በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አጋንንትን እንዴት መቋቋም እንችላለን?

አጋንንትን እንዴት መቋቋም እንችላለን?

አጋንንትን እንዴት መቋቋም እንችላለን?

“የሥልጣን ስፍራቸውን ያልጠበቁትን ነገር ግን መኖሪያቸውን የተዉትን መላእክት [አምላክ] በዘላለም እስራት እስከ ታላቁ ቀን ፍርድ ድረስ በጨለማ ጠብቆአቸዋል።”—ይሁዳ 6

1, 2. ሰይጣን ዲያብሎስንና አጋንንቱን በተመለከተ ምን ጥያቄዎች ይነሳሉ?

 ሐዋርያው ጴጥሮስ “ራሳችሁን የምትገዙ ሁኑ፤ ንቁም፤ ጠላታችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን በመፈለግ እንደሚያገሣ አንበሳ ወዲያ ወዲህ ይዞራል” በማለት አስጠንቅቋል። (1 ጴጥሮስ 5:8) ሐዋርያው ጳውሎስ ደግሞ አጋንንትን አስመልክቶ እንዲህ ብሏል:- “ከአጋንንት ጋር እንድትተባበሩም አልሻም። የጌታን ጽዋና፣ የአጋንንትን ጽዋ በአንድ ላይ መጠጣት አትችሉም፤ ከጌታ ማዕድና ከአጋንንት ማዕድ ተካፋይ መሆን አትችሉም።”—1 ቆሮንቶስ 10:20, 21

2 ይሁንና ሰይጣንና አጋንንቱ እነማን ናቸው? ወደ ሕልውና የመጡት እንዴትና መቼ ነው? የፈጠራቸው አምላክ ነው? በሰዎች ላይ የሚያሳድሩት ተጽዕኖስ ምን ያህል ከባድ ነው? የሚሰነዝሩብንን ጥቃት መመከት የምንችልበት መከላከያ ይኖር ይሆን?

ሰይጣንና አጋንንቱ ወደ ሕልውና የመጡት እንዴት ነው?

3. አንድ የአምላክ መልአክ ሰይጣን ዲያብሎስ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው?

3 በሰው ዘር ታሪክ መጀመሪያ ላይ ማለትም ሰዎች በኤደን የአትክልት ስፍራ መኖር በጀመሩበት ጊዜ አንድ የአምላክ መልአክ ዓመጸኛ ሆነ። ለምን? ምክንያቱም በይሖዋ ሰማያዊ ድርጅት ውስጥ የተሰጠው ቦታ አላረካውም። ይህ መልአክ አዳምና ሔዋን ሲፈጠሩ እውነተኛውን አምላክ ሳይሆን እርሱን እንዲያመልኩትና እንዲታዘዙት ለማድረግ የሚያስችል አጋጣሚ እንዳለ ተመለከተ። በዚህ መንገድ በአምላክ ላይ በማመጽና የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት የኃጢአት ጎዳና እንዲከተሉ በማድረግ ራሱን ሰይጣን ዲያብሎስ አደረገ። ከጊዜ በኋላ ሌሎች መላእክት የዓመጹ ተባባሪ ሆኑ። እንዴት?—ዘፍጥረት 3:1-6፤ ሮሜ 5:12፤ ራእይ 12:9

4. ከኖኅ የጥፋት ውኃ በፊት አንዳንድ ዓመጸኛ መላእክት ምን አደረጉ?

4 በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉት ቅዱሳን መጻሕፍት፣ አንዳንድ መላእክት በኖኅ ዘመን ከመጣው ታላቅ የጥፋት ውኃ በፊት በምድር ለሚኖሩ ሴቶች ተገቢ ያልሆነ ስሜት እንዳሳደሩ ይነግሩናል። መጽሐፍ ቅዱስ “[በሰማይ የሚኖሩት] የእግዚአብሔር ልጆች” በተሳሳተ ዓላማ ተነሳስተው “የሰውን ሴቶች ልጆች መልካሞች እንደ ሆኑ አዩ፤ ከመረጡአቸውም ሁሉ ሚስቶችን ለራሳቸው ወሰዱ” በማለት ይናገራል። እንዲህ ያለው ጥምረት ከተፈጥሮ ውጪ ሲሆን ኔፊሊም በመባል የሚታወቁ ዲቃላዎችም ተወለዱ። (ዘፍጥረት 6:2-4 የ1954 ትርጉም) በዚህ መንገድ አምላክን ለመታዘዝ ፈቃደኛ ያልሆኑት እነዚህ መንፈሳዊ ፍጥረታት ከሰይጣን ጋር በማበር በይሖዋ ላይ ዓመጹ።

5. ይሖዋ ታላቁን የጥፋት ውኃ ባመጣ ጊዜ ዓመጸኞቹ መላእክት ምን ሆኑ?

