የአንባቢያን ጥያቄዎች
የአንባቢያን ጥያቄዎች
ኖኅ ከእያንዳንዱ ንጹሕ እንስሳ ወደ መርከቡ ያስገባው ስንት ስንት ነበር? ሰባት ሰባት ወይስ ሰባት ሰባት ጥንድ?
ኖኅ መርከቡን ሠርቶ ከጨረሰ በኋላ ይሖዋ እንዲህ አለው:- “በዚህ ትውልድ መካከል አንተን ጻድቅ ሆነህ አግኝቼሃለሁና ቤተ ሰብህን በሙሉ ይዘህ ወደ መርከቧ ግባ። ከንጹሕ እንስሳት ሁሉ ሰባት ሰባት ተባዕትና እንስት፣ ንጹህ ካልሆኑት እንስሳት ደግሞ ሁለት ሁለት ተባዕትና እንስት [አስገባ]።” (ዘፍጥረት 7:1, 2) አዲሱ መደበኛ ትርጉም (የግርጌ ማስታወሻ)፣ ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል፣ ዘ ኒው ጀሩሳሌም ባይብል እና ታናክ—ዘ ሆሊ ስክሪፕቸርስ የተባሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች የዕብራይስጡን ቃል “ሰባት ጥንድ” ብለው ተርጉመውታል።
መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ በተጻፈበት ቋንቋ እዚህ ጥቅስ ላይ የገባው ቃል በቀጥታ ሲተረጎም “ሰባት ሰባት” የሚል ፍቺ አለው። (ዘፍጥረት 7:2) ይሁንና በዕብራይስጥ ቋንቋ ቁጥሩ በድጋሚ መጻፉ ቁጥሮቹ የግድ መደመር እንዳለባቸው የሚያመለክት አይደለም። ለምሳሌ ያህል 2 ሳሙኤል 21:20 “በእያንዳንዱ እጁና በእያንዳንዱ እግሩ ስድስት ስድስት ጣቶች” ስለነበሩት “አንድ ግዙፍ ሰው” ይናገራል። እዚህ ጥቅስ ላይ “ስድስት” የሚለው ቁጥር በዕብራይስጡም ላይ ተደግሟል። ይህ ማለት ግን ግዙፉ ሰው በእያንዳንዱ እጁና በእያንዳንዱ እግሩ ላይ ስድስት ስድስት ጥንድ ጣቶች ማለትም አሥራ ሁለት አሥራ ሁለት ጣቶች ነበሩት ማለት አይደለም። ቁጥሩ የተደገመው በእያንዳንዱ እጁና እግሩ ላይ ያሉት ጣቶች ብዛት ምን ያህል መሆኑን ለማመልከት ብቻ ነው።
የዕብራይስጥ ቋንቋ የሰዋስው ሕግ ቁጥሮችን መድገምን በተመለከተ ምን ይላል? ዊልያም ሃርፐር ኢንትሮዳክተሪ ሂብሪው ሜተድ ኤንድ ማኑዋል በተባለው መጽሐፋቸው ላይ ዘፍጥረት 7:2, 9ን ሲያብራሩ፣ “ቃላት አብዛኛውን ጊዜ የሚደገሙት በአንድ ቡድን ውስጥ የታቀፉ ነገሮችን እያንዳንዳቸውን በተናጠል ለማመልከት ሲባል ነው” ብለዋል። እንዲህ ያለው ሐሳብ “ቁጥሩን በመድገም ሊገለጽ ይችላል” ሲል ሂብሪው ግራመር የተባለው የጋዛኒውስ መጽሐፍ (እንግሊዝኛ፣ ሁለተኛ ጥራዝ) ገልጿል። ይህ መጽሐፍ “ሁለት” እና “ስድስት” የሚሉት ቁጥሮች ተደግመው የተጻፉባቸውን ዘፍጥረት 7:9, 15ን (የ1954 ትርጉም) እና 2 ሳሙኤል 21:20ን እንደ ምሳሌ ጠቅሷል።
በዘፍጥረት 7:9, 15 (የ1954 ትርጉም) ላይ “ሁለት” የሚለው ቁጥር መደገሙ ሁለት ጥንዶችን በሌላ አባባል አራት መሆንን እንደማያመለክት ሁሉ በዘፍጥረት 7:2 ላይ የሚገኘው “ሰባት ሰባት” የሚለውም ሐረግ ሰባት ጥንዶችን ማለትም 14 መሆንን አያመለክትም። ስለዚህ ከእያንዳንዱ ንጹሕ እንስሳ ወደ መርከቡ የገቡት “ሰባት ሰባት” ሲሆኑ ንጹሕ ካልሆኑት ደግሞ “ሁለት ሁለት” ብቻ ተወስደዋል።
ታዲያ በዘፍጥረት 7:2 ላይ “ሰባት ሰባት” ከሚለው ቀጥሎ “ተባዕትና እንስት” የሚለው አባባል መግባቱ ምን ያመለክታል? ይህ አባባል አንዳንድ ሰዎች ኖኅ ንጹሕ ከሆኑት እንስሳት ሰባት ሰባት ጥንዶችን ወደ መርከቡ እንዲያስገባ ታዟል ወደሚል መደምደሚያ አድርሷቸዋል። ይሁንና ንጹሕ የሆኑት እንስሳት በሕይወት እንዲተርፉ የተደረጉት እንዲራቡ ብቻ ታስቦ አይደለም። ዘፍጥረት 8:20 ኖኅና ቤተሰቡ ከመርከቡ ከወጡ በኋላ የተከናወነውን ሁኔታ ሲገልጽ “ኖኀ ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሠራ፤ መሠዊያው ላይ ንጹሕ ከሆኑት እንስሳት ሁሉ፣ እንዲሁም ንጹሕ ከሆኑት ወፎች የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረበ” ይላል። ኖኅ ከእያንዳንዱ ንጹሕ እንስሳ ሰባተኛ ጨምሮ ማስገባቱ መሥዋዕት የሚያደርገው እንስሳ እንዲያገኝ ያስቻለው ሲሆን የተረፉት ስድስቱ ማለትም ሦስቱ ጥንዶች በምድር ላይ ለመራባት ይቀራሉ።