በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እንደጠበቁት ሳይሆን ሲቀር

እንደጠበቁት ሳይሆን ሲቀር

እንደጠበቁት ሳይሆን ሲቀር

አንድ ወንድና አንዲት ሴት ለጋብቻ በሚጠናኑበት ወቅት በጣም የሚጣጣሙ መስለው ቢታዩም እንኳ በማንኛውም ትዳር ውስጥ ሊያጋጥም እንደሚችለው ሁሉ ነገሮች እንደጠበቋቸው ባለመሆናቸው ቅሬታ ሊፈጠር ይችላል። ይሁንና የጋብቻ መሐላ ከመፈጸማቸው በፊት አንዳቸው ለሌላው የተፈጠሩ እስኪመስሉ ድረስ ፍጹም ተስማሚ ሆነው የሚታዩ ሁለት ሰዎች ከተጋቡ በኋላ በጣም የተለያዩ የሚሆኑት ለምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ የሚያገቡ ሰዎች “መከራና ሐዘን” እንዳለባቸው ይናገራል። (1 ቆሮንቶስ 7:28 ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል) በአብዛኛው ለዚህ ችግር አስተዋጽኦ የሚያደርገው የሰዎች አለፍጽምና ነው። (ሮሜ 3:23) በተጨማሪም አንደኛው ወይም ሁለቱም የትዳር ጓደኛሞች የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በተግባር ላይ አያውሉ ይሆናል። (ኢሳይያስ 48:17, 18) ይሁን እንጂ አንዳንድ ወንዶችና ሴቶች ወደ ትዳር የሚገቡት ከእውነታው የራቀ ተስፋ ይዘው ነው። እንዲህ ያለው ሁኔታ የሚፈጥረው አለመግባባት ወደከፋ ችግር ሊያመራ ይችላል።

ከእውነታው የራቀ ተስፋ

ብዙዎች እንደሚሰማቸው ሁሉ እናንተም፣ ባሎችም ሆናችሁ ሚስቶች ወደ ትዳር ዓለም ስትገቡ ብዙ የጠበቃችኋቸው ነገሮች ይኖሯችኋል። ከትዳር በኋላ ይኖረናል ብላችሁ ስለጠበቃችሁት ሕይወት እስቲ ለአንድ አፍታ ቆም ብላችሁ አስቡ። ትዳራችሁ መጀመሪያ እንደጠበቃችሁት አልሆነላችሁም? እንዲህ ከሆነ፣ ችግሮች እልባት ሊያገኙ አይችሉም ብላችሁ ለመደምደም አትቸኩሉ። የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በተግባር ማዋላችሁ ችግሮችን ለመፍታት ይረዳችኋል። a (2 ጢሞቴዎስ 3:16) እስቲ አሁን ከማግባታችሁ በፊት ከትዳር ትጠብቋቸው ስለነበሩት አንዳንድ ነገሮች መለስ ብላችሁ አስቡ።

ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንዶች የትዳር ሕይወት በተረት ውስጥ እንደሚገለጸው ሁልጊዜ በፍቅር የተሞላና ምንም ችግር የሌለበት ይመስላቸዋል። ወይም አብዛኛውን ጊዜያችሁን ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር እንደምታሳልፉ አሊያም ማንኛውንም አለመግባባት በተረጋጋና ብስለት በሚታይበት መንገድ እንደምትፈቱት አስባችሁ ይሆናል። ብዙዎች ትዳር ሲይዙ ከጾታ ፍላጎት ጋር በተያያዘ ራሳቸውን ለመግዛት ብዙ መጨነቅ እንደማያስፈልጋቸው ተሰምቷቸው ነበር። እንዲህ ዓይነቶቹ የተለመዱ ተስፋዎች በተወሰነ መጠን ከእውነታው የራቁ በመሆናቸው አንዳንዶችን ወደ ሐዘን ሊመሯቸው ይችላሉ።—ዘፍጥረት 3:16