5 ይሖዋ የጥፋት ውኃ በሰው ዘር ላይ ባመጣ ጊዜ ኔፊሊሞቹና ሰብዓዊ እናቶቻቸው ጠፉ። ዓመጸኞቹ መላእክት ደግሞ ሰብዓዊ አካላቸውን በመተው ወደ መንፈሳዊው ዓለም መመለስ ግድ ሆነባቸው። ይሁን እንጂ በአምላክ ዘንድ የነበራቸውን “የሥልጣን ስፍራቸውን” መልሰው ማግኘት አልቻሉም። ከዚህ ይልቅ እንጦርጦስ በሚባል “[መንፈሳዊ] ጨለማ” ውስጥ ተጣሉ።—ይሁዳ 6፤ 2 ጴጥሮስ 2:4 NW

6. አጋንንት ሰዎችን የሚያስቱት እንዴት ነው?

6 ክፉዎቹ መላእክት “የሥልጣን ስፍራቸውን” ካጡ ጀምሮ የሰይጣን አጋንንት በመሆን የእርሱን ክፉ ዓላማ ሲያራምዱ ቆይተዋል። ከዚያን ጊዜ አንስቶ አጋንንት ሰብዓዊ አካል የመልበስ ችሎታቸውን አጥተዋል። ይሁንና ወንዶችንም ሆነ ሴቶችን ከተፈጥሮ ውጭ የሆኑ የጾታ ብልግናዎች እንዲፈጽሙ ማነሳሳት ይችላሉ። ከዚህም በተጨማሪ አጋንንት ሰዎችን በመናፍስታዊ ድርጊቶች አማካኝነት ያስታሉ፤ ይህም እንደ ድግምት፣ አስማትና መናፍስት መጥራት የመሳሰሉትን ድርጊቶች ይጨምራል። (ዘዳግም 18:10-13፤ 2 ዜና መዋዕል 33:6) የእነዚህ ክፉ መላእክት ዕጣ ፈንታ ከዲያብሎስ ጋር ተመሳሳይ ሲሆን ይኸውም የዘላለም ጥፋት ነው። (ማቴዎስ 25:41፤ ራእይ 20:10) እስከዚያው ጊዜ ድረስ ግን በአቋማችን በመጽናት ልንቋቋማቸው ይገባል። በመሆኑም ሰይጣን ምን ያህል ኃይል እንዳለውና እርሱንም ሆነ አጋንንቱን በተሳካ ሁኔታ መቋቋም የምንችለው እንዴት እንደሆነ መመርመራችን ጥበብ ነው።

ሰይጣን ምን ያህል ኃይል አለው?

7. ሰይጣን በዓለም ላይ ምን ያህል ኃይል አለው?

7 በታሪክ ዘመናት ሁሉ ሰይጣን የይሖዋን ስም ሲያጠፋ ኖሯል። (ምሳሌ 27:11 የ1954 ትርጉም) እንዲሁም አብዛኛውን የሰው ዘር በቁጥጥሩ ሥር አድርጓል። አንደኛ ዮሐንስ 5:19 ‘መላው ዓለም በክፉው ሥር እንደ ሆነ’ ይገልጻል። ዲያብሎስ “የዓለምን መንግሥታት ሁሉ” ሥልጣንና ክብር እሰጥሃለሁ በማለት ኢየሱስን ሊፈትነው የቻለው ለዚህ ነው። (ሉቃስ 4:5-7) ሐዋርያው ጳውሎስ ሰይጣንን አስመልክቶ እንዲህ ብሏል:- “ወንጌላችን የተከደነ ቢሆን እንኳ፣ የተከደነው ለሚጠፉት ነው። የእግዚአብሔር አምሳል የሆነውን የክርስቶስ፣ የክብሩን ወንጌል ብርሃን እንዳያዩ፣ የዚህ ዓለም አምላክ የማያምኑትን ሰዎች ልቡና አሳውሮአል።” (2 ቆሮንቶስ 4:3, 4) ሰይጣን “ሐሰተኛ፣ የሐሰትም አባት” ሆኖ ሳለ ራሱን “የብርሃን መልአክ” አስመስሎ ያቀርባል። (ዮሐንስ 8:44፤ 2 ቆሮንቶስ 11:14) የዓለምን ገዥዎችና የተገዥዎቻቸውን አእምሮ ለማሳወር የሚያስችል ኃይልም ሆነ ስልት አለው። የሐሰት ወሬ በመንዛት እንዲሁም ሃይማኖታዊ አፈ ታሪክና ውሸት በማስፋፋት የሰውን ዘር ያስታል።

8. መጽሐፍ ቅዱስ የሰይጣንን ተጽዕኖ በተመለከተ ምን ይጠቁማል?

