በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጭካኔ ድርጊት የማይኖርበት ጊዜ ይመጣ ይሆን?

የጭካኔ ድርጊት የማይኖርበት ጊዜ ይመጣ ይሆን?

የጭካኔ ድርጊት የማይኖርበት ጊዜ ይመጣ ይሆን?

ብዙዎች በዛሬው ጊዜ ለሚፈጸመው የጭካኔ ድርጊት ዋናው መንስኤ ራስ ወዳድነት እንደሆነ ይስማማሉ። ‘እኔ ልቅደም’ የሚል መርሕ የነበረው ትውልድ ከብዙ ዓመታት በፊት የዘራው ዘር በዋነኝነት ስለራሳቸው የሚጨነቁ ሰዎች የበዙበት ማኅበረሰብ አፍርቷል። ብዙዎች የሚፈልጉትን ለማግኘት ሲሉ ማንኛውንም ነገር ያደርጋሉ፤ ይህም አብዛኛውን ጊዜ የጭካኔ ድርጊት ወደ መፈጸም ይመራቸዋል። ይህ ሁኔታ በግለሰቦች ላይ ብቻ ሳይሆን በብሔራትም ላይ ይንጸባረቃል።

የሌሎች ሰዎችን ሕይወት እንደ ክቡር አድርጎ ማየት የቀረ ይመስላል። እንዲያውም አንዳንዶች ጨካኝ መሆን ያስደስታቸዋል። ሌሎችን የጎዱት ደስታ ለማግኘት ሲሉ እንደሆነ እንደሚናዘዙ ወንጀለኞች እነዚህ ሰዎችም የጭካኔ ድርጊት መፈጸም ያዝናናቸዋል። ዓመጽና ጭካኔ የሚታይባቸውን ፊልሞች ምርጫቸው በማድረግ የፊልሙ ኢንዱስትሪ ትርፋማ እንዲሆንና እንደነዚህ ያሉትን ፊልሞች ይበልጥ እንዲያመርት ስለሚያበረታቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችስ ምን ማለት ይቻላል? ብዙዎች በፊልሞችና በመገናኛ ብዙኃን የሚተላለፉትን የጭካኔ ድርጊቶች ዘወትር መመልከታቸው ስሜተ ደንዳና አድርጓቸዋል።

የጭካኔ ድርጊት ሰለባ የሆኑ ሰዎች በአብዛኛው ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ስለሚደርስባቸው እነርሱም ተመሳሳይ ድርጊት ለመፈጸም ሊገፋፉ ይችላሉ። በሜክሲኮ ራስ ገዝ ብሔራዊ ዩኒቨርሲቲ መምህርት የሆኑት ኖኢሚ ዲያስ ሜሮኪን በጭካኔ ስለሚፈጸሙ የዓመጽ ድርጊቶች እንዲህ ብለዋል:- “ዓመጽ በመማር የሚገኝ ሲሆን የባሕላችን ክፍልም ሆኗል። . . . አካባቢያችን ዓመጽን በቸልታ ሲያልፍና ሲያበረታታ እኛም የዓመጽን መንገድ እንማራለን።” በመሆኑም በተደጋጋሚ የዓመጽ ድርጊት ሰለባ የሆኑ ሰዎች እነርሱም ተመሳሳይ ድርጊት የመፈጸማቸው አጋጣሚ ከፍተኛ ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ የአልኮል መጠጥ ከመጠን በላይ የሚጠጡና አደገኛ ዕፅ የመሰሉ ነገሮችን አላግባብ የሚጠቀሙ ሰዎች የጭካኔ ድርጊት ሊፈጽሙ ይችላሉ። የአገራቸው መንግሥት የሕዝቡን ፍላጎት ባለማሟላቱ ቅሬታ ያላቸው ሰዎችም ሳይጠቀሱ አይታለፉም። ከእነዚህ አንዳንዶቹ አመለካከታቸውን ለማሳወቅ ቆርጠው በመነሳት ብዙውን ጊዜ ንጹሐን ዜጎችን ለጉዳት የሚዳርግ የጭካኔ ድርጊት ሲፈጽሙና ሽብርተኝነትን ሲያስፋፉ ይታያሉ።

ይሁንና ‘የሰው ልጆች ጭካኔን የተማሩት በራሳቸው ነው? አሁን ላለው ሁኔታ መንስኤ የሆነው ምንድን ነው?’ ብለህ ጠይቀህ ይሆናል።

