ይሖዋን በደስታ መጠበቅ
ይሖዋን በደስታ መጠበቅ
ያልበሰለ ፍሬ በልተህ ታውቃለህ? ጣዕሙን እንዳልወደድከው የታወቀ ነው። አንድ ፍሬ ለመብሰል ጊዜ ቢወስድም እስኪበስል ድረስ መጠበቁ ግን የሚክስ ነው። በትዕግሥት በመጠበቃችን የምንካስባቸው ሌሎች ሁኔታዎችም አሉ። መጽሐፍ ቅዱስ “ለእኛ የሚበጀን [የይሖዋን] አዳኝነት በትዕግሥት መጠበቅ ብቻ ነው” ይላል። (ሰቆቃወ ኤርምያስ 3:26 የ1980 ትርጉም፤ ቲቶ 2:13) ክርስቲያኖች ይሖዋን በትዕግሥት መጠበቅ ያለባቸው በየትኞቹ መንገዶች ነው? ይሖዋን በመጠበቅ የምንጠቀመውስ እንዴት ነው?
አምላክን መጠበቅ ምን ማድረግን ይጨምራል?
ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን የምንኖረው ‘የይሖዋን ቀን እየተጠባበቅንና መምጫውን እያፋጠንን’ ነው። አምላክ ‘ኀጢአተኞችን ሲያጠፋ’ እፎይታ የምናገኝበትን ጊዜ በጉጉት እንጠባበቃለን። (2 ጴጥሮስ 3:7, 12) ይሖዋ ራሱም ክፋትን ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ ከፍተኛ ፍላጎት አለው፤ ሆኖም ለስሙ ክብር በሚያመጣ መንገድ ክርስቲያኖችን ለማዳን ሲል በትዕግሥት ይጠብቃል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “እግዚአብሔር ቊጣውን ለማሳየት፣ ኀይሉንም ለማሳወቅ ፈልጎ የቊጣው መግለጫ የሆኑትን፣ ለጥፋትም የተዘጋጁትን እጅግ ታግሦ . . . የምሕረቱም መግለጫዎች ለሆኑት፣ የክብሩ ባለ ጠግነት እንዲታወቅ ይህን አድርጎ እንደ ሆነስ?” (ሮሜ 9:22, 23) ይሖዋ በኖኅ ዘመን እንዳደረገው ሁሉ በዛሬው ጊዜም ሕዝቦቹን የሚያድንበትን ትክክለኛ ጊዜ ያውቃል። (1 ጴጥሮስ 3:20) በመሆኑም አምላክን መጠበቅ ሲባል እርምጃ የሚወስድበት ጊዜ እስኪደርስ በትዕግሥት መጠበቅ ማለት ነው።
የይሖዋን ቀን ስንጠባበቅ፣ በዙሪያችን ያለው ዓለም የሥነ ምግባር መሥፈርት ከቀን ወደ ቀን እየዘቀጠ በመሄዱ እንበሳጭ ይሆናል። እንደዚህ ሲሰማን እንደሚከተለው ብሎ የጻፈውን የነቢዩ ሚክያስን ቃላት ማስታወሳችን ያበረታታናል:- “ፈሪሃ እግዚአብሔር ያደረበት ሰው ከምድር ጠፍቶአል፤ አንድም እንኳ ቅን ሰው የለም፣ . . . እኔ ግን እግዚአብሔርን ተስፋ አደርጋለሁ፤ አዳኜ የሆነውን አምላክ እጠብቃለሁ።” (ሚክያስ 7:2, 7) ይሖዋን ‘ስንጠብቅ’ ምን ዓይነት ዝንባሌ ሊኖረን ይገባል? አብዛኛውን ጊዜ መጠበቅ የሚያበሳጭ በመሆኑ አምላክን በደስታ መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?