8 በነቢዩ ዳንኤል ዘመን ሰይጣን ያለው ኃይልና የሚያሳድረው ተጽዕኖ በግልጽ ታይቷል። ይሖዋ ዳንኤልን እንዲያበረታታ የላከውን አንድ መልአክ “የፋርስ መንግሥት [መንፈሳዊ] አለቃ” ተቋቁሞት ነበር። “ከዋነኞቹ አለቆች አንዱ የሆነው ሚካኤል” መጥቶ እስኪረዳው ድረስ ታማኙ መልአክ ለ21 ቀናት ታግዶ ነበር። በተጨማሪም ይኸው ታሪክ “የግሪክ አለቃ” ስለሆነ ጋኔን ይናገራል። (ዳንኤል 10:12, 13, 20) ከዚህም ባሻገር በራእይ 13:1, 2 ላይ ሰይጣን በአውሬ ለተመሰለው የፖለቲካ ሥርዓት “የራሱን ኀይልና የራሱን ዙፋን እንዲሁም ታላቅ ሥልጣን” እንደሚሰጥ “ዘንዶ” ተደርጎ ተገልጿል።

9. ክርስቲያኖች የሚዋጉት ከእነማን ጋር ነው?

9 ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው ሲል መጻፉ አያስደንቅም:- “ተጋድሎአችን ከሥጋና ከደም ጋር ሳይሆን ከዚህ ከጨለማ ዓለም ገዦች፣ ከሥልጣናትና ከኀይላት እንዲሁም በሰማያዊ ስፍራ ካሉ ከርኩሳን መናፍስት ሰራዊት ጋር ነው።” (ኤፌሶን 6:12) በዛሬው ጊዜም ቢሆን በሰይጣን ዲያብሎስ ቁጥጥር ሥር ያሉት አጋንንታዊ ኃይሎች፣ ሰብዓዊ ገዥዎችና የሰው ልጆች በአጠቃላይ አሰቃቂ የዘር ማጥፋት ዘመቻና ሽብርተኝነት እንዲያካሂዱ እንዲሁም ሰዎችን እንዲገድሉ ተጽዕኖ ያደርጋሉ። እነዚህን ኃይለኛ መንፈሳዊ ፍጥረታት በተሳካ ሁኔታ መቋቋም የምንችለው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመርምር።

የአጋንንትን ጥቃት የምንመክትበት ምን መከላከያ አለን?

10, 11. ሰይጣንንና ክፉዎቹን መላእክት እንዴት መቋቋም እንችላለን?

10 ሰይጣንንና ክፉዎቹን መላእክት በራሳችን አካላዊም ሆነ አእምሯዊ ጥንካሬ ልንቋቋማቸው አንችልም። ጳውሎስ “በጌታና ብርቱ በሆነው ኀይሉ ጠንክሩ” ሲል መክሮናል። ጥበቃ ለማግኘት ፊታችንን ወደ አምላክ ማዞር ይኖርብናል። ጳውሎስ በመቀጠል እንዲህ ብሏል:- “የዲያብሎስን የተንኰል ሥራ መቋቋም ትችሉ ዘንድ፣ የእግዚአብሔርን ሙሉ የጦር ዕቃ ልበሱ። ክፉው ቀን ሲመጣ መቋቋም ትችሉ ዘንድ የእግዚአብሔርን ሙሉ የጦር ዕቃ ልበሱ፤ ሁሉን ከፈጸማችሁ በኋላ ጸንታችሁ መቆም ትችላላችሁና።”—ኤፌሶን 6:10, 11, 13

11 ጳውሎስ ክርስቲያን ባልንጀሮቹን “የእግዚአብሔርን ሙሉ የጦር ዕቃ” እንዲለብሱ ሁለት ጊዜ አሳስቧቸዋል። “ሙሉ” የሚለው ቃል በተከፋፈለ ልብ ወደ አምላክ መቅረብ የአጋንንትን ጥቃት ለመመከት እንደማያስችል ይጠቁማል። ታዲያ በዛሬው ጊዜ ክርስቲያኖች የአጋንንትን ጥቃት ለመቋቋም በአስቸኳይ ሊታጠቋቸው የሚገቡ መንፈሳዊው የጦር ዕቃ ያካተታቸው ትጥቆች ምንድን ናቸው?

