በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለክርስቶስና ለታማኙ ባሪያ ታማኝ ሁኑ

ለክርስቶስና ለታማኙ ባሪያ ታማኝ ሁኑ

ለክርስቶስና ለታማኙ ባሪያ ታማኝ ሁኑ

“ባለቤቱ . . . በንብረቱ ሁሉ ላይ ይሾመዋል።”—ማቴዎስ 24:45-47

1, 2. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ መሪያችን ማን እንደሆነ ይናገራል? (ለ) ክርስቲያን ጉባኤን የሚመራው ክርስቶስ መሆኑን የሚያሳየው ምንድን ነው?

 “መምህራችሁ [“መሪያችሁ፣” NW] አንዱ ክርስቶስ ስለሆነ፣ ‘መምህር [“መሪ፣” NW]’ ተብላችሁ አትጠሩ።” (ማቴዎስ 23:10) ኢየሱስ እነዚህን ቃላት በመናገር በምድር ላይ የሚኖር ማንኛውም ሰው መሪያቸው ሊሆን እንደማይችል ለተከታዮቹ ግልጽ አድርጎላቸዋል። መሪያቸው አንድ እርሱም በሰማይ የሚኖረው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ኢየሱስን መሪ አድርጎ የሾመው አምላክ ነው። ይሖዋ ‘ክርስቶስን ከሙታን አስነስቶ በቤተ ክርስቲያን [“በጉባኤ፣” NW] ባለ በማንኛውም ነገር ላይ ራስ አድርጎ ሾሞታል። እርሷም አካሉ ናት።’—ኤፌሶን 1:20-23

2 ክርስቶስ ከክርስቲያን ጉባኤ ጋር በተያያዘ “በማንኛውም ነገር ላይ ራስ” ተደርጎ ስለተሾመ በጉባኤው ውስጥ የሚደረጉትን ነገሮች በሙሉ የመቆጣጠር ሥልጣን አለው። ኢየሱስ በጉባኤ ውስጥ የሚከናወኑትን እንቅስቃሴዎች በሙሉ ይመለከታል። እያንዳንዱ የክርስቲያኖች ቡድን ወይም ጉባኤ ያለበትን መንፈሳዊ ሁኔታ በቅርበት ይከታተላል። ይህ ሁኔታ በመጀመሪያው መቶ ዘመን መጨረሻ አካባቢ ዮሐንስ በተመለከተው ራእይ ላይ በግልጽ ታይቷል። ኢየሱስ ለሰባቱ ጉባኤዎች በላከው መልእክት ላይ ሥራቸውን እንዲሁም ጠንካራና ደካማ ጎናቸውን እንደሚያውቅ አምስት ጊዜ የተናገረ ሲሆን አስፈላጊውን ምክርና ማበረታቻም ሰጥቷቸዋል። (ራእይ 2:2, 9, 13, 19፤ 3:1, 8, 15) ክርስቶስ በትንሿ እስያ፣ በፍልስጥኤም፣ በሶርያ፣ በባቢሎን፣ በግሪክ፣ በጣሊያን እንዲሁም በሌሎች ቦታዎች ይገኙ የነበሩ ጉባኤዎች ያሉበትን መንፈሳዊ ሁኔታም ያውቅ ነበር ለማለት የሚያስችል በቂ ምክንያት አለን። (የሐዋርያት ሥራ 1:8) በአሁኑ ጊዜ ስላሉት ጉባኤዎችስ ያውቃል ማለት ይቻላል?

ታማኝ ባሪያ

3. ክርስቶስን በራስ፣ ጉባኤው ደግሞ በአካል መመሰሉ ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?

