በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጉባኤው እየተጠናከረ ይሂድ

ጉባኤው እየተጠናከረ ይሂድ

ጉባኤው እየተጠናከረ ይሂድ

‘ጉባኤው በሰላም መኖር ጀመረ፤ ተጠናከረም።’—የሐዋርያት ሥራ 9:31

1. ‘የአምላክን ጉባኤ’ በተመለከተ ምን ጥያቄዎች ሊነሱ ይችላሉ?

 በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በጰንጠቆስጤ ዕለት ይሖዋ የተወሰኑ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርትን እንደ አዲስ ብሔር ይኸውም ‘የአምላክ እስራኤል’ አድርጎ ተቀበላቸው። (ገላትያ 6:16) እነዚህ በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ‘የአምላክ ጉባኤ’ ተብለውም ተጠርተዋል። (1 ቆሮንቶስ 11:22) ይሁን እንጂ የአምላክ ጉባኤ መሆን ምንን ይጨምራል? ‘የአምላክ ጉባኤ’ የተደራጀው እንዴት ነው? አባላቱ የትም ቢኖሩ ጉባኤው በምድር ላይ ሥራውን የሚያከናውነው እንዴት ነው? ጉባኤው በሕይወታችንና በደስታችን ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል?

2, 3. ኢየሱስ፣ ጉባኤው የተደራጀ እንደሚሆን ያመለከተው እንዴት ነው?

2 ቀደም ባለው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው ኢየሱስ፣ ለሐዋርያው ጴጥሮስ “በዚህ ዐለት [በኢየሱስ ክርስቶስ] ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፤ የገሃነም ደጆችም አያሸንፏትም” ብሎ ሲናገር ቅቡዓን ተከታዮቹን ያቀፈው ይህ ጉባኤ እንደሚቋቋም አስቀድሞ መግለጹ ነበር። (ማቴዎስ 16:18) ከዚህም በላይ ኢየሱስ ይህንን ከተናገረ ብዙም ሳይቆይ ስለሚቋቋመው ስለዚህ ጉባኤ አሠራርና አደረጃጀት ለሐዋርያቱ ነግሯቸው ነበር።

3 ኢየሱስ በጉባኤው ውስጥ አንዳንዶች የመምራት ኃላፊነት እንደሚኖራቸው በንግግሩም ሆነ በድርጊቱ አስተምሯል። እነዚህ ክርስቲያኖች ኃላፊነታቸውን የሚወጡት የጉባኤውን አባላት በማገልገል ነው። ክርስቶስ እንዲህ ብሏቸዋል:- “የአሕዛብ አለቆች ተብለው የሚታሰቡት እንደሚገዟቸው፤ ሹሞቻቸውም በእነርሱ ላይ ሥልጣናቸውን እንደሚያሳዩ ታውቃላችሁ፤ በእናንተ ዘንድ ግን እንዲህ አይደለም፤ ከመካከላችሁ ታላቅ መሆን የሚፈልግ ሁሉ አገልጋይ ይሁን፤ ፊተኛ ለመሆን የሚፈልግ ሁሉ፣ የሁሉ ባሪያ ይሁን።” (ማርቆስ 10:42-44) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ‘የአምላክ ጉባኤ’ የተበታተኑና በተናጠል የሚንቀሳቀሱ አባላት ያሉት ያልተደራጀ ጉባኤ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ግለሰቦች አብረው የሚሠሩበትና እርስ በርስ ሐሳብ የሚለዋወጡበት ሥርዓታማ አደረጃጀት ይኖረዋል።

4, 5. ጉባኤው መንፈሳዊ ትምህርት እንደሚያስፈልገው የሚያሳየው ምንድን ነው?

4 ‘የአምላክ ጉባኤ’ ራስ የሆነው ኢየሱስ፣ ሐዋርያቱም ሆኑ ሌሎች ከእርሱ የተማሩ ሰዎች በጉባኤው ውስጥ የተወሰኑ ኃላፊነቶች እንደሚኖሯቸው ጠቁሟል። እነዚህ ኃላፊነቶች ምንድን ናቸው? ዋነኛው ኃላፊነታቸው ለጉባኤው አባላት መንፈሳዊ ትምህርት መስጠት ነው። ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ የተወሰኑ ሐዋርያቱ ባሉበት ጴጥሮስን “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፤ . . . ትወደኛለህን?” ብሎት እንደነበር አስታውስ። ጴጥሮስም “አዎን፣ ጌታ ሆይ፤ እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ” በማለት መለሰለት። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ “ጠቦቶቼን መግብ . . . በጎቼን ጠብቅ . . . በጎቼን መግብ” አለው። (ዮሐንስ 21:15-17) ይህ በእርግጥም በቁም ነገር ሊታይ የሚገባው ኃላፊነት ነበር!

