በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የክርስቶስ መምጣት ምን ያከናውናል?

የክርስቶስ መምጣት ምን ያከናውናል?

የክርስቶስ መምጣት ምን ያከናውናል?

“ሳኦ ፓውሎ በሽብር ታመሰች።” በ2006 ግንቦት ወር የተከሰተውን ሁኔታ ቬጃ መጽሔት የገለጸው እንዲህ በማለት ነበር። የተደራጁ ወንጀለኞች የብራዚልን ትልቅና የበለጸገች ከተማ እንዳልነበረች አደረጓት። “ለአራት ቀናት ያህል በዘለቀው በዚህ ሽብር” 150 የሚያህሉ ሰዎች ሕይወታቸውን ያጡ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ሕግ አስከባሪዎች፣ ወንጀለኞችና ንጹሐን ዜጎች ይገኙበታል።

ዓመጽ በመላው ዓለም ዋና ርዕሰ ዜና ከሆነ ሰንብቷል። ሰብዓዊ መሪዎች ዓመጽን መግታት የቻሉ አይመስልም። ዓለማችን ከጊዜ ወደ ጊዜ ለሕይወት አደገኛ እየሆነች መጥታለች። በሁሉም ቦታዎች የሚሰማው መጥፎ ዜና የተስፋ መቁረጥ ስሜት አሳድሮብህ ይሆናል። ይሁንና ይህ ሁሉ በቅርቡ ይለወጣል።

ኢየሱስ ተከታዮቹ የአምላክ መንግሥት እንዲመጣና የአምላክ ፈቃድ ‘በሰማይ እንደ ሆነች፣ እንዲሁ በምድር እንድትሆን’ እንዲጸልዩ አስተምሯቸዋል። (ማቴዎስ 6:9, 10) ይህ መንግሥት አምላክ በሾመው ንጉሥ ማለትም በኢየሱስ ክርስቶስ የሚመራ መስተዳድር ሲሆን የሰው ልጆችን ችግር ሙሉ በሙሉ ያስወግዳል። ይሁንና የአምላክ መንግሥት በምድር ላይ እነዚህን ለውጦች እንዲያመጣ ከተፈለገ ሰብዓዊው አገዛዝ በክርስቶስ አገዛዝ መተካት ይኖርበታል። የክርስቶስ መምጣት ይህን ያከናውናል።

የሥልጣን ርክክቡ ሰላማዊ ይሆን?

መንግሥታት ሥልጣናቸውን ለክርስቶስ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ያስረክቡ ይሆን? ሐዋርያው ዮሐንስ ለዚህ ጥያቄ መልስ የሚሰጥ ራእይ ተመልክቷል። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “አውሬው [የዓለም የፖለቲካ ሥርዓት]፣ የምድር ነገሥታትና ሰራዊታቸው በፈረሱ ላይ ከተቀመጠውና [ከኢየሱስና] ከሰራዊቱ ጋር ለመዋጋት ተሰብስበው አየሁ።” (ራእይ 19:19) በዚህ ውጊያ ላይ የምድር ነገሥታት ምን ይደርስባቸዋል? መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ የቀባው ንጉሥ ‘በብረት በትር ይቀጠቅጣቸዋል፤ እንደ ሸክላ ዕቃም ያደቃቸዋል’ ሲል ይገልጻል። (መዝሙር 2:9) የፖለቲካው ሥርዓት ሙሉ በሙሉ ይንኮታኮታል። የአምላክ መንግሥት ሰብዓዊ “መንግሥታት[ን] ሁሉ ያደቃል፤ እስከ መጨረሻውም ያጠፋቸዋል፤ ይህ መንግሥት ራሱ ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።”—ዳንኤል 2:44