3 ኢየሱስ ከሞት ከተነሳና በሰማይ ወደሚኖረው አባቱ ከማረጉ ከጥቂት ጊዜ በፊት ለደቀ መዛሙርቱ “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጥቶኛል፤ . . . እኔም እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” ብሏቸዋል። (ማቴዎስ 28:18-20) ኢየሱስ በበላይነት እነርሱን መምራቱን ይቀጥላል። ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶንና በቈላስይስ ለሚገኙ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ የክርስቲያን ጉባኤን ክርስቶስ ራስ ከሆነለት ‘አካል’ ጋር አመሳስሎታል። (ኤፌሶን 1:22, 23፤ ቈላስይስ 1:18) ዘ ካምብሪጅ ባይብል ፎር ስኩልስ ኤንድ ኮሌጅስ የተባለው መጽሐፍ እንደገለጸው ይህ ዘይቤያዊ አነጋገር “ራስ ከሆነው [ከክርስቶስ] ጋር አንድነት መፍጠሩ አስፈላጊ መሆኑን ብቻ ሳይሆን ራስ የሆነው አካል አባላቱን እንደሚመራም ያመለክታል። አባላቱ ፈቃዱን ለመፈጸም የሚጠቀምባቸው መሣሪያዎች ናቸው።” ክርስቶስ መንግሥታዊ ሥልጣኑን ከተቀበለበት ከ1914 ጀምሮ መሣሪያ አድርጎ ሲጠቀምበት የቆየው ቡድን የትኛው ነው?—ዳንኤል 7:13, 14

4. በሚልክያስ ትንቢት መሠረት ይሖዋና ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ መንፈሳዊው ቤተ መቅደስ ለምርመራ በመጡበት ጊዜ የነበረው ሁኔታ ምን ይመስል ነበር?

4 የሚልክያስ ትንቢት አስቀድሞ እንደተናገረው እውነተኛ “ጌታ” የሆነው ይሖዋ፣ ‘ከቃል ኪዳኑ መልእክተኛና’ አዲስ ከተሾመው ንጉሥ ማለትም ከልጁ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ለመፍረድ እንዲሁም ለመመርመር ወደ “ቤተ መቅደሱ” ወይም ወደ መንፈሳዊ የአምልኮ ቤቱ ይመጣል። ‘ፍርድ ከአምላክ ቤት የጀመረው’ በ1918 መሆኑን ከሁኔታዎቹ በግልጽ መረዳት ይቻላል። a (ሚልክያስ 3:1፤ 1 ጴጥሮስ 4:17) በዚያን ወቅት አምላክንና እውነተኛውን አምልኮ በምድር ላይ እንወክላለን የሚሉ ሁሉ በሚገባ ተመረመሩ። አምላክን የማያስከብሩ ትምህርቶችን ለዘመናት ሲያስተምሩ የቆዩትና በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በደረሰው እልቂት ከፍተኛ ተሳትፎ የነበራቸው የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት አጡ። በመንፈስ የተቀቡት ታማኝ ቀሪዎች ከተፈተኑና በእሳት ከተጣሩ በኋላ ተቀባይነት አግኝተው ለይሖዋ “ቍርባንን በጽድቅ የሚያቀርቡ ሰዎች” ሆነዋል።—ሚልክያስ 3:3

5. ኢየሱስ ‘መምጣቱን’ አስመልክቶ ከተናገረው ትንቢት ጋር በሚስማማ መልኩ ታማኝ “ባሪያ” ሆኖ የተገኘው ማን ነው?

5 ኢየሱስ፣ ለደቀ መዛሙርቱ ‘መምጣቱንና የዓለም መጨረሻ’ መድረሱን ማስተዋል እንዲችሉ የተለያዩ ገጽታዎች ያሉት ምልክት ሰጥቷቸው ነበር፤ ከእነዚህ ምልክቶች መካከል ‘ባሪያው’ በቡድን ደረጃ ተለይቶ የሚታወቅበት መለያ የሚገኝ ሲሆን ይህም ከሚልክያስ ትንቢት ጋር ይስማማል። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- “በተገቢው ጊዜ ምግባቸውን እንዲሰጣቸው ባለቤቱ በቤተ ሰዎቹ ላይ የሾመው ታማኝና ብልኅ አገልጋይ [“ታማኝና ልባም ባሪያ፣” የ1954 ትርጉም] እንግዲህ ማነው? ባለቤቱ ተመልሶ በሚመጣበት ጊዜ የተጣለበትን ዐደራ እየፈጸመ የሚያገኘው ያ አገልጋይ የተባረከ ነው፤ እውነት እላችኋለሁ፤ በንብረቱ ሁሉ ላይ ይሾመዋል።” (ማቴዎስ 24:3, 45-47) ክርስቶስ ‘ባሪያውን’ ለመመርመር በ1918 ‘በመጣ ጊዜ’ በመንፈስ የተቀቡት ቀሪዎች ከ1879 ጀምሮ በመጠበቂያ ግንብ መጽሔትና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተመሠረቱ ሌሎች ጽሑፎች አማካኝነት “በተገቢው ጊዜ” መንፈሳዊ ‘ምግብ’ በማቅረብ በታማኝነት ሲያገለግሉ አግኝቷቸዋል። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ በቡድን ደረጃ ሥራውን ለማከናወን እንደሚጠቀምበት መሣሪያ ወይም “ባሪያ” አድርጎ የተቀበላቸው ከመሆኑም በላይ በ1919 በምድር ያለውን ንብረቱን ሁሉ እንዲያስተዳድሩ ሾሟቸዋል።

