በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መላእክት—በሰው ልጆች ሕይወት ውስጥ የሚጫወቱት ሚና

መላእክት—በሰው ልጆች ሕይወት ውስጥ የሚጫወቱት ሚና

መላእክት—በሰው ልጆች ሕይወት ውስጥ የሚጫወቱት ሚና

“ከዚህ በኋላ ታላቅ ሥልጣን ያለው ሌላ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ፤ . . . እርሱም በብርቱ ድምፅ እንዲህ ብሎ ጮኸ፤ ‘ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች! ወደቀች!’” —ራእይ 18:1, 2

1, 2. ይሖዋ ፈቃዱን ለማስፈጸም መላእክትን እንደሚጠቀም የሚያሳየው ምንድን ነው?

 አረጋዊው ሐዋርያው ዮሐንስ በፍጥሞ ደሴት በእስር ላይ ሳለ ትንቢታዊ ራእዮችን አይቷል። “በመንፈስ” ተመስጦ “በጌታ ቀን” የሚከናወኑትን አስደናቂ ክስተቶች ተመልክቷል። የጌታ ቀን የጀመረው ኢየሱስ ክርስቶስ በ1914 በነገሠበት ጊዜ ሲሆን እስከ ሺህ ዓመት ግዛቱ መጨረሻ ድረስ ይዘልቃል።—ራእይ 1:10

2 ይሖዋ አምላክ ይህን ራእይ ለዮሐንስ የሰጠው በቀጥታ ሳይሆን በተዋረድ ነበር። ራእይ 1:1 እንዲህ ይላል:- “ቶሎ መሆን የሚገባውን ነገር ለአገልጋዮቹ እንዲያሳይ፣ እግዚአብሔር ለእርሱ የሰጠው የኢየሱስ ክርስቶስ ራእይ ይህ ነው፤ ኢየሱስም መልአኩን ልኮ ለአገልጋዩ ለዮሐንስ ገለጠለት።” ይሖዋ በኢየሱስ፣ ኢየሱስ ደግሞ በአንድ መልአክ ተጠቅሞ “በጌታ ቀን” የሚከናወኑትን አስደናቂ ነገሮች ለዮሐንስ አሳውቆታል። በአንድ ወቅት ላይ ዮሐንስ “ታላቅ ሥልጣን ያለው ሌላ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ” ተመልክቷል። የዚህ መልአክ ተልእኮ ምን ነበር? መልአኩ ‘“ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች! ወደቀች!” በማለት በብርቱ ድምጽ ጮኸ።’ (ራእይ 18:1, 2) ይህ ኃያል መልአክ የሐሰት ሃይማኖት ግዛት የሆነችው ታላቂቱ ባቢሎን መውደቋን የማወጅ መብት አግኝቷል። በመሆኑም ይሖዋ ፈቃዱን ለማስፈጸም መላእክትን እንደሚጠቀም እርግጠኛ መሆን እንችላለን። መላእክት በአምላክ ዓላማ ውስጥ ምን ድርሻ እንዳላቸውና በእኛ ሕይወት ውስጥ ምን ሚና እንደሚጫወቱ በጥልቀት ከመመርመራችን በፊት እነዚህ መንፈሳዊ ፍጥረታት እንዴት ወደ ሕልውና እንደመጡ እስቲ እንመልከት።

መላእክት ወደ ሕልውና የመጡት እንዴት ነው?

3. ብዙ ሰዎች ስለ መላእክት ምን የተሳሳተ አመለካከት አላቸው?

3 በዛሬው ጊዜ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መላእክት መኖራቸውን ያምናሉ። ይሁንና ብዙዎች ስለ መላእክትም ሆነ ወደ ሕልውና ስለመጡበት መንገድ የተሳሳተ አመለካከት አላቸው። ለምሳሌ ያህል አንዳንድ ሃይማኖተኛ ሰዎች የሚወዱት ሰው ሲሞት አምላክ ከእርሱ ጋር እንዲሆን እንደጠራውና በዚያም መልአክ እንደሚሆን ያስባሉ። የአምላክ ቃል መላእክት ስለተፈጠሩበትና ወደ ሕልውና ስለመጡበት መንገድ እንዲሁም ስለሚያከናውኑት ተግባር የሚያስተምረው ይህንን ነው?

4. ቅዱሳን መጻሕፍት መላእክት ወደ ሕልውና ስለመጡበት መንገድ ምን ይላሉ?