ለጭካኔ ድርጊት መንስኤው ምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ሰይጣን ዲያብሎስን “የዚህ ዓለም አምላክ” ብሎ በመጥራት በዚህ ዓለም ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑን ይነግረናል። (2 ቆሮንቶስ 4:4) ሰይጣን ዲያብሎስ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ የመጨረሻው ራስ ወዳድና ጨካኝ ፍጡር ነው። ኢየሱስ ሰይጣንን “ነፍሰ ገዳይ” እንዲሁም ‘የሐሰት አባት’ ሲል መጥራቱ የተገባ ነው።—ዮሐንስ 8:44

አዳምና ሔዋን ካመጹበት ጊዜ አንስቶ የሰው ልጅ ኃይለኛ በሆነው የሰይጣን ተጽዕኖ ሥር ወድቋል። (ዘፍጥረት 3:1-7, 16-19) የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት በይሖዋ ላይ ካመጹ ከ1,500 ዓመታት ገደማ በኋላ ዓመጸኛ የሆኑ መላእክት ሥጋ ለብሰው ወደ ምድር በመምጣት የሰውን ሴቶች ልጆች ያገቡ ሲሆን ኔፊሊም የተባሉ ዲቃላዎችን ወለዱ። ኔፊሊሞችን ልዩ የሚያደርጋቸው ባሕርይ ምንድን ነው? የስማቸው ፍቺ መልሱን ይሰጠናል። ኔፊሊም ማለት “የሚዘርሩ” ወይም “ሰዎችን አንስተው የሚያፈርጡ” ማለት ነው። በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው ኔፊሊሞች በዘመኑ ለነበረው የጭካኔ ድርጊትና የሥነ ምግባር ብልግና መባባስ ምክንያት ሆነዋል። ይህን ሁኔታ ማስቆም የቻለው አምላክ ያመጣው የጥፋት ውኃ ብቻ ነበር። (ዘፍጥረት 6:4, 5, 17) ኔፊሊሞቹ በጥፋት ውኃ የጠፉ ቢሆንም አባቶቻቸው ሥጋዊ አካላቸውን ትተው አጋንንት በመሆን ወደ መንፈሳዊው ዓለም ተመለሱ።—1 ጴጥሮስ 3:19, 20

በኢየሱስ ዘመን፣ ጋኔን የያዘው አንድ ልጅ የነበረበት ሁኔታ ዓመጸኞቹ መላእክት ምን ያህል ጨካኝ እንደሆኑ ያሳያል። ጋኔኑ ልጁን በተደጋጋሚ ያንፈራግጠውና ሊገድለው ፈልጎ ወደ እሳትና ወደ ውኃ ይጥለው ነበር። (ማርቆስ 9:17-22) እንደዚህ ያሉት ‘የርኩሳን መናፍስት ሰራዊት’ ጨካኝ የሆነው አዛዣቸው ሰይጣን ዲያብሎስ የሚያሳየውን ርኅራኄ የሌለው ባሕርይ እንደሚያንጸባርቁ ግልጽ ነው።—ኤፌሶን 6:12

መጽሐፍ ቅዱስ አስቀድሞ እንደተናገረው በዛሬው ጊዜም አጋንንት የሰው ልጆች የጭካኔ ድርጊት እንዲፈጽሙ ተጽዕኖ ማድረጋቸውን ቀጥለዋል። “በመጨረሻው ዘመን የሚያስጨንቅ ጊዜ እንደሚመጣ ይህን ዕወቅ። ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉ፤ . . . ትምክሕተኞች፣ ትዕቢተኞች፣ . . . የማያመሰግኑ፣ ቅድስና የሌላቸው፣ ፍቅር የሌላቸው፣ ለዕርቅ የማይሸነፉ፣ ሐሜተኞች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ መልካም የሆነውን የማይወዱ፣ ከዳተኞች፣ ችኩሎች፣ በከንቱ በትዕቢት የተወጠሩ፣ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉና። ሃይማኖታዊ መልክ አላቸው፤ ኀይሉን ግን ክደዋል።”—2 ጢሞቴዎስ 3:1-5

የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች በተለይ የእኛ ጊዜ ይህን ያህል አስጨናቂ የሆነበትን ምክንያት ይናገራሉ። በክርስቶስ ኢየሱስ የሚተዳደረው የአምላክ መንግሥት በ1914 ሲቋቋም ሰይጣንና አጋንንታዊ ጭፍሮቹ ከሰማይ ተባርረዋል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “ምድርና ባሕር ግን ወዮላችሁ! ምክንያቱም ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን ብቻ እንደ ቀረው ስላወቀ፣ በታላቅ ቁጣ ተሞልቶ ወደ እናንተ ወርዶአል።”—ራእይ 12:5-9, 12

ይህ ሲባል ግን ሁኔታው ፈጽሞ ሊሻሻል አይችልም ማለት ነው? ቀደም ሲል የተጠቀሱት ዲያስ ሜሮኪን ሰዎች ተገቢ ያልሆኑ ባሕርያትን “ቀስ በቀስ ማስወገድን መማር ይችላሉ” ብለዋል። ይሁን እንጂ የሰይጣን ተጽዕኖ በተንሰራፋበት በዛሬው ጊዜ፣ አንድ ሰው ከዚህ ዓለም መንፈስ የተለየና የላቀ ኃይል በአስተሳሰቡና በድርጊቱ ላይ ተጽዕኖ እንዲያሳድር ካልፈቀደ የዓመጸኝነትን ባሕርይ ማስወገድ አይችልም። ይህ ኃይል ምንድን ነው?

ለውጥ ማድረግ ይቻላል—ግን እንዴት?

የሚያስደስተው ነገር የአምላክ ቅዱስ መንፈስ እጅግ ታላቅ ኃይል በመሆኑ ማንኛውንም ዓይነት አጋንንታዊ ተጽዕኖ ማሸነፍ ይችላል። ይህ ኃይል ፍቅርን ያበረታታል እንዲሁም ለሰው ልጆች ደህንነት ያስባል። ይሖዋን የማስደሰት ፍላጎት ያላቸው ሁሉ በአምላክ መንፈስ ለመሞላት ከፈለጉ የጭካኔ ድርጊት ሊፈጽሙ ይቅርና ከዚያ ጋር የሚቀራረብ ምግባር እንኳ ማስወገድ ይኖርባቸዋል። ይህም ከመለኮታዊው ፈቃድ ጋር ለመስማማት ራስን መለወጥን ይጠይቃል። ይህ መለኮታዊ ፈቃድ ምንድን ነው? አምላክ በተቻለን መጠን እርሱን እንድንመስል ይፈልግብናል። ይህም ሌሎችን በአምላክ ዓይን መመልከትን ይጨምራል።—ኤፌሶን 5:1, 2፤ ቈላስይስ 3:7-10

አምላክ ነገሮችን የሚይዝበትን መንገድ ስታጠና ይሖዋ ለሌሎች ስሜት የማያስብ አለመሆኑን ትገነዘባለህ። በማንኛውም ሰው ሌላው ቀርቶ በእንስሳ ላይ እንኳ ፍትሕ የጎደለው ድርጊት ፈጽሞ አያውቅም። a (ዘዳግም 22:10፤ መዝሙር 36:7፤ ምሳሌ 12:10) ይሖዋ ጭካኔንም ሆነ የጭካኔ ድርጊት የሚፈጽሙ ሰዎችን ይጸየፋል። (ምሳሌ 3:31, 32) ይሖዋ ክርስቲያኖች እንዲያዳብሩት የሚጠብቅባቸው አዲሱ ሰው፣ ሌሎችን ከእነርሱ እንደሚሻሉ አድርገው እንዲቆጥሩና እንዲያከብሯቸው ይገፋፋቸዋል። (ፊልጵስዩስ 2:2-4) አዲሱን ሰው መልበስ “ርኅራኄን፣ ቸርነትን፣ ትሕትናን፣ ጨዋነትንና ትዕግሥትን” ማንጸባረቅ ይጨምራል። “በፍጹም አንድነት የሚያስተሳስረው” ፍቅርም ቸል ሊባል አይገባውም። (ቈላስይስ 3:12-14) ሁሉም ሰው እነዚህን ባሕርያት ቢያንጸባርቅ ኖሮ ዓለም ፍጹም የተለየ መልክ ይኖራት ነበር ቢባል አትስማማም?