በምድር ላይ ያሉትን የክርስቶስ ንብረቶች ማስተዳደር

6, 7. (ሀ) ኢየሱስ ታማኙን “ባሪያ” ለማመልከት ምን ሌሎች መግለጫዎችን ተጠቅሟል? (ለ) ኢየሱስ ባሪያውን “መጋቢ” ብሎ መጥራቱ ምን ያመለክታል?

6 ኢየሱስ በንጉሣዊ ሥልጣኑ ላይ መገኘቱን የሚጠቁመውን ምልክት የያዘውን ትንቢት ሲናገር በምድር ላይ እርሱን ስለሚወክለው “ባሪያ” ገልጾ ነበር፤ ትንቢቱን ከመናገሩ ከጥቂት ወራት በፊት ይህን “ባሪያ” አስመልክቶ የሰጠው ለየት ያለ መግለጫ ባሪያው ምን ኃላፊነቶች እንዳሉበት እንድንገነዘብ ይረዳናል። ኢየሱስ እንደሚከተለው ብሏል:- “እንግዲህ፣ ምግባቸውን በተገቢው ጊዜ እንዲሰጣቸው ጌታው በቤተ ሰዎቹ ላይ የሚሾመው ታማኝና ብልህ መጋቢ ማነው? እውነት እላችኋለሁ፤ ባለው ንብረት ሁሉ ላይ ይሾመዋል።”—ሉቃስ 12:42, 44

7 እዚህ ላይ ባሪያው መጋቢ ተብሎ ተጠርቷል። መጋቢ ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል “የቤት ወይም የንብረት አስተዳዳሪ” የሚል ፍቺ አለው። ይህ መጋቢ ትኩረት የሚስቡ ሐሳቦችን ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚያብራራ የምሑራን ቡድን አይደለም። ‘ታማኙ መጋቢ’ ገንቢ የሆነ መንፈሳዊ ምግብን “በተገቢው ጊዜ” ከማቅረብ በተጨማሪ በሁሉም የክርስቶስ ተከታዮች ላይ ተሹሟል፤ እንዲሁም በምድር ላይ ያሉትን ‘ንብረቶች ሁሉ’ ማለትም የክርስቶስን ጉባኤና በውስጡ የሚደረጉትን እንቅስቃሴዎች የመቆጣጠር ኃላፊነት ተሰጥቶታል። ታዲያ የክርስቶስ ንብረቶች የተባሉት ምንድን ናቸው?

8, 9. ባሪያው እንዲያስተዳድር የተሾመው በየትኞቹ ‘ንብረቶች’ ላይ ነው?

