አምላክን የሚያስደስት መሥዋዕት ማቅረብ
አምላክን የሚያስደስት መሥዋዕት ማቅረብ
“በሜሶአሜሪካ ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ሰዎችን መሥዋዕት አድርገው ያቀርቡ የነበሩት አዝቴኮች ሕይወት የተገኘው ከሞት እንደሆነ ያምኑ ነበር” በማለት ዘ ማይቲ አዝቴክስ የተባለው መጽሐፍ ዘግቧል። አክሎም “ግዛታቸው እየሰፋ ሲሄድ አገዛዙን ለማጠናከር ሲባል ብዙ የሰው መሥዋዕት ያቀርቡ ነበር” በማለት ተናግሯል። አንድ ሌላ ኢንሳይክሎፒዲያ እንደገለጸው አዝቴኮች በየዓመቱ 20,000 ሰዎችን መሥዋዕት አድርገው ያቀርቡ ነበር።
በታሪክ ዘመናት ሁሉ ሰዎች በጥፋተኝነትና በጸጸት ስሜት በመገፋፋት ወይም ደግሞ በፍርሃትና በጥርጣሬ የተነሳ ለአማልክቶቻቸው የተለያዩ መሥዋዕቶችን ሲያቀርቡ ኖረዋል። በሌላ በኩል ግን፣ ሁሉን ቻይ አምላክ የሆነው ይሖዋ ያዘዛቸው አንዳንድ መሥዋዕቶች እንደነበሩ መጽሐፍ ቅዱስ ያሳየናል። በመሆኑም እንደሚከተለው ብሎ መጠየቁ ተገቢ ነው:- አምላክን የሚያስደስቱት ምን ዓይነት መሥዋዕቶች ናቸው? በዛሬው ጊዜ መሥዋዕት ማቅረብ የአምልኳችን ክፍል ሊሆን ይገባል?
መሥዋዕት በእውነተኛው አምልኮ ውስጥ ያለው ቦታ
የእስራኤል ብሔር ሲቋቋም ይሖዋ፣ ሕዝቡ እንዴት ሊያመልኩት እንደሚገባ የሚያሳዩ ግልጽ መመሪያዎችን የሰጣቸው ሲሆን ከእነዚህም መካከል ስለ መሥዋዕት የሚገልጸው መመሪያ ይገኝበታል። (ዘኍልቊ ምዕራፍ 28 እና 29) ከሚያቀርቧቸው መሥዋዕቶች አንዳንዶቹን የሚወስዱት ከምድር ፍሬ ነበር፤ እንደ በሬ፣ በግ፣ ፍየል፣ ርግብና ዋኖስ ያሉትን እንስሳትም መሥዋዕት አድርገው ያቀርባሉ። (ዘሌዋውያን 1:3, 5, 10, 14፤ 23:10-18፤ ዘኍልቍ 15:1-7፤ 28:7) እስራኤላውያን ሙሉ በሙሉ በእሳት የሚቃጠል መሥዋዕት ያቀርቡ ነበር። (ዘፀአት 29:38-42) ከዚህም በተጨማሪ የኅብረት መሥዋዕት ሲቀርብ መሥዋዕቱን የሚያቀርቡት ሰዎች ለአምላክ ከቀረበው መሥዋዕት ይበላሉ።—ዘሌዋውያን 19:5-8
የሙሴ ሕግ በሚያዝዛቸው መሥዋዕቶች አማካኝነት እስራኤላውያን፣ ለይሖዋ አምልኮ ያቀርቡ እንዲሁም እርሱ የአጽናፈ ዓለም ሉዓላዊ ገዢ እንደሆነ መገንዘባቸውን ያሳዩ ነበር። ሕዝቡ ከይሖዋ ለሚያገኙት በረከትና ለሚያደርገላቸው ጥበቃ ምስጋናቸውን ለመግለጽ ብሎም የኃጢአት ሥርየት ለማግኘት እንደነዚህ ያሉ መሥዋዕቶችን ያቀርቡ ነበር። እስራኤላውያን ለይሖዋ በሚያቀርቡት አምልኮ ረገድ እርሱ የሚፈልግባቸውን ብቃቶች እስካሟሉ ድረስ የተትረፈረፈ በረከት ያገኙ ነበር።—ምሳሌ 3:9, 10
ሆሴዕ 6:6) በዚህም የተነሳ ሕዝቡ ከእውነተኛ አምልኮ ዘወር በማለት ርኩሰት እየፈጸሙና የንጹሐንን ደም እያፈሰሱ በይሖዋ መሠዊያ ላይ የሚያቀርቡት መሥዋዕት ዋጋ አልነበረውም። ይሖዋ በኢሳይያስ አማካኝነት ለእስራኤል ብሔር እንደሚከተለው በማለት የተናገረው በዚህ ምክንያት ነው:- “የመሥዋዕታችሁ ብዛት ለእኔ ምኔ ነው? . . . የሚቃጠለውን የአውራ በግና የሰቡ እንስሳትን ስብ ጠግቤአለሁ፤ በበሬ፣ በበግ ጠቦትና በፍየል ደም ደስ አልሰኝም።”—ኢሳይያስ 1:11