በደስታ መጠበቅ
በትዕግሥት በመጠበቅ ረገድ ትክክለኛውን ዝንባሌ ለማዳበር ከይሖዋ መማር እንችላለን። ይሖዋ ምንጊዜም ቢሆን “ደስተኛ አምላክ” ነው። (1 ጢሞቴዎስ 1:11 NW) ይሖዋ እርሱን የሚወዱትን ሰዎች፣ የሰው ዘሮችን ሲፈጥር ወዳሰበው የፍጽምና ደረጃ የማድረስ ዓላማ አለው፤ ይህን ዓላማውን ከዳር ለማድረስ እየሠራ በመሆኑ ዓላማውን የሚፈጽምበትን ጊዜ የሚጠብቀው በደስታ ነው። (ሮሜ 5:12፤ 6:23) በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ እውነተኛው አምልኮ እየመጡ በመሆኑ ይሖዋ የሥራውን አስደሳች ውጤት እየተመለከተ ነው። ኢየሱስ “አባቴ እስካሁን እየሠራ ነው፤ እኔም ደግሞ እሠራለሁ” ብሏል። (ዮሐንስ 5:17) ደስተኛ ለመሆን ቁልፉ ሌሎችን የሚጠቅም ሥራ ማከናወን ነው። (የሐዋርያት ሥራ 20:35) በተመሳሳይም እውነተኛ ክርስቲያኖች የይሖዋን ቀን ሲጠብቁ እጃቸውን አጣጥፈው አይቀመጡም። ከዚህ ይልቅ አምላክ ለሰው ዘር ስላለው ዓላማ ለሰዎች ለማሳወቅ ይጥራሉ።
ቀደም ካሉት ዘመናት ጀምሮ ታማኝ የሆኑ ሰዎች አምላክ እርምጃ የሚወስድበትን ወቅት ሲጠባበቁ ምንጊዜም እርሱን በደስታ ማወደሳቸውን አላቋረጡም። መዝሙራዊው ዳዊትን እንደ ምሳሌ እንመልከት። ዳዊት፣ ንጉሡ ያሳደደው ሲሆን የቅርብ ጓደኛውና ልጁ ደግሞ ከድተውታል። ታዲያ ዳዊት እነዚህ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙት ይሖዋ መዝሙር 71 እንዲህ ይላል:- “እኔ ግን ሁልጊዜ ተስፋ አደርጋለሁ፤ በምስጋና ላይ ምስጋና አቀርብልሃለሁ። አንደበቴ ስለ ጽድቅህ፣ ቀኑን ሙሉ ስለ ማዳንህ ይናገራል።” (መዝሙር 71:14, 15) ዳዊት፣ ይሖዋን በሚጠብቅበት ጊዜ ትዕግሥት አጥቶ ከመበሳጨት ይልቅ እርሱን ያወድስና በእውነተኛው አምልኮ እንዲጸኑ ሌሎችን ያበረታታ ስለነበር ደስተኛ እንደሆነ ተናግሯል።—መዝሙር 71:23
ባሰበው ጊዜ እረፍት እስኪሰጠው ድረስ በደስታ መጠበቅ ይችል ነበር? በእርሱ እንደተጻፈ የሚገመተውይሖዋን መጠበቅ የዘገየን አውቶቡስ እንደመጠበቅ የሚያበሳጭ አይደለም። ከዚህ ይልቅ፣ ወላጆች ልጃቸው አድጎ የሚኮሩበት ሰው እስኪሆን ድረስ በደስታ በሚጠብቁበት ጊዜ ከሚሰማቸው ስሜት ጋር ይመሳሰላል። ልጁ አድጎ እዚያ ደረጃ ላይ እስኪደርስ ድረስ ያሉት ዓመታት በሥራ የተሞሉ ናቸው፤ የሚፈልጉትን ውጤት ለማግኘት በእነዚህ ዓመታት ለልጃቸው ሥልጠና፣ መመሪያና ተግሣጽ ይሰጡታል። በተመሳሳይም ይሖዋን ስንጠብቅ ሌሎች ወደ አምላክ እንዲቀርቡ በመርዳት ደስታ እናገኛለን። እኛም የአምላክን ሞገስ ማግኘትና መዳን እንፈልጋለን።
ተስፋ አለመቁረጥ
ይሖዋን መጠበቅ ሲባል ተስፋ ሳንቆርጥና ለእርሱ ያለን ፍቅር ሳይቀንስ አምላክን ማገልገላችንን መቀጠል ማለት ነው። ይህን ማድረግ ተፈታታኝ ሊሆን ይችላል። በዛሬው ጊዜ አብዛኞቹ የአምላክ አገልጋዮች በሚኖሩበት ማኅበረሰብ ውስጥ ይሖዋ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ እምነት የሚያሳድር ሰው ይፌዝበታል። ሆኖም ለ70 ዓመታት በባቢሎን በግዞት በኖሩበት ወቅት ተስፋቸው ሳይደበዝዝ የቆዩትን ታማኝ እስራኤላውያን ምሳሌ እንመልከት። እነዚህ እስራኤላውያን እንዲህ እንዲያደርጉ የረዳቸው ምን ነበር? መዝሙራትን ማንበባቸው እንዳጠናከራቸው ምንም ጥርጥር የለውም። በዚያ ወቅት ተጽፎ ሊሆን የሚችል አንድ የሚያበረታታ መዝሙር እንዲህ ይላል:- “በቃሉም ተስፋ አደርጋለሁ። ዘብ ዐዳሪ ንጋትን ከሚጠባበቅ ይልቅ፣ አዎን፤ ዘብ ዐዳሪ ንጋትን ከሚጠባበቅ ይልቅ፣ ነፍሴ ጌታን ትጠባበቃለች። . . . እስራኤል ሆይ፤ በእግዚአብሔር ተስፋ አድርግ።”—መዝሙር 130:5-7