8 የባሪያው ኃላፊነት የክርስቶስ ተከታዮች ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴያቸውን ለማከናወን የሚጠቀሙባቸውን ቁሳዊ ንብረቶች መቆጣጠርን ይጨምራል። ከእነዚህ መካከል የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት፣ ቅርንጫፍ ቢሮዎች እንዲሁም ለአምልኮ የሚጠቀሙባቸው በዓለም ዙሪያ ያሉ የመንግሥት አዳራሾችና ትላልቅ መሰብሰቢያዎች ይገኙበታል። ከዚህም በላይ ባሪያው በመንፈሳዊ የሚያንጹ ፕሮግራሞችን ማለትም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚካሄድባቸውን ሳምንታዊ ስብሰባዎች እንዲሁም በዓመት ሦስት ጊዜ የሚደረጉትን ትላልቅ ስብሰባዎች በበላይነት ይቆጣጠራል። በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜዎች የሚብራሩ ሲሆን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በዕለት ተዕለት ሕይወታችን እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደምንችል የሚገልጽ ወቅታዊ መመሪያም ይሰጣል።

9 መጋቢው እጅግ አስፈላጊ የሆነውን ‘የመንግሥቱን ወንጌል በዓለም ሁሉ’ የመስበኩንና ‘ሕዝቦችን ሁሉ ደቀ መዛሙርት’ የማድረጉን ሥራ በኃላፊነት ይቆጣጠራል። ይህም የጉባኤው ራስ የሆነው ክርስቶስ በዚህ የመጨረሻ ዘመን ሰዎች እንዲያደርጉት ያዘዘውን ነገር ሁሉ እንዲፈጽሙ ሌሎችን ማስተማርን ያጠቃልላል። (ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20፤ ራእይ 12:17) የስብከቱና የማስተማሩ ሥራ የቅቡዓን ቀሪዎች ታማኝ ደጋፊ የሆኑትን ‘እጅግ ብዙ ሕዝቦች’ አስገኝቷል። ‘የሕዝቦች ሁሉ ሀብት’ የሆኑት እነዚህ ሰዎች ታማኙ ባሪያ ከሚያስተዳድራቸው የክርስቶስ ውድ ‘ንብረቶች’ መካከል እንደሚቆጠሩ ጥርጥር የለውም።—ራእይ 7:9፤ ሐጌ 2:7

ባሪያውን የሚወክለው የበላይ አካል

10. በመጀመሪያው መቶ ዘመን ውሳኔ የማድረግ ኃላፊነት የተሰጠው አካል የትኛው ነበር? በጉባኤዎችስ ላይ ምን ውጤት አስከትሏል?

10 ታማኙ ባሪያ ከተጣሉበት ከባድ ኃላፊነቶች መካከል ውሳኔ ማድረግ የሚጠይቁ በርካታ ጉዳዮች መኖራቸው ግልጽ ነው። በጥንቱ የክርስቲያን ጉባኤ፣ በኢየሩሳሌም የነበሩ ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ታማኙን ባሪያ በመወከል መላውን የክርስቲያን ጉባኤ የሚመለከቱ ውሳኔዎችን ያሳልፉ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 15:1, 2) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው የበላይ አካል ያስተላለፈው ውሳኔ በደብዳቤና ተወካዮችን በመላክ ለጉባኤዎች ይዳረስ ነበር። በጥንት ዘመን ይኖሩ የነበሩት ክርስቲያኖች እነዚህን ግልጽ መመሪያዎች በደስታ ይቀበሉ የነበረ ሲሆን ከበላይ አካሉ ጋር ተባብረው ለመሥራት ፈቃደኞች መሆናቸው ሰላምና አንድነት አስገኝቶላቸዋል።—የሐዋርያት ሥራ 15:22-31፤ 16:4, 5፤ ፊልጵስዩስ 2:2

11. በዛሬው ጊዜ ክርስቶስ ጉባኤውን ለመምራት የሚጠቀመው በማን ነው? እኛስ ይህን የቅቡዓን ክርስቲያኖች ቡድን እንዴት ልንመለከተው ይገባል?