4 ከመላእክት ሁሉ በኃይልና በሥልጣን የላቀው መልአክ፣ የመላእክት አለቃ ሚካኤል ተብሎ ይጠራል። (ይሁዳ 9) ይህ መልአክ ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ማንም ሊሆን አይችልም። (1 ተሰሎንቄ 4:16) ሕልቆ መሳፍርት ከሌላቸው ዘመናት በፊት ይሖዋ ለመፍጠር በወሰነ ጊዜ በመጀመሪያ የፈጠረው ልጁ የሆነውን ይህን መልአክ ነው። (ራእይ 3:14 የ1954 ትርጉም) በኋላም ይሖዋ በዚህ የበኩር ልጁ አማካኝነት ሁሉንም መንፈሳዊ ፍጥረታት ፈጥሯል። (ቈላስይስ 1:15-17) ይሖዋ እነዚህን መንፈሳዊ ፍጥረታት ማለትም መላእክትን እንደ ልጆቹ አድርጎ በመናገር የእምነት አባት ለሆነው ለኢዮብ እንዲህ ሲል ጠይቆታል:- “ምድርን በመሠረትሁ ጊዜ አንተ የት ነበርህ? በእርግጥ የምታስተውል ከሆንህ፣ ንገረኝ። . . . የማእዘን ድንጋይዋንስ ማን አቆመ? ይህም የሆነው የንጋት ከዋክብት በዘመሩበት ጊዜ፣ መላእክትም [“የእግዚአብሔር ልጆች፣” የግርጌ ማስታወሻ] እልል ባሉበት ጊዜ ነበር።” (ኢዮብ 38:4, 6, 7) በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው መላእክትን የፈጠራቸው አምላክ ሲሆን ወደ ሕልውና የመጡትም የሰው ልጆች ከመፈጠራቸው ከብዙ ዘመናት አስቀድሞ ነው።

5. መላእክት የተደራጁት እንዴት ነው?

5 አንደኛ ቆሮንቶስ 14:33 “እግዚአብሔር የሰላም አምላክ እንጂ የሁከት አምላክ አይደለም” ይላል። ከዚህ ጋር በሚስማማ መልኩ ይሖዋ መንፈሳዊ ልጆቹን በሦስት ዋና ዋና ክፍሎች አደራጅቷቸዋል። እነዚህም የሚከተሉት ናቸው:- (1) ሱራፌል፣ በአምላክ ዙፋን አካባቢ ተገኝተው ቅድስናውን ያውጃሉ እንዲሁም ሕዝቡ መንፈሳዊ ንጽሕናቸውን እንዲጠብቁ ያግዛሉ። (2) ኪሩቤል፣ የይሖዋን ሉዓላዊነት ያስከብራሉ። (3) ሌሎች መላእክት ደግሞ የይሖዋን ፈቃድ ያስፈጽማሉ። (መዝሙር 103:20፤ ኢሳይያስ 6:1-3፤ ሕዝቅኤል 10:3-5፤ ዳንኤል 7:10) እነዚህ መንፈሳዊ ፍጥረታት በሰው ልጆች ሕይወት ውስጥ ከሚጫወቱት ሚና መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?—ራእይ 5:11

መላእክት ምን ሚና ይጫወታሉ?

6. ይሖዋ ከኤደን የአትክልት ስፍራ ጋር በተያያዘ ኪሩቤልን የተጠቀመው እንዴት ነው?

6 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መንፈሳዊ ፍጥረታት ለመጀመሪያ ጊዜ በቀጥታ የተጠቀሱት በዘፍጥረት 3:24 ላይ ነው። ጥቅሱ እንዲህ ይላል:- “[ይሖዋ] ሰውንም ካስወጣው በኋላ፣ ወደ ሕይወት ዛፍ የሚወስደውን መንገድ ለመጠበቅ ኪሩቤልንና በየአቅጣጫው የምትገለባበጥ ነበልባላዊ ሠይፍ ከዔድን በስተ ምሥራቅ አኖረ።” እነዚህ ኪሩቦች አዳምና ሔዋን መኖሪያቸው ወደነበረችው ገነት ተመልሰው እንዳይገቡ አግደዋቸዋል። ይህ የሆነው በሰው ልጅ ታሪክ መጀመሪያ ላይ ነው። ከዚያን ጊዜ አንስቶ መላእክት ምን ሲያከናውኑ ቆይተዋል?

