አፍቃሪ ለሆኑት እረኞች በትሕትና ተገዙ
አፍቃሪ ለሆኑት እረኞች በትሕትና ተገዙ
“ለመሪዎቻችሁ ታዘዙ፤ ተገዙላቸውም።”—ዕብራውያን 13:17
1, 2. ይሖዋና ኢየሱስ አፍቃሪ እረኞች መሆናቸውን የትኞቹ ጥቅሶች ያሳያሉ?
ይሖዋ አምላክና ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ አፍቃሪ እረኞች ናቸው። ኢሳይያስ እንዲህ በማለት ተንብዮአል:- “እነሆ፤ ልዑል እግዚአብሔር በኀይል ይመጣል፤ ክንዱ ስለ እርሱ ይገዛል። . . . መንጋውን እንደ እረኛ ያሰማራል፤ ጠቦቶቹን በክንዱ ይሰበስባል፤ በዕቅፉም ይይዛቸዋል፤ የሚያጠቡትንም በጥንቃቄ ይመራል።”—ኢሳይያስ 40:10, 11
2 ስለ መልሶ መቋቋም የተነገረው ይህ ትንቢት በ537 ከክርስቶስ ልደት በፊት አይሁዳውያን ቀሪዎች ወደ ይሁዳ በተመለሱበት ወቅት የመጀመሪያ ፍጻሜውን አግኝቷል። (2 ዜና መዋዕል 36:22, 23) ከዚህም በተጨማሪ በ1919 ቅቡዓን ቀሪዎች በታላቁ ቂሮስ ማለትም በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ‘ከታላቂቱ ባቢሎን’ ነጻ በወጡበት ወቅት ለሁለተኛ ጊዜ ፍጻሜውን አግኝቷል። (ራእይ 18:2፤ ኢሳይያስ 44:28) ይሖዋ በጎቹን ለመግዛት፣ ለመሰብሰብ እንዲሁም በፍቅር ለመምራት የሚጠቀመው “ክንዱ” በሆነው በኢየሱስ ነው። ኢየሱስ ራሱ “መልካም እረኛ እኔ ነኝ፤ በጎቼን ዐውቃለሁ፤ እነርሱም ያውቁኛል” በማለት ተናግሯል።—ዮሐንስ 10:14
3. ይሖዋ በጎቹ የሚያዙበትን መንገድ በተመለከተ ፍቅራዊ አሳቢነት ያሳየው እንዴት ነው?
3 በኢሳይያስ 40:10, 11 ላይ ያለው ትንቢት ይሖዋ ሕዝቦቹን በፍቅር እንደሚመራቸው ጎላ አድርጎ ይገልጻል። (መዝሙር 23:1-6) ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ወቅት ለደቀ መዛሙርቱ ብሎም ለሰው ልጆች በሙሉ ጥልቅ አሳቢነት አሳይቷል። (ማቴዎስ 11:28-30፤ ማርቆስ 6:34) በጥንቷ እስራኤል የነበሩት እረኞች ወይም መሪዎች በእነርሱ ጥበቃ ሥር ያለውን መንጋ ያላንዳች ኃፍረት ችላ በማለታቸውና በጭካኔ በመበዝበዛቸው ይሖዋም ሆነ ኢየሱስ አውግዘዋቸዋል። (ሕዝቅኤል 34:2-10፤ ማቴዎስ 23:3, 4, 15) ይሖዋ እንደሚከተለው ሲል ቃል ገብቷል:- “እኔ መንጋዬን አድናለሁ፤ ከእንግዲህ ለንጥቂያ አይዳረጉም፤ በአንዱ በግና በሌላውም በግ መካከል እፈርዳለሁ። በእነርሱ ላይ አንድ እረኛ፣ ባሪያዬን ዳዊትን አቆማለሁ፤ እርሱም ያሰማራቸዋል፤ እረኛቸውም ይሆናል።” (ሕዝቅኤል 34:22, 23) በዚህ የመጨረሻ ዘመን ይሖዋ በምድር ላይ በሚኖሩት አገልጋዮቹ ማለትም በመንፈስ በተቀቡ ክርስቲያኖችም ሆነ ‘በሌሎች በጎች’ ላይ የሾመው ‘አንድ እረኛ’ ታላቁ ዳዊት ማለትም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።—ዮሐንስ 10:16
ይሖዋ ለጉባኤ የሰጣቸው ስጦታዎች
4, 5. (ሀ) ይሖዋ በምድር ላይ ለሚኖሩት ሕዝቦቹ ምን ውድ ስጦታ ሰጥቷል? (ለ) ኢየሱስ ለጉባኤው የሰጠው ስጦታ ምንድን ነው?