የአምላክን መንግሥት የሚቃወሙ ሰዎችስ ምን ይሆናሉ? ‘ጌታ ኢየሱስ በሚንበለበል እሳት ከኀያላን መላእክት ጋር ከሰማይ በሚገለጥበት ጊዜ፣ እግዚአብሔርን የማያውቁትንና ለወንጌል የማይታዘዙትን እንደሚበቀል’ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (2 ተሰሎንቄ 1:7, 8) ምሳሌ 2:22 “ክፉዎች ግን ከምድሪቱ ይወገዳሉ፤ ታማኝነት የጐደላቸውም ከእርሷ ይነቀላሉ” ሲል ይገልጻል።

መጽሐፍ ቅዱስ የክርስቶስን መምጣት አስመልክቶ ሲናገር “እነሆ፤ በደመና ይመጣል፤ . . . ዐይን ሁሉ ያየዋል” ይላል። (ራእይ 1:7) ይህ ሲባል ሰዎች ቃል በቃል በዓይናቸው ያዩታል ማለት አይደለም። ኢየሱስ ወደ ሰማይ ካረገበት ጊዜ አንስቶ መንፈሳዊ አካል በመሆን “ሊቀረብ በማይቻል ብርሃን ውስጥ ይኖራል”፤ ስለሆነም “እርሱን ያየ ማንም የለም፤ ሊያየውም የሚችል የለም።”—1 ጢሞቴዎስ 6:16

ይሖዋ በሙሴ ዘመን በነበሩት ግብፃውያን ላይ አሥሩን መቅሰፍት ባወረደበት ጊዜ በአካል መገለጥ እንዳላስፈለገው ሁሉ ኢየሱስም የምድር ነዋሪዎች ‘እንዲያዩት’ ለማድረግ የግድ ሰብዓዊ አካል መልበስ አያስፈልገውም። በሙሴ ዘመን የነበሩት ሰዎች መቅሰፍቱን ያመጣባቸው ይሖዋ ስለመሆኑ አልተጠራጠሩም ነበር፤ ኃይሉን አምነው ለመቀበል ተገደዋል። (ዘፀአት 12:31) በተመሳሳይም ክርስቶስ የአምላክ ፍርድ አስፈጻሚ በመሆን እርምጃ በሚወስድበት ጊዜ ክፉዎች እርሱን ‘ለማየት’ ማለትም አምላክ በእነርሱ ላይ ለመፍረድ ኢየሱስን እየተጠቀመበት መሆኑን ለማስተዋል ይገደዳሉ። ጥፋት ከመምጣቱ በፊት ሁሉም የሰው ዘር ማስጠንቀቂያ ስለሚደርሰው ይህን ማወቅ አይሳናቸውም። አዎን፣ “ዐይን ሁሉ [ኢየሱስን] ያየዋል፤ የምድርም ሕዝቦች ሁሉ ከእርሱ የተነሣ ዋይ ዋይ ይላሉ።”—ራእይ 1:7

እውነተኛ ሰላምና ብልጽግና በምድር ላይ እንዲሰፍን ከተፈለገ በቅድሚያ ክፉዎችም ሆኑ አገዛዛቸው መወገድ ይኖርባቸዋል። ክርስቶስ ይህን ይፈጽማል። ከዚያም በምድር ላይ የሚከናወኑ ጉዳዮችን ሙሉ ለሙሉ ይቆጣጠራል፤ በዚህ ጊዜ እጅግ አስፈላጊ ለውጦች መታየት ይጀምራሉ።

