በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአድሪያና ምኞት

የአድሪያና ምኞት

የአድሪያና ምኞት

በዩናይትድ ስቴትስ ኦክላሆማ ግዛት ውስጥ በምትገኘው ተልሳ ከተማ የምትኖረው አድሪያና አንድ ምኞት ነበራት። ይህ ምኞቷ መዝሙራዊው ዳዊት “ይሖዋን አንዲት ነገር እለምነዋለሁ፤ እርሷንም እሻለሁ፤ ይኸውም በሕይወቴ ዘመን ሁሉ፣ በይሖዋ ቤት እኖር ዘንድ፣ የይሖዋን ክብር ውበት አይ ዘንድ፣ መቅደሱንም በአድናቆት እመለከት ዘንድ ነው” በማለት በመዝሙር ከገለጸው ምኞት ጋር የሚመሳሰል ነው።—መዝሙር 27:4 NW

አድሪያና የስድስት ወር ሕፃን እያለች ኒውሮብላስቶማ የተባለ በተወሰኑ የነርቭ ሥርዓት ክፍሎች ውስጥ የሚያድግ አደገኛ ዕጢ እንዳለባት ታወቀ። ለሞት የሚዳርገው ይህ በሽታ ሁለቱን እግሮቿን ሽባ አደረጋቸው። ሐኪሞች በተለያዩ ጊዜያት ቀዶ ሕክምና ያደረጉላት ከመሆኑም በላይ አንድ ዓመት ሙሉ ኬሞቴራፒ በሚባል የሕክምና ዓይነት ረድተዋታል።

ከአድሪያና እና ከእናቷ የተለየ ሃይማኖት ያለው አባቷ ልጁ በዓለም ታዋቂ የሆነን አንድ የመዝናኛ ቦታ እንድትጎበኝ ለማድረግ ሲል ከአንድ ተቋም ጋር ተነጋገረ። ተቋሙ የአድሪያናን ምኞት ለማሟላት ቃል ከመግባቱ በፊት ቃለ መጠይቅ አደረገላት። አድሪያና ድርጅቱ ትኩረት ስለሰጣት የተሰማትን አድናቆት ከገለጸች በኋላ ከመዝናኛ ቦታው ይልቅ ኒው ዮርክ የሚገኘውን ቤቴል ማለትም የዓለም አቀፉ የይሖዋ ምሥክሮች እንቅስቃሴ ማዕከል የሆነውን ቦታ ብትጎበኝ እንደምትመርጥ ተናገረች። አባቷ የመዝናኛ ቦታውን እንድትጎበኝ መጠየቁን ካወቀች በኋላ አድሪያና ቤቴልን የመጎብኘት አጋጣሚ ማግኘት እንድትችል ወደ ይሖዋ ጸልያ ነበር። ምንም እንኳ ተቋሙ መጀመሪያ ላይ አድሪያና ቤቴልን መጎብኘቷ እምብዛም የሚያዝናናት እንዳልሆነ ቢሰማውም አባቷ ምርጫዋን ስላልተቃወመ ፍላጎቷን ለማሟላት ተስማማ።

አድሪያና ከእናቷ፣ ከእህቷና ከአንዲት ጓደኛዋ ጋር በመሆን ቤቴልን ለመጀመሪያ ጊዜ ለመጎብኘት ወደ ኒው ዮርክ ሄደች። አድሪያና እንዲህ ብላለች:- “ይሖዋ ለጸሎቴ ምላሽ ሰጥቶኛል። ቤቴልን እንድንጎበኝ እንደሚረዳን እርግጠኛ ነበርኩ። መጻሕፍት፣ መጽሔቶችና መጽሐፍ ቅዱሶች እንዴት እንደሚታተሙ አየሁ፤ ይህ ደግሞ አንድን የመዝናኛ ቦታ ከመጎብኘት የተሻለ ነው።”

አድሪያና “የይሖዋን ክብር ውበት” ከማየቷም ባሻገር በዛሬው ጊዜ የሚገኙት የይሖዋ ሕዝቦች የእንቅስቃሴ ማዕከል የሆነውን ቦታ በመጎብኘት በአድናቆት ተሞልታለች። እርስዎም መጥተው ቤቴልን እንዲጎበኙ ግብዣ እናቀርብልዎታለን። ኒው ዮርክ ከሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት በተጨማሪ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ውስጥ ሌሎች ቅርንጫፍ ቢሮዎች ይገኛሉ።