11 በክርስትና ዘመን መጀመሪያ ላይ እንደነበረው ሁሉ በዛሬው ጊዜም በምድር ላይ ያሉት የክርስቶስ ተከታዮች የበላይ አካል የተዋቀረው በመንፈስ በተቀቡ ጥቂት የበላይ ተመልካቾች ነው። እነዚህ ታማኝ ወንዶች የመንግሥቱን ሥራ በበላይነት በሚቆጣጠሩበት ጊዜ የቤተ ክርስቲያን ራስ የሆነው ክርስቶስ “በቀኝ እጁ” በተመሰለው ኃይሉ አማካኝነት ይመራቸዋል። (ራእይ 1:16, 20) የበላይ አካል አባል በመሆን ለረጅም ጊዜያት ያገለገለውና በቅርቡ ምድራዊ ሕይወቱን ያጠናቀቀው ወንድም አልበርት ሽሮደር በሕይወት ታሪኩ ላይ እንደሚከተለው በማለት ጽፎ ነበር:- “የአስተዳደር አካሉ በየሳምንቱ ረቡዕ ይሰበሰባል። የይሖዋን መንፈስ መሪነት በመጠየቅ ስብሰባውን በጸሎት ይከፍታል። እያንዳንዱ ጉዳይና ውሳኔ የሚሰጥበት ነገር ከአምላክ ቃል ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚስማማ እንዲሆን ከፍተኛ ጥረት ይደረጋል።” b በመንፈስ በተቀቡት በእነዚህ ታማኝ ክርስቲያኖች ላይ እምነት ልንጥልባቸው እንችላለን። በተለይም ደግሞ ሐዋርያው ጳውሎስ የበላይ አካሉን አስመልክቶ “ለመሪዎቻችሁ ታዘዙ፤ ተገዙላቸውም። ምክንያቱም . . . ስለ ነፍሳችሁ ጉዳይ ይተጋሉ” በማለት የሰጠውን መመሪያ መታዘዝ ይገባናል።—ዕብራውያን 13:17

ለታማኙ ባሪያ ተገቢ አክብሮት ማሳየት

12, 13. ለባሪያው ክፍል አክብሮት ማሳየት እንዳለብን የሚጠቁሙ ምን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክንያቶች አሉ?

12 ለታማኙ ባሪያ ተገቢ አክብሮት እንድናሳይ የሚገፋፋን ዋነኛ ምክንያት እንዲህ ማድረጋችን የባሪያው ባለቤት ለሆነው ለኢየሱስ ክርስቶስ አክብሮት እንዳለን ስለሚያሳይ ነው። ጳውሎስ ለቅቡዓኑ እንዲህ በማለት ጽፎላቸዋል:- “ሲጠራ ነጻ የነበረ ሰው የክርስቶስ ባሪያ ነው። በዋጋ ተገዝታችኋል።” (1 ቆሮንቶስ 7:22, 23፤ ኤፌሶን 6:6) በመሆኑም ታማኙ ባሪያና የበላይ አካሉ የሚሰጡንን መመሪያ በታማኝነት መታዘዛችን ለባሪያው ባለቤት ማለትም ለክርስቶስ መገዛታችን ነው። ክርስቶስ በምድር ያሉ ንብረቶቹን ለማስተዳደር መሣሪያ አድርጎ ለሚጠቀምበት አካል ተገቢውን አክብሮት ማሳየታችን ‘ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ የምንመሰክርበት’ ወይም አምነን መቀበላችንን የምናሳይበት አንዱ መንገድ ነው።—ፊልጵስዩስ 2:11

13 ለታማኙ ባሪያ አክብሮት እንድናሳይ የሚያነሳሳን ሌላው ምክንያት ደግሞ በምድር ላይ የሚገኙት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ይሖዋ “በመንፈሱ” አማካኝነት የሚያድርበት “ቤተ መቅደስ” እንደሆኑ ተደርገው በምሳሌያዊ መንገድ መገለጻቸው ነው። በመሆኑም “ቅዱስ” ናቸው። (1 ቆሮንቶስ 3:16, 17፤ ኤፌሶን 2:19-22) ኢየሱስ በምድር ላይ ያሉትን ንብረቶቹን በአደራ የሰጠው በቤተ መቅደስ ለተመሰለው ለዚህ አካል ነው፤ ይህም ሲባል በጉባኤው ውስጥ ያሉ አንዳንድ መብቶችና ኃላፊነቶች ለባሪያው ክፍል ብቻ የተሰጡ ናቸው ማለት ነው። በመሆኑም የጉባኤው አባላት በሙሉ ከታማኝና ልባም ባሪያ እንዲሁም ከበላይ አካሉ የሚመጡትን መመሪያዎች የመታዘዝና የመደገፍ መለኮታዊ ግዴታ እንዳለባቸው ይሰማቸዋል። ‘ሌሎች በጎች’ የባሪያው ክፍል የጌታውን ፈቃድ ለመፈጸም በሚያደርገው ጥረት የበኩላቸውን እርዳታ ማበርከት መቻላቸውን እንደ ልዩ መብት አድርገው ይቆጥሩታል።—ዮሐንስ 10:16