በረከት የሚያስገኝ የእድሳት ዘመን

ሐዋርያው ጴጥሮስ ‘አምላክ አስቀድሞ በቅዱሳን ነቢያቱ አፍ ስለተናገረው ሁሉን ነገር ስለሚያድስበት ዘመን’ ተናግሯል። (የሐዋርያት ሥራ 3:21) ይህ እድሳት በክርስቶስ የግዛት ዘመን በምድር ላይ የሚከናወኑትን ከፍተኛ ለውጦች ይጨምራል። አምላክ በምድር ላይ ‘ሁሉን ነገር ስለሚያድስበት ዘመን’ እንዲናገሩ ከላካቸው ነቢያት መካከል በስምንተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት የኖረው ነቢዩ ኢሳይያስ ይገኝበታል። ኢሳይያስ፣ “የሰላም ልዑል” የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ ሰላምን እንደሚያሰፍን ተንብዮአል። የኢሳይያስ ትንቢት የክርስቶስን አገዛዝ አስመልክቶ “ለመንግሥቱ ስፋት፣ ለሰላሙም ብዛት ፍጻሜ የለውም” ይላል። (ኢሳይያስ 9:6, 7) ኢየሱስ የምድር ሕዝቦች ሰላማዊ እንዲሆኑ ያስተምራቸዋል። በእርግጥም ምድርን የሚወርሱ ሰዎች ‘በታላቅ ሰላም ሐሤት ያደርጋሉ።’—መዝሙር 37:11

በክርስቶስ አገዛዝ ሥር ድህነትም ሆነ ረሃብ ይኖራል? ኢሳይያስ እንዲህ ብሏል:- “የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር በዚህ ተራራ ላይ፣ ለሕዝብ ሁሉ ታላቅ የምግብ ግብዣ፣ የበሰለ የወይን ጠጅ ድግስ፣ ማለፊያ ጮማና ምርጥ የወይን ጠጅ ያዘጋጃል።” (ኢሳይያስ 25:6) መዝሙራዊው ደግሞ “በምድሪቱ ላይ እህል ይትረፍረፍ፤ በተራሮችም ዐናት ላይ ይወዛወዝ” በማለት ዘምሯል። (መዝሙር 72:16) ከዚህም በላይ የምድር ነዋሪዎችን በተመለከተ እንዲህ የሚል እናነባለን:- “ሰዎች ቤት ይሠራሉ፤ በውስጡም ይኖራሉ፤ ወይንን ይተክላሉ፤ ፍሬውንም ይበላሉ። ከእንግዲህ ለሌሎች መኖሪያ ቤት አይሠሩም፤ ወይም ሌላው እንዲበላው አይተክሉም፤ የሕዝቤ ዕድሜ፣ እንደ ዛፍ ዕድሜ ይረዝማል፤ እኔ የመረጥኋቸው፣ በእጃቸው ሥራ ለረጅም ዘመን ደስ ይላቸዋል።”—ኢሳይያስ 65:21, 22

ኢሳይያስ በሽታና ሞት እንደሚጠፋም ተንብዮአል። አምላክ በኢሳይያስ በኩል እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “በዚያን ጊዜም የዕውር ዐይኖች ይገለጣሉ፤ የደንቈሮም ጆሮዎች ይከፈታሉ። አንካሳ እንደ ሚዳቋ ይዘላል፤ የድዳውም አንደበት በደስታ ይዘምራል።” (ኢሳይያስ 35:5, 6) በዚያ “ተቀምጦ፣ ‘ታምሜአለሁ’ የሚል አይኖርም።” (ኢሳይያስ 33:24) ይሖዋ ‘ሞትን ለዘላለም ይውጣል። ጌታ አምላክም ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል።’—ኢሳይያስ 25:8

“መቃብር ውስጥ ያሉ” ሙታንስ ምን ተስፋ አላቸው? (ዮሐንስ 5:28, 29) ኢሳይያስ ‘ሙታንህ ሕያዋን ይሆናሉ፤ ይነሣሉ’ ሲል ተንብዮአል። (ኢሳይያስ 26:19) አዎን፣ በሞት ያንቀላፉ ሰዎች ዳግም ሕያው ይሆናሉ!

“ዙፋንህ አምላክ ለዘላለም ነው”

የክርስቶስ መምጣት ፕላኔታችን ምድር ሙሉ በሙሉ እንድትታደስ መንገድ ይጠርጋል። ምድር ውብ ወደ ሆነች ገነት ትለወጣለች፤ እንዲሁም ሁሉም የሰው ልጆች እውነተኛውን አምላክ በአንድነት ያመልካሉ። ኢየሱስ ክርስቶስ ከምድር ላይ ክፋትን እንደሚያስወግድና ጽድቅን እንደሚያሰፍን እርግጠኞች መሆን እንችላለን?