4 ይሖዋ በምድር ላይ ላሉት አገልጋዮቹ ‘አንድ እረኛ’ የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን በማስነሳት ለክርስቲያን ጉባኤ ውድ ስጦታ ሰጥቷል። ይሖዋ ስጦታ አድርጎ የሰጠው በሰማይ የሚኖረው ይህ መሪ በኢሳይያስ 55:4 ላይ “እነሆ፤ እርሱን ለሕዝቦች ምስክር፣ መሪ፣ የጦር አዝማችም አድርጌዋለሁ” የሚል ትንቢት ተነግሮለት ነበር። ቅቡዓን ክርስቲያኖችም ሆኑ ‘እጅግ ብዙ ሕዝቦች’ የተሰበሰቡት ከሕዝብ፣ ከነገድ፣ ከወገንና ከቋንቋ ነው። (ራእይ 5:9, 10፤ 7:9) ይሁንና ‘በአንድ እረኛ’ የሚመራ “አንድ መንጋ” በመሆን ዓለም አቀፋዊ ጉባኤ መሥርተዋል።
5 ኢየሱስም በበኩሉ በምድር ላይ ለሚገኘው ጉባኤው ውድ የሆኑ ስጦታዎችን ሰጥቷል። ኢየሱስ የእርሱንና የይሖዋን ምሳሌ በመከተል መንጋውን በፍቅር የሚጠብቁ ታማኝ የበታች እረኞችን ሾሟል። ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን ለሚገኙ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ እነዚህን ፍቅራዊ ስጦታዎች አስመልክቶ እንዲህ ብሏል:- “‘ወደ ላይ በወጣ ጊዜ፣ ምርኮ ማረከ፤ ለሰዎችም ስጦታን [“ስጦታ የሆኑ ወንዶችን፣” NW] ሰጠ።’ አንዳንዶቹ ሐዋርያት፣ አንዳንዶቹ ነቢያት፣ አንዳንዶቹም ወንጌል ሰባኪዎች፣ ሌሎቹ ደግሞ እረኞችና አስተማሪዎች ይሆኑ ዘንድ የሰጠ እርሱ ነው፤ ይኸውም የክርስቶስ አካል ይገነባ ዘንድ፣ ቅዱሳንን ለአገልግሎት ሥራ ለማዘጋጀት [ነው]።”—ኤፌሶን 4:8, 11, 12
6. የሽማግሌዎች አካል ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩት ቅቡዓን የበላይ ተመልካቾች በራእይ 1:16, 20 ላይ እንዴት ተደርገው ተገልጸዋል? የሌሎች በጎች አባላት ስለሆኑት የተሾሙ ሽማግሌዎችስ ምን ለማለት ይቻላል?
