በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ብርታትና መጽናናት ከሚሰጠው አምላክ’ የሚገኝ እርዳታ

‘ብርታትና መጽናናት ከሚሰጠው አምላክ’ የሚገኝ እርዳታ

‘ብርታትና መጽናናት ከሚሰጠው አምላክ’ የሚገኝ እርዳታ

ከ2,000 ዓመታት ገደማ በፊት የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ጳውሎስ፣ ይሖዋ “ብርታትንና መጽናናትን የሚሰጥ አምላክ” እንደሆነ ተናግሯል። (ሮሜ 15:5) መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ ምንጊዜም እንደማይለወጥ ስለሚያረጋግጥልን አገልጋዮቹን እንደሚያጽናናቸው ልንተማመን እንችላለን። (ያዕቆብ 1:17) ይሖዋ መጽናናት የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች በተለያዩ መንገዶች እንደሚያጽናናቸው መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። ከእነዚህ መንገዶች አንዳንዶቹ የትኞቹ ናቸው? አምላክ፣ በጸሎት አማካኝነት እርዳታ ለሚጠይቁት ሰዎች ብርታት ይሰጣቸዋል። በተጨማሪም እውነተኛ ክርስቲያኖች የእምነት አጋሮቻቸውን እንዲያጽናኑ ያነሳሳቸዋል። እንዲሁም ይሖዋ ልብ የሚነኩ ዘገባዎችን በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሰፈረ ሲሆን እነዚህ ታሪኮች በተለይ ልጃቸውን በሞት ላጡ ወላጆች የሚያበረታቱ ናቸው። አምላክ ለማጽናናት የሚጠቀምባቸውን እነዚህን ሦስት መንገዶች አንድ በአንድ እንመልከት።

‘ይሖዋ ሰማው’

ንጉሥ ዳዊት ፈጣሪያችን ስለሆነው ስለ ይሖዋ ሲጽፍ እንዲህ ብሏል:- “ሰዎች ሆይ፤ ሁልጊዜ በእርሱ ታመኑ፤ ልባችሁን በፊቱ አፍስሱ፤ እግዚአብሔር መጠጊያችን ነውና።” (መዝሙር 62:8) ዳዊት በይሖዋ ላይ እንዲህ የመሰለ እምነት የነበረው ለምንድን ነው? ስለ ራሱ ሲጽፍ “ይህ ችግረኛ ጮኸ፤ እግዚአብሔርም ሰማው፤ ከመከራውም ሁሉ አዳነው” ብሏል። (መዝሙር 34:6) ይህ የአምላክ አገልጋይ በሕይወቱ ባጋጠሙት አስጨናቂ ሁኔታዎች ሁሉ ምንጊዜም ለእርዳታ ወደ አምላክ ይጸልይ የነበረ ሲሆን ይሖዋም ሁልጊዜ በችግሩ ይደርስለት ነበር። ዳዊት፣ መጽናት እንዲችል አምላክ እንደሚረዳውና እንደሚደግፈው በሕይወቱ ካሳለፈው ተሞክሮ ያውቅ ነበር።

በሐዘን የተደቆሱ ወላጆች፣ ይሖዋ ለዳዊት እንዳደረገለት ሁሉ እነርሱንም ከጥልቅ ሐዘናቸው እንዲያገግሙ እንደሚረዳቸው ማወቃቸው አስፈላጊ ነው። ይሖዋ እንደሚረዳቸው በመተማመን ታላቅ ‘ጸሎት ሰሚ’ ወደሆነው አምላክ መቅረብ ይችላሉ። (መዝሙር 65:2) ቀደም ባለው ርዕስ ላይ የተጠቀሰው ዊልያም እንዲህ ብሏል:- “ልጄ ከሞተ በኋላ መኖር እንደማልችል ብዙ ጊዜ ይሰማኝ ስለነበር ይሖዋ እረፍት እንዲሰጠኝ እጠይቀው ነበር። ይሖዋም በሕይወት መቀጠል እንድችል የሚያስፈልገኝን ጥንካሬና ድፍረት ምንጊዜም ይሰጠኝ ነበር።” አንተም ወደ ይሖዋ በእምነት ከጸለይክ በሰማይ የሚኖረው ታላቅ አምላክ ይረዳሃል። ደግሞም ይሖዋ አምላክ እርሱን ለማገልገል ለሚጥሩት “እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ‘አትፍራ፤ እረዳሃለሁ’ ብዬ ቀኝ እጅህን እይዛለሁና” በማለት ቃል ገብቶላቸዋል።—ኢሳይያስ 41:13