5 ከኢየሱስ አነጋገር መመልከት እንደምንችለው ወደ ጉባኤው የሚሰበሰቡት ሰዎች በበረት ውስጥ ካሉ በጎች ጋር ተመሳስለዋል። ክርስቲያን ወንዶችን፣ ሴቶችንና ልጆችን የሚያመለክቱት እነዚህ በጎች መንፈሳዊ ምግብ የሚያቀርብላቸውና በተገቢው መንገድ የሚጠብቃቸው እረኛ ያሻቸዋል። ከዚህም በላይ ኢየሱስ፣ ተከታዮቹ በሙሉ ሰዎችን እንዲያስተምሩና ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጓቸው ስላዘዘ የእርሱ በጎች የሚሆኑ አዲሶች ይህንን መለኮታዊ ተልእኮ እንዴት መፈጸም እንደሚችሉ መሠልጠን ያስፈልጋቸዋል።—ማቴዎስ 28:19, 20

6. አዲስ በተቋቋመው ‘የአምላክ ጉባኤ’ ውስጥ ምን ዓይነት ዝግጅቶች ነበሩ?

6 ‘የአምላክ ጉባኤ’ ከተመሠረተ በኋላ የጉባኤው አባላት ለመማርና እርስ በርስ ለመበረታታት አዘውትረው ይሰበሰቡ ነበር፤ “በሐዋርያት ትምህርትና በኀብረት፣ እንጀራውንም በመቊረስና በጸሎት ይተጉ ነበር።” (የሐዋርያት ሥራ 2:42, 46, 47) በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ ከሰፈረው ዘገባ የምናገኘው ሌላው ትኩረት የሚስብ ሐሳብ ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጹትን ብቃቶች ያሟሉ የተወሰኑ ወንዶች፣ አንዳንድ ጠቃሚ ጉዳዮችን በማከናወን ረገድ እርዳታ እንዲያበረክቱ ይሾሙ የነበረ መሆኑ ነው። እነዚህ ወንድሞች የተመረጡት በትምህርት ደረጃቸው ወይም በሙያ ችሎታቸው አልነበረም። ከዚህ ይልቅ “በመንፈስ ቅዱስና በጥበብ የተሞሉ” ነበሩ። ከእነዚህ አንዱ እስጢፋኖስ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስ ይህ ክርስቲያን “በእምነትና በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ” እንደነበረ ይነግረናል። እንዲህ ዓይነት የጉባኤ ዝግጅት በመኖሩ “የእግዚአብሔርም ቃል እየሰፋ ሄደ፤ የደቀ መዛሙርቱም ቊጥር በኢየሩሳሌም እጅግ እየበዛ ሄደ።”—የሐዋርያት ሥራ 6:1-7

አምላክ የሚጠቀምባቸው ወንዶች

7, 8. (ሀ) በኢየሩሳሌም የነበሩት ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ጥንት በነበሩት ክርስቲያኖች ዘንድ ምን ኃላፊነት ነበራቸው? (ለ) በጉባኤዎቹ አማካኝነት መመሪያ መላኩ ምን ውጤት አስገኝቷል?

7 በጥንት ዘመን በነበረው የጉባኤ ዝግጅት ውስጥ ሐዋርያት ቀዳሚውን ቦታ እንደያዙ መረዳት የሚቻል ቢሆንም ሌሎችም ከእነርሱ ጋር ሆነው ይሠሩ ነበር። በአንድ ወቅት ጳውሎስና ባልንጀሮቹ በሶርያ ወደምትገኘው አንጾኪያ ተመልሰው ነበር። በሐዋርያት ሥራ 14:27 ላይ የሚገኘው ዘገባ “እዚያም በደረሱ ጊዜ፣ ቤተ ክርስቲያንን በአንድነት ሰብስበው፣ እግዚአብሔር በእነርሱ አማካይነት ያደረገውን ሁሉ . . . ተናገሩ” ይላል። ጳውሎስና ባልንጀሮቹ እዚያው ጉባኤ እያሉ ከአሕዛብ የመጡ አማኞች መገረዝ ይኖርባቸው እንደሆነና እንዳልሆነ ጥያቄ ተነሳ። ለጉዳዩ መፍትሔ ለማስገኘት፣ ጳውሎስና በርናባስ “ወደ ኢየሩሳሌም ወጥተው” የበላይ አካል ሆነው ያገለግሉ የነበሩ “ሐዋርያትንና ሽማግሌዎችን እንዲጠይቁ” ተላኩ።—የሐዋርያት ሥራ 15:1-3