የባሪያውን ክፍል በታማኝነት መደገፍ

14. በኢሳይያስ ትንቢት መሠረት ሌሎች በጎች ከቅቡዓኑ በኋላ የተከተሉትና ‘በነጻ እንደሚሠሩ የጉልበት ሠራተኞች’ ሆነው የሚያገለግሉት እንዴት ነው?

14 የኢሳይያስ ትንቢት ሌሎች በጎች የመንፈሳዊ እስራኤል አባላት ለሆኑት ቅቡዓን በትሕትና እንደሚገዙ ሲገልጽ እንደሚከተለው ብሏል:- “እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል:- ‘የግብፅ ሀብትና [“በነጻ የሚሠሩ የጉልበት ሠራተኞችና፣” NW] የኢትዮጵያ ንግድ፣ ቁመተ ረጃጅሞቹ የሳባ ሰዎች፣ ወደ አንተ ይመጣሉ፤ የአንተ ይሆናሉ፤ ከኋላ ይከተሉሃል፤ በሰንሰለትም ታስረው ወደ አንተ በመምጣት፣ በፊትህ እየሰገዱ፣ “በእውነት እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነው፤ ከእርሱም በቀር ሌላ አምላክ የለም” ብለው ይለምኑሃል።’” (ኢሳይያስ 45:14) በዛሬው ጊዜም ሌሎች በጎች በመንፈስ የተቀባው የባሪያው ክፍልና የበላይ አካሉ የሚሰጡትን መመሪያ በመታዘዝ በምሳሌያዊ ሁኔታ ከኋላ ይከተሏቸዋል። ‘በነጻ እንደሚሠሩ የጉልበት ሠራተኞች’ ክርስቶስ በምድር ላይ ያሉት ቅቡዓን ተከታዮቹ እንዲያከናውኑ ያዘዘውን ዓለም አቀፍ የስብከት ሥራ ለመደገፍ ጉልበታቸውንና ሀብታቸውን በፈቃደኝነት ይሰጣሉ።—የሐዋርያት ሥራ 1:8፤ ራእይ 12:17

15. በኢሳይያስ 61:5, 6 ላይ የሚገኘው ትንቢት በሌሎች በጎችና በመንፈሳዊ እስራኤል መካከል ያለውን ግንኙነት የሚገልጸው እንዴት ነው?

15 ሌሎች በጎች በባሪያው ክፍልና በበላይ አካሉ አመራር ሥር ሆነው ይሖዋን በማገልገላቸው እጅግ ደስተኞችና አመስጋኞች ናቸው። ቅቡዓኑ ‘የአምላክ እስራኤል’ አባላት መሆናቸውን አምነው ይቀበላሉ። (ገላትያ 6:16) በምሳሌያዊ ሁኔታ ከመንፈሳዊ እስራኤል ጋር እንደተባበሩ “መጻተኞች” እና “ባዕዳን” ተደርገው የተገለጹት ሌሎች በጎች ‘የይሖዋ ካህናትና የአምላክ ባሮች’ በሆኑት ቅቡዓን ክርስቲያኖች አመራር ሥር ‘አራሾችና የወይን ተክል ሠራተኞች’ በመሆን ማገልገላቸው ያስደስታቸዋል። (ኢሳይያስ 61:5, 6) የመንግሥቱን ወንጌል በመስበኩና ሕዝቦችን ሁሉ ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ በቅንዓት ይካፈላሉ። ሌሎች በጎች አዲስ የተገኙ በግ መሰል ሰዎችን በመጠበቅና በመንከባከብ የባሪያውን ክፍል በሙሉ ልብ ይደግፋሉ።

16. ሌሎች በጎች ታማኝና ልባም ባሪያን በታማኝነት እንዲደግፉ የገፋፋቸው ምንድን ነው?