ስለ ተስፋቸው በማንበብና ለሌሎች በመናገር ተስፋቸው እንዳይደበዝዝ ያደረጉት አይሁዳውያን ከጊዜ በኋላ ባቢሎን በወራሪዎች እጅ ስትወድቅ ተክሰዋል። በሺዎች የሚቆጠሩ ታማኝ አይሁዳውያን ጊዜ ሳያጠፉ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ አስመልክቶ “እግዚአብሔር የጽዮንን ምርኮ በመለሰ ጊዜ፣ . . . አፋችን በሣቅ . . . ተሞላ” ተብሎ ተጽፏል። (መዝሙር 126:1, 2) እነዚህ አይሁዳውያን ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ እምነታቸውን ማጠናከራቸውን ቀጥለዋል። ይሖዋን በመዝሙር ማወደሳቸውንም በፍጹም አላቋረጡም።
በተመሳሳይም “የዓለም መጨረሻ” በደረሰበት በዚህ ዘመን አምላክን የሚጠባበቁ እውነተኛ ክርስቲያኖች እምነታቸው እንዳይጠፋ የማያቋርጥ ጥረት ያደርጋሉ። የአምላክን ቃል ያጠናሉ፣ እርስ በእርስ ይበረታታሉ እንዲሁም የመንግሥቱን ምሥራች በመስበክ ይሖዋን ማወደሳቸውን ይቀጥላሉ።—ማቴዎስ 24:3, 14
ከሚሰጠን ተግሣጽ ለመጠቀም አምላክን መጠበቅ
የአምላክ ነቢይ የሆነው ኤርምያስ “ለእኛ የሚበጀን [የይሖዋን] አዳኝነት በትዕግሥት መጠበቅ ብቻ ነው” በማለት ጽፎ ነበር። (ሰቆቃወ ኤርምያስ 3:26 የ1980 ትርጉም) ኤርምያስ ይህን ሲል፣ ይሖዋ ኢየሩሳሌም እንድትጠፋ በመፍቀድ ሕዝቡን በመቅጣቱ የአምላክ ሕዝቦች ቅሬታ ሊያድርባቸው እንደማይገባ መናገሩ ነበር። ከዚህ ይልቅ አለመታዘዛቸው ያስከተለባቸውን መዘዞች በማሰብ እንዲሁም የአመለካከት ለውጥ የማድረግን አስፈላጊነት በመገንዘብ ከደረሰባቸው መከራ ጠቃሚ ትምህርት ማግኘት ነበረባቸው።—ሰቆቃወ ኤርምያስ 3:40, 42
ይሖዋ ከሚሰጠን ተግሣጽ የምናገኘው ጥቅም አንድ ፍሬ ከሚበስልበት መንገድ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው፣ አምላክ የሚሰጠው ተግሣጽ “ለለመዱት ሰዎች የጽድቅና የሰላም ፍሬ ያስገኝላቸዋል።” (ዕብራውያን 12:11) አንድ ፍሬ ለመብሰል ጊዜ እንደሚወስድ ሁሉ እኛም አምላክ የሚሰጠንን ሥልጠና ተቀብለን አመለካከታችንን ለመለወጥ ጊዜ ያስፈልገናል። ለምሳሌ ያህል፣ መጥፎ ድርጊት በመፈጸማችን በጉባኤ ውስጥ ያሉንን አንዳንድ ኃላፊነቶች ብናጣ አምላክን ለመጠበቅ ፈቃደኛ መሆናችን ተስፋ እንዳንቆርጥ ይረዳናል። በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ውስጥ ስንሆን ዳዊት በመንፈስ አነሳሽነት እንደሚከተለው ብሎ የጻፈው ሐሳብ ያበረታታናል:- “[የአምላክ ቍጣ] ለዐጭር ጊዜ ነው፤ ቸርነቱ ግን እስከ ዕድሜ ልክ ነውና፤ ሌሊቱን በልቅሶ ቢታደርም፣ በማለዳ ደስታ ይመጣል።” (መዝሙር 30:5) ይሖዋን በትዕግሥት የመጠበቅ ዝንባሌ ካዳበርንና ከአምላክ ቃል እንዲሁም ከድርጅቱ የምናገኘውን ምክር በተግባር የምናውል ከሆነ “ደስታ” የምናገኝበት ጊዜ ይመጣል።
ወደ ጉልምስና ማደግ ጊዜ ይወስዳል