ይሁንና ዘላቂ የሆነ የባሕርይ ለውጥ ማምጣት የመቻሉ ጉዳይ ያሳስብህ ይሆናል። እስቲ አንድ እውነተኛ የሕይወት ታሪክ ተመልከት። ማርቲን b ሚስቱን በልጆቻቸው ፊት ይጮህባትና ክፉኛ ይደበድባት ነበር። እንዲያውም በአንድ አጋጣሚ ሁኔታው በጣም አደገኛ ከመሆኑ የተነሳ ልጆቹ ጎረቤት ሄደው ሰው መጥራት አስፈልጓቸው ነበር። ከበርካታ ዓመታት በኋላ ቤተሰቡ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረ። ማርቲን ምን ዓይነት ሰው መሆን እንዳለበትና ሌሎችን እንዴት መያዝ እንዳለበት ተማረ። ለውጥ ማድረግ ይችል ይሆን? ባለቤቱ እንዲህ ትላለች:- “ባለፉት ጊዜያት ባለቤቴ በቁጣ ሲገነፍል ፍጹም ሌላ ሰው ይሆን ነበር። በዚህ ምክንያት ሕይወታችን ለረጅም ጊዜ የተመሰቃቀለ ነበር። ማርቲንን እንዲለወጥ ስለረዳው ይሖዋን የማመሰግንበት ቃላት ያጥረኛል። አሁን ማርቲን ጥሩ አባትና ግሩም ባል ሆኗል።”

ይሁንና ይህ አንድ ምሳሌ ብቻ ነው። በዓለም ዙሪያ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ያጠኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የጨካኝነትን ባሕርይ አስወግደዋል። አዎን፣ መለወጥ ይቻላል።

የጭካኔ ድርጊት በሙሉ የሚወገድበት ጊዜ ቀርቧል

ርኅሩኅ ገዥ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ የሚተዳደረውና በሰማይ የተቋቋመው የአምላክ መንግሥት በቅርቡ ምድርን ሙሉ በሙሉ ማስተዳደር ይጀምራል። ይህ መንግሥት የጭካኔ ድርጊት ምንጭ የሆነውን ሰይጣንንና አጋንንቱን ከሰማይ አስወግዷል። በቅርቡ ደግሞ በምድር ላይ ለሚኖሩት ሰላም ወዳድ ተገዢዎቹ የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ ያሟላላቸዋል። (መዝሙር 37:10, 11፤ ኢሳይያስ 11:2-5) በዓለም ላይ ለሚገኙት ችግሮች እውነተኛ መፍትሔ የሚያመጣው ይህ መንግሥት ብቻ ነው። ይሁንና ይህ መንግሥት እስኪመጣ ድረስ የጭካኔ ድርጊት ቢፈጸምብህስ?

ለተፈጸመብህ የጭካኔ ድርጊት ተመሳሳይ ምላሽ መስጠት ምንም አይጠቅምም። ለባሰ የጭካኔ ተግባር ከማነሳሳት ሌላ የሚፈይደው ነገር የለም። መጽሐፍ ቅዱስ፣ እርሱ በወሰነው ጊዜ “ለሰው ሁሉ እንደ መንገዱ፣ እንደ ሥራው ፍሬ” በሚሰጠው በይሖዋ እንድንታመን ያበረታታናል። (ኤርምያስ 17:10) (“የጭካኔ ድርጊት ሰለባ ከሆንክ ምን ማድረግ ይኖርብሃል?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) እውነት ነው፣ የጭካኔ ድርጊት ሰለባ መሆንህ ለሥቃይ ይዳርግህ ይሆናል። (መክብብ 9:11) ይሁንና አምላክ የጭካኔ ድርጊት ያስከተለውን ጉዳት ሌላው ቀርቶ ሞትን እንኳ ይሽራል። አምላክ ቃል በገባው መሠረት በጭካኔ ድርጊት ሕይወታቸውን ያጡ በእርሱ መታሰቢያ ያሉ ሰዎች ዳግም ሕያው ይሆናሉ።—ዮሐንስ 5:28, 29