6 እነዚህ “ስጦታ የሆኑ ወንዶች” በጎቹን በፍቅር እንዲጠብቁ ይሖዋና ልጁ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት የሾሟቸው የበላይ ተመልካቾች ወይም ሽማግሌዎች ናቸው። (የሐዋርያት ሥራ 20:28, 29) ቀደም ባሉት ጊዜያት ሁሉም የበላይ ተመልካቾች በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያን ወንዶች ነበሩ። በቅቡዓን ክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የሽማግሌዎች አካላት በመሆን ሲያገለግሉ የነበሩት እነዚህ ወንዶች በራእይ 1:16, 20 ላይ በክርስቶስ ቀኝ እጅ ውስጥ እንዳሉ “ከዋክብት” ወይም “መላእክት” ተደርገው ተገልጸዋል። ይህም በቁጥጥሩ ሥር መሆናቸውን ያመለክታል። ይሁንና በዚህ የመጨረሻ ዘመን፣ በመንፈስ የተቀቡት የበላይ ተመልካቾች ቁጥር እያሽቆለቆለ በመሄዱ በጉባኤዎች ውስጥ የሚገኙ አብዛኞቹ ክርስቲያን ሽማግሌዎች የሌሎች በጎች ክፍል ናቸው። እነዚህ ሽማግሌዎች የሚሾሙት የበላይ አካሉ በወከላቸው ሰዎች አማካኝነትና በመንፈስ ቅዱስ መሪነት በመሆኑ እነርሱም በመልካሙ እረኛ በኢየሱስ ክርስቶስ ቀኝ እጅ ውስጥ (በእርሱ አመራር ሥር) ናቸው ማለት ይቻላል። (ኢሳይያስ 61:5, 6) በጉባኤያችን ያሉት ሽማግሌዎች የጉባኤው ራስ ለሆነው ለክርስቶስ ስለሚገዙ ሙሉ ትብብር ልናደርግላቸው ይገባል።—ቈላስይስ 1:18
ለበታች እረኞች መታዘዝና መገዛት
7. ሐዋርያው ጳውሎስ ለክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች ሊኖረን ስለሚገባው አመለካከት ምን ምክር ሰጥቷል?
7 በሰማይ ያሉት እረኞቻችን ማለትም ይሖዋ አምላክና ኢየሱስ ክርስቶስ በጉባኤ ውስጥ በኃላፊነት ቦታ ላይ ላስቀመጧቸው የበታች እረኞች እንድንታዘዝና እንድንገዛ ይጠብቁብናል። (1 ጴጥሮስ 5:5) ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ ተነሳስቶ እንደሚከተለው ሲል ጽፏል:- “የእግዚአብሔርን ቃል የነገሯችሁን መሪዎቻችሁን ዐስቡ፤ የኑሮአቸውን ፍሬ ተመልከቱ፤ በእምነታቸውም ምሰሉአቸው። ለመሪዎቻችሁ ታዘዙ፤ ተገዙላቸውም። ምክንያቱም እነርሱ በብርቱ የሚያስጠይቃቸው ነገር ስላለባቸው፣ ስለ ነፍሳችሁ ጒዳይ ይተጋሉ። ስለዚህ ሥራቸውን በሐዘን ሳይሆን በደስታ ማከናወን እንዲችሉ ታዘዟቸው። አለበለዚያ አይበጃችሁም።”—ዕብራውያን 13:7, 17
8. ጳውሎስ ስለምን ነገር ‘እንድንመለከት’ አበረታቶናል? ‘ታዛዥ’ መሆን ያለብን ለምንድን ነው?
8 ጳውሎስ፣ ሽማግሌዎች በአኗኗራቸው ታማኝ መሆናቸው ያስገኘላቸውን ውጤት ‘እንድንመለከት’ ወይም በጥንቃቄ እንድንመረምር እንዲሁም በእምነታቸው እንድንመስላቸው አበረታቶናል። ከዚህም በላይ፣ ለእነዚህ የተሾሙ ወንዶች እንድንታዘዝና ለሚሰጡን መመሪያ እንድንገዛ መክሮናል። የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር የሆኑት ሪቻርድ ፍራንስ እንደገለጹት በዚህ ጥቅስ ላይ “ታዘዙ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “መታዘዝን ለማመልከት የሚሠራበት የተለመደው ቃል” አይደለም። “ከዚህ ይልቅ ይህ ቃል በቀጥታ ሲተረጎም ‘አምናችሁ ተቀበሉ’ ማለት ሲሆን ይህም የሽማግሌዎችን የመሪነት ቦታ በፈቃደኝነት መቀበልን ያመለክታል።” ሽማግሌዎችን የምንታዘዘው የአምላክ ቃል እንዲህ እንድናደርግ ስለሚያሳስበን ብቻ ሳይሆን ስለመንግሥቱ ፍላጎትና ስለደህንነታችን ከልብ የሚጨነቁ መሆናቸውን ስለምንገነዘብም ጭምር ነው። የሽማግሌዎችን የመሪነት ቦታ በፈቃደኝነት አምነን መቀበላችን ደስታ እንደሚያመጣልን ጥርጥር የለውም።
9. ታዛዥ ከመሆን በተጨማሪ ‘መገዛት’ ያለብን ለምንድን ነው?
