ልጆቼ በሚገባ የተማሩ እንዲሆኑ መርዳት የምችለው እንዴት ነው?
ልጆቼ በሚገባ የተማሩ እንዲሆኑ መርዳት የምችለው እንዴት ነው?
ልጅን ማስተማር አስደሳች ሆኖም አስቸጋሪ ከሆነ ጉዞ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ይህን ጉዞ የምታደርገው ብቻህን ሳይሆን ከልጆችህ ጋር ነው። ለልጆችህ ማበረታቻና ፍቅራዊ መመሪያ በመስጠት በሕይወት ጎዳና ላይ እድገት እያደረጉ እንዲሄዱ ትረዳቸዋለህ። ልጆችህ በጣም ብዙ የሚማሩት ነገር አለ!
ልጆች ሕይወታቸው የተሳካና አስደሳች እንዲሆን ክፉውን ከደጉ ለመለየት የሚያስችሏቸውን ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ እሴቶች ማዳበር ይገባቸዋል። ይሖዋን ካወቁትና ከወደዱት የተማሩት ነገር በእርግጥ የሚክስና ዘላቂ ጥቅም የሚያስገኝ ይሆንላቸዋል። ወላጅ እንደመሆንህ መጠን፣ ልጆችህ በሚማሩት ነገር ላይ የጎላ አስተዋጽኦ ታበረክታለህ፤ እንዲሁም ለሚማሩት ነገር ከፍ ያለ ግምት እንዲሰጡትና በሚገባ እንዲረዱት በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚና ትጫወታለህ።
በዚህ ጉዞ ላይ ወላጆች ሊወጧቸው የሚገቡ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል። ልጆች በቀላሉ ሊቀረጹ የሚችሉ ሲሆን ከቤት ውጪ ብዙ መጥፎ ነገሮች ሊማሩ ይችላሉ። የምንኖርበት ዓለም በሰይጣን ዲያብሎስ ቁጥጥር ሥር ነው። (1 ዮሐንስ 5:19) ሰይጣን ለተለየ ዓላማ ቢሆንም ልጆችህን ለማስተማር ይጥራል። ሰይጣን የረጅም ጊዜ ተሞክሮ ያለውና የተዋጣለት አስተማሪ ነው። ሆኖም እጅግ ክፉ አስተማሪ መሆኑ የታወቀ ነው። “የብርሃን መልአክ” መስሎ ለመታየት ቢሞክርም እርሱ የሚሰጠው ብርሃን አታላይ ከመሆኑም በላይ ከይሖዋ ቃልና ፈቃድ ጋር ይጋጫል። (2 ቆሮንቶስ 4:4፤ 11:14፤ ኤርምያስ 8:9) ዲያብሎስና አጋንንቱ ሰዎችን በማሳትም ሆነ ውሸትን፣ የሥነ ምግባር ዝቅጠትንና ራስ ወዳድነትን በማስፋፋት ረገድ የተዋጣላቸው ናቸው።—1 ጢሞቴዎስ 4:1
ልጆችህ እንዳይታለሉ ልትጠብቃቸው የምትችለው እንዴት ነው? እውነትና ጠቃሚ የሆነውን ነገር እንዲይዙ እንዴት ልታስተምራቸው ትችላለህ? በመጀመሪያ ልትወስደው የሚገባህ አስፈላጊ እርምጃ ራስህን መመርመር ነው። ለልጆችህ ጥሩ ምሳሌ መሆን አለብህ። በተጨማሪም እነርሱን የማሠልጠን ኃላፊነት እንዳለብህ አምነህ መቀበልና ይህን ለማድረግ የሚያስችልህን ጊዜ መዋጀት አስፈላጊ ነው። ይሁንና እነዚህን ነጥቦች ከመመርመራችን በፊት የትክክለኛ ትምህርት መሠረቱ ምንድን ነው ለሚለው ጥያቄ መልስ ማግኘት ይኖርብናል።
የትክክለኛ ትምህርት መሠረት ምንድን ነው?
በምድር ላይ ከኖሩት እጅግ ጠቢባን ሰዎች መካከል አንዱ ከሆነው ከሰሎሞን ትምህርት ልናገኝ እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱስ የእስራኤል ንጉሥ ስለነበረው ስለዚህ ሰው እንደሚከተለው በማለት ይነግረናል:- “አምላክ ለሰሎሞን ጥበብንና እጅግ ታላቅ ማስተዋልን እንዲሁም በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ የልብ ስፋትን ሰጠው። የሰሎሞን ጥበብ ከምሥራቅ ሰዎች ሁሉ ጥበብ በጣም የላቀ ከግብፅም ጥበብ ሁሉ የበለጠ ነበር።” ሰሎሞን “ሦስት ሺህ ምሳሌዎችን ተናገረ፤ የመሓልዩም ቍጥር ሺህ አምስት ነበር።” ከዚህም ባሻገር ስለ ዕፅዋትና እንስሳት ብዙ እውቀት ነበረው። (1 ነገሥት 4:29-34) በተጨማሪም ንጉሥ ሰሎሞን በኢየሩሳሌም የነበረውን የይሖዋን ዕጹብ ድንቅ ቤተ መቅደስ ጨምሮ በመላው እስራኤል የተካሄዱትን የግንባታ ሥራዎች በበላይነት ተቆጣጥሯል።
በመክብብ መጽሐፍ ውስጥ እንደሚገኙት ያሉት ሰሎሞን የጻፋቸው ነገሮች ስለ ሰው ተፈጥሯዊ ባሕርይ ጥልቅ ማስተዋል እንደነበረው ያሳያሉ። ሰሎሞን በመንፈስ ቅዱስ ተነሳስቶ የትክክለኛ ትምህርት መሠረት ምን እንደሆነ ጠቁሟል። ጠቢቡ ንጉሥ “እግዚአብሔርን መፍራት የዕውቀት መጀመሪያ ነው” ብሏል። አክሎም “የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው፤ ቅዱሱንም ማወቅ ማስተዋል ነው” ሲል ተናግሯል።—ምሳሌ 1:7፤ 9:10
አምላክን የምንፈራ ከሆነ ለእርሱ ጥልቅ አክብሮት የሚኖረን ሲሆን እንዳናሳዝነውም እንጠነቀቃለን። እርሱ የሁሉም የበላይ መሆኑንና በፊቱ ተጠያቂዎች እንደሆንን 1 ቆሮንቶስ 3:19) ልጆችህ ‘ከላይ በሆነችው ጥበብ’ ላይ የተመሠረተ ትምህርት ማግኘት ያስፈልጋቸዋል።—ያዕቆብ 3:15, 17
እንገነዘባለን። ሕልውናችን የተመካበትን አካል የማያከብሩ ሰዎች በሌሎች ዘንድ ጠቢብ ሊባሉ ቢችሉም፣ እንዲህ ያለው ጥበብ “በእግዚአብሔር ፊት ሞኝነት ነው።” (ይሖዋን ላለማሳዘን መፍራት ለእርሱ ካለን ፍቅር ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው። ይሖዋ አገልጋዮቹ እንዲፈሩት ብቻ ሳይሆን እንዲወዱትም ይፈልጋል። ሙሴ እንዲህ ብሏል:- “እስራኤል ሆይ፤ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ የሚፈልገው ምንድን ነው? አምላክህን እግዚአብሔርን እንድትፈራው፣ በመንገዶቹ ሁሉ እንድትሄድ፣ እንድትወደው፣ በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ እንድታገለግለው፣ መልካም እንዲሆንልህና ዛሬ እኔ የምሰጥህን ትእዛዞችና ሥርዐቶች እንድትጠብቅ አይደለምን?”—ዘዳግም 10:12, 13
ልጆቻችን ለይሖዋ አክብሮታዊ ፍርሃት እንዲያድርባቸው ስናደርግ እውነተኛ ጥበብ የሚያስገኝላቸውን ትምህርት እንዲቀስሙ መሠረት እየጣልን ነው። ይህን ዓይነቱን ፍርሃት እያዳበሩ በሄዱ መጠን የትክክለኛ እውቀት ምንጭ ለሆነው ፈጣሪያቸው ያላቸው አድናቆትም የዚያኑ ያህል ይጨምራል። ይህ ደግሞ ልጆቻችን የተማሩትን ነገር ማገናዘብ እንዲችሉና ትክክለኛ መደምደሚያ ላይ እንዲደርሱ ይረዳቸዋል። በተጨማሪም “መልካሙን ከክፉው ለመለየት” የሚያስችል ችሎታ ያዳብራሉ። (ዕብራውያን 5:14) እንዲህ ዓይነቱ መሠረት ትሑት እንዲሆኑና መጥፎ ነገር ከማድረግ እንዲቆጠቡ ይረዳቸዋል።—ምሳሌ 8:13፤ 16:6
ልጆችህ አንተን ያያሉ!
ልጆቻችን ይሖዋን እንዲወዱትና እንዲፈሩት ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? የዚህ ጥያቄ መልስ ይሖዋ በሙሴ አማካኝነት ለእስራኤላውያን በሰጠው ሕግ ውስጥ ይገኛል። እስራኤላውያን ወላጆች የሚከተለው ትእዛዝ ተሰጥቷቸው ነበር:- “አምላክህን እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ኀይልህ ውደድ። ዛሬ የምሰጥህን እነዚህን ትእዛዛት በልብህ ያዝ። ለልጆችህም አስጠናቸው፤ በቤትህ ስትቀመጥ፣ በመንገድም ስትሄድ፣ ስትተኛና ስትነሣም ስለ እነርሱ ተናገር።”—ዘዳግም 6:5-7
ይህ ትእዛዝ ለወላጆች ትልቅ ትምህርት ይዟል። አንደኛው:- ወላጅ እንደመሆንህ መጠን ለልጆችህ ጥሩ ምሳሌ መሆን ይኖርብሃል። ልጆችህ ይሖዋን እንዲወዱት ማስተማር ከፈለግህ አንተ ራስህ አምላክን መውደድና ቃሉን በልብህ ውስጥ ማኖር ይገባሃል። እንዲህ ማድረግህ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ልጆችህ በዋነኝነት የሚማሩት ከአንተ ስለሆነ ነው። ከአንተ ምሳሌ የሚቀስሙት ትምህርት በእነርሱ ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ይኖረዋል። በልጆች ሕይወት ውስጥ ከወላጅ ምሳሌነት የበለጠ ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚያሳድር ነገር የለም።
ምኞቶችህ፣ የምትመራባቸው ደንቦች፣ ከፍተኛ ግምት የምትሰጣቸው ነገሮችና ፍላጎቶችህ በምትናገረው ነገር ብቻ ሳይሆን በድርጊትህም ጭምር ይንጸባረቃሉ። (ሮሜ 2:21, 22) ልጆች ከጨቅላነታቸው አንስቶ የወላጆቻቸውን ድርጊት በጥንቃቄ በመመልከት ይማራሉ። ብዙውን ጊዜ ልጆች ወላጆቻቸው ከፍ አድርገው የሚመለከቷቸው ነገሮች ምን እንደሆኑ ስለሚገነዘቡ እነርሱም ተመሳሳይ አመለካከት ያዳብራሉ። ይሖዋን ከልብ የምትወድ ከሆነ ልጆችህ ይህን ያስተውላሉ። ለምሳሌ ያህል መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብና ለማጥናት ከፍተኛ ቦታ እንደምትሰጥ ያያሉ። በሕይወትህ ውስጥ የአምላክን መንግሥት እንደምታስቀድም ይገነዘባሉ። (ማቴዎስ 6:33) በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አዘውትረህ መገኘትህና የመንግሥቱን ምሥራች በመስበኩ ሥራ ላይ መካፈልህ፣ ለይሖዋ ቅዱስ አገልግሎት ማቅረብ ከምንም በላይ ከፍ አድርገህ የምትመለከተው ነገር መሆኑን እንዲያስተውሉ ያደርጋቸዋል።—ማቴዎስ 28:19, 20፤ ዕብራውያን 10:24, 25
ኃላፊነትህን ተወጣ
ዘዳግም 6:5-7 ለወላጆች የሚሆን ሌላም ትምህርት ይዟል። ልጆቻችሁን የማሠልጠን ኃላፊነት የተጣለው በእናንተ ላይ ነው። በጥንት ዘመን የነበሩ የይሖዋ ሕዝቦች ልጆቻቸውን የማስተማር ኃላፊነት ተጥሎባቸው ነበር። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያን ወላጆችም ልጆቻቸውን በማስተማር ረገድ ትልቅ ድርሻ ነበራቸው። (2 ጢሞቴዎስ 1:5፤ 3:14, 15) ሐዋርያው ጳውሎስ ለእምነት አጋሮቹ በጻፈው ደብዳቤ ላይ በተለይ አባቶች ‘[ልጆቻቸውን] በጌታ ምክርና ተግሣጽ የማሳደግ’ ኃላፊነት እንዳለባቸው ገልጿል።—ኤፌሶን 6:4
በዛሬው ጊዜ፣ ወላጆች ባለባቸው የሥራ ጫና እንዲሁም ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን በሚያሟጥጡባቸው ሌሎች እንቅስቃሴዎች የተነሳ ልጆቻቸውን የማስተማሩን ኃላፊነት ለአስተማሪዎችና ለሕፃናት መዋያ ሠራተኞች አሳልፈው ለመስጠት ይፈተኑ ይሆናል። ይሁንና አፍቃሪና አሳቢ ወላጅን ሊተካ የሚችል አይኖርም። በልጆችህ ሕይወት ውስጥ የምትጫወተውን ሚና እና የምታሳድረውን ተጽዕኖ ፈጽሞ አቅልለህ መመልከት የለብህም። ልጆችህን በማስተማር ረገድ እርዳታ እንደሚያስፈልግህ ከተሰማህ ጥበብ ያለበት ምርጫ ማድረግ ይኖርብሃል። ይሁንና የተሰጠህን የተቀደሰ ኃላፊነት መቼም ቢሆን ለሌሎች አሳልፈህ መስጠት የለብህም።
ልጆችህን ለማሠልጠን ጊዜ መድብ
ወላጆች ከዘዳግም 6:5-7 የሚያገኙት ሌላው ትምህርት ደግሞ ልጆችን ማሠልጠን ጊዜና ጥረት የሚጠይቅ መሆኑ ነው። እስራኤላውያን ወላጆች የአምላክን እውነት ለልጆቻቸው ‘ማስጠናት’ ወይም በልባቸው ውስጥ መቅረጽ ነበረባቸው። ‘ማስጠናት’ ወይም መቅረጽ ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል “ደግሞ ደጋግሞ መናገር” የሚል ፍቺ አለው። ይህም ቀኑን ሙሉ ማለትም ከጠዋት እስከ ማታ ‘በቤትም ሆነ በመንገድ’ ልጆቻቸውን ማስተማር ይጠይቅባቸው ነበር። ልጆች አምላክን የሚያስደስቱ እንዲሆኑ ማስተማር እንዲሁም አመለካከታቸውንና ባሕርያቸውን መቅረጽ ጊዜና ጥረት ይጠይቃል።
ታዲያ ልጆችህ በሚገባ የተማሩ እንዲሆኑ ለመርዳት ምን ማድረግ ትችላለህ? ብዙ ልታደርግ የምትችለው ነገር አለ። ይሖዋን እንዲወዱትና እንዲፈሩት አስተምራቸው። አንተ ራስህ ጥሩ ምሳሌ ሁን። ልጆችህን የማስተማር ኃላፊነትህን ተወጣ፤ እንዲሁም እነርሱን ለማሠልጠን ጊዜ መድብ። ፍጹም ስላልሆንክ ልጆችህን በምታስተምርበት ጊዜ አንዳንድ ስህተቶችን መሥራትህ አይቀርም። ይሁንና የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ በቅንነት የምትጥር ከሆነ ልጆችህ ለምታደርገው ነገር አመስጋኝ መሆናቸውና ጥቅም ማግኘታቸው አይቀርም። ምሳሌ 22:6 “ልጅን የሚሄድበትን መንገድ አስተምረው፤ በሚሸመግልበት ጊዜ ከዚያ ፈቀቅ አይልም” ይላል።
ትምህርት በሕይወት ዘመን ሁሉ የሚዘልቅ ጉዞ ነው። አንተም ሆንክ ልጆችህ አምላክን የምትወዱ ከሆነ ይህ ጉዞ ለዘላለም የሚቀጥል ይሆናል። ምክንያቱም ስለ ይሖዋም ሆነ ዓላማውን እንዴት መፈጸም እንደምንችል የምንማረው ነገር መቼም ቢሆን አያልቅም።—መክብብ 3:10, 11
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ለልጆቻችሁ መጽሐፍ ቅዱስ ታነቡላቸዋላችሁ?
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ልጆቻችሁን ስለ ፈጣሪ ለማስተማር ጊዜ መድቡ