላቅ ስሙን ከፍ ከፍ ሲያደርገው መመልከት ምንኛ አስደሳች ይሆናል! ልባችን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በጥልቅ አክብሮታዊ ፍርሃት ይሞላል፤ ተቃዋሚዎች በሙሉ ውርደት ተከናንበው ይጠፋሉ። “መታሰቢያቸውን ከምድር ለማጥፋት፣ የእግዚአብሔር [“የይሖዋ፣” NW] ፊት በክፉ አድራጊዎች ላይ ነው።” (መዝሙር 34:16) ከጥፋት ተርፎ አምላክ ወዳዘጋጀው ጽድቅ የሰፈነበት አዲስ ዓለም መግባት እንዴት ያለ ታላቅ በረከት ነው!

ለመጽናት የሚረዱን ተስፋዎች

14. መከራዎች ቢደርሱብንም የትኞቹ ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳቦች እንድንጸና ይረዱናል?

14 እስከዚያው ድረስ ግን ጥላቻ በነገሠበትና ምግባረ ብልሹ በሆነ ዓለም ውስጥ እየኖርን ይሖዋን መታዘዛችንን መቀጠል ጽናት ይጠይቃል። አምላካዊ ፍርሃት ታዛዥነትን ለማዳበር በእጅጉ ይረዳናል። የምንኖርበት ዘመን አስጨናቂ በመሆኑ አንዳንድ የይሖዋ አገልጋዮች ልባቸውን የሚሰብርና መንፈሳቸውን የሚደቁስ ከባድ ችግር ይደርስባቸዋል። ሆኖም በይሖዋ ከታመኑ እርሱ ለመጽናት እንደሚረዳቸው ሙሉ በሙሉ እርግጠኞች መሆን ይችላሉ። “እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፤ መንፈሳቸው የተሰበረውንም ያድናቸዋል” የሚሉት የዳዊት ቃላት እውነተኛ ማጽናኛ ይሰጣሉ። (መዝሙር 34:18) ዳዊት አክሎም “የጻድቅ መከራው ብዙ ነው፤ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ግን ከሁሉም ያድነዋል” በማለት የሚያበረታታ ሐሳብ ሰጥቷል። (መዝሙር 34:19) የቱንም ያህል በርካታ መከራዎች ቢደርሱብን ይሖዋ ኃያል በመሆኑ ያድነናል።

15, 16. (ሀ) ዳዊት መዝሙር 34ን ካቀናበረ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ምን አሳዛኝ ነገር ሰማ? (ለ) መከራዎች በሚደርሱብን ጊዜ ለመጽናት ምን ሊረዳን ይችላል?

15 ዳዊት መዝሙር 34ን ካቀናበረ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሳኦል የኖብ ከተማ ነዋሪዎችንና አብዛኞቹን ካህናት እንደፈጀ ሰማ። ይህ የአምላክ አገልጋይ፣ ሳኦል ተቆጥቶ እንዲህ ዓይነት እርምጃ የወሰደው እርሱ ወደ ኖብ በመሄዱ እንደሆነ ሲያስብ እንዴት አዝኖ ይሆን! (1 ሳሙኤል 22:13, 18-21) ዳዊት እርዳታ ለማግኘት ወደ ይሖዋ ዘወር እንዳለ ጥርጥር የለውም፤ “ጻድቃን” ወደፊት ትንሣኤ እንደሚያገኙ የሚናገረው ተስፋም እንዳጽናናው እሙን ነው።—የሐዋርያት ሥራ 24:15

16 በዛሬው ጊዜም የትንሣኤ ተስፋ ያጠናክረናል። ጠላቶቻችን የሚያደርጉት ማንኛውም ነገር ዘላቂ ጉዳት ሊያደርስብን እንደማይችል እናውቃለን። (ማቴዎስ 10:28) ዳዊት “[የጻድቁን ዐጥንቶች] ሁሉ ይጠብቃል፤ ከእነርሱም አንድ አይሰበርም” በማለት እንዲህ ዓይነት እምነት እንዳለው ገልጿል። (መዝሙር 34:20) ይህ ጥቅስ በኢየሱስ ላይ ቃል በቃል ተፈጻሚነት አግኝቷል። ኢየሱስ ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ቢገደልም ከአጥንቶቹ አንዱም እንኳ ‘አልተሰበረም።’ (ዮሐንስ 19:36) መዝሙር 34:20 በአሁኑ ጊዜም ቅቡዓን ክርስቲያኖችም ሆኑ “ሌሎች በጎች” ምንም ዓይነት መከራ ቢያጋጥማቸውም ዘላቂ ጉዳት እንደማይደርስባቸው ያረጋግጥልናል። በምሳሌያዊ አነጋገር አጥንታቸው ፈጽሞ አይሰበርም።—ዮሐንስ 10:16

17. የይሖዋን ሕዝቦች የሚጠሉ ንስሐ የማይገቡ ሰዎች ምን ይጠብቃቸዋል?