ይሖዋ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው መሥዋዕቶቹን ለሚያቀርቡት ሰዎች የልብ ዝንባሌ ነው። ይሖዋ በነቢዩ ሆሴዕ አማካኝነት “ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን፣ ከሚቃጠልም መሥዋዕት ይልቅ እግዚአብሔርን ማወቅ እሻለሁ” ብሏል። (“እኔ ያላዘዝኋቸውን”
ከእስራኤላውያን ፈጽሞ በተለየ መልኩ የከነዓን ነዋሪዎች ሞሎክ ወይም ሚልኮም ተብሎ ለሚጠራው የአሞናውያን አምላክና ለሌሎች አማልክቶቻቸው ልጆቻቸውን መሥዋዕት አድርገው ያቀርቡ ነበር። (1 ነገሥት 11:5, 7, 33፤ የሐዋርያት ሥራ 7:43) ሃሊስ ባይብል ሀንድቡክ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “ከነዓናውያን አምልኳቸውን ሲያከናውኑ በአማልክቶቻቸው ፊት ልቅ የጾታ ብልግና የሚፈጽሙበት ሃይማኖታዊ ሥርዓት ነበራቸው፤ ከዚያም የበኩር ልጆቻቸውን ለእነዚህ አማልክት መሥዋዕት አድርገው ያቀርቧቸዋል።”
እንደነዚህ ያሉት ልማዶች ይሖዋ አምላክን ያስደስቱት ነበር? በፍጹም። እስራኤላውያን ወደ ከነዓን ምድር ለመግባት ሲቃረቡ ይሖዋ በዘሌዋውያን 20:2, 3 ላይ የሚገኘውን የሚከተለውን ትእዛዝ ሰጥቷቸው ነበር:- “ለእስራኤላውያን እንዲህ በላቸው፤ ‘ከልጆቹ አንዱን ለሞሎክ የሚሰጥ ማንኛውም እስራኤላዊ ወይም በእስራኤል የሚኖር መጻተኛ ይገደል፤ እርሱንም የአገሩ ሕዝብ በድንጋይ ይውገረው። ልጁን ለሞሎክ በመስጠት መቅደሴን አርክሶአልና፣ ቅዱሱን ስሜንም አቃልሎአልና፣ በዚያ ሰው ላይ ጠላት እሆንበታለሁ፤ ከወገኖቹም ለይቼ አጠፋዋለሁ።’”
ፈጽሞ ሊሆን የማይችል ነገር ቢመስልም፣ ከእውነተኛው አምልኮ ዘወር ያሉ አንዳንድ እስራኤላውያን ልጆቻቸውን ለሐሰት አማልክት መሥዋዕት የማድረግን አጋንንታዊ ልማድ ተከተሉ። ይህንን በተመለከተ መዝሙር 106:35-38 እንዲህ ይላል:- “ከሕዝቦቹ ጋር ተደባለቁ፤ ልማዳቸውንም ቀሠሙ፤ ጣዖቶቻቸውንም አመለኩ፤ ይህም ወጥመድ ሆነባቸው። ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን ለአጋንንት ሠዉ። የወንዶችና የሴቶች ልጆቻቸውን ደም፣ ለከነዓን ጣዖታት የሠዉአቸውን፣ ንጹሕ ደም አፈሰሱ፤ ምድሪቱም በደም ተበከለች።”
ይሖዋ፣ ለዚህ ልማድ ያለውን ጥላቻ ሲገልጽ በነቢዩ ኤርምያስ አማካኝነት የይሁዳ ልጆችን በተመለከተ እንዲህ ብሏል:- “አስጸያፊ ነገራቸውን ስሜ በተጠራበት ቤት በማስቀመጥ አርክሰውታል። እኔ ያላዘዝኋቸውን፣ ከቶም ያላሰብሁትን ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን በእሳት አቃጥለው ለመሠዋት በሄኖም ልጅ ሸለቆ የቶፌትን መስገጃ ኰረብቶች ሠሩ።”—ኤርምያስ 7:30, 31
የእስራኤል ብሔር እንዲህ ባሉት ኤርምያስ 7:32-34) ሰዎችን መሥዋዕት አድርጎ ማቅረብ ከእውነተኛው አምላክ የመነጨ ልማድ እንዳልሆነ ከዚህ በግልጽ መመልከት እንችላለን፤ ይህ ዓይነቱ ድርጊት የእውነተኛው አምልኮ ክፍልም አይደለም። በማንኛውም መልኩ ሰዎችን መሥዋዕት አድርጎ ማቅረብ አጋንንታዊ ድርጊት ሲሆን እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮችም ከዚህ ጋር ከተያያዙ ልማዶች በሙሉ ይርቃሉ።
አስጸያፊ ልማዶች በመጠላለፉ ምክንያት በመጨረሻ የይሖዋን ሞገስ አጣ። ከጊዜ በኋላ ዋና ከተማቸው ኢየሩሳሌም የተደመሰሰች ሲሆን ሕዝቡም በግዞት ወደ ባቢሎን ተወሰደ። (የኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት
አንዳንዶች ‘ይሖዋ ለእስራኤላውያን በሰጣቸው ሕግጋት ውስጥ የእንስሳት መሥዋዕት የተካተተው ለምንድን ነው?’ ብለው ይጠይቁ ይሆናል። ሐዋርያው ጳውሎስ ይህንን ጥያቄ አንስቶ የሚከተለውን መልስ ሰጥቷል:- “ታዲያ ሕግ የተሰጠበት ምክንያት ምንድን ነው? ሕግ የተጨመረው ከመተላለፍ የተነሣ ተስፋው ያመለከተው ዘር እስኪመጣ ድረስ ነበር፤ . . . ስለዚህ . . . ሕግ ወደ ክርስቶስ የሚያደርሰን ሞግዚታችን ሆነ።” (ገላትያ 3:19-24) በሙሴ ሕግ ውስጥ የነበሩት የእንስሳት መሥዋዕቶች ይሖዋ አምላክ ለሰው ዘሮች ያዘጋጀውን ታላቅ መሥዋዕት ማለትም ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን የሚያመለክቱ ነበሩ። ኢየሱስ ይህን ፍቅራዊ ዝግጅት አስመልክቶ እንዲህ ብሏል:- “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስከ መስጠት ድረስ ዓለምን እንዲሁ ወዶአል።”—ዮሐንስ 3:16
ኢየሱስ ለአምላክና ለሰዎች ባለው ፍቅር ተነሳስቶ ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወቱን ለአዳም ዘሮች በፈቃደኝነት ቤዛ አድርጎ ሰጥቷል። (ሮሜ 5:12, 15) ኢየሱስ “የሰው ልጅ እንዲያገለግሉት ሳይሆን፣ ለማገልገልና ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ አድርጎ ለመስጠት መጥቶአል” በማለት ስለ ራሱ ተናግሯል። (ማቴዎስ 20:28) በምድር ላይ ካሉት ሰዎች መካከል የሰው ዘሮችን በአዳም ምክንያት ከወደቁበት የኃጢአትና የሞት ባርነት ሊዋጃቸው የሚችል ማንም የለም። (መዝሙር 49:7, 8) በመሆኑም ጳውሎስ፣ ስለ ኢየሱስ ሲናገር “የገባውም የፍየልንና የጥጃዎችን ደም ይዞ አይደለም፤ ነገር ግን የዘላለም ቤዛነት ሊያስገኝ የራሱን ደም ይዞ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ገባ” ብሏል። (ዕብራውያን 9:12) አምላክ፣ ኢየሱስ መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበውን ደሙን በመቀበል ‘ሲቃወመን የነበረውን የዕዳ ጽሕፈት ደምስሶታል።’ ይህም ሲባል፣ ይሖዋ መሥዋዕቶች እንዲቀርቡ ይጠይቅ የነበረውን የሕጉን ቃል ኪዳን አስወግዶታል ማለት ነው፤ በዚህ መንገድ ‘የዘላለም ሕይወት ስጦታ’ ሰጥቶናል።—ቈላስይስ 2:14፤ ሮሜ 6:23
መንፈሳዊ መሥዋዕቶች
በዛሬው ጊዜ በእውነተኛው አምልኮ ውስጥ የእንስሳት መሥዋዕት እንድናቀርብ አይጠበቅብንም፤ ታዲያ ማቅረብ የሚኖርብን መሥዋዕት አለ? አዎን፣ አለ። ኢየሱስ ክርስቶስ፣ አምላክን ለማገልገል ሲል የራሱን ጥቅም መሥዋዕት ያደረገ ሲሆን በመጨረሻም ራሱን ለሰው ልጆች መሥዋዕት አድርጎ አቅርቧል። በዚህም የተነሳ “ሊከተለኝ የሚወድ ራሱን ይካድ፣ መስቀሉንም [“የመከራውን እንጨትም፣” NW] ተሸክሞ ይከተለኝ” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 16:24) ይህም ሲባል የኢየሱስ ተከታይ መሆን የሚፈልግ ማንኛውም ሰው አንዳንድ መሥዋዕቶችን መክፈል ይጠበቅበታል ማለት ነው። እነዚህ መሥዋዕቶች ምንድን ናቸው?
