በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መከራና ሥቃይ ሁሉ በቅርቡ ይወገዳል

መከራና ሥቃይ ሁሉ በቅርቡ ይወገዳል

መከራና ሥቃይ ሁሉ በቅርቡ ይወገዳል

“እርሱ ዐለት፣ ሥራውም ፍጹም ነው።”—ዘዳግም 32:4

1, 2. (ሀ) የዘላለም ሕይወት ተስፋን ከፍ አድርገህ የምትመለከተው ለምንድን ነው? (ለ) ብዙዎች አስደናቂ ተስፋዎችን በሰጠው አምላክ እንዳያምኑ ያደረጋቸው ምንድን ነው?

 በገነት ውስጥ መኖር ምን እንደሚመስል ማሰብ ያስደስትሃል? ምናልባትም ድንቅ በሆነችው ፕላኔታችን ላይ ምርምር እያደረግህ ሥፍር ቁጥር ስለሌላቸው ልዩ ልዩ ሕያዋን ፍጥረታት እውቀት ስትቀስም በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ ይሆናል። አሊያም ከሌሎች ጋር ሆነህ ምድርን በመንከባከቡና ወደ ገነትነት በመለወጡ ሥራ ስትካፈል ስለምታገኘው እርካታ ታስብ ይሆናል። ወይም ደግሞ በዚህ ሩጫ በበዛበት ዓለም ውስጥ ጊዜ አግኝተህ ልትማራቸው ባልቻልካቸው ከሥነ ጥበብ፣ ከሥነ ሕንጻ፣ ከሙዚቃ አሊያም ከሌሎች ሙያዎች ጋር በተያያዙ መስኮች ችሎታህን ስታዳብር ይታይህ ይሆናል። ያም ሆነ ይህ መጽሐፍ ቅዱስ ‘እውነተኛ ሕይወት’ በማለት የሚጠራውን ይኸውም ይሖዋ ለእኛ ያሰበውን የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋ ከፍ አድርገህ ትመለከተዋለህ።—1 ጢሞቴዎስ 6:19

2 ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ለሌሎች ማካፈል አስደሳችና ውድ መብት ነው ቢባል አትስማማም? ይሁንና ብዙዎች እንዲህ ያለውን ተስፋ ለማመን ፈቃደኞች አይደሉም። እንዲያውም በቀላሉ የሚታለሉ ሰዎች ብቻ የሚያምኑበት ተጨባጭነት የሌለው ሕልም እንደሆነ ይሰማቸዋል። እነዚህ ሰዎች በገነት ውስጥ የዘላለም ሕይወት ለመስጠት ቃል በገባው አምላክ እንኳ ማመን ይቸግራቸዋል። ለምን? አንዳንዶቹ እንዲህ እንዲሰማቸው ያደረጋቸው የክፋት መብዛት ነው። ‘አምላክ ካለ፣ እንዲሁም ሁሉን ቻይና አፍቃሪ ከሆነ በዓለም ላይ ክፋትና መከራ እንዴት ሊበዛ ይችላል’ ብለው ያስባሉ። ‘ክፋትን ዝም ብሎ የሚያይ አምላክ ሊኖር አይችልም። አለ ከተባለም፣ ወይ ሁሉን ቻይ አይደለም፣ አለዚያም ስለ እኛ ደንታ የለውም’ የሚል ምክንያት ያቀርባሉ። ለአንዳንዶች እንዲህ ዓይነቱ ማስረጃ አሳማኝ መስሎ ይታያቸዋል። በእርግጥም ሰይጣን የሰዎችን ልቦና በማሳወር ረገድ ተሳክቶለታል።—2 ቆሮንቶስ 4:4

3. ሰዎች ለየትኛው ከባድ ጥያቄ መልስ እንዲያገኙ ልንረዳቸው እንችላለን? ይህን ለማድረግ የሚያስችል ልዩ መብት አለን የምንለውስ ለምንድን ነው?

3 የይሖዋ ምሥክሮች እንደመሆናችን መጠን በሰይጣንና በዚህ ዓለም ጥበብ የተታለሉ ሰዎችን የመርዳት ልዩ መብት አግኝተናል። (1 ቆሮንቶስ 1:20፤ 3:19) ብዙዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋዎች የማያምኑት ለምን እንደሆነ እንገነዘባለን። እነዚህ ሰዎች ይሖዋን አያውቁም። ስሙንም ሆነ የስሙን ትርጉም ላያውቁ ይችላሉ፤ ከዚህም በላይ ስለ ባሕርያቱ ወይም ቃሉን በመጠበቅ ረገድ ስላስመዘገበው ታሪክ የሚያውቁት ነገር የለም ማለት ይቻላል። እኛ ግን ይህን መሰሉን እውቀት በማግኘታችን ተባርከናል። በመሆኑም ‘ልቦናቸው የጨለመባቸው’ ሰዎች “አምላክ ክፋትና ሥቃይ እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው?” ሲሉ ለሚያነሱት ከባድ ጥያቄ መልስ እንዲያገኙ ለመርዳት ምን ማድረግ እንደምንችል በየጊዜው መከለሳችን ጠቃሚ ነው። (ኤፌሶን 4:18) በመጀመሪያ ለጥያቄው አጥጋቢ መልስ ለመስጠት መሠረት መጣል የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን። ከዚያም ይሖዋ ክፋትን በተመለከተ ሁኔታዎችን የያዘበት መንገድ ባሕርያቱን ግልጽ አድርጎ የሚያሳየው እንዴት እንደሆነ እንመረምራለን።

ትክክለኛው አቀራረብ

4, 5. አንድ ሰው አምላክ መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምን እንደሆነ ጥያቄ በሚያነሳበት ጊዜ አስቀድመን ምን ማድረጋችን አስፈላጊ ነው? አብራራ።

4 አንድ ሰው አምላክ መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምን እንደሆነ ቢጠይቀን መልስ የምንሰጠው እንዴት ነው? ወዲያውኑ በኤደን የአትክልት ሥፍራ ከተከሰተው ሁኔታ ጀምረን ዝርዝር ማብራሪያ ለመስጠት እንሞክር ይሆናል። አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ማድረጉ ጥሩ ሊሆን ይችላል። ይሁንና ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። በቅድሚያ መሠረት መጣል ያስፈልግ ይሆናል። (ምሳሌ 15:23፤ ቈላስይስ 4:6) ለግለሰቡ መልስ ከመስጠታችን በፊት ልናስብባቸው የሚገቡ ሦስት ነጥቦችን እንመልከት።

5 በመጀመሪያ፣ አንድ ሰው በዓለም ላይ የተንሰራፋው ክፋት በጣም የሚያስጨንቀው ከሆነ ምናልባት እርሱ ራሱ ወይም ወዳጆቹ የክፋት ድርጊት ሰለባ ሆነው ሊሆን ይችላል። በዚህ ጊዜ ከልብ አዘኔታ ማሳየታችን አስተዋይነት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያኖችን “ከሚያዝኑም ጋር እዘኑ” ሲል መክሯል። (ሮሜ 12:15) አዘኔታ ማሳየታችን ወይም ‘የሌላው መከራ የእኛ እንደሆነ አድርገን’ ማሰባችን ልቡን ሊነካው ይችላል። (1 ጴጥሮስ 3:8 የ1954 ትርጉም) ሰውየው እንደምናስብለት ከተገነዘበ የምንናገረውን ነገር ለመስማት ፈቃደኛ መሆኑ አይቀርም።

6, 7. ቀና አመለካከት ያለው አንድ ሰው ያሳሰቡትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎች በማንሳቱ ልናመሰግነው የሚገባን ለምንድን ነው?

6 ሁለተኛ፣ ይህ ቅን ግለሰብ እንዲህ ያለውን ጥያቄ በማንሳቱ ልናመሰግነው እንችላለን። አንዳንድ ሰዎች እንደዚህ ያለ ጥያቄ በአእምሯቸው ውስጥ መመላለሱ እምነት እንደጎደላቸው ወይም ለአምላክ አክብሮት እንደሌላቸው የሚያሳይ ምልክት እንደሆነ ይሰማቸዋል። ምናልባትም እንዲህ ብለው እንዲያስቡ ያደረጓቸው ቀሳውስት ሊሆኑ ይችላሉ። ይሁን እንጂ እነዚህን ጥያቄዎች ማንሳት የእምነት ማነስ ምልክት አይደለም። እንዲያውም በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የኖሩ ታማኝ ሰዎች ተመሳሳይ ጥያቄዎች አንስተው ነበር። ለምሳሌ መዝሙራዊው ዳዊት “እግዚአብሔር ሆይ፤ ለምን እንዲህ ርቀህ ቆምህ? በመከራ ጊዜስ ለምን ድምፅህን አጠፋህ?” በማለት ጠይቋል። (መዝሙር 10:1) በተመሳሳይም ነቢዩ ዕንባቆም እንዲህ የሚል ጥያቄ አቅርቧል:- “እግዚአብሔር ሆይ፤ ለርዳታ እየተጣራሁ፣ አንተ የማትሰማው እስከ መቼ ነው? ‘ግፍ በዛ’ ብዬ እየጮኽሁ፣ አንተ የማታድነው እስከ መቼ ነው? ስለ ምን በደልን እንዳይ አደረግኸኝ? እንዴትስ ግፍ ሲፈጸም ትታገሣለህ? ጥፋትና ግፍ በፊቴ አለ፤ ጠብና ግጭት በዝቶአል።”—ዕንባቆም 1:2, 3

7 እነዚህ ሰዎች ለአምላክ ጥልቅ አክብሮት ያላቸው ታማኝ አገልጋዮች ነበሩ። እነዚህን አሳሳቢ ጥያቄዎች በማንሳታቸው ተወቅሰዋል? በፍጹም። ከዚህ በተቃራኒ ይሖዋ እነዚህ ሰዎች በቅንነት ያነሷቸው ጥያቄዎች በቃሉ ውስጥ እንዲሰፍሩ አድርጓል። በዛሬው ጊዜም ክፋት እየተባባሰ መሄዱ የሚያስጨንቀው አንድ ሰው በመንፈሳዊ የተራበ ይኸውም መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ሊሰጠው የሚችለውን መልስ ለማግኘት የሚጓጓ ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ በመንፈሳዊ የተራቡ ወይም “ለመንፈሳዊ ፍላጎቶቻቸው ንቁ የሆኑ” ሰዎችን ማመስገኑን አትዘንጋ። (ማቴዎስ 5:3 NW) እንደነዚህ ያሉት ሰዎች ኢየሱስ ቃል የገባውን ደስታ እንዲያገኙ መርዳት መቻል ምንኛ ታላቅ መብት ነው!

8. ሰዎች በዓለም ላይ ለሚደርሰው መከራ ተጠያቂው አምላክ ነው ብለው እንዲያምኑ ያደረጓቸው ግራ የሚያጋቡ ትምህርቶች የትኞቹ ናቸው? እውነቱን እንዲያውቁስ እንዴት ልንረዳቸው እንችላለን?

8 በሦስተኛ ደረጃ፣ ግለሰቡ በዓለም ላይ ለተስፋፋው ክፋት ተጠያቂው አምላክ አለመሆኑን እንዲያስተውል መርዳት ይኖርብናል። ብዙ ሰዎች ዓለማችንን የሚገዛው አምላክ እንደሆነ፣ የሚደርሱብንን ነገሮች ሁሉ ከረጅም ጊዜ በፊት አስቀድሞ እንደወሰነ፣ እንዲሁም በሰው ዘር ላይ መከራ የሚያመጣበት ምክንያት የማይታወቅ እንደሆነና ሐሳቡን መረዳት እንደማይቻል ተምረዋል። እነዚህ ትምህርቶች ሐሰት ናቸው። ለአምላክ ክብር የማያመጡ ከመሆናቸውም ባሻገር በዓለም ላይ ላለው ክፋትና መከራ ተጠያቂ ያደርጉታል። ስለዚህ እነዚህን የተሳሳቱ አስተሳሰቦች ለማረም በአምላክ ቃል መጠቀም ይኖርብናል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) የዚህ ብልሹ ሥርዓት ገዥ ሰይጣን ዲያብሎስ እንጂ ይሖዋ አይደለም። (1 ዮሐንስ 5:19) ይሖዋ የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጥረታቱን ዕድል አስቀድሞ አልወሰነም፤ ከዚህ ይልቅ ለእያንዳንዳቸው ጥሩውን ወይም መጥፎውን፣ ትክክል ወይም ስህተት የሆነውን ጎዳና የመምረጥ ነፃነትና አጋጣሚ ሰጥቷቸዋል። (ዘዳግም 30:19) በተጨማሪም ይሖዋ ፈጽሞ የክፋት ምንጭ አይደለም፤ እንዲያውም ክፋትን የሚጠላ ሲሆን በፍትሕ መጓደል ምክንያት ሥቃይ ለሚደርስባቸው ሰዎች ያስባል።—ኢዮብ 34:10፤ ምሳሌ 6:16-19፤ 1 ጴጥሮስ 5:7

9. “ታማኝና ልባም ባሪያ” ይሖዋ መከራና ሥቃይ እንዲኖር የፈቀደበትን ምክንያት ሰዎች እንዲረዱ ለማድረግ ያዘጋጃቸው አንዳንድ ጽሑፎች ምንድን ናቸው?

9 በዚህ መንገድ መሠረት ከጣልክ አድማጭህ አምላክ መከራ እንዲቀጥል የፈቀደው ለምን እንደሆነ ለመስማት ዝግጁ ሊሆን ይችላል። “ታማኝና ልባም ባሪያ” በዚህ ረገድ የሚረዱህን ጠቃሚ ጽሑፎች አዘጋጅቷል። (ማቴዎስ 24:45-47 የ1954 ትርጉም) ለምሳሌ ያህል፣ በ2005 በተደረገው “አምላካዊ ታዛዥነት” በተሰኘው የአውራጃ ስብሰባ ላይ መከራና ሥቃይ ሁሉ በቅርቡ ይወገዳል! የሚል ርዕስ ያለው ትራክት ወጥቶ ነበር። ይህ ትራክት በቋንቋህ የሚገኝ ከሆነ ይዘቱን በሚገባ ለማወቅ ለምን አታነበውም? በተመሳሳይም በአሁኑ ጊዜ በ157 ቋንቋዎች የተተረጎመው ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለው መጽሐፍ ለዚህ ወሳኝ ጥያቄ መልስ የሚሰጥ አንድ ምዕራፍ አለው። እነዚህን ጠቃሚ መሣሪያዎች በሚገባ ተጠቀምባቸው። እነዚህ ጽሑፎች በኤደን ገነት የሉዓላዊነት ጥያቄ እንዲነሳ ምክንያት ስለሆኑት ነገሮች መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ሐሳብ የሚገልጹ ሲሆን ይሖዋ ጉዳዩን በዚህ መንገድ የያዘው ለምን እንደሆነ ያብራራሉ። ይህን ጉዳይ በምታብራራበት ጊዜ ለአድማጭህ ስለ ይሖዋና ግሩም ስለሆኑት ባሕርያቱ የሚገልጸውን ከሁሉ የላቀ እውቀት እያካፈልከው መሆኑን አትዘንጋ።

በይሖዋ ባሕርያት ላይ አተኩር

10. ብዙዎች አምላክ መከራና ሥቃይ እንዲኖር መፍቀዱን በተመለከተ መረዳት የሚያዳግታቸው ነገር ምንድን ነው? ስለ ምን ማወቃቸውስ ሊረዳቸው ይችላል?

10 የሰው ልጆች በሰይጣን ተጽዕኖ ሥር ሆነው ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ አምላክ የፈቀደው ለምን እንደሆነ በምታስረዳበት ጊዜ ሰዎች የይሖዋን ድንቅ ባሕርያት እንዲያስተውሉ ለማድረግ ጣር። ብዙ ሰዎች አምላክ ኃያል እንደሆነ ያውቃሉ፤ ሁሉን ቻይ ተብሎ ሲጠራም በተደጋጋሚ ይሰማሉ። ይሁንና አምላክ በታላቅ ኃይሉ ተጠቅሞ የፍትሕ መጓደልንና መከራን የማያስወግደው ለምን እንደሆነ መረዳት ይከብዳቸዋል። ምናልባትም ይህ የሆነው እንደ ቅድስና፣ ፍትሕ፣ ጥበብና ፍቅር ስላሉት የይሖዋ ባሕርያት እምብዛም ስለማያውቁ ሊሆን ይችላል። ይሖዋ እነዚህን ባሕርያት የሚያንጸባርቀው ፍጹምና ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ነው። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ‘ሥራው ፍጹም ነው’ ይላል። (ዘዳግም 32:4) ሰዎች ከዚህ ርዕስ ጋር በተያያዘ በአብዛኛው ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች መልስ ስትሰጥ እነዚህን ባሕርያት ጎላ አድርገህ መግለጽ የምትችለው እንዴት ነው? እስቲ ጥቂት ምሳሌዎችን እንመልከት።

11, 12. (ሀ) አዳምና ሔዋን ኃጢአት በሠሩ ጊዜ እነርሱን ይቅር ማለት ለምርጫ የሚቀርብ አልነበረም የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ ኃጢአትን ለዘላለም የማይታገሰው ለምንድን ነው?

11 ይሖዋ አዳምንና ሔዋንን በቀላሉ ይቅር ሊላቸው አይችልም ነበር? በዚህ ጉዳይ ላይ ይቅርታ ማድረግ ፈጽሞ ምርጫ ውስጥ የሚገባ አልነበረም። አዳምና ሔዋን ፍጹማን ስለነበሩ የይሖዋን ሉዓላዊ ገዥነት ተቃውመው የሰይጣንን አመራር የተቀበሉት ሆነ ብለው ነው። በመሆኑም፣ ዓመጸኞቹ ምንም ዓይነት የንስሐ ዝንባሌ አለማሳየታቸው አያስደንቅም። ሰዎች አዳምና ሔዋን ለምን ይቅርታ አልተደረገላቸውም ብለው ሲናገሩ፣ ይሖዋ የአቋም ደረጃውን ዝቅ በማድረግ ኃጢአትንና ዓመጽን በቸልታ የማያልፈው ለምንድን ነው ብለው የጠየቁ ያህል ነው። ለዚህ ጥያቄ የምንሰጠው መልስ ከይሖዋ ዓይነተኛ ባሕርያት መካከል አንዱ ከሆነው ከቅድስናው ጋር በጥብቅ የተያያዘ ነው።—ዘፀአት 28:36 የ1954 ትርጉም፤ 39:30 የ1954 ትርጉም

12 መጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ቦታዎች ላይ የይሖዋን ቅድስና አጉልቶ ይናገራል። የሚያሳዝነው ግን በዚህ ብልሹ ዓለም ውስጥ የዚህን ባሕርይ ምንነት የሚረዱት በጣም ጥቂቶች መሆናቸው ነው። ይሖዋ ንጹሕ፣ የጠራና ምንም ዓይነት ኃጢአት የሌለበት ነው። (ኢሳይያስ 6:3፤ 59:2) ኃጢአትን ለማስተሰረይ ወይም ለማስወገድ ዝግጅት አድርጓል፤ ስለሆነም ኃጢአትን ለዘላለም አይታገስም። ይሖዋ ኃጢአትን ለዘላለም ቢታገስ ኖሮ የወደፊት ተስፋ ባልኖረን ነበር። (ምሳሌ 14:12) ይሖዋ፣ እርሱ በወሰነው ጊዜ ፍጥረታቱ በሙሉ ወደ ቅድስና እንዲደርሱ ያደርጋል። ይህ የቅዱሱ አምላክ ፈቃድ ስለሆነ መፈጸሙ አይቀርም።

13, 14. ይሖዋ በኤደን ውስጥ የነበሩትን ዓመጸኞች ያላጠፋቸው ለምንድን ነው?

13 ይሖዋ በኤደን የነበሩትን ዓመጸኞች አጥፍቶ እንደ አዲስ መጀመር አይችልም ነበር? እንደዚህ ለማድረግ የሚያስችል ኃይል እንዳለው አያጠራጥርም፤ በቅርቡም ይህን ኃይሉን ክፋዎችን በሙሉ ጠራርጎ ለማጥፋት ይጠቀምበታል። ምናልባት አንዳንዶች እንደሚከተለው ሲሉ ይጠይቁ ይሆናል:- ‘በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ሦስት ዓመጸኞች ብቻ በነበሩ ጊዜ እርምጃ ያልወሰደው ለምንድን ነው? እንዲህ አድርጎ ቢሆን ኖሮ የኃጢአትን መስፋፋትና በዓለም ላይ የሚታየውን መከራ ሁሉ ማስቀረት ይቻል አልነበረም?’ ይሖዋ እንዲህ ማድረግ ያልፈለገው ለምንድን ነው? ዘዳግም 32:4 “መንገዱም ሁሉ ትክክል [“ፍትሕ፣” NW] ነው” ይላል። ይሖዋ ለፍትሕ ትልቅ ቦታ ይሰጣል። እንዲያውም “ፍትሕን ይወዳል።” (መዝሙር 37:28) ፍትሕን በመውደዱም በኤደን የነበሩትን ዓመጸኞች ከማጥፋት ተቆጥቧል። ይህ እርምጃ ፍትሐዊ ነው ሊባል የሚችለው እንዴት ነው?

14 የሰይጣን ዓመጽ በአምላክ ሉዓላዊነት ላይ ጥያቄ አስነስቷል። ይሖዋ ለፍትሕ ያለው ስሜት ሰይጣን ላስነሳው ግድድር ፍትሐዊ በሆነ መንገድ መልስ እንዲሰጥ አነሳስቶታል። ዓመጸኞቹ ወዲያውኑ መጥፋት ይገባቸው የነበሩ ቢሆኑም እንዲህ ማድረጉ ፍትሐዊ አይሆንም። ዓመጸኞቹን ማጥፋት ይሖዋ ኃያል መሆኑን የሚያረጋግጥ ተጨማሪ ማስረጃ ሊሆን ቢችልም ጉዳዩ የኃያልነት ጥያቄ አልነበረም። ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ ዓላማውን ለአዳምና ለሔዋን በግልጽ ነግሯቸዋል። ልጆች ወልደው ምድርን መሙላት፣ እንዲሁም ምድርንና በእርሷ ላይ ያሉትን ፍጥረታት መግዛት ነበረባቸው። (ዘፍጥረት 1:28) ይሖዋ አዳምንና ሔዋንን አጥፍቷቸው ቢሆን ኖሮ ለሰው ልጆች ያለው ዓላማ ግቡን አይመታም ነበር። የይሖዋ ፍትሕ እንዲህ እንዲሆን አይፈቅድም፤ ምክንያቱም ዓላማው ሁልጊዜ መፈጸም አለበት።—ኢሳይያስ 55:10, 11

15, 16. ሰዎች በኤደን ገነት ለተነሳው ችግር አማራጭ “የመፍትሔ ሐሳቦችን” በሚያቀርቡበት ጊዜ ሁኔታውን እንዲያስተውሉ እንዴት ልንረዳቸው እንችላለን?

15 በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ከይሖዋ በቀር በኤደን ለተነሳው ዓመጽ በተሻለ መንገድ መልስ መስጠት የሚችል የላቀ ጥበብ ያለው አካል ሊኖር ይችላል? አንዳንድ ሰዎች በኤደን ለተነሳው ዓመጽ የራሳቸውን “የመፍትሔ ሐሳቦች” ያቀርቡ ይሆናል። ይሁንና፣ እንዲህ ማድረጋቸው ሁኔታውን ለመፍታት የሚያስችል የተሻለ ሐሳብ ማመንጨት እንችላለን ማለት አይሆንባቸውም? ምናልባት እነዚህ ሰዎች እንዲህ የሚሉት ለክፋት ብለው ሳይሆን ስለ ይሖዋም ሆነ ድንቅ ስለሆነው ጥበቡ እውቀት ስለሌላቸው ሊሆን ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም ለነበሩት ክርስቲያኖች የጻፈው ደብዳቤ የአምላክን ጥበብ በጥልቀት እንደመረመረ ያሳያል። ይህ ጥበብ ይሖዋ በመሲሐዊው መንግሥት አማካኝነት ታማኝ የሆኑ የሰው ዘሮችን ከኃጢአት ነፃ ለማውጣትና ስሙን ለማስቀደስ ያለውን ዓላማ የሚገልጸውን “ቅዱስ ምስጢር” ይጨምራል። ጳውሎስ እንዲህ ዓይነት ዓላማ ያለው አምላክ ስላለው ጥበብ ምን ተሰምቶታል? ሐዋርያው ደብዳቤውን ሲደመድም “እርሱ ብቻ ጥበበኛ ለሆነ አምላክ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን” ብሏል።—ሮሜ 11:25 NW፤ 16:25-27

16 ጳውሎስ ይሖዋ “ብቻ ጥበበኛ” እንደሆነ ይኸውም በአጽናፈ ዓለም ውስጥ በጥበቡ አቻ የማይገኝለት መሆኑን ተገንዝቦ ነበር። ታዲያ ፍጽምና ከጎደላቸው የሰው ልጆች መካከል፣ ሰይጣን የአምላክን አገዛዝ ትክክለኛነት በተመለከተ ያስነሳውን ከባድ ጥያቄ ይቅርና ተራ የሚባሉትን ችግሮች እንኳ ከይሖዋ በተሻለ መንገድ መፍታት የሚችል ይኖራል? ስለዚህ ሰዎች “ልቡ ጠቢብ” ለሆነው አምላክ እኛ ያለን ዓይነት አክብሮት እንዲኖራቸው መርዳት ይገባናል። (ኢዮብ 9:4 የ1954 ትርጉም) የይሖዋን ጥበብ በጥልቀት በተረዳን መጠን ነገሮችን የሚይዝበት መንገድ ከሁሉ የተሻለ ስለመሆኑ ይበልጥ እንተማመናለን።—ምሳሌ 3:5, 6

የይሖዋ ዋነኛ ባሕርይ የሚጫወተውን ሚና መረዳት

17. አምላክ መከራና ሥቃይ እንዲቀጥል መፍቀዱ የሚያስጨንቃቸው ሰዎች ስለ ይሖዋ ፍቅር ይበልጥ መረዳታቸው እንዴት ሊጠቅማቸው ይችላል?

17 ‘አምላክ ፍቅር ነው።’ (1 ዮሐንስ 4:8) መጽሐፍ ቅዱስ የይሖዋን ዋነኛ ባሕርይ የሚገልጸው በእነዚህ ማራኪ ቃላት ነው። ፍቅር ይሖዋ ካሉት ባሕርያት መካከል እጅግ ማራኪ ሲሆን በክፋት መብዛት የተጨነቁ ሰዎችን ከሁሉም በላይ ያጽናናቸዋል። ይሖዋ፣ ኃጢአት በፍጥረታቱ ላይ ያስከተለውን አስከፊ መዘዝ ለማስተካከል ሁኔታዎችን የያዘበት መንገድ ፍቅሩን የሚያንጸባርቅ ነው። ይሖዋ ኃጢአተኛ የሆኑት የአዳምና የሔዋን ዘሮች ወደ እርሱ እንዲቀርቡና ከእርሱ ጋር ወዳጅነት እንዲመሠርቱ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ተስፋ እንዲሰጣቸው ያነሳሳው ፍቅር ነው። በተጨማሪም ፍቅር ኃጢአትን ሙሉ በሙሉ ለማስተሰረይ እንዲሁም ፍጹምና ዘላለማዊ ሕይወት ለማስገኘት የሚያስችል ቤዛ እንዲያዘጋጅ ገፋፍቶታል። (ዮሐንስ 3:16) ከዚህም ባሻገር ይሖዋ፣ የሰው ልጆች ሰይጣንን እንዲቃወሙና እርሱን ሉዓላዊ ገዢያቸው አድርገው እንዲቀበሉ በርካታ አጋጣሚዎች በመስጠት እንዲታገሳቸው የገፋፋው ፍቅር ነው።—2 ጴጥሮስ 3:9

18. ስለ የትኛው ጉዳይ ማስተዋል በማግኘታችን ተባርከናል? በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን ይብራራል?

18 አንድ ቄስ በአሸባሪዎች ጥቃት ለሞቱ ሰዎች በተዘጋጀ የመታሰቢያ በዓል ላይ “አምላክ ክፋትና መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምን እንደሆነ አናውቅም” ብለው ነበር። ይህ እንዴት ያሳዝናል! ስለዚህ ጉዳይ ማስተዋል በመቻላችን አልተባረክንም? (ዘዳግም 29:29) ይሖዋ ጥበበኛ፣ ፍትሐዊና አፍቃሪ በመሆኑ በቅርቡ መከራንና ሥቃይን ሁሉ እንደሚያስወግድ እናውቃለን። እንዲህ ለማድረግም ቃል ገብቷል። (ራእይ 21:3, 4) ይሁንና ባለፉት ዘመናት የሞቱ ሰዎችስ ምን ይሆናሉ? ይሖዋ በኤደን ገነት የተነሳውን አከራካሪ ጉዳይ የያዘበት መንገድ ሙታንን ያለ ተስፋ ትቷቸዋል? በፍጹም። አምላክ በፍቅር ተነሳስቶ በትንሣኤ አማካኝነት ተስፋ እንዲኖራቸው አድርጓል። የሚቀጥለው ርዕስ ይህን ጉዳይ ያብራራል።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• አምላክ መከራና ሥቃይ እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው ብሎ ለሚጠይቅ ሰው ምን ማለት እንችላለን?

• ይሖዋ በኤደን የነበሩትን ዓመጸኞች የያዘበት መንገድ ቅድስናውንና ፍትሑን የሚያሳየው እንዴት ነው?

• ሰዎች የይሖዋን ፍቅር ይበልጥ እንዲያስተውሉ መርዳት ያለብን ለምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በዓለም ላይ ያለው መከራና ሥቃይ የሚያስጨንቃቸውን ሰዎች ለመርዳት ጥረት አድርጉ

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ታማኝ አገልጋዮች የነበሩት ዳዊትና ዕንባቆም በቅንነት አምላክን ጠይቀዋል