በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች!

ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች!

ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች!

በዛሬው ጊዜ ባሉት በርካታ ራስ አገዝ መጻሕፍት ውስጥ የሚገኘው አብዛኛው ምክር ሕይወታቸው የተመሰቃቀለባቸውን ሰዎች በመርዳት ላይ ያተኮረ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ግን ከዚህ የተለየ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ምክር የተጨነቁ ሰዎችን የሚረዳ ቢሆንም ከዚህ የበለጠ ጥቅምም አለው። ምክሩ አንድ ሰው ሳያስፈልግ ችግር ውስጥ እንዲገባ ሊያደርጉት የሚችሉ ስህተቶችን ከመፈጸም እንዲቆጠብ ይረዳዋል።

መጽሐፍ ቅዱስ “ብስለት ለሌላቸው አስተዋይነትን፣ በዕድሜ ለጋ ለሆኑት ዕውቀትንና ልባምነትን” ሊሰጥ ይችላል። (ምሳሌ 1:4) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ምክር ተግባራዊ ካደረግህ “ጥንቃቄ ይጠብቅሃል፣ ማስተዋልም ይጋርድሃል፣ ከክፉ መንገድ” ያድንሃል። (ምሳሌ 2:11, 12 የ1954 ትርጉም) የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር መከተል ጤንነትህን በመጠበቅ፣ የቤተሰብ ሕይወትህን በማሻሻል እንዲሁም የተሻልክ ሠራተኛ ወይም አሠሪ በመሆን ረገድ እንዴት ሊረዳህ እንደሚችል የሚያሳዩ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት።

የአልኮል መጠጥ ከመጠን በላይ ከመጠጣት ተቆጠብ

መጽሐፍ ቅዱስ የአልኮል መጠጥ በልኩ መጠጣትን አያወግዝም። ሐዋርያው ጳውሎስ ወጣቱን ጢሞቴዎስን “ለሆድህና ደጋግሞ ለሚነሣብህ ሕመም፣ ጥቂት የወይን ጠጅ ጠጣበት” ብሎ መምከሩ፣ የወይን ጠጅ ለመድኃኒትነት ሊያገለግል እንደሚችል ያሳያል። (1 ጢሞቴዎስ 5:23) ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች፣ አምላክ የወይን ጠጅን የሰጠን ለሕክምና እንድንጠቀምበት ብቻ እንዳልሆነ ያሳያሉ። የወይን ጠጅ ‘የሰውን ልብ ደስ እንደሚያሰኝ’ ተገልጿል። (መዝሙር 104:15) ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ‘በወይን ጠጅ ሱስ እንዳንጠመድ’ ያስጠነቅቀናል። (ቲቶ 2:3) “ብዙ የወይን ጠጅ ከሚጠጡ፣ ሥጋ ከሚሰለቅጡ ጋር አትወዳጅ፤ ሰካራሞችና ሆዳሞች ድኾች ይሆናሉና” ይላል። (ምሳሌ 23:20, 21) እንዲህ ያለውን ሚዛናዊ ምክር ችላ ማለት ምን ያስከትላል? ከጥቂት አገሮች የተሰባሰቡ አንዳንድ መረጃዎችን እንመልከት።

የዓለም የጤና ድርጅት ያወጣው የአልኮል መጠጥን የተመለከተ የ2004 ዓለም አቀፍ ሪፖርት እንዲህ ይላል:- “በአየርላንድ ማኅበረሰብ ውስጥ ከአልኮል መጠጥ ጋር በተያያዙ ችግሮች ሳቢያ በየዓመቱ 2.4 ቢሊዮን ዩሮ [3 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር] ይወጣል።” ይህም “በጤና ችግሮች (279 ሚሊዮን ዩሮ)፣ በመንገድ ላይ በተከሰቱ አደጋዎች (315 ሚሊዮን ዩሮ) እና ከአልኮል መጠጥ ጋር በተያያዘ በተፈጸሙ ወንጀሎች (100 ሚሊዮን ዩሮ) ሳቢያ የወጡ ወጪዎችን እንዲሁም ሰዎች ከመጠጥ ጋር በተያያዙ ችግሮች የተነሳ ከሥራ መቅረታቸው ያስከተለውን ኪሳራ (1,034 ሚሊዮን ዩሮ)” እንደሚያጠቃልል ሪፖርቱ ገልጿል።