ጸንተን ‘መቆም’ የምንችለው እንዴት ነው?

12. ክርስቲያኖች ወገባቸውን በእውነት መታጠቅ የሚችሉት እንዴት ነው?

12 ጳውሎስ “እንግዲህ ወገባችሁን በእውነት ዝናር ታጥቃችሁ፣ የጽድቅንም ጥሩር ለብሳችሁ . . . [ጸንታችሁ] ቁሙ” ብሏል። (ኤፌሶን 6:14, 15) እዚህ ላይ የተጠቀሱት ሁለት የጦር ትጥቆች ዝናር ወይም ቀበቶ እና ጥሩር ናቸው። አንድ ወታደር ወገቡን (ሽንጡን፣ ብሽሽቱንና የታችኛውን የሆዱን ክፍል) ከአደጋ ለመጠበቅና ሰይፉን ሳይቸገር ለመያዝ ቀበቶውን ጠበቅ አድርጎ መታጠቅ ይኖርበታል። እኛም በተመሳሳይ ከአምላክ ቃል ጋር ተስማምተን መኖር እንድንችል የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በሚገባ መታጠቅ ይኖርብናል። መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ የምናነብበት ፕሮግራም አለን? ፕሮግራሙ መላውን የቤተሰብ አባል ያካትታል? የዕለቱን ጥቅስ በቤተሰብ መልክ የመመርመር ልማድ አለን? በተጨማሪም “ታማኝና ልባም ባሪያ” በሚያዘጋጃቸው ጽሑፎች ላይ የሚወጡትን ማብራሪያዎች በየጊዜው እንከታተላለን? (ማቴዎስ 24:45 የ1954 ትርጉም) እንዲህ ካደረግን የጳውሎስን ምክር ለመከተል እየጣርን ነው ማለት ይቻላል። ከዚህ ባሻገር ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያዎች የምናገኝባቸው የቪዲዮ ካሴቶችና ዲቪዲዎች አሉን። እውነትን አጥብቀን መያዛችን ጥበብ ያለበት ውሳኔ እንድናደርግ የሚረዳን ሲሆን የተሳሳተ ጎዳና ከመከተልም ይጠብቀናል።

13. ምሳሌያዊ ልባችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?

13 ጥሩር የአንድን ወታደር ደረት፣ ልብና ሌሎች አስፈላጊ የአካል ክፍሎች ከጉዳት ለመጠበቅ ያገለግላል። አንድ ክርስቲያንም ለአምላክ ጽድቅ ፍቅር በማዳበር እና ከይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶች ጋር ተስማምቶ በመኖር ምሳሌያዊ ልቡን ማለትም ውስጣዊ ማንነቱን ከጉዳት መጠበቅ ይችላል። ምሳሌያዊው ጥሩር በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን የአቋም ደረጃ አቅልለን እንዳንመለከት ይረዳናል። ‘ክፉውን እየጠላንና መልካሙን እየወደድን’ በሄድን መጠን እግራችንን “ከክፉ መንገድ ሁሉ” እንጠብቃለን።—አሞጽ 5:15፤ መዝሙር 119:101

14. ‘በሰላም ወንጌል ዝግጁነት እግሮቻችን ተጫምተዋል’ ሲባል ምን ማለት ነው?

14 ሮማውያን ወታደሮች ግዛቲቱን አቆራርጠው በሚያልፉ አውራ ጎዳናዎች ላይ በእግራቸው ይጓዙ ነበር። ጉዟቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮችን ስለሚሸፍን አብዛኛውን ጊዜ ጠንካራ ጫማ ይጫሙ ነበር። “በሰላም ወንጌል ዝግጁነት እግሮቻችሁ ተጫምተው ቁሙ” የሚለው አባባል ለክርስቲያኖች ምን ትርጉም አለው? (ኤፌሶን 6:15) ለሥራ ዝግጁ መሆናችንን የሚያሳይ ነው። ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለመስበክ ዝግጁ ነን። (ሮሜ 10:13-15) በክርስቲያናዊ አገልግሎት ንቁ ተሳትፎ ማድረጋችን ራሳችንን ከሰይጣን “የተንኰል ሥራ” ለመጠበቅ ያስችለናል።—ኤፌሶን 6:11

15. (ሀ) ትልቅ የእምነት ጋሻ በጣም አስፈላጊ መሆኑን የሚያሳየው ምንድን ነው? (ለ) በእምነታችን ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ የሚችሉ ‘የሚንበለበሉ ፍላጻዎች’ የትኞቹ ናቸው?