8 “ሐዋርያትና ሽማግሌዎችም ይህንኑ ጉዳይ ለማጤን” በተሰበሰቡበት ወቅት ስብሰባውን የመራው የክርስቶስ ወንድም የሆነው ያዕቆብ ነበር፤ ያዕቆብ የክርስቶስ ሐዋርያ ባይሆንም የጉባኤ ሽማግሌ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 15:6) በጉዳዩ ላይ በጥሞና ከተወያዩበት በኋላ በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ከቅዱሳን መጻሕፍት ጋር የሚስማማ ውሳኔ አደረጉ። ይህንንም በጽሑፍ አስፍረው በአካባቢው ለነበሩት ጉባኤዎች ላኩት። (የሐዋርያት ሥራ 15:22-32) ይህ መልእክት የደረሳቸው ጉባኤዎችም መመሪያውን ተቀብለው ተግባራዊ አደረጉት። እንዲህ ማድረጋቸው ምን ውጤት አስገኘ? ወንድሞችና እህቶች እንዲጠናከሩና እንዲበረታቱ አድርጓቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ “አብያተ ክርስቲያናትም በእምነት እየበረቱና ዕለት ዕለትም በቁጥር እየጨመሩ ይሄዱ ነበር” ይላል።—የሐዋርያት ሥራ 16:5

9. መጽሐፍ ቅዱስ ብቃት ያላቸው ክርስቲያን ወንድሞች ምን ዓይነት ኃላፊነት እንደሚሰጣቸው ይገልጻል?

9 የእነዚህ ጉባኤዎች የዘወትር እንቅስቃሴ ምን ይመስል ነበር? በቀርጤስ ደሴት ላይ የነበሩትን ጉባኤዎች እንደ ምሳሌ እንመልከት። በዚህች ደሴት ላይ የሚኖሩ በርካታ ሰዎች መጥፎ ስም የነበራቸው ቢሆንም አንዳንዶች አኗኗራቸውን ለውጠው እውነተኛ ክርስቲያኖች ሆነው ነበር። (ቲቶ 1:10-12፤ 2:2, 3) በቀርጤስ የነበሩት እነዚህ ክርስቲያኖች በኢየሩሳሌም ከነበረው የበላይ አካል በጣም ርቀው በሚገኙ የተለያዩ ከተሞች ውስጥ ይኖሩ ነበር። ሆኖም በሌሎች ቦታዎች ይደረግ እንደነበረው ሁሉ በቀርጤስ በሚገኙት ጉባኤዎች ውስጥም በመንፈሳዊ የጎለመሱ “ሽማግሌዎች” ተሹመው ስለነበር ጉባኤዎቹ ከበላይ አካሉ መራቃቸው ያን ያህል ችግር አልፈጠረም። ሽማግሌ ሆነው የተሾሙት ወንዶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙትን ብቃቶች ያሟሉ ነበሩ። እነዚህ የተሾሙ ሽማግሌዎች ወይም የበላይ ተመልካቾች ‘ሌሎችን ትክክል በሆነው ትምህርት ያበረታቱና ይህንኑ ትምህርት የሚቃወሙትን ይወቅሱ’ ነበር። (ቲቶ 1:5-9፤ 1 ጢሞቴዎስ 3:1-7) የጉባኤ አገልጋዮች ወይም ዲያቆናት ሆነው በማገልገል ጉባኤዎችን ለመርዳት መንፈሳዊ ብቃት ያላቸው ሌሎች ወንዶችም ነበሩ።—1 ጢሞቴዎስ 3:8-10, 12, 13

10. በማቴዎስ 18:15-17 መሠረት ከበድ ያሉ አለመግባባቶች መፈታት ያለባቸው እንዴት ነበር?