የአልኮል መጠጥ ከመጠን በላይ መጠጣት ከሚያስከትለው የገንዘብ ኪሳራ በላይ አሳሳቢ የሆነው ግን በሰዎች ላይ የሚያደርሰው ሥቃይ ነው። ለምሳሌ በአውስትራሊያ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ብቻ፣ የአልኮል መጠጥ ከልክ በላይ በወሰዱ ግለሰቦች አካላዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሰዎች ከግማሽ ሚሊዮን ይበልጣሉ። በፈረንሳይ፣ በቤተሰብ አባላት ላይ ከሚፈጸሙት የዓመጽ ድርጊቶች ውስጥ 30 በመቶ ለሚሆኑት መነሾው የአልኮል መጠጥ ከልክ በላይ መጠጣት ነው። እነዚህን መረጃዎች ስትመለከት መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አልኮል መጠጥ የሚሰጠው ምክር ምክንያታዊ እንደሆነ አይሰማህም?

ሰውነትን ከሚያረክሱ ልማዶች ራቅ

ሲጋራ ማጨስ እንደ ፋሽን ይታይ በነበረበት በ1942፣ ትንባሆ ማጨስ ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት ጋር እንደሚጋጭና ልናስወግደው የሚገባ ልማድ እንደሆነ ይህ መጽሔት ለአንባቢዎቹ ገልጾ ነበር። በዚያው ዓመት በዚህ መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ርዕስ አምላክን ማስደሰት የሚፈልጉ ሰዎች “ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ነገር ሁሉ ራሳችንን እናንጻ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ መከተል እንዳለባቸው ገልጿል። (2 ቆሮንቶስ 7:1) ይህ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ምክር ከወጣ 65 ዓመታት ያለፉ ቢሆንም ይህ ምክር ጥበብ ያዘለ እንደሆነ በዛሬው ጊዜም እየተመለከትን አይደለም?

በ2006 የዓለም የጤና ድርጅት እንደገለጸው ትንባሆ ማጨስ “በዓለም ላይ ሰዎችን ለህልፈተ ሕይወት ከሚዳርጉት ዋና ዋና ምክንያቶች ውስጥ ሁለተኛውን ደረጃ ይይዛል።” በየዓመቱ ወደ አምስት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ትንባሆ በማጨሳቸው ምክንያት ሕይወታቸውን የሚያጡ ሲሆን በኤች አይ ቪ/ኤድስ ምክንያት በየዓመቱ የሚሞቱት ሰዎች ግን ሦስት ሚሊዮን ገደማ ናቸው። በ20ኛው መቶ ዘመን ሲጋራ ማጨስ 100 ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈ ሲሆን ይህም በዚያ ምዕተ ዓመት በተካሄዱት ጦርነቶች በሙሉ ከሞቱት ሰዎች ቁጥር ጋር የሚተካከል ነው። በእርግጥም፣ ከትንባሆ መራቅ የጥበብ እርምጃ እንደሆነ በአሁኑ ጊዜ ብዙዎች ይስማሙበታል።

“ከዝሙት ሽሹ”

ብዙዎች መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጾታ ግንኙነት የሚሰጠውን ሐሳብ ለመቀበል ይከብዳቸዋል። ሆኖም በርካታ ሰዎች ከተማሩት በተቃራኒ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ማንኛውም ዓይነት የጾታ ስሜት ኃጢአት እንደሆነ አይናገርም። ከዚህ ይልቅ የሰው ልጆች ይህንን ፍላጎታቸውን እንዴት ማርካት እንደሚገባቸው የሚገልጽ ጥበብ ያዘለ ምክር ይሰጣል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ የጾታ ግንኙነት በተጋቡ ወንድና ሴት መካከል ብቻ ሊፈጸም የሚገባ ድርጊት እንደሆነ ያስተምራል። (ዘፍጥረት 2:24፤ ማቴዎስ 19:4-6፤ ዕብራውያን 13:4) የጾታ ግንኙነት፣ የትዳር ጓደኛሞች አንዳቸው ለሌላው ያላቸውን ፍቅር የሚገልጹበት መንገድ ነው። (1 ቆሮንቶስ 7:1-5) በትዳር የተጣመሩ ሰዎች የሚወልዷቸው ልጆች እርስ በርስ የሚተሳሰቡ አባትና እናት ስለሚኖሯቸው ይጠቀማሉ።—ቈላስይስ 3:18-21

መጽሐፍ ቅዱስ ልቅ የጾታ ብልግናን በተመለከተ “ከዝሙት ሽሹ” የሚል መመሪያ ይሰጣል። (1 ቆሮንቶስ 6:18) እንዲህ ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው? ይኸው ጥቅስ “ሰው የሚሠራው ኀጢአት ሁሉ ከአካሉ ውጭ ነው፤ ዝሙትን የሚፈጽም ግን በገዛ አካሉ ላይ ኀጢአት ይሠራል” በማለት አንዱን ምክንያት ይነግረናል። መጽሐፍ ቅዱስ የጾታ ግንኙነትን አስመልክቶ የሰጠውን ምክር ችላ ማለት ምን ያስከትላል?