15 ጳውሎስ በመቀጠል “ከእነዚህም ሁሉ ጋር፣ የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ልታጠፉ የምትችሉበትን የእምነትን ጋሻ አንሡ” ብሏል። (ኤፌሶን 6:16) የእምነት ጋሻ እንድናነሳ ከተሰጠው ምክር በፊት “ከእነዚህም ሁሉ ጋር” የሚለው ሐረግ መግባቱ ይህ የጦር ትጥቅ በጣም አስፈላጊ መሆኑን ያሳያል። ፈጽሞ እምነት ሊያንሰን አይገባም። እምነታችን ልክ እንደ ትልቅ ጋሻ ከሰይጣን ‘የሚንበለበሉ ፍላጻዎች’ ይጠብቀናል። በዛሬው ጊዜ እነዚህ ፍላጻዎች ምንን ሊወክሉ ይችላሉ? እምነታችንን ለማዳከም የሚጥሩት ጠላቶቻችንና ከሃዲዎች የሚሰነዝሯቸውን እንደ ጦር የሚወጉ ስድቦች፣ ውሸቶችና ከፊል እውነት የያዙ አሳሳች ወሬዎች ሊያመለክቱ ይችላሉ። በተጨማሪም እነዚህ “ፍላጻዎች” የፍቅረ ንዋይ ዝንባሌ እንዲኖረን የሚቀርቡልንን ፈተናዎች ሊያመለክቱ ይችላሉ። ይህ ዓይነቱ ዝንባሌ ያየነውን ዕቃ ሁሉ የመሸመት አባዜ እንዲጠናወተን አልፎ ተርፎም የይታይልኝ መንፈስ ካላቸው ሰዎች ጋር እንድንፎካከር ሊያደርገን ይችላል። የይታይልኝ መንፈስ ያላቸው ሰዎች ቪላ ቤቶችና ዘመናዊ መኪኖች ይኖሯቸው ይሆናል፤ ወይም ደግሞ ውድ በሆኑ ጌጣጌጦች የተንቆጠቆጡና ፋሽን የማያመልጣቸው ሊሆኑ ይችላሉ። ሌሎች ምንም ያድርጉ ምን፣ የሰይጣንን ‘የሚንበለበሉ ፍላጻዎች’ ለመመከት የሚያስችል ጠንካራ እምነት ሊኖረን ይገባል። ጠንካራ እምነት መገንባትና እምነታችን ጥንካሬውን እንደጠበቀ እንዲቆይ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?—1 ጴጥሮስ 3:3-5፤ 1 ዮሐንስ 2:15-17

16. ጠንካራ እምነት መገንባት የምንችለው እንዴት ነው?

16 ቋሚ የሆነ የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በማድረግና ከልብ የመጸለይ ልማድ በማዳበር ወደ አምላክ መቅረብ እንችላለን። ይሖዋ እምነታችንን እንዲያጠነክርልን መለመን እንችላለን፤ ከዚያም ከጸሎታችን ጋር የሚስማማ እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል። ለምሳሌ ያህል፣ ተሳትፎ የማድረግ ግብ ይዘን ለሳምንታዊው የመጠበቂያ ግንብ ጥናት በጥልቀት እንዘጋጃለን? መጽሐፍ ቅዱስንና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን የምናጠና ከሆነ እምነታችን ይጠናከራል።—ዕብራውያን 10:38, 39፤ 11:6

17. ‘የመዳንን ራስ ቊር የምናደርገው’ እንዴት ነው?

