በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ ሕይወቴን ቀርጾታል

ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ ሕይወቴን ቀርጾታል

የሕይወት ታሪክ

ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ ሕይወቴን ቀርጾታል

ሊኔት ፒተርስ እንደተናገረችው

አገሪቷን ለቅቀን እንድንወጣ ለመርዳት ወታደሮች መጥተው ነበር። በሕንፃው አናት ላይ አነጣጣሪ ተኳሽ የሆነ ወታደር ቆሟል። ሌሎች ወታደሮች ደግሞ ሣሩ ላይ ተኝተው ጠመንጃዎቻቸውን ደግነው ይጠብቁን ነበር። ይህ የሆነው አንድ እሁድ ጠዋት ላይ ሲሆን እኔና ሌሎች ሚስዮናውያን ወደሚጠብቀን ሄሊኮፕተር እየሮጥን በምንሄድበት ወቅት ራሳችንን ለማረጋጋት መታገል ነበረብን። ወዲያው ሄሊኮፕተሩ መብረር ጀመረ። ከአሥር ደቂቃ በኋላ በባሕሩ ዳርቻ አካባቢ ቆማ በነበረች የወታደር መርከብ ላይ በሰላም ተሳፈርን።

በንጋታው፣ ዓማጺያን ከዚያ ቀን በፊት ያደርንበትን ሆቴል በቦምብ እንደደበደቡት ሰማን። ሴራሊዮንን ለዓመታት ሲያምሳት የነበረው የሕዝብ ዓመጽ ተባብሶ በመጨረሻ ጦርነት በመቀስቀሱ እኛን ጨምሮ የውጪ አገር ዜጎች በሙሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ አገሪቱን ለቅቀን እንድንወጣ ተደረግን። በዚህ ሁኔታ ውስጥ እንዴት ልገባ እንደቻልኩ ከመጀመሪያው አንስቼ ላውጋችሁ።

ያደግሁት በብሪቲሽ ጊያና (ከ1966 ጀምሮ ጋያና ተብላለች) ሲሆን በ1950ዎቹ ዓመታት የልጅነት ሕይወቴን ያሳለፍኩት ያላንዳች ጭንቀት በደስታ ነበር። በጊዜው አብዛኞቹ ወላጆች ለትምህርት ከፍተኛ ቦታ የሚሰጡ ሲሆን ወጣቶችም በትምህርት ቤት ጥሩ ውጤት እንዲያመጡ ይጠበቅባቸው ነበር። በአንድ ወቅት አንድ የባንክ ሠራተኛ አባቴን “ለልጆችህ ትምህርት ቤት ይህን ያህል ብዙ ገንዘብ የምትከፍለው ለምንድን ነው?” በማለት ጠይቆት እንደነበር አስታውሳለሁ። አባቴም “በሕይወታቸው ስኬታማ መሆን የሚችሉት ጥሩ ትምህርት ካገኙ ብቻ ነው” በማለት መለሰለት። በዚያን ጊዜ ጥሩ ትምህርት ማግኘት የሚቻለው ስመ ጥር በሆኑ ትምህርት ቤቶች ውስጥ እንደሆነ ያስብ ነበር። ብዙም ሳይቆይ ግን አመለካከቱ ተለወጠ።

የአሥራ አንድ ዓመት ልጅ ሳለሁ እናቴ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረች። ከአንዲት ጎረቤታችን ጋር ሆነው ወደ መንግሥት አዳራሽ ሄደው ነበር። በዚያን ምሽት ስብሰባው ላይ የሰሙት ነገር ሁለቱም እውነትን እንዳገኙ እንዲያምኑ አደረጋቸው። ቆየት ብሎም እናቴ የሰማችውን ነገር ለሌላ ጎረቤታችን ነገረቻት። ብዙም ሳይቆይ ዳፍኒ ሃሪ (በኋላ ዳፍኒ ባርድ ሆናለች) እና ሮዝ ከፊ ከተባሉ ሚስዮናውያን ጋር ሦስቱም ማጥናት ጀመሩ። እናቴና ሁለት ጓደኞቿ አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ተጠመቁ። ይህ ከሆነ ከአምስት ዓመት በኋላ አባቴ የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያንን ለቅቆ ወጣና ራሱን ለአምላክ ወስኖ በመጠመቅ የይሖዋ ምሥክር ሆነ።

በቤተሰባችን ውስጥ ካሉት አሥር ልጆች መካከል ትልልቆች የሆንነው እኔና ሁለት ታናናሽ እህቶቼ ልጆች እያለን ዳፍኒና ሮዝ በሚኖሩበት የሚስዮናውያን ቤት ውስጥ አስደሳች ጊዜያት አሳልፈናል። በእነዚያ ወቅቶች በአገልግሎት ያጋጠሟቸውን ተሞክሮዎች ሲያወሩ እንሰማ ነበር። እነዚህ ሚስዮናውያን ሌሎችን በመንፈሳዊ ለመርዳት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በመሥራት ይደሰቱ ነበር። ሚስዮናዊ የመሆን ፍላጎት እንዲያድርብኝ ያደረገው የእነርሱ ምሳሌነት ነው።

ይሁን እንጂ ዘመዶቼና የትምህርት ቤት ጓደኞቼ በሙሉ ተጨማሪ ትምህርት ተከታትለው ጥሩ ሥራ በማግኘት ላይ ትኩረት ሲያደርጉ እኔ ግን የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን ግቤ አድርጌ እንድቀጥል የረዳኝ ምንድን ነው? በሕግ፣ በሙዚቃ፣ በሕክምና ወይም በሌላ በማንኛውም መስክ ትምህርቴን መከታተል እችል ስለነበር በርካታ ፈታኝ አጋጣሚዎች ተዘርግተውልኝ ነበር። የወላጆቼ ግሩም ምሳሌነት ትክክለኛውን አቅጣጫ ለመከተል እንድችል ረድቶኛል። እውነትን በሕይወታቸው ውስጥ ተግባራዊ ያደርጉ፣ መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት ያጠኑ እንዲሁም ሌሎች ስለ ይሖዋ እንዲያውቁ ለመርዳት ራሳቸውን ያቀርቡ ነበር። a ከዚህም በላይ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮችን ዘወትር ቤታችን ይጋብዙ ነበር። እነዚህ ወንድሞችና እህቶች ያላቸው ደስታና እርካታ ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ ሕይወቴን እንዲቀርጸው ያለኝን ፍላጎት አጠናክሮልኛል።

አሥራ አምስት ዓመት ሲሆነኝ ተጠመቅሁ። ከዚያም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን እንደጨረስኩ አቅኚ ሆኜ በማገልገል በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መካፈል ጀመርኩ። ራሳቸውን ወስነው እንዲጠመቁ ከረዳኋቸው ሰዎች መካከል የመጀመሪያዋ ፊሎሚና የተባለች በሆስፒታል ውስጥ የምትሠራ አንዲት ሴት ናት። ፊሎሚና ለይሖዋ ፍቅር ስታዳብር መመልከቴ ያስገኘልኝ ደስታ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመቀጠል ያለኝን ፍላጎት አጠናክሮታል። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ጸሐፊ ሆኜ በምሠራበት የመንግሥት መሥሪያ ቤት ውስጥ እድገት አገኘሁ። ሆኖም በአቅኚነት ለመቀጠል ስለፈለግሁ የተሰጠኝን እድገት ለመቀበል ፈቃደኛ አልሆንኩም።

በዚያን ጊዜ የምኖረው ከቤተሰቤ ጋር ሲሆን ሚስዮናውያኑም እየመጡ ይጠይቁን ነበር። የእነርሱን ተሞክሮ ማዳመጥ በጣም ያስደስተኝ ነበር! ምንም እንኳ በሚስዮናዊነት ማገልገል የማይቻል ነገር ቢመስልም እነዚህ ሁኔታዎች ሚስዮናዊ ለመሆን የነበረኝን ፍላጎት ይበልጥ አጠናከሩልኝ። በዚያን ጊዜ ሚስዮናውያን ወደ ጋያና ይላኩ ነበር፤ አሁንም ቢሆን በዚያች አገር ሚስዮናውያን ይመደባሉ። በ1969 በብሩክሊን ኒው ዮርክ በሚገኘው የጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት እንድካፈል የሚጋብዝ ደብዳቤ ሲደርሰኝ ብገረምም በጣም ተደስቼ ነበር።

ያልጠበቅሁት ምድብ

በጊልያድ ትምህርት ቤት በ48ኛው ክፍል ውስጥ ከ21 አገሮች የመጡ 54 ተማሪዎች ነበሩ። ከእነዚህ መካከል አሥራ ሰባታችን ያላገባን እህቶች ነበርን። በትምህርት ቤቱ የተካፈልነው ከ37 ዓመታት በፊት ቢሆንም በእነዚያ አምስት ወራት ውስጥ ያሳለፍነውን ጊዜ አሁንም በደንብ አስታውሰዋለሁ። በትምህርት ቤቱ ውስጥ ብዙ ነገሮችን ተምረናል፤ ቅዱስ ጽሑፋዊ እውነቶችን ከመማራችንም በተጨማሪ ወደፊት ሚስዮናውያን ሆነን በምንመራው ሕይወት የሚረዱን ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ሐሳቦችና ምክሮች ይሰጡን ነበር። ለአብነት ያህል መመሪያዎችን መከተልን፣ ፋሽንን በተመለከተ ሚዛናዊ አመለካከት ማዳበርን እንዲሁም አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙኝም መጽናትን ተምሬያለሁ።

ወላጆቼ አዘውትሮ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ የመገኘትን አስፈላጊነት ጎላ አድርገው ይገልጹልን ነበር። እሁድ ዕለት አሞኛል ብሎ ከጉባኤ የቀረ ልጅ በቀጣዩ ምሽት የፒያኖ ወይም የሙዚቃ ዝግጅት መመልከት አይፈቀድለትም። ይሁን እንጂ በጊልያድ ትምህርት ቤት በነበርኩበት ወቅት ለተወሰነ ጊዜ ከአንዳንድ የጉባኤ ስብሰባዎች እቀር ነበር። ወደ ስብሰባ የሚወስዱኝ ዳን እና ደሎሬስ አደምስ የተባሉ ቤቴላውያን ባልና ሚስት አንድ ቀን ዓርብ ምሽት ወደሚካሄደው ስብሰባ ሊወስዱኝ ሲመጡ፣ የቤት ሥራ እንደበዛብኝና ሪፖርት መጻፍ እንዳለብኝ ነገርኳቸው። ታዲያ ይህ ሁሉ እያለኝ በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤትና በአገልግሎት ስብሰባ ላይ እንዴት መገኘት እችላለሁ? ወንድም አደምስ የተወሰነ ሐሳብ ከሰጠኝ በኋላ “እንግዲህ ሕሊናሽ የሚነግርሽን ተከተይ” አለኝ። የሰጠኝን ምክር በመከተል የዚያን ዕለትም ሆነ ከዚያ በኋላ ከስብሰባ ቀርቼ አላውቅም። ባለፉት ዓመታት ሁሉ ከአቅሜ በላይ የሆነ ችግር ካላጋጠመኝ በስተቀር ፈጽሞ ከክርስቲያናዊ ስብሰባዎች አልቀረሁም።

በሥልጠናው አጋማሽ አካባቢ ስለ ምድባችን ይወራ ጀመር። ሰባኪዎች በጣም በሚያስፈልጉበት በጋያና እንደምመደብ አስብ ነበር። ሆኖም ወደዚያ እንደማልመለስ ሳውቅ ምን ያህል እንደተገረምኩ መገመት ትችላላችሁ። ከዚህ ይልቅ በምዕራብ አፍሪካ ወደምትገኘው ወደ ሴራሊዮን ተላክሁ። ይሖዋ፣ ከትውልድ አገሬ ርቆ በሚገኝ አካባቢ በሚስዮናዊነት ለማገልገል የነበረኝን ፍላጎት ስላሟላልኝ ምንኛ አመስጋኝ ነበርኩ!

ብዙ ነገሮች ተምሬያለሁ

በርካታ ኮረብቶችና ተራሮች እንዲሁም የባሕር ወሽመጦችና የባሕር ዳርቻዎች ያሏትን ሴራሊዮንን ለመጀመሪያ ጊዜ ስመለከታት “እንዴት ውብ ናት” የሚል ስሜት አደረብኝ። በምዕራብ አፍሪካ የምትገኘው የዚህች አገር ሕዝቦች የሚያሳዩት ፍቅርና ደግነት ደግሞ ከመልክዓ ምድሩ የበለጠ ማራኪ ነው፤ የሕዝቡ አቀባበል የውጭ አገር ዜጎችም እንኳ አገራቸው እንዳሉ እንዲሰማቸው ያደርጋል። ይህም አዳዲስ ሚስዮናውያን የቤተሰባቸውን ናፍቆት መቋቋም እንዲችሉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው። የሴራሊዮን ሰዎች ስለ ባሕላቸው ማውራት የሚወዱ ሲሆን በተለይም አዳዲስ ሰዎች ክሪዮ የተባለውን የአገሪቱ የመግባቢያ ቋንቋ እንዲለምዱ መርዳት ያስደስታቸዋል።

የክሪዮ ቋንቋ ተናጋሪዎች ሐሳባቸውን ጥሩ አድርገው የሚገልጹ በርካታ አባባሎች አሏቸው። ለምሳሌ ‘ጦጣ ይሠራል፣ ዝንጀሮ ይበላል’ የሚለው አባባል አንድ ሰው የደከመበትን ሁልጊዜ እንደማያገኝ ያመለክታል። ይህ ምሳሌ፣ በዓለማችን ላይ ተስፋፍቶ የሚታየውን የፍትሕ መጓደል እንዴት ጥሩ አድርጎ ይገልጸዋል!—ኢሳይያስ 65:22

የስብከቱና ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ አስደሳች ነበር። አብዛኞቹ ሰዎች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ለማወቅ ይፈልጋሉ። ባለፉት ዓመታት ሁሉ ሚስዮናውያንና ይሖዋን ለረጅም ዓመታት ያገለገሉ ወንድሞች፣ ወጣት አረጋዊ ሳይሉ የተለያየ ጎሳ እና የኑሮ ደረጃ ያላቸው ሰዎች እውነትን እንዲያውቁ ረድተዋል።

በሚስዮናዊነት ሳገለግል የመጀመሪያ ጓደኛዬ የሆነችው ኧርላ ሴንት ሂል ደከመኝ የማታውቅ ታታሪ ሠራተኛ ነበረች። ለአገልግሎቷ ከፍተኛ ቅንዓት የነበራት ሲሆን በምንኖርበት የሚስዮናውያን ቤት ውስጥ ያሏትን ኃላፊነቶችም በትጋት ትወጣ ነበር። ከጎረቤቶቻችን ጋር መግባባት፣ የታመሙ ወንድሞችንና ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች መጠየቅ እንዲሁም የሚመቸኝ ከሆነ በቀብር ሥነ ሥርዓቶች ላይ መገኘትና እነዚህን የመሳሰሉ በርካታ ጉዳዮችን ማከናወን ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ እንድገነዘብ ረድታኛለች። ከዚህም በላይ በአንድ ክልል ውስጥ ሳገለግል ከቆየሁ በኋላ ክልሉን ለቅቄ ከመውጣቴ በፊት በአካባቢው የሚገኙትን ወንድሞችና እህቶች ለጥቂት ደቂቃዎችም ቢሆን ጠይቄያቸው ማለፌ አስፈላጊ እንደሆነ ትነግረኝ ነበር። እንዲህ በማድረጌ ብዙም ሳይቆይ እናቶች፣ ወንድሞች፣ እህቶችና ወዳጆች ማግኘት የቻልኩ ሲሆን የሚስዮናዊነት ምድቤም እንደ ትውልድ አገሬ ሆነልኝ።—ማርቆስ 10:29, 30

ከዚህም በላይ አብረውኝ ከሚያገለግሉት ግሩም ሚስዮናውያን ጋር ጠንካራ ወዳጅነት ለመመሥረት ችያለሁ። ከእነዚህም መካከል አብራኝ ትኖር የነበረችውና በ1978 እና በ1981 መካከል ባለው ጊዜ ውስጥ በሴራሊዮን ያገለገለችው አድና ቢርድ እንዲሁም ላለፉት 24 ዓመታት አብራኝ የኖረችው ሼረል ፈርገሰን ይገኙበታል።

የእርስ በርስ ጦርነት ያስከተለው ፈተና

በ1997 በሴራሊዮን የሚገኘው አዲስ ቅርንጫፍ ቢሮ ለይሖዋ አገልግሎት ከተወሰነ ከአንድ ወር ገደማ በኋላ በመግቢያው ላይ እንደጠቀስኩት ጦርነት በመነሳቱ አገሪቱን ለመልቀቅ ተገደድን። ይህ ከመሆኑ ከስድስት ዓመታት በፊት በላይቤሪያ በተነሳው ጦርነት ሳቢያ በዚያ የነበሩት ወንድሞች ወደ ሴራሊዮን ሸሽተው ሲመጡ ባሳዩት እምነት ተደንቀን ነበር። አንዳንዶቹ ወደ ሴራሊዮን የመጡት ምንም ሳይዙ ነው። የነበሩበት ሁኔታ አስቸጋሪ ቢሆንም በየቀኑ በአገልግሎት ይካፈሉ ነበር። እነዚህ ወንድሞች ለይሖዋና ለሰዎች ያላቸውን ፍቅር መመልከት ልብ ይነካል።

እኛም ራሳችን ጊኒ ወደ ተባለችው አገር ስንሰደድ የላይቤሪያ ወንድሞችን ምሳሌ በመከተል በይሖዋ ታምነን መንግሥቱን ማስቀደማችንን ቀጠልን። ከአንድ ዓመት በኋላ ወደ ሴራሊዮን መመለስ ብንችልም በሰባት ወር ጊዜ ውስጥ ውጊያው በመቀስቀሱ እንደገና ወደ ጊኒ ለመሸሽ ተገደድን።

ብዙም ሳይቆይ፣ ከተፋላሚዎቹ አንጃዎች የአንዱ አባላት በኪሲ በሚገኘው የሚስዮናውያን ቤታችን ውስጥ መኖር እንደጀመሩና ንብረቶቻችን በጠቅላላ እንደተዘረፉ ወይም እንደወደሙ ሰማን። በዚህ ሁኔታ ከማዘን ይልቅ በሕይወት በመትረፋችን ይሖዋን አመሰገንን። የነበሩን ንብረቶች በጣም ጥቂት ቢሆኑም ይህን አስቸጋሪ ጊዜ ለማለፍ ችለናል።

ለሁለተኛ ጊዜ ከሴራሊዮን ከወጣን በኋላ እኔና አብራኝ የምትኖረው ሼረል በጊኒ ቀረን። በዚህም የተነሳ የፈረንሳይኛ ቋንቋ መማር ነበረብን። አብረውኝ ከነበሩት ሚስዮናውያን አንዳንዶቹ፣ ፈረንሳይኛ ለመናገር ሲሞክሩ በሚሠሯቸው ስህተቶች ሳይጨነቁ የተማሩትን ወዲያው ይጠቀሙበት ነበር። እኔ ግን መሳሳት ስለማልፈልግ ፈረንሳይኛ የምናገረው የግድ ካስፈለገኝ ብቻ ነበር። በዚህ ቋንቋ መጠቀም በጣም ያስጨንቀኝ ነበር። በጊኒ የምኖረው ሌሎች ስለ ይሖዋ እንዲያውቁ ለመርዳት እንደሆነ በየቀኑ ራሴን ማስታወስ ነበረብኝ።

ይህን ቋንቋ በማጥናትና አጥርተው የሚናገሩ ሰዎችን በማዳመጥ ቀስ በቀስ የፈረንሳይኛ ቋንቋ ችሎታዬን ማሻሻል ችያለሁ። ልጆች ግልጽ በመሆናቸው በጉባኤ ውስጥ የሚገኙ ልጆችን እገዛ መጠየቄም ረድቶኛል። ከዚያም ሳይታሰብ ከይሖዋ ድርጅት ወቅታዊ የሆነ እርዳታ አገኘሁ። ከመስከረም 2001 ጀምሮ የመንግሥት አገልግሎታችን የተለያየ ሃይማኖት ላላቸው ሰዎች መጽሐፎችንና ብሮሹሮችን ብቻ ሳይሆን መጽሔቶችንም ጭምር ለማበርከት የሚያስችሉ ሐሳቦችን ይዞ መውጣት ጀመረ። አሁን የአፍ መፍቻ ቋንቋዬን ያህል በፈረንሳይኛ ሐሳቤን መግለጽ ባልችልም ከበፊቱ ይበልጥ በድፍረት በአገልግሎት መካፈል ችያለሁ።

በትልቅ ቤተሰብ ውስጥ ማደጌ ከብዙ ሰዎች ጋር መኖር እንዳይከብደኝ ረድቶኛል፤ እንዲያውም በአንድ ወቅት በሚስዮናውያን ቤት ውስጥ 17 ሆነን አብረን ኖረናል። በሚስዮናዊነት ባሳለፍኳቸው 37 ዓመታት ውስጥ ከ100 ከሚበልጡ ሌሎች ሚስዮናውያን ጋር ኖሬያለሁ። የተለያየ ባሕርይ ቢኖራቸውም ለአንድ ዓላማ የሚሠሩትን እነዚህን ሁሉ ሰዎች ማወቅ እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው! ከአምላክ ጋር አብሮ የመሥራትና ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ሲቀበሉ የመመልከት አጋጣሚ ማግኘት ምንኛ አስደሳች ነው!—1 ቆሮንቶስ 3:9

ባለፉት ዓመታት፣ በቤተሰቦቼ ሕይወት ውስጥ ትልቅ ቦታ በሚሰጣቸው በርካታ ክንውኖች ላይ አልተገኘሁም፤ ለምሳሌ በአብዛኞቹ ታናናሽ እህቶቼና ወንድሞቼ ሠርግ ላይ አልነበርኩም። እንዲሁም ከእህቶቼና ከወንድሞቼ ልጆች ጋር የምፈልገውን ያህል ጊዜ ማሳለፍ አልቻልኩም። ይህም ለእኔም ሆነ የራሳቸውን ጥቅም ሳይፈልጉ በሚስዮናዊነት አገልግሎት እንድቀጥል ላበረታቱኝ ቤተሰቦቼ መሥዋዕትነት የሚጠይቅ ነበር።

ይሁን እንጂ ከቤተሰቦቼ ጋር ባለመሆኔ ያጣሁትን ነገር በሚስዮናዊነት አገልግሎቴ በተለያዩ ጊዜያት አግኝቼዋለሁ። በነጠላነት ለማገልገል ብወስንም በርካታ መንፈሳዊ ልጆች አግኝቻለሁ፤ መጽሐፍ ቅዱስን ያስጠናኋቸው ብቻ ሳይሆኑ የቀረብኳቸው ሰዎችም እንደ ልጆች ሆነውልኛል። ከዚህም በላይ የእነዚህ ሰዎች ልጆች አድገው፣ አግብተውና የራሳቸውን ልጆች ወልደው በእውነት ውስጥ ሲያሳድጉ ለመመልከት ችያለሁ። ከእነዚህም መካከል አንዳንዶቹ፣ ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ እንደ እኔ ሕይወታቸውን እንዲቀርጸው አድርገዋል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a እናቴ ከ25 ዓመታት በላይ በዘወትር አቅኚነት ያገለገለች ሲሆን አባቴም ጡረታ ከወጣ በኋላ ረዳት አቅኚ ሆኖ አገልግሏል።

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1950ዎቹ ዓመታት ከእነዚህ ሁለት እህቶቼ ጋር በሚስዮናውያኑ ቤት አስደሳች ጊዜያት አሳልፈናል

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ48ኛው የጊልያድ ክፍል ውስጥ አብረውኝ ከነበሩት ተማሪዎች ጋር

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በምዕራብ አፍሪካ በምትገኘው በሴራሊዮን እንዳገለግል ተመድቤ ነበር

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጊኒ

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሴራሊዮን

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሴራሊዮን አዲሱ ቅርንጫፍ ቢሮ ለይሖዋ አገልግሎት ሲወሰን