9 ይሁንና በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ሽማግሌዎች ከሚሰጡት መመሪያ የተሻለ አማራጭ እንዳለ ሆኖ ቢሰማንስ? መገዛት የሚያስፈልገው እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች በሚገጥሙን ጊዜ ነው። ግልጽ ለሆኑልንና ለምንስማማባቸው መመሪያዎች ወይም ውሳኔዎች መታዘዝ ቀላል ነው፤ ይሁንና መመሪያው ግልጽ በማይሆንልን ጊዜም እንኳ ለመገዛት ፈቃደኞች መሆን ይኖርብናል። ከጊዜ በኋላ ሐዋርያ የሆነው ጴጥሮስ እንዲህ ዓይነት የተገዥነት ባሕርይ አሳይቷል።—ሉቃስ 5:4, 5
ለመተባበር ፈቃደኞች እንድንሆን የሚያነሳሱን አራት ምክንያቶች
10, 11. በመጀመሪያው መቶ ዘመንም ሆነ በዛሬው ጊዜ የበላይ ተመልካቾች ለእምነት አጋሮቻቸው ‘የአምላክን ቃል የተናገሩት’ በምን መንገድ ነው?
10 ቀደም ሲል በተጠቀሰው ጥቅስ ማለትም በዕብራውያን 13:7, 17 ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ ለክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች እንድንታዘዝና እንድንገዛ የሚገፋፉንን አራት ምክንያቶች ዘርዝሯል። በመጀመሪያ ደረጃ፣ ‘የአምላክን ቃል ነግረውናል።’ ኢየሱስ እነዚህን ስጦታ የሆኑ ወንዶች ለጉባኤው የሰጠው “ቅዱሳንን ለአገልግሎት ሥራ ለማዘጋጀት” ወይም ለማስተካከል መሆኑን አትዘንጉ። (ኤፌሶን 4:11, 12) ኢየሱስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖሩ የነበሩትን ክርስቲያኖች አስተሳሰብና ሥነ ምግባር ለማስተካከል ታማኝ በሆኑ የበታች እረኞች ተጠቅሟል። ከእነዚህ እረኞች መካከል አንዳንዶቹ በመንፈስ ተመርተው ለጉባኤዎች ደብዳቤዎችን ጽፈዋል። ኢየሱስ የጥንት ክርስቲያኖችን ለመምራትና እምነታቸውን ለማጠናከር በመንፈስ በተቀቡት በእነዚህ የበላይ ተመልካቾች ተጠቅሟል።—1 ቆሮንቶስ 16:15-18፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:2፤ ቲቶ 1:5
11 በዛሬው ጊዜ ኢየሱስ ‘ታማኝና ልባም ባሪያን’ በሚወክሉት በበላይ አካሉና በተሾሙ ሽማግሌዎች አማካኝነት ይመራናል። (ማቴዎስ 24:45 የ1954 ትርጉም) “የእረኞች አለቃ” ለሆነው ለኢየሱስ ክርስቶስ ያለን አክብሮት፣ ጳውሎስ ‘በእናንተ መካከል በትጋት የሚሠሩትን፣ በጌታም የበላዮቻችሁና መካሪዎቻችሁ የሆኑትን አክብሯቸው’ በማለት የሰጠንን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ ያነሳሳናል።—1 ጴጥሮስ 5:4፤ 1 ተሰሎንቄ 5:12፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:17
12. የበላይ ተመልካቾች ‘ስለ ነፍሳችን የሚተጉት’ እንዴት ነው?