ከእውነተኛ ወዳጆች የሚገኝ እርዳታ

ልጅ የሞተባቸው ወላጆች በአብዛኛው ለብቻቸው ሆነው በማልቀስ ስሜታቸውን ለማውጣት ጊዜ ያስፈልጋቸዋል። ይሁን እንጂ ረዘም ላለ ጊዜ ራሳቸውን ከሌሎች ሰዎች ማግለላቸው የጥበብ መንገድ አይደለም። በምሳሌ 18:1 መሠረት “ወዳጅነትን የማይፈልግ ሰው” ራሱን ሊጎዳ ይችላል። በመሆኑም በሐዘን ላይ ያሉ ሰዎች ራሳቸውን እንዳያገሉ መጠንቀቅ አለባቸው።

ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ወዳጆች፣ በሐዘን ላይ ላሉ ግለሰቦች አስፈላጊውን እርዳታ ሊሰጡ ይችላሉ። ምሳሌ 17:17 “ወዳጅ ምንጊዜም ወዳጅ ነው፤ ወንድምም ለክፉ ቀን ይወለዳል” ይላል። በፊተኛው ርዕስ ላይ የተጠቀሰችው ሉሲ ወንድ ልጇን በሞት ካጣች በኋላ እውነተኛ ወዳጆቿ አጽናንተዋታል። በጉባኤ ስላሉት ወዳጆቿ ስትገልጽ እንዲህ ብላለች:- “አንዳንድ ጊዜ ብዙ ነገር ባይናገሩም እንኳ መምጣታቸው ብቻ በጣም አጽናንቶናል። አንድ ጓደኛዬ ብቻዬን በሆንኩባቸው ቀናት መጥታ ትጠይቀኝ ነበር። ቤት ውስጥ ቁጭ ብዬ እንደማለቅስ ስለምታውቅ ብዙ ጊዜ እየመጣች ከእኔ ጋር ታለቅሳለች። ሌላዋ ጓደኛዬ ደግሞ እኔን ለማበረታታት በየቀኑ ትደውል ነበር። ከዚህም በተጨማሪ ሌሎች ክርስቲያኖች ቤታቸው ምግብ ይጋብዙናል፤ እስካሁንም ድረስ እንዲህ የሚያደርጉ አሉ።”

ወላጆች ልጅ ሲሞትባቸው የሚሰማቸው ጥልቅ ሐዘን በቀላሉ የሚጠፋ አይደለም፤ በመሆኑም በሐዘን የተደቆሱ ሰዎች ወደ አምላክ መጸለያቸውና ከእውነተኛ ክርስቲያን ወዳጆቻቸው ጋር መሆናቸው እውነተኛ ማጽናኛ ያስገኝላቸዋል። ልጃቸውን በሞት ያጡ በርካታ ክርስቲያን ወላጆች ይሖዋ ከእነርሱ ጋር እንደሆነ ተመልክተዋል። አዎን፣ ይሖዋ “ልባቸው የተሰበረውን ይፈውሳል፤ ቍስላቸውንም ይጠግናል።”—መዝሙር 147:3

የሚያጽናኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች

ከጸሎትና አበረታች ከሆነ ወዳጅነት በተጨማሪ የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ በሐዘን ላይ የሚገኙ ሰዎችን ያጽናናቸዋል። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኙ ዘገባዎች እንደሚጠቁሙት ኢየሱስ የሞቱትን በማስነሳት በሐዘን የተደቆሱ ወላጆችን ሥቃይ የማስወገድ ልባዊ ፍላጎትም ሆነ ችሎታ አለው። እንደነዚህ ዓይነት ዘገባዎች በሐዘን ላይ ለሚገኙ ሰዎች እውነተኛ ማጽናኛ ይሰጣሉ። ከእነዚህ መካከል ሁለቱን እንመልከት።

