በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ታስታውሳለህ?

ታስታውሳለህ?

ታስታውሳለህ?

በቅርቡ የወጡትን የመጠበቂያ ግንብ እትሞች በማንበብ ተጠቅመሃል? እስቲ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ሞክር:-

• ኢየሱስ ወዳጁን ስለነዘነዘው ሰው ከተናገረው ምሳሌ ምን እንማራለን? (ሉቃስ 11:5-10)

ይህ ምሳሌ፣ በምንጸልይበት ጊዜ ምን አመለካከት ሊኖረን እንደሚገባ ያሳያል። በተለይ የአምላክን ቅዱስ መንፈስ ለማግኘት ሳንታክት ወይም ሳናቋርጥ መለመን ይኖርብናል። (ሉቃስ 11:11-13)—12/15 ገጽ 20-22

• ኢየሱስ ስለ አንዲት መበለትና ስለ አንድ ዳኛ የተናገረው ምሳሌ ምን ትምህርት ይዞልናል? (ሉቃስ 18:1-8)

ይህ ምሳሌ የመጸለይን አስፈላጊነት የሚያጎላ ነው። ከዓመጸኛው ዳኛ በተቃራኒ ይሖዋ ጻድቅ ነው፤ በመሆኑም እኛን ለመርዳት ይፈልጋል። ከዚህም በላይ በምሳሌው ላይ የተጠቀሰችው መበለት የነበራት ዓይነት እምነት ሊኖረን እንደሚገባ ያሳያል።—12/15 ገጽ 26-28

• ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች “ልባችሁን ወለል አድርጋችሁ ክፈቱልን” ያላቸው ለምን ነበር? (2 ቆሮንቶስ 6:11-13)

በቆሮንቶስ ጉባኤ የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች ለእምነት ባልንጀሮቻቸው ልባዊ ፍቅር አለማሳየታቸው ለወንድሞቻቸው አድናቆት እንደሌላቸው የሚጠቁም ነበር። ለእምነት ባልንጀሮቻችን ልባዊ አድናቆት ለማዳበር ጥረት ማድረግ ይገባናል። ሌላው ቀርቶ አዳዲስ ወዳጆች ለማፍራት እንኳ መጣር ይኖርብናል።—1/1 ገጽ 9-11

በራእይ 7:3 ላይ የተጠቀሰው መታተም ምን ያመለክታል?

አምላክ ክርስቲያኖችን በመንፈስ ቅዱስ ሲቀባቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ይታተማሉ። ይሁንና ራእይ 7:3 የሚያመለክተው እነዚህ ቅቡዓን ታማኝ መሆናቸውን ሙሉ በሙሉ በተግባር ካስመሠከሩ በኋላ የሚታተምላቸውን የመጨረሻ ማኅተም ነው።—1/1 ገጽ 30-31

• ወላጆች መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሳሙኤል ከሚናገረው ዘገባ ምን ትምህርት ያገኛሉ?

በመጀመሪያ፣ የሳሙኤል ወላጆች እንዳደረጉት ሁሉ እነርሱም ለልጆቻቸው የአምላክን ቃል ማስተማር አለባቸው። በተጨማሪም ልጆቻቸው ይሖዋን ማገልገልን የሙሉ ጊዜ ሥራቸው እንዲያደርጉት ማበረታታት ይኖርባቸዋል።—1/15 ገጽ 16

• ይሖዋን በደስታ እየጠበቅን እንደሆነ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

አምላክ ኃጢአተኞችን ሲያጠፋ እፎይታ የምናገኝበትን ‘የይሖዋን ቀን [በጉጉት] እንጠባበቃለን።’ (2 ጴጥሮስ 3:7, 12) ይሖዋ ራሱም ክፋትን ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ ከፍተኛ ፍላጎት አለው፤ ሆኖም ለስሙ ክብር በሚያመጣ መንገድ ክርስቲያኖችን ለማዳን ሲል ይታገሳል። ይሖዋ እርምጃ መውሰድ ያለበትን ትክክለኛ ጊዜ እንደሚያውቅ ልንተማመን ይገባል። እስከዚያው ድረስ እርሱን ማወደሳችንን ማቋረጥ አይኖርብንም። (መዝሙር 71:14, 15)—3/1 ገጽ 17-18

• ኖኅ ከእያንዳንዱ ንጹሕ እንስሳ ወደ መርከቡ ያስገባው ሰባት ሰባት ነው ወይስ ሰባት ሰባት ጥንድ?

ኖኅ ከእያንዳንዱ ንጹሕ እንስሳ “ሰባት ሰባት” እንዲያስገባ ተነግሮት ነበር። (ዘፍጥረት 7:1, 2) መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ በተጻፈበት ቋንቋ እዚህ ጥቅስ ላይ የገባው ቃል በቀጥታ ሲተረጎም “ሰባት ሰባት” የሚል ፍቺ አለው። ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች እንደሚያሳዩት ይህ አገላለጽ ሰባት ጥንድ መሆንን አያመለክትም። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ኖኅ ወደ መርከቡ ያስገባው ከእያንዳንዱ እንስሳ ሰባት ሰባት ማለትም ሦስት ጥንድና በኋላ ላይ ለመሥዋዕት የሚሆን አንድ እንስሳ ነው። (ዘፍጥረት 8:20)—3/15 ገጽ 31

• ክርስቲያኖች የመሪዎቻቸውን ማለትም የሽማግሌዎችን የእምነት ፍሬ ‘መመልከት’ ያለባቸው ለምንድን ነው?

ሐዋርያው ጳውሎስ ሽማግሌዎች የታማኝነት አኗኗር በመከተል ያገኙትን ውጤት ‘እንድንመለከት’ ወይም በጥንቃቄ እንድናጤንና እነዚህን የእምነት ምሳሌዎች እንድንኮርጅ አበረታቶናል። (ዕብራውያን 13:7) ይህን የምናደርገው መጽሐፍ ቅዱስ ስለሚያዘን ነው። እንዲሁም ሽማግሌዎች የመንግሥቱን ፍላጎት ለማራመድም ሆነ ለአካላዊና ለመንፈሳዊ ደህንነታችን ከልብ የሚጨነቁ መሆናቸውን ስለምናምን ነው።—4/1 ገጽ 28