17 ጳውሎስ ስለ መንፈሳዊው የጦር ዕቃ የሰጠውን መግለጫ የደመደመው “የመዳንን ራስ ቊር አድርጉ፤ የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ፤ እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው” በሚለው ምክር ነው። (ኤፌሶን 6:17) የራስ ቁር የወታደሩን ራስም ሆነ ውሳኔ ለማድረግ የሚረዳውን አእምሮውን ከጥቃት ይጠብቅለታል። በተመሳሳይም ክርስቲያናዊ ተስፋችን አስተሳሰባችንን ይጠብቅልናል። (1 ተሰሎንቄ 5:8) አእምሯችንን በዓለማዊ ግቦችና በፍቅረ ንዋይ ቅዠት ከመሙላት ይልቅ ልክ እንደ ኢየሱስ አስተሳሰባችን አምላክ በሰጠን ተስፋ ላይ እንዲያተኩር ማድረግ ይኖርብናል።—ዕብራውያን 12:2

18. መጽሐፍ ቅዱስን ዘወትር የማንበብ ልማዳችንን ችላ ማለት የማይኖርብን ለምንድን ነው?

18 የሰይጣንንና የአጋንንቱን ጥቃት ለመመከት የሚያስችለን መጨረሻ ላይ የተጠቀሰው የጦር ትጥቅ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈረው የአምላክ ቃል ወይም መልእክት ነው። ይህም መጽሐፍ ቅዱስ የማንበብ ልማዳችንን ችላ እንዳንል የሚያነሳሳን ተጨማሪ ምክንያት ነው። ስለ አምላክ ቃል ትክክለኛና ጥልቅ የሆነ እውቀት ካለን፣ ከሰይጣን ውሸትና ከአጋንንት ፕሮፓጋንዳ እንዲሁም ከሃዲዎች የሚሰነዝሩብን የጥላቻ ንግግር ሊያደርስብን ከሚችለው ጉዳት እንጠበቃለን።

‘በማንኛውም ሁኔታ ጸልዩ’

19, 20. (ሀ) ሰይጣንና አጋንንቱ ምን ይጠብቃቸዋል? (ለ) በመንፈሳዊ እንድንጠነክር ምን ሊረዳን ይችላል?

19 ሰይጣንና አጋንንቱም ሆኑ ይህ ክፉ ዓለም የሚጠፉበት ጊዜ ቀርቧል። ሰይጣን “ጥቂት ዘመን ብቻ” እንደቀረው ያውቃል። እጅግ ተቆጥቷል እንዲሁም ‘የእግዚአብሔርን ትእዛዛት በሚጠብቁትና የኢየሱስን ምስክር አጥብቀው በያዙት’ ላይ ጦርነት ከፍቷል። (ራእይ 12:12, 17) በመሆኑም ሰይጣንንና አጋንንቱን መቋቋማችን አስፈላጊ ነው።

20 የአምላክን ሙሉ የጦር ዕቃ እንድንለብስ ለተሰጠን ማሳሰቢያ ምንኛ አመስጋኞች ነን! ጳውሎስ ስለ መንፈሳዊ የጦር ዕቃ የሚገልጸውን ሐሳብ የደመደመው በሚከተለው ምክር ነው:- “በሁሉ ዐይነት ጸሎትና ልመና፣ በማንኛውም ሁኔታ በመንፈስ ጸልዩ፤ ይህንም በማሰብ ንቁ፤ ስለ ቅዱሳንም ሁሉ በትጋት ልመና አቅርቡ።” (ኤፌሶን 6:18) ጸሎት በመንፈሳዊ ያጠነክረናል እንዲሁም ንቁ ሆነን እንድንኖር ይረዳናል። የጳውሎስን ምክር ልብ እንበል እንዲሁም በጸሎት እንትጋ። እንዲህ ማድረጋችን ሰይጣንንና አጋንንቱን ለመቋቋም ይረዳናል።

ምን ትምህርት አግኝተሃል?

• ሰይጣንና አጋንንቱ ወደ ሕልውና የመጡት እንዴት ነው?

• ዲያብሎስ ምን ያህል ኃይል አለው?

• የሰይጣንንና የአጋንንቱን ጥቃት የምንመክትበት ምን መከላከያ አለን?

• የአምላክን ሙሉ የጦር ዕቃ መልበስ የምንችለው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“የእግዚአብሔር ልጆችም የሰውን ሴቶች ልጆች መልካሞች እንደ ሆኑ አዩ”

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መንፈሳዊው የጦር ዕቃ የሚያካትታቸውን ስድስት ትጥቆች መጥቀስ ትችላለህ?

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በእነዚህ እንቅስቃሴዎች መሳተፍ የሰይጣንንና የአጋንንቱን ጥቃት ለመመከት የሚረዳን እንዴት ነው?