16 ሌሎች በጎች ታማኙ ባሪያ ለእነርሱ ወቅታዊ የሆነ መንፈሳዊ ምግብ ለማቅረብ የሚያደርገው ትጋት የተሞላበት ጥረት በእጅጉ እንደጠቀማቸው ይገነዘባሉ። እነዚህ ሌሎች በጎች፣ ታማኝና ልባም ባሪያ መንፈሳዊ ምግብ ባያቀርብላቸው ኖሮ ውድ ስለሆኑት የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ያላቸው እውቀት በጣም ውስን ሊሆን ይችል እንደነበረ ወይም ምንም ሊያውቁ እንደማይችሉ በትሕትና አምነው ይቀበላሉ። ከእነዚህ እውነቶች መካከል ስለ ይሖዋ ሉዓላዊነት፣ ስለ ስሙ መቀደስ፣ ስለ መንግሥቱ፣ ስለ አዲስ ሰማይና ምድር፣ ስለ ነፍስና ሙታን ስላሉበት ሁኔታ እንዲሁም ስለ ይሖዋ፣ ስለ ልጁና ስለ መንፈስ ቅዱስ ትክክለኛ ማንነት የሚናገሩት ይገኙበታል። ሌሎች በጎች፣ በዚህ በመጨረሻ ዘመን በምድር ላይ ላሉት የክርስቶስ ቅቡዓን ‘ወንድሞች’ ከልብ በመነጨ የአመስጋኝነት ስሜት ተነሳስተው በታማኝነት ፍቅራዊ ድጋፍ ያደርጉላቸዋል።—ማቴዎስ 25:40

17. የበላይ አካሉ ምን ማድረጉን አስፈላጊ ሆኖ አግኝቶታል? በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ ምን ይብራራል?

17 በምድር ላይ ያሉት ቅቡዓን ቁጥራቸው እየቀነሰ በመሄዱ የክርስቶስን ንብረት ለማስተዳደር በእያንዳንዱ ጉባኤ ውስጥ መገኘት አይችሉም። በመሆኑም የበላይ አካሉ ቅርንጫፍ ቢሮዎችን፣ አውራጃዎችንና ወረዳዎችን እንዲሁም የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎችን በበላይነት የሚቆጣጠሩ ወንዶችን ሾሟል። ለእነዚህ የበታች እረኞች የሚኖረን አመለካከት ለክርስቶስና ለታማኙ ባሪያ ያለንን ታማኝነት የሚነካው እንዴት ነው? ይህ በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ ይብራራል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a ይህን ርዕስ በተመለከተ ዝርዝር ማብራሪያ ለማግኘት የመጋቢት 1, 2004 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 13-18ን እና የታኅሣሥ 1, 1992 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 13ን ተመልከት።

b የወንድም ሽሮደርን የሕይወት ታሪክ በመጋቢት 1, 1988 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 10-17 (መጠበቂያ ግንብ 6-109 ገጽ 3-11) ላይ ማግኘት ይቻላል።

ለክለሳ ያህል

• መሪያችን ማን ነው? በጉባኤዎች ውስጥ ያለውን ሁኔታ እንደሚያውቅ የሚያሳየውስ ምንድን ነው?

• ‘ቤተ መቅደሱ’ በተመረመረ ጊዜ ታማኝ ባሪያ ሆነው የተገኙት እነማን ናቸው? በአደራ የተሰጧቸው ንብረቶችስ የትኞቹ ናቸው?

• ታማኙን ባሪያ በታማኝነት መደገፍ እንዳለብን የሚያሳዩ ምን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክንያቶች አሉ?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

‘መጋቢው’ በበላይነት ከሚቆጣጠራቸው ‘ንብረቶች’ መካከል ቁሳዊ ንብረቶች፣ መንፈሳዊ ፕሮግራሞችና የስብከቱ እንቅስቃሴ ይገኙበታል

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሌሎች በጎች በቅንዓት በመስበክ የታማኙን ባሪያ ክፍል ይደግፋሉ