17 ለኃጢአተኞች ግን ሁኔታው ከዚህ የተለየ ነው። እንደነዚህ ያሉት ሰዎች በቅርቡ የዘሩትን መጥፎ ነገር ያጭዳሉ። “ኀጢአተኞችን ክፋት ይገድላቸዋል፤ ጻድቃንን የሚጠሉ ይፈረድባቸዋል።” (መዝሙር 34:21) የአምላክን ሕዝቦች መቃወማቸውን የሚቀጥሉ ሁሉ አስከፊ የሆነ መከራ ይደርስባቸዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ እነዚህ ሰዎች “በዘላለም ጥፋት ይቀጣሉ።”—2 ተሰሎንቄ 1:9

18. ‘የእጅግ ብዙ ሕዝብ’ አባላት በአሁኑ ጊዜ የተቤዡት በምን መንገድ ነው? ወደፊትስ ምን ያገኛሉ?

18 ዳዊት፣ “እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] የባሪያዎቹን ነፍስ ይቤዣል፤ እርሱንም መጠጊያ ያደረገ አይፈረድበትም” በሚሉት የሚያበረታቱ ቃላት መዝሙሩን ደምድሟል። (መዝሙር 34:22) ንጉሥ ዳዊት ለ40 ዓመታት በቆየው የግዛት ዘመኑ መገባደጃ አካባቢ “ነፍሴን ከመከራ ሁሉ ያዳናት ሕያው እግዚአብሔር” በማለት ተናግሮ ነበር። (1 ነገሥት 1:29) እንደ ዳዊት ይሖዋን የሚፈሩ ሁሉ በቅርቡ፣ በኃጢአት ምክንያት ከፈጸሙት ከማንኛውም ጥፋት እንደተቤዡና ካጋጠሟቸው መከራዎች ሁሉ እንደዳኑ መለስ ብለው ሲያስቡ ይደሰታሉ። በአሁኑ ጊዜ አብዛኞቹ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በሰማይ ሽልማታቸውን አግኝተዋል። ከሕዝብ ሁሉ የተውጣጡት “እጅግ ብዙ ሕዝብ” ደግሞ ከቀሩት የኢየሱስ ወንድሞች ጋር ተባብረው አምላክን እያገለገሉ ሲሆን እነዚህ ሰዎች የፈሰሰው የኢየሱስ ደም የመቤዠት ኃይል እንዳለው ስለሚያምኑ በይሖዋ ፊት ንጹሕ አቋም አላቸው። እነዚህ እጅግ ብዙ ሕዝቦች በቅርቡ በሚመጣው የክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት ከኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ሙሉ በሙሉ ተጠቃሚ ስለሚሆኑ ወደ ፍጽምና ይደርሳሉ።—ራእይ 7:9, 14, 17፤ 21:3-5

19. ‘የእጅግ ብዙ ሕዝብ’ አባላት ምን ቁርጥ ውሳኔ አድርገዋል?

19 “እጅግ ብዙ ሕዝብ” የሆኑት የአምላክ አገልጋዮች እነዚህን ሁሉ በረከቶች የሚያገኙት ለምንድን ነው? ይሖዋን በከፍተኛ የአድናቆት ስሜት በማገልገልና እርሱን በአክብሮት በመታዘዝ ፈሪሃ አምላክ እንዳላቸው ማሳየታቸውን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ በማድረጋቸው ነው። በእርግጥም ይሖዋን መፍራት በአሁኑ ጊዜ ሕይወታችን አስደሳች እንዲሆን ከማድረጉም በላይ “እውነተኛ የሆነውን ሕይወት” ማለትም በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ የዘላለም ሕይወት እንድናገኝ ይረዳናል።—1 ጢሞቴዎስ 6:12, 18, 19፤ ራእይ 15:3, 4

ታስታውሳለህ?

• አምላክን መፍራት ያለብን ለምንድን ነው? እርሱን መፍራት ሲባልስ ምን ማለት ነው?

• አምላካዊ ፍርሃት በአኗኗራችን ላይ ምን ተጽዕኖ ሊያሳድር ይገባል?

• አምላክን መፍራት ምን በረከት ያስገኛል?

• እንድንጸና የሚረዱን የትኞቹ ተስፋዎች ናቸው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋን የሚፈሩ ሰዎች በእገዳ ሥር በሚሆኑበት ጊዜም አምልኳቸውን በጥበብ ያከናውናሉ

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለሰዎች ማድረግ የምንችለው ከሁሉ የላቀው መልካም ተግባር ስለ አምላክ መንግሥት ምሥራች መስበክ ነው