10 ኢየሱስ ይህ ዓይነቱ ዝግጅት እንደሚኖር ጠቁሞ ነበር። በማቴዎስ 18:15-17 ላይ የሚገኘው ዘገባ እንደሚገልጸው አንድ የአምላክ አገልጋይ ሌላውን በሚበድልበት ወቅት በሁለት ክርስቲያኖች መካከል አለመግባባት ይፈጠር ይሆናል። በዚህ ጊዜ የተበደለው ወገን ወደ ሌላው ግለሰብ ሄዶ ሁለቱ ብቻ ባሉበት ‘ጥፋቱን ሊነግረው’ ይገባል። አለመግባባቱ በዚህ መንገድ ሊፈታ ካልቻለ ግን ጉዳዩን የሚያውቁ አንድ ወይም ሁለት ሰዎች መጥራት ይቻላል። ይህ ሁሉ ተደርጎም ጉዳዩ ባይፈታስ? ኢየሱስ “እነርሱን ባይሰማ ለቤተ ክርስቲያን ንገር፤ ቤተ ክርስቲያንንም ባይሰማ እንደ አሕዛብና እንደ ቀረጥ ሰብሳቢ ቊጠረው” ብሏል። ኢየሱስ ይህንን በተናገረበት ወቅት አይሁዳውያን ‘የአምላክ ጉባኤ’ ስለነበሩ ሐሳቡ በዋነኝነት የሚሠራው ለእነርሱ ነበር። a ይሁን እንጂ የክርስቲያን ጉባኤ ከተቋቋመ በኋላ ኢየሱስ የሰጠው መመሪያ ለዚህ ጉባኤም ይሠራል። ይህም የአምላክ ሕዝቦች በግለሰብ ደረጃ እንዲጠናከሩና መመሪያ እንዲያገኙ የሚረዳ የጉባኤ ዝግጅት እንደሚኖር የሚጠቁም ሌላው ማስረጃ ነው።

11. ሽማግሌዎች ችግሮችን በመፍታት ረገድ ምን ሚና ይጫወቱ ነበር?

11 ሽማግሌዎች ወይም የበላይ ተመልካቾች ችግሮችን በመፍታት አሊያም ኃጢአት ከመሥራት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በመመልከት ረገድ በአካባቢው የነበረውን ጉባኤ ወክለው ማገልገላቸው ተገቢ ነው። ይህም በቲቶ 1:9 ላይ ሽማግሌዎች ሊያሟሏቸው እንደሚገቡ ከተገለጹት ብቃቶች ጋር የሚስማማ ነው። በእነዚያ ጉባኤዎች ውስጥ የሚገኙት ሽማግሌዎችም ሆኑ ‘ያልተስተካከለውን ነገር እንዲያስተካክል’ ጳውሎስ ወደ ጉባኤዎች የላከው ቲቶ ፍጹም እንዳልነበሩ አይካድም። (ቲቶ 1:4, 5) በዛሬው ጊዜም ወንድሞች ሽማግሌ ሆነው ለመሾም ብቁ መሆናቸውን ለመወሰን፣ እምነት እንዳላቸውና ለአምላክ ያደሩ እንደሆኑ መመልከት ያስፈልጋል። በመሆኑም በጉባኤ ውስጥ ያሉ ሌሎች ክርስቲያኖች በዚህ ዝግጅት አማካኝነት የተሾሙት ወንድሞች በሚሰጧቸው መመሪያም ሆነ አመራር ለመተማመን የሚያበቃ ምክንያት አላቸው።

12. ሽማግሌዎች ጉባኤውን በተመለከተ ምን ኃላፊነት አለባቸው?

12 ጳውሎስ በኤፌሶን ለሚገኙት ሽማግሌዎች “ለራሳችሁና መንፈስ ቅዱስ ኤጲስቆጶሳት አድርጎ በላዩ ለሾማችሁ መንጋ ሁሉ ተጠንቀቁ፤ በገዛ ደሙ [“በገዛ ልጁ ደም፣” የታረመው የ1980 ትርጉም] የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ጠብቁ” ብሏቸው ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 20:28) በዛሬው ጊዜም በተመሳሳይ የጉባኤ የበላይ ተመልካቾች የሚሾሙት ‘የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን እንዲጠብቁ’ ነው። ይህንንም የሚያደርጉት በፍቅር እንጂ በመንጋው ላይ በመሠልጠን አይደለም። (1 ጴጥሮስ 5:2, 3) የበላይ ተመልካቾቹ ‘መንጋውን ሁሉ’ ለማጠናከርና ለመርዳት መጣር ይኖርባቸዋል።

ከጉባኤው ጋር ተቀራርቦ መኖር

13. አንዳንድ ጊዜ በጉባኤ ውስጥ ምን ሊከሰት ይችላል? ለምንስ?