7. “መልአክ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጡም ሆነ የግሪኩ ቃል ፍቺ፣ መላእክት የሚያከናውኑትን የትኛውን ተግባር ይጠቁማል?

7 መላእክት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ወደ 400 ጊዜ ያህል ተጠቅሰዋል። “መልአክ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጡም ሆነ የግሪክኛው ቃል “መልእክተኛ” የሚል ፍቺ ሊሰጠው ይችላል። በመሆኑም መላእክት በአምላክና በሰው መካከል መልእክተኞች ሆነው አገልግለዋል። በዚህ ርዕስ የመጀመሪያዎቹ ሁለት አንቀጾች ላይ እንደተገለጸው ይሖዋ ለሐዋርያው ዮሐንስ መልእክት ለማድረስ በአንድ መልአክ ተጠቅሟል።

8, 9. (ሀ) አንድ መልአክ ማኑሄንና ሚስቱን ያበረታታቸው እንዴት ነው? (ለ) ማኑሄ ከአምላክ መልአክ ጋር ካደረገው ውይይት ወላጆች ምን መማር ይችላሉ?

8 በተጨማሪም መላእክት በምድር ላይ ለሚኖሩት የአምላክ አገልጋዮች ድጋፍና ማበረታቻ በመስጠት ያገለግላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ መሳፍንት እስራኤልን ያስተዳድሩ በነበረበት ጊዜ ማኑሄና መካን የሆነችው ሚስቱ ልጅ የማግኘት ጉጉት ነበራቸው። በመሆኑም ይሖዋ መልአኩን ልኮ ለማኑሄ ሚስት ወንድ ልጅ እንደምትወልድ ነገራት። ዘገባው እንዲህ ይላል:- “ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ። በራሱ ላይ ምላጭ አይድረስበት፤ ልጁ ከእናቱ ማሕፀን ጀምሮ ናዝራዊ በመሆን ለእግዚአብሔር የተለየ ይሆናልና፤ እስራኤልንም ከፍልስጥኤማውያን እጅ መታደግ ይጀምራል።”—መሳፍንት 13:1-5

9 ከጊዜ በኋላ የማኑሄ ሚስት በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ ታዋቂ የሆነውን ሳምሶንን ወለደች። (መሳፍንት 13:24) ልጁ ከመወለዱ በፊት ማኑሄ፣ ሕፃኑን እንዴት ማሳደግ እንደሚገባቸው ለማወቅ መልአኩ ተመልሶ እንዲመጣ ጠይቆ ነበር። ማኑሄ “የልጁ ሕይወት የሚመራው እንዴት ነው?” ሲል ጠየቀ። የይሖዋ መልአክ ለማኑሄ ሚስት የሰጣትን መመሪያ ለእርሱም በድጋሚ ነገረው። (መሳፍንት 13:6-14) ማኑሄ ምን ያህል እንደተበረታታ መገመት አያዳግትም! በዛሬው ጊዜ መላእክት ሰዎችን አያነጋግሩም። ይሁንና ወላጆች ልክ እንደ ማኑሄ ልጆቻቸውን ለማሠልጠን የሚያስችላቸውን መመሪያ ለማግኘት ይሖዋን መጠየቅ ይችላሉ።—ኤፌሶን 6:4

10, 11. (ሀ) ኤልሳዕና አገልጋዩ የሶርያ ሠራዊት እንደከበባቸው ሲመለከቱ ምን ተሰማቸው? (ለ) በዚህ ታሪክ ላይ ማሰላሰላችን እንዴት ይጠቅመናል?

10 በነቢዩ ኤልሳዕ ዘመን የመላእክት እርዳታ የታየበት አስደናቂ ክንውን አለ። ኤልሳዕ ዶታይን በተባለች የእስራኤል ከተማ ይኖር ነበር። አንድ ቀን የኤልሳዕ አገልጋይ ማለዳ ተነስቶ ወደ ውጭ ሲመለከት ከተማዋ በፈረሶችና በጦር ሰረገሎች ተከብባ አየ። የሶርያ ንጉሥ ኤልሳዕን ለመያዝ ታላቅ የጦር ሠራዊት ልኮ ነበር። የኤልሳዕ አገልጋይ ምን ተሰማው? በፍርሃት ተውጦ ምናልባትም በጣም እየተርበተበተ “ጌታዬ ሆይ፤ ምን ማድረግ ይሻለናል?” ሲል ጮኸ። ለእርሱ ሁሉም ነገር ተስፋ አስቆራጭ ይመስል ነበር። ሆኖም ኤልሳዕ “ከእኛ ጋር ያሉት ከእነርሱ ጋር ካሉት ይበልጣሉና አትፍራ” በማለት መለሰለት። እንዲህ ሲል ምን ማለቱ ነበር?—2 ነገሥት 6:11-16