ወጣት ከሆንክ ወይም የተጠመቅከው በቅርቡ ከሆነ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ አንዳንድ ኃላፊነቶችን ለማግኘት ትጓጓ ይሆናል። ይሁን እንጂ እነዚህን ኃላፊነቶች ለመሸከም የሚያስፈልግህ መንፈሳዊ ጉልምስና ላይ ለመድረስ ጊዜ ይወስዳል። በመሆኑም ወጣትነትህን በመንፈሳዊ ለማደግ ተጠቀምበት። ለአብነት ያህል፣ ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ ለማንበብ እንዲሁም ክርስቲያናዊ ባሕርያትን ለማፍራትና ደቀ መዛሙርት የማድረግ ችሎታን ለማዳበር ወጣትነት ጥሩ ጊዜ ነው። (መክብብ 12:1) ትሑት በመሆን ይሖዋን የመጠበቅ ዝንባሌ ካዳበርክ ይሖዋ በጊዜው ተጨማሪ ኃላፊነቶች ይሰጥሃል።
ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራም ቢሆን ትዕግሥት ይጠይቃል። አንድ ገበሬ ዘሩን አምላክ እስከሚያሳድገው ድረስ ውኃ ማጠጣቱን መቀጠል እንዳለበት ሁሉ ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራም ተመሳሳይ ነው። (1 ቆሮንቶስ 3:7፤ ያዕቆብ 5:7) ሰዎች በይሖዋ ላይ እምነት እንዲኖራቸውና ለእርሱ አድናቆት እንዲያድርባቸው ለመርዳት፣ ለወራት ወይም ደግሞ ለዓመታት በትዕግሥት መጽሐፍ ቅዱስን ማስጠናት ያስፈልጋል። ይሖዋን በትዕግሥት መጠበቅ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችን የሚማሩትን ነገር መጀመሪያ ላይ ተግባራዊ ባያደርጉትም እንኳ ሳንሰለች ጥረት ማድረግን ይጠይቃል። ተማሪዎቹ በተወሰነ መጠንም ቢሆን አድናቆት ካሳዩ ይህ ለይሖዋ መንፈስ ምላሽ እየሰጡ መሆኑን የሚጠቁም ሊሆን ይችላል። በትዕግሥት ከጸናህ ጥናትህ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር እንዲሆን ይሖዋ ሲረዳው በመመልከት ልትደሰት ትችል ይሆናል።—ማቴዎስ 28:20
በመጠበቅ ፍቅር ማሳየት
በትዕግሥት መጠበቅ ለአንድ ሰው ፍቅር እንዳለንና በእርሱ እንደምንተማመን የሚያሳይ መሆኑን በምሳሌ ለማስረዳት በደቡብ አሜሪካ፣ በአንዲስ ተራሮች በረሃማ አካባቢ የሚኖሩ አንዲት አረጋዊት እህት ያጋጠማቸውን ሁኔታ እንመልከት። በመንደሩ ውስጥ ያሉት የይሖዋ ምሥክሮች እሳቸውና አንዲት መንፈሳዊ እህታቸው ብቻ ነበሩ። እነዚህ እህቶች የእምነት ባልንጀሮቻቸውን መምጣት ምን ያህል በጉጉት እንደሚጠብቁ መገመት ትችላለህ! በአንድ ወቅት አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ለመጀመሪያ ጊዜ እነርሱን ለመጎብኘት ሲሄድ ቦታው ጠፋበት። በመሆኑም በመጣበት መንገድ እንደገና ወደኋላ ሲመለስ ረጅም ሰዓታት ስላጠፋ በጣም ዘገየ። በመጨረሻም መንደሩን ከሩቅ ተመለከተው፤ በዚህ ጊዜ እኩለ ሌሊት አልፎ ነበር። በዚያ አካባቢ የኤሌክትሪክ መብራት ስላልነበረ ብርሃን ሲያይ በጣም ተገረመ። በኋላም ወደ መንደሩ መግቢያ ሲደርስ እኚህ አረጋዊት እህት ኩራዝ ይዘው ሲመለከት ምን ያህል እንደተደሰተ መገመት አያዳግትም! እኚህ እህት፣ ወንድም እንደሚመጣ እርግጠኛ ስለነበሩ እየጠበቁት ነበር።
እኛም ልክ እንደ እኚህ አረጋዊት እህት ትዕግሥት በማሳየት ይሖዋን በደስታ እንጠባበቃለን። ይሖዋ ቃሉን እንደሚጠብቅ እርግጠኞች ነን። ከላይ እንደተገለጸው ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሁሉ እኛም በፍቅር ተነሳስተው የሚጠብቁንን እናደንቃቸዋለን። በመሆኑም አምላክ እርሱን የሚጠብቁትን የሚያደንቅ መሆኑ ምንም አያስገርምም። መጽሐፍ ቅዱስ “ይሖዋ . . . ፍቅራዊ ደግነቱን በሚጠብቁ ይደሰታል” ይላል።—መዝሙር 147:11 NW
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል8]
አምላክን በማወደሱ ሥራ የሚጠመዱ ሰዎች ይሖዋን በመጠበቅ ይደሰታሉ