13 ሽማግሌዎችን ጨምሮ ሁሉም የጉባኤው አባላት ፍጹማን አይደሉም፤ በመሆኑም በመጀመሪያው መቶ ዘመን አንዳንድ ሐዋርያት በሕይወት በነበሩበት ጊዜ እንደሆነው ሁሉ ዛሬም በጉባኤ ውስጥ አልፎ አልፎ አለመግባባቶች ወይም ችግሮች ሊፈጠሩ ይችላሉ። (ፊልጵስዩስ 4:2, 3) አንድ የበላይ ተመልካች ወይም ሌላ ግለሰብ የተናገረው ነገር ደግነት የጎደለው አሊያም ከእውነት የራቀ እንደሆነ ይሰማን ወይም ደግሞ በሁኔታው ቅር እንሰኝ ይሆናል። አሊያም ከቅዱሳን መጻሕፍት ጋር የሚጋጭ ድርጊት እንደተፈጸመና የጉባኤያችን ሽማግሌዎች ጉዳዩን ቢያውቁትም ማስተካከያ እንዳላደረጉ እናስብ ይሆናል። ይሁን እንጂ ሽማግሌዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር በሚስማማ መንገድ ጉዳዩን ተመልክተውት ወይም እየተመለከቱት ሊሆን ይችላል፤ ይህን በሚያደርጉበት ወቅት እኛ የማናውቃቸው ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ነገሮች ይኖሩ ይሆናል። ይሁን እንጂ እኛ እንዳሰብነው ከቅዱሳን መጻሕፍት ጋር የሚጋጭ ድርጊት በጉባኤው ውስጥ ተፈጽሞ ከሆነም በቆሮንቶስ ጉባኤ የተፈጸመውን ሁኔታ ማስታወሱ ጠቃሚ ነው። ይሖዋ ይንከባከበው በነበረው በቆሮንቶስ ጉባኤ ውስጥ ከባድ ኃጢአት ተፈጽሞ ለተወሰነ ጊዜ እርምጃ ሳይወሰድ ቆይቶ ነበር። ከጊዜ በኋላ ግን ይሖዋ ይህን ኃጢአት በተመለከተ ተገቢ የሆነ ጥብቅ እርምጃ እንዲወሰድ አደረገ። (1 ቆሮንቶስ 5:1, 5, 9-11) ‘በዚያን ወቅት በቆሮንቶስ ጉባኤ ብሆን ኖሮ እርምጃ እስኪወሰድ ድረስ ምን አደርግ ነበር?’ ብለን ራሳችንን ልንጠይቅ እንችላለን።

14, 15. አንዳንዶች ኢየሱስን መከተል ያቆሙት ለምን ነበር? እኛስ ከዚህ ምን ትምህርት ልናገኝ እንችላለን?

14 በጉባኤ ውስጥ ሊከሰት የሚችል ሌላም ሁኔታ እንመልከት። አንድ ሰው ለመረዳትና ለመቀበል የከበደው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት አለ እንበል። ግለሰቡ በመጽሐፍ ቅዱስና በጉባኤው በኩል በሚያገኛቸው ጽሑፎች አማካኝነት ምርምር አድርጎ እንዲሁም ከሽማግሌዎችም ሆነ ከሌሎች የጎለመሱ ክርስቲያኖች እርዳታ ጠይቆ ይሆናል። ያም ሆኖ ግን ነጥቡን ለመረዳት ወይም ለመቀበል ቢከብደው ምን ማድረግ ይችላል? ኢየሱስ ከመሞቱ ከአንድ ዓመት ገደማ በፊት ተመሳሳይ ነገር ተከስቶ ነበር። ኢየሱስ፣ እርሱ “የሕይወት እንጀራ” እንደሆነና አንድ ሰው ለዘላለም ለመኖር ከፈለገ ‘የሰውን ልጅ ሥጋ መብላትና ደሙንም መጠጣት’ እንዳለበት ተናገረ። ይህ ከደቀ መዛሙርቱ አንዳንዶቹን አስደነገጣቸው። አብዛኞቹ ደቀ መዛሙርት ማብራሪያ ከመጠየቅ ወይም ይሖዋ ነገሮችን በጊዜው እንደሚያስተካክል በማመን በትዕግስት ከመጠበቅ ይልቅ “ከዚያም ወዲያ [ኢየሱስን] አልተከተሉትም።” (ዮሐንስ 6:35, 41-66) በዚያን ጊዜ ኖረን ቢሆን ምን እናደርግ ነበር?