11 ኤልሳዕ የመላእክት ሠራዊት እርሱን ለመርዳት በዚያ እንደነበሩ ተገንዝቦ ነበር። አገልጋዩ ግን አንዳች ነገር አላየም። ስለዚህ ኤልሳዕ “‘እግዚአብሔር ሆይ፤ ያይ ዘንድ እባክህ ዐይኖቹን ክፈትለት’ ብሎ ጸለየ፤ እግዚአብሔርም የአገልጋዩን ዐይኖች ከፈተለት፤ ሲመለከትም፤ የእሳት ፈረሶችና ሠረገሎች በኤልሳዕ ዙሪያ ተራራውን ሞልተውት አየ።” (2 ነገሥት 6:17) አገልጋዩ የመላእክቱን ሠራዊት ማየት የቻለው በዚህ ጊዜ ነበር። እኛም መላእክት በይሖዋና በክርስቶስ አመራር ሥር ሆነው ለይሖዋ ሕዝቦች እርዳታና ጥበቃ እንደሚያደርጉ በመንፈሳዊ የማስተዋል ዓይናችን መመልከት እንችላለን።

መላእክት በክርስቶስ ዘመን የሰጡት እርዳታ

12. ማርያም ከመልአኩ ገብርኤል ምን እርዳታ አግኝታለች?

12 አይሁዳዊቷ ድንግል ማርያም “እነሆ፤ ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ” የሚለውን ምሥራች በሰማች ጊዜ የመላእክት እርዳታ ያገኘችው እንዴት እንደሆነ ተመልከት። ከአምላክ የተላከው መልአኩ ገብርኤል ይህን አስደናቂ መልእክት ከመናገሩ በፊት “ማርያም ሆይ፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስ አግኝተሻልና አትፍሪ” ብሏት ነበር። (ሉቃስ 1:26, 27, 30, 31) ማርያም የአምላክን ሞገስ እንዳገኘች በሚያረጋግጡላት በእነዚህ ቃላት ተበረታታ መሆን አለበት!

13. መላእክት ኢየሱስን የረዱት እንዴት ነው?

13 በተጨማሪም ኢየሱስ በምድረ በዳ ሦስት ጊዜ በሰይጣን ከተፈተነ በኋላ የመላእክት እርዳታ ታይቶ ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ፈተናው ካበቃ በኋላ “ዲያብሎስ ትቶት ሄደ፤ መላእክትም መጥተው [ኢየሱስን] አገለገሉት” ይላል። (ማቴዎስ 4:1-11) ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ላይም ተመሳሳይ ሁኔታ ተፈጽሟል። ኢየሱስ በጭንቀት ተውጦ ተንበርክኮ “አባት ሆይ፤ ፈቃድህ ከሆነ፣ ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ፤ ነገር ግን የእኔ ፈቃድ ሳይሆን የአንተ ፈቃድ ይፈጸም” በማለት እየጸለየ ሳለ ‘መልአክ ከሰማይ ተገልጦ አበረታታው።’ (ሉቃስ 22:42, 43) በዛሬው ጊዜ መላእክት እኛን የሚረዱን በምን መንገድ ነው?

መላእክት በዘመናችን የሚሰጡት እርዳታ

14. የይሖዋ ምሥክሮች በዘመናችን እንዴት ያሉ ፈተናዎችን መቋቋም አስፈልጓቸዋል? ምንስ ውጤት አግኝተዋል?