12 ከክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች ጋር እንድንተባበር የሚያነሳሳን ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ‘ስለ ነፍሳችን የሚተጉ’ መሆናቸው ነው። እነዚህ የበላይ ተመልካቾች መንፈሳዊነታችንን አደጋ ላይ የሚጥል አንድ ዓይነት ዝንባሌ ወይም ባሕርይ ማሳየት እንደጀመርን ከተገነዘቡ ወዲያውኑ አስፈላጊውን ምክር ይሰጡናል። ይህን የሚያደርጉትም እኛን ለማስተካከል በማሰብ ነው። (ገላትያ 6:1) “ይተጋሉ” ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል በቀጥታ ሲተረጎም “እንቅልፍ አጥተው ያድራሉ” የሚል ፍቺ አለው። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑር እንዳሉት ይህ ቃል “እረኛው ሁልጊዜ ንቁ መሆኑን ያመለክታል።” ሽማግሌዎች በመንፈሳዊ ንቁ ሆነው ከመኖር ባሻገር ስለ እኛ መንፈሳዊ ደህንነት በማሰብ እንቅልፍ አጥተው ሊያድሩ ይችላሉ። ታዲያ፣ ‘ታላቅ እረኛ’ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ያሳየውን ጥልቅ አሳቢነት ለመኮረጅ ከልብ ከሚጥሩት ከእነዚህ አፍቃሪ እረኞች ጋር በፈቃደኝነት መተባበር አይገባንም?—ዕብራውያን 13:20
13. የበላይ ተመልካቾችም ሆኑ ሁሉም ክርስቲያኖች በማን ዘንድ ተጠያቂዎች ናቸው? የሚያስጠይቃቸውስ ምንድን ነው?
13 ከክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች ጋር እንድንተባበር የሚያነሳሳን ሦስተኛው ምክንያት ደግሞ “በብርቱ የሚያስጠይቃቸው ነገር ስላለ” ነው። የበላይ ተመልካቾች በሰማይ ባሉት እረኞች ማለትም በይሖዋና በኢየሱስ ሥር ሆነው የሚያገለግሉ የበታች እረኞች መሆናቸውን አይዘነጉም። (ሕዝቅኤል 34:22-24) የበጎቹ ባለቤት ይሖዋ ሲሆን እርሱም ‘በገዛ ልጁ ደም ዋጅቷቸዋል፤’ በመሆኑም የተሾሙ የበላይ ተመልካቾች በጎቹን ይሖዋ በሚይዝበት መንገድ ማለትም ‘በርኅራሄ’ ስለመያዛቸው ይጠየቁበታል። (የሐዋርያት ሥራ 20:28, 29 የታረመው የ1980 ትርጉም) ይህም በመሆኑ ሁላችንም ብንሆን ከይሖዋ ለምናገኘው መመሪያ የምንሰጠውን ምላሽ በተመለከተ በእርሱ ዘንድ ተጠያቂዎች ነን። (ሮሜ 14:10-12) ከዚህም በተጨማሪ፣ ለተሾሙ ሽማግሌዎች መታዘዛችን የጉባኤው ራስ ለሆነው ለክርስቶስ እንደምንገዛ ያሳያል።—ቈላስይስ 2:19
14. ክርስቲያን ሽማግሌዎች “በሐዘን” እንዲያገለግሉ ምክንያት የሚሆነው ነገር ምን ሊሆን ይችላል? ይህስ ምን ውጤት ይኖረዋል?
14 ጳውሎስ ለክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች በትሕትና መገዛት አስፈላጊ የሆነበትን አራተኛ ምክንያት ሲገልጽ “ስለዚህ ሥራቸውን በሐዘን ሳይሆን በደስታ ማከናወን እንዲችሉ ታዘዟቸው። አለበለዚያ አይበጃችሁም” በማለት ጽፏል። (ዕብራውያን 13:17) ክርስቲያን ሽማግሌዎች ማስተማርን፣ እረኝነትን፣ በስብከቱ ሥራ ግንባር ቀደም መሆንን፣ ልጆቻቸውን ማሳደግን እንዲሁም በጉባኤ ውስጥ ለሚነሱ ችግሮች እልባት መስጠትን የመሳሰሉ ከባድ ኃላፊነቶች አሉባቸው። (2 ቆሮንቶስ 11:28, 29) ከሽማግሌዎች ጋር የማንተባበር ከሆነ ተጨማሪ ሸክም እንሆንባቸዋለን። ይህም ‘እንዲያዝኑ’ ምክንያት ይሆናል። የትብብር መንፈስ የማናሳይ ከሆነ ይሖዋን የምናሳዝን ከመሆኑም ባሻገር ለእኛም አይበጀንም። ከዚህ ይልቅ ተገቢ የሆነ አክብሮትና የትብብር መንፈስ ማሳየታችን ሽማግሌዎች ሥራቸውን በደስታ እንዲያከናውኑ ያደርጋል፤ እንዲሁም በመካከላችን አንድነት እንዲኖርና በመንግሥቱ ስብከት ሥራ በደስታ እንድንካፈል ይረዳናል።—ሮሜ 15:5, 6
ተገዥ መሆናችንን በተግባር ማሳየት
15. ታዛዥና ተገዥ መሆናችንን እንዴት ማሳየት እንችላለን?
15 ከተሾሙ የበላይ ተመልካቾች ጋር መተባበራችንን የምናሳይባቸው በርካታ መንገዶች አሉ። የጉባኤያችን ሽማግሌዎች በአገልግሎት ክልላችን ውስጥ በተከሰተ አዲስ ሁኔታ ምክንያት ቀኑም ሆነ ሰዓቱ ከእኛ ሁኔታ ጋር የማይስማማ ብሎም አንዳንድ ማስተካከያዎችን ማድረግ የሚጠይቅብን የአገልግሎት ስምሪት ስብሰባ ፕሮግራም አውጥተው ይሆን? ይህን ዝግጅት ለመደገፍ ጥረት እናድርግ። እንዲህ ማድረጋችን ያልተጠበቀ በረከት ያስገኝልን ይሆናል። የአገልግሎት የበላይ ተመልካቹ እኛ ያለንበትን የመጽሐፍ ጥናት ቡድን እየጎበኘ ነው? ከሆነ፣ በዚያ ሳምንት በሚደረገው የስብከት ሥራ ላይ የተቻለንን ያህል ተሳትፎ እናድርግ። በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ክፍል እንድናቀርብ ተሰጥቶናል? በቦታው ተገኝተን ክፍላችንን በተገቢው መንገድ ለማቅረብ የቻልነውን ሁሉ እንጣር። የመጽሐፍ ጥናት የበላይ ተመልካቹ የመንግሥት አዳራሹን የማጽዳት ተራው የእኛ እንደሆነ ማስታወቂያ ተናግሯል? እንዲህ ከሆነ ጤንነታችንና አቅማችን በፈቀደልን መጠን ከእርሱ ጋር ልንተባበር ይገባል። በእነዚህና በሌሎችም በርካታ መንገዶች ይሖዋና ልጁ መንጋውን እንዲጠብቁ ለሾሟቸው ወንዶች እንደምንገዛ እናሳያለን።
16. አንድ ሽማግሌ አንድን ነገር በመመሪያው መሠረት አለማከናወኑ ለማመጽ ምክንያት የማይሆነን ለምንድን ነው?
16 አንዳንድ ጊዜ አንድ ሽማግሌ፣ ታማኙ ባሪያና የበላይ አካሉ ከሚሰጡት መመሪያ በተለየ መንገድ ነገሮችን ያከናውን ይሆናል። እንዲህ ማድረጉን ከቀጠለ ‘የነፍሳችን እረኛና ጠባቂ’ በሆነው በይሖዋ ፊት ተጠያቂ መሆኑ አይቀርም። (1 ጴጥሮስ 2:25) ይሁንና አንዳንድ ሽማግሌዎች ጥፋት ማጥፋታቸው አሊያም ስህተት መሥራታቸው ላለመታዘዝ ሰበብ አይሆነንም። ይሖዋ ታዛዥ ያልሆኑትንና ዓመጸኞችን አይባርክም።—ዘኍልቍ 12:1, 2, 9-11
ይሖዋ ለመተባበር ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎችን ይባርካል
17. ለበላይ ተመልካቾች ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል?
17 ይሖዋ አምላክ የበላይ ተመልካቾች አድርጎ የሾማቸው ወንዶች ፍጹም አለመሆናቸውን ያውቃል። ይሁን እንጂ ይሖዋ በእነዚህ የበላይ ተመልካቾች ይጠቀማል፤ ከዚህም በላይ በመንፈሱ አማካኝነት በምድር ላይ ያሉ ሕዝቦቹን ይመራቸዋል። ሽማግሌዎችም ሆኑ ሁላችንም ያገኘነው ይህ “እጅግ ታላቅ ኀይል ከእግዚአብሔር እንጂ ከእኛ አለመሆኑ” ግልጽ ነው። (2 ቆሮንቶስ 4:7) ስለሆነም ይሖዋ ታማኝ በሆኑት የበላይ ተመልካቾቻችን ተጠቅሞ ለሚያከናውንልን ነገሮች አመስጋኞች መሆን ይኖርብናል። እንዲሁም ከእነዚህ የበላይ ተመልካቾች ጋር በፈቃደኝነት መተባበር ይገባናል።
18. ለበላይ ተመልካቾች መገዛታችን ምን እንዳለን ያሳያል?
18 የበላይ ተመልካቾች፣ ይሖዋ በመጨረሻው ዘመን በመንጋው ላይ የሚሾማቸውን እረኞች አስመልክቶ በኤርምያስ 3:15 ላይ ባሰፈረው ሐሳብ መሠረት ለመመላለስ ትጋት የተሞላበት ጥረት ያደርጋሉ። ትንቢቱ “እንደ ልቤም የሆኑ፣ በዕውቀትና በማስተዋል የሚመሯችሁን እረኞች እሰጣችኋለሁ” ይላል። በመካከላችን የሚገኙት ሽማግሌዎች የይሖዋን በጎች በማስተማርና በመጠበቅ የሚያስመሰግን ሥራ በማከናወን ላይ ይገኛሉ። በመሆኑም የትብብር መንፈስ በማሳየት እንዲሁም ለእነርሱ በመታዘዝና በመገዛት ለሚያከናውኑት ከባድ ሥራ አመስጋኞች መሆናችንን ማሳየት እንችላለን። ይህን ማድረጋችን በሰማይ ለሚኖሩት እረኞቻችን ማለትም ለይሖዋ አምላክና ለኢየሱስ ክርስቶስ አድናቆት እንዳለን ያሳያል።
ለክለሳ ያህል
• ይሖዋና ኢየሱስ ክርስቶስ አፍቃሪ እረኞች መሆናቸውን ያሳዩት እንዴት ነው?
• ታዛዥ ከመሆን በተጨማሪ ተገዥ መሆን ያለብን ለምንድን ነው?
• ተገዥ መሆናችንን በተግባር ማሳየት የምንችልባቸው ምን ተግባራዊ መንገዶች አሉ?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ክርስቲያን ሽማግሌዎች ለክርስቶስ አመራር ይገዛሉ
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ ለሾማቸው እረኞች መገዛታችንን የምናሳይባቸው በርካታ መንገዶች አሉ