በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አዝመራው ‘ለመከር ደርሷል’

አዝመራው ‘ለመከር ደርሷል’

አዝመራው ‘ለመከር ደርሷል’

በደቡብ አሜሪካ ሰሜናዊ ጫፍ ላይ ግዋሄራ የሚባል ባሕረ-ገብ መሬት አለ። ይህ ቦታ በሰሜን ኮሎምቢያ እና በሰሜን ምዕራብ ቬኔዝዌላ አካባቢ የሚገኝ ነው። ይህን ከፊል በረሃማ ቦታ አስቸጋሪ የሚያደርገው የፀሐዩ ትኩሳትና አነስተኛ የዝናብ መጠን ያለው መሆኑ ሲሆን የሙቀቱ መጠን እስከ 43 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ይደርሳል። የአየሩ ጠባይ አስቸጋሪ ቢሆንም የአካባቢው ነዋሪዎች ታታሪና ምርታማ ገበሬዎች ናቸው። ከውቅያኖሱ ያለማቋረጥ የሚመጣው ነፋሻማ አየርና ከሰሜን ምሥራቅ የሚነሱት ነፋሳት ቦታው ለመኖሪያነት ተስማሚ እንዲሆን ከማድረጋቸውም ባሻገር ጎብኚዎች በሚማርከው መልክዓ ምድርና ውብ በሆኑት የባሕር ዳርቻዎች እንዲደሰቱ አስችለዋቸዋል።

የዋዩ ሕንዶችን ምድር እንድትጎበኝ ተጋብዘሃል! በጠቅላላው 305,000 የሚሆኑ ዋዩ ሕንዶች እንዳሉ የሚገመት ሲሆን 135,000 ያህሉ የሚኖሩት በኮሎምቢያ ነው። ይህ ጎሳ እዚህ አካባቢ መኖር የጀመረው ከስፔን ቅኝ ግዛት በፊት ነው።

የዋዩ ጎሳ ሰዎች በዋነኝነት የሚተዳደሩት በከብት እርባታና በእርሻ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ዓሣ በማስገርና ከአጎራባች አገሮች ጋር የንግድ ልውውጥ በማድረግ ኑሯቸውን የሚመሩ ሰዎችም አሉ። ባለሙያ የሆኑት ሴቶቻቸው የሚሸምኗቸው ደማቅ ቀለማት ያላቸው ልብሶች በቱሪስቶች ዘንድ ተወዳጅነት አትርፈዋል።

ዋዩ ሕንዶች በቅንነታቸውና በእንግዳ ተቀባይነታቸው ይታወቃሉ። ይሁንና እነርሱም የሚኖሩት ‘በሚያስጨንቅ ጊዜ’ ውስጥ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) ካሉባቸው በዋነኝነት የሚጠቀሱ ችግሮች መካከል አንዱ ድህነት ነው። ይህም ለመሃይምነት፣ ለሕፃናት የተመጣጠነ ምግብ እጥረት፣ ለሕክምና እጦትና በአንዳንድ ቦታዎች ለዓመጽ መስፋፋት ምክንያት ሆኗል።

የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት ለበርካታ ዓመታት ሚስዮናውያንን ወደ ዋዩ ሕንዶች ሲልኩ ቆይተዋል። በዚህም ምክንያት አብዛኞቹ የመምህራን ማሠልጠኛዎችና አዳሪ ትምህርት ቤቶች የሚተዳደሩት በቤተ ክርስቲያን ነው። ብዙዎቹ የዋዩ ሰዎች እንደ ምስል አምልኮና የሕፃናት ጥምቀት ያሉትን የክርስቲያኖች ባሕል እንደሆኑ የሚታሰቡትን ልማዶች ተቀብለዋል። ይሁን እንጂ በአፈ ታሪክና በአጉል እምነት ላይ የተመሠረቱትን ባሕላዊ እምነቶቻቸውንና ሃይማኖታዊ ሥርዓቶቻቸውን አልተዉም።

በጥቅሉ ሲታይ የዋዩ ሰዎች ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ሲሆን የይሖዋ ምሥክሮች የሚያስተምሩትን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት መስማት ያስደስታቸዋል። በ1980ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ በግዋሄራ የነበሩት ዋዩ የይሖዋ ምሥክሮች ሰባት ብቻ ሲሆኑ ከእነርሱም መካከል ሦስቱ ሪዮሃቻ በተባለችው የግዛቲቱ ዋና ከተማ ይኖሩ ነበር። የአካባቢው ተወላጅ ከሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች በተጨማሪ 20 አስፋፊዎች የመንግሥቱን ምሥራች በስፓንኛ ይሰብኩ ነበር።

በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መልእክቱን መስበክ

በሪዮሃቻ የሚኖሩት አብዛኞቹ የዋዩ ሕንዶች ዋዩናይኪ ከተባለው የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው በተጨማሪ ስፓንኛ ትንሽ ትንሽ መናገር ይችላሉ። መጀመሪያ ላይ የመንግሥቱን መልእክት የመስበኩ ሥራ እምብዛም ውጤታማ አልነበረም። የአገሬው ተወላጆች አሪሁናስ ብለው ከሚጠሯቸው ዋዩ ያልሆኑ ሰዎች ጋር መቀራረብ አይፈልጉም ነበር። አብዛኞቹ ዋዮዎች የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ቤታቸው ሲመጡ የሚያናግሯቸው በስፓንኛ ሳይሆን በራሳቸው ቋንቋ ነበር። በዚህ ጊዜ ወንድሞች ወደሚቀጥለው ቤት ያልፋሉ።

ይሁን እንጂ በ1994 መገባደጃ ላይ በኮሎምቢያ የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ በርከት ያሉ ልዩ አቅኚዎችን ወይም የሙሉ ጊዜ ሰባኪዎችን በሪዮሃቻ ጉባኤ እንዲያገለግሉ ላከ። አቅኚዎቹ የዋዩ ሕንድ የሆነ አንድ ወንድም ዋዩናይኪ የተባለውን ቋንቋ እንዲያስተምራቸው ጠየቁ። ከዚያም ቀለል ያሉ መግቢያዎችን ከተለማመዱ በኋላ ለመስበክ የሄዱ ሲሆን የሰዎቹ ምላሽ ከፍተኛ ለውጥ እንዳለው ለማስተዋል ጊዜ አልወሰደባቸውም። የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪዎቹ የሚናገሩት የተሰባበረ ዋዩናይኪ ቢሆንም የቤቱ ባለቤቶች ከመገረማቸው የተነሳ ለማዳመጥ ፈቃደኞች ይሆኑ ነበር። አንዳንዴም ነዋሪዎቹ ውስን በሆነው የስፓንኛ ቋንቋ ችሎታቸው ታግዘው ጥሩ ውይይት ያደርጋሉ።

አዝመራው ‘ለመከር ደርሷል’

ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያኖች የሚያከናውኑትን ደቀ መዛሙርት የማድረግ ሥራ ከእርሻ ሥራ ጋር አመሳስሎታል። የዋዩ ሕንዶች ይህን ንጽጽር በቀላሉ ሊረዱት ይችላሉ። (1 ቆሮንቶስ 3:5-9) በምሳሌያዊ አገላለጽ የዋዩ አዝመራ በእርግጥም ‘ለመከር ደርሷል።’—ዮሐንስ 4:35

በማናዉሬ የሚኖረው የዋዩ ሕንድ ተወላጅ የሆነው ኒል ሲወለድ ጀምሮ በነበረበት የጤና ችግር ይሠቃይ ነበር። ኒል የችግሩ መንስኤ አምላክ እንደሆነ ያስብ ስለነበር ሕይወቱን ለማጥፋት ሙከራ እስኪያደርግ ድረስ በጭንቀት ተውጦ ነበር። በሥራ ጉዳይ ወደተለያዩ ከተሞች የሚሄድ አንድ የይሖዋ ምሥክር በሄደበት አካባቢ ሁሉ ከቤት ወደ ቤት ያገለግል ነበር። በዚህ አጋጣሚ ለኒል ስለ ይሖዋ መንግሥት ነገረው። በወቅቱ ኒል ገና የ14 ዓመት ልጅ ነበር። የይሖዋ ምሥክሩ ፍላጎቱን ሲመለከት መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠናው ጀመር። ኒል ይሖዋ አፍቃሪ መሆኑን ሲገነዘብ የተደሰተ ከመሆኑም ባሻገር ለደረሰበት ሥቃይ መንስኤው አምላክ እንዳልሆነ ተረዳ። በሽታ የማይኖርበትን ገነት በምድር ላይ ለማምጣት አምላክ የገባውን ቃል ሲማር ልቡ በጥልቅ ተነክቶ መሆን አለበት።—ኢሳይያስ 33:24፤ ማቴዎስ 6:9, 10

በዚህ ጊዜ የኒል ቤተሰብ ከሌላ ቤተሰብ ጋር ቁርሾ ነበራቸው። ቤተሰቡ ራሳቸውን ከጉዳት ለመጠበቅ በማሰብ የጎሳውን ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ፈጸሙ። ኒል እንደሚከተለው ሲል የነበረውን ሁኔታ ያስታውሳል:- “መጀመሪያ ላይ ለቤተሰቦቼ በተለይም ታላቅ ክብር ለሚሰጣቸው የቤተሰብ ሽማግሌዎች ስለ አዲሱ እምነቴ መንገር አስፈርቶኝ ነበር።” ወላጆቹ ኒል ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ በሌለው እምነታቸውም ሆነ ከመናፍስት ድርጊት ጋር በተያያዙት ልማዶቻቸው ላይ ለመካፈል ፈቃደኛ አለመሆኑን ሲያውቁ እጅግ ተቆጡ። ከዚያም ኒል ወደ ሪዮሃቻ በመሄድ በዚያ አካባቢ በሚገኘው ጉባኤ መሰብሰብ ጀመረ። ቆየት ብሎም ተጠመቀ። በ1993 የጉባኤ አገልጋይ ሆኖ የተሾመ ሲሆን ከሦስት ዓመታት በኋላ የዘወትር አቅኚ ለመሆን በቃ። ከዚያም በ1997 የጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ እንዲያገለግል ተሾመ። በ2000 አገልግሎቱን ይበልጥ በማስፋት ልዩ አቅኚ ሆነ።

ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት የጀመረችውን የዋዩ ተወላጇን የተሪሳን ሁኔታም ተመልከት። አብሯት የሚኖረው ዳንኤል ያፌዝባትና እርሷንና ሦስቱን ልጆቻቸውን ይደበድብ ነበር። በኋላ ላይ ከተሪሳ ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት የተስማማ ቢሆንም ብዙውን ጊዜ ከጓደኞቹ ጋር ሲጠጣ ያመሻል፤ አንዳንዴም ለዚህ ሲል ለአራትና ለአምስት ቀናት ትቷቸው ይጠፋል። ቤተሰቡ ግን በድህነት ይማቅቅ ነበር። ተሪሳ በታማኝነት ማጥናቷንና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘቷን አላቋረጠችም። ይህ አቋሟ ዳንኤል መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ እንዲገነዘብ ረድቶታል። በዚህ ሁኔታ ላይ እያሉ አንዱ ልጃቸው እየፈላ ያለ ውኃ ውስጥ ወድቆ ክፉኛ በመጎዳቱ ሕይወቱ አለፈ። ተሪሳ ወንድ ልጇን ማጣቷ ካስከተለባት ከባድ ሐዘን በተጨማሪ ጓደኞቿና ጎረቤቶቿ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚጋጭ የቀብር ሥነ ሥርዓት እንድታከናውን ለማድረግ የሚያደርሱባትን ተጽዕኖ መቋቋም አስፈልጓት ነበር።

በዚህ አስቸጋሪ ወቅት በአቅራቢያው በሚገኘው ጉባኤ ያሉ ወንድሞችና እህቶች የረዷቸው ከመሆኑም ባሻገር አጽናንተዋቸዋል። ከቀብሩ ሥነ ሥርዓት በኋላ በዋዩ ቋንቋ በሚመራው ጉባኤ ያሉ ወንድሞች ቤታቸው እየመጡ አጽናንተዋቸዋል። ዳንኤል ክርስቲያናዊ ፍቅር በተግባር ሲገለጽ መመልከቱ መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርግ አነሳሳው። መጠጣቱንም ሆነ ተሪሳን ማንገላታቱን አቆመ። ዳንኤል እና ተሪሳ ጋብቻቸውን ሕጋዊ ያደረጉ ሲሆን እርሱም ቤተሰቡን ለመርዳት ጠንክሮ መሥራት ጀመረ። ሁለቱም መንፈሳዊ እድገት አድርገው በ2003 ተጠመቁ። አሁን በርካታ ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠናሉ። ተሪሳ ለዘመዶቿ ግሩም ምሥክርነት በመስጠቷ አሁን የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ቤታቸው ሲመጡ ለማዳመጥ ፈቃደኞች ሆነዋል። ከዳንኤል የታላቅ እህት ልጆች መካከል አንዱ ያልተጠመቀ አስፋፊ ሆኗል። እንዲሁም የታላቅ እህቱና የታላቅ ወንድሙ ሁለት ሴቶች ልጆች መጽሐፍ ቅዱስ እያጠኑ ሲሆን በጉባኤ ስብሰባዎችም ላይ ይገኛሉ። ወንድ ልጇን በአደጋ ምክንያት በሞት ያጣች የተሪሳ አይት እና ቤተሰቧ መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።

በዋዩናይኪ ቋንቋ መንፈሳዊ ምግብ ማዘጋጀት

በ1998 በምድር ላይ ለዘላለም በደስታ ኑር! a የተባለው ብሮሹር በዋዩናይኪ ቋንቋ ተዘጋጀ። ይህ ጽሑፍ በዋዩ ክልል የሚኖሩ ሰዎችን ፍላጎት ለማሳደግና የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመምራት ጠቃሚ መሣሪያ ሆኖ አገልግሏል። በ2003 በዋዩናይኪ ቋንቋ የይሖዋ ምሥክሮችን ጽሑፎች የሚተረጉሙ ወንድሞችን ለማሠልጠን ዝግጅት ተደረገ። በሪዮሃቻ የሚገኙት እነዚህ ተርጓሚዎች ባደረጉት ብርቱ ጥረት ተጨማሪ ብሮሹሮችን ማግኘት ተችሏል። እነዚህ ብሮሹሮች የዋዩናይኪ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ ደቀ መዛሙርትን እምነት ለማጠናከርና በቁጥር እያደጉ እንዲሄዱ ለመርዳት አስችለዋል።

ከ2001 አንስቶ የአውራጃ ስብሰባ የተወሰኑ ክፍሎች ወደ ዋዩናይኪ ቋንቋ እየተተረጎሙ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች እነዚህን ክፍሎች በገዛ ቋንቋቸው መስማታቸው በመንፈሳዊ ይበልጥ እንዲያድጉ ያበረታታቸዋል። የዋዩ ወንድሞች የመጽሐፍ ቅዱስ ድራማ በቅርቡ በዋዩናይኪ ቋንቋ እንደሚቀርብ ተስፋ ያደርጋሉ።

ፍሬያማ የሆነ መስክ

ዩሪብያ ከሪዮሃቻ በስተ ሰሜን ምሥራቅ 100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ከተማ ነች። በዩሪብያ የሚገኘው የዋዩ ጉባኤ 16 አስፋፊዎች ያሉት ሲሆን አብዛኞቹ በገጠር አካባቢ ለሚኖሩት ሕንዶች ምሥራቹን ለመስበክ ተጨማሪ ጥረት እያደረጉ ነው። ከጉባኤው ሽማግሌዎች መካከል አንዱ በአካባቢው ለመስበክ ያደረጉትን ጥረት አስመልክቶ እንዲህ ብሏል:- “አጭር ጣሪያና ትንንሽ መስኮቶች ያሏቸው ብዙ ቤቶች ያሉበት አንድ ግቢ ገባን። በእያንዳንዱ ቤት ፊት ለፊት ከዮቶሆሎ (ከቁልቋል ውስጠኛ ክፍል የሚገኝ እንጨት መሰል ነገር ነው) የተሠራ ዳስ አለ። በዚህ ዳስ ሥር ቤተሰቦችና እንግዶች ከፀሐይ ይጠለላሉ። ብዙዎች ፍላጎት እንዳላቸው ስንመለከት ተደሰትን። በመሆኑም ተመልሰን ለመምጣትና መጽሐፍ ቅዱስ ለማስጠናት ዝግጅት አደረግን። ተመልሰን ስንመጣ ብዙዎች ማንበብና መጻፍ እንደማይችሉ ተገነዘብን። ከዚህ ቀደም በአካባቢው ትምህርት ቤት እንደነበርና በገንዘብ እጥረት ምክንያት እንደተዘጋ ነገሩን። የትምህርት ቤቱ ኃላፊ አንደኛውን ክፍል መሠረተ ትምህርት እንድናስተምርበትና መጽሐፍ ቅዱስ ለማስጠናት እንድንጠቀምበት ፈቀደልን። ስድስት የዋዩ ሕንዶች ማንበብና መጻፍ የተማሩ ሲሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታቸውም እድገት በማድረግ ላይ ይገኛሉ። የአካባቢው ነዋሪዎች ያላቸው አድናቆት ስሜታችንን በጥልቅ ስለነካው በግቢው ውስጥ ስብሰባ ለማካሄድ እቅድ አወጣን።”

የአካባቢው ተወላጅ ያልሆኑ በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች ዋዩናይኪ ቋንቋ ተምረዋል። የሚያበረክቱት እርዳታም በእጅጉ የሚደነቅ ነው። በአሁኑ ጊዜ በግዋሄራ ባሕረ-ገብ መሬት በዋዩናይኪ ቋንቋ የሚመሩ ስምንት ጉባኤዎችና ሁለት ቡድኖች አሉ።

ይሖዋ ይህንን ጥረት እንደባረከው በግልጽ ይታያል። ምሥራቹን ለዋዩ ሕንዶች በመስበክ ረገድ ብዙ የሚሠራ ሥራ እንዳለ ምንም ጥርጥር የለውም። ለመንፈሳዊ ፍላጎቶቻቸው ንቁ የሆኑ ሰዎች ክርስቲያን ደቀ መዛሙርት ሲሆኑ ወደፊት ጥሩ ውጤት ይገኛል። አዝመራው ‘ለመከር ስለደረሰ’ ይሖዋ በዚህ መስክ ላይ የሚሠሩ ተጨማሪ አገልጋዮች እንዲልክ ምኞታችን ነው።—ማቴዎስ 9:37, 38

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ካርታ]

( መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ቬኔዝዌላ

ኮሎምቢያ

ላ ግዋሄራ

ማናዉሬ

ሪዮሃቻ

ዩሪብያ

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ከታች፣ የዋዩዎች መንደር:- Victor Englebert