ኢየሱስ በናይን ከተማ ወደ ቀብር ሥነ ሥርዓት ከሚሄዱ ሰዎች ጋር በተገናኘ ጊዜ ምን እንደተከሰተ በሉቃስ ምዕራፍ 7 ላይ የሚገኘው ታሪክ ይገልጽልናል። ሰዎቹ የአንዲትን መበለት ብቸኛ ልጅ ለመቅበር እየሄዱ ነበር፤ በቁጥር 13 ላይ እንዲህ እናነባለን:- “ጌታም ባያት ጊዜ ራራላትና፣ ‘አይዞሽ፤ አታልቅሺ’ አላት።”

በልጇ ቀብር ላይ አንዲትን እናት አታልቅሺ ለማለት ማንም አይደፍርም። ኢየሱስ ይህችን መበለት እንዲህ ያላት ለምን ነበር? የእናትየው ሐዘን ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ እንደሚወገድ ያውቅ ስለነበር ነው። ዘገባው በመቀጠል እንዲህ ይላል:- “[ኢየሱስ] ቀረብ ብሎም ቃሬዛውን ነካ፤ የተሸከሙትም ሰዎች ቀጥ ብለው ቆሙ፤ ኢየሱስም፣ ‘አንተ ጐበዝ፤ ተነሥ እልሃለሁ!’ አለው። የሞተውም ሰው ቀና ብሎ ተቀመጠ፤ መናገርም ጀመረ። ኢየሱስም ወስዶ ለእናቱ ሰጣት።” (ሉቃስ 7:14, 15) በዚህ ጊዜ እናትየው በደስታ አልቅሳ መሆን አለበት።

በሌላ ጊዜ ደግሞ የ12 ዓመት ልጁ በጠና የታመመችበት ኢያኢሮስ የተባለ አንድ አባት ኢየሱስ ልጁን እንዲፈውስለት ጠይቆት ነበር። ብዙም ሳይቆይ ግን ኢያኢሮስ ልጁ እንደሞተች ሰማ። ይህ መልእክት ኢያኢሮስን በጣም እንዲያዝን ቢያደርገውም ክርስቶስ ግን “እመን ብቻ እንጂ አትፍራ” አለው። ኢየሱስ ኢያኢሮስ ቤት ሲደርስ ወደሞተችዋ ልጅ በመሄድ እጇን ይዞ “አንቺ ልጅ ተነሺ” አላት። በዚህ ጊዜ ምን ሆነ? “ብላቴናዪቱም ወዲያውኑ ተነሥታ ቆመች፤ ወዲያ ወዲህም ሄደች።” ወላጆቿ ይህን ሲያዩ ምን ተሰምቷቸው ይሆን? ዘገባው “በሁኔታው እጅግ ተደነቁ” ይላል። ኢያኢሮስና ባለቤቱ ልጃቸውን ሲያቅፉ በጣም ተደሰቱ። ሁኔታው ሕልም እንጂ እውን አልመሰላቸውም።—ማርቆስ 5:22-24, 35-43

እንደነዚህ ያሉ ስለ ልጆች ትንሣኤ የሚናገሩ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ታሪኮች በዛሬው ጊዜ በሐዘን የተደቆሱ ወላጆችም ወደፊት ምን መጠበቅ እንደሚችሉ ይጠቁማሉ። ኢየሱስ “መቃብር ውስጥ ያሉ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ጊዜ ይመጣል፤ . . . [በመቃብር ያሉት] ይወጣሉ” ብሏል። (ዮሐንስ 5:28, 29) የይሖዋ ዓላማ ልጁ የሞቱ ሰዎችን እንዲያስነሳ ነው። ኢየሱስ ብላቴናይቱን “አንቺ ልጅ ተነሺ” እንዳላት ሁሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የሞቱ ልጆችም ‘ተነሱ’ የሚለውን የእርሱን ‘ድምፅ ይሰማሉ።’ እነዚህ ልጆች እንደ ድሮው ማውራትም ሆነ መሄድ ይችላሉ። ልክ እንደ ኢያኢሮስና ባለቤቱ የእነዚህ ልጆች ወላጆችም ‘በሁኔታው እጅግ ይደነቃሉ’ ወይም ይደሰታሉ።

ወንድ ወይም ሴት ልጅህን በሞት አጥተህ ከሆነ ይሖዋ በትንሣኤ አማካኝነት ጥልቅ ሐዘንህን ወደ ደስታ እንደሚለውጠው እርግጠኛ ሁን። ከእንዲህ ዓይነቱ ታላቅ ተስፋ ለመካፈል “እግዚአብሔርንና ብርታቱን ፈልጉ፤ ፊቱንም ዘወትር ፈልጉ። ያደረጋቸውን ድንቅ ሥራዎች፣ ታምራቱን . . . አስቡ” የሚለውን የመዝሙራዊውን ምክር ታዘዝ። (መዝሙር 105:4, 5) አዎን፣ እውነተኛ አምላክ የሆነውን ይሖዋን አገልግል፤ እንዲሁም እርሱ በሚፈልገው መንገድ አምልከው።

‘ይሖዋን የምትፈልግ’ ከሆነ በአሁኑ ጊዜ ምን ጥቅም ታገኛለህ? ወደ አምላክ በመጸለይህ ጥንካሬ ታገኛለህ፣ እውነተኛ ክርስቲያኖች የሆኑ ወዳጆችህ በሚያሳዩህ ፍቅራዊ አሳቢነት ትጽናናለህ፤ እንዲሁም የአምላክን ቃል በማጥናትህ ትበረታታለህ። በቅርቡ ደግሞ ይሖዋ ለአንተም ሆነ በሞት ላጣኸው ልጅህ ዘላለማዊ ጥቅም የሚያስገኙ ‘ድንቅ ሥራዎችና ታምራት’ ሲፈጽም ትመለከታለህ።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

‘ሁለት ልጆቿን ያጣችውን ሴት ጥሩልኝ’

የናይጄሪያ ተወላጆች የሆኑት ከሂንዴ እና ቢንቱ የተባሉ የይሖዋ ምሥክሮች ከአራት ልጆቻቸው መካከል ሁለቱን በመኪና አደጋ አጥተዋል። እነዚህ ባልና ሚስት በዚህ አሳዛኝ ክስተት የተነሳ ከፍተኛ ሐዘን ደርሶባቸዋል። ያም ቢሆን በይሖዋ ላይ ያላቸው እምነት ስላበረታታቸው የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት የያዘውን ተስፋ ለሰዎች ማካፈላቸውን ቀጠሉ።

ሌሎች ሰዎች ከሂንዴ እና ቢንቱ ያላቸውን መረጋጋትና ጥንካሬ በግልጽ ለመመልከት ችለዋል። አንድ ቀን ሚስስ ዩኮሊ የተባለች ሴት ከቢንቱ ጓደኞች ለአንዷ እንዲህ አለቻት:- “በአንድ ጊዜ ሁለት ልጆቿን ብታጣም የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት አሁንም የምትሰብከውን ሴት ጥሩልኝ። ሐዘኗን ለመቋቋም የረዳት ምን እንደሆነ ለማወቅ እፈልጋለሁ።” ቢንቱ፣ ሚስስ ዩኮሊ ቤት ስትደርስ ሴትየዋ እንዲህ አለቻት:- “ልጆችሽን ስለገደለብሽ አምላክ አሁንም የምትሰብኪው ለምን እንደሆነ ማወቅ እፈልጋለሁ። አምላክ የነበረችኝን አንድ ልጅ ወስዶብኛል። ከዚያን ጊዜ አንስቶ ስለ አምላክ መስማት አልፈልግም።” ቢንቱ፣ ሰዎች ለምን እንደሚሞቱ እንዲሁም በሞት ያጣናቸው የምንወዳቸው ሰዎች እንደሚነሱ እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምን እንደሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አስረዳቻት።—የሐዋርያት ሥራ 24:15፤ ሮሜ 5:12

ሚስስ ዩኮሊም “ሰዎችን የሚገድለው አምላክ ይመስለኝ ነበር። አሁን ግን እውነቱን አውቄያለሁ” አለቻት። ይህች ሴት አምላክ ስለሰጣቸው ተስፋዎች ይበልጥ ለማወቅ ስለፈለገች መጽሐፍ ቅዱስን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ለማጥናት ወሰነች።

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

‘ለመርዳት ብፈልግም ምን ማድረግ እንዳለብኝ ግን አላውቅም’

አንድ ልጅ ሲሞት ወላጆቹ፣ ወንድሞቹና እህቶቹ ከፍተኛ ሐዘን የሚሰማቸው ሲሆን የእነርሱ ጓደኞች ደግሞ ምን እንደሚያደርጉ ይጨንቃቸው ይሆናል። ቤተሰቡን ማጽናናት ቢፈልጉም እንኳ ትክክል ያልሆነ ነገር ተናግረው ወይም አድርገው የቤተሰቡን ሐዘን እንዳያባብሱ ይፈራሉ። ‘ለመርዳት ብፈልግም ምን ማድረግ እንዳለብኝ ግን አላውቅም’ ብለው ለሚያስቡ ሰዎች ከዚህ በታች አንዳንድ ሐሳቦች ቀርበዋል።

❖ ምን እንደምትል ወይም ምን እንደምታደርግ ግራ ስለሚገባህ ብቻ ከሐዘንተኞቹ አትራቅ። ከእነርሱ ጋር መሆንህ ብቻ እንኳ ያበረታታቸዋል። ምን ማለት እንዳለብህ ጨንቆህ ይሆን? ሐዘንተኞቹን እቅፍ አድርገህ ከልብ በመነጨ ስሜት “በጣም አዝናለሁ” ማለትህ ለእነርሱ እንደምታስብላቸው እንዲያውቁ ያደርጋል። ማልቀስ ከጀመርክ ሐዘናቸውን እንደምታባብስባቸው በማሰብ ፈርተህ ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ “ከሚያለቅሱም ጋር አልቅሱ” ይላል። (ሮሜ 12:15 የ1954 ትርጉም) ማልቀስህ ሐዘናቸውን እየተጋራህ እንዳለ ስለሚያሳይ የሚያጽናና ነው።

❖ ቅድሚያውን ውሰድ። ለቤተሰቡ ቀለል ያለ ምግብ ማዘጋጀት ትችላለህ? የተጠራቀሙትን የቆሸሹ ዕቃዎች ማጠብ ትችል ይሆን? ልትላላካቸውስ ትችላለህ? “የምትፈልጉት ነገር ካለ ንገሩኝ” አትበል። ይህ አባባል ከልብ የመነጨ ቢሆንም እንኳ እንዲህ ማለትህ በሐዘን ላይ የሚገኙ በርካታ ወላጆች እነርሱን ለመርዳት ጊዜ እንደሌለህ እንዲያስቡ ሊያደርጋቸው ይችላል። ከዚህ ይልቅ “ልረዳችሁ የምችለው ነገር አለ?” ብለህ በመጠየቅ የፈለጉትን ነገር አድርግላቸው። ይሁን እንጂ ቤታቸው ውስጥ መግባት የሌለብህ ቦታ ከመግባት ተቆጠብ፤ እንዲሁም በግል ጉዳያቸው ወይም ሕይወታቸው ውስጥ ጣልቃ አትግባ።

❖ “እንዴት እንደሚሰማህ አውቃለሁ” አትበል። እያንዳንዱ ግለሰብ የሚወደውን ሰው በሞት ሲያጣ የሚያዝንበት መንገድ የተለያየ ነው። ልጅህን በሞት ያጣህ ብትሆንም እንኳ ተመሳሳይ ሐዘን የደረሰባቸው ሌሎች ሰዎች ምን እንደሚሰማቸው በትክክል ማወቅ አትችልም።

❖ ሁኔታዎች እንደወትሮው እስኪሆኑ ድረስ ረዘም ያለ ጊዜ ይወስድ ይሆናል። የምትችለውን ያህል መርዳትህን ቀጥል። አብዛኛውን ጊዜ መጀመሪያ ላይ ብዙ ሰዎች ሐዘን የደረሰባቸውን ሰዎች ያጽናኗቸው ይሆናል፤ ይሁን እንጂ ሐዘንተኞቹ ከዚያ በኋላ ባሉት ጊዜያትም ማጽናኛ ያስፈልጋቸዋል። በቀጣዮቹ ሳምንታትና ወራት የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ለማድረግ ንቁ ሁን። a

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a ልጃቸውን በሞት ያጡ ሐዘንተኞችን እንዴት መርዳት እንደሚቻል ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች በተዘጋጀው የምትወዱት ሰው ሲሞት በተባለው ብሮሹር ገጽ ከ20-24 ላይ ያለውን “ሌሎች መርዳት የሚችሉት እንዴት ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኙ ዘገባዎች እንደሚጠቁሙት ኢየሱስ የሞቱ ልጆችን የማስነሳት ልባዊ ፍላጎትም ሆነ ችሎታ አለው