15 በዘመናችን አንዳንዶች አምላክን በግላቸው እንደሚያመልኩት በማሰብ በአካባቢያቸው ካለው ጉባኤ ጋር መተባበር አቁመዋል። እነዚህ ሰዎች እንዲህ ያደረጉት በአንድ ጉዳይ ቅር ስለተሰኙ፣ የተፈጸመውን ስህተት ለማስተካከል እርምጃ እንዳልተወሰደ ስለተሰማቸው ወይም አንድን ትምህርት ለመቀበል ስለከበዳቸው እንደሆነ ይናገራሉ። ይሁን እንጂ ይህ አካሄዳቸው ምን ያህል ምክንያታዊ ነው? እያንዳንዱ ክርስቲያን ከአምላክ ጋር የግል ዝምድና መመሥረት እንዳለበት እሙን ቢሆንም አምላክ በሐዋርያት ዘመን እንዳደረገው ሁሉ ዛሬም በዓለም አቀፉ ጉባኤ እየተጠቀመ እንዳለ መካድ አንችልም። ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ በመጀመሪያ መቶ ዘመን በየአካባቢው በነበሩት ጉባኤዎች ይጠቀም ነበር፤ እነዚህን ጉባኤዎች ይባርካቸው እንዲሁም ጉባኤዎቹን የሚረዱ ብቃት ያላቸው ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች እንዲሾሙ ያደርግ ነበር። በዘመናችንም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው።

16. አንድ ሰው ከጉባኤው ጋር መተባበሩን ማቆም እንዳለበት ቢሰማው የትኛውን ነጥብ ሊያስብበት ይገባል?

16 አንድ ክርስቲያን ከጉባኤ ጋር መተባበር ሳያስፈልገው ከአምላክ ጋር ባለው ግንኙነት ብቻ ተማምኖ መኖር እንደሚችል የሚሰማው ከሆነ ይሖዋ ያቋቋመውን ዝግጅት ማለትም ዓለም አቀፉንም ሆነ በአካባቢው የሚገኘውን የአምላክ ሕዝቦች ጉባኤ አልቀበልም ማለቱ ነው። ግለሰቡ ብቻውን ሆኖ አምላክን ሊያመልክ ወይም ከሌሎች ጥቂት ሰዎች ጋር ሊገናኝ ይችላል፤ ሆኖም ጉባኤ ከሌለ የሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች ዝግጅትም አይኖርም። ጳውሎስ ለቈላስይስ ጉባኤ ደብዳቤ ከጻፈ በኋላ ይኸው ደብዳቤ በሎዶቅያ እንዲነበብ ባደረገ ጊዜ ‘በክርስቶስ ስለመተከልና ስለመታነጽ’ መናገሩ ትኩረት የሚስብ ነው። እንዲህ ዓይነት ጥቅም ሊያገኙ የሚችሉት ከጉባኤው ጋር የሚተባበሩ ክርስቲያኖች እንጂ ራሳቸውን ያገለሉ ግለሰቦች አይደሉም።—ቈላስይስ 2:6, 7፤ 4:16

የእውነት ዐምድና መሠረት

17. አንደኛ ጢሞቴዎስ 3:15 ስለ ጉባኤው ምን ያስተምረናል?