ኢየሱስ ኃይልም ሆነ ሥልጣን ያገኘው ከማን እንደሆነ ተመልከት። መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክን ልጅ አስመልክቶ እንዲህ ይላል:- “ዙፋንህ አምላክ ለዘላለም ነው። የመንግሥትህ በትር የቅንነት በትር ነው። ጽድቅን ወደድህ ዓመፃንም ጠላህ።” (ዕብራውያን 1:8, 9 የ1879 ትርጉም) ኢየሱስ ዙፋኑን ማለትም ሥልጣኑን ያገኘው ከይሖዋ ነው። የዚህ ዙፋን ምንጭም ሆነ ሰጭ አምላክ ነው። በመሆኑም ኢየሱስ ሊፈታው የማይችለው ምንም ችግር አይኖርም።

ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጥቶኛል” ብሏቸዋል። (ማቴዎስ 28:18) አንደኛ ጴጥሮስ 3:22 “መላእክትና ሥልጣናት፣ ኀይላትም ተገዝተውለታል” ሲል ይናገራል። ኢየሱስን የሚቃወም ማንኛውም ኃይልም ሆነ ሥልጣን ሊሳካለት አይችልም። ለሰው ልጆች ዘላቂ ጥቅሞችን ከማምጣት ምንም ነገር ሊያግደው አይችልም።

የክርስቶስ መምጣት የሰዎችን ሕይወት የሚነካው እንዴት ነው?

ሐዋርያው ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ሰዎች በጻፈው ደብዳቤ ላይ “ከእምነት የሆነውን ሥራችሁን፣ ከፍቅር የመነጨውን ድካማችሁንና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ባላችሁ ተስፋ የተገኘውን ጽናታችሁን በአምላካችንና በአባታችን ፊት ዘወትር እናስባለን” ብሏቸዋል። (1 ተሰሎንቄ 1:3) ጳውሎስ አንድ ሰው ከድካሙ ፍሬ የሚያገኘውና ለመጽናት የሚችለው በኢየሱስ ክርስቶስ ተስፋ በማድረጉ እንደሆነ ገልጿል። ይህ ተስፋ ደግሞ በክርስቶስ መምጣትና መምጣቱን ተከትሎ በሚካሄደው ተሃድሶ ማመንን ይጨምራል። እንዲህ ዓይነቱ ተስፋ እውነተኛ ክርስቲያኖች በጣም አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢገጥሟቸውም እንኳ ጸንተው እንዲኖሩ ይረዳቸዋል።

ለምሳሌ ያህል በሳኦ ፓውሎ፣ ብራዚል የሚኖረው ካርሎስ የገጠመውን ሁኔታ ተመልከት። በነሐሴ 2003፣ ካርሎስ ካንሰር እንዳለበት አወቀ። ከዚህ ጊዜ አንስቶ ካርሎስ ስምንት ቀዶ ሕክምናዎች ተደርገውለታል፤ በዚህም ምክንያት ከፍተኛ ሥቃይ ለሚያስከትሉና ከጊዜ ወደ ጊዜ ሰውነቱ እየተዳከመ እንዲሄድ ለሚያደርጉ ተያያዥ ችግሮች ተጋልጧል። ያም ሆኖ ካርሎስ ለሌሎች የብርታት ምንጭ ሆኗል። ለምሳሌ ያህል በአንድ ወቅት፣ በአንድ ትልቅ ሆስፒታል ፊት ለፊት በማገልገል ላይ እያለ ኬሞቴራፒ የሚባል የካንሰር ሕክምና በመከታተል ላይ የሚገኝ ባል ካላት አንዲት የይሖዋ ምሥክር ጋር ተገናኘ። ካርሎስ ካንሰር የሚያስከትለው አስከፊ ውጤት በራሱ ላይ ስለደረሰ ባልና ሚስቱን ማበረታታትና ማጽናናት ችሏል። ቆየት ብሎም እነዚህ ባልና ሚስት ከካርሎስ ጋር ያደረጉት ጭውውት የብርታት ምንጭ እንደሆነላቸው ተናግረዋል። በመሆኑም ካርሎስ የሚከተሉት የጳውሎስ ቃላት እውነት እንደሆኑ ተመልክቷል:- “እኛ ራሳችን ከእግዚአብሔር በተቀበልነው መጽናናት፣ በመከራ ያሉትን ማጽናናት እንድንችል፣ እርሱ በመከራችን ሁሉ ያጽናናናል።”—2 ቆሮንቶስ 1:4

