በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

አንድ ክርስቲያን ካፌይን ያላቸውን መጠጦችና ምግቦች መውሰዱ ስህተት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ክርስቲያን ካፌይን ያላቸውን እንደ ቡና፣ ሻይ፣ ቸኮሌት፣ ሜት እና ለስላሳ መጠጦች ያሉ ነገሮችን እንዳይወስድ አይከለክልም። ይሁን እንጂ ቅዱሳን መጻሕፍት ትክክለኛ ውሳኔ እንድናደርግ የሚረዱንን መሠረታዊ ሥርዓቶች ይዘዋል። በቅድሚያ አንዳንድ ሰዎች ካፌይን ያላቸውን መጠጦችና ምግቦች ከመውሰድ የሚቆጠቡት ለምን እንደሆነ እንመልከት።

አንደኛው ትልቁ ምክንያት ካፌይን አእምሮን ስለሚያነቃቃ በባሕርይ ላይ ለውጥ እንደሚያመጣ መድኃኒት ተደርጎ ሊቆጠር የሚችል መሆኑ ነው። በተጨማሪም ሱስ ሊያስይዝ ይችላል። ለመድኃኒት ቀማሚዎች የተዘጋጀ አንድ የማመሳከሪያ መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “ከፍተኛ መጠን ያለው ካፌይን ለረጅም ጊዜ መውሰድ ሰውነት መድኃኒትን እንዲቋቋም እንዲሁም የካፌይን ጥገኛ እንዲሆን ሊያደርግ ይችላል። አንድ ሰው ካፌይን መውሰዱን በአንድ ጊዜ ካቆመ እንደ ራስ ምታት፣ መነጫነጭ፣ አለመረጋጋት፣ ጭንቀትና ድብታ ያሉ ምልክቶች ይታዩበታል።” ዲያግኖስቲክ ኤንድ ስታትስቲካል ማኑዋል ኦቭ ሜንታል ዲስኦርደርስ በተባለው መጽሐፍ ውስጥ ካፌይን መውሰድን ማቆም የሚያመጣቸው ችግሮች (ካፌይን-ዊዝድሮዋል ሲንድሮም) ዕፅ ማቆም ከሚያስከትላቸው ሌሎች ምልክቶች ጋር እንዲካተቱ ጥናት እየተደረገ ነው። በመሆኑም አንዳንድ ክርስቲያኖች ከማንኛውም ዓይነት ሱስ መራቅና ራስን የመግዛት ባሕርይ ማንጸባረቅ ስለሚፈልጉ ካፌይን መውሰድ ተገቢ እንዳልሆነ ቢሰማቸው ምንም አያስደንቅም።—ገላትያ 5:23

አንዳንዶች ደግሞ ካፌይን የአንድን ሰው ጤንነት ሌላው ቀርቶ በማኅፀን ውስጥ ያለን ሕፃን ደህንነት እንኳ ሊጎዳ ይችላል የሚል እምነት አላቸው። ክርስቲያኖች አምላክን ‘በፍጹም ነፍሳቸው’ መውደድ አለባቸው፤ በመሆኑም ሕይወታቸውን የሚያሳጥር ማንኛውንም ድርጊት አይፈጽሙም። በተጨማሪም ባልንጀራቸውን እንዲወዱ ስለታዘዙ ገና በማኅፀን ውስጥ ያለን ሕፃን የሚጎዳ ነገር ከማድረግ ይቆጠባሉ።—ሉቃስ 10:25-27

ካፌይን በጤንነት ላይ ይህን ያህል ጉዳት እንደሚያደርስ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል? ካፌይን ለተለያዩ በሽታዎች መንስኤ ሊሆን እንደሚችል ሲነገር የቆየ ቢሆንም በዚህ ሐሳብ የማይስማሙ ሰዎች አሉ። እንዲያውም አንዳንድ ተመራማሪዎች ቡና መጠጣት ለጤና ጥሩ እንደሆነ ሲናገሩ ይደመጣል። ታይም መጽሔት በ2006 እንደሚከተለው ሲል ሪፖርት አድርጓል:- “ቀደም ሲል የተደረጉ ጥናቶች [ካፌይን] ለፊኛ ካንሰር፣ ለደም ግፊት እና ለሌሎች በሽታዎች ሊያጋልጥ እንደሚችል ጠቁመው ነበር። በቅርቡ የተካሄዱ ጥናቶች ከዚህ ቀደም የተደረሰባቸውን መደምደሚያዎች ውድቅ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ካፌይን አንዳንድ ጉልህ ጥቅሞች እንዳሉት ጭምር አሳይተዋል። ካፌይን የጉበት በሽታን፣ ፓርኪንሰንስ ዲዚዝ የተባለውን የነርቭ በሽታ፣ የስኳር በሽታን፣ የመርሳት በሽታን፣ የሐሞት ጠጠርን፣ የመንፈስ ጭንቀትንና ሌላው ቀርቶ አንዳንድ የካንሰር ዓይነቶችን ለመከላከል እንደሚረዳ ይታመናል።” ይኸው መጽሔት ከዚህ በፊት ባወጣው እትሙ ላይ የካፌይን አጠቃቀምን በተመለከተ “ቁልፉ ከመጠን አለማለፍ ነው” ብሏል።

እያንዳንዱ ክርስቲያን በአሁኑ ጊዜ ስለ ካፌይን ባለው መረጃና ተያያዥነት ባላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ ተመርኩዞ የራሱን ውሳኔ ማድረግ ይኖርበታል። ለምሳሌ ያህል፣ ነፍሰ ጡር የሆነች አንዲት ክርስቲያን ጽንሱን ሊጎዳው እንደሚችል ከተሰማት በእርግዝናዋ ወራት ካፌይን ላለመውሰድ ትወስን ይሆናል። አንድ ክርስቲያን ካፌይን አዘውትሮ አለመውሰዱ ነጭናጫ እንዲሆን ወይም የሕመም ስሜት እንዲሰማው እንዳደረገው ከተገነዘበ ቢያንስ ለጊዜው ካፌይን መውሰድ ቢያቆም ጥሩ ሊሆን ይችላል። (2 ጴጥሮስ 1:5, 6) ክርስቲያኖች አመለካከታቸውን ሌሎች ሰዎች እንዲቀበሉ ባለመጫን እንዲህ ያለውን ውሳኔ ማክበር ይኖርባቸዋል።

ካፌይን ያላቸውን መጠጦችና ምግቦች በተመለከተ የምታደርገው ውሳኔ ምንም ይሁን ምን፣ ጳውሎስ “ስትበሉም ሆነ ስትጠጡ፣ ወይም ማንኛውንም ነገር ስታደርጉ ሁሉንም ነገር ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት” በማለት የሰጠውን ማሳሰቢያ አትዘንጋ።—1 ቆሮንቶስ 10:31