በማንኛውም ጊዜ የጭካኔ ድርጊት ሊፈጸምብን የሚችል ቢሆንም ከአምላክ ጋር የመሠረትነው የቅርብ ዝምድናና በተስፋዎቹ ላይ ያለን ጽኑ እምነት መጽናኛ ይሆኑናል። ያለ ትዳር ጓደኛ እርዳታ ሁለት ወንዶች ልጆቿን ያሳደገችውን ሳራን ተመልከት። ሳራ ልጆቿ ጥሩ ትምህርት እንዲያገኙ የተቻላትን ሁሉ አድርጋለች። ይሁንና ዕድሜዋ በገፋ ጊዜ ልጆቿ ተዉአት። ቁሳዊ ድጋፍም ይሁን በታመመች ጊዜ የሚያስፈልጋትን እንክብካቤ ለማድረግ ፈቃደኛ አልሆኑም። አሁን የይሖዋ ምሥክር የሆነችው ሳራ እንዲህ ትላለች:- “አሁንም ድረስ ሁኔታው የሚያሳዝነኝ ቢሆንም ይሖዋ አልተወኝም። ሁልጊዜ በሚንከባከቡኝ መንፈሳዊ ወንድሞቼና እህቶቼ አማካኝነት ድጋፍ እንደሚያደርግልኝ ይሰማኛል። በቅርቡ የእኔን ችግሮች ብቻ ሳይሆን እርሱ ባለው ኃይል የሚታመኑና ትእዛዛቱን የሚፈጽሙ ሰዎች ሁሉ ያለባቸውን ችግር እንደሚያስወግድ ጽኑ እምነት አለኝ።”

ሳራ የጠቀሰቻቸው መንፈሳዊ ወንድሞችና እህቶች እነማን ናቸው? የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑት ክርስቲያን ባልንጀሮቿ ናቸው። የጭካኔ ድርጊት በቅርቡ እንደሚወገድ የሚያምኑት እነዚህ ክርስቲያኖች ርኅሩኅ የሆኑ ሰዎች የሞሉበት ዓለም አቀፍ የወንድማማች ማኅበር መሥርተዋል። (1 ጴጥሮስ 2:17 NW) ለጭካኔ ድርጊት በዋነኝነት ተጠያቂ የሆነው ሰይጣን ዲያብሎስም ሆነ የእርሱን ጎዳና የሚከተል ማንኛውም ፍጡር ይጠፋል። አንድ ጸሐፊ “የጭካኔ ዘመን” ብለው የጠሩት ይህ ዘመን የማይታሰብበት ጊዜ ይመጣል። ይህን ተስፋ በተመለከተ ከአንድ የይሖዋ ምሥክር ጋር ተገናኝተህ ለምን አትማርም?

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a ስለ አምላክ ባሕርያትና ስለ ማንነቱ በጥልቀት ለማወቅ በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ወደ ይሖዋ ቅረብ የተባለውን መጽሐፍ ተመልከት።

b አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የጭካኔ ድርጊት ሰለባ ከሆንክ ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

የአምላክ ቃል የጭካኔ ድርጊት ቢፈጸምብህ ምን ማድረግ እንደሚኖርብህ ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ምክር ይሰጣል። ቀጥሎ የተዘረዘሩትን ጥበብ ያዘሉ ቃላት እንዴት በተግባር ልታውላቸው እንደምትችል አስብ:-

“‘ለደረሰብኝ በደል ብድሬን ባልመልስ!’ አትበል፤ እግዚአብሔርን ጠብቅ፤ እርሱ ይታደግሃል።”—ምሳሌ 20:22

“ድኻ ተጨቍኖ፣ ፍትሕ ተጓድሎ፣ መብትም ተረግጦ ብታይ፣ እንደነዚህ ባሉ ነገሮች አትደነቅ፤ ምክንያቱም አንዱን አለቃ የበላዩ ይመለከተዋል።”—መክብብ 5:8

“የዋሆች ብፁዓን ናቸው፤ ምድርን ይወርሳሉና።”—ማቴዎስ 5:5

“ሌሎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ነገር እናንተም አድርጉላቸው።”—ማቴዎስ 7:12

“ለማንም ክፉን በክፉ አትመልሱ፤ በሰው ሁሉ ፊት በጎ የሆነውን ነገር ለማድረግ ትጉ። ቢቻላችሁስ በበኩላችሁ ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ። ወዳጆቼ ሆይ፤ ለእግዚአብሔር ቁጣ ፈንታ ስጡ እንጂ አትበቀሉ፤ ‘በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ’ ይላል ጌታ ተብሎ ተጽፎአልና።”—ሮሜ 12:17-19

“ክርስቶስ ስለ እናንተ መከራን የተቀበለው የእርሱን ፈለግ እንድትከተሉ ምሳሌን ሊተውላችሁ ነው። . . . ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም፤ መከራ ሲደርስበት አልዛተም፤ ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ።”—1 ጴጥሮስ 2:21-23

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ ብዙዎች የጭካኔ ባሕርይን እንዲያስወግዱ አስተምሯቸዋል