ካርሎስ ሕመሙን ተቋቁሞ ሌሎችን ለማጽናናት የሚያስችል ጥንካሬ እንዲያገኝ የረዳው ምንድን ነው? ካርሎስ በክርስቶስ መምጣትና በሚያከናውናቸው ነገሮች ላይ ያለው ተስፋ ‘በጎ ነገር ማድረጉን’ እንዲቀጥል አነሳስቶታል።—ገላትያ 6:9

ወንድሙን በሞት ያጣውን የሳሙኤልን ሁኔታም ተመልከት። ወንድሙ የተገደለው ከቤታቸው 50 ሜትር ያህል ብቻ ርቆ ሲሆን ሰውነቱ በአሥር ጥይት ተበሳስቶ ነበር። ፖሊስ ምርመራውን እስኪጨርስ ድረስ አስከሬኑ ለስምንት ሰዓታት ያህል ከመንገዱ ላይ አልተነሳም። ሳሙኤል በዚያን ቀን የሆነውን ነገር ፈጽሞ አይረሳውም። ይሁንና ክርስቶስ በምድር ላይ የሚታየውን ክፋት በሙሉ እንደሚያስወግድና የጽድቅ አገዛዙም ለሰው ልጆች በረከትን እንደሚያመጣ ያለው ተስፋ አጽናንቶታል። ሳሙኤል ገነት በሆነችው ምድር ላይ ትንሣኤ ከሚያገኘው ወንድሙ ጋር ሲገናኝ ብዙ ጊዜ በዓይነ ሕሊናው ይታየዋል።—የሐዋርያት ሥራ 24:15

ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

በክርስቶስ መምጣትና በሚያከናውናቸው ነገሮች ላይ ተስፋ ማድረግህ ከፍተኛ ማጽናኛ ያስገኝልሃል። ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆች ላሉባቸው ችግሮችና ለጭንቀቶቻችን መንስኤ የሚሆኑ ነገሮችን በሙሉ እንደሚያስወግድ ጥርጥር የለውም።

የክርስቶስ አገዛዝ ለሰው ልጆች ከሚያዘንብላቸው በረከቶች ተጠቃሚ እንድትሆን ምን ማድረግ ይኖርብሃል? የአምላክ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን በጥንቃቄ አጥና። ኢየሱስ ወደ አባቱ በጸለየ ጊዜ “አንተ ብቻ እውነተኛ አምላክ የሆንኸውንና የላክኸውን ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት” ብሏል። (ዮሐንስ 17:3) መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚያስተምር ለመመርመር ግብ አውጣ። በዚህ ረገድ በአካባቢህ የሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች አንተን ለመርዳት ፈቃደኞች ናቸው። ከእነርሱ ጋር እንድትገናኝ ወይም ለዚህ መጽሔት አዘጋጆች እንድትጽፍ ሞቅ ያለ ግብዣ እናቀርብልሃለን።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የትንሹ ፎቶ የዳራ ምስል:- Rhino and Lion Park, Gauteng, South Africa

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የክርስቶስ መምጣት ምድር ሙሉ በሙሉ እንድትታደስ መንገድ ይጠርጋል