በዩናይትድ ስቴትስ ያለውን ሁኔታ እንመልከት። በዚህች አገር በየዓመቱ 850,000 የሚያህሉ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች ያረግዛሉ፤ በመሆኑም ዩናይትድ ስቴትስ በኢንዱስትሪ በበለጸጉት አገሮች ውስጥ በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ እያሉ በሚያረግዙ ወጣቶች ቁጥር ቀዳሚውን ሥፍራ ይዛለች። በውርጃ ሕይወታቸውን ከማጣት ተርፈው የሚወለዱት አብዛኞቹ ሕፃናት ያለ አባት ያድጋሉ። ብቻቸውን ሆነው ልጆቻቸውን የሚያሳድጉት እነዚህ ወጣት እናቶች፣ ልጆቻቸውን በፍቅርና በሥርዓት ለማሳደግ የተቻላቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉ ጥርጥር የለውም፤ ከእነዚህም አንዳንዶቹ ስኬታማ ሆነዋል። ይሁን እንጂ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ያሉ እናቶች የወለዷቸው ወንዶች ልጆች አብዛኛውን ጊዜ ወኅኒ ቤት የሚወርዱ ሲሆን ሴት ልጆቻቸው ደግሞ እንደ እናቶቻቸው ገና በልጅነታቸው ይወልዳሉ። ሮበርት ለርማን የተባሉ ተመራማሪ ያለፉትን በርካታ አሥርተ ዓመታት አኃዛዊ መረጃዎች ከመረመሩ በኋላ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “በነጠላ ወላጅ የሚተዳደሩ ቤተሰቦች መብዛታቸው ሌሎች ማኅበራዊ ችግሮች እንዲበራከቱ አስተዋጽኦ አድርጓል። ከእነዚህም መካከል ትምህርት ማቋረጥ፣ የአልኮል መጠጦችንና አደንዛዥ ዕፆችን አላግባብ መጠቀም፣ የወጣት ጥፋተኞች መብዛት እንዲሁም በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች ማርገዝና ልጅ መውለድ ይገኙበታል።”

ልቅ የጾታ ብልግና የሚፈጽሙ ሰዎች ለአካላዊም ሆነ ለሥነ ልቦናዊ ቀውስ የመጋለጥ አጋጣሚያቸው ከፍተኛ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ፒዲያትሪክስ የተባለው መጽሔት “በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ሆነው የጾታ ግንኙነት የሚፈጽሙ ወጣቶች በመንፈስ ጭንቀት የመሠቃየትና ራሳቸውን የመግደል አጋጣሚያቸው ሰፊ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ” በማለት ዘግቧል። አሜሪካን ሶሻል ኸልዝ አሶሲዬሽን የተባለው ድርጅት፣ ይህ ዓይነቱ አኗኗር የሚያስከትላቸውን ሌሎች የጤና ችግሮች አስመልክቶ እንዲህ ብሏል:- “[በዩናይትድ ስቴትስ] ከሚኖሩት ሰዎች ውስጥ ከ50 በመቶ በላይ የሚሆኑት በሕይወታቸው ውስጥ በአንድ ወቅት ላይ በጾታ ግንኙነት በሚተላለፉ በሽታዎች መያዛቸው አይቀርም።” ሰዎች፣ መጽሐፍ ቅዱስ የጾታ ግንኙነትን በተመለከተ የሚሰጠውን ጠቃሚ ምክር ቢከተሉ ኖሮ በዚህ ምክንያት የሚፈጠረውን ሐዘንና ሥቃይ ማስወገድ ይችሉ ነበር!