ሌላው ከእውነታው የራቀ አስተሳሰብ ደግሞ ትዳር በራሱ አንድን ሰው ደስተኛ ያደርገዋል የሚለው ነው። እውነት ነው፣ የሕይወት አጋር ማግኘት ታላቅ ደስታ ሊያስገኝ ይችላል። (ምሳሌ 18:22፤ 31:10፤ መክብብ 4:9) ይሁንና ትዳር ለሁሉም ዓይነት አለመግባባት ተአምራዊ ፈውስ ያስገኛል ብሎ መጠበቅ ይቻላል? እንዲህ ብለው የሚያስቡ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ባላሰቡት መንገድ ከቅዠታቸው ይባንናሉ!

ከትዳር ጓደኛችሁ የምትጠብቁትን ነገር ሳትናገሩ ስትቀሩ

ባልና ሚስት ከትዳራቸው የሚጠብቋቸው ነገሮች በሙሉ ከእውነታው የራቁ ናቸው ማለት አይቻልም። አንዳንዶቹ ተስፋዎች ምክንያታዊ ናቸው። ያም ሆኖ አንዳንድ ጊዜ ችግር ሊፈጠር ይችላል። አንድ የትዳር አማካሪ ያስተዋሉትን ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል:- “ባለትዳሮች የሚጠብቁት ነገር ባለመሟላቱ ምክንያት አንዳቸው በሌላው ላይ ሲቆጡ አያለሁ። ይሁንና አንደኛው ወገን ምን እንደሚፈለግበት እንኳ ጨርሶ ላያውቅ ይችላል።” ይህ እንዴት ሊያጋጥም እንደሚችል ለማየት የሚከተለውን ምሳሌ ተመልከት።

ሜሮን እርሷ ከምትኖርበት አካባቢ በመቶ ኪሎ ሜትሮች ርቆ የሚገኘውን ዳዊትን አገባች። ሜሮን በተፈጥሮዋ አይናፋር ስለሆነች ወደ አዲስ አካባቢ መዛወሯ አስቸጋሪ ሊሆንባት እንደሚችል ከማግባቷ በፊት ተገንዝባ ነበር። ቢሆንም ዳዊት ከአካባቢው ጋር እንደሚያለማምዳት ተማምናለች። ለምሳሌ ሜሮን ዳዊት ከጎኗ ሆኖ ከጓደኞቹ ጋር በደንብ እንደሚያስተዋውቃት ጠብቃለች። ይሁንና ሁኔታው እንዳሰበችው አልሆነም። ዳዊት ለአካባቢው እንግዳ የሆነችውን ሜሮንን ብቻዋን ትቶ ከጓደኞቹ ጋር ሞቅ ያለ ጨዋታ ይዟል። ሜሮን ችላ እንደተባለች አልፎ ተርፎም እንደተተወች ሆኖ ተሰማት። በመሆኑም ‘ዳዊት እንዴት ይህን ያህል ደንታ ቢስ ይሆናል?’ እያለች ታስባለች።

ሜሮን ከዳዊት የጠበቀችው ነገር ምክንያታዊ አይደለም ማለት ይቻላል? በፍጹም። እርሷ የፈለገችው ባሏ ከአዲሱ ሁኔታ ጋር እንድትላመድ እንዲረዳት ብቻ ነው። ሜሮን አይናፋር ስለሆነች እምብዛም ከማታውቃቸው ብዙ ሰዎች ጋር አብሮ መሆን ያስፈራታል። ይሁንና ይህን ስሜቷን ለዳዊት ገልጻለት አታውቅም። በመሆኑም ዳዊት ባለቤቱ ምን እየተሰማት እንዳለ አላወቀም። ሁኔታው በዚሁ ከቀጠለ ምን ሊከሰት ይችላል? ሜሮን ያደረባት ቅሬታ እያደገ ይሄድና በጊዜ ሂደት ዳዊት ለስሜቷ ፈጽሞ ደንታ ቢስ እንደሆነ ልታስብ ትችላለች።