በመጀመሪያ ደረጃ እውነተኛ የኢየሱስ ተከታይ የሆነ ሰው የአምላክን ፈቃድ ለመፈጸም እንጂ ለራሱ አይኖርም። የአምላክን ፈቃድና ፍላጎት በማስቀደም የግል ፍላጎቶቹን በሁለተኛ ደረጃ ያስቀምጣቸዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ ሁኔታውን እንዲህ በማለት አስቀምጦታል:- ሮሜ 12:1, 2
“ወንድሞች ሆይ፤ ሰውነታችሁን ቅዱስና እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሕያው መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኀራኄ እለምናችኋለሁ፤ ይህም እንደ ባለ አእምሮ የምታቀርቡት አምልኮአችሁ ነው። መልካም፣ ደስ የሚያሰኝና ፍጹም የሆነውን የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በአእምሮአችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ።”—ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ ለአምላክ የምናቀርበው ውዳሴ ለይሖዋ እንደሚቀርብ መሥዋዕት ሆኖ ሊቆጠር እንደሚችል ይገልጻል። ነቢዩ ሆሴዕ “የከንፈራችንንም ፍሬ እንድናቀርብ” ብሎ ሲጽፍ፣ አምላክ በከንፈራችን የምናቀርበውን ውዳሴ በእርሱ ዘንድ ከፍ ያለ ቦታ ከሚሰጣቸው መሥዋዕቶች እንደ አንዱ አድርጎ እንደሚመለከተው መግለጹ ነበር። (ሆሴዕ 14:2) ሐዋርያው ጳውሎስ የዕብራውያን ክርስቲያኖችን “የምስጋናን መሥዋዕት ይኸውም ለስሙ የሚመስክሩ የከንፈሮችን ፍሬ . . . ለእግዚአብሔር እናቅርብ” በማለት አሳስቧቸዋል። (ዕብራውያን 13:15) በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ምሥራቹን በመስበኩና ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ሰዎችን ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ተጠምደዋል። (ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20) በዚህ መንገድ በዓለም ዙሪያ ለአምላክ ቀንና ሌሊት የውዳሴ መሥዋዕት እያቀረቡ ነው።—ራእይ 7:15
ከስብከቱ ሥራ በተጨማሪ አምላክን ከሚያስደስቱት መሥዋዕቶች አንዱ ለሌሎች መልካም ማድረግ ነው። ጳውሎስ “መልካም ማድረግንና ያላችሁንም ከሌሎች ጋር መካፈልን አትርሱ፤ እግዚአብሔር ደስ የሚሰኘው እንደዚህ ባለው መሥዋዕት ነውና” የሚል ምክር ሰጥቷል። (ዕብራውያን 13:16) ለአምላክ የውዳሴ መሥዋዕት የሚያቀርቡት ሰዎች መሥዋዕታቸው እርሱን የሚያስደስት እንዲሆን ከፈለጉ ምግባራቸው መልካም መሆን አለበት። ጳውሎስ “ለክርስቶስ ወንጌል እንደሚገባ ኑሩ” የሚል ምክር ለግሷል።—ፊልጵስዩስ 1:27፤ ኢሳይያስ 52:11
ቀደም ባሉት ዘመናት እንደነበረው ሁሉ አሁንም በእውነተኛው አምልኮ ውስጥ የሚቀርቡ መሥዋዕቶች በሙሉ ከፍተኛ ደስታና የይሖዋን በረከት ያስገኛሉ። እንግዲያው አምላክን የሚያስደስቱ መሥዋዕቶች ለማቅረብ የተቻለንን ሁሉ እናድርግ!
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
‘ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን ለከነዓን ጣዖታት ሠዉአቸው’
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እውነተኛ ክርስቲያኖች ምሥራቹን በመስበክና በሌሎች መንገዶች ሰዎችን በመርዳት አምላክን የሚያስደስቱ መሥዋዕቶች ያቀርባሉ