በቤተሰብህ መካከል ያለው ግንኙነት ጠንካራ እንዲሆን አድርግ

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ጎጂ ከሆኑ ልማዶች እንድንርቅ በመምከር ብቻ አይወሰንም። የቤተሰብ ሕይወትን ማሻሻል የሚቻልበትን መንገድ በተመለከተ የሚሰጣቸውን ተግባራዊ የሆኑ ምክሮች እስቲ እንመልከት።

የአምላክ ቃል “ባሎችም እንደዚሁ ሚስቶቻቸውን እንደ ገዛ ሥጋቸው መውደድ ይገባቸዋል” ይላል። (ኤፌሶን 5:28) ባሎች፣ ሚስቶቻቸውን አቅልለው ከመመልከት ይልቅ “በቀላሉ እንደምትሰበር ዕቃ በክብር በመያዝ በእውቀት [አብረዋቸው እንዲኖሩ]” ተመክረዋል። (1 ጴጥሮስ 3:7 NW) በጋብቻ ውስጥ ሊፈጠሩ የሚችሉ አለመግባባቶችን በተመለከተም ባሎች “ሚስቶቻችሁን ውደዱ፤ መራራም አትሁኑባቸው” የሚል ምክር ተሰጥቷቸዋል። (ቈላስይስ 3:19) አንድ ባል ይህንን ምክር ተግባራዊ ማድረጉ የሚስቱን ፍቅርና አክብሮት እንዲያገኝ ይረዳዋል ቢባል አትስማማም?

መጽሐፍ ቅዱስ ለሚስቶችም የሚከተለውን መመሪያ ይሰጣል:- “ሚስቶች ሆይ፤ ለጌታ እንደምትገዙ ለባሎቻችሁም ተገዙ። ክርስቶስ፣ . . . [ለቤተ ክርስቲያን] ራስ እንደ ሆነ ሁሉ፣ ባልም የሚስቱ ራስ ነውና። . . . ሚስትም ባሏን ታክብር።” (ኤፌሶን 5:22, 23, 33) አንዲት ሚስት፣ ባሏን ስታነጋግረውም ሆነ ስለ እርሱ ስታወራ ይህንን ምክር የምትከተል ከሆነ ባሏ በጣም የሚወዳት አይመስልህም?

መጽሐፍ ቅዱስ የልጆችን አስተዳደግ በተመለከተ ለእናንተ ለወላጆች የሚሰጠው ምክር፣ ከልጆቻችሁ ጋር መነጋገር እንዳለባችሁ የሚገልጽ ነው። ዘዳግም 6:7 “[የአምላክን መመሪያዎች] ለልጆችህም አስጠናቸው፤ በቤትህ ስትቀመጥ፣ በመንገድም ስትሄድ፣ ስትተኛና ስትነሣም ስለ እነርሱ ተናገር” ይላል። በተለይም አባቶች ለልጆቻቸው የሥነ ምግባር መመሪያ እንዲሰጧቸውና ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ እንዲገስጿቸው ታዝዘዋል። የአምላክ ቃል “አባቶች ሆይ፤ እናንተም ልጆቻችሁን አታስቈጧቸው፤ ነገር ግን በጌታ ምክርና ተግሣጽ አሳድጓቸው” ይላል። (ኤፌሶን 6:4) ልጆች ደግሞ በበኩላቸው “ለወላጆቻችሁ በጌታ ታዘዙ” እንዲሁም “አባትህንና እናትህን አክብር” ተብለው ተመክረዋል። aኤፌሶን 6:1, 2

ቤተሰቦች ይህንን ምክር ተግባራዊ ቢያደርጉ የሚጠቀሙ ይመስልሃል? ‘አዎን፣ ምክሩ በፅንሰ ሐሳብ ደረጃ ጥሩ ይመስላል፤ ሆኖም በእርግጥ ተግባራዊ ሊሆን ይችላል?’ ትል ይሆናል። በአካባቢህ ወደሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ እንድትሄድ እንጋብዝሃለን። በዚያም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ጥበብ ያዘለ ምክር ተግባራዊ ለማድረግ የሚጥሩ ቤተሰቦች ታገኛለህ። ቀረብ ብለህ አነጋግራቸው። በዚያ የሚገኙት የቤተሰብ አባላት እርስ በርስ ያላቸውን ግንኙነት ለማስተዋል ሞክር። በእርግጥም በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች መመራት የቤተሰብን ሕይወት አስደሳች እንደሚያደርግ በገዛ ዓይንህ መመልከት ትችላለህ!

