በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትክክለኛውን መልስ ለማግኘት የሚደረግ ጥረት

ትክክለኛውን መልስ ለማግኘት የሚደረግ ጥረት

ትክክለኛውን መልስ ለማግኘት የሚደረግ ጥረት

ጤንነቴን መጠበቅ የምችለው እንዴት ነው?

የቤተሰቤ ሕይወት አስደሳች እንዲሆን ምን ማድረግ እችላለሁ?

ሥራዬን እንዳላጣ ምን ባደርግ ይሻላል?

እንደነዚህ ያሉ ጥያቄዎችን አንስተህ ታውቃለህ? ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ መልሶች አግኝተሃል? በእነዚህና በሌሎች አስፈላጊ ርዕሶች ዙሪያ ምክር የሚሰጡ 2,000 ያህል መጻሕፍት በየዓመቱ ይታተማሉ። በብሪታንያ ብቻ፣ በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሟቸውን ውጣ ውረዶች እንዴት መወጣት እንደሚችሉ የሚገልጹ መጻሕፍትን ለመግዛት ሕዝቡ በየዓመቱ ወደ 80 ሚሊዮን ፓውንድ (150 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገደማ) የሚጠጋ ገንዘብ ያወጣል። በዩናይትድ ስቴትስ፣ ራስ አገዝ የሆኑ መጻሕፍትን ለመግዛት በየዓመቱ 600 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ይወጣል። ከዚህ መመልከት እንደሚቻለው በየዕለቱ የሚያጋጥሙህን ሁኔታዎች እንዴት መወጣት እንደምትችል የሚገልጽ ጥሩ ምክር ለማግኘት የምትጥረው አንተ ብቻ አይደለህም።

አንድ ደራሲ፣ በእነዚህ ሁሉ ጽሑፎች ውስጥ የሚገኘውን ምክር በተመለከተ “አብዛኞቹ አዳዲስ መጻሕፍት ከዚህ ቀደም የተጻፈውን የሚደግሙ ናቸው” በማለት ተናግረዋል። በእርግጥም በእነዚህ መጻሕፍት ውስጥ የሚገኘው አብዛኛው ምክር በዓለም ላይ እጅግ ጥንታዊ ከሆኑት መጻሕፍት በአንዱ ላይ የሰፈረውን ጥበብ ያዘለ ሐሳብ የሚያስተጋባ ነው። ይህ መጽሐፍ በዓለም ላይ በስፋት በመሰራጨት ረገድ ተወዳዳሪ የለውም። መጽሐፉ፣ ሙሉውንም ሆነ በከፊል በ2,400 ቋንቋዎች የተተረጎመ ሲሆን በዓለም ዙሪያ በአጠቃላይ በ4.6 ቢሊዮን ቅጂዎች ታትሟል። ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ እንዲህ ሊባልለት የሚችል ሌላ መጽሐፍ የለም።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ “ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው ናቸው፤ ለማስተማር፣ ለመገሠጽ፣ ለማቅናት በጽድቅም መንገድ ለመምከር ይጠቅማሉ” በማለት በግልጽ ይናገራል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) እርግጥ ነው፣ መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው ራስ አገዝ መጽሐፍ እንዲሆን አይደለም። የተጻፈበት ዋነኛ ዓላማ አምላክ ለሰው ዘሮች ያለውን ፈቃድ መግለጽ ነው። ያም ቢሆን ግን መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ዘሮች በሙሉ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች እንዴት መወጣት እንደሚችሉ የሚገልጽ ሰፊ ሐሳብ ይዟል፤ ከዚህም በላይ በውስጡ የሰፈረውን መመሪያ የሚከተሉ ሰዎች የሚጠቅማቸው ትምህርት እንደሚያገኙ ይናገራል። (ኢሳይያስ 48:17, 18) አንድ ሰው ዘሩ፣ ባሕሉ ወይም የትምህርት ደረጃው ምንም ይሁን ምን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ጠቃሚ ምክር ተግባራዊ ካደረገ ምንጊዜም ቢሆን ስኬታማ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ እንደ ጤና፣ የቤተሰብ ሕይወት እንዲሁም ሥራ በመሳሰሉት መስኮች ረገድ የሚሰጠው ሐሳብ ጠቃሚ መሆኑን ማየት እንድትችል ለምን የሚቀጥለውን ርዕስ አታነብም?