14 የይሖዋ ምሥክሮች በዘመናችን እያከናወኑ ያሉትን የስብከት ሥራ ስንመረምር የመላእክት እርዳታ እንዳለበት የሚያሳይ ማስረጃ እናገኛለን። ለምሳሌ ያህል የይሖዋ ሕዝቦች በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅትም ሆነ ከዚያ በፊት (1939-1945) በጀርመንና በምዕራብ አውሮፓ የናዚ አገዛዝ ያደረሰባቸውን አሰቃቂ ጥቃት መቋቋም ችለዋል። በካቶሊክ ፋሺስት አገዛዝ ይተዳደሩ በነበሩት በጣሊያን፣ በስፔንና በፖርቹጋል የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮችም ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ስደት መቋቋም አስፈልጓቸዋል። በቀድሞዋ ሶቪየት ሕብረትና በዚህች አገር ተጽዕኖ ሥር በነበሩ አገሮች የሚገኙ ወንድሞች ለአሥርተ ዓመታት የደረሰባቸውን ስደት ተቋቁመው ጸንተዋል። በአንዳንድ የአፍሪካ አገሮች የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች የደረሰባቸው መከራም ሳይጠቀስ አይታለፍም። a በቅርብ ጊዜ ውስጥ ደግሞ በጆርጂያ የሚኖሩ የይሖዋ አገልጋዮች ጭካኔ የተሞላበት ስደት ደርሶባቸዋል። ሰይጣን የይሖዋ ምሥክሮችን እንቅስቃሴ ለመግታት የተቻለውን ሁሉ አድርጓል። ይሁን እንጂ በቡድን ደረጃ ሲታይ ይህን ዓይነቱን ተቃውሞ ተቋቁመው ለማለፍና እድገት ለማድረግ በቅተዋል። ለዚህ ደግሞ የመላእክት ጥበቃ ማግኘታቸው በከፊል አስተዋጽኦ አድርጓል።—መዝሙር 34:7፤ ዳንኤል 3:28፤ 6:22

15, 16. የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ዙሪያ በሚያከናውኑት አገልግሎት ከመላእክት ምን እርዳታ አግኝተዋል?

15 የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክን መንግሥት ምሥራች በዓለም ዙሪያ እንዲሰብኩና የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በማስተማር ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉ የተሰጣቸውን ተልእኮ በቁም ነገር ይመለከቱታል። (ማቴዎስ 28:19, 20) ይሁን እንጂ ይህን ተልእኳቸውን ያለ መላእክት እርዳታ ከግብ ማድረስ እንደማይችሉ ጠንቅቀው ያውቃሉ። ስለሆነም በራእይ 14:6, 7 ላይ የተጠቀሰው ሐሳብ ምንጊዜም የብርታት ምንጭ ይሆናቸዋል። ሐዋርያው ዮሐንስ እንዲህ ብሏል:- “ሌላ መልአክ በሰማይ መካከል ሲበር አየሁ፤ እርሱም በምድር ላይ ለሚኖሩ ለሕዝብ፣ ለነገድ፣ ለቋንቋና ለወገን ሁሉ የሚሰብከውን የዘላለም ወንጌል ይዞ ነበር፤ በታላቅ ድምፅም፣ ‘እግዚአብሔርን ፍሩ፤ ክብርም ስጡት፤ ምክንያቱም የፍርዱ ሰዓት ደርሶአል፤ ሰማይንና ምድርን፣ ባሕርንና የውሃ ምንጮችን ለፈጠረው ስገዱ’ አለ።”

16 እነዚህ ቃላት የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም አቀፍ ደረጃ እያከናወኑ ያሉት የወንጌላዊነት ሥራ የመላእክት እርዳታና አመራር እንዳለበት በግልጽ ያሳያሉ። ይሖዋ ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች ወደ ምሥክሮቹ ለመምራት በመላእክቱ ይጠቀማል። በተጨማሪም መላእክት የይሖዋ ምሥክሮችን ምሥራቹ ወደሚገባቸው ሰዎች ይመሯቸዋል። ይህን የመሰሉት ሁኔታዎች አንድ ሰው በሆነ አስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ መንፈሳዊ እርዳታ ባስፈለገው ወቅት ብዙውን ጊዜ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር የሚገናኘው ለምን እንደሆነ እንድናስተውል ይረዱናል። እንዲህ ያሉት ሁኔታዎች በጣም መደጋገማቸው የአጋጣሚ ጉዳይ እንዳልሆነ እንድንገነዘብ ያደርጉናል።

መላእክት በቅርቡ የሚያከናውኑት አስደናቂ ተግባር

17. አንድ መልአክ ብቻውን በአሦራውያን ላይ ምን ጥፋት አድርሷል?

