በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሐና ሰላም ያገኘችው እንዴት ነው?

ሐና ሰላም ያገኘችው እንዴት ነው?

ሐና ሰላም ያገኘችው እንዴት ነው?

አንዲት ታማኝ ሴት ጮክ ብላ በመጸለይ ይሖዋን አወደሰች። አምላክ ሐዘኗን ወደ ደስታ በመለወጥ ከትቢያ ላይ እንዳነሳት ተሰምቷታል።

የዚህች ሴት ስም ሐና ይባላል። በስሜቷ ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣው ምንድን ነው? በጣም የተደሰተችውስ ለምንድን ነው? ከእርሷ ተሞክሮ ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት የሐናን ታሪክ መለስ ብለን እንመልከት።

ውጥረት ላይ ያለ ቤተሰብ

ሐና በኤፍሬም አገር የሚኖር ሕልቃና የተባለ አንድ ሌዋዊ ካሉት ሁለት ሚስቶች መካከል አንዷ ነች። (1 ሳሙኤል 1:1, 2ሀ፤ 1 ዜና መዋዕል 6:33, 34) ምንም እንኳ ሰዎች ከአንድ በላይ ማግባታቸው የአምላክ የመጀመሪያ ዓላማ ባይሆንም በሙሴ ሕግ ሥር እንዲህ ማድረግ ተፈቅዶና ሕግ ወጥቶለት ነበር። የሕልቃና ቤተሰብ ይሖዋን የሚያመልክ ቢሆንም በዚህ ቤተሰብ ውስጥ ከተከሰቱት ሁኔታዎች መመልከት እንደሚቻለው ከአንድ በላይ ማግባት ብዙውን ጊዜ ለግጭት መንስኤ ይሆናል።

ሐና መካን ስትሆን ሌላኛዋ የሕልቃና ሚስት ፍናና ግን ልጆች ነበሯት። ፍናና የሐና ባላንጣ ነበረች።—1 ሳሙኤል 1:2ለ

መካንነት በእስራኤላውያን ሴቶች ዘንድ እንደ ውርደት የሚታይ ሲሆን የአምላክን ሞገስ የማጣት ምልክት እንደሆነ ተደርጎም ይታሰባል። ይሁንና ሐና ልጅ መውለድ ያልቻለችው የአምላክን ሞገስ በማጣቷ እንደሆነ የሚያመለክት ምንም ነገር የለም። ፍናና ግን ሐናን ለማጽናናት ከመሞከር ይልቅ ልጅ የመውለድ ችሎታዋን ጣውንቷን ለማበሳጨት ትጠቀምበት ነበር።

ወደ ይሖዋ መቅደስ የሚደረጉ ጉዞዎች

በሕልቃና ቤተሰብ ውስጥ እንዲህ ዓይነት ውጥረት የነገሠ ቢሆንም ቤተሰቡ ሴሎ በሚገኘው የይሖዋ መቅደስ መሥዋዕት ለማቅረብ በየዓመቱ ወደዚያ ይሄዱ ነበር። a ደርሶ መልስ ወደ 60 ኪሎ ሜትር ገደማ የሚሆነውን ይህን ጉዞ የሚያደርጉት በእግር ሳይሆን አይቀርም። ይህ ወቅት በተለይ ለሐና አስቸጋሪ ሳይሆንባት አልቀረም፤ ምክንያቱም የኅብረት መሥዋዕት በሚቀርብበት ጊዜ በርከት ያለው ድርሻ ለፍናና እና ለልጆቿ ሲሰጥ ለሐና ግን የሚሰጣት “አንድ ድርሻ” [NW] ብቻ ነበር። ይሖዋ የሐናን ‘ማሕፀን የዘጋው’ ይመስል ስለነበር ፍናና ይህን አጋጣሚ ሐናን ለማበሳጨትና አንገቷን እንድትደፋ ለማድረግ ትጠቀምበት ነበር። ይህ ሁኔታ በየዓመቱ ስለሚደጋገም ሐና ሥራዋ ማልቀስ ብቻ ሆኖ ነበር፤ ብሎም ምግብ መብላት አስጠልቷት ነበር። በዚህም ምክንያት ጉዞው ለሐና የደስታ ምንጭ ከመሆን ይልቅ የጭንቀት ወቅት ሆኖባታል። ቢሆንም ሐና ወደ ይሖዋ መቅደስ ከመሄድ ወደኋላ አላለችም።—1 ሳሙኤል 1:3-7

በእርግጥም ሐና ግሩም ምሳሌ ትታልናለች! የሚያበሳጭ ሁኔታ ሲያጋጥምህ ምን ታደርጋለህ? ራስህን በማግለል ከእምነት አጋሮችህ ጋር ያለህን ግንኙነት ታቋርጣለህ? ሐና እንደዚህ አላደረገችም። ከይሖዋ አምላኪዎች መካከል የመገኘት ልማድ ነበራት። ያጋጠመን ሁኔታ የቱንም ያህል አስጨናቂ ቢሆን እኛም ተመሳሳይ ነገር ማድረግ ይኖርብናል።—መዝሙር 26:12፤ 122:1፤ ምሳሌ 18:1 የ1954 ትርጉም፤ ዕብራውያን 10:24, 25

ሕልቃና “ሐና ሆይ፤ ለምን ታለቅሻለሽ? ለምንስ አትበዪም? ልብሽስ ለምን ያዝናል? ከዐሥር ወንዶች ልጆች እኔ አልበልጥብሽምን?” ብሎ በመጠየቅ እርሷን ለማጽናናትና የልቧን አውጥታ እንድትነግረው ለማድረግ ሞክሯል። (1 ሳሙኤል 1:8) ፍናና በሐና ላይ የምትፈጽመውን በደል ሕልቃና ስለማያውቅ ሐና ለእርሱ ስሞታ ከመናገር ይልቅ ችግሯን ችላ ለመኖር መርጣ ይሆናል። ያም ሆነ ይህ፣ መንፈሳዊ አስተሳሰብ የነበራት ሐና በጸሎት ወደ ይሖዋ በመቅረብ ሰላም ለማግኘት ጥራለች።

ሐና ስዕለት ተሳለች

የኅብረት መሥዋዕት የሚበላው በይሖዋ መቅደስ ውስጥ ነበር። ሐና ከመመገቢያው ክፍል በመውጣት ወደ አምላክ ትጸልይ ነበር። (1 ሳሙኤል 1:9, 10) “የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ የአገልጋይህን መዋረድ ተመልክተህ ብታስበኝና አገልጋይህን ሳትረሳት ወንድ ልጅ ብትሰጣት፣ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ለእግዚአብሔር እሰጠዋለሁ፤ ምላጭም በራሱ ላይ አይደርስም” ስትል ይሖዋን ተማጸነች።—1 ሳሙኤል 1:11

ሐና በዚህ ጸሎቷ ላይ የምትፈልገውን ነገር ለይታ ጠቅሳለች። ወንድ ልጅ እንዲሰጣት የጠየቀች ሲሆን ልጁም በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ለይሖዋ የተወሰነ ናዝራዊ እንደሚሆን ተስላለች። (ዘኍልቍ 6:1-5) እንዲህ ዓይነቱን ስዕለት ባሏ መፍቀድ ስለሚኖርበት ሕልቃና በኋላ ላይ የወሰደው እርምጃ የሚወዳት ሚስቱ በገባችው ቃል እንደተስማማ ያሳያል።—ዘኍልቍ 30:6-8

ሐና የጸለየችበት መንገድ ሊቀ ካህናቱ ዔሊ ሰክራለች ብሎ እንዲያስብ አድርጎታል። ከንፈሯ ይንቀሳቀስ የነበረ ቢሆንም በልቧ ስለምትናገር ድምጿ አይሰማም ነበር። በዚህ ወቅት ያቀረበችው ጸሎት ከልብ የመነጨ ነበር። (1 ሳሙኤል 1:12-14) ዔሊ እንደሰከረች አድርጎ ሲነቅፋት ሐና ምን ያህል ተሰምቷት ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም! ቢሆንም ለሊቀ ካህናቱ መልስ የሰጠችው በአክብሮት ነበር። ዔሊ፣ ሐና ‘ከባድ ከሆነው ጭንቀቷና ሐዘኗ የተነሣ’ በመጸለይ ላይ እንደነበረች ሲገነዘብ “የእስራኤል አምላክ የለመንሺውን ይስጥሽ” አላት። (1 ሳሙኤል 1:15-17) ሐናም “መንገዷን ሄደች፤ ምግብም በላች፤ ከዚያም በኋላ በፊቷ ላይ ሐዘን አልታየም።”—1 ሳሙኤል 1:18

ከዚህ ምን እንማራለን? ስለሚያስጨንቁን ነገሮች ወደ ይሖዋ ስንጸልይ ምን እንደሚሰማን ልንነግረው እንዲሁም የሚያስፈልጉንን ነገሮች እንዲሰጠን ከልብ በመነጨ ስሜት ልንጠይቀው እንችላለን። ችግሩን ለመፍታት ማድረግ የምንችለው ነገር ከሌለ ጉዳዩን ለእርሱ መተው ይኖርብናል። ልንከተለው የሚገባ ከዚህ የተሻለ አካሄድ የለም።—ምሳሌ 3:5, 6

የይሖዋ አገልጋዮች ከልብ የመነጨ ጸሎት ካቀረቡ በኋላ ሐና የተሰማት ዓይነት ሰላም እንደሚሰማቸው እሙን ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ጸሎትን አስመልክቶ “በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ፣ ከምስጋናም ጋር ልመናችሁን በእግዚአብሔር ፊት አቅርቡ እንጂ ስለማንኛውም ነገር አትጨነቁ። ከማስተዋል በላይ የሆነው የእግዚአብሔር ሰላም፣ ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል” በማለት ጽፏል። (ፊልጵስዩስ 4:6, 7) ሸክማችንን በይሖዋ ላይ እስከጣልን ድረስ ጉዳዩን ለእሱ መተው ይኖርብናል። እንደ ሐና ሁሉ እኛም ከዚያ በኋላ ያንን ነገር እያሰብን ማዘን አይኖርብንም።—መዝሙር 55:22

ለይሖዋ የተሰጠ ልጅ

ከዚያ በኋላ አምላክ ሐናን ስላሰባት ፀንሳ ወንድ ልጅ መውለድ ቻለች። (1 ሳሙኤል 1:19, 20) ይህ ዘገባ አምላክ ወደፊት አገልጋዮቹ የሚሆኑ ልጆች እንዲወለዱ እጁን እንዳስገባ ከሚገልጹት ጥቂት የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ውስጥ አንዱ ነው። የሕልቃናና የሐና ልጅ ሳሙኤል የእስራኤልን ንጉሣዊ አገዛዝ በመመሥረት ረገድ ትልቅ ሚና የሚጫወት የይሖዋ ነቢይ ሊሆን ነው።

ሐና ለሳሙኤል ስለ ይሖዋ ማስተማር የጀመረችው በልጅነቱ እንደነበር ጥርጥር የለውም። ይሁንና ስዕለቷን ረስታ ነበር? በጭራሽ! “ሕፃኑ ጡት ከተወ በኋላ፣ ወስጄ በእግዚአብሔር ፊት አቀርበዋለሁ፤ እስከ ሕይወቱ ፍጻሜም በዚያ ይኖራል” ስትል ተናገረች። ሳሙኤል ምናልባትም በሦስት ዓመቱ ወይም ከዚያ ትንሽ ከፍ ብሎ ጡት ሲጥል ሐና በተሳለችው መሠረት ወደ ይሖዋ መቅደስ ወሰደችው።—1 ሳሙኤል 1:21-24፤ 2 ዜና መዋዕል 31:16

ሐናና ባሏ ለይሖዋ መሥዋዕት ካቀረቡ በኋላ ሳሙኤልን ወደ ዔሊ ወሰዱት። ሐና የትንሹ ልጇን እጅ ይዛ ሳይሆን አይቀርም ዔሊን እንዲህ አለችው:- “ጌታዬ ሆይ፤ በነፍስህ እምላለሁ፤ እዚህ ቦታ ላይ በአጠገብህ ቆማ ወደ እግዚአብሔር ስትጸልይ የነበረች ያች ሴት እኔ ነኝ። ይህን ልጅ እንዲሰጠኝ ጸለይሁ፤ እግዚአብሔርም የለመንሁትን ሰጠኝ። ስለዚህ እኔም ለእግዚአብሔር እሰጠዋለሁ፤ በሕይወት ዘመኑም ሁሉ ለእግዚአብሔር የተሰጠ ይሆናል።” ሳሙኤል ለአምላክ የሚያቀርበውን ልዩ አገልግሎት የጀመረው በዚህ መንገድ ነበር።—1 ሳሙኤል 1:25-28፤ 2:11

ከጊዜ በኋላ ሐና ሳሙኤልን እንዳልረሳችው ግልጽ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “እናቱም ከባሏ ጋር ዓመታዊ መሥዋዕት ለማቅረብ በምትሄድበት ጊዜ ሁሉ ትንሽ መደረቢያ እየሠራች ይዛለት ትሄድ ነበር” በማለት ይናገራል። (1 ሳሙኤል 2:19) ሐና ስለ ሳሙኤል መጸለይዋን እንዳላቋረጠች የታወቀ ነው። በየዓመቱ ልትጠይቀው ስትሄድ ለአምላክ በሚያቀርበው አገልግሎት እንዲጸና ታበረታታው እንደነበር እሙን ነው።

እንዲህ ባለው አንድ አጋጣሚ ላይ ዔሊ የሳሙኤልን ወላጆች ከመረቃቸው በኋላ ሕልቃናን “ለእግዚአብሔር በሰጠችው ልጅ ምትክ እግዚአብሔር ከዚህችው ሴት ዘር ይስጥህ” ብሎታል። ከእነዚህ ቃላት ጋር በሚስማማ መንገድ ሐናና ሕልቃና ሦስት ወንድና ሁለት ሴት ልጆችን በማግኘት ተባርከዋል።—1 ሳሙኤል 2:20, 21

ሕልቃናና ሐና ለክርስቲያን ወላጆች እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ትተዋል! በርካታ ወላጆች ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸው ከመኖሪያ አካባቢያቸው ርቀው በመሄድ በአንድ ዓይነት የሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንዲካፈሉ በማበረታታት ልጆቻቸውን ለይሖዋ ለመስጠት ፈቃደኞች ሆነዋል። እንዲህ ዓይነት አፍቃሪ ወላጆች ለከፈሉት መሥዋዕትነት ሊመሰገኑ ይገባል፤ ይሖዋም ይክሳቸዋል።

የሐና የምስጋና ጸሎት

በአንድ ወቅት መካን የነበረችው ሐና ከጊዜ በኋላ ምንኛ ተደስታለች! በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ ሴቶች የጸለዩአቸው ጸሎቶች እምብዛም አይገኙም። ሐና ካቀረበቻቸው ጸሎቶች መካከል ግን ሁለቱ ተመዝግበዋል። የመጀመሪያው በተጨነቀች ጊዜ የጸለየችው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከደስታዋ የተነሳ ያቀረበችው የምስጋና ጸሎት ነው። ሐና ይህን ጸሎት የጀመረችው “ልቤ በእግዚአብሔር ጸና” በማለት ነበር። ‘መካኒቱ ስለወለደች’ በመደሰቷ “እርሱ ድኻውን ከትቢያ ያነሣል” በማለት ይሖዋን አወድሳለች። በእርግጥም ይሖዋ “ምስኪኑንም ከጕድፍ ከፍ ከፍ ያደርጋል።”—1 ሳሙኤል 2:1-10

ሐናን አስመልክቶ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው ይህ ዘገባ ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎች በሚፈጽሙት የክፋት ድርጊት ልንጎዳ እንደምንችል ያሳያል። ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነቶቹ ፈተናዎች ይሖዋን በማገልገል የምናገኘውን ደስታ እንዲያሳጡን መፍቀድ አይኖርብንም። ይሖዋ ጸሎት የሚሰማ ታላቅ አምላክ ነው። ታማኝ ሕዝቦቹን ከመከራ በመታደግ እንዲሁም ብዙ ሰላም በመስጠትና በሌሎች መንገዶች በመባረክ ለጩኸታቸው ምላሽ ይሰጣል።—መዝሙር 22:23-26፤ 34:6-8፤ 65:2

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a መጽሐፍ ቅዱስ ይህን የእውነተኛ አምልኮ ማዕከል የይሖዋ “ቤተ መቅደስ” በማለት ይጠራዋል። ይሁን እንጂ በዚህ ዘመን የቃል ኪዳኑ ታቦት ያረፈው በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ነበር። ለይሖዋ የመጀመሪያው ቋሚ ቤተ መቅደስ የተገነባው በንጉሥ ሰሎሞን የግዛት ዘመን ነው።—1 ሳሙኤል 1:9፤ 2 ሳሙኤል 7:2, 6፤ 1 ነገሥት 7:51፤ 8:3, 4

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሐና ሳሙኤልን ለይሖዋ ሰጥታለች