17 ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያን ሽማግሌ ለነበረው ለጢሞቴዎስ በጻፈው የመጀመሪያ ደብዳቤ ላይ በጉባኤዎች ውስጥ የሚያገለግሉ ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች ማሟላት ያለባቸውን ብቃቶች ዘርዝሮ ነበር። ከዚያ ቀጥሎም ጳውሎስ “የሕያው እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን” ወይም ጉባኤ “የእውነት ዐምድና መሠረት” እንደሆነ ጠቅሷል። (1 ጢሞቴዎስ 3:15) ቅቡዓን ክርስቲያኖችን በሙሉ ያቀፈው ጉባኤ በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንዲህ ያለ ዐምድ እንደነበረ ጥርጥር የለውም። እያንዳንዱ ክርስቲያን በዋነኝነት ይህንን እውነት ማግኘት የሚችለው በአካባቢው ባለው ጉባኤ አማካኝነት እንደሆነ የሚያጠያይቅ አይደለም። ክርስቲያኖች በመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ላይ የተመሠረተ ትምህርት ሲሰጥና ቅዱስ ጽሑፉን የሚደግፍ ማስረጃ ሲቀርብ ሊሰሙ እንዲሁም ሊጠናከሩ የሚችሉት በጉባኤ ውስጥ ነው።

18. የጉባኤ ስብሰባዎች አስፈላጊ የሆኑት ለምንድን ነው?

18 በተመሳሳይም ዓለም አቀፉ የክርስቲያን ጉባኤ የአምላክ ቤት ይኸውም “የእውነት ዐምድና መሠረት ነው።” ከአምላክ ጋር ያለንን ዝምድና ለማጠናከርና የእርሱን ፈቃድ ለማድረግ ዝግጁ መሆን እንድንችል በአካባቢያችን በሚደረጉት የጉባኤ ስብሰባዎች ላይ አዘውትረን መገኘታችን ብሎም ተሳትፎ ማድረጋችን ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው። ጳውሎስ በቆሮንቶስ ለነበረው ጉባኤ ሲጽፍ በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ በሚቀርበው ትምህርት ላይ ትኩረት አድርጓል። በስብሰባዎች ላይ ተሰብሳቢዎቹ ‘መታነጽ’ እንዲችሉ የሚቀርቡት ትምህርቶች ግልጽና ለመረዳት የማያስቸግሩ እንዲሆኑ እንደሚፈልግ ጽፎ ነበር። (1 ቆሮንቶስ 14:12, 17-19) እኛም ዛሬ፣ በአካባቢያችን ያሉትን ጉባኤዎች ያቋቋመው ይሖዋ አምላክ እንደሆነና ይህንን ዝግጅት እንደሚደግፈው አምነን የምንቀበል ከሆነ ልንታነጽ እንችላለን።

19. ጉባኤህ በብዙ መንገዶች እንደጠቀመህ የሚሰማህ ለምንድን ነው?

19 በእርግጥም ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን መታነጽ ከፈለግን ከጉባኤው ጋር መተባበር አለብን። ይህ ጉባኤ ከረጅም ጊዜ ጀምሮ የሐሰት ትምህርቶች እንዳይገቡ ሲከላከል ቆይቷል፤ አምላክም የመሲሐዊው መንግሥት ምሥራች በዓለም ዙሪያ እንዲታወጅ ሲጠቀምበት ቆይቷል። አምላክ በክርስቲያን ጉባኤ አማካኝነት ብዙ ነገሮች እንዳከናወነ ምንም ጥርጥር የለውም።—ኤፌሶን 3:9, 10

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑር የሆኑት አልበርት ባርንስ እንደተናገሩት ኢየሱስ ለጉባኤ ወይም “ለቤተ ክርስቲያን ንገር” ሲል “እንዲህ ያሉ ጉዳዮችን ለመመልከት ሥልጣን ያላቸውን ሰዎች ማለትም የቤተ ክርስቲያን ተወካዮችን” ማመልከቱ ሊሆን ይችላል። “በአይሁዳውያን ምኩራብ ውስጥ እንዲህ ዓይነት ጉዳዮችን ለመመልከት ዳኞች ሆነው የሚያገለግሉ ሽማግሌዎች ነበሩ።”

ታስታውሳለህ?

• አምላክ በምድር ላይ በጉባኤዎች ይጠቀማል እንድንል የሚያደርገን ምንድን ነው?

• ሽማግሌዎች ፍጹማን ባይሆኑም እንኳ ለጉባኤው ምን እርዳታ ያበረክታሉ?

• ጉባኤህ እንድትጠናከር የሚረዳህ እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በኢየሩሳሌም የነበሩት ሐዋርያትና ሽማግሌዎች የበላይ አካል ሆነው አገልግለዋል

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች በጉባኤ ውስጥ ያሏቸውን ኃላፊነቶች መወጣት እንዲችሉ ትምህርት ይሰጣቸዋል