ታታሪ ሠራተኛና ሐቀኛ አሠሪ

መጽሐፍ ቅዱስ ሥራችንን ላለማጣት በየቀኑ ስለምናደርገው ትግል ምን ይላል? ሥራውን ጥሩ አድርጎ የሚያከናውን ሰው ከፍተኛ ግምት እንደሚሰጠውና እንደሚካስ ይናገራል። ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን “በሙያው ሥልጡን የሆነውን ሰው አይተሃልን? በነገሥታት ዘንድ ባለሟል ይሆናል” ብሏል። (ምሳሌ 22:29) በሌላ በኩል ግን “ጢስ ዐይንን እንደሚጐዳ” ሁሉ “ሰነፍም” አሠሪውን ያበሳጫል። (ምሳሌ 10:26) መጽሐፍ ቅዱስ ሠራተኞች፣ ሐቀኞችና ትጉዎች እንዲሆኑ ያበረታታል። “ይሰርቅ የነበረ ከእንግዲህ አይስረቅ፤ ነገር ግን . . . በገዛ እጆቹ በጎ የሆነውን እየሠራ ለማግኘት ይድከም።” (ኤፌሶን 4:28) አሠሪያችን አጠገባችን ባይኖርም እንኳ ይህ ምክር ይሠራል። “ሰውን ለማስደሰትና ለታይታ ብላችሁ ሳይሆን በቅን ልብ ጌታን በመፍራት ለምድራዊ ጌቶቻችሁ በሁሉ ነገር ታዘዙ።” (ቈላስይስ 3:22) አሠሪ ከሆንክ ይህንን ምክር ተግባራዊ ለሚያደርግ ሠራተኛ ከፍ ያለ ግምት አይኖርህም?

መጽሐፍ ቅዱስ ለአሠሪዎች ደግሞ “ለሠራተኛ ደመወዙ ይገባዋል” የሚል ማሳሰቢያ ይሰጣል። (1 ጢሞቴዎስ 5:18) አምላክ ለእስራኤላውያን የሰጠው ሕግ አሠሪዎች ለሠራተኞቻቸው ተገቢውን ክፍያ በጊዜው እንዲሰጡ ያዝዝ ነበር። ሙሴ “ባልንጀራህን አታጭበርብር፤ አትቀማውም፤ የሙያተኛውን ደመወዝ ሳትከፍል አታሳድር” በማለት ጽፏል። (ዘሌዋውያን 19:13) የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያ በመታዘዝ የሚገባህን ደሞዝ ሳይዘገይ ለሚከፍል አሠሪ መሥራት አያስደስትህም?

የላቀ የጥበብ ምንጭ

የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል ጥንታዊ የሆነ መጽሐፍ ለዘመናችን ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ምክር መያዙ ያስገርምሃል? ሌሎች በርካታ መጻሕፍት ጠቀሜታቸውን ሲያጡ መጽሐፍ ቅዱስ የያዘው ምክር ግን አሁንም ሊሠራ የቻለው፣ መጽሐፉ የሰው ሳይሆን ‘የአምላክ ቃል’ በመሆኑ ነው።—1 ተሰሎንቄ 2:13

ጊዜ ወስደህ የአምላክን ቃል ይበልጥ እንድትመረምር እናበረታታሃለን። እንዲህ ካደረግህ የመጽሐፍ ቅዱስ ባለቤት ለሆነው ለይሖዋ አምላክ ፍቅር ታዳብራለህ። አምላክ የሚሰጠውን ምክር ተግባራዊ የምታደርግ ከሆነ ምክሩ ከጉዳት ይጠብቅሃል፤ እንዲሁም ሕይወትህን ለማሻሻል ይረዳሃል። በዚህ መንገድ “ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ፤ እርሱም ወደ እናንተ ይቀርባል” የሚለው ጥቅስ በሕይወትህ ውስጥ ሲፈጸም ማየት ትችላለህ። (ያዕቆብ 4:8) የትኛውም መጽሐፍ ቢሆን በእነዚህ ሁሉ መንገዶች ሊረዳህ አይችልም።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a ቤተሰብህን የሚጠቅሙ የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎችን በተመለከተ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ተመልከት።

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መጽሐፍ ቅዱስ የአልኮል መጠጥን በተመለከተ የሚሰጠው ምክር ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ይመስልሃል?

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መጽሐፍ ቅዱስ ትንባሆ ከማጨስ እንድንርቅ የሚሰጠውን ምክር ትስማማበታለህ?

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር መከተል የተሻለ የቤተሰብ ሕይወት እንዲኖር ያደርጋል

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ምድር:- Based on NASA Photo