17 መላእክት መልእክተኞችና ለይሖዋ አምላኪዎች የብርታት ምንጭ ከመሆን በተጨማሪ ሌሎች አገልግሎቶችን ያከናውናሉ። ባለፉት ዘመናት መለኮታዊ ፍርድ አስፈጽመዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በስምንተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት የአሦራውያን ሠራዊት ኢየሩሳሌምን ስጋት ላይ ጥሏት ነበር። ይሖዋ ምን አደረገ? “ስለ ራሴና ስለ ባሪያዬም ስለ ዳዊት ስል፣ ይህችን ከተማ አድናት ዘንድ እጋርዳታለሁ” ሲል ተናገረ። የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ቀጥሎ የሆነውን እንደሚከተለው ሲል ይነግረናል:- “በዚያችም ሌሊት የእግዚአብሔር መልአክ ወጥቶ ከአሦራውያን ሰፈር መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ ሰው ገደለ። በማግስቱም ሰዎቹ ሲነቁ ቦታው ሬሳ በሬሳ ሆኖ ተገኘ።” (2 ነገሥት 19:34, 35) የሰው ሠራዊት ከአንድ መልአክ ጋር ብቻ እንኳ ሲወዳደር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም!

18, 19. በቅርቡ መላእክት ምን አስደናቂ ተግባር ያከናውናሉ? ይህስ በሰዎች ላይ ምን ተጽዕኖ ይኖረዋል?

18 በቅርቡ መላእክት የአምላክ ፍርድ አስፈጻሚ ኃይል በመሆን ያገለግላሉ። ኢየሱስ “በሚንበለበል እሳት ከኀያላን መላእክት ጋር” በቅርቡ ይመጣል። የሚመጡበት ዓላማም “እግዚአብሔርን የማያውቁትንና ለጌታችንም ለኢየሱስ ወንጌል የማይታዘዙትን” ለመበቀል ነው። (2 ተሰሎንቄ 1:7, 8) ይህ ሁኔታ በሰው ዘር ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ይኖረዋል! አሁን በመላው ዓለም እየተሰበከ ያለውን የአምላክ መንግሥት ምሥራች ለመቀበል አሻፈረን ያሉ ሰዎች ይጠፋሉ። ይሖዋን፣ ጽድቅንና ትሕትናን የሚፈልጉ ብቻ ‘በእግዚአብሔር የቍጣ ቀን ይሰወራሉ’ እንዲሁም አንዳች ጉዳት አይደርስባቸውም።—ሶፎንያስ 2:3

19 ይሖዋ በምድር ያሉትን ሕዝቦቹን ለመርዳትና ለማበረታታት ኃያል የሆኑትን መላእክቱን የሚጠቀም በመሆኑ አመስጋኞች ልንሆን ይገባል። በይሖዋ ላይ በማመጽ የሰይጣን ተከታይ የሆኑ መላእክት በመኖራቸው፣ መላእክት በአምላክ ዓላማ ውስጥ የሚጫወቱትን ሚና መረዳታችን ያጽናናናል። የሚቀጥለው ርዕስ እውነተኛ ክርስቲያኖች ራሳቸውን ከሰይጣንና ከአጋንንቱ ኃይለኛ ተጽዕኖ ለመጠበቅ ምን ማድረግ እንደሚችሉ ያብራራል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ስለተነሳው የስደት ማዕበል ዝርዝር ዘገባ ለማግኘት የሚከተሉትን የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ ተመልከት:- 1983 (አንጎላ)፣ 1972 (ቼኮዝሎቫኪያ)፣ 2000 (ቼክ ሪፑብሊክ)፣ 1992 (ኢትዮጵያ)፣ 1974 እና 1999 (ጀርመን)፣ 1982 (ጣሊያን)፣ 1999 (ማላዊ)፣ 2004 (ሞልዶቫ)፣ 1996 (ሞዛምቢክ)፣ 1994 (ፖላንድ)፣ 1983 (ፖርቹጋል)፣ 1978 (ስፔን)፣ 2002 (ዩክሬን)፣ እንዲሁም 2006 (ዛምቢያ)።

ምን ትምህርት አግኝተሃል?

• መላእክት ወደ ሕልውና የመጡት እንዴት ነው?

• መላእክት በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ምን ሚና ተጫውተዋል?

ራእይ 14:6, 7 በዘመናችን መላእክት ምን እንደሚሠሩ ይጠቁማል?

• በቅርቡ መላእክት ምን አስደናቂ ተግባር ያከናውናሉ?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድ መልአክ ማኑሄንና ሚስቱን አበረታቷቸዋል

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ከእኛ ጋር ያሉት ከእነርሱ ጋር ካሉት ይበልጣሉ”