ምናልባት እናንተም የትዳር ጓደኛችሁ ፍላጎታችሁን እንዳላሟላላችሁ ስለተሰማችሁ አዝናችሁ ወይም ተበሳጭታችሁ ይሆናል። እንዲህ ተሰምቷችሁ ከሆነ ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

ስሜታችሁን አውጥታችሁ ተናገሩ

የጠበቁት ነገር ሳይፈጸም መቅረቱ ለሐዘን ሊዳርግ ይችላል። (ምሳሌ 13:12) ቢሆንም ሁኔታዎችን ለማስተካከል ማድረግ የምትችሉት ነገር አለ። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “ብልህና በማስተዋል የምትናገር ከሆንክ ሌሎችን ማሳመን ትችላለህ” ይላል። (ምሳሌ 16:23 ኮንቴምፖራሪ ኢንግሊሽ ቨርሽን) ስለሆነም ያልተሟላላችሁ ነገር ምክንያታዊ እንደሆነ ከተሰማችሁ ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር በጉዳዩ ላይ ተወያዩበት።

ይህን ስታደርጉ ትክክለኛውን ጊዜና ምቹ ሁኔታ ምረጡ፤ እንዲሁም የሚያሳስባችሁን ጉዳይ ስትናገሩ በቃላት ምርጫችሁ ላይ ጥንቃቄ አድርጉ። (ምሳሌ 25:11) ረጋ ባለ ስሜትና በአክብሮት ተናገሩ። ዓላማችሁ የትዳር አጋራችሁን መውቀስ ሳይሆን ምን እንደምትጠብቁና ምን እንደሚሰማችሁ ለእርሱ ወይም ለእርሷ ማሳወቅ መሆኑን አትዘንጉ።—ምሳሌ 15:1

ይሁንና እንዲህ ማድረግ ለምን አስፈለገ? አሳቢ የሆነ የትዳር ጓደኛ የሌላውን ስሜት ይረዳ የለ? ምናልባት የትዳር ጓደኛችሁ ነገሮችን ያየው ከተለየ አቅጣጫ ሊሆን ይችላል። ስሜታችሁን አውጥታችሁ ብትገልጹለት ግን የእናንተን አመለካከት ለመረዳት እንደሚፈልግ አያጠራጥርም። ምን እንደምትፈልጉ መናገራችሁ ትዳራችሁ እንዳልሰመረ ወይም የትዳር ጓደኛችሁ ለስሜታችሁ ደንታ ቢስ እንደሆነ የሚጠቁም አይደለም።

ስለዚህ ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር ያሳሰባችሁን ጉዳይ አንስታችሁ ለመወያየት አታመንቱ። ለአብነት ያህል፣ ቀደም ሲል በተጠቀሰው ሁኔታ ላይ ሜሮን ለዳዊት እንዲህ ልትለው ትችላለች:- “ብዙም ከማላውቃቸው ሰዎች ጋር መሆን ይከብደኛል፤ በደንብ እስክተዋወቃቸው ድረስ አብረኸኝ ብትሆን ደስ ይለኛል።”

‘ለመስማት የፈጠናችሁ ሁኑ’

አሁን ደግሞ ሁኔታውን ከሌላ አቅጣጫ እንመልከተው። የትዳር ጓደኛችሁ ወደ እናንተ ቀርቦ ምክንያታዊ የሆነ አንድ ፍላጎቱን ስላላሟላችሁለት ማዘኑን ገለጸላችሁ እንበል። እንዲህ ከሆነ፣ የትዳር ጓደኛችሁን በጥሞና አዳምጡ! ጉዳዩን ለማስተባበል አትሞክሩ። ከዚህ ይልቅ ‘ለመስማት የፈጠናችሁ እንዲሁም ለመናገርና ለቊጣ የዘገያችሁ ሁኑ።’ (ያዕቆብ 1:19፤ ምሳሌ 18:13) ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያኖችን “እያንዳንዱ ሰው የባልንጀራውን ጥቅም እንጂ የራሱን ብቻ አይፈልግ” በማለት አሳስቧቸዋል።—1 ቆሮንቶስ 10:24

ይህን ማሳሰቢያ ተግባራዊ ለማድረግ ራሳችሁን በትዳር ጓደኛችሁ ቦታ ማስቀመጥ ይኖርባችኋል። መጽሐፍ ቅዱስ “እናንተ ባሎች ሆይ . . . ከሚስቶቻችሁ ጋር በማስተዋል አብራችሁ ኑሩ” ወይም እንደ ጄ ቢ ፊሊፕ ትርጉም “እናንተም ባሎች አብረዋችሁ የሚኖሩትን የሚስቶቻችሁን ሁኔታ ለመረዳት መጣር ይገባችኋል” ይላል። (1 ጴጥሮስ 3:7 የ1954 ትርጉም) እርግጥ ነው፣ ሚስቶችም የባሎቻቸውን ስሜት ለመረዳት ተመሳሳይ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል።

ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር ምንም ያህል የምትጣጣሙ ብትሆኑ በሁሉም ጉዳዮች ላይ አንድ ዓይነት አመለካከት ይኖራችኋል ማለት እንዳልሆነ አስታውሱ። (“አንድ መልክዓ ምድር፣ ግን የተለያየ እይታ” የሚለውን ሣጥን ተመልከቱ።) ነገሮችን ከሌሎች አንጻር መመልከት መቻል በእርግጥም እጅግ ጠቃሚ ነው። እናንተም ሆናችሁ የትዳር አጋራችሁ በአስተዳደግ፣ በባሕልና በሌሎች ጉዳዮች ምክንያት ከትዳራችሁ የምትጠብቁት ነገር የተለየ ሊሆን ይችላል። በዚህም ምክንያት ከትዳራችሁ በምትጠብቋቸው አንዳንድ ነገሮች ረገድ በጣም የተለያየ አመለካከት እያላችሁም ከልብ ልትዋደዱ ትችላላችሁ።

ለምሳሌ ያህል፣ ክርስቲያን የሆኑ ባልና ሚስት መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ራስነት ያወጣውን መሠረታዊ ሥርዓት በሚገባ ያውቁ ይሆናል። (ኤፌሶን 5:22, 23) ሆኖም የራስነት ሥልጣን በቤተሰባችሁ ውስጥ በሥራ ላይ የሚውለው እንዴት ነው? አንድ ሰው ለራስነት ሥልጣን ተገዝቷል የሚባለው እንዴት ነው? ሁለታችሁም በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት ትመራላችሁ? በተግባር ለማዋልስ ልባዊ ጥረት ታደርጋላችሁ?

በተጨማሪም በዕለት ተዕለት ሕይወታችሁ በሚያጋጥሟችሁ ነገሮች ላይ የተለያየ አመለካከት ይኖራችሁ ይሆናል። አንዳንድ የቤት ውስጥ ሥራዎችን ማን ይሥራ? ዘመዶቻችሁን የምትጠይቁት መቼ ነው? ምንስ ያህል ጊዜ ታሳልፋላችሁ? ክርስቲያን የሆኑ ባልና ሚስት በሕይወታቸው ውስጥ የአምላክን መንግሥት እንደሚያስቀድሙ የሚያሳዩት እንዴት ነው? (ማቴዎስ 6:33) ገንዘብ ነክ ጉዳዮችን በተመለከተም ዕዳ ውስጥ መግባት ቀላል ስለሆነ ቆጣቢ መሆን ይጠቅማል። ይሁንና ቆጣቢ መሆን ሲባል ምን ማለት ነው? እነዚህን የመሳሰሉትን ጉዳዮች በግልጽና አክብሮት በተሞላበት መንገድ ልትወያዩባቸው ይገባል።

በዚህ መንገድ መወያየት አንዳንድ የጠበቃችኋቸው ነገሮች ባይሟሉላችሁም እንኳ ትዳራችሁ ሰላም የሰፈነበት እንዲሆን ይረዳችኋል። ከዚህም በተጨማሪ ሐዋርያው ጳውሎስ የሰጠውን ማሳሰቢያ ይበልጥ ተግባራዊ ለማድረግ ትችላላችሁ:- “እርስ በርሳችሁ ተቻቻሉ፤ ከእናንተ አንዱ በሌላው ላይ ቅር የተሰኘበት ነገር ቢኖር ይቅር ተባባሉ።”—ቈላስይስ 3:13

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው? የተባለው በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ መጽሐፍ ለባልና ሚስት የሚሆን ጠቃሚ ምክር ይዟል።

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

አንድ መልክዓ ምድር፣ ግን የተለያየ እይታ

“ውብ የሆነን መልክዓ ምድር በመቃኘት ላይ ያሉ ቱሪስቶችን በዓይነ ሕሊናህ ተመልከት። ሁሉም የሚያዩት አንድ ሥፍራን ቢሆንም እያንዳንዱ ሰው የሚመለከተው በተለያየ መንገድ ነው። ለምን? ምክንያቱም እያንዳንዱ ሰው የተለያየ የትኩረት አቅጣጫ አለው። ፍጹም አንድ ዓይነት አመለካከት ያላቸው ሁለት ሰዎች ሊኖሩ አይችሉም። ከዚህም በላይ ሁሉም ሰው በዕይታው አንድ ገጽታ ላይ አያተኩርም። እያንዳንዱ ሰው ይበልጥ ስሜቱን የሚመስጠው የተለያየ ገጽታ ይኖራል። በጋብቻ ውስጥም ሁኔታው ከዚህ የተለየ አይደለም። ሁለት የትዳር ጓደኛሞች አስተሳሰባቸው የቱንም ያህል የሚገጥም ቢሆን ፍጹም አንድ ዓይነት የሆነ አመለካከት ሊኖራቸው አይችልም። . . . የሐሳብ ግንኙነት ማድረግ እነዚህን ልዩነቶች በማቻቻል እንደ አንድ ሥጋ ሆኖ ለመኖር የሚደረገውን ጥረት ይጨምራል። ይህ ለመነጋገር ጊዜ መመደብን ይጠይቃል።”—ነሐሴ 1, 1993 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 4

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

አሁን ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

• ከትዳራችሁ የጠበቃችኋቸውን ነገሮች እንደገና አጢኑ። እነዚህ ነገሮች ምክንያታዊ ናቸው? ከትዳር ጓደኛችሁ የምትጠብቁት ከአቅሙ በላይ የሆነ ነገር ነው?—ፊልጵስዩስ 2:4፤ 4:5 NW

• የምትጠብቁት ነገር ከእውነታው የራቀ እንደሆነ ከተሰማችሁ ማስተካከያ ለማድረግ ጣሩ። ለምሳሌ ያህል “ፈጽሞ በመካከላችን አለመግባባት አይፈጠርም” ከማለት ይልቅ ልዩነታችሁን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ግብ ይኑራችሁ።—ኤፌሶን 4:32

• ከትዳር ጓደኛችሁ ስለምትጠብቋቸው ነገሮች ተወያዩ። በሚያሳስባችሁ ጉዳይ ላይ መነጋገራችሁ አንዳችሁ ለሌላው ፍቅርና አክብሮት ማሳየትን የምትማሩበት ወሳኝ እርምጃ ነው።—ኤፌሶን 5:33

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የትዳር ጓደኛችሁ የሚያሳስቡትን ጉዳዮች ‘ለመስማት